የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን አስፋ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ዓሣ ማጥመጃ መረቦች
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከኢየሱስ ተከታዮች አንዳንዶቹ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። (ማር. 1:16-20) እነዚህ ሰዎች በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ለማጥመድ መረቦችን ይጠቀሙ ነበር።
ዓሣ ማጥመጃ መረቦች የሚሠሩት ቃጫ ወይም የበፍታ ክር በመቆጣጠር ነበር። የመረቡ ቀዳዳ ስፋት የሚወሰነው ዓሣ አጥማጆቹ ማጥመድ በሚፈልጉት ዓሣ ዓይነት ላይ ነው። ትናንሽ ዓሣዎችን ማጥመድ ከፈለጉ ትናንሽ ቀዳዳ ያለው መረብ ይጠቀማሉ፤ ትላልቅ ዓሣዎችን ማጥመድ ከፈለጉ ደግሞ ትላልቅ ቀዳዳ ያለው መረብ ይጠቀማሉ። በዘመኑ ሁለት ዓይነት የዓሣ ማጥመጃ መረቦች ነበሩ። አንዳንዶቹ መረቦች አነስ ያለ ስፋትና ክብ ቅርጽ ያላቸው ሲሆን ወደ ውኃው እንዲሰምጡ ለማድረግ ድንጋይ ወይም ሌላ ከባድ ነገር ይታሰርባቸው ነበር። ወደ ውኃው በሚሰምጡበት ጊዜ ዓሣዎችን ሰብስበው ይይዛሉ። አንዳንዶቹ መረቦች ደግሞ ትላልቅና አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ነበሩ። በእነዚህ መረቦች ዓሣ የሚጠመደው መረቡን ባሕሩ ላይ በመጎተት ነው። የታችኛው የመረቡ ክፍል ወደ ውስጥ እንዲሰምጥ ከባድ ነገር ይታሰርበታል፤ የላይኛው የመረቡ ክፍል ደግሞ ከላይ እንዲንሳፈፍ እንጨት ወይም ቡሽ ይታሰርበታል።
ዓሣ ማጥመጃ መረቦች ዋጋቸው ውድ ነበር። በባሕሩ ወለል ላይ ያሉ ድንጋዮች ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ዓሣ በሚይዙበት ጊዜ ሊበጣጠሱ ይችላሉ። (ሉቃስ 5:6) መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብና ዮሐንስ “መረቦቻቸውን እየጠገኑ” እንደነበር ይናገራል፤ ይህን ያደረጉት መርፌና የበፍታ ክር በመጠቀም ሳይሆን አይቀርም። (ማቴ. 4:21) ዓሣ አጥማጆች መረቦቻቸውን በተጠቀሙ ቁጥር ይጠግኗቸው የነበረ ይመስላል። ሉቃስ ደግሞ “መረቦቻቸውን እያጠቡ” ስለነበሩ ዓሣ አጥማጆች ተናግሯል፤ ይህን የሚያደርጉት በመረቡ ላይ ያለውን ጭቃና ቆሻሻ ለማጽዳት ነው። (ሉቃስ 5:2) ከዚያም መረቡን አስጥተው ያደርቁታል፤ አለዚያ በቀላሉ አርጅቶ ሊበጣጠስ ይችላል።—ሕዝ. 47:10
ኢየሱስ መረብ ተጠቅመው ዓሣ ያጠምዱ የነበሩ ሰዎችን “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ ጋብዟቸዋል።