ከነሐሴ 17-23, 2026
መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ
ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
“ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላ. 3:12
ዓላማ
ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎችን መቋቋም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1. እውነተኛ ወዳጆችን ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?
“ሕልሜ ተሳካ የትናንቱ፣ አምላክ አይቶ መሻቴን አስጠጋኝ ከቤቱ። ተካሰ ልቤ ፍቅር የተራበው፣ ምን ወዳጅ ብቻ፣ ይኸው ቤተሰብ አገኘሁ!” እነዚህ ስንኞች የተወሰዱት “የይሖዋ ቤተሰብ” የሚል ርዕስ ካለው ኦሪጅናል መዝሙር ነው። አንተስ በእነዚህ ቃላት አትስማማም? በእርግጥም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል እንዲህ ያሉ እውነተኛ ወዳጆችን ማግኘት መቻላችን ትልቅ በረከት ነው! (መዝ. 119:63) በአንድነት ይሖዋን በሚያመልክና እርስ በርስ በሚዋደድ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ታቅፈናል።
2. ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ምን ዓይነት ወዳጅነት እንዲኖረን እንፈልጋለን?
2 ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለን ወዳጅነት ላይ ላዩን ያለ ወይም የይስሙላ ያህል ብቻ እንዲሆን አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋንና ኢየሱስን በሚወድ ቤተሰብ ውስጥ ታቅፈናል። እርስ በርስ የሚያስተሳስረን ይህ ፍቅር ነው። (ዮሐ. 13:35) ሆኖም በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ስለታቀፍን ብቻ እርስ በርሳችን የጠበቀ ወዳጅነት ይኖረናል ማለት አይደለም። እንዲህ ያለውን ወዳጅነት መመሥረት ጥረት ይጠይቃል። ደግሞም ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን ወዳጅነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮች ያጋጥሙናል።
3. ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ይዞ መቀጠል ከባድ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?
3 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ከሁሉም ወንድሞችና እህቶች ጋር እኩል ቅርበት ሊኖረን አይችልም። ለምን? ከአንዳንዶቹ ጋር ተመሳሳይ ነገሮችን ስለምንወድ ወይም ባሕርያችን ስለሚጣጣም እነሱን መቅረብ ሊቀለን ይችላል። ሆኖም ከአንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ወዳጅነታችንን ይዘን መቀጠል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በመካከላችን አለመግባባት በመፈጠሩ የተነሳ ልንራራቅ እንችላለን። ወይም ደግሞ ባሕርያችን በጣም የተለያየ ከመሆኑ የተነሳ አብረን መሆን እንኳ ሊከብደን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞቻችን ከባድ ሕመም ወይም የስሜት ቀውስ ሲያጋጥማቸው ከእነሱ ጋር ያለን ወዳጅነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የኢየሱስን ምሳሌ እንመለከታለን። የእሱን ምሳሌ መከተላችን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም እንኳ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። በመጀመሪያ ግን፣ አንዳንድ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበራችን ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ይዘን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ክርስቲያናዊ ባሕርያት ወዳጅነታችንን ይዘን ለመቀጠል ይረዱናል
4. ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
4 ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጠናከር መልካም ጎናቸውን ለማየት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። መልካም ጎናቸውን ማየት የምንችለው ደግሞ ከእነሱ ጋር አብረን ጊዜ ስናሳልፍ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ጋር አብሮ ለመሆን ይጓጓ ነበር። ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ከእናንተ ጋር በአካል ለመገናኘት ብርቱ ጥረት አደረግን” ብሏቸዋል። (1 ተሰ. 2:17) በዛሬው ጊዜም ብዙ ወንድሞችና እህቶች በአካል ተገናኝቶ የመጨዋወትን ያህል ወዳጅነትን የሚያጠናክር ነገር እንደሌለ አስተውለዋል። በአገልግሎት ስንካፈል እንዲሁም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይህን ማድረግ የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች እናገኛለን። ሆኖም አብረን ጊዜ ስላሳለፍን ብቻ ወዳጅነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮች አያጋጥሙንም ማለት አይደለም።
5. ከሌሎች ጋር ያለን ወዳጅነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ወዳጅነታችንን ለማዳን ምን ሊረዳን ይችላል? በምሳሌ አስረዳ። (ቆላስይስ 3:12)
5 ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ወዳጅነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ወዳጅነታችንን ለማዳን ይረዱናል። (ቆላስይስ 3:12ን አንብብ።) ትሕትና፣ ትዕግሥት፣ ደግነት እና ርኅራኄ ማዳበራችን ወዳጅነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ለመወጣት ይረዳናል። የሞተር ዘይት የመኪናው ሞተር በጥሩ ሁኔታ መሥራቱን እንዲቀጥል እንደሚረዳው ሁሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትም ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ዝምድና ሊያሻክሩ የሚችሉ ነገሮችን ለመቀነስ ይረዱናል። ከዚህ በመቀጠል፣ ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሦስት ችግሮችን እንመለከታለን። ከእያንዳንዱ ችግር ጋር በተያያዘ የኢየሱስን ትሕትና፣ ትዕግሥት፣ ደግነትና ርኅራኄ መኮረጃችን ለሌሎች እውነተኛ ወዳጅ ሆነን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
አለመግባባት ሲፈጠር
6. አለመግባባቶች ወዳጅነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 ይህ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በሁለት ሰዎች መካከል አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁለቱም የራሳቸው አመለካከት ትክክል እንደሆነ እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ሁለት ወንድሞች የመስክ አገልግሎት ቡድናቸው አገልግሎቱን እንዴት ቢያከናውን ይሻላል ከሚለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ አልተስማሙም እንበል። ሁለቱም ‘እኔ ያቀረብኩት ሐሳብ የተሻለ ነው’ ብለው ያስባሉ። ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ ወዳጅነታቸውን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ሁለቱም አልሸነፍ ባይ ከሆኑና ጉዳዩን ተወያይተው ለመፍታት ጥረት ካላደረጉ አንዳቸው በሌላው ላይ ቂም ሊይዙ ይችላሉ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ደግሞ የባሰ ሊራራቁና ወዳጅነታቸው ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ ይችላል። ይህ ሁሉ የተፈጠረው በቀላሉ ሊፈታ በሚችል ጉዳይ መሆኑ አያሳዝንም?
7. ኢየሱስ አለመግባባቶችን ለመፍታት ቁልፉ ትሕትና እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው? ኢየሱስ አለመግባባቶችን ለመፍታት ቁልፉ ትሕትና እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ ከመካከላቸው ታላቅ የሆነው ማን እንደሆነ በተደጋጋሚ ይከራከሩ ነበር። ኢየሱስ ይህን ሥር የሰደደ ችግር እንዲያስተካክሉ ለመርዳት ሌሎችን ከራሳቸው እንደሚበልጡ አድርገው ማየት እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 20:25-28) በሌላ አባባል፣ ትሕትና ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ነግሯቸዋል። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ እንኳ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን ሥራ በትሕትና በመሥራት ማለትም እግራቸውን በማጠብ ‘አርዓያ ሆኖላቸዋል።’ (ዮሐ. 13:3-5, 12-16) በዚህ መንገድ ወዳጅነታቸውን ጠብቀው መቆየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይቷቸዋል። ሌሎችን ከራሳቸው እንደሚበልጡ አድርገው የሚመለከቱ ከሆነ ከአንድ ሰው ጋር አለመግባባት ሲያጋጥማቸው የዚያን ሰው ሐሳብ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ይሆናሉ። በመካከላቸው የአመለካከት ልዩነት ቢኖርም እንኳ የቅርብ ወዳጆች ሆነው መቀጠል ቀላል ይሆንላቸዋል።
8. አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ትሕትና ከሌሎች ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት ነው? (ቆላስይስ 3:13) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
8 እኛስ ወዳጅነታችንን ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ትሕትና ጥቃቅን አለመግባባቶችን ለመተውና ሌሎችን በነፃ ይቅር ለማለት ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።) ትሑት ከሆንን በአንድ ጉዳይ ባንስማማም እንኳ ጉዳዩን ችላ ብለን ለማለፍ እንመርጣለን፤ ይህም ከሌሎች ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ይዘን ለመቀጠል ይረዳናል። (መዝ. 4:4) ሌላኛው ወገን ደግነት የጎደለው ነገር ቢናገር እንኳ ሁላችንም በኋላ ላይ የምንቆጭበትን ነገር እንደምንናገር እናስታውሳለን። (መክ. 7:21, 22) ራሳችንን ‘ትክክል መሆኔን ማረጋገጥ ከወዳጅነታችን ይበልጥብኛል?’ ብለን መጠየቅ እንችላለን። ከዚያም የእኛን ሐሳብ ትተን የግለሰቡን ሐሳብ ለመቀበል እንወስን ይሆናል። በተፈጠረው አለመግባባት ላይ ባለመብሰልሰልም ሆነ ጉዳዩን ዳግመኛ ባለማንሳት የአእምሮ ሰላማችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን።
ትሕትና ጥቃቅን አለመግባባቶችን ችላ ብለን እንድናልፍና ሌሎችን በነፃ ይቅር እንድንል ይረዳናል (አንቀጽ 8ን ተመልከት)a
9. በቀላሉ የማይፈታ አለመግባባት ሲያጋጥመን ትሕትና የሚረዳን እንዴት ነው? (ምሳሌ 17:9)
9 ትሕትና አለመግባባቱ በቀላሉ የሚፈታ በማይሆንበት ጊዜም ይረዳናል። ትክክል መሆናችንን ለማሳመን መከራከር አይኖርብንም። (ምሳሌ 17:9ን አንብብ፤ 1 ቆሮ. 6:7) ግባችን ወዳጅነታችንን ማዳን መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ብዙዎች ግለሰቡን ቀርበው በደግነት በማነጋገር ችግሩን መፍታት ችለዋል። (መዝ. 34:14) ግለሰቡን እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ ‘በዚህ ምክንያት ወዳጅነታችን እንዲበላሽ አልፈልግም። ተነጋግረን ብንፈታው ምን ይመስልሃል?’ በግጭቱ ውስጥ የእኛም እጅ እንዳለበት አምነን ለመቀበልና ስሜቱን ስለጎዳነው ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል። ግለሰቡ ይቅርታ ከጠየቀን ደግሞ በትሕትና ይቅርታውን ልንቀበል ይገባል። (ሉቃስ 17:3, 4) ግባችን ‘ጥፋተኛው ማን ነው’ የሚለውን መወሰን ሳይሆን አለመግባባቱን ፈቶ ወዳጅነታችንን ማስቀጠል እንደሆነ ማስታወስ አለብን።—ምሳሌ 18:24
የባሕርይ ልዩነት ሲኖር
10. ከአንዳንዶች ጋር ጓደኛ መሆን የሚከብደን ለምን ሊሆን ይችላል?
10 ይህ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ከእኛ የተለየ ባሕርይ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር የቅርብ ወዳጅ መሆን ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንዶች የሚያበሳጨን ባሕርይ ይኖራቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ቀደም ሲል በደረሰባቸው በደል ወይም ባደጉበት ጥብቅ የሆነ ወይም ለቀቅ ያለ ባሕል የተነሳ ከሌሎች ጋር ሲነጋገሩ ምን ማለት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ባሕርያችን ተቃራኒ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ እኛ ተግባቢ፣ እነሱ ደግሞ ዓይናፋር ሊሆኑ ይችላሉ።
11. ኢየሱስ ከእሱ የተለየ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነቱን ይዞ መቀጠል የቻለው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው? ከእሱ የተለየ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነቱን ይዞ ቀጥሏል። ለምሳሌ ሐዋርያው ያዕቆብና ሐዋርያው ዮሐንስ በመንግሥቱ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ የሥልጣን ጥመኝነት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ማር. 10:35-37) ኢየሱስ ግን በተቃራኒው በሰማይ የነበረውን የላቀ ሥልጣንና ቦታ ትቶ በትሕትና ወደ ምድር መጥቷል። (ፊልጵ. 2:5-8) በመካከላቸው ያለው የባሕርይ ልዩነት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ አስተዋልክ? ያም ሆኖ ኢየሱስ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ሆነ ሌሎቹን በትዕግሥት ይዟቸዋል።
12. ኢየሱስ ወዳጆቹን በትዕግሥት እንዲይዝ የረዳው ምንድን ነው?
12 ኢየሱስ ከወዳጆቹ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊ ነበር። ያዕቆብና ዮሐንስ ብቻ ሳይሆኑ አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርትም እንዲህ ያለ የፉክክር መንፈስ እንዳላቸው ያውቃል። (ማር. 9:34) ኢየሱስም ያደገው ለሥልጣንና ለክብር ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚሁ ማኅበረሰብ ውስጥ ስለሆነ አስተሳሰባቸውን መረዳት አልከበደውም። በመሆኑም በትዕግሥት ይዟቸዋል። በዓመታት ሂደት በውስጣቸው ሥር የሰደደውን ኩራትና የሥልጣን ጥመኝነት በአንዴ እንዲያስወግዱ ከመጠበቅ ይልቅ ቀስ በቀስ እንዲያሻሽሉ ጊዜ ሰጥቷቸዋል።—ማር. 10:42-45
13. ታጋሽ መሆናችን ወዳጅነታችንን ይዘን ለመቀጠል የሚረዳን እንዴት ነው? (ኤፌሶን 4:2)
13 እኛስ ወዳጅነታችንን ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ትዕግሥት ማዳበራችንን እንቀጥል። የሚያበሳጨን ባሕርይ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች ለመቻል ጥረት እናድርግ። (ምሳሌ 14:29) ሁላችንም ልዩ የሚያደርጉን ባሕርያት አሉን። አንዳንዶቹ ባሕርያት ከሌሎች ሰዎች የተለዩ ቢሆኑም ስህተት ናቸው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የማንነታችን መገለጫ ናቸው። ሌሎች ይህን ተረድተው በትዕግሥት ሲይዙን ደስ ይለናል። (ኤፌሶን 4:2ን አንብብ።) ስለዚህ እኛም ከሌሎች በምንጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊ መሆንና ሌሎች ራሳቸውን እንዲሆኑ መፍቀድ ይኖርብናል። ለምሳሌ ዝምተኛና ዓይናፋር የሆነ ሰው ከሌሎች ጋር አብሮ መሆንና መጨዋወት ምን ያህል ሊከብደው እንደሚችል እናስብ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች በጣም ተጫዋች ሊሆኑና ብዙ ሊያወሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ያሉ ሰዎችንም በትዕግሥት መያዝ ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ ከሁሉም ሰው ጋር የቅርብ ወዳጅ እንሆናለን ማለት አይደለም። ያም ቢሆን በጣም የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ክርስቲያኖችም ተባብረው በሰላም መሥራት እንደሚችሉ ልናስታውስ ይገባል።
14. ትዕግሥት በምን ላይ እንድናተኩር ይረዳናል?
14 ትዕግሥት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ባላቸው መልካም ባሕርይ ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። እንዲህ ካደረግን በመካከላችን ያለው የባሕርይ ልዩነት ወዳጅነት እንዳንመሠርት እንቅፋት አይሆንብንም። ለምሳሌ ያዕቆብና ዮሐንስ ራስ ወዳድ በመሆን ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት ተመኝተዋል። ሆኖም ያቀረቡት ጥያቄ መንግሥቱ እውን እንደሆነላቸው የሚጠቁም ነው። ኢየሱስ ይህን እምነታቸውን ተመልክቶላቸዋል። እኛም የወዳጆቻችንን መልካም ጎን ለማየት ጥረት በማድረግ ኢየሱስንና አባቱን ይሖዋን መምሰል እንችላለን።
15. ከእኛ የተለየ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነታችንን ይዘን ለመቀጠል ማን ሊረዳን ይችላል?
15 ከእኛ የተለየ ባሕርይ ካላቸው ወንድሞች ጋር ወዳጅነታችንን ይዘን ለመቀጠል የሚረዳን ከሁሉ የተሻለው እርምጃ ወደ ይሖዋ መጸለይ ነው። ሊያጋጥሙን የሚችሉ ከባድ ሁኔታዎችን አስቀድመን በማሰብ ይሖዋ ለመረጋጋት እንዲረዳን ከወዲሁ መጸለይ እንችላለን። ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም የተለያየ ባሕርይ እንዳለን ያውቃል። ስለዚህ ሁኔታውን በጽናት ለመቋቋም ምን እንደሚያስፈልገን እንደሚያውቅ በመተማመን ወደ እሱ እንጸልይ። ትዕግሥታችን እንደተሟጠጠ ሲሰማን ደግሞ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ራሳችንን ለመቆጣጠር እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን።—ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው
16. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ በመካከላችን ምን ሊፈጠር ይችላል?
16 ይህ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አካላዊ ሕመም ወይም የስሜት ቀውስ ሲያጋጥማቸው የሚያበሳጨን ነገር ሊናገሩ ወይም ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ራሳቸውን ሊያገሉ፣ ቁጡ ሊሆኑ ወይም እንግዳ የሆነ ባሕርይ ሊያሳዩ ይችላሉ። ምናልባትም ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ይናገሩ ወይም ያደርጉ ይሆናል። (ኢዮብ 6:2, 3) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከምን ጋር እየታገሉ እንደሆነ ካላወቅን ደግሞ የምንጠብቅባቸው ነገር ከአቅማቸው በላይ ሊሆን ይችላል።
17. ኢየሱስ በርጤሜዎስ የተባለን ዓይነ ስውር ከረዳበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
17 ኢየሱስ ደግነትና ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው? የማያውቃቸውን ሰዎች ጨምሮ በመከራ ውስጥ ላሉ ደግነትና ርኅራኄ ያሳይ ነበር። ለምሳሌ በርጤሜዎስ የተባለን አንድ ዓይነ ስውር እንዴት እንደረዳው እንመልከት። በርጤሜዎስ፣ ኢየሱስ በዚያ አካባቢ እያለፈ መሆኑን ሲሰማ ኢየሱስ እንዲያየው ሲል መጮኽ ጀመረ። በዚያ የነበሩት ሰዎች ጩኸቱ ስለረበሻቸው ዝም እንዲል ነገሩት። እሱ ግን ኢየሱስ እንዲፈውሰው በጣም ስለፈለገ የባሰ መጮኹን ቀጠለ። ያደረገው ነገር አንዳንዶችን አበሳጭቷቸው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ግን ‘በጣም አዘነለት’፤ ሁኔታውን ሲያይ ከልቡ ራራለት። (ማቴ. 20:34፤ ማር. 10:46-52) በመሆኑም በደግነት አነጋገረው፤ እምነት በማሳየቱም አመሰገነው። ከዚያም የዓይኑን ብርሃን መለሰለት።
18. ወዳጆቻችን በመከራ ውስጥ ሲሆኑ ምን ልናደርግላቸው ይገባል? (1 ተሰሎንቄ 5:14)
18 እኛስ ወዳጅነታችንን ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ደግና ሩኅሩኅ እንሁን። እነዚህ ባሕርያት አካላዊ ሕመም ወይም የስሜት ቀውስ ያጋጠማቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንድናዝንላቸውና ‘እንድናጽናናቸው’ ይረዱናል። (1 ተሰሎንቄ 5:14ን አንብብ።) እውነተኛ ወዳጅ ሁሌም በተለይ ደግሞ ‘በመከራ ቀን’ የእርዳታ እጁን ለመዘርጋት ዝግጁ እንደሆነ አስታውስ። (ምሳሌ 17:17) እንዲህ ያለው ወዳጅ በመከራ ውስጥ ላለ ጓደኛው በማዘን ብቻ አይወሰንም፤ ከዚህ ይልቅ ጓደኛውን ለማጽናናት፣ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን ለማካፈል እንዲሁም ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል።
19. ደግነትና ርኅራኄ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
19 ደግነትና ርኅራኄ ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? እርግጥ ነው፣ ግለሰቡን ከአካላዊም ሆነ ከስሜታዊ ሥቃዩ መፈወስ እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም አቅማችን በፈቀደ መጠን ስሜቱን ለመረዳት ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ማቴ. 7:12፤ 1 ጴጥ. 3:8) ያለበትን ትግል ሲገልጽ በጥሞና አዳምጠው። አስፈላጊ ከሆነ፣ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን አካፍለው። (ምሳሌ 12:25) ስላለበት ሁኔታ የማታውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል ከግምት አስገባ። (ምሳሌ 18:13) ግለሰቡን በትዕግሥት ለመያዝ ጥረት አድርግ። እንዲሁም ከአቅሙ በላይ እንዳትጠብቅበት ተጠንቀቅ።—ኤፌ. 4:32
እውነተኛ ወዳጆች ደግነትና ርኅራኄ በማሳየት ጓደኞቻቸውን ያጽናናሉ (አንቀጽ 19ን ተመልከት)
20. ምን ዓይነት ወዳጅ መሆን ትፈልጋለህ?
20 ሁላችንም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ሆኖም ፍጹማን ስላልሆንን አንዳንድ ጊዜ ማድረግ የማንፈልገውን ነገር እናደርጋለን። ብዙዎቻችን በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን መጥፎ ነገሮች በባሕርያችን ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። እንደዚያም ሆኖ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ይዘን መቀጠል የቻልነው በትሕትና፣ በትዕግሥት፣ በደግነትና በርኅራኄ ስለያዙን ነው። ለዚህም በጣም አመስጋኞች ነን። እንግዲያው እኛም እንዲህ ያለ ወዳጅ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።
መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን
a የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ በዕድሜ የገፋ ወንድምና አንድ ወጣት ወንድም ከጉባኤው የአገልግሎት ክልል ጋር በተያያዘ የአመለካከት ልዩነት አጋጥሟቸዋል። በኋላ ላይ አብረው በአገልግሎት ይካፈላሉ።