ከነሐሴ 10-16, 2026
መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!
እምነታችን ሲፈተን ታማኝነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
“ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።”—ዮሐ. 6:68
ዓላማ
ምንም ዓይነት የእምነት ፈተና ቢያጋጥመን ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ እንችላለን።
1-2. ኢየሱስ በቅፍርናሆም እያስተማረ ሳለ ምን ተፈጠረ?
አንድ ቀን ኢየሱስ በቅፍርናሆም እያስተማረ ሳለ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” አለ። ቀጥሎም “ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በመጨረሻውም ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ” ሲል ተናገረ። (ዮሐ. 6:53, 54) ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲሰሙ ደስ አላላቸውም። እንዲያውም “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ።—ዮሐ. 6:60
2 እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በተናገረው ነገር ተሰናክለው እሱን መከተላቸውን አቆሙ። ይህን ያደረጉት በእሱ ላይ ምንም እምነት ስላልነበራቸው ነው? እንደዚያ ማለት አይቻልም። እንዲያውም ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ባደረገው ነገር በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ “ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረለት ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው” ብለው ነበር። (ዮሐ. 6:14) ስለዚህ እነዚህ ደቀ መዛሙርት በተወሰነ መጠንም ቢሆን በኢየሱስ ላይ እምነት ነበራቸው ማለት ነው። ሆኖም እምነታቸው ሲፈተን ለእሱ ታማኝ ሆነው አልቀጠሉም።
3. የኢየሱስ ሐዋርያት ምን አደረጉ? ለምንስ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
3 በሌላ በኩል ግን ሐዋርያቱ ያደረጉት ነገር ከዚህ የተለየ ነበር። ኢየሱስ እነሱም መሄድ ይፈልጉ እንደሆነ ሲጠይቃቸው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ። አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።” (ዮሐ. 6:68, 69) ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ሥጋውን ስለመብላትና ደሙን ስለመጠጣት ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸው ይሆናል። ያም ሆኖ ለእሱ ታማኝ ለመሆን መርጠዋል። ለምን? ምክንያቱም እምነታቸው የተመሠረተው በማይካድ እውነታ ላይ ነበር፤ ኢየሱስ “የአምላክ መሲሕ” እንደሆነ እርግጠኞች ነበሩ።—ሉቃስ 9:20, 35
በርካታ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ትተውት ቢሄዱም ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ለእሱ ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል (አንቀጽ 3ን ተመልከት)
4. እምነታችንን የሚፈትኑ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ?
4 ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት የሚፈትኑ የተለያዩ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ለምሳሌ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በምንረዳበት መንገድ ወይም የስብከቱ ሥራችን በተደራጀበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ሲደረግ ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል። ወይም ደግሞ ከባድ መከራ ሲደርስብን ይሖዋ እንዲህ ያለ ነገር እንዲደርስብን የፈቀደበት ምክንያት ግራ ሊገባን ይችላል። በተጨማሪም አንድ የቅርብ ጓደኛችን ሲበድለን ወይም አንድ የምናከብረው ክርስቲያን ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዳደረገብን ሲሰማን እምነታችን ሊፈተን ይችላል።
5. እምነታችን ጠንካራ መሠረት ሊኖረው የሚገባው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ቆላስይስ 1:23)
5 ፈተና ሲያጋጥመን ታማኝነታችንን ለመጠበቅ እምነታችን ጠንካራ መሠረት ሊኖረው ይገባል። ሕንፃዎች የሚገነቡበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንድ ሕንፃ የሚገነባው የምድር ነውጥ በሚበዛበት አካባቢ ከሆነ እንዲህ ያለውን ነውጥ ለመቋቋም ጠንካራ መሠረት ሊኖረው ይገባል። እኛም በተመሳሳይ ባለፈው አንቀጽ ላይ የተጠቀሱትን የእምነት ፈተናዎች ማለፍ ከፈለግን እምነታችን ጠንካራ መሠረት ሊኖረው ይገባል። የእምነታችንን መሠረት ማጠናከራችንን ከቀጠልን ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ጸንተን መቆምና ታማኝነታችንን መጠበቅ እንችላለን።—1 ቆሮ. 15:58፤ ቆላስይስ 1:23ን አንብብ።
6. ሐዋርያቱ ለኢየሱስ ታማኝ እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው?
6 በርካታ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተላቸውን ቢያቆሙም ሐዋርያቱ ታማኝ እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያቱ ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነና አምልኮ እንደሚገባው፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና “የዘላለም ሕይወት ቃል” እንዳለው እንዲሁም ኢየሱስ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው እርግጠኞች ነበሩ። ከዚህ በመቀጠል እምነታችንን ሊፈትኑ የሚችሉ የተለያዩ ነገሮችን ከመዘርዘር ይልቅ ማንኛውም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ጸንተን ለመቆም በሚረዱን ሦስት እውነቶች ላይ እናተኩራለን። (1) ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ ነው። (2) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በይሖዋ መንፈስ መሪነት ነው። (3) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ድርጅቱን እየመራው ነው። እነዚህ ሦስት ነገሮች እውነት እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ከሆንን የእምነት ፈተና ሲያጋጥመን ታማኝነታችንን መጠበቅ እንችላለን።
ይሖዋ ፈጣሪ ነው
7. ራእይ 4:11 ስለ ይሖዋ ምን ይናገራል? ይህን ማወቃችን ፈተና ሲያጋጥመን የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ራእይ 4:11ን አንብብ። ይህ ጥቅስ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ እንደሆነ ይናገራል። ይሖዋ ፈጣሪ ስለሆነ ብቻ እንኳ መመለክ ይገባዋል። እሱ ባለው አስደናቂ ኃይል ላይ ስናሰላስል ደግሞ ይሖዋ ከየትኛውም መከራ ሊታደገን እንደሚችል እርግጠኞች እንሆናለን። ሆኖም ሰይጣን፣ ሰዎች አምላክ መኖሩን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳ ይነዛል። አንዳንድ አንቱ የተባሉ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ እንደሌለው አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ። ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነና እንደሚወደን መቶ በመቶ እርግጠኞች ካልሆንን የእምነት ፈተና ሲያጋጥመን እሱ መኖሩንና እኛን የሚረዳን መሆኑን መጠራጠር ልንጀምር እንችላለን።—ዕብ. 11:6
8-9. ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን መጠራጠር ከጀመርክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን መጠራጠር ከጀመርክ አፋጣኝ እርምጃ ውሰድ። ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ መሆኑን የሚያረጋግጡ አጥጋቢ ማስረጃዎችን ለማግኘት በጽሑፎቻችን ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር አድርግ። ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች በሚሉት ብሮሹሮች ውስጥ እምነት የሚያጠናክሩ በርካታ መረጃዎችን ማግኘት ትችላለህ። jw.org ላይ በሚገኘው ንድፍ አውጪ አለው? በሚለው ዓምድ ውስጥም ተጨማሪ ማስረጃዎች ይገኛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ጄሲካ የተባለች ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የሕይወት አመጣጥ የሚለውን ብሮሹር ካነበብኩ በኋላ ማስረጃዎቹ ጥበበኛ የሆነ ንድፍ አውጪ አለ የሚል መደምደሚያ ላይ እንደሚያደርሱ እርግጠኛ ሆንኩ። ቀድሞውንም ቢሆን ይህን አውቅ ነበር፤ በብሮሹሩ ውስጥ ያለውን ማብራሪያ ማንበቤ ደግሞ ይህን ይበልጥ አረጋገጠልኝ።” በተጨማሪም ብዙዎች ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (በአማርኛ አይገኝም) የሚለውን መጽሐፍ ማንበባቸው ጠቅሟቸዋል። እነዚህን ጽሑፎች ከዚህ በፊትም አንብበሃቸው ሊሆን ይችላል። ግን ለምን ድጋሚ አታነባቸውም?
9 በግል ጥናት ፕሮግራምህ ወቅት የአምላክን መኖር የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን መመርመር ትችላለህ። ምርምር ማድረግህ ይሖዋ መኖሩን እርግጠኛ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን የእሱን ባሕርያት ይበልጥ እንድታውቅም ይረዳሃል። (ሮም 1:20) በተጨማሪም ያገኘኸውን እውቀት ተጠቅመህ አምላክ መኖሩን የሚጠራጠሩ ሰዎችን መርዳት ትችላለህ። በእርግጥም ይሖዋ እሱ ፈጣሪ መሆኑን የሚያረጋግጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ማስረጃዎች ሰጥቶናል።
Nebula: IAC/RGO/David Malin Images; fish and car: Mercedes-Benz USA; plane: Kristen Bartlett/University of Florida
ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የተባለውን ብሮሹር ከዚህ በፊት አንብበኸው ሊሆን ይችላል። ግን ለምን ድጋሚ አታነበውም? (አንቀጽ 8ን ተመልከት)
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በይሖዋ መንፈስ መሪነት ነው
10. ለመጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት አመለካከት አለን? (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17)
10 ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለሰው ልጆች ያስተላለፈውን መልእክት ይዟል። በሰዎች አእምሮ ውስጥ ለሚመላለሱ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። እንዲሁም የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነና ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ያስተምረናል። መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው ይሖዋ እንደሆነ ስለምናምን ከየትኛውም መጽሐፍ ይበልጥ ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናነበውን ነገር መረዳትና አቅማችን በፈቀደ መጠን በሥራ ላይ ማዋል እንፈልጋለን።
11. መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ የሚያሳምንህ ምንድን ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በይሖዋ መንፈስ መሪነት እንደሆነ የምናምነው ለምንድን ነው? በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። (ሉቃስ 3:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አንጻር ትክክል ነው። ስለ ተፈጥሮ የሚናገራቸው ነገሮችም ትክክል ናቸው። (ኢዮብ 26:7) ሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም በታሪክ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ወደ 40 የሚያህሉ ሰዎች ሲሆኑ ተጽፎ የተጠናቀቀውም በ1,600 ዓመታት ገደማ ውስጥ ነው፤ ያም ቢሆን መልእክቱ እርስ በርሱ ይስማማል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ቢሆንም በውስጡ ያለው ምክር በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየጠቀመ ነው። (ምሳሌ 13:20፤ 15:21፤ ማቴ. 7:12) ከዚህም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ትንቢቶች ተፈጽመዋል፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። (ኢያሱ 23:14) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ መተማመን እንችላለን!
12. መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን መጠራጠር ብንጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
12 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን መጠራጠር ብንጀምርስ? ስለ ጉዳዩ መጸለይ እንዲሁም ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ጆርዳን የተባለ እውነት ቤት ውስጥ ያደገ ወጣት ወንድም ምን እንዳለ እንመልከት፦ “የተነገረኝን ነገር ሁሉ ዝም ብዬ የማምን ሰው አይደለሁም። ራሴ አመዛዝኜ መደምደሚያ ላይ መድረስ እፈልጋለሁ። እውነቱን ለመናገር፣ አሁንም አልፎ አልፎ የሚያጠራጥር ነገር ያጋጥመኛል። በዚህ ጊዜ ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘትና ጥርጣሬዎቼን ለማስወገድ በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አደርጋለሁ።” እኛም መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በይሖዋ መንፈስ መሪነት እንደሆነ የሚያሳምኑንን ምክንያቶች አዘውትረን የምናስታውስ ከሆነ የእምነታችንን መሠረት እናጠናክራለን።—1 ቆሮ. 3:12, 13
ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ድርጅቱን እየመራው ነው
13. የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ሕዝቦች መሆናቸውን መጠራጠር ብንጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
13 የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ሕዝቦች መሆናቸውን መጠራጠር ብንጀምር እንዲህ ያለው ጥርጣሬ ሥር እንዲሰድ ልንፈቅድለት አይገባም። ከዚህ ይልቅ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን በመጠየቅ ጥርጣሬያችንን ማስወገድ እንችላለን፦ ‘ሕይወታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ለመምራት ልባዊ ጥረት እያደረጉ ያሉት እነማን ናቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ የተመሠረተ ትምህርት የሚያስተምሩት እነማን ናቸው?’ (2 ጢሞ. 4:3, 4) ‘በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ እያደረጉ ያሉት እነማን ናቸው?’—ማቴ. 7:20, 21
14. የይሖዋ ምሥክሮች ማቴዎስ 24:14 እንዲፈጸም ምን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው?
14 በዛሬው ጊዜ የአምላክ ፈቃድ በሁሉም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ ነው። ታዲያ ኢየሱስ በተናገረው መሠረት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ምሥራቹን እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው? (ማቴ. 24:14) መልሱ ግልጽና የማያሻማ ነው። አምላክ የስብከቱን ሥራ ለማሠራት ሕዝቦቹን ማለትም የይሖዋ ምሥክሮችን እየተጠቀመ ነው። ከ240 በሚበልጡ አገሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበክን ያለነው እኛ ብቻ ነን። ይህን ሥራ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ስናከናውን ቆይተናል። ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ሥራ የስብከቱና የማስተማሩ ሥራ ነው።—ማቴ. 28:19, 20
15. የይሖዋ ምሥክሮች በዛሬው ጊዜ የአምላክ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉት እንዴት ነው? (ማቴዎስ 6:9፤ ኢሳይያስ 43:10)
15 ማቴዎስ 6:9ን እና ኢሳይያስ 43:10ን አንብብ። በአምላክ ስም ተጠርተናል፤ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራታችንም ያኮራናል። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ይህን ስም ባያውቀውም እኛ ግን የአምላክን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ትክክለኛው ቦታ መልሰነዋል። የአምላክ ስም አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ይገኛል።
16. በዮሐንስ 13:34, 35 ላይ የሚገኘውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ። ፍቅርና አንድነት የሰፈነበት የወንድማማች ማኅበራችን በዘመናችን እየተፈጸመ ያለ ተአምር ነው። ጥላቻ በነገሠበትና በተከፋፈለው በዚህ ዓለም ውስጥ የትም ቦታ እንዲህ ያለ ነገር የለም። የመጣነው ከተለያየ የዓለም ክፍል ነው፤ አስተዳደጋችንና ባሕላችንም ቢሆን የተለያየ ነው፤ ያም ቢሆን በመካከላችን ፍቅርና ሰላም ለማስፈን የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። በሌላ አካባቢ የሚገኝ ጉባኤ ተካፍለህ ታውቃለህ? እንዲህ ስታደርግ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነት ለማስተዋል ሞክር። ይህም በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ እያደረጉ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል። ይህን ማስታወሳችን ምንም ዓይነት የእምነት ፈተና ቢያጋጥመን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመኖር ይረዳናል።
ፍቅርና አንድነት የሰፈነበት የወንድማማች ማኅበራችን በዘመናችን እየተፈጸመ ያለ ተአምር ነው (አንቀጽ 16ን ተመልከት)a
ፈጽሞ ከይሖዋ አትራቅ
17-18. ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? ሆኖም በልበ ሙሉነት ምን ማለት እንችላለን?
17 የምንኖረው ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን ውስጥ ስለሆነ ሁላችንም ከባድ ችግሮች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞ. 3:1, 13) በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት ያደረገውን አንድ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መረዳት ሊከብደን ይችላል። አሊያም ደግሞ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በተሳሳተ መንገድ ሊረዱን ወይም ስሜታችንን ሊጎዱት ይችላሉ። ያጋጠመን ችግር ወዲያውኑ እልባት ላያገኝ ወይም ለጥያቄያችን መልስ ላናገኝ እንችላለን።
18 እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ስሜታችን ሊረበሽ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ሕዝቦች መሆናቸውን እርግጠኞች ከሆንን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን መቀጠል እንችላለን። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንዳለው እኛም ይሖዋን “ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” እንለዋለን።
መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት
a የሥዕሉ መግለጫ፦ አውቶቡስ ውስጥ ያሉ እናትና ልጅ አገልግሎት ላይ ያሉ የእምነት አጋሮቻቸውን በደስታ ሲመለከቱ።