የሃይማኖቶች ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?
በሃይማኖቶች ተስፋ ቆርጠሃል? የሚያደርጉት ነገርስ አንገሽግሾሃል? ሃይማኖቶች በመጠኑም ቢሆን ለማኅበረሰቡ በጎ ነገር እንዳበረከቱ አይካድም፤ ለብዙ ችግሮች ግን መንስኤ ሆነዋል። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው “በታሪክ ውስጥ አስከፊ ለሚባሉ አንዳንድ ጦርነቶች መንስኤው የሃይማኖት አስተምህሮ ነው።” ብዙ ጊዜ እንደታየው የሃይማኖት መሪዎች ሃይማኖትን የፖለቲካ አጀንዳን ለማራመድ ይጠቀሙበታል። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ በሃይማኖታቸው ውስጥ የተፈጸመን ፆታዊ ጥቃት ወይም የማጭበርበር ወንጀል ለመሸፋፈን ይሞክራሉ።
አንተስ የሃይማኖት ጉዳይ ግራ አጋብቶሃል? አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ማወቅ ትፈልጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን በግልጽ ይናገራል። አምላክ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የሚያደርጉትን ነገር አጥብቆ እንደሚያወግዝ ይነግረናል። በሃይማኖቶች ላይ ምን እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጹ ትንቢቶችንም ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ በሆነ አገላለጽ እንደሚያስረዳው አምላክ በቅርቡ በዓለም ዙሪያ በሃይማኖቶች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖቶች ስለሚጠብቃቸው ነገር ምን ይላል?
ትንቢት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በራእይ መጽሐፍ ላይ አንዲት አመንዝራ ተጠቅሳለች፤ ይህች አመንዝራ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ስም ተሰጥቷታል። ይህች አመንዝራ፣ ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣለች። በኋላ ላይ ግን ይህ አውሬ በዚህች አመንዝራ ላይ ይነሳባታል እንዲሁም ይገድላታል።—ራእይ 17:3, 5, 16
ትርጓሜው፦ ታላቂቱ ባቢሎን የተባለችው አመንዝራ ሁሉንም የሐሰት ሃይማኖቶች ትወክላለች፤ እነዚህ ሃይማኖቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም።a ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው አውሬ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ያመለክታል።b አመንዝራዋ፣ ደማቅ ቀይ ቀለም ባለው አውሬ ላይ እንደተቀመጠች ሁሉ የሐሰት ሃይማኖቶችም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ጫና ለማድረግ ወይም ተጽዕኖ ለመፍጠር ይሞክራሉ። አውሬው አመንዝራዋን እንደገደላት ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ይህን ተቋም የሚደግፉት መንግሥታት በዓለም ዙሪያ ባሉ የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ይነሳሉ ከዚያም ያጠፏቸዋል። ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቀው ይህ ክስተት ታላቅ ጥፋት ያስከትላል።
የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋው እንዴት ነው?
ትንቢት፦ “ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና አውሬውም አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ . . . ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል። አምላክ . . . ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ አዎ፣ መንግሥታቸውን ለአውሬው በመስጠት አንድ የሆነውን የራሳቸውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ ይህን በልባቸው [ማለትም በዓለም መሪዎች ልብ ውስጥ] አኑሯልና። መቅሰፍቶቿ ይኸውም ሞትና ሐዘን እንዲሁም ረሃብ በአንድ ቀን የሚመጡባት ለዚህ ነው፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ትቃጠላለች፤ ምክንያቱም የፈረደባት ይሖዋc አምላክ ብርቱ ነው።”—ራእይ 17:16, 17፤ 18:8
ትርጓሜው፦ አምላክ በመንግሥታት ልብ ውስጥ “ሐሳቡን” ያኖራል። ይህ ሐሳብ “መንግሥታቸውን” ወይም ሥልጣናቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመስጠት ያነሳሳቸዋል። ከእነሱ ሥልጣን የተቀበለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ በዓለም ዙሪያ ባሉ የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ እርምጃ ይወስዳል። ይህ ጥፋት “በአንድ ቀን” የተከናወነ ያህል ፈጣንና ድንገተኛ በመሆኑ ለብዙዎች አስደንጋጭ ይሆናል።—ራእይ 18:21
የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋው ለምንድን ነው?
ትንቢት፦ “ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተቆልሏልና፤ አምላክም የፈጸመቻቸውን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች አስቧል።”—ራእይ 18:5
ትርጓሜው፦ የሐሰት ሃይማኖቶች ላለፉት በርካታ ዘመናት አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች ሲያደርጉ ቆይተዋል። ታላቂቱ ባቢሎን የአምላክ ፍርድ እንዲገባት ካደረጉት ‘ኃጢአቶቿ’ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት፦
ፖለቲካ ውስጥ ይገባሉ። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ ከዚህ ይልቅ ተስፋቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያደርጉ አስተምሯል፤ የአምላክ መንግሥት፣ ሰማይ ላይ ያለ መስተዳድር ሲሆን ሰዎች ያቋቋሟቸውን መንግሥታት አጥፍቶ በምትካቸው ይገዛል።d (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ዮሐንስ 6:15፤ 18:36) የሐሰት ሃይማኖቶች ያደረጉት ነገር ግን ኢየሱስ ካስተማረው ነገር ተቃራኒ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከታላቂቱ ባቢሎን ኃጢአቶች አንዱ ‘ዝሙት’ እንደሆነ ይጠቅሳል፤ እንዲያውም “ታላቂቱ አመንዝራ” ብሎ ይጠራታል። ይህ የሆነው ለአምላክ ታማኝ ከመሆን ይልቅ ፖለቲካ ውስጥ በመዘፈቋ ነው።—ራእይ 17:1, 2፤ ያዕቆብ 4:4
ለብዙዎች ደም ተጠያቂ ናቸው። የሐሰት ሃይማኖቶች ‘በምድር ላይ ለታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም’ ተጠያቂ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 18:24) ብዙ ሃይማኖቶች፣ አማኞቻቸው ሰላማዊ እንዲሆኑ ማስተማር አልቻሉም፤ እንዲያውም ጦርነቶችን እና የሽብር ጥቃቶችን ደግፈዋል አልፎ ተርፎም ቆስቁሰዋል።
ስግብግቦች ናቸው። ታላቂቱ ባቢሎን ‘ያላንዳች ኀፍረት የተቀማጠለ’ ሕይወት እንደምትኖር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 17:4፤ 18:7) ብዙዎቹ የሐሰት ሃይማኖቶች ሥልጣናቸውን እና ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ብዙ ሀብት አግበስብሰዋል። እንዲህ ያለው ስግብግብነት አምላክን ያሳዝነዋል።—ቲቶ 1:7
ውሸት ያስተምራሉ። የሐሰት ሃይማኖቶች፣ አማኞቻቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ ነገሮችን እንዲያምኑ ወይም እንዲያደርጉ ያስተምራሉ።e ሰዎችን የሚያሳስቱና አምላክን የሚያሰድቡ ብዙ አስተምህሮዎች እና ልማዶች የመነጩት ከሐሰት ሃይማኖት ነው፤ በዚህም ምክንያት ትንቢቱ፣ ታላቂቱ ባቢሎንን “የምድር አስጸያፊ ነገሮች እናት” ሲል ይጠራታል።—ራእይ 17:5፤ 18:23
ሁሉም ሃይማኖቶች ናቸው የሚጠፉት?
አይደለም። የራእይ መጽሐፍ፣ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጣ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንዳለ ይናገራል። (ራእይ 7:9) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት “ነጭ ልብስ” እንደለበሱ ተገልጿል፤ ይህም አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ እንደሚያመልኩት የሚያሳይ ነው። ትንቢቱ ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ ‘ከታላቁ መከራ’ እንደሚተርፍ ይናገራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው መሠረት ታላቁ መከራ፣ የሐሰት ሃይማኖትን ጨምሮ የአምላክ ጠላቶች በሙሉ የሚጠፉበት ወቅት ነው። (ራእይ 7:13, 14፤ 19:11, 19-21) ነጭ ልብስ የለበሱት የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፤ ይህ ሃይማኖት ፈጽሞ አይጠፋም።f
አምላክን በትክክለኛው መንገድ የሚያመልክ እጅግ ብዙ ሕዝብ በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ከሚመጣው ጥፋት ይተርፋል
የሐሰት ሃይማኖት እንደሚጠፋ ማወቅህ ምን ለውጥ ያመጣል?
አምላክ፣ ሃይማኖቶች የሚፈጽሟቸውን ዘግናኝ ተግባራት እንደማይደግፍ ስታውቅ አልተጽናናህም? መጪውን ጊዜ በተስፋ እንድትጠብቅ የሚያደርግ ምክንያትም አለህ፤ አምላክን የሚያሰድቡ እና ለሰው ልጆች መከራ መንስኤ የሆኑ ሃይማኖቶች በሙሉ ከምድር ገጽ እንደሚወገዱ አውቀሃል።
አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ የሚያመልክ ሃይማኖት እንዳለም አውቀሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው።” (ዮሐንስ 4:23) አምላክ ለእነዚህ ሰዎች አንድ ጥሪ አቅርቧል፤ “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ [ማለትም ከታላቂቱ ባቢሎን] ውጡ” ብሏል። (ራእይ 18:4, 5) አዎ፣ አምላክ ሰዎች በእውነት እንዲያመልኩት ጥሪ እያቀረበ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ጥሪውን የሚቀበሉ ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል።—1 ዮሐንስ 2:17
a የታላቂቱ ባቢሎንን ማንነት ለማወቅ የሚያግዙ አራት ፍንጮችን “ታላቂቱ ባቢሎን ማን ናት?” በሚለው ርዕስ ላይ ተመልከት።
b የዚህን አውሬ ማንነት ለማወቅ የሚያግዙ ስድስት ፍንጮችን “በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰው ደማቅ ቀይ አውሬ ምን ያመለክታል?” በሚለው ርዕስ ላይ ተመልከት።
c ይሖዋ የአምላክ ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
e ለአብነት ያህል “‘ክርስቲያን ነን’ ከሚሉት ሃይማኖቶች መካከል ታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ የሚካተት አለ?” በሚለው ሣጥን ውስጥ የተቀመጡትን ነጥቦች ተመልከት።
f መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት እውነተኛው ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ ማወቅ ከፈለግክ “እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።