ከነሐሴ 24-30, 2026
መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!
ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት ጥቅም ማግኘት
“ቅኖች በተሰበሰቡበት ማኅበር . . . ይሖዋን በሙሉ ልቤ አወድሰዋለሁ።”—መዝ. 111:1
ዓላማ
ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. ብዙዎች ስለ መስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት ምን ይሰማቸዋል?
አስፋፊ የሆንክበትን ቀን ታስታውሳለህ? ይህ ቀን በጣም የተደሰትክበት ቀን እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንያቱም በመላው ዓለም የይሖዋን ስም ከሚያወድሱ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች አንዱ ሆነሃል። (መዝ. 148:1, 2, 12, 13) ሆኖም በዚያ ቀን፣ ጥቂት አስፋፊዎችን በያዘ አንድ አነስተኛ ቡድን ውስጥም ተካተሃል። ይህ ቡድን የመስክ አገልግሎት ቡድን ይባላል። የመስክ አገልግሎት ቡድኖች “በመላው ምድር” የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልእኮ እንድንወጣ በእጅጉ ይረዱናል።—ማቴ. 24:14
2 የመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅትን በተመለከተ ምን ይሰማሃል? ዌንዲa የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ዝግጅት ለአገልግሎቴ በጣም ረድቶኛል። በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት የተነሳ ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች አዳዲስ የስብከትና የማስተማር ዘዴዎችን ተምሬያለሁ፤ መንፈሳዊ ግቦች ማውጣትና ግቦቼ ላይ መድረስ ችያለሁ፤ የልብ ጓደኞችም አፍርቻለሁ።” ሪክ የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የቡድን የበላይ ተመልካች መሆን ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል። አንዳንድ አስፋፊዎች አንድን ሰው አስጠንተው ጥምቀት ደረጃ እንዲደርስ የመርዳት አጋጣሚ ያገኛሉ። የቡድን የበላይ ተመልካቾች ደግሞ ያ ሰው በቀጣዮቹ ዓመታት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የመርዳት ልዩ አጋጣሚ አላቸው።” ዳይና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት ከፍተኛ አድናቆት አለኝ። በቡድኔ ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች የማያቸው ልክ እንደ ቤተሰቤ አድርጌ ነው።”
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ በመጀመሪያ የቡድን የበላይ ተመልካቹና ረዳቱ ምን ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲሁም በቡድናቸው ውስጥ ያሉትን አስፋፊዎች እንዴት እንደሚረዱ እንመለከታለን። ከዚያም በቡድኑ ውስጥ ያለን እያንዳንዳችን ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደምንችል እናያለን። በመጨረሻም ከዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ምን ጥቅም እንደምናገኝ እንመረምራለን።
የቡድን የበላይ ተመልካቹና ረዳቱ
4. (ሀ) የመስክ አገልግሎት ቡድን የበላይ ተመልካች ምን ዋና ዋና ኃላፊነቶች አሉበት? (ለ) የቡድን የበላይ ተመልካቹ በቡድኑ ውስጥ ያሉትን አስፋፊዎች ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላል? (“ለቡድን የበላይ ተመልካቹ የተሰጡ ጠቃሚ ሐሳቦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
4 የመስክ አገልግሎት ቡድን የበላይ ተመልካች፣ የሽማግሌዎች አካል በአንድ ቡድን ውስጥ ያሉ አስፋፊዎችን እንዲረዳ የሾመው ሽማግሌb ነው። ይህ ወንድም በቡድኑ ውስጥ ያሉ አስፋፊዎችን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። እንዴት? በመጀመሪያ፣ በቡድኑ ውስጥ ላሉ አስፋፊዎች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጣል። (ምሳሌ 27:23) ያሉበትን ሁኔታ በንቃት ይከታተላል፤ እንዲሁም አዘውትሮ ያነጋግራቸዋል። እንዲህ ማድረጉ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ማበረታቻ፣ ስሜታዊ ድጋፍና ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት ያስችለዋል። (ምሳሌ 12:25፤ ኢሳ. 32:2፤ ያዕ. 2:15-17) ሁለተኛ፣ በቡድኑ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ አስፋፊ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርግ ይረዳል። በተለይ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ግንባር ቀደም ሆኖ በቅንዓት በአገልግሎት ይካፈላል። እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ ካለ ከእያንዳንዱ አስፋፊ ጋር አዘውትሮ በማገልገል አስፈላጊውን ማበረታቻና ሥልጠና ይሰጣል። ከስንት አንዴ አገልግሎት መውጣት ካልቻለ ደግሞ ረዳቱ ወይም ሌላ ብቃት ያለው አስፋፊ ለቡድኑ አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርግ ይመድባል። ሦስተኛ፣ የተጠመቁ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበል ብቃቱን እንዲያሟሉ ይረዳል። (1 ጢሞ. 3:1) ላከናወኑት መልካም ነገር ከልብ ያመሰግናቸዋል፤ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይሰጣቸዋል፤ እንዲሁም የጉባኤ አገልጋይና ሽማግሌ ለመሆን ብቃቱን እንዲያሟሉ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ይሰጣቸዋል። የቡድን የበላይ ተመልካቾች ካለባቸው ከባድ ኃላፊነት አንጻር የሽማግሌዎች አካል ለዚህ ኃላፊነት የሚመርጠው ብቃቱን በሚገባ የሚያሟሉ ሽማግሌዎችን ነው።
5. አንዳንድ የቡድን የበላይ ተመልካቾች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?
5 የቡድን የበላይ ተመልካቾች ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ጊዜ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። በጀርመን የሚኖረውን ዮርግ የተባለ የቡድን የበላይ ተመልካች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንደ ብዙዎቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች እሱም በጉባኤ ውስጥ ተደራራቢ ኃላፊነቶች አሉበት። እንዲህ ብሏል፦ “የተለያዩ ኃላፊነቶችን ጎን ለጎን ማስኬድ ቀላል አይደለም። በዚህም የተነሳ በቡድኔ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን አስፋፊ ለማነጋገር ብፈልግም ከባድ ይሆንብኛል።” በኡጋንዳ የሚኖር የ70 ዓመት ዕድሜ ያለው አቤል የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህ በአንድ የመስክ አገልግሎት ቡድን ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች ብዙ ናቸው። በዚህም ምክንያት በምፈልገው መጠን ለእያንዳንዱ አስፋፊ እረኝነት ማድረግ ከባድ ነው።” በሱሪናም የሚኖር ኦቤድ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌም እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “ሌሎችን ማሠልጠን ቢያስደስተኝም ሥልጠና ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል፤ በአብዛኛው ደግሞ ውጤቱ ቶሎ አይታይም። ስለዚህ ሌሎች ኃላፊነቶች ሲደራረቡብኝ ሥልጠና መስጠትን ወደ ጎን ገሸሽ ለማድረግ እፈተናለሁ።” ታዲያ ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለማሸነፍ ምን ይረዳቸዋል?
6. የመስክ አገልግሎት ቡድኖች አነስ ያሉ መሆናቸው ምን ጥቅም አለው?
6 የሚቻል እስከሆነ ድረስ የመስክ አገልግሎት ቡድኖች አነስ ያሉ ቢሆኑ ይመረጣል። ይህም የቡድን የበላይ ተመልካቾች እያንዳንዱን አስፋፊ በደንብ ማወቅና በመንፈሳዊ ጠንካራ እንዲሆን መርዳት እንዲችሉ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ይሁንና በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች ጥቂት ከሆኑስ? ቡድኖቹን ማተለቅ የቡድን የበላይ ተመልካቹ ሁሉንም ኃላፊነቶቹን በአግባቡ መወጣት ከባድ እንዲሆንበት ያደርጋል። ስለዚህ የሽማግሌዎች አካል ለጊዜውም ቢሆን አንድ የጉባኤ አገልጋይ ይህን ኃላፊነት እንዲወጣ ቢመድብ የተሻለ ይሆናል። ቡድኖቹ አነስ ያሉ ከሆኑ የቡድን የበላይ ተመልካቾች በዋነኛ ኃላፊነታቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ይችላሉ፤ ይህም ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መርዳት ነው።
7. ብዙ ሽማግሌዎች በሌሉበት ጉባኤ ውስጥ የቡድን የበላይ ተመልካቾች እያንዳንዱ አስፋፊ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኝ ምን ማድረግ ይችላሉ? (1 ጴጥሮስ 5:2) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 ብዙ ሽማግሌዎች በሌሉበት ጉባኤ ውስጥ የቡድን የበላይ ተመልካች ሆነህ የምታገለግል ከሆነ የአምላክን መንጋ በመንከባከብ እንዲያግዝህ ረዳትህን በማሠልጠን ላይ ትኩረት አድርግ። (1 ጴጥሮስ 5:2ን አንብብ።) ለረዳትህ አንዳንድ ሥራዎችን ስጠው። ለምሳሌ በየተወሰነ ጊዜው ስምሪት እንዲመራ ወይም የቡድኑን እንቅስቃሴ እንዲያደራጅ ልትጠይቀው ትችላለህ። በቡድኑ ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች ስላሉበት ሁኔታ ተወያዩ። እረኝነት ስታደርግ ረዳትህን አዘውትረህ ይዘኸው ሂድ። ከእረኝነቱ በፊትም ሆነ በኋላ አንዳንድ ሐሳቦችን አካፍለው። ውሎ አድሮ ረዳትህ የቡድን የበላይ ተመልካች ለመሆን ብቃቱን ሊያሟላ ይችላል። (2 ጢሞ. 2:2) በቡድንህ ውስጥ ያሉ ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖችም ሌሎችን በማሠልጠን እንዲያግዙህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። አቅኚዎችና ተሞክሮ ያላቸው ሌሎች አስፋፊዎች ከአዲሶችና ተሞክሮ ከሌላቸው አስፋፊዎች ጋር ማገልገል ይችላሉ። እንዲሁም አገልግሎት ላይ ውይይት በመጀመር፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ ሊያሠለጥኗቸው ይችላሉ። ከዚህ በመቀጠል፣ በመስክ አገልግሎት ቡድን ውስጥ ያለን እያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመለከታለን።
አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በቡድኑ ውስጥ ያለን የጉባኤ አገልጋይ ሊያሠለጥን ይችላል፤ ለምሳሌ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲመራ ሊጠይቀው ይችላል (አንቀጽ 7ን ተመልከት)
በቡድኑ ውስጥ ያለን እያንዳንዳችን ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን?
8. በቡድኑ ውስጥ ያለን እያንዳንዳችን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? (ሮም 1:12)
8 ከቡድንህ አስፋፊዎች ጋር አብረህ አገልግል። ከሌሎች ጋር አብረን ስናገለግል ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። (ሮም 1:12ን አንብብ።) በተጨማሪም ከሌሎች ጋር አብረን ማገልገላችን ሰዎችን ስናነጋግር እንዳንፈራ እንዲሁም አደጋ ሊያስከትሉ ከሚችሉ ነገሮች እንድንጠበቅ ይረዳናል። በሥራህ ምክንያት ቡድንህ በሚያደርጋቸው የአገልግሎት እንቅስቃሴዎች አዘውትረህ መካፈል ካልቻልክ አሠሪህ ፕሮግራምህን እንዲያስተካክልልህ ለምን አትጠይቀውም? ያልጠበቅከውን ጥሩ ምላሽ ልታገኝ ትችላለህ። (ነህ. 2:4-6) በጤና እክል ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ ቡድንህ በሚያደርገው የስምሪት ስብሰባ ላይ በአካል መገኘት ካልቻልክ ደግሞ የቡድን የበላይ ተመልካችህን ለምን አታነጋግረውም? በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በስምሪት ስብሰባው ላይ እንድትገኝ እንዲሁም በደብዳቤ ወይም በስልክ ምሥክርነት እንድትካፈል ሊያመቻችልህ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣትና ጤናማ ብትሆንም አዘውትረህ አገልግሎት መውጣት ከባድ ቢሆንብህስ? ከሆነ፣ በየሳምንቱ በቡድንህ ውስጥ ከሚገኝ አንድ አስፋፊ ጋር ለማገልገል ለምን ቀጠሮ አትይዝም? ምናልባት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መገምገም ወይም የጊዜ አጠቃቀምህን ማስተካከል ሊያስፈልግህ ይችላል። (ሮም 12:11፤ ቆላ. 4:5) በዚህ ረገድ የምታደርገው ጥረት ብዙ መልካም ውጤቶችን ያስገኛል። ወደ ይሖዋ ጸልይ። እሱም ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎትም ሆነ ኃይል’ ይሰጥሃል።—ፊልጵ. 2:13
9. በመስክ አገልግሎት ቡድናችን ውስጥ ፍቅርና ሞቅ ያለ መንፈስ እንዲሰፍን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ሮም 12:13)
9 እንግዳ ተቀባይ ሁን። “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” ካዳበርን በመስክ አገልግሎት ቡድናችን ውስጥ ፍቅርና ሞቅ ያለ መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ሮም 12:13ን አንብብ።) በቤትህ ውስጥ የስምሪት ስብሰባ እንዲደረግ መፍቀድ ትችል ይሆን? በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ የአገልግሎት ቡድኖች ከሌላ ጉባኤ የመጡ ተናጋሪዎችን በዙር ይጋብዛሉ። በተመደቡበት ሳምንት ላይ በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አስፋፊዎች ተናጋሪው ግብዣው ላይ ባይገኝ እንኳ አንድ ላይ ተገናኝተው ሊመገቡና ሊጨዋወቱ ይችላሉ። ሣራ የተባለች ልዩ አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “እንግዶች ቤቴ መጋበዝ በጣም ይጨንቀኛል። ስለዚህ ዝግጅቱን በተቻለኝ መጠን ቀለል ለማድረግ እሞክራለሁ። ስለማቀርበው ምግብ ከመጨነቅ ይልቅ የጋበዝኳቸውን ሰዎች በደንብ በማወቅ ላይ ለማተኮር ጥረት አደርጋለሁ።” በመስክ አገልግሎት ቡድናችን ውስጥ እንደ ቤተሰብ ያለ ቅርርብ ለመፍጠር ጥረት የምናደርግ ከሆነ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን፤ እርስ በርሳችንም እንቀራረባለን።—ነህ. 8:10፤ ሥራ 20:35
10. በአንድ የአገልግሎት መስክ ማሻሻያ ማድረግ ከፈለግን ምን ማድረግ እንችላለን? (ምሳሌ 1:5፤ 27:17) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 እርዳታ ጠይቅ። የመስበክና የማስተማር ክህሎታችንን ባዳበርን ቁጥር በቡድናችን ውስጥ ካሉ አስፋፊዎች ጋር አገልግሎት መውጣት ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል። ማሻሻያ ማድረግ የምትፈልግበት የአገልግሎት መስክ አለ? ከሆነ፣ ግብህን ለቡድን የበላይ ተመልካችህ አሳውቀው። ግብህ ላይ እንድትደርስ ሊረዳህ ይችል ይሆናል። በቡድንህ ውስጥ ያለን አንድ አቅኚ ወይም ተሞክሮ ያለው አስፋፊ እርዳታ መጠየቅም ትችላለህ። (ምሳሌ 1:5፤ 27:17ን አንብብ።) ሄዘር የተባለች ዓይናፋር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ እንድታግዘኝ አንዲትን አቅኚ ጠየቅኳት። እሷም በደግነትና በፍቅር ረድታኛለች። አዘውትራ አብራኝ ታገለግል ነበር። እንዲያውም ተመላልሶ መጠየቅ ከማደርግላቸው ሰዎች አንዷን ጥናት እንዳስጀምር ረድታኛለች። እርዳታ በመጠየቄ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም አገልግሎት መውጣት አስደሳች ሆኖልኛል።” በእርግጥም በቡድኑ ውስጥ ያለን ሁላችንም አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችልበት ብዙ መንገድ አለ።
የመስክ አገልግሎት ቡድን ጥቂት አስፋፊዎችን የያዘ መሆኑ እርስ በርስ ለመተዋወቅና አብረን ለማገልገል አጋጣሚ ይሰጠናል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)
ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት የምናገኘው ጥቅም
11-12. ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት የትኞቹን መንፈሳዊ ጥቅሞች እናገኛለን? አንድ ተሞክሮ ጥቀስ።
11 መንፈሳዊ ጥቅሞች። ሁላችንም ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት መንፈሳዊ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ እንደ መበለቶች፣ ወላጅ አልባ ልጆችና አረጋውያን ያሉ ይሖዋ ለየት ያለ ትኩረት የሚሰጣቸው ወንድሞችና እህቶች በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ላይ የሚያበረታታ እረኝነት ይደረግላቸዋል። (1 ተሰ. 2:8፤ ያዕ. 1:27) በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዳ ሥልጠና ይሰጠናል። ምሳሌ የሚሆኑ የተጠመቁ ወንድሞች ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት መሸከም እንዲችሉ ይሠለጥናሉ።—1 ጢሞ. 3:10
12 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዌንዲ ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት ምን ጥቅም እንዳገኘች እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ ተቃዋሚ ስለነበር እናቴ ብዙውን ጊዜ ቅዳሜና እሁድ ከመስክ አገልግሎት ቡድኗ ጋር ማገልገል አትችልም ነበር። እኔ ግን ስለሚፈቀድልኝ እሄዳለሁ። አንዲት በዕድሜ የገፋች አቅኚ ትኩረት ሰጥታ አሠለጠነችኝ። ለአገልግሎትም ሆነ ለጉባኤ የሚጠቅሙኝን ክህሎቶች እንዳዳብር ረድታኛለች። የቡድን የበላይ ተመልካቼ በተደጋጋሚ ፍቅር የተንጸባረቀበት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሰጥቶኛል። ምክሩ እስከ ዛሬ ጠቅሞኛል።”
13. ከመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት የትኞቹን ስሜታዊ ጥቅሞች እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ስሜታዊ ጥቅሞች። በቡድናችን ውስጥ ካሉ አስፋፊዎች ጋር አንድ ላይ ሆነን ስናገለግል በመካከላችን የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠረታል። (ፊልጵ. 1:27) የመስክ አገልግሎት ቡድኖች ጥቂት አስፋፊዎችን የያዙ መሆናቸው ዓይናፋር የሆኑ ወይም ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ መሆን የሚጨንቃቸው አስፋፊዎች ጓደኛ ማፍራት ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። (2 ቆሮ. 6:13) እነዚህ ጓደኞች ስንታመም፣ በጭንቀት ስንዋጥ፣ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ወይም ሌላ ችግር ሲያጋጥመን ይደርሱልናል። (1 ተሰ. 5:14) ወደፊት ደግሞ ከአሁኑም ይበልጥ ጥሩ ጓደኞች እንደሚያስፈልጉን ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 24:21) ጓደኞቻችን ችግሮቻችንን ላያስወግዱልን ይችላሉ፤ ሆኖም የሚወዱንና የሚደግፉን ወንድሞችና እህቶች በዙሪያችን እንዳሉ ማወቃችን ችግሩን ለመቋቋም የበለጠ ጥንካሬ ይሰጠናል።—ምሳሌ 17:17
በአንድ የአገልግሎት ቡድን ውስጥ ያሉ ሁለት እህቶች በአገልግሎት አብረው ሲካፈሉ (አንቀጽ 13ን ተመልከት)
14. በአደጋ ጊዜ ከመስክ አገልግሎት ቡድናችን ምን ጥቅም እናገኛለን?
14 ተግባራዊ ጥቅሞች። ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ድንገተኛ ሕመም፣ ስደትና የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን ከመስክ አገልግሎት ቡድናችን አፋጣኝ እርዳታ እናገኛለን። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የአገልግሎት ኮሚቴው ከመስክ አገልግሎት ቡድን የበላይ ተመልካቾች ጋር በመመካከር ወደፊት አደጋ ወይም ድንገተኛ ሁኔታ ቢያጋጥም ልዩ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት የሚያስችል ዕቅድ ከወዲሁ ያዘጋጃል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ደግሞ የቡድን የበላይ ተመልካቾች በቡድናቸው ውስጥ ያለውን የእያንዳንዱን ቤተሰብ ደህንነት ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋሉ። በተጨማሪም ሕክምና፣ ምግብ፣ ውኃ፣ ልብስ ወይም መጠለያ ያስፈልጋቸው እንደሆነ ያጣራሉ። ይህም የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንዲያገኙ ያስችላል። እንዲህ ያለ ፍቅራዊ እንክብካቤ የምናገኝበት ዝግጅት ስለተደረገልን ምንኛ አመስጋኞች ነን!
15. በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የታቀፍነውን ሁሉ አንድ የሚያደርገን ምንድን ነው?
15 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ የይሖዋ ድርጅት በጣም ሰፊ ነው። ሰማያዊው ክፍል በመቶ ሚሊዮኖች ምናልባትም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን የያዘ ነው። ምድራዊው ክፍል ደግሞ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የአምላክ አገልጋዮችን ይዟል፤ ይህ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው። (ዘካ. 8:23፤ ራእይ 5:11) በሰማይም ሆነ በምድር ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች የመንግሥቱን ምሥራች በማስፋፋቱ ሥራ በአንድነት ይካፈላሉ። (ራእይ 14:6, 7) የመስክ አገልግሎት ቡድን ዝግጅት ይሖዋን በሙሉ ልብ እንድናወድስ ይረዳናል። እንግዲያው ሁላችንም ከዚህ ዝግጅት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።—መዝ. 111:1
መዝሙር 61 እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b አስፈላጊ ከሆነ፣ ኃላፊነቱን የሚሸከም ሽማግሌ እስኪገኝ ድረስ ብቃት ያለው የጉባኤ አገልጋይ ይህን ሥራ ሊያከናውን ይችላል። ይህን ኃላፊነት የተቀበለ የጉባኤ አገልጋይ የቡድን የበላይ ተመልካች ሳይሆን የቡድን አገልጋይ ይባላል። ምክንያቱም በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ አያገለግልም። ከዚህ ይልቅ፣ በሽማግሌዎች አካል አመራር ሥር ሆኖ ኃላፊነቱን ይወጣል።