Imagination World/stock.adobe.com
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ መልእክት—ተስፋ ለስደተኞች!
በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ይፈናቀላሉ። አንተስ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ አጋጥሞሃል? ከሆነ፣ አምላክ እንደሚረዳህ አትጠራጠር። ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚኖርህ ቃል ገብቶልሃል፤ ይህ ተስፋ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው።
“ስደተኞች እና ተፈናቃዮችa የሚያስፈልጋቸው አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ብቻ አይደለም፤ . . . ተስፋም ያስፈልጋቸዋል” በማለት የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነርb የሆኑት ክሪስቶስ ስታሊያኒደስ ተናግረዋል። ተስፋ ያላቸው ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት ይኖራቸዋል። ስደተኞች ከደረሰባቸው የስሜት ቁስል ለማገገም ከተስፋ በተጨማሪ መጽናኛም ያስፈልጋቸዋል።
“ቤተሰቤን ትቼ ከአገሬ በተሰደድኩበት ወቅት ለመቋቋም የሚያዳግት የባዶነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። በፍርሃት፣ በሐዘንና በጭንቀት ተዋጥኩ።”—ኢማኑኤል፣ ሄይቲ
አንተስ ከእነዚህ ስሜቶች ጋር እየታገልክ ነው? ከመኖሪያህ ተፈናቅለህ ከሆነ መጽናኛና ተስፋ እንደሚያስፈልግህ ጥያቄ የለውም። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ መጽናኛ
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋc . . . የባዕድ አገሩን ሰው ይወደዋል።”—ዘዳግም 10:17, 18
ስለዚህ ብቻህን አይደለህም። መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ አምላክ ያለህበትን ሁኔታ ይረዳልሃል፤ ይወድሃል፤ እንዲሁም በጣም ያስብልሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው።”—መዝሙር 145:18
ስለዚህ ስትጸልይ ይሖዋ ይሰማሃል። ውስጣዊ ሰላም እንድታገኝ ይረዳሃል። በተጨማሪም ያለህበትን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይሰጥሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል’ . . . ማለት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው! . . . ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ፍትሕን አያዛባም።”—ኢዮብ 34:10, 12
ስለዚህ ለሚደርስብህ መከራ ተጠያቂው አምላክ አይደለም። ይህ ሁኔታ የደረሰብህ አምላክ እየቀጣህ ወይም እየፈተነህ ስለሆነ አይደለም።
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ ተስፋ
አምላክ ወደፊት ምን እንደሚያደርግልን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህ ተስፋ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4
ስለዚህ መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል። አምላክ ሕይወት ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆንብን ያደረጉ ችግሮችን በሙሉ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል።
“አምላክ በዓለም ላይ የሚፈጸመውን ግፍና ክፋት በቅርቡ ያስወግዳል። ይህን ማወቄ መከራ የማይኖርበትን ጊዜ ተስፋ እያደረግኩ እንድኖር ረድቶኛል።”—ካርላ፣ ኤል ሳልቫዶር
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም።”—ኢሳይያስ 65:17
ስለዚህ በመጥፎ ትዝታዎች ምክንያት ከሚሰማን ሥቃይ ነፃ እንወጣለን። አምላክ የደረሱብህ መጥፎ ነገሮች ያስከተሉብህን የስሜት ጠባሳዎች ሙሉ በሙሉ ይሽርልሃል።
“መጽሐፍ ቅዱስ የደረሰብንን ሥቃይና መከራ ጨርሶ እንደማናስታውሰው ይናገራል። ይህ ተስፋ ያጋጠመኝን አስቸጋሪ ሁኔታ እንድቋቋም ይረዳኛል፤ ምክንያቱም በቅርቡ ሁሉም ነገር እንደሚቀየር አውቃለሁ።”—ናታሊያ፣ ዩክሬን
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት . . . እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል።”—ዳንኤል 2:44
ስለዚህ በሰማይ ላይ የሚገኝ ፍጹም የሆነ መንግሥት ምድርን ማስተዳደር ይጀምራል። በቅርቡ አምላክ በምድር ላይ ያሉትን መንግሥታት አጥፍቶ በሰማይ ላይ ባቋቋመው የራሱ መንግሥት ይተካቸዋል። ይህ መንግሥት እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ያሰፍናል፤ ለሁሉም ሰው ፍትሕና ብልጽግና ያስገኛል።—ሚክያስ 4:3, 4
“እንደ ጭቆና፣ መድልዎ፣ ዘረኝነት እና በጥርጣሬ ዓይን መተያየት ያሉት ችግሮች ጊዜያዊ እንደሆኑ ማወቄ ያበረታታኛል፤ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ እነዚህን ችግሮች በሙሉ ያስወግዳል።”—ሙስጠፋ፣ መካከለኛው ምሥራቅ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ተስፋ ሰጪ መልእክት መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ ጥበብ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር ያጋጠመህን ሁኔታ ለመቋቋም ይረዳሃል። ንብረትህን በማጣትህ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሕይወትህ ከቀድሞው የተለየ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ከዚህ አዲስ ሁኔታ ጋር ተላምደህ ለመኖር እንድትችልም ይረዳሃል። ስደተኞችን ሊጠቅሙ የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እስቲ እንመልከት፦
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም።”—ሉቃስ 12:15
ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ያጋጠመህ ሁኔታ በጣም አስደንግጦህ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ በተጨማሪም ብዙ ነገሮችን በማጣትህ ሐዘን ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሕይወትህ ምን ያህል ውድ እንደሆነ ቆም ብለህ ማሰብህ ያጣሃቸውን ነገሮች በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል።
“ሕይወት ከቁሳዊ ንብረት የበለጠ ዋጋ አለው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ንብረትና ገንዘብ ጨርሶ ሊረዳን አይችልም።”—ናታሊያ፣ ዩክሬን
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “‘የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?’ አትበል።”—መክብብ 7:10
ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? አሁን ያለህበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የአሁኑን ሕይወትህን ከቀድሞው ጋር ከማወዳደር መቆጠብህ በምሬት እንዳትዋጥ ይረዳሃል።
“አሁን ያለሁበትን ሁኔታ አምኜ መቀበሌ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳኛል።”—ኢላይ፣ ሩዋንዳ
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:8
ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ለሕይወት የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ካሉህ በእነሱ ረክተህ ለመኖር ጥረት አድርግ። ባለህ ነገር ረክተህ የምትኖር ከሆነ የሚሰማህ ውጥረት ይቀንሳል፤ ይህም ለመረጋጋት ይረዳሃል።
“መጽሐፍ ቅዱስ አመለካከቴን እንዳስተካክልና ባጣኋቸው ነገሮች ላይ እንዳላተኩር ረድቶኛል። እኔና ባለቤቴ ደህንነታችን ተጠብቆ በሕይወት በመኖራችን ብቻ ደስተኞች ነን።”—ኢቫን፣ ዩክሬን
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12
ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ታጋሽና ደግ ለመሆን አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ካደረግክ ከሌሎች ጋር ተስማምተህ መኖር ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። በተጨማሪም እንዲህ ማድረግህ ተሰደህ በሄድክበት አካባቢ ያሉት ሰዎች በጭፍን እንዳይጠሉህና እንዲቀበሉህ ሊያደርግ ይችላል።
“አብዛኞቹ ሰዎች በአክብሮት፣ በደግነትና በፍቅር ስንይዛቸው ይደሰታሉ። እነዚህ ባሕርያት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንድንመሠርት ይረዱናል።”—አንጄሎ፣ ስሪ ላንካ
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ . . . የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? የሚሰማህን ስሜት እንዲሁም የሚያስፈልግህን፣ የሚያስፈራህንና የሚያስጨንቅህን ነገር አስመልክቶ ወደ አምላክ ጸልይ። እንዲህ ያለው ጸሎት፣ ባጋጠመህ ሁኔታ ምክንያት የሚሰማህ ጭንቀት እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።
“ችግር ባጋጠመኝ ቁጥር ወደ አምላክ እጸልያለሁ፤ እሱም ጸሎቴን ይመልስልኛል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር እውነተኛ የአእምሮ ሰላም ሰጥቶኛል።”—ዮል፣ ደቡብ ሱዳን
“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥሩ ምክር ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ውስጣዊ ሰላም አስገኝቶልኛል።”—ቫለንቲና፣ ዩክሬን
“ይሖዋ አምላክ ከአሁኑ እጅግ የተሻለ ሕይወት እንደሚሰጠን ቃል የገባልን መሆኑ በጣም ያበረታታኛል።”—ኢማኑኤል፣ ሄይቲ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው አጽናኝ እና ተስፋ ሰጪ መልእክት እንዲሁም በዚህ መልእክት ላይ እምነት መጣል ስለምትችልበት ምክንያት ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? አንድ የይሖዋ ምሥክር ያለምንም ክፍያ እንዲያነጋግርህ ጥያቄ ማቅረብ ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።
a በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ መሠረት “ስደተኞች” የሚለው መጠሪያ በአገራቸው ውስጥ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችንም ሆነ ከአገራቸው ውጭ የተሰደዱ ሰዎችን ያካትታል።
b የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ እርዳታ እና የአደጋ መቆጣጠር ኮሚሽነር።
c ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።