ከግንቦት 11-17, 2026
መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን
በሉዓላዊው አምላክ በይሖዋ ታመኑ
‘ይሖዋ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል ነህ።’—መዝ. 83:18
ዓላማ
ሉዓላዊ አምላክ የሆነው ይሖዋ አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም እንደሚረዳን ያለንን እምነት ማጠናከር።
1. ኢዮብ የትኞቹ መከራዎች ደርሰውበታል?
በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ሀብት ንብረቱን፣ ጤንነቱን አልፎ ተርፎም ልጆቹን አጥቷል። ያከብሩት የነበሩ ሰዎች ንቀውታል። ‘እናጽናናዋለን’ ብለው የመጡት ጓደኞቹም ቢሆኑ ስሜቱን ከመደቆስ ውጭ የፈየዱለት ነገር አልነበረም። የሚወዳት ሚስቱ እንኳ በምሬት ተውጣ “አምላክን እርገምና ሙት!” አለችው። (ኢዮብ 2:9፤ 15:4, 5፤ 19:1-3) እነዚህ ሁሉ ተደራራቢ መከራዎች ኢዮብ፣ ይሖዋ የሚወዱትን አገልጋዮቹን ይንከባከባል በሚለው እውነታ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ ሊያደርጉት ይችሉ ነበር።
2-3. ምን ዓይነት ጥርጣሬ ሊያድርብን ይችላል? ከኢዮብ መጽሐፍ ምን ትምህርት እናገኛለን?
2 እኛም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) በመሆኑም እንደ ኢዮብ ከባድ መከራ ሊያጋጥመን ይችላል። ፈተናዎች ሲደራረቡብን ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነና ከዚህ በላይ መጽናት እንደማንችል ሊሰማን ይችላል። በዚህ ጊዜ እምነታችን በእጅጉ ሊፈተን እንዲሁም ‘ይሖዋ በእርግጥ ያስብልኛል?’ የሚለውን ጉዳይ መጠራጠር ልንጀምር እንችላለን።
3 እናንተም እንዲህ ተሰምቷችሁ የሚያውቅ ከሆነ ብቻችሁን አይደላችሁም። ኢዮብም እንዲህ ዓይነት ስሜት አድሮበት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚያድን ተምሯል። እኛም በሰማዩ አባታችን ላይ እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ማዳበር እንችላለን። ከኢዮብ መጽሐፍ የምናገኛቸው የሚከተሉት ሁለት ትምህርቶች እንዲህ ያለውን እምነት ለማዳበር ይረዱናል፦ አንደኛ፣ ከሁሉ የበላይ የሆነው የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ይሖዋ ነው። ሁለተኛ፣ አምላካችን ሁኔታዎችን በመቆጣጠር የተናገረው ነገር እንዲፈጸም ማድረግ እንዲሁም በአገልጋዮቹ ላይ ዘላቂ የሆነ መንፈሳዊና አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ይችላል።
ሰይጣን መጥቶ በመካከላቸው ቆመ
4. በሰማይ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ማን ተገኝቶ ነበር?
4 አንድ ቀን፣ “የእውነተኛው አምላክ ልጆች” በሰማይ በይሖዋ ፊት ተሰብስበው ሳለ “ሰይጣንም መጥቶ በመካከላቸው ቆመ።” (ኢዮብ 1:6) “ሰይጣን” የሚለው መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ ነው። ሰይጣን የይሖዋ ጠላት እንደመሆኑ መጠን “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ያለው ይህ ስያሜ ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። በዚህ ወቅት ሰይጣን ከአምላክ ታማኝ ልጆች አንዱ አልነበረም። የይሖዋ እንዲሁም በሰማይም ሆነ በምድር ያለው የይሖዋ ቤተሰብ ጠላት ሆኗል። ይሖዋ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተናገረው ሐሳብ ሰይጣን የይሖዋ ሰማያዊ ቤተሰብ አባል መሆኑ እንዳበቃ ያመለክታል። እዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ “በአንተና በሴቲቱ” በማለት ለይቶ ስለጠቀሰ ሰይጣን የሴቲቱ ክፍል አይደለም ማለት ነው። ይህች ሴት የይሖዋን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈውን ቤተሰብ የምታመለክት ሲሆን ‘ዘሩም’ የሚገኘው ከእሷ ነው።
5. በሰማይ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከተከናወነው ነገር ምን እንማራለን?
5 ይሖዋ በሰማይ በተካሄደው በዚያ ስብሰባ ላይ የተከናወነው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲቆይልን አድርጓል። ሰይጣን የተናገረው ነገር ጨካኝና ስም አጥፊ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። (ኢዮብ 1:9፤ ከራእይ 12:10 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ከዚህ ዘገባ የሚያጽናና ትምህርት እናገኛለን፤ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ቢሆንም ምንጊዜም ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ትክክለኛና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው። ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ የሁሉም የበላይ እንደመሆኑ መጠን እሱ ካስቀመጠው ገደብ ማለፍ የሚችል ማንም እንደሌለ እንማራለን።
ይሖዋ ካስቀመጠው ገደብ ማለፍ የሚችል ማንም የለም
6. ይሖዋ በሰማይ ላይ የተካሄደውን ስብሰባ የሚቆጣጠረው እሱ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው? (ኢዮብ 1:7, 8)
6 ኢዮብ 1:7, 8ን አንብብ። በሰማይ የተካሄደውን ያንን ስብሰባ የሚቆጣጠረው ይሖዋ ነበር። ይሖዋ ሰይጣን በኢዮብ ላይ ዓይኑን እንደጣለበት ቀድሞውንም አውቆ ነበር። ስለዚህ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትከው?” ብሎ በመጠየቅ ውይይቱን ያስጀመረው እሱ ራሱ ነው። ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይሉን ኢዮብን ለመርዳት የተጠቀመበት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
7. በኢዮብ 1:10, 11 መሠረት ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ምን የሚል ክስ ሰንዝሯል?
7 ኢዮብ 1:10, 11ን አንብብ። ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ሥልጣኑንና ኃይሉን እሱ በፈለገው መንገድ የመጠቀም መብት አለው፤ ደግሞም እሱ የሚያደርገው ነገር ምንጊዜም ትክክል ነው። (ኤር. 32:17፤ ዳን. 4:35) ያም ሆኖ ሰይጣን፣ ይሖዋ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት መንገድ አጠያያቂ እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ ተናገረ። ሰይጣን፣ ይሖዋ እንደ ኢዮብ ያሉ ሰዎች እሱን እንዲያገለግሉት የሚያደርገው በጥቅም እየደለለ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉት ከእሱ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ብለው እንደሆነ በመግለጽ ከሷቸዋል። ታዲያ ይሖዋ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን?
8-9. ይሖዋ በሰይጣን ላይ የትኛውን ግልጽ ገደብ ጥሏል? ለምንስ? (ኢዮብ 1:12) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 ኢዮብ 1:12ን አንብብ። ይሖዋ ለዲያብሎስ ክሱ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥበት አጋጣሚ ሰጠው፤ ሆኖም “[ኢዮብን] ራሱን ግን እንዳትነካው!” የሚል ግልጽ ገደብ አስቀመጠለት። ይሖዋ ለሰይጣን ያስቀመጠለትን ገደብ ሌሎቹ መላእክት ሁሉ ሰምተዋል። ሰይጣንም ይህን ገደብ ከማክበር ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረውም። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ከፈቀደለት ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም። በዚህ መንገድ ይሖዋ ሥልጣኑንና ኃይሉን ለኢዮብ ጥበቃ ለማድረግ እንዲሁም ስሙን ከተሰነዘረበት ነቀፋ ነፃ ለማድረግ ተጠቅሞበታል።
9 የሰይጣን የመጀመሪያ ሙከራ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል። ኢዮብ ለሰማዩ አባቱ ያለውን ታማኝነት ጠብቋል። (ኢዮብ 1:22) ያም ሆኖ ሰይጣን ተስፋ አልቆረጠም፤ አሁንም ኢዮብ ይሖዋን ማገልገሉን እንዲያቆም ማድረግ እንደሚችል ተሰምቶታል።
ይሖዋ ሰይጣን በሌሎች ፊት ክሱን እንዲያቀርብ ፈቅዶለታል (አንቀጽ 8-9ን ተመልከት)
10. ይሖዋ ሰይጣን በኢዮብ ላይ ተጨማሪ ፈተና እንዲያደርስበት የፈቀደለት ለምንድን ነው? (ኢዮብ 2:2-6)
10 ኢዮብ 2:2-6ን አንብብ። ሰይጣን በኢዮብ ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ለማፋፋም አሰበ። ኢዮብ ሕይወቱ አደጋ ላይ ከወደቀ አምላክን መርገሙ እንደማይቀር ተናገረ። ይሖዋ ለዚህ ክስ ምላሽ ለመስጠት ሲል ዲያብሎስ በኢዮብ ላይ አካላዊ ጉዳት እንዲያደርስበት ፈቀደለት። ግን አሁንም ቢሆን ይሖዋ “ሕይወቱን እንዳታጠፋ” የሚል ግልጽ ገደብ አስቀመጠለት። ሰይጣን የተጣለበትን ገደብ ከማክበር ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረውም። በዚህ ወቅትም ቢሆን ይሖዋ የሁሉም የበላይ መሆኑ ታይቷል፤ ምክንያቱም ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው ቢፈቀድለትም ይሖዋ ካስቀመጠለት ገደብ ማለፍ አይችልም ነበር።
ይሖዋ የኢዮብ መከራ እንዲያበቃ አደረገ
11. ይሖዋ የኢዮብ ፈተና እንዲያበቃ ካደረገ በኋላ የባረከው እንዴት ነው? (ኢዮብ 42:10-13)
11 ኢዮብ 42:10-13ን አንብብ። ኢዮብ አቋሙን እንደማያላላ በግልጽ ከታየ በኋላ ይሖዋ ሰይጣንን አስቆመው። በኢዮብ ላይ የሚደርሰው መከራም እንዲያበቃ አደረገ፤ እንዲሁም አትረፍርፎ ባረከው። አሁንም ቢሆን ሰይጣን የይሖዋን ውሳኔ ከማክበር ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረውም። ይሖዋ ውድ አገልጋዩን ኢዮብን በቀጥታ መፈተኑን እንዲቀጥል አልፈቀደለትም።
12. ይሖዋ በማዳን ኃይሉ የሚተማመኑ አገልጋዮቹን እንደሚረዳቸው የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
12 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በርካታ ክርስቲያኖች የይሖዋን የማዳን ኃይል በሕይወታቸው ማየት ችለዋል። ለምሳሌ 230 የይሖዋ ምሥክሮች በ1945 ከማጎሪያ ካምፕ ወጥተው ረጅምና አደገኛ ጉዞ በማድረግ ወደ ባሕር እንዲሄዱ ተደርጎ ነበር። የናዚ ወታደሮች ይህን ያደረጉት ሊገድሏቸው አስበው ቢሆንም ሁሉም በሕይወት ተርፈዋል። ያንን አስፈሪ ወቅት በጽናት ያለፉት ክርስቲያኖች ከጊዜ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ከባድ የፈተና ጊዜ አልፎ በሕይወት ለመትረፍ የበቁት ሰዎች ከእቶን እሳት የወጡ ያህል የሚቆጠር ሲሆን የእሳት ሽታ እንኳ የለባቸውም። . . . እንዲያውም ከይሖዋ ያገኙት ብርታትና ኃይል አጠናክሯቸዋል።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን ከአንበሶች ጉድጓድ ወጥተናል፤ . . . ከዚህ በኋላ ምኞታችን አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እሱም ይሖዋን ለዘላለም . . . ማገልገል ነው። ለእኛ ከሁሉ የላቀው ሽልማት ይህ ነው።”—ከዳንኤል 3:27፤ 6:22 ጋር አወዳድር።
13. በመከራ ውስጥ ስንሆን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
13 እኛም በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደተጣልን የሚሰማን ጊዜ ሊኖር ይችላል። (1 ጴጥ. 5:8-10) አንዳንድ ጊዜ አቅማችን ሙሉ በሙሉ እንደተሟጠጠና የሚደርስብን መከራ ማብቂያ እንደሌለው ይሰማን ይሆናል። በእነዚህ ጊዜያት የኢዮብን ታሪክ ማስታወሳችን ይረዳናል። ይሖዋ የሚደርስብንን መከራ ለማስቆም የሚያስችል ኃይል እንዳለው ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን፤ ይህን የሚያደርገው ወይ አሁን አሊያም ደግሞ በአዲሱ ዓለም ሊሆን ይችላል። ይህን ሥርዓት እሱ ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ አንድም ቀን እንኳ እንዲያልፍ አይፈቅድለትም!
ይሖዋ በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ የሚደርሰው መከራ እንዲያበቃ ያደርጋል (አንቀጽ 13ን ተመልከት)
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይወዳቸዋል
14-15. ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ምን ሊያደርግላቸው ይፈልጋል? ለምንስ? (ኢዮብ 14:15) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 ኢዮብ 14:15ን አንብብ። የሰማዩ አባታችን ለታማኝ አገልጋዮቹ ልዩ ፍቅር አለው። እንዲያውም በጣም ስለሚወዳቸው ቢሞቱ እንኳ መልሶ ሊያስነሳቸው ይጓጓል። ሞት ያስከተለውን ሐዘንና ሥቃይ በደስታና በእልልታ ይተካዋል።—ኢሳ. 65:17
15 ኢዮብ በሰይጣን ዓለም ውስጥ መኖሩን ቢቀጥልም ይሖዋ ጤንነቱን በመመለስና ከበፊቱ የበለጠ ብዙ መልካም ነገሮችን በመስጠት እንደባረከው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሆኖም እነዚህ በረከቶች ይሖዋ ወደፊት ለኢዮብ ከሚሰጠው ነገር አንጻር የቅምሻ ያህል ብቻ ነበሩ። ይሖዋ ለኢዮብ ያደረገለት ነገር አገልጋዮቹ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ያሳያል። ደግሞም ታማኝነታቸውን ላስመሠከሩ ሁሉ ፍጹም ሆነው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ራእይ 21:3, 4) ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ለማድረግ ከፈለገ የሚያግደው ምንም ነገር የለም። በመከራ ውስጥ ስንሆን ይህን ማሰባችን በጣም ያጽናናናል!
የኢዮብ ፈተና ካበቃ በኋላ ይሖዋ እሱንም ሆነ ሚስቱን አትረፍርፎ ባርኳቸዋል (አንቀጽ 14-15ን ተመልከት)
16. ይሖዋ የሁሉ የበላይ እንደሆነ የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ምንድን ነው?
16 ኢዮብ ረጅም ዕድሜ ቢኖርም ውሎ አድሮ መሞቱ አልቀረም። ሆኖም ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በሞትም ላይ ጭምር ሥልጣን አለው። (ዘዳ. 32:39) በመሆኑም የሚወዳቸውን ሰዎች እሱ ራሱ በወሰነው ጊዜ ከሞት እንዳያስነሳ የሚያግደው ምንም ነገር የለም።—ሮም 8:38, 39
ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኑ
17. ሰይጣን የይሖዋን ሕዝቦች ማጥፋት እንዳልቻለ የሚያሳየው ምንድን ነው?
17 የኢዮብ ታሪክ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ለመታመን የሚያነሳሱ አጥጋቢ ምክንያቶች ይሰጠናል። ሰይጣን ቢችል ኖሮ የይሖዋን ሕዝቦች ጠራርጎ ቢያጠፋ ደስ ይለው ነበር። ነገር ግን ይሖዋ ይህን እንዲያደርግ ስላልፈቀደለት ምንኛ አመስጋኞች ነን! በዛሬው ጊዜ ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መኖራቸው በራሱ ይሖዋ የሁሉ የበላይ መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። የይሖዋን አገልጋዮች ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ መክሸፉ እንደማይቀር በተደጋጋሚ ተመልክተናል። (ኢሳ. 54:17) እንደ ብረት የጠነከሩ መንግሥታትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ደካማ የሚመስሉትን የይሖዋ ሕዝቦች ማጥፋት አልቻሉም። በተጨማሪም ስለ ይሖዋ እውነቱን ከመናገር እንዲሁም ሰይጣን አጭበርባሪና ነፍሰ ገዳይ መሆኑን ከማጋለጥ ሊያግደን የሚችል ምንም ነገር የለም። ሞትም እንኳ ሊያስቆመን አይችልም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለእሱ ያላቸውን ታማኝነት ጠብቀው የሞቱ አገልጋዮቹን ከሞት ያስነሳቸዋል።—ሆሴዕ 13:14
18. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስናስብ ስጋት ሊያድርብን የማይገባው ለምንድን ነው?
18 በኢዮብ ታሪክ ላይ ስናሰላስል እምነታችን ስለሚጠናከር ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስጋት አያድርብንም። በታላቁ መከራ ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ደካማና ረዳት የለሽ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ ደግሞ እየተሳካላቸው ያለ ሊመስል ይችላል። ሆኖም በኢዮብ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ያኔም ከይሖዋ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ምንም ነገር የለም። ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ምንም ዓይነት ዘላቂ ጉዳት እንዲያደርስ አይፈቀድለትም። ይሖዋ ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ያደረሰውን መከራ ሁሉ የሚያስወግድበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው። ዲያብሎስና አጋንንቱ ለ1,000 ዓመት ያህል በጥልቁ ውስጥ ይታሰራሉ። (ሉቃስ 8:31፤ ራእይ 20:1-3) ከዚያ በኋላ ሰይጣንና ደጋፊዎቹ ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። (ራእይ 20:10) ይሖዋ እንዳለው የሰይጣን ራስ ይጨፈለቃል።—ዘፍ. 3:15፤ ሮም 16:20
19. በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑ ሰዎች የትኞቹን በረከቶች ያገኛሉ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
19 ፍጹምና ደስተኛ ሆነን የምንኖርበትን አዲሱን ዓለም በጉጉት እንጠባበቃለን። ያኔ ሕይወት ልንገምት ከምንችለው በላይ አስደሳች ይሆናል። ይሖዋ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:5) ይህ ምን ያካትታል? ከኤደን ገነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ዘር ሰይጣንና አጋንንቱ ከሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ ነፃ ይሆናል። ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ዓይነት ጉዳት በማያደርሱበት ዓለም ውስጥ መኖር እንዴት ያለ ግልግል ነው! ሥርዓቱ በሚያሳድርብን ጭንቀት ምክንያት እንቅልፍ አጥተን የምናድርባቸው ሌሊቶች ያለፈ ታሪክ ይሆናሉ። ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ብዙ ተአምር ሲፈጸም ይመለከታሉ። ሕመምተኞች ሁሉ ይፈወሳሉ። በተጨማሪም በሞት ያጣናቸውን ወዳጅ ዘመዶቻችንን በጉጉት ስንጠብቅ እንደነበረው በትንሣኤ እናገኛቸዋለን። የሰማዩ አባታችን ከመጀመሪያው አንስቶ ያሰበልንን ዓይነት ሕይወት መምራት እንችላለን!
ይሖዋ ብዙ መከራዎችን ያሳለፉ ታማኝ አገልጋዮቹን ወደፊት አትረፍርፎ ይባርካቸዋል (አንቀጽ 19ን ተመልከት)
20. ቁርጥ ውሳኔያችሁ ምንድን ነው?
20 በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እስከኖርን ድረስ ወደፊት የትኞቹ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን አናውቅም። ሆኖም ማንኛውንም ፈተና በድፍረት መጋፈጥ እንችላለን። እንግዲያው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ለመታመንና ከሉዓላዊነቱ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የሰማዩን አባታችንን ከልባችን እንደምንወደው በማሳየት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እናጋልጥ። ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ አስደሳች ተስፋ እንደሚጠብቀን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ምክንያቱም ሉዓላዊው አምላካችን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ለመባረክ ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ አለው።
መዝሙር 153 ድፍረት ስጠኝ