የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ሐምሌ ገጽ 20-25
  • ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ እርዷቸው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ እርዷቸው
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥናቶቻችሁ ይሖዋን በሚገባ እንዲያውቁ እርዷቸው
  • ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ አስተምሯቸው
  • እውቀታቸውን እንዲጠቀሙበት እርዷቸው
  • ይሖዋን በደንብ የሚያውቁ ሰዎች በረከት ያገኛሉ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ እርምጃ እንዲወስዱ እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት—ክፍል ሁለት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት—ክፍል አንድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ሐምሌ ገጽ 20-25

ከመስከረም 28–ጥቅምት 4, 2026

መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው

ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ እርዷቸው

“ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተን . . . ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ዮሐ. 17:3

ዓላማ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ይህም ባሕርያቱን እንዲሁም እሱን የሚያስደስተውንና የሚያሳዝነውን ነገር እንዲያውቁ መርዳትን ያካትታል።

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ እድገት ሲያደርጉ ስትመለከቱ ምን ይሰማችኋል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሲገኝ፣ በስብሰባ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ፣ ለሌሎች መስበክ ሲጀምር፣ ውሎ አድሮ ደግሞ ራሱን ለይሖዋ ሲወስን ምን ይሰማችኋል? በጣም እንደምትደሰቱ ምንም ጥያቄ የለውም። እርግጥ ነው፣ ግለሰቡ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የረዳው ይሖዋ ስለሆነ ሊመሰገን የሚገባው እሱ ነው።—1 ቆሮ. 3:5-9፤ 3 ዮሐ. 3, 4

2. ይሖዋ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ያለው ፈቃድ ምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4)

2 የአምላክ “ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4ን አንብብ።) ይሖዋ ሰዎች እሱንም ሆነ ዓላማዎቹን በሚገባ እንዲያውቁ ይፈልጋል። (ኤር. 9:24) ለዚህ ሲባል ደግሞ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አለባቸው። ትክክለኛ እውቀት ሲባል ምን ማለት ነው? ስለ አምላክ መረጃ የመሰብሰብ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት ይህ ሐረግ “አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ እንዲያደርግ የሚያነሳሳውን እውቀት” ያመለክታል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይሖዋን ሲያውቅ እውቀቱ ሕይወቱን ይቀይረዋል። በተጨማሪም “የዘላለም ሕይወት” የማግኘት አጋጣሚ ይከፍትለታል።—ዮሐ. 17:3

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ይሖዋ ሌሎች እሱን እንዲያውቁ የመርዳት መብት ሰጥቶናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይሖዋን በሚገባ ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ልናስተምራቸው የምንችለው እንዴት ነው? በተጨማሪም ጥናቶቻችን ስለ ይሖዋ ያገኙትን እውቀት እንዲጠቀሙበት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

ጥናቶቻችሁ ይሖዋን በሚገባ እንዲያውቁ እርዷቸው

4. በማርቆስ 12:30 መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ወቅት ዋነኛ ዓላማችን ምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ከሁሉ የላቀው ትእዛዝ ይሖዋን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ ነፍስ፣ በሙሉ አእምሮና በሙሉ ኃይል መውደድ እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:30ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይሖዋን እንዲወደው በመጀመሪያ ሊያውቀው ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ራሱን እንዲወስን የምንፈልገው ለእኛ፣ ለተማረው ትምህርት ወይም ለአንድ ድርጅት ሳይሆን ለይሖዋ ነው። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ወቅት ዋነኛ ዓላማችን ጥናታችን ይሖዋን እንዲያውቀውና እንዲወደው መርዳት ነው።

5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ለይሖዋ ያለው ፍቅር ምን እንዲያደርግ ያነሳሳዋል?

5 ፍቅርና ታዛዥነት የተያያዙ ነገሮች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ይሖዋን ሲያውቀውና ሲወደው እሱን ለመታዘዝ ይነሳሳል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው።” (ዮሐ. 14:31) በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ይሖዋን እንዲታዘዘውና ለእሱ ታማኝ እንዲሆን የሚያነሳሳው ዋነኛው ነገር ለይሖዋ ያለው ፍቅር ነው።—1 ዮሐ. 5:3

6. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ይሖዋን ማወቃቸው ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

6 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይሖዋን ይበልጥ እያወቁ ሲሄዱ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ እየቀለላቸው ይመጣል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው የአውቶቡስ ሹፌር ለመሆን የትራፊክ ሕጎችን ማጥናቱ ወይም የጽሑፍ ፈተና ማለፉ ብቻውን በቂ አይደለም። ለረጅም ጊዜ አውቶቡስ እየነዳ መለማመድ አለበት። በጊዜ ሂደት ደግሞ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ጥሩ አድርጎ ማሽከርከር የሚችለው እንዴት እንደሆነ ይማራል። በተመሳሳይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይሖዋን የሚያውቀው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ብቻ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል የሚያስገኝለትን ጥቅም ሲያይ ይሖዋን እያወቀው ይሄዳል። ስለ ይሖዋ ያለው እውቀት ሲጨምር እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ የይሖዋን እርዳታ ሲያይ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ይማራል።

7. ዮሴፍ ይሖዋን ማወቁ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርግ የረዳው እንዴት ነው?

7 ዮሴፍ ይሖዋን ማወቁ የጶጢፋር ሚስት ልታማልለው በሞከረችበት ወቅት ጠቅሞታል። ዮሴፍ ከልጅነቱ አንስቶ የአዳምንና የሔዋንን እንዲሁም የአብርሃምንና የሣራን ታሪክ እንደሰማ ምንም ጥያቄ የለውም። (ዘፍ. 2:24፤ 20:3, 6) ዮሴፍ ይሖዋ ስለ ትዳርና ስለ ፆታ ግንኙነት ያለውን አመለካከት ከእነዚህ ታሪኮች መማር ይችላል። ዮሴፍ ይሖዋን በደንብ ስላወቀው ለጶጢፋር ሚስት “እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥቷታል። (ዘፍ. 39:7-9) ዮሴፍ በይሖዋ ዓይን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ያውቅ ነበር። አምላኩን የሚያሳዝኑት የትኞቹ ድርጊቶች እንደሆኑ ተገንዝቧል። በዚህም ምክንያት ጥሩ ውሳኔ ሊያደርግ ችሏል። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ በደንብ እንዲያውቁ ከረዳናቸው እሱን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ይችላሉ።

ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ አስተምሯቸው

8. ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን ጥናቶቻችን ይሖዋን ይበልጥ እንዲያውቁት መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ታዲያ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ ኢዮብን ስለ እሱ ይበልጥ እንዲያውቅ የረዳው ጥያቄዎችን በመጠቀም ነው፤ ከ50 የሚበልጡ ጥያቄዎችን ጠይቆታል! (ኢዮብ 38:1–41:34) እኛም ጥያቄዎችን መጠቀም እንችላለን። ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ጥያቄዎች የተዘጋጁት ጥናቶቻችን ደረጃ በደረጃ ስለ ይሖዋ ባሕርያት እንዲማሩ ለመርዳት ታስበው ነው። (“ለማስተማር የሚረዱን ጥያቄዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎች ጥናቶቻችሁ ይሖዋን ይበልጥ እንዲያውቁ ለመርዳት ተጠቀሙባቸው።

አንዲት እህት ጥናቷ “ለዘላለም በደስታ ኑር!” በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ የሚገኝን ጥያቄ ስትመልስ ስታዳምጣት።

ለማስተማር የሚረዱን ጥያቄዎች

ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ጥናቶች ደረጃ በደረጃ ስለ ይሖዋ እንዲማሩ የሚረዱ ብዙ ጥያቄዎችን ይዟል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  • “ይሖዋ ምሥራቹን ለሚሰብኩ ሰዎች ምን አመለካከት አለው?” (ምዕራፍ 21)

  • “ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ የተማርከው ነገር እነሱ [በአርማጌዶን ወቅት] የሚወስዱት እርምጃ ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደሆነ እንድትተማመን የሚያደርግህ እንዴት ነው?” (ምዕራፍ 33)

  • “ይሖዋ ጥበበኛ ስትሆንና እሱን ስትታዘዘው ምን ይሰማዋል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?” (ምዕራፍ 34)

  • “ይሖዋ እሱን የማይወድ ሰው ብናገባ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?” (ምዕራፍ 42)

  • “ይሖዋ ምን ያህል ይቅር ባይ ነው?” (ምዕራፍ 56)

  • “ይሖዋ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችን የሚይዝበት መንገድ ፍትሐዊ፣ መሐሪና አፍቃሪ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?” (ምዕራፍ 57)

9-10. (ሀ) ጥናቶቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው የተሟላ ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? (ያዕቆብ 5:11) (ለ) ከአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ይሖዋን ስለሚያስደስተውና ስለሚያሳዝነው ነገር መማር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

9 ከሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመርን አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲጀምሩ እናበረታታቸዋለን።a ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ባነበቡ ቁጥር ይሖዋ ይህ ዘገባ በቃሉ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ከዚያ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ትምህርት እንደሚያገኙ እንዲያስቡ ልናበረታታቸው እንችላለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ምን እንዳደረገ እንመልከት። ስለ ኢዮብ ታሪክ በጠቀሰበት ወቅት የኢዮብን ጽናት ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ባሕርያት ማለትም እጅግ አፍቃሪና መሐሪ መሆኑንም ገልጿል።—ያዕቆብ 5:11ን አንብብ።

10 ጥናቶቻችን ከእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋን ስለሚያስደስተውና ስለሚያሳዝነው ነገር እንዲማሩ እንፈልጋለን። ለምሳሌ ጥናታችን ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀምር” የሚለውን ሰንጠረዥ ከተመለከተ በኋላ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደተጣለ የሚገልጸውን ዘገባ ለማንበብ ወሰነ እንበል። እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ እንዲያሰላስል ልናበረታታው እንችላለን፦ ‘ይሖዋ ዳንኤልን ያዳነው ለምንድን ነው? ይህስ ይሖዋን ስለሚያስደስተው ነገር ምን ያስተምረኛል?’ (ዳን. 6:10, 22) በተጨማሪም እንዲህ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይችላል፦ ‘ዳንኤልን የከሰሱት ሰዎች ምን ደረሰባቸው? ይህስ ይሖዋን ስለሚያሳዝነው ነገር ምን ያስተምረኛል?’ (ዳን. 6:4, 5, 24) በመጨረሻም ‘ከዚህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ሌላ ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?’ ብሎ እንዲያስብ ልናበረታታው እንችላለን።—ዳን. 6:26, 27

11. ጥናታችን የሚማረው ነገር ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ እንዲገነዘብ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

11 ጥናታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማረው ነገር እየጠቀመው እንዳለ ሲሰማው ደስ ይለናል። ይሁንና የእነዚህ ጠቃሚ ትምህርቶች ምንጭ ታላቅ አስተማሪ የሆነው ይሖዋ እንደሆነ እንዲገነዘብ ልንረዳው ይገባል። (ኢሳ. 30:20, 21) ጥናታችን ለምናስተምረው ነገር ያመሰግነን እንዲሁም በማስተማር ችሎታችን ያደንቀን ይሆናል። ጥናታችን ልባዊ ምስጋናውን መግለጹ ስህተት ባይሆንም ለእነዚህ ነገሮች ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ ልንጠቁመው ይገባል።

እውቀታቸውን እንዲጠቀሙበት እርዷቸው

12-13. ጥናቶቻችን ይሖዋን ማወቃቸው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መረዳት ሲከብዳቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ከቀሰምነው ትክክለኛ እውቀት የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን እውቀታችንን ልንጠቀምበት ይገባል። ታዲያ ጥናቶቻችን እውቀታቸውን እንዲጠቀሙበት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛ፣ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መረዳት ከከበዳቸው እስካሁን ስለ ይሖዋ የተማሩትን ነገር እንዲያስታውሱ ልናበረታታቸው እንችላለን። ለምሳሌ ይሖዋ ስለወሰዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ሲያነቡ ይሖዋ አንዳንድ ሰዎችን ያጠፋው አንዳንዶችን ደግሞ ያላጠፋው ለምን እንደሆነ ግራ ሊገባቸው ይችላል። ታዲያ ጥናቶቻችን በጉዳዩ ላይ እንዲያመዛዝኑ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

13 ጥናቶቻችን ስለ ይሖዋ በሚያውቁት ነገር ላይ እንዲያሰላስሉ ልናበረታታቸው እንችላለን። በይሖዋ ዓይን ሕይወት ምን ያህል ውድ ነው? (2 ጴጥ. 3:9) ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ እኛን ለማዳን ሲል ምን ያህል ርቀት ሄዷል? (ኤፌ. 2:4, 5) ይሖዋ ቅጣት የማይገባቸውን ሰዎች ይቀጣል? ወይም ደግሞ ቅጣት የሚገባቸውን ሰዎች ሳይቀጣ ያልፋል? (ዘፀ. 34:6, 7) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ አንድን ነገር ያደረገበት ምክንያት በዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ በቀጥታ አይጠቀስ ይሆናል። ሆኖም ይህ መረጃ አያስፈልገንም። ምክንያቱም አምላካችንን እናውቀዋለን፤ እንዲሁም አምላካችን ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ እንተማመናለን።

ሥዕሎች፦ ያቺው እህት ጥናቷ እስካሁን የተማረችውን ነገር እንድትከልስ ስትረዳት። 1. ይሖዋ በሰማይ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ። 2. ሔዋን ለአዳም የተከለከለውን ፍሬ ከሰጠችው በኋላ አዳም ፍሬውን ስለመብላት ሲያስብ። 3. አንድ ተረከዝ የአንድን እባብ ራስ ሲጨፈልቅ። 4. በጥፋት ውኃው ወቅት የኖኅ መርከብ ውኃ ላይ ሲንሳፈፍ። 5. ሙሴ ቀይ ባሕርን ሲከፍል። 6. የኢያሪኮ ቅጥር ሲፈራርስ የረዓብ ቤት ብቻውን ቆሞ። 7. ኤቤድሜሌክ ኤርምያስን ከጉድጓድ ሲያወጣው። 8. ኢየሱስ እንጨት ላይ ተሰቅሎ።

ጥናታችሁ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መረዳት ከከበደው ስለ ይሖዋ የሚያውቀውን ነገር እንዲያስታውስ አበረታቱት (አንቀጽ 12-13ን ተመልከት)


14. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከአንድ ወንድም ጋር መስማማት ከከበደው ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው?

14 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስለ ይሖዋ ያገኘውን እውቀት መጠቀም የሚችልበትን ሁለተኛ መንገድ እንመልከት። ጥናታችሁ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምሯል እንበል። ሆኖም በጉባኤ ውስጥ ካለ አንድ ወንድም ጋር መስማማት ከብዶታል። ምናልባት ያ ወንድም ቅር አሰኝቶት ሊሆን ይችላል። ጥናታችሁ ይሖዋ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለውን አመለካከት እንዲያስብ አበረታቱት። ለእነሱ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ሲል ምን ዋጋ ከፍሏል? (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ ለክርስቲያናዊ አንድነታችን ምን ያህል ቦታ ይሰጣል? (መዝ. 133:1) ይህን አንድነት ለመጠበቅ ጥረት ስናደርግስ ምን ይሰማዋል? (2 ቆሮ. 13:11) በወንድሞቻችን ድክመት ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ ስናተኩር ይሖዋ ምን ያህል እንደሚደሰት ጥናታችሁ እንዲገነዘብ እርዱት።

15-16. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከባድ ውሳኔ ሲደቀንበት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት ነው? (ዮሐንስ 8:29) (ለ) ማሪያን ጥናቷን ጥሩ ውሳኔ እንድታደርግ የረዳቻት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 በመጨረሻም፣ ጥናታችሁ ውሳኔ በሚያደርግበት ወቅት ስለ ይሖዋ ያገኘውን እውቀት እንዲጠቀምበት ልትረዱት ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 35 ላይ የሚገኘውን “ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ እንዲያነብ ልታበረታቱት ትችላላችሁ። ይሁንና ጥናታችሁ ከጸለየና ምርምር ካደረገ በኋላም ውሳኔ ላይ መድረስ ቢቸገርስ? ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመኖራቸው ምን መወሰን እንዳለበት ግራ ይገባው ይሆናል። በዚህ ጊዜ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንዲያሰላስል ሐሳብ ልትሰጡት ትችላላችሁ። ኢየሱስ ውሳኔዎችን የሚያደርገው እንዴት ነበር? ‘ሁልጊዜ አባቴን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:29ን አንብብ።) ስለዚህ ጥናታችሁ እንዲህ ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ አበረታቱት፦ ‘ባደረግኩት ምርምርና ስለ ይሖዋ በማውቀው ነገር መሠረት ይሖዋን የሚያስደስተው የትኛው ውሳኔ ነው?’ አንድ ውሳኔ ይሖዋን የሚያስደስት እስከሆነ ድረስ ጥሩ ውሳኔ ነው።

16 በቺሊ የምትኖር አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከባድ ውሳኔ ተደቅኖባት ነበር። ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ቢሆንም ከስብሰባ ፕሮግራሟ ጋር የሚጋጭ ሥራ አገኘች። ቤተሰቦቿ ይህን ሥራ እንድትቀበል ጫና አሳደሩባት። አስጠኚዋ የሆነችው ማሪያን እንዲህ ብላለች፦ “‘ውሳኔዬ ይሖዋን ያስደስተዋል ወይስ ያሳዝነዋል’ የሚለውን እንድታስብ አበረታታኋት። በተጨማሪም ስለ ጉዳዩ ጠቅሳ ወደ ይሖዋ እንድትጸልይና የእሱን መልስ ለማስተዋል ጥረት እንድታደርግ መከርኳት። በኋላም ሥራውን ላለመቀበል ወሰነች። ብዙም ሳይቆይ ከስብሰባ ፕሮግራሟ ጋር የማይጋጭ ሥራ አገኘች።” ማሪያን ጥናቷ ምን ማድረግ እንዳለባት ከመንገር ይልቅ ስለ ይሖዋ በምታውቀው ነገር ላይ እንድታሰላስል ረድታታለች። በዚህም የተነሳ ጥናቷ ከይሖዋ ጋር ያላት ወዳጅነት ይበልጥ ሊጠናከር ችሏል። ማሪያን ስለ ጥናቷ ስትናገር “ይሖዋ የእሱን አምልኮ እስካስቀደምን ድረስ እንደሚንከባከበን ተምራለች” ብላለች።

አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድን ሥራ እንደማትቀበል ለኃላፊው በአክብሮት ስትገልጽ፤ ኃላፊው የሥራ ውልና ብዕር ይዟል።

ጥናታችሁ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲማር እርዱት (አንቀጽ 15-16ን ተመልከት)b


ይሖዋን በደንብ የሚያውቁ ሰዎች በረከት ያገኛሉ

17. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ከሁሉ በላይ የሚያስፈልጋቸው እውቀት ምንድን ነው?

17 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማችን በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል። ጥናቶች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶችን ይማራሉ። ለምሳሌ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ፣ ስለ ቤዛውና ስለ አምላክ መንግሥት ያጠናሉ። ጥናቶች ስለ ድርጅታዊ ጉዳዮችም ይማራሉ። ለምሳሌ ስለ ስብሰባዎች፣ ስለ ሽማግሌዎችና ስለ በላይ አካሉ ያጠናሉ። ይሁንና ዓላማችን ጥናቶቻችን ስለ እነዚህ ጉዳዮች እውቀት እንዲያገኙ መርዳት ብቻ አይደለም። ይሖዋን በደንብ እንዲያውቁት እንፈልጋለን።

18. ይሖዋን የሚያውቁ ሁሉ የትኞቹን በረከቶች ያገኛሉ?

18 ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! ይሖዋን የሚያውቁና የሚያመልኩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት መምራት ይችላሉ። (መዝ. 25:12-15) ወደፊት ደግሞ፣ “ስለ እውነተኛው አምላክ እውቀት” የሚያገኙ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (1 ዮሐ. 5:20) ግን ይህ ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉና እሱን የሚወዱ ሰዎች ‘በእሱ ዘንድ የታወቁ’ እንደሆኑ ይናገራል። (1 ቆሮ. 8:3) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ትኩረት ይሰጠናል፤ እንዲሁም እንደ ወዳጆቹ ይቆጥረናል። ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማወቅ የሚያስገኘው ትልቁ በረከት ይሄ ነው!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይሖዋን በሚገባ ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ልናስተምራቸው የምንችለው እንዴት ነው?

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ስለ ይሖዋ ያገኙትን እውቀት እንዲጠቀሙበት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 84 እገዛ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት

a ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 05 ላይ የሚገኘው ግብ እንዲህ ይላል፦ “‘መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀምር’ የሚለውን ሰንጠረዥ ተጠቅመህ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ።”

b የሥዕሉ መግለጫ፦ የማሪያን ጥናት ሥራውን እንደማትቀበል ስትገልጽ የሚያሳይ ትወና።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ