የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
አሁንም ጽሑፎችን የምናትመው ለምንድን ነው?
ሚያዝያ 1, 2026
መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ሌሎች ጽሑፎቻችንን ስታነብ የታተመውን ቅጂ ትመርጣለህ ወይስ የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን? አብዛኞቻችን እንደ ድሮው፣ የታተመውን መጽሐፍ ወይም መጽሔት ከማንበብ ይልቅ ስልካችን ወይም ታብሌታችን ላይ ማንበብ ይቀናናል። ምናልባትም ይህን ርዕስ ራሱ እያነበብክ ያለኸው በኤሌክትሮኒክ መሣሪያህ ሊሆን ይችላል። ጽሑፎቻችንን JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን እና jw.org ላይ በቀላሉ ማግኘት በመቻላችን ደስተኞች ነን!
አሁን አሁን አብዛኞቹ ጽሑፎቻችን ከሕትመት ይልቅ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የሚወጡት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የኤሌክትሮኒክ ቅጂው ለአጠቃቀም ይበልጥ ምቹ ነው፤ እንዲሁም በታተመው ጽሑፍ ላይ የሌሉ ተጨማሪ ገጽታዎች አሉት። በዚህም የተነሳ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እሱን መጠቀም ይመርጣሉ። ሌላው ምክንያት ደግሞ በአገልግሎት ላይ ጽሑፎችን መጠቀም ባናቆምም አሁን ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው ውይይት በመጀመር ላይ ስለሆነ ነው።
በዚህም የተነሳ አሁን የምናትመው ጽሑፍ ብዛት የዛሬ አሥር ዓመት እናትም ከነበረው የጽሑፍ ብዛት ጋር ሲወዳደር 60 በመቶ ቀንሷል! በ2015 ማለትም JW ላይብረሪ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ከመጀመሩ በፊት ብዙዎቹ የማተሚያ ማሽኖቻችን ያለማቋረጥ በቀን ለ16 ሰዓት ይሠሩ ነበር። እንደዚያም ሆኖ አቅርቦቱና ፍላጎቱ ሊመጣጠን ስላልቻለ አንዳንዶቹ ማሽኖች በቀን ውስጥ ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓት እንዲሠሩ ታስቦ ነበር። አሁን ግን አብዛኞቹ ማሽኖቻችን የሚሠሩት በቀን ለስምንት ሰዓት ያህል ብቻ ነው።
የምናትመውን ጽሑፍ ብዛት የቀነስነው እኛ ብቻ አይደለንም። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ድርጅቶች የሚያትሟቸውን ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ሌሎች ጽሑፎች ቁጥር ቀንሰዋል። ሰዎች ይበልጥ ወደ ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች እያደሉ በመጡበት በአሁኑ ጊዜ የታተሙ ቅጂዎችን ማዘጋጀት በእርግጥ ያስፈልጋል? አዎ! አሁንም ጽሑፎችን እያተምን ያለነው ለምን እንደሆነና የእናንተ መዋጮ ይህን ለማሳካት እየረዳ ያለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
በማላዊ የሚኖሩ እህቶች ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር የታተመ ቅጂ ይዘው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ
የታተሙ ጽሑፎች አሁንም የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው?
አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የታተሙ ጽሑፎች የግድ ያስፈልጓቸዋል። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፦
“የታተመውን ጽሑፍ ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ የለኝም። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ለመግዛት አቅሜ አይፈቅድም። አቅሜ ፈቅዶ ብገዛ እንኳ በአካባቢያችን መብራት በተደጋጋሚ ስለሚጠፋ ቻርጅ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የኤሌክትሮኒክ ቅጂዎችን ብቻ ተማምኖ መኖር አይቻልም።”—ኦዴተ፣ ሞዛምቢክ
“ስልክ ወይም ታብሌት ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ የለኝም። ዋጋቸው ረከስ ያሉት መሣሪያዎች ደግሞ ቶሎ ይበላሻሉ፤ በየጊዜው ጥገና ያስፈልጋቸዋል። እስኪጠገኑ ድረስ ምንም ነገር ላላነብ ነው ማለት ነው።”—ሊነሊ፣ ማላዊ
“እኔና ሁለት ሴት ልጆቼ አንድ ስልክ ነው በጋራ የምንጠቀመው። ምክንያቱም ለሦስታችንም ስልክ ለመግዛት አቅም የለኝም። ስብሰባ ላይ አንዳችን ስልኩን ከያዝን የተቀረነው ሁለታችን ደግሞ የታተመውን ጽሑፍ እንይዛለን።”—ስኒነ፣ ማይክሮኔዥያ
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ጽሑፎችን በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ለማግኘት ባይቸገሩም የታተመውን ቅጂ ቢጠቀሙ ይመርጣሉ። አንዳንዶች የሰጡትን አስተያየት እስቲ እንመልከት፦
“የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን በብዛት እጠቀማለሁ። ለስብሰባ ስዘጋጅ ግን የታተመውን ጽሑፍ ብጠቀም እመርጣለሁ። የታተመውን ጽሑፍ በእጄ ይዤ ሳነብ፣ ዋና ዋና ነጥቦቹን ሳቀልምና በኅዳጉ ላይ ማስታወሻዎችን ስጽፍ ደስ ይለኛል። እነዚህን ነገሮች የኤሌክትሮኒክ ቅጂው ላይም ማድረግ እችላለሁ። ግን ወረቀት ላይ ሲሆን ሐሳቡ ይበልጥ በአእምሮዬና በልቤ ላይ እንደሚታተም ይሰማኛል።”—ማርሲያ፣ ብራዚል
“የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ ማንበብ ዓይኔን ያደክመዋል፤ የታተሙ ጽሑፎችን ማንበብ ይቀለኛል። በዚያ ላይ ለቴክኖሎጂ ብዙም ቅርብ አይደለሁም። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ ማስታወሻ መያዝ፣ ጽሑፎችን ማውረድና አንዳንድ መረጃዎችን ፈልጎ ማግኘት ያታግለኛል።”—ሰሊና፣ ሞዛምቢክ
“ቀኑን ሙሉ ስልኬንና ኮምፒውተር ስጠቀም ነው የምውለው። የግል ጥናት ሳደርግ ግን ከእነዚህ ነገሮች ተላቅቄ በታተመው ቅጂ ብጠቅም እመርጣለሁ። ይህም በሚመጡልኝ መልእክቶች ትኩረቴ ሳይከፋፈል ተረጋግቼ ለማንበብ ያስችለኛል።”—ጊዮም፣ ካናዳ
“አገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች የጽሑፎቻችንን የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ለመላክ የስልክ ቁጥራቸውን ወይም የኢሜይል አድራሻቸውን መጠየቅ ያስፈልገናል። ሆኖም ገና በመጀመሪያው ውይይት ላይ ይህን መረጃ መጠየቅ ቀላል አይደለም። ስለዚህ በአብዛኛው የምንመርጠው የታተመውን ቅጂ መስጠት ነው። አንዳንዴም የምንሰብክበት አካባቢ ወንጀል የሚበዛበት ነው። እንዲህ ባሉ ቦታዎች ደግሞ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መጠቀም አስቸጋሪ ነው።”—በደቡብ አሜሪካ የሚኖር የወረዳ የበላይ ተመልካች
ለስብሰባ ለመዘጋጀት የታተሙ ቅጂዎችን መጠቀም የሚመርጡ ብዙ አሉ
ታዲያ የታተሙ ጽሑፎች የግድ የሚያስፈልጓቸውንም ሆነ እነሱን መጠቀም የሚመርጡትን ወንድሞቻችንን ለመርዳት ምን እያደረግን ነው?
የሚያስፈልገውን ያህል ጽሑፍ ማተም
በዘጠኝ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን ውስጥ ጽሑፎችን ማተማችንን ቀጥለናል። በ2025 የአገልግሎት ዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ ከ18 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት እንዲሁም ከ941 ሚሊዮን በላይ ትራክቶችና መጋበዣዎች አትመናል፤ በአጠቃላይ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ጽሑፎች ታትመዋል። እነዚህን ጽሑፎች ለማተም ከ35 ሚሊዮን ዶላርa በላይ ወጪ ተደርጓል። በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ዓመታት የማተሚያና የመጠረዣ መሣሪያዎቻችንን ለማሻሻል ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ አድርገናል።
በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በጥበብ መጠቀም ስለምንፈልግ የምናትመው የሚያስፈልገውን ያህል ጽሑፍ ብቻ ነው። ቀደም ሲል እንደተገለጸው በአገልግሎት ላይ ጽሑፎችን መጠቀማችንን የቀጠልን ቢሆንም አሁን ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው ውይይት በመጀመር ላይ ነው። ስለዚህ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ፣ የምናትመውን የንቁ! መጽሔት ብዛት ቀንሰናል። ቀደም ሲል በምናትመው መጽሔት ብዛት በዓመት ለአንድ አስፋፊ 86 ንቁ! መጽሔት ይደርሰው ነበር። አሁን ግን በዓመት ለአንድ አስፋፊ የሚደርሰው 11 መጽሔት ብቻ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ አስፋፊዎች አዘውትረው የአድራሻ ካርዶችን እንደሚጠቀሙ ስለተስተዋለ የምናትማቸው የአድራሻ ካርዶች ብዛት ከ2020 በፊት ከነበረው በሦስት እጥፍ ጨምሯል።
‘አምላክ ለእያንዳንዱ ሰው ያስባል’
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጽሑፎችን ማተም በመቀጠላችን አመስጋኞች ናቸው። በብራዚል የሚኖረው ሪካርዶ እንዲህ ብሏል፦ “የኤሌክትሮኒክ ቅጂዎችን ማግኘት የማይችሉትን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት ሰዎች መንፈሳዊ ምግብ እንዲደርሳቸው ልዩ ጥረት በሚያደርግ አፍቃሪ ድርጅት ውስጥ በመታቀፌ ደስተኛ ነኝ። ‘የተጠማ ሁሉ’ እና ‘የሚፈልግ ሁሉ’ ሕይወት አድን የሆነውን መልእክት በቀላሉ ማግኘት ይችላል።” (ራእይ 22:17) በታሂቲ የሚኖረው በርናርድ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የጽሑፎቻችን የታተሙ ቅጂዎች አሁንም እየተዘጋጁ በመሆናቸው በጣም አመስጋኝ ነኝ። የይሖዋ ድርጅት አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ምክንያታዊ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። ድርጅቱ ልጅ አዋቂ፣ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉም ሰው የመንግሥቱ ምሥራች እንዲደርሰው እያደረገ ነው። ይህም አምላካችን ለእያንዳንዱ ግለሰብ ምን ያህል እንደሚያስብ በግልጽ ያሳያል።”
በብራዚል የምትኖረው አንድሬያ፣ የምታደርገው መዋጮ ጽሑፎችን የማተሙን ሥራ እንደሚደግፍ ታውቃለች። ይህን በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “የታተሙ ቅጂዎችን ማዘጋጀት ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ክህሎትና ጥረት ይጠይቃል። ያም ቢሆን ድርጅታችን የኤሌክትሮኒክ ቅጂዎችን ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ሲል ጽሑፎችን ማተሙን ቀጥሏል። ይህ አምላክ ለእያንዳንዱ ሰው እንደሚያስብ አሳምኖኛል። የሕትመት ሥራው ብቻ እንኳ በደስታ መዋጮ ለማድረግ የሚያነሳሳኝ በቂ ምክንያት ነው።”
donate.jw.orgን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅማችሁ የምታደርጓቸውን መዋጮዎች ከልብ እናደንቃለን። መዋጯችሁ የታተሙ ጽሑፎች የግድ ለሚያስፈልጓቸውም ሆነ እነሱን መጠቀም ለሚመርጡ ሰዎች ስንል ጽሑፎችን ማተማችንን እንድንቀጥል አስችሎናል።
a በዚህ ርዕስ ውስጥ ሁሉም ገንዘቦች የተጠቀሱት በአሜሪካ ዶላር ነው።