የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ
አብድዩ—አምላካዊ ፍርሃት አዳብር
አብድዩ በንጉሥ አክዓብ ቤት ላይ አዛዥ ነበር። ክፉው ንጉሥ አክዓብ አስጸያፊ የሆነው የባአል አምልኮ በምድሪቱ እንዲስፋፋ ፈቅዶ ነበር። አብድዩ ግን ‘ከወጣትነቱ ጀምሮ’ ይሖዋን ይፈራ ነበር። (1 ነገ. 18:1-13) በመሆኑም ንግሥት ኤልዛቤል ሁሉም የይሖዋ ነቢያት እንዲገደሉ ትእዛዝ ስታስተላልፍ አብድዩ እነሱን ለመርዳት በድፍረት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተገነዘበ። በወቅቱ አንድ ነቢይ መደበቅ እንኳ አደገኛ ነበር፤ አብድዩ ግን 100 ነቢያትን የደበቀ ከመሆኑም ሌላ ከባድ ረሃብ በተከሰተበት ወቅት ይመግባቸው ነበር! ንጉሡንና ንግሥቲቱን የሚያገለግሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐሰት ነቢያት ሳያዩት ይህን ማድረግ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም።—1 ነገ. 18:19
እኛስ ፈሪሃ አምላክ ከነበረው ከዚህ ሰው ምን ትምህርት እናገኛለን? አብድዩ አክዓብን ይፈራው የነበረ ቢሆንም ለአምላክ የነበረው ፍርሃት ግን ከዚህ የላቀ ነበር። ይህም ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ወንድሞቹን እንዲታደግ ድፍረት ሰጥቶታል። እኛም በምንኖርበት አካባቢ በእውነተኛው አምልኮ ላይ እገዳ ከተጣለ አምላካዊ ፍርሃት ማዳበር እንችላለን። እንዲህ ያለው ፍርሃት በፈተና ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመደገፍ ብርታት ይሰጠናል።