ከሰኔ 22-28, 2026
መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ
‘ከመጽናናት ሁሉ አምላክ’ ተማሩ
‘ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ ሰዎችን እናጽናና።’—2 ቆሮ. 1:4
ዓላማ
ሌሎችን በማጽናናት ረገድ ከይሖዋና የእሱን ምሳሌ ከሚከተሉ ወዳጆቹ ምን እንማራለን?
1. ሌሎችን ማጽናናት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
ሁላችንም ‘ልዩ ልዩ ፈተናዎች ስለሚደርሱብን እንጨነቃለን’፤ በመሆኑም ማጽናኛና ማበረታቻ የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። (1 ጴጥ. 1:6) ሌሎች ሲያጽናኑን ደስ እንደሚለን ሁሉ እኛም ሌሎችን ለማጽናናት ፈጣን መሆን አለብን። (ማቴ. 7:12) ‘በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉ ሰዎችን’ እንዴት ማጽናናት እንደምንችል “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ መማር እንችላለን። ‘እርስ በርሳችን በመጽናናት’ የእሱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 1 ተሰ. 4:18) እንዲህ የምናደርገው ግዴታ ስለሆነብን ሳይሆን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ስለምንወዳቸው ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ (1) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ማጽናኛ ማለት ምን ማለት ነው? (2) ሌሎችን ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው? (3) እኛ ራሳችን መጽናኛ ሲያስፈልገን ምን ማድረግ እንችላለን?
ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ማጽናኛ ምንድን ነው?
2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማጽናናት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ምን መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማጽናናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል እንደየአገባቡ የተለያየ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ለምሳሌ “ማበረታታት፣” “ማሳሰብ” ወይም “መምከር” ማለት ሊሆን ይችላል። (ሮም 12:8 ግርጌ) ቃሉ፣ ቃል በቃል “ከአጠገብ መሆን” የሚል ፍቺ አለው። ጓደኛው ችግር ሲያጋጥመው ቶሎ ደርሶ ከአጠገቡ የሚሆንን ሰው እንድናስብ ያደርገናል። እንዲህ ያለው ጓደኛ ለወዳጁ የሚያስፈልገውን ድጋፍና እርዳታም ያደርግለታል። የእርዳታው ዓይነት የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ነገር መከራ የደረሰበት ሰው መጽናናቱና መበረታታቱ ነው።
3. በርናባስ ሌሎችን በማጽናናት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
3 እስቲ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ዮሴፍ የተባለ አንድ ክርስቲያን ሌሎችን በማጽናናትና በማበረታታት በጣም የታወቀ ከመሆኑ የተነሳ ሐዋርያት በርናባስ ብለው ሰየሙት። በርናባስ ማለት “የመጽናናት ልጅ” ማለት ነው። (ሥራ 4:36) ይህ ስም ጥሩ አድርጎ ስለሚገልጸው መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ ዮሴፍ በሚለው ስሙ ጠርቶት አያውቅም። በርናባስ የእምነት አጋሮቹ ችግር ሲያጋጥማቸው በተደጋጋሚ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በመስጠት “የመጽናናት ልጅ” መሆኑን አሳይቷል። ለሳኦል ያደረገለትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሳኦል ክርስትናን እንደተቀበለ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር። በዚያ ያሉትን ደቀ መዛሙርት ማግኘት ቢፈልግም እነሱ በአሳዳጅነቱ ስለሚያውቁት ፈሩት። በርናባስ ግን ሳኦልን ስላመነው ከሐዋርያት ጋር አስተዋወቀው።—ሥራ 9:26-28
በርናባስ እንደ ስሙ “የመጽናናት ልጅ” መሆኑን በተግባር አሳይቷል (አንቀጽ 3ን ተመልከት)
ሌሎችን ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
4. ማጽናኛ ለመስጠት የተሻለው መንገድ የትኛው ነው? (ሮም 1:11, 12)
4 የሚቻል ከሆነ ሄዳችሁ ጠይቋቸው። ይሖዋ ሰዎችን ለማበረታታት አገልጋዮቹን ይጠቀማል። ለምሳሌ ነቢዩ ኤልያስ ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ይሖዋ መልአኩን ልኮ አበረታቶታል። (1 ነገ. 19:4-7) ሐዋርያው ጳውሎስም ወንድሞቹን ለማበረታታት እነሱን ሄዶ መጠየቅ አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ሮም 1:11, 12ን አንብብ።) አንድን ሰው ለማጽናናት ስንሄድ እንዲሁ ብቅ ብለን ሰላም ከማለት ባለፈ ሰፋ ያለ ጊዜ ልንሰጠው ይገባል። (1 ቆሮ. 16:7) ሆኖም በአካል መሄድ ባትችሉስ? ስልክ መደወል፣ ደብዳቤ ወይም ካርድ መጻፍ አሊያም የጽሑፍ መልእክት መላክ ትችላላችሁ። እነዚህ ነገሮች ያላቸውን ጠቀሜታ አቅልላችሁ አትመልከቱ። ታዲያ ሌሎችን ለማጽናናት ይሖዋ እንዲጠቀምባችሁ ትፈቅዳላችሁ?
5. ወንድሞቻችንን ማጽናናት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
5 ወደ መጨረሻው ይበልጥ እየተጠጋን ስንሄድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በአካል ሄደን ማጽናናት ከባድ እየሆነብን ሊመጣ ይችላል። በኤፌሶን ይኖር ከነበረው ከኦኔሲፎሮስ ግሩም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ኦኔሲፎሮስ ሊያጽናናው ፈልጎ ነበር። ጳውሎስን አፈላልጎ ማግኘቱ ሊያሳስረው አልፎ ተርፎም ሊያስገድለው እንደሚችል ቢያውቅም ይህን ከማድረግ ወደኋላ አላለም። (2 ጢሞ. 1:16-18) በሩሲያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በእምነታቸው ምክንያት ስደት ሲደርስባቸው ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል። ወንድሞቻቸው ችሎት ፊት ሲቀርቡ ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ ድጋፋቸውን አሳይተዋቸዋል። ይህን ያደረጉት በዚህ የተነሳ ራሳቸውም ለእስር ሊዳረጉ እንደሚችሉ እያወቁ ነው። እናንተስ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ለማጽናናት ራሳችሁን ማዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው? በዘመናችንም ሆነ በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች እርስ በርስ የተጽናኑት እንዴት እንደሆነ ማጥናት ትችላላችሁ። እንዲህ ስታደርጉ ስደት እየደረሰባቸውም ደስታቸውን መጠበቅ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ።
6. ሌሎችን ስናጽናና ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 አዳምጧቸው። ነቢዩ ኤልያስ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደወደቀ በተሰማው ጊዜ ልቡን በይሖዋ ፊት አፍስሷል። አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ ኤልያስን ያሳሰበው ምን እንደሆነ ቢያውቅም ኤልያስ ስሜቱን ሲገልጽ በጥሞና አዳምጦታል። ኤልያስ ያንኑ ሐሳብ ደጋግሞ በሚናገርበት ጊዜም ይሖዋ እሱን ለመስማት ፈቃደኛ ነበር! (1 ነገ. 19:9, 10, 14) ነቢዩ ዕንባቆም በዙሪያው ስለሚፈጸመው ግፍ የተሰማውን ሲናገርም ይሖዋ አዳምጦታል። ዕንባቆም የተናገረበት መንገድ አክብሮት የጎደለው ቢመስልም ይሖዋ ሐሳቡን እንዲገልጽ ፈቅዶለታል። (ዕን. 1:2, 3) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልገን የሚያውቅ ቢሆንም ጸሎታችንን ያዳምጣል። እኛም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በጥሞና እና በአክብሮት በማዳመጥ ይሖዋን መምሰል እንችላለን። ሌሎች ሲናገሩ፣ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ።’ እንዳመጣላቸው ቢናገሩም፣ ምናልባትም ያንኑ ሐሳብ ደጋግመው ሲናገሩ ብትሰሙም አታቋርጧቸው ወይም አትበሳጩባቸው።—ያዕ. 1:19፤ መክ. 7:9
ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ሲናገሩ በጥሞና በማዳመጥ ይሖዋን ምሰሉ (አንቀጽ 6ን ተመልከት)
7. መከራ ያጋጠመው አንድ ሰው ምን እንደሚያስፈልገው መረዳት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ግለሰቡ ምን እንደሚያስፈልገው ለማስተዋል ሞክሩ። ይሖዋ ልብ ማንበብ ይችላል፤ እኛ ግን አንችልም። ስለዚህ ግለሰቡ ምን ዓይነት ማጽናኛ እንደሚያስፈልገው ልናውቅ የምንችለው በትኩረት ካዳመጥነው ብቻ ነው። ‘እኔ በእሱ ቦታ ብሆን የሚያስፈልገኝ ይሄ ነው’ ብላችሁ በማሰብ ግለሰቡ የሚያስፈልገውን ለመገመት አትሞክሩ፤ ሁላችንም የተለያየን ነን። ስለዚህ ረጋ ብላችሁ በትኩረት አዳምጡት። እንዲሁም የውስጡን አውጥቶ እንዲናገር የሚረዱ ጥያቄዎችን ጠይቁት።—ምሳሌ 20:5
8. አልዓዛር ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ማርታንና ማርያምን ያጽናናቸው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
8 ኢየሱስ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ማርታንና ማርያምን ካጽናናበት መንገድ ምን እንደምንማር እንመልከት። ሁለቱም ያጡት ወንድማቸውን ቢሆንም ኢየሱስ ያጽናናቸው በተለያየ መንገድ ነው። ከማርታ ጋር ሲነጋገር ስለ ትንሣኤ ጠቅሶላታል። እንዲሁም በዚህ ተስፋ ላይ ያላትን እምነት እንድታጠናክር ረድቷታል። ማርያም እያለቀሰች ወደ እሱ ስትመጣ ግን ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ እንደነገራት ዘገባው አይናገርም። ከዚህ ይልቅ አብሯት አልቅሷል፤ እንዲሁም “የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠይቋል። (ዮሐ. 11:20-35) ከዚህ ምን እንማራለን? መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ ማጽናናት እንደምንችል ልናስብ አይገባም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ምን እንደሚያስፈልገው ማስተዋል ይኖርብናል።
ሌሎችን ስታጽናኑ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለመረዳት ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 8ን ተመልከት)a
9. ሌሎችን ለማጽናናት መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ሮም 15:4, 5)
9 መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቀሙ። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን የሚያጽናኑ ሐሳቦች ለሰዎች ስናነብ ተስፋቸው ይጠናከራል። (ሮም 15:4, 5ን አንብብ።) ተስፋቸው ሲጠናከር ደግሞ ይጽናናሉ እንዲሁም ይበረታታሉ። (ኢሳ. 40:31) ታዲያ የሚያበረታቱ ጥቅሶችን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ጥቅሶችን በማስታወሻ የመያዝ ልማድ አላቸው። ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት በተባለው መጽሐፍ ላይ “ማጽናኛ” በሚለው ርዕስ ሥር እንዲህ ዓይነት ጥቅሶችን ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም ቃሉን በሚያጽናና መንገድ ጥሩ አድርገህ መጠቀም እንድትችል ይሖዋ እንዲረዳህ በጸሎት ጠይቀው። መንፈሱ ለምታጽናናው ሰው ተስማሚ የሆነውን ጥቅስ ልክ ሲያስፈልግህ እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል።—ዮሐ. 14:26
10. ሌሎችን ስናጽናና በደግነት መናገር ያለብን ለምንድን ነው?
10 ንግግራችሁ ደግነት የተሞላበት ይሁን። “ማጽናናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማሳሰብ” ወይም “መምከር” የሚል ትርጉም ሊኖረውም ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የምናጽናናው ሰው አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ማሳሰብ ወይም መምከር ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ ማድረግ ካለብን የምንናገራቸው ቃላት የሚፈውሱ እንጂ የሚያቆስሉ እንዳይሆኑ፣ ከመናገራችን በፊት በጥንቃቄ ማሰብ አለብን። (ምሳሌ 12:18) ይሖዋ ኤልያስን ያነጋገረበት መንገድ በዚህ ረገድ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። ኤልያስ አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገለ ያለው እሱ ብቻ እንደሆነና አገልግሎቱ ምንም ጥቅም እንዳላስገኘ ተሰምቶት ነበር። ይሖዋ ለኤልያስ በቀጥታ ስህተቱን መንገር ሳያስፈልገው አመለካከቱን እንዲያስተካክል በደግነት ረድቶታል። (1 ነገ. 19:15-18) እናንተም ደግነት በማሳየትና ከመናገራችሁ በፊት ቆም ብላችሁ በማሰብ ይሖዋን መምሰል ትችላላችሁ። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ ክፍል ስታቀርቡ ወይም መልስ ስትመልሱ ምንጊዜም ደጎችና አዎንታዊ ሁኑ። እንዲህ ካደረጋችሁ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ታበረታታላችሁ እንዲሁም ታጠናክራላችሁ።
11. መከራ የደረሰባቸው ሰዎች በአብዛኛው ምን ያስፈልጋቸዋል? (1 ዮሐንስ 3:18)
11 ተግባራዊ እርዳታ ስጡ። መከራ የደረሰባቸው ሰዎች በአብዛኛው ከቃላት ባለፈ ተግባራዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (1 ዮሐንስ 3:18ን አንብብ።) በርናባስ ያደረገው ነገር በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። መሬቱን ሸጦ ገንዘቡ በቅርቡ የተጠመቁ ወንድሞቹንና እህቶቹን ለመርዳት እንዲውል ለሐዋርያት ሰጥቷል። (ሥራ 4:36, 37) በዛሬው ጊዜም ልክ እንደ በርናባስ ለእምነት አጋሮቻቸው ተግባራዊ እርዳታ የሚሰጡ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። በፖላንድ የምትኖረው ጋብሪኤላ ጎርፍ በቤቷ ላይ ከባድ ጉዳት ባደረሰበት ወቅት ተስፋ ቆርጣ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በፍርሃትና በጭንቀት ተዋጥኩ። አብረውኝ የሚኖሩት ወላጆቼም በጣም ተጨንቀው ነበር። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። በአቅራቢያችን ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች ግን በአንድ ቀን ውስጥ ተረባርበው ቤታችንን ጠገኑልን። ያደረጉልን ነገር በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል። ይሖዋ ሕዝቦቹን በመምራት መከራ የደረሰባቸውን እንደሚያጽናና ተመልክቻለሁ።”
12. መጽናታችን ሌሎችን የሚያጽናናው እንዴት ነው?
12 እናንተ ስትጸኑ ሌሎች ይጽናናሉ። ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በታማኝነት መጽናታቸውን ሲሰማ እንደተጽናና እንዲሁም ኃይሉ እንደታደሰ ገልጿል። እነሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያደረገው ጥረት ከንቱ እንዳልቀረ በማወቁ ተደስቷል። (1 ተሰ. 3:5-8) በሌላ በኩል ደግሞ እሱ ራሱ በመጽናቱ በአካል አግኝተውት የማያውቁትን ጨምሮ ሌሎችን ማጽናናት እንደሚችል ያውቅ ነበር። (ቆላ. 2:1, 2) በተመሳሳይም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋም ይሖዋ እየረዳን ያለው እንዴት እንደሆነ ሲመለከቱ በእጅጉ ይጽናናሉ።
13. ሌሎችን ስናጽናና የትኛው ባሕርይ ያስፈልገናል?
13 ታጋሽ ሁኑ። ተስፋ የቆረጡ ወንድሞችንና እህቶችን ለማጽናናት ስትሞክሩ ወዲያውኑ አይጽናኑ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ” ይላል፤ “ሁልጊዜ” የሚለው ቃል በቀጣይነት ማጽናኛ መስጠትን የሚያመለክት ነው። (1 ተሰ. 4:18) እናንተም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ስታጽናኑ እነሱን በትዕግሥት መርዳታችሁን ቀጥሉ። (1 ተሰ. 5:14) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ማጽናኛ የሚያስፈልገን እኛ ራሳችን ልንሆን እንችላለን። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
አንተ ራስህ ማጽናኛ ሲያስፈልግህ
14-15. የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
14 ወደ ይሖዋ ጸልይ። የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥምህ እንዲያጽናናህ ጠይቀው። (መዝ. 94:19) የሚሰማህን ሁሉ ግልጥልጥ አድርገህ በመንገር ልብህን በፊቱ አፍስስ። (መዝ. 62:8) እርግጥ ይሖዋ ከመጸለይህ በፊትም የሚሰማህን ያውቃል። ያም ሆኖ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የውስጥህን ግልጥልጥ አድርገህ ስትነግረው እምነትህን ያያል። ደግሞም ይሖዋ በእምነት ለቀረበ ጸሎት እሱ ትክክለኛ ነው ብሎ ባሰበው መንገድ ምንጊዜም መልስ ይሰጣል። (ማር. 11:24) ፊልጵስዩስ 4:6, 7 እንዲህ ይላል፦ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”
15 ሌሎች እንዲረዱህ ጠይቅ። ለአንድ የጎለመሰ ወዳጅህ ወይም ለምታምነው ሽማግሌ የሚሰማህን ንገረው። ወንድሞችህና እህቶችህ ሊያጽናኑህ ይችላሉ። ሆኖም የሚሰማህን ወይም የሚያስፈልግህን ካልነገርካቸው ያንን ለማወቅ ይቸገራሉ። (ምሳሌ 14:10) ጊዜ ሰጥተው እንዲያዳምጡህ አሊያም የሚያጽናና ጥቅስ ወይም ጽሑፍ እንዲልኩልህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ።
16. ሌሎች ሊያጽናኑን ሲሞክሩ ምን ሊፈጠር ይችላል? ሆኖም ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
16 ታጋሽና ይቅር ባይ ሁን። ወንድሞችህና እህቶችህ አንተን ለማጽናናት ሲሞክሩ ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የተናገሩት ወይም ያደረጉት ነገር ከማጽናናት ይልቅ ጭራሽ ስሜትህን ሊጎዳው ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ ታጋሽ ሁን። (1 ቆሮ. 13:4, 7) እንዲሁም ያዕቆብ 3:2 ላይ የሚገኘውን “በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው . . . ፍጹም ሰው ነው” የሚለውን ሐሳብ አትርሳ። ወንድሞችህና እህቶችህ ፍላጎታቸው አንተን ማጽናናት እንደሆነ አስታውስ። “እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”—ማቴ. 26:41
17. ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 ሁላችንም ማጽናኛና ማበረታቻ ያስፈልገናል። በተለይ የመጨረሻዎቹ ቀናት ይበልጥ አስጨናቂ እየሆኑ ሲመጡና የአምላክ ጠላቶች የሚያደርሱብን ተቃውሞ እየበረታ ሲሄድ ማጽናኛ ይበልጥ ያስፈልገናል። እንግዲያው አንዳችን ሌላውን ለማጽናናት የቻልነውን ሁሉ እናድርግ።
መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ
a የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ በቅርቡ ሚስቱ የሞተችበትን አንድ ወንድም በርኅራኄ ሲያዳምጥ። በሌላ ጊዜ ላይ ደግሞ ይኸው ሽማግሌ ሌላን ወንድም ሄዶ ይጠይቃል። የዚህ ወንድም ሚስት ከሞተች የተወሰነ ጊዜ አልፏል፤ በሕይወት ሳለች ያደረገቻቸውን መልካም ነገሮች እያስታወሱ ያወራሉ።