የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ እንዲያሠለጥነኝ ፈቅጃለሁ
በብሩክሊን ቤቴል በሚገኘው የመጻሕፍት መጠረዣ ክፍል ውስጥ መሥራት የጀመርኩበትን ቀን መቼም ቢሆን አልረሳውም። ወደ መጠረዣ ክፍሉ እንደገባሁ ያለማቋረጥ የሚሠሩትን ማሽኖች ሳይ እንዲሁም የሚያሰሙትን ጩኸት ስሰማ በድንጋጤ ፈዝዤ ቀረሁ። የወረቀት ብናኝና የዘይት ሽታ አየሩን ሞልቶታል።
ከሁሉ በላይ ትኩረቴን የሳበው ግን የሰዎቹ ሁኔታ ነው። በዚያ ያሉት ወጣት ወንድሞችና እህቶች የሚሠሩት ሥራ አሰልቺ ይመስላል፤ ዓይን ውስጥ የሚገባም አይደለም። ያም ቢሆን በደስታና በእርካታ ሥራቸውን ያከናውናሉ። የእነሱ ምሳሌ ይሖዋን በትሕትና ማገልገል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስተምሮኛል።
ይሖዋ ባለፉት ዓመታት እሱን በተሻለ ሁኔታ ማገልገል እንድችል እንዳሠለጠነኝ ይሰማኛል። በመጀመሪያ ግን፣ ቡዲስት በነበርኩበት ወቅት እውነትን ለማግኘት ስላደረግኩት ጥረት ላጫውታችሁ።
በልጅነቴ አምላክን ለማግኘት ያደረግኩት ፍለጋ
የተወለድኩት በቺካጎ፣ ኢሊኖይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን ከአራት ልጆች መካከል የመጀመሪያ ነኝ። ወላጆቼ ከጃፓን ወደ ቺካጎ የመጡት የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ነው። ልጆቻቸው ምርጥ የሚባለውን ትምህርት እንዲያገኙና ስኬታማ እንዲሆኑ ይፈልጉ ነበር።
ወላጆቼ አጥባቂ ቡዲስቶች ነበሩ። እናቴ ያደገችው የቡዲስት ቤተ መቅደስ ያለበት ቤት ውስጥ ነው። አባቷና ሁለት ወንድሞቿ የቡዲስት መነኩሴዎች ነበሩ። በመሆኑም የቡዲዝም እምነት በልጅነት ሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከትምህርት ቤት ስመጣ የማደርገው የመጀመሪያ ነገር ቤታችን ላለው የቡዲስት ጣዖት ሰንደል ማጨስ እንዲሁም ሩዝና ውኃ ማቅረብ ነው። እሁድ እሁድ ወደ ቡዲስት ቤተ መቅደስ ሄደን በተመሳሳይ ጣዖት ፊት እናነበንባለን። ይሄኛውን ጣዖት በቤታችን ካለው ጣዖት የሚለየው ነገር ቢኖር ትልቅና በወርቅ የተለበጠ መሆኑ ነው።
ትዝ ይለኛል፣ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤታችን ውስጥ ያለውን ጣዖት እያየሁ ‘ከሞትኩ በኋላ ምን ያጋጥመኝ ይሆን?’ ብዬ አስብ ነበር። ከሞትኩ በኋላ መንፈስ እንደምሆን ከቡዲዝም እምነት ተምሬያለሁ። ይህን ሳስብ ‘ለካስ ሕይወቴ ማብቂያ አለው’ የሚለውን ጉዳይ ተገነዘብኩ። መንፈስ ሆኜ መኖሬን ብቀጥልም እንኳ እንደ ሰው ሕይወትን ማጣጣም አልችልም። በጣም አዘንኩ! ድንገት የተስፋ ቢስነት ስሜት ተሰማኝ።
አሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ስደርስ የቡዲስት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ትርጉም አጡብኝ። በሕይወቴ ውስጥ የሆነ የጎደለኝ ነገር እንዳለ ይሰማኝ ጀመር። (ማቴ. 5:3) ሁሉን ቻይና ሕያው የሆነ አምላክ መኖር እንዳለበት ውስጤ ይነግረኝ ነበር። ይህን አምላክ ለማወቅ ተነሳሳሁ። ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቼ መልስ ይሰጠኝ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ያገለገለ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ገዛሁ። የሚገርመው ይህን መጽሐፍ ቅዱስ የገዛሁት በቡዲስት ክብረ በዓል ላይ ነው!
እውነትን ካስተማረኝ ከዊልሰን ባሹ ጋር
አንድ ቀን በ17 ዓመቴ ውሻዬን እያንሸራሸርኩ ሳለ ዊልሰን ባሹ የተባለ ወንድም መንገድ ላይ አነጋገረኝ። “አምላክ ለወደፊቱ ጊዜ ምን ቃል እንደገባልን ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። ከዚያም ጥልቀት ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት አደረግን። ዊልሰን ራእይ 17:1ን አነበበልኝና “አመንዝራዋ የተቀመጠችባቸው ብዙ ውኃዎች ምን ያመለክታሉ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም መልሱን እንደማላውቅ ነገርኩት። ከዚያም ቁጥር 15ን አሳየኝና ውኃዎቹ ሕዝቦችን እንደሚያመለክቱ ነገረኝ። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለመፍታት ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚጠቀሙ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። ከመለያየታችን በፊት ዊልሰን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የሚለውን መጽሐፍ ሰጠኝ። ያቺ ሰማያዊ መጽሐፍ ሕይወቴን ቀየረችው።
ከአሥር ቀን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። የተደረገልኝን አቀባበል ፈጽሞ አልረሳውም። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በስብሰባዎች ላይ መገኘቴን ቀጠልኩ። በኋላም ዊልሰን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ ጀመር። የምማረውን ነገር በጣም ስለወደድኩት አንዳንድ ጊዜ ለስምንት ሰዓት ያህል እናጠና ነበር። ወላጆቼ መጽሐፍ ቅዱስን እንደማጠና ሲያውቁ በጣም ደነገጡ። በመሆኑም አምርረው ይቃወሙኝ ጀመር። ሆኖም ማጥናቴን ስቀጥል እውነትን እንዳገኘሁ ይበልጥ እርግጠኛ ሆንኩ። በ1983 ተጠመቅኩ።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አቋርጬ አቅኚ ሆንኩ
በተጠመቅኩበት ወቅት ስመ ጥር በሆነ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሕክምና ትምህርት እየተከታተልኩ ነበር። ወላጆቼ ይህን ትምህርት እንድማር ሲሉ ብዙ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን መቀጠል እችል ነበር። ግን ለይሖዋ ምርጤን መስጠትና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ፈለግኩ።
አባቴ “የዩኒቨርሲቲ ትምህርትህን ካቋረጥክ ከቤት አባርርሃለሁ!” ብሎ አስጠነቀቀኝ። በጣም አዝኜና ግራ ተጋብቼ ነበር። ወላጆቼን እወዳቸዋለሁ፤ ላስከፋቸውም አልፈልግም። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ሌሊት ላይ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ እየተመለከትኩ “ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ጥሩ ውሳኔ እንዳደርግ እርዳኝ” በማለት አጥብቄ እጸልይ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ለማቋረጥ ስወስን አባቴ ከቤት አባረረኝ። ዊልሰን ጋ ደውዬ ምን እንዳጋጠመኝ ነገርኩት። እሱም አብሬው እንድኖር ግብዣ አቀረበልኝ። ዕቃዎቼን ሁሉ በአንድ ሻንጣ ውስጥ አድርጌ ወደ ዊልሰን ቤት የሚሄድ አውቶቡስ ተሳፈርኩ። በዚያ ሰዓት ለመግለጽ የሚያዳግት የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ። ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደረግኩ እርግጠኛ ሆንኩ።
ከተያዘችበት እንደተለቀቀች ወፍ እንደሆንኩ ተሰማኝ! አሁን በነፃነት የፈለግኩትን ያህል ማገልገል እችላለሁ። በ1984 አቅኚነት ጀመርኩ።
የዘወትር አቅኚ ሳለሁ ይሖዋ እንደ ጽናት ያሉ ጠቃሚ ባሕርያትን እንዳዳብር ረድቶኛል። ለምሳሌ አንድ ቀን አገልግሎት እንዳልወጣ እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አጋጠሙኝ። ከሰዓት በኋላ አብሮኝ የሚያገለግል ሰው ባለማግኘቴ ከፍቶኝ ነበር። እንደዚያም ሆኖ አገልግሎት ወጣሁ። ሁለት ሰዓት ያህል ካገለገልኩ በኋላ የመጨረሻውን ቤት ለማንኳኳት ወሰንኩ። ድካምና ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር። ደግሞም ዝናብ የሚዘንብ ይመስላል። ስለዚህ ‘ቢቀርብኝ ይሻል ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ወደ ሦስተኛ ፎቅ በደረጃ ስወጣ አንድ ወጣት የፊሊፒንስ ተወላጅ አገኘሁ። ‘መቼም ፍላጎት አይኖረውም’ ብዬ አስቤ ነበር። ግን ለካ ተሳስቻለሁ! ሰውየው ጥናት ጀመረ፤ በኋላም ወንድማችን ሆነ።
በብሩክሊን ቤቴል ያገኘሁት ሥልጠና
ከዊልሰን ጋር ሁለት ዓመት ከኖርኩ በኋላ በ1985 በብሩክሊን ቤቴል እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት የተመደብኩት በመጻሕፍት መጠረዣ ክፍል ውስጥ እንድሠራ ነው። አንድ ቀን በመጻሕፍቱ ሽፋን ላይ ርዕሱን በሚያትመው ማሽን ላይ እየሠራሁ ሳለ አንድ ስህተት በመሥራቴ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጻሕፍት ሽፋኖች ተበላሹ። በመጻሕፍት መጠረዣ ቢሮ የሚያገለግሉት ወንድሞች ጉዳዩን ሪፖርት ማድረግ እንዳለብኝ ነገሩኝ። ለተፈጠረው ስህተት ብዙ ምክንያት ደረደርኩ፤ ሆኖም አንድ የጎደለኝ ነገር ነበር። የበላይ ተመልካቹ ደግነት በሚንጸባረቅበት የድምፅ ቃና “ሁልጊዜም ቢሆን ይቅርታ መጠየቅ የተሻለ ነው” አለኝ። በዚያ ሰዓት፣ ስህተቴን አምኜ መቀበልና ይቅርታ መጠየቅ ያለውን አስፈላጊነት ተማርኩ።
በብሩክሊን ቤቴል የመጻሕፍት መጠረዣ ክፍሉን ሳስጎበኝ
ቤቴል ውስጥ በታማኝነት የሚያገለግሉ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችን ምሳሌ መመልከቴ ሌሎችን ስለማገልገል ያለኝን አመለካከት አስተካክሎልኛል። ለምሳሌ አንድ ቀን ምሳ ሰዓት ላይ የበላይ አካል አባል ከሆነው ከወንድም ሚልተን ሄንሸል ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ነበር። በዚያ ዕለት በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ በጣም ብዙ ሰው ስለነበር አስተናጋጆቹ ምግብ ለማቅረብ እየተሯሯጡ ነበር። በጠረጴዛው ዙሪያ የነበርነው ወጣት ወንድሞች ምግብ ቶሎ ስላልቀረበልን ማጉረምረም ጀመርን። ወንድም ሄንሸል ግን አንድም ቃል ሳይተነፍስ ከተቀመጠበት ተነሳ። ከዚያም ከአስተናጋጆቹ ጋር አብሮ የውኃ ጆግ እንዲሁም ዳቦና የገበታ ቅቤ የያዙ ሳህኖችን ማቀራረብ ጀመረ። ወንድም ሄንሸል ያደረገውን ትሕትና የሚንጸባረቅበት ድርጊት ፈጽሞ አልረሳውም። ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንዳገለገለ የሚገልጸውን ታሪክ አስታውሶኛል።—ዮሐ. 13:3-5
“ጃፓንኛ መማር አለብህ!”
ከሚቺኮ ኦዳ እና ከባለቤቷ ጋር
በ1987 ለጉብኝት ጃፓን ሄጄ ነበር። በጃፓን የሚኖሩት አስፋፊዎች ያላቸውን ቅንዓትና ትሕትና ሳይ በጣም ተገረምኩ። ልረዳቸው ፈልጌ ነበር። ችግሩ ግን ጃፓንኛ አልተማርኩም። በቤቴል የምታገለግል ሚቺኮ ኦዳ የተባለች አንዲት እህት ትኩር ብላ እያየችኝ “ጃፓንኛ መማር አለብህ!” አለችኝ። እኔም መማር ጀመርኩ። እነዚህ ቃላት ምን ያህል ሕይወቴን እንደሚቀይሩት አላወቅኩም ነበር።
ከተወሰኑ ወራት በኋላ በኒው ዮርክ ወደሚገኝ ጃፓንኛ ጉባኤ ተዛወርኩ። ጃፓንኛ መማሬ ይሖዋ አምላክን ማገልገል የምችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ከፍቶልኛል። በ1989 በጃፓንኛ በሚካሄድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘሁ። ስብሰባው የተካሄደው በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ነው። በድራማው ላይ ተዋናይ የነበረች ሚዋኮ ኦናሚ የተባለች አንዲት አቅኚ እህት ቀልቤን ሳበችው።
እኔና ሚዋኮ በ1992 ተጋባን። ከዚያም በብሩክሊን ቤቴል አብረን የማገልገል መብት አገኘን። ሚዋኮ በጣም አሳቢ ሰው ነች፤ ሌሎችን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነች። የእሷ ምሳሌ ሌሎችን የምይዝበትን መንገድ እንዳሻሽል ረድቶኛል። ከይሖዋ ያገኘኋት ስጦታ እንደሆነች ይሰማኛል። ሁልጊዜም የደስታና የመጽናኛ ምንጭ ሆናልኛለች።
በሠርጋችን ቀን
በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮና በመስክ ላይ ማገልገል
በጃፓን የሚኖሩት ሁለቱም የሚዋኮ ወላጆች ከጊዜ በኋላ በጠና ታመሙ። ስለዚህ ቅርባቸው ሆነን እነሱን መንከባከብ እንድንችል ወደ ጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ እንድንዛወር ተፈቀደልን። በ1999 ወደዚያ ሄድን።
በጃፓን ያለው የቤቴል ቤተሰብ ወዲያውኑ ጥሩ አቀባበል አደረገልን፤ አዲሱን መኖሪያችንን ቶሎ ለመድነው። በጃፓን ያሉትን ወንድሞችና እህቶች መልካም ምሳሌ መከተሌ ተጨማሪ ሥልጠና ሰጥቶኛል። ለምሳሌ አስደናቂ ልግስናና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያሳያሉ። የሥራ ሰዎች ናቸው። በተጨማሪም ተባብረው በቡድን መሥራት ይችሉበታል። የጃፓን ባሕል ለግል ስኬት ከመሥራት ይልቅ ለጋራ ጥቅም ሲባል ተባብሮ በአንድነት መሥራትን ያበረታታል። መልካም ምሳሌነታቸው በትሕትና ከሌሎች ጋር ተባብሬ እንድሠራ እንዲሁም የእኔ አነስተኛ አስተዋጽኦ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ የሚያበረክተውን ድርሻ እንድገነዘብ ረድቶኛል።
ያም ቢሆን፣ በባሕል ልዩነት ምክንያት አንዳንድ ነገሮች የተያዙበትን መንገድ መረዳት ከብዶኝ ያውቃል። ታጋሽ መሆን እንዳለብኝና ስሜታዊ መሆን እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ። ውሎ አድሮ አመለካከቴን አስተካከልኩ። ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ እስከታዘዝን ድረስ እሱ የትኛውንም ውሳኔ ሊባርክ እንደሚችል ተገነዘብኩ። ዞሮ ዞሮ ሁሉንም ነገር የሚያሳካው ይሖዋ ነው።
በቤቴል ያገኘሁት ሥልጠና ሙሴ ካገኘው ሥልጠና ጋር እንደሚመሳሰል ይሰማኛል። ሙሴ እረኛ ሆኖ ባሳለፋቸው 40 ዓመታት ይሖዋ የዋህነትን እንዲያዳብር ረድቶታል። እንደ ሙሴ ሁሉ እኔም ከፍተኛ ትምህርት ተከታትያለሁ። ይህ ትምህርት ኩራተኛና በራሴ የምታመን ሰው እንድሆን አድርጎኛል። ቤቴል ግን ትሑት እንድሆንና በይሖዋ እንድታመን አሠልጥኖኛል። ይሖዋ ሙሴን በትዕግሥት እንዳሠለጠነው ሁሉ እኔንም ለበርካታ ዓመታት አሠልጥኖኛል።
በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ስሠራ
የሚዋኮ ወላጆች እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ለ24 ዓመታት ገደማ ተንከባክበናቸዋል። ብዙ የስልክ ጥሪዎችን ማድረግና ሆስፒታል መመላለስ አስፈልጎናል። በጭንቀት የተዋጥንባቸው ጊዜያትም ነበሩ። የሚዋኮ እናት ማሳኮ ጤንነቷ በጣም አሽቆልቁሎ በራሷ መራመድ የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል ለእሷ ቀላል አልነበረም። ከመሞቷ በፊት በነበሩት የመጨረሻ ሳምንታት ዊልቼር ለመጠቀም ተገዳለች። በዚህ ሁሉ ግን ለይሖዋ ያላት ፍቅር ቀዝቅዞ አያውቅም። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ስታወራ ፊቷ በደስታ ያበራ ነበር። ማሳኮ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሖዋን በማገልገልና ደስታዋን ጠብቃ በመኖር ረገድ የተወችው ምሳሌ በጣም አበረታቶኛል።
ከሚዋኮ ጋር በኦኪናዋ ስናገለግል
በ2024 ትልቅ ለውጥ አጋጠመን። ከ30 ዓመት በላይ በቤቴል ካገለገልን በኋላ በመስኩ ላይ እንድናገለግል ተመደብን። በአሁኑ ወቅት በኦኪናዋ ደሴት ልዩ አቅኚዎች ሆነን እያገለገልን ነው። በአካባቢያችን በሚገኘው የወታደሮች ካምፕ ውስጥ ለሚኖሩ ቤተሰቦች የመመሥከር መብት አግኝተናል። በቤቴል ያገኘነው ጥሩ ሥልጠና አዲሱን ምድባችንን ቶሎ ለመልመድ ረድቶናል። በፕሮግራም ለመመራት ጥረት እናደርጋለን፤ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ በማተኮር ጊዜያችንን ጥሩ አድርገን ለመጠቀም እንሞክራለን። ይሖዋ እንደ ቤተሰብ የምንቀርባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመስጠት ባርኮናል። ሰዎችን መውደድ ያለውን አስፈላጊነት በደንብ እየተማርን ነው። እኔና ሚዋኮ ይህን አስደሳች ምድብ ስለሰጠን ይሖዋን በየቀኑ እናመሰግነዋለን።
በይሖዋ መሠልጠኔን ለመቀጠል ቆርጫለሁ
ቤተሰቦቼ መቃወማቸውን ቢያቆሙም እስካሁን አብረውኝ ይሖዋን ማገልገል አልጀመሩም። ያም ሆኖ፣ ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ሲሉ ቤተሰቦቻቸውን የሚተዉ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ መቶ እጥፍ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ማር. 10:29, 30) የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። ባለፉት አሥርተ ዓመታት እንደ ቤተሰባቸው ቆጥረው ፍቅር ያሳዩኝንና የተንከባከቡኝን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ቤተሰቦች ቆጥሬ መጨረስ አልችልም።
ዊልሰን ያበረከተልኝን ያቺን እውነት መጽሐፍ እስካሁን አስቀምጫታለሁ። ያቺ ሰማያዊ መጽሐፍ ይሖዋ በደግነት እንደተገኘልኝ ሁሌም ታስታውሰኛለች። (1 ዜና 28:9) በይሖዋ መሠልጠኔን ለመቀጠልና ሌሎችም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውነት እንዲያገኙ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።