የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
የሕትመት ሥራችንን በማቀላጠፍ እውነትን “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ማድረስ
ጥቅምት 1, 2025
ይሖዋ አምላክ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ሆኖም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም የምንሰብክላቸው ሰዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ መሆኑ ይህን ፈታኝ ያደርገዋል። በየዓመቱ በእነዚህ ቋንቋዎች ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ ጽሑፎችን እናትማለን። ታዲያ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ሳናባክን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በእነዚህ ሁሉ ቋንቋዎች የምናዘጋጀው እንዴት ነው?
የምናትምባቸውን ቦታዎች መቀነስና ማሽኖቹን ማዘመን
በ1980ዎቹ መጽሔቶችን የምናትምባቸው አገሮች ከ40 ይበልጡ ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን በሕትመት ሥራችን ላይ ደረጃ በደረጃ ለውጥ አድርገናል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ጽሑፎቻችንን የምናትመው ዘጠኝ አገሮች ውስጥ ብቻ ነው። የሚገርመው ግን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁባቸው ቋንቋዎች ብዛት በ500 ፐርሰንት ገደማ ጨምሯል! የምናትምባቸውን ቦታዎች ቀንሰን ቋንቋዎቹን መጨመር የቻልነው እንዴት ነው? ለዚህ የረዳን አንዱ ነገር ማተሚያ ማሽኖቻችንን ማዘመናችን ነው።
ዘመናዊ ማሽኖችን መጠቀማችን ተጨማሪ ጽሑፎችን ከቀድሞው ባነሰ ጊዜ ለማተም አስችሎናል። ቀደም ሲል በነበሩን ማሽኖች አንድን የሕትመት ሥራ ጨርሰን ወደ ቀጣዩ ለመሸጋገር ረጅም ጊዜ ይወስድብን ነበር። አሁን ባሉን ማሽኖች ግን ይህን የምናደርግበት ፍጥነት በአራት እጥፍ ጨምሯል። በመሆኑም የሕትመት ሥራችን ከበፊቱ ይበልጥ ተቀላጥፏል። ጥቂት ተናጋሪ ባላቸው ቋንቋዎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጽሑፎችንም ማተም ችለናል። እርግጥ ነው፣ ለእያንዳንዱ የሕትመት ሥራ አዲስ ፕሌት (የሚታተመውን ጽሑፍና ሥዕል የያዘ ስስ ብረት) ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በቅርቡ ፕሌቶችን ለማዘጋጀት ብቻ በ12 ወር ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ገደማ አውጥተናል።a ስለዚህ በጣም አነስተኛ ለሆኑ የሕትመት ሥራዎች፣ ፕሌት ማዘጋጀት የማይጠይቁ ዲጂታል ማተሚያዎችን እንጠቀማለን። እነዚህ ማተሚያ ማሽኖች (ጨረር የሚጠቀሙትን ጨምሮ ማለት ነው) በአንጻራዊ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁና ብክነት የሚቀንሱ ናቸው።
ከአንዱ የሕትመት ሥራ ወደ ቀጣዩ ለመሸጋገር ፕሌቶችን ሲቀይሩ
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የማተሚያና የመጠረዣ ማሽኖቻችንን ለማዘመን ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥተናል። ከእነዚህ ማሽኖች መካከል አንዳንዶቹን ለመጽሐፍ ቅዱስ የሕትመት ሥራ እንጠቀምባቸዋለን። ከዚህ ቀደም አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ገጾቹ ከታተሙ በኋላ መጽሐፍ ሆኖ እንዲወጣ ከ40 የሚበልጡ ሂደቶችን ማለፍ ነበረበት። ከእነዚህ መካከል ገጾቹን መስፋት፣ መቁረጥ፣ ጠርዞቹን ማስተካከል፣ ማለስለስ እንዲሁም የሚያብረቀርቅ ነገር መቀባት ይገኙበታል። በተጨማሪም እያንዳንዱ ሂደት ሲጠናቀቅ ሠራተኞች መጽሐፍ ቅዱሶቹን ወደ ቀጣዩ ቦታ መውሰድና መደርደር ያስፈልጋቸው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉት ሂደቶች አሥር ብቻ ሆነዋል። ይህ ሊሆን የቻለው በአዲሱ ማሽን ላይ ብዙ ሂደቶች ስለተቀላቀሉና መጽሐፍ ቅዱሶቹን ከአንዱ ሂደት ወደ ቀጣዩ ሂደት የሚያጓጉዝ ማሽን ስለተገጠመ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ከ55 በመቶ በላይ መቀነስ ችለናል። በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ያለው የመጠረዣ ክፍል በየስምንት ሰዓቱ የሚያዘጋጀው 2,000 መጽሐፍ ቅዱሶችን ብቻ ነበር። አሁን ግን በስምንት ሰዓት ውስጥ ወደ 35,000 የሚጠጉ መጽሐፍ ቅዱሶችን ያዘጋጃል!
እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመለየት ባርኮዶች ይደረጋሉ፤ በዚያ መሠረት ገጾቹ ይሰበሰባሉ እንዲሁም በፈርጅ በፈርጅ ይቀመጣሉ
የምናከማቻቸውን ነገሮች በመቀነስ ወጪ መቆጠብ
ከላይ እንደተመለከትነው አሁን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጽሑፎችን ማተም ችለናል። ከአንድ የሕትመት ሥራ ወደ ሌላው ለመሸጋገር የሚያስፈልገን ጊዜም ቀንሷል። በዚህ የተነሳ እንደ በፊቱ በማተሚያ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን ውስጥ ብዙ ጽሑፎችን ማከማቸት አያስፈልገንም። ይህ ደግሞ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ለመጠቀም አስችሎናል። በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ጌሪ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በአንዴ ብዙ ጽሑፎች ከማተም ይልቅ በየጊዜው አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ጽሑፎች ማተም ይሻላል የሚለው ሐሳብ መጀመሪያ ላይ የሚያስኬድ አልመሰለንም ነበር።” አክሎም ጌሪ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ለውጥ ባደረግንበት በመጀመሪያው ዓመት የፕሌቶችና የወረቀት ወጪያችን በ60,000 ዶላር ጨመረ። ሆኖም ወረቀትና የታተሙ መጻሕፍትን ለማከማቸት የምናወጣው ወጪ ስለቀነሰ በዚያው ዓመት ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማትረፍ ችለናል!” ይህ ገንዘብ እንደ ስብሰባ አዳራሽ ግንባታና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ላሉ አስፈላጊ ሥራዎች እንዲውል ይደረጋል።
እንደ ድሮው ወረቀትና የታተሙ ጽሑፎችን አለማከማቸታችን በአንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን ተጨማሪ ነፃ ቦታ እንዲገኝ አስችሏል። ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ያንን ነፃ ቦታ ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የሕትመት ሥራው የሚከናወነው በጥቂት ቦታዎች ብቻ መሆኑ ደግሞ አዳዲስ የሚገነቡ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስፋት ለመቀነስ አስችሏል። ለምሳሌ በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ይከናወን የነበረው የሕትመት ሥራ በ2018 ወደ ማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮና ወደ ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲዛወር ተደረገ። በመሆኑም በቼልምስፎርድ፣ እንግሊዝ የተገነባው አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ የማተሚያ ቦታ አላስፈለገውም። ይህም ከግንባታ ወጪው ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለመቀነስ አችሎናል።
“እኔንም አሰብከኝ ማለት ነው!”
የሕትመት ሥራችን መቀላጠፉ ያስገኘው ትልቁ ጥቅም ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት መቻላችን ነው። አሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅጂዎችን ብቻ በሚፈልጉ ቋንቋዎችም ጭምር ጽሑፎቻችንን ማተም ችለናል። ለምሳሌ የዋሊስኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩት በኒው ካሊዶኒያ እንዲሁም በዋሊስ እና በፉቱና ሲሆን ቁጥራቸውም 35,000 ገደማ ብቻ ነው። ሆኖም ነሐሴ 2024 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በዋሊስኛ ወጣ። የዋሊስኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች ሴላፊና የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “ፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉት አንዳንድ አገላለጾች አይገቡኝም ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በዋሊስኛ ሲወጣ እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ። ‘ይሖዋ ሆይ፣ እኔንም አሰብከኝ ማለት ነው! እውነትም የማታዳላ አምላክ ነህ’ ብዬ ጸለይኩ።”
አሁን ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በዋሊስኛ ወጥቷል
በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ውስጥ የሚኖሩት የሳንጋ ቋንቋ ተናጋሪዎች 500,000 እንኳ አይሞሉም። ያም ሆኖ ሙሉው ለዘላለም በደስታ ኑር! መጽሐፍ በዚህ ቋንቋ ወጥቷል። በሳንጋ ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግለው ዦዝዌ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ለምናስተምራቸው ሰዎች አንዳንድ ቃላትንና አገላለጾችን ማብራራት ወይም መተርጎም ቀላል አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ብዙ ለፍተን አብራርተንላቸው እንኳ መጽሐፉ ምን ሊል እንደፈለገ አይገባቸውም ነበር። ስለዚህ መጽሐፉ በሳንጋ ቋንቋ ሲወጣ እፎይ አልን! አሁን መጽሐፍ ቅዱስ የማስተምራቸው ሰዎች የሚማሩት ነገር ቶሎ ይገባቸዋል፤ ረጅም ማብራሪያ መስጠትም አያስፈልገኝም።”
ሆንዱራስ ውስጥ፣ በጋሪፉና ቋንቋ የተዘጋጀውን ለዘላለም በደስታ ኑር! መጽሐፍ ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ፤ ይህ ቋንቋ ወደ 120,000 የሚጠጉ ተናጋሪዎች አሉት
በአሁኑ ጊዜ ጽሑፎቻችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለብዙ ሰዎች መድረስ ችለዋል፤ የሚታተሙባቸውና የሚሰራጩባቸው ቋንቋዎች ብዛትም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጨምሯል። ይህ ሊሳካ የቻለው በdonate.jw.org እና በሌሎች መንገዶች በምታደርጉት የገንዘብ መዋጮ አማካኝነት ነው። ለልግስናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።
a በዚህ ርዕስ ውስጥ ሁሉም ገንዘቦች የተጠቀሱት በአሜሪካ ዶላር ነው።