ከግንቦት 18-24, 2026
መዝሙር 35 ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ’
ምንም ነገር ትኩረትህን እንዲከፋፍልብህ አትፍቀድ
“የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።”—ኤፌ. 5:17
ዓላማ
ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ቢኖሩም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. አስፈላጊ የሆነ ነገርም እንኳ ትኩረት ከሚከፋፍሉ ነገሮች መካከል ሊመደብ የሚችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
በሕይወታችን ውስጥ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ያጋጥሙናል። በዚህ ወቅት ‘አሁን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?’ የሚለውን መወሰን ይኖርብናል። ለምሳሌ መኪና እየነዳህ እያለ ስልክ ተደወለልህ እንበል። የደወለልህ ሰው አስፈላጊ መልእክት ሊኖረው ይችላል። ሆኖም ጥያቄው ‘መልእክቱ አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም?’ የሚለው ሳይሆን ‘በዚያ ሰዓት ማተኮር ያለብህ በምን ላይ ነው?’ የሚለው ነው። በወቅቱ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር በመንገዱ ላይ ማተኮርህ እንደሆነ ግልጽ ነው።
2 ሕይወታችን አስፈላጊ በሆኑ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነው። ሆኖም ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችa መካፈላችን ነው። (ማቴ. 6:33) የይሖዋ ሕዝቦች ልክ እንደ አንድ ጠንቃቃ ሹፌር በመንገዳቸው ላይ እንዳያተኩሩ እንቅፋት የሚሆኑባቸውን ነገሮች ለይተው ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ።—ምሳሌ 4:25፤ ማቴ. 6:22
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? ለምንስ?
3 ማናችንም ብንሆን ሆን ብለን ትኩረታችን እንዲከፋፈል እንደማንፈቅድ የታወቀ ነው። ሆኖም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት እንዳናደርግ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። (ሉቃስ 21:34-36) የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች መመርመራችን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ትኩረት ለማድረግ ይረዳናል፦ (1) ትኩረታችንን ሊከፋፍሉ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (2) ኢየሱስ ምንም ነገር ትኩረቱን እንዳይከፋፍልበት ያደረገው እንዴት ነው? እንዲሁም (3) የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
ትኩረታችንን ሊከፋፍሉ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
4-6. ትኩረታችንን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
4 በሕይወታችን ውስጥ ትኩረታችንን የሚሹ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የጤንነታችን ወይም የቤተሰባችን ጉዳይ ያሳስበን ይሆናል። ልናከናውናቸው የሚገቡ ሌሎች የግል ጉዳዮችም ይኖራሉ። እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ ናቸው፤ ትኩረት ልንሰጣቸውም ይገባል። ይሁንና አእምሯችንን እንዲቆጣጠሩት እንዲሁም ጊዜያችንንና ጉልበታችንን እንዲያሟጥጡብን ከፈቀድን ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ሊሆኑብን ይችላሉ።
5 በተጨማሪም የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ስለሆነ በዙሪያችን የሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች ሕይወታችንን ሊያመሰቃቅሉት ይችላሉ። ከእነዚህ ነገሮች መካከል የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ወረርሽኝ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭቶች ይገኙበታል። (2 ጢሞ. 3:1) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን በጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ስለ ሌላ ነገር ማሰብ እንኳ ሊያቅተን ይችላል።
6 አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ምክንያት ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል፤ እኛም እንዲህ ያሉ ሰዎችን እናውቅ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ባጋጠማቸው ነገር የተነሳ በከፍተኛ ሐዘን ቢዋጡ የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም ሰዎች የተፈጠሩት በመከራ የተሞላ ሕይወት እንዲመሩ አይደለም፤ ስለዚህ ረዘም ላለ ጊዜ የዘለቀ ውጥረትን መቋቋም ይከብዳቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ካለፉ በኋላ መቼም ቢሆን እንደ ሌላው ሰው የተረጋጋ ሕይወት መምራት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ስለዚህ ጭንቀታቸውን ለመርሳት ሲሉ ያላቸውን ትርፍ ጊዜ ሁሉ በመዝናናት ለማሳለፍ ሊሞክሩ ይችላሉ። አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞሃል? ከሆነ፣ የኢየሱስ ምሳሌ ትኩረታችን ሳይከፋፈል በሙሉ ልባችን ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ የሚረዳን እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።
ኢየሱስ ትኩረቱ እንዳይከፋፈል የረዳው ምንድን ነው?
7. የኢየሱስን ትኩረት ሊከፋፍሉ የሚችሉ ምን ነገሮች ነበሩ?
7 ኢየሱስ ትኩረቱን ሊከፋፍሉበት የሚችሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ። በዘመኑ የነበሩትን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ብዙዎች በድህነትና በሕመም ይማቅቁ ነበር። (ማቴ. 14:14፤ ማር. 14:7) ከሮማውያንና ወገኖቻቸው ከሆኑት አይሁዳውያን የሚደርስባቸው ግፍም አለ። ሕዝቡ ኢየሱስ ተአምራትን የመፈጸም ችሎታ እንዳለው ሲያዩ ሊያነግሡት ፈልገው ነበር። (ዮሐ. 6:14, 15) ሰይጣንም በአቋራጭ ዓለምን መግዛት የሚችልበት አጋጣሚ በማቅረብ ኢየሱስን ሊፈትነው ሞክሯል። (ማቴ. 4:8, 9) የሚገርመው፣ የኢየሱስ የቅርብ ጓደኛ የሆነው ጴጥሮስም እንኳ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን” ብሎት ነበር፤ ይህም ቢሆን የመሥዋዕትነት ሕይወት እንዳይመራ ሊያዘናጋው የሚችል ፈተና ነው።—ማቴ. 16:21, 22
8. ኢየሱስ ትኩረቱ እንዳይከፋፈል የረዳው ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ትኩረቱ እንዳይከፋፈል የረዳው ምንድን ነው? አንደኛ፣ የይሖዋን አስተሳሰብ አዳብሯል። (ዮሐ. 8:28፤ 14:9) ሁለተኛ፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠምዷል። (ማቴ. 9:35) እንዲሁም ሦስተኛ፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ተገንዝቧል። (ዮሐ. 4:34) በመሆኑም ሰይጣን ላቀረበለት ፈተናዎች በቆራጥነት ምላሽ መስጠት ችሏል። ጴጥሮስ በቅን ልቦና ተነሳስቶ የሰጠው ምክርም ቢሆን አላታለለውም፤ ምክንያቱም የጴጥሮስ ምክር ከይሖዋ ዓላማ ጋር እንደሚጋጭ ተረድቶ ነበር። (ማቴ. 4:10፤ 16:23) ኢየሱስ የሰዎች አስተሳሰብ፣ ንግግርም ሆነ ድርጊት የአምላክን ዓላማ ከመፈጸም ትኩረቱን እንዲከፋፍልበት አልፈቀደም። እርግጥ ነው፣ የእኛን ትኩረት ሊከፋፍሉብን የሚችሉት ነገሮች ኢየሱስን ካጋጠሙት ነገሮች የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ነጥቦች ኢየሱስን እንደረዱት ሁሉ እኛም ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዱናል።
ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ምን ይረዳናል?
9. ‘የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል’ የምንችለው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 5:17)
9 የይሖዋን ዓይነት አስተሳሰብ አዳብር። እንዲህ ማድረግህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል? ‘የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል’ ማለትም እሱን የሚያስደስተው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዳሃል። (ኤፌሶን 5:17ን አንብብ።) ይህን ማወቅ የምትችለው ቃሉን በማንበብና በማሰላሰል ነው። እርግጥ ነው፣ አንተን ያጋጠመህ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ አልተጠቀሰ ይሆናል። እንደዚያም ቢሆን ይሖዋ የሚያስብበትን መንገድ ከተረዳህና ያገኘኸውን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆንክ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሖዋን የሚያስደስተው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ትችላለህ።
10. የይሖዋን አስተሳሰብ መረዳት የምንችለው እንዴት ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ወቅት ይሖዋ ሰዎችን የያዘበትን መንገድ በመመርመር የእሱን አስተሳሰብ ማወቅ እንችላለን። (ኤር. 45:5) የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ስናነብ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? ከዚህ ዘገባ አንጻር አስተሳሰቤን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ማስማማት የምችለው እንዴት ነው?’ እርግጥ ነው፣ የይሖዋ አስተሳሰብ ከእኛ አስተሳሰብ እጅግ ከፍ ያለ ነው። (ኢሳ. 55:9) በመሆኑም ፈቃዱን ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ለመማር የእሱ እርዳታ ያስፈልገናል። (መዝ. 143:10) ስለዚህ የእሱን አስተሳሰብ ለመረዳትና ለማዳበር እንዲረዳን በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል።—1 ዮሐ. 5:14
11. ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?
11 የይሖዋን ዓይነት አስተሳሰብ እያዳበርን ስንሄድ እሱ ትኩረታችን ሳይከፋፈል የዚህን ሥርዓት መጨረሻ ዝግጁ ሆነን እንድንጠብቅ እንደሚፈልግ እንገነዘባለን። (ማቴ. 24:44) ይሖዋ በሚሰማን ጭንቀት የተነሳ ልባችን ሸክም እንዲበዛበት አይፈልግም። (ማቴ. 6:31, 32) በመሆኑም ጤንነታችንን፣ ሥራችንን፣ ቤታችንን፣ ቤተሰባችንን ወይም ሌሎች ነገሮችን አስመልክቶ የሚሰማንን ጭንቀት ለመቋቋም የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል። በእሱ በመታመን እንዲረዳን ከጠየቅነው ያጋጠመንን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ብርታት ይሰጠናል።—መዝ. 55:22፤ ምሳሌ 3:5-7
12. በዓለም ላይ በሚከሰቱ ነገሮች የተነሳ የሚሰማንን ጭንቀት ለመቋቋም ምን ይረዳናል? (ማቴዎስ 5:3)
12 በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመድ። ሁላችንም በዓለም ላይ በሚከሰቱት ነገሮች የተነሳ በተወሰነ መጠን ጭንቀት ይሰማናል። ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን ውጭ ናቸው። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን ከቁጥጥራችን ውጭ በሆኑ ነገሮች የተነሳ ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል። ይሖዋ የፈጠረን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። በመሆኑም መንፈሳዊ ጥማታችንን ለማርካት ጥረት ስናደርግ ደስተኞች እንሆናለን። (ማቴዎስ 5:3ን አንብብ።) ይህን ጥማት ማርካት የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና አቅማችን በፈቀደ መጠን በይሖዋ አገልግሎት በመካፈል ነው። በዚህ መልኩ ጊዜያችንን በጥበብ ስንጠቀምበት ይሖዋ ይደሰታል።—ምሳሌ 23:15
13. ‘ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት’ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ክርስቲያኖች ‘ጊዜያቸውን በተሻለ መንገድ እንዲጠቀሙበት’ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 5:15, 16) ይህ ሐሳብ የተጻፈበት ዋነኛ ዓላማ ዕለታዊ የጊዜ አጠቃቀማችንን በተመለከተ ምክር ለመስጠት አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት ያለውን ጊዜ በጥበብ እንድንጠቀምበት ለማሳሰብ ነው። ታዲያ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ማባሪያ የሌላቸውን መጥፎ ዜናዎች በመከታተል ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ ትኩረታችን ሊከፋፈል፣ ተስፋ ልንቆርጥ እንዲሁም የአገልግሎት ቅንዓታችን ሊቀዘቅዝ ይችላል። እንግዲያው ዜና በማየት ወይም በማንበብ የምናሳልፈውን ጊዜ መገደባችን ምንኛ የተሻለ ነው! እንዲህ ካደረግን ከአላስፈላጊ ጭንቀት ራሳችንን እንጠብቃለን፤ እንዲሁም ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ልንጠቀምበት የምንችለው ተጨማሪ ጊዜ እናገኛለን። አገልግሎታችንን ማስፋት የምንችልበት መንገድ ይኖር እንደሆነ ማሰባችንም ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ማሻሻል ያለብን ነገር ይኖር ይሆን? ከጊዜው አጣዳፊነት አንጻር “ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ለመርዳት ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን።—1 ጢሞ. 2:4
14. በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን ምን ጥቅም አለው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን ዓለማችን ይህን ያህል በመከራ የተሞላው ለምን እንደሆነ እንድናስታውስ ይረዳናል። ዛሬ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና ወረርሽኝ ስናይ ከመጠን በላይ አንረበሽም። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆኑ እንገነዘባለን። ስለዚህ በሚሰማን ከመጠን ያለፈ ፍርሃት የተነሳ ትኩረታችን አይከፋፈልም። ይልቁንም የይሖዋ ዓላማ የሚፈጸምበት ጊዜ እንደቀረበ ስለምናውቅ በድፍረት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ደግሞ፣ ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም እንደሚረዳን በመተማመን ተረጋግተን እንኖራለን።—መዝ. 16:8፤ 112:1, 6-8
ዓለማችን በሚያስጨንቁ ክስተቶች የተሞላ ቢሆንም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመድህን ቀጥል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)b
15. “ጤናማ አስተሳሰብ” ምን ለማድረግ ይረዳናል? (1 ጴጥሮስ 4:7)
15 ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ አትዘንጋ። በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች የዚህ ሥርዓት መጥፊያ እንደቀረበ አያስተውሉም። ከዚህ ይልቅ ትኩረታቸው በሙሉ ያረፈው በመዝናኛ ላይ ነው። እርግጥ መዝናናት በራሱ ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም የዚህ ዓለም አመለካከት እንዳይጋባብን “ጤናማ አስተሳሰብ” ሊኖረን ይገባል። (1 ጴጥሮስ 4:7ን አንብብ።) ጤናማ አስተሳሰብ ካለን የማመዛዘን ችሎታችንን ጥሩ አድርገን እንጠቀምበታለን። ይህም በመዝናኛ ከመጠን ያለፈ ጊዜ እንዳናጠፋ ይረዳናል። በዚህ መልኩ ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀማችን የይሖዋን አስተሳሰብ እንደተረዳንና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ እንደተገነዘብን ያሳያል።—2 ጢሞ. 1:7
16. ኢየሱስ መሞቻው በተቃረበበት ወቅት ትኩረቱ ያረፈው በምን ላይ ነበር?
16 ኢየሱስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም ያስታውስ ነበር። ከመሞቱ በፊት በነበሩት እጅግ ፈታኝ ሰዓታት ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ ያረፈው ታማኝነቱን በመጠበቅና የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ነበር። በዚህም የተነሳ አጥብቆ ጸልዮአል። ደቀ መዛሙርቱ ግን እንደ ኢየሱስ ነቅተው መጠበቅ አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ “ከሐዘን የተነሳ ደክሟቸው ስለነበር” እንቅልፍ ወሰዳቸው።—ሉቃስ 22:39-46፤ ዮሐ. 19:30
17. ብዙዎች ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙት ለምንድን ነው? ሆኖም ማኅበራዊ ሚዲያ ምን አደጋ አለው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እኛም የምንዝልበትና በጭንቀት የምንዋጥበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ቢሰማን የሚያስገርም አይደለም። በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሰዎች ጭንቀታቸውን ለመርሳት ሲሉ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ዘወር ይላሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መዝናኛ በገፍ ይቀርባል። እርግጥ አንዳንዶች ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚኖሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት እንዲሁም ፎቶዎችንና አንዳንድ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ነው። ይሁንና አንድ ሰው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ ነገር ሁሉ አያምልጠኝ ካለ ጊዜውና ጉልበቱ ሊሟጠጥበት ይችላል። ለማኅበራዊ ሚዲያ ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ማኅበራዊ ሚዲያን የምጠቀምበት መንገድ ኃይሌን እያደሰልኝ ነው? ወይስ ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባው ነገር ያለኝን አመለካከት እያዛባብኝ ነው?’
የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀማችን በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በመዝናኛና በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል (አንቀጽ 17ን ተመልከት)
18. መዝናኛ በምንመርጥበት ወቅት የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
18 ቪዲዮ በሚታይባቸው ድረ ገጾችና አፕሊኬሽኖች ላይ ፊልሞችን፣ ተከታታይ ድራማዎችን ወይም አጫጭር ቪዲዮዎችን የምናይ ከሆነ የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ይኖርብናል፤ ከቪዲዮ ጌሞች ጋር በተያያዘም እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እነዚህ ነገሮች ሊያስደስቱንና አእምሯችንን ዘና ሊያደርጉልን ይችላሉ። ሆኖም የመዝናኛውን ዓይነት እንዲሁም በመዝናናት የምናሳልፈውን ጊዜ በምንወስንበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። እነዚህን አፕሊኬሽኖች ስንጠቀም አንድ ቪዲዮ አይተን ከጨረስን በኋላ ከሥር ከሥር ሌላ ቪዲዮ ይመጣልናል። የሚመጣልን ቪዲዮ ደግሞ ዓመፅ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። እስያ ውስጥ የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። በመጀመሪያ ከፊልሞች ላይ ተቀንጭበው የተወሰዱ ቪዲዮዎችን ኢንተርኔት ላይ ማየት ጀመረ። ከሥር ከሥር የሚመጡለትን ቪዲዮዎች ማየቱን ሲቀጥል ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ድርጊቶች ወደሚያሳዩ ቪዲዮዎች መራው። ውሎ አድሮ ደግሞ ፖርኖግራፊ መመልከት ጀመረ። ደግነቱ፣ በሽማግሌዎችና በቅርብ ጓደኞቹ እርዳታ ቆራጥ እርምጃዎችን ወሰደ። ቪዲዮ የሚያይባቸውን አፕሊኬሽኖች አጠፋ፤ እንዲሁም ስልኩን በመጠቀም በሚያሳልፈው ሰዓት ላይ ገደብ አበጀ። ይህ ተሞክሮ መዝናኛ በምንመርጥበት ወቅት የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ ጥሩ አድርጎ ያሳያል።
19. ሕይወታችን በመዝናኛ ላይ ያተኮረ ከሆነ ምን ሊፈጠር ይችላል?
19 በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ከመካፈልና ወጣ ብሎ ከመዝናናት ጋር በተያያዘም የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ሊያስፈልገን ይችላል። ሁላችንም አልፎ አልፎ ዘና ማለትና እረፍት ማድረግ ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረጋችን ለጤንነታችንም ጠቃሚ ነው። ሆኖም ለትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ከመጠን ያለፈ ቦታ የምንሰጥ ከሆነ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሚዛናችንን ሊያስቱንና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች የምናውለውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። (ፊልጵ. 1:10) ‘በምን ልዝናና’ እንዲሁም ‘በመዝናናት ምን ያህል ጊዜ ላሳልፍ’ የሚለው ጉዳይ ለእያንዳንዱ ሰው የተተወ የግል ውሳኔ ነው። እንዲህ ያለውን ውሳኔ በምናደርግበት ወቅት ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ወጣ ብሎ በመዝናናትና በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች በመካፈል የማጠፋው ጊዜ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዳለኝ ያሳያል? የጊዜ አጠቃቀሜ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ እንደምሰጥና “የሁሉም ነገር መጨረሻ” ለሚመጣበት ጊዜ እየተዘጋጀሁ እንዳለ ያሳያል?’—1 ጴጥ. 4:7
20. ምንም ነገር ትኩረታችንን እንዲከፋፍለው አለመፍቀዳችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
20 ምንም ነገር ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን ትኩረታችንን እንዲከፋፍለው አለመፍቀዳችን ይጠቅመናል። (ኢሳ. 48:17) ይሖዋ ስለሚረዳን በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን። በዓለም ላይ የሚከሰቱ አስደንጋጭ ክንውኖች ከመጠን በላይ አያስጨንቁንም። እንዲሁም በመዝናኛ ላይ ያተኮረ ሕይወት ከመምራት እንጠበቃለን። እንግዲያው የይሖዋን ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበራችንን፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችንን እንዲሁም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስታወሳችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን፣ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማሸነፍና ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀን መያዝ’ እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:19
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚለው አገላለጽ ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ያመለክታል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትን፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ የቤተሰብ አምልኮ ማድረግንና በአገልግሎት መካፈልን ይጨምራል። የስብሰባ አዳራሾችን መገንባትና መንከባከብ፣ በእርዳታ ሥራ መካፈል፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ መሆን እንዲሁም በቤቴል ማገልገልም እዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት በዓለም ላይ በሚከሰቱ አስጨናቂ ክንውኖች ሳይረበሹ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ሲካፈሉ።