ከሰኔ 15-21, 2026
መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!
ለመከራ ትክክለኛው እይታ ይኑርህ
“ጭንቀትና ችግር ቢደርስብኝም ትእዛዛትህን ምንጊዜም እወዳለሁ።”—መዝ. 119:143
ዓላማ
ለሚደርስብን መከራ ትክክለኛውን እይታ መያዛችን በተሳካ ሁኔታ እንድንቋቋመው ይረዳናል።
1-2. የሚደርስብንን መከራ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
በእምነትህ ምክንያት ከቤተሰቦችህ ወይም ከባለሥልጣናት ተቃውሞና ስደት እየደረሰብህ ነው? ከዕድሜ መግፋት ወይም ከጤና እክል ጋር እየታገልክ ነው? ሞት የምትወደውን ሰው ነጥቆሃል? እንደ ብዙዎቹ የይሖዋ ውድ በጎች አንተም “በችግርና በሐዘን የተሞላ” ሕይወት እየመራህ ይሆናል።—መዝ. 90:10
2 የሚደርስብንን ማንኛውንም መከራ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ለመከራው ትክክለኛ እይታ ሊኖረን ይገባል። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሹፌር መኪና ሲነዳ መንገዱን አጥርቶ ማየት ያስፈልገዋል። መስተዋቱ ከቆሸሸ ወይም በጉም ከተሸፈነ መንገዱ ላይ ያሉትን መሰናክሎች በትክክል ማየት አይችልም። መስተዋቱ ንጹሕ ከሆነ ግን ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ መጓዝና መሰናክሎች ሲያጋጥሙት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይችላል። እኛም በተመሳሳይ ለሚያጋጥመን መከራ ይሖዋ እንዲኖረን የሚፈልገው ዓይነት እይታ ካለን መከራውን በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ (1) ለመከራ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛው እይታ ምንድን ነው? (2) የተሳሳተ እይታ መያዛችን የሚጎዳን እንዴት ነው? እንዲሁም (3) መከራ ሲደርስብን ትክክለኛውን እይታ ይዘን ለመቀጠል ምን ማድረግ እንችላለን?
መከራን በተሳካ ሁኔታ መወጣት የምንችለው ትክክለኛው እይታ ካለን ብቻ ነው (አንቀጽ 2ን ተመልከት)
ለመከራ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ እይታ
3. በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ስላለን ሕይወት የትኛውን እውነታ አምነን መቀበል አለብን?
3 በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ መከራ አይቀሬ ነው። ሁላችንም ፍጽምና ይጎድለናል፤ እንዲሁም የምንኖረው ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ነው። ስለዚህ መከራ በሁሉም ሰው ላይ ይደርሳል። ይህ ሥርዓት ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ ደግሞ የሚያጋጥሙን ችግሮች እየበዙ እንደሚሄዱ እንጠብቃለን። ወንጀል እንዲሁም ሰው ሠራሽም ሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች እየተበራከቱ መሄዳቸው አይቀርም። (ማቴ. 24:8፤ 2 ጢሞ. 3:13) ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በአሁኑ ወቅት ቢያስተካክል የዚህ ዓለም ገዢ የሆነውን ሰይጣንን መርዳት ይሆንበታል። ስለዚህ በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስከኖርን ድረስ “ክፉ ጊዜ” ያጋጥመናል።—መክ. 9:12
4. ክርስቲያኖች ተጨማሪ መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
4 ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት ተጨማሪ መከራ ይደርስብናል። ኢየሱስ ተከታዮቹ በእምነታቸው ምክንያት ስደት እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ማቴ. 24:9፤ ዮሐ. 16:2) ይህን ስለምናውቅ ስደት ሲደርስብን እምነታችን አይናወጥም። (1 ተሰ. 3:3, 4) ከዚህ ይልቅ በታማኝነት እንጸናለን። እስከጸናን ድረስ ደግሞ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። በተጨማሪም ስንጸና ሰይጣን በይሖዋ ላይ ላነሳው ግድድር መልስ መስጠት እንችላለን። ሰይጣን፣ ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉት ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ነው የሚል ክስ ሰንዝሯል። ክሱ እውነት መሆኑን ለማሳየት ደግሞ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ከባድ መከራ ያደርሳል። (ኢዮብ 1:9-11) ለይሖዋ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ስንጸና በዚህ ጽንፈ ዓለማዊ ጥያቄ ከይሖዋ ጎን እንደቆምን እናሳያለን፤ ልቡንም እናስደስተዋለን።—ምሳሌ 27:11
5. ከመክብብ 7:13, 14 ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
5 ይሖዋ መከራ እንዲደርስብን ይፈቅዳል። ይሖዋ መቼም ቢሆን መጥፎ ነገር አያደርግም፤ ወይም በክፉ ነገር አይፈትነንም። (ያዕ. 1:13) ታዲያ ንጉሥ ሰለሞን “ክፉ ቀን” ‘የእውነተኛው አምላክ ሥራ’ እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው? (መክብብ 7:13, 14ን አንብብ፤ ግርጌ) ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እንዲሆን የፈቀደውን ነገር እሱ ራሱ እንዳደረገው አድርጎ ይገልጻል። እዚህ ጥቅስ ላይም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ሰለሞን ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? አንደኛ፣ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ስላለን ሕይወት እውነታውን አምነን መቀበል ይኖርብናል። በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ቀንም ይኖራል፤ ክፉ ቀንም ይኖራል። የጥሩ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ በጥሩ ቀን እሱን ማመስገን ይኖርብናል። ሁለተኛ ደግሞ፣ ሰለሞን የተናገረው ነገር ‘ወደፊት የሚደርስብንን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ እርግጠኞች መሆን እንደማንችል’ ያስገነዝበናል። ነገ ጥሩ ቀን ይሁን መጥፎ ማወቅ የምንችልበት መንገድ የለም። ጥሩ ሰዎችም ሆኑ መጥፎ ሰዎች ያልተጠበቁ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።
በሰይጣን ዓለም ውስጥ እስከኖርን ድረስ ጥሩ ቀንም፣ መጥፎ ቀንም ያጋጥመናል፤ ይህን አምነን መቀበል ይኖርብናል (አንቀጽ 5ን ተመልከት)
6. ይሖዋ መከራ እንዲደርስብን የሚፈቅደው ለምን ሊሆን ይችላል? (ዕብራውያን 12:7, 11)
6 በመከራ ውስጥ ስናልፍ ይሖዋ በራሳችን ሳይሆን በእሱ እንድንታመን ያስተምረናል። ይሖዋ እየደረሰብን ያለውን ነገር በትኩረት ይመለከታል፤ ስንሠቃይ ያዝናል። “ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ሸለቆ” ውስጥ እንድናልፍ ቢፈቅድም እንኳ እኛን መምራቱን ይቀጥላል፤ ፍቅሩን ያሳየናል፤ እንዲሁም ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል። (መዝ. 23:4) በተጨማሪም የሚደርስብን መከራ ድክመቶቻችንን ለይተን እንድናውቅና ባሕርያችንን እንድናሻሽል ይረዳናል። (ዕብራውያን 12:7, 11ን አንብብ።) ለምሳሌ ኢዮብ ይበልጥ ትሕትና ማዳበር ያስፈልገው ነበር። በኢዮብ ላይ የደረሰውን መከራ ያመጣው ይሖዋ ባይሆንም መከራው እንዲደርስበት ፈቅዷል፤ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ኢዮብ አስፈላጊ ትምህርቶችን እንዲያገኝ አድርጓል። (ኢዮብ 42:1-6) እርግጠኛ የምንሆንበት አንድ ነገር አለ፤ ይሖዋ እንዲደርስብን የሚፈቅደው የትኛውም መከራ ዘላቂ ጉዳት አያስከትልብንም። የሚደርስብንን መከራ በጽናት ስንቋቋም ‘ሙሉ በሙሉ ድል አድራጊዎች’ እንሆናለን።—ሮም 8:35-39
7. በእምነትህ ምክንያት ስደት እየደረሰብህም ደስተኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?
7 ስደት እየደረሰብንም ደስተኛ መሆን እንችላለን። በእምነትህ ምክንያት ስደት እየደረሰብህ ከሆነ ይሖዋ እንደተወህ ሊሰማህ አይገባም። እንዲያውም እንዲህ ያለ ተቃውሞ እየደረሰብህ መሆኑ የእሱ ሞገስ እንዳለህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ማቴ. 5:10-12) ትክክለኛው እይታ ካለህ ስደት ሲደርስብህ ልክ እንደ ሐዋርያቱ ልበ ሙሉና ደስተኛ ትሆናለህ። (ሥራ 5:40-42) በተጨማሪም ሰዎች እውነትን እንዲያውቁና ‘አምላክን እንዲያከብሩ’ የመርዳት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። (1 ጴጥ. 2:12) ይሖዋ ዮሴፍን የረዳውና የባረከው መከራው ካበቃ በኋላ ብቻ ሳይሆን እዚያው መከራ ውስጥ እያለም ጭምር ነው። አንተም በመከራ ውስጥ እያለህም የይሖዋን በረከት ማጣጣም ትችላለህ።—ዘፍ. 39:3, 23
8. እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያነሳሳ ምን ተጨማሪ ምክንያት አለን?
8 የሚደርስብን መከራ ማብቃቱ አይቀርም። የኢዮብ ታሪክ ይህን ያረጋግጥልናል። የኢዮብ መከራ ከጊዜ በኋላ ያበቃ ከመሆኑም ሌላ “ይሖዋ ከፊተኛው የኢዮብ ሕይወት ይልቅ የኋለኛውን አብዝቶ [ባርኳል]።” (ኢዮብ 42:12) አንተም ‘የፊተኛው ሕይወትህ’ ማለትም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለህ አጭር ሕይወት በመከራ የተሞላ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ ‘በኋለኛው ሕይወትህ’ ማለትም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልህ ቃል ገብቷል። ይህን ማሰብህ እስከ መጨረሻው ለመጽናት ያነሳሳሃል!—ማቴ. 24:13
የተሳሳተ እይታ መያዛችን የሚጎዳን እንዴት ነው?
9. ለሚደርስብን መከራ የተሳሳተ እይታ ካለን ምን ጉዳት ሊደርስብን ይችላል?
9 መከራ ሲደርስብን የተሳሳተ እይታ ካለን በራሳችን ላይ ተጨማሪ ችግር ልናመጣ እንችላለን። ምን ዓይነት የተሳሳተ እይታ ሊኖረን ይችላል? ለምሳሌ መከራውን ይሖዋ እንዳመጣብን እናስብ ይሆናል። ኢዮብ መጀመሪያ ላይ መከራውን ያመጣበት ይሖዋ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ይህ ደግሞ “ከአምላክ ይልቅ ራሱን ጻድቅ ለማድረግ” እንዲሞክር አነሳስቶታል። (ኢዮብ 32:2) ናኦሚም መጀመሪያ ላይ፣ ለደረሱባት ችግሮች ይሖዋን ተጠያቂ አድርጋ ነበር። (ሩት 1:13, 20, 21) ኢዮብና ናኦሚ ይህን የተሳሳተ እይታቸውን ይዘው ቢቀጥሉ ኖሮ ከይሖዋ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ይበላሽ ነበር። (ምሳሌ 19:3) ይሖዋ ግን ለችግሮቻቸው ያላቸውን አመለካከት እንዲያስተካክሉ ረድቷቸዋል፤ እንዲሁም ለታማኝነታቸው ባርኳቸዋል።
10. መከራ ሲደርስብን ምን ዓይነት ጥርጣሬ ሊያድርብን ይችላል?
10 ይሖዋ መከራ እንዳመጣብን ባይሰማንም እንኳ ‘ይሖዋ ትቶኝ ይሆን?’ ብለን ማሰብ ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ያለው አፍራሽ አመለካከት ጉልበታችንን ሊያዳክመው ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ንጉሥ ዳዊትም ሆነ ነቢዩ ዕንባቆም መከራ በደረሰባቸው ጊዜ ይሖዋ ጸሎታቸውን እየሰማ መሆኑን ተጠራጥረው ነበር። (መዝ. 10:1፤ ዕን. 1:2) ያም ቢሆን መጸለያቸውን አላቆሙም። ይሖዋም ጸሎታቸውን ሰምቶ ረድቷቸዋል። ለአንተም እንዲሁ ያደርግልሃል።—መዝ. 10:17
11. ለመከራ ትክክለኛው አመለካከት ከሌለን ምን ሊያጋጥመን ይችላል?
11 ስለ መከራ ትክክለኛው እይታ ከሌለን መከራ ሲደርስብን ልንደናገጥ እንችላለን። ምናልባትም ‘እንዴት በእኔ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ይደርሳል?’ ብለን እናስብ ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:12) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ከባድ ስደት እንደሚደርስበትና እንደሚገደል መቀበል ከብዷቸው ነበር። (ሉቃስ 18:33, 34) ኢየሱስ ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው በግልጽ ቢናገርም ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሱስ ላይ እንዲህ ያለ መከራ እንደማይደርስ ተሰምቶት ነበር። ኢየሱስ ግን በዚህ መንገድ ለማሰብ ፈቃደኛ አልነበረም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የይሖዋን ፈቃድ እንዳያደርግ እንቅፋት እንደሚሆንበት አውቋል። ስለዚህ ጴጥሮስን ገሥጾታል። (ማር. 8:31-33) ኢየሱስ ከሞተ በኋላም ጭምር ደቀ መዛሙርቱ መከራ መቀበልና መሞት ያስፈለገው ለምን እንደሆነ አልገባቸውም ነበር። ኢየሱስ ግን ተስፋ አልቆረጠባቸውም። ከሞት ከተነሳ በኋላ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በማብራራት’ ስለደረሰበት መከራ ትክክለኛው እይታ እንዲኖራቸው ረዳቸው። (ሉቃስ 24:25-27, 32, 44-48) ኢየሱስ ባስተማራቸው ነገር ላይ ማሰላሰላቸው እነሱም በቅርቡ ለሚያጋጥማቸው ስደት እንዲዘጋጁ ይረዳቸዋል። እኛም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ስደትና ስለ መከራ በሚናገራቸው ሐሳቦች ላይ በማሰላሰል ከወዲሁ ራሳችንን ማዘጋጀት እንችላለን።
12. ስላለንበት ሁኔታ የተሳሳተ እይታ ካለን ምን ሊፈጠር ይችላል?
12 ስላለንበት ሁኔታ የተሳሳተ እይታ ካለን ችግሩን ከሆነው በላይ አግዝፈን ልንመለከተው እንችላለን። ኢየሱስ በወይን እርሻው ላይ ስለተቀጠሩት ሠራተኞች የተናገረው ምሳሌ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። አንዳንዶቹ ሠራተኞች የሚገባቸው ደሞዝ እንዳልተሰጣቸው ስለተሰማቸው አዝነው ነበር። የእርሻው ባለቤት ግን ‘ምንም የበደላቸው ነገር እንደሌለ’ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 20:10-13) ሠራተኞቹ ቅር የተሰኙት አግባብ ያልሆነ ነገር ተፈጽሞባቸው ሳይሆን የጠበቁት ነገር የተሳሳተ ስለነበረ ነው። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል። ለምሳሌ እንዲህ የሚሰማቸው የሚፈልጉትን የአገልግሎት መብት ሳያገኙ ሲቀሩ ወይም ያላቸውን የአገልግሎት መብት ሲያጡ ሊሆን ይችላል። ታዲያ መከራ ሲያጋጥመን ትክክለኛውን እይታ ለመያዝ ምን ይረዳናል?
መከራ ሲያጋጥመን ትክክለኛውን እይታ ለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን?
13. መከራ ሲያጋጥመን ምን ሊከብደን ይችላል?
13 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መከራ ምን እንደሚል ጠንቅቀህ ታውቅ ይሆናል። ምናልባትም መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት እነዚህን ሐሳቦች ጠቅሰህላቸው ይሆናል። መከራው በአንተ ላይ ሲደርስ ግን ትክክለኛውን እይታ መያዝ ሊከብድህ ይችላል። ለምሳሌ ይሖዋ እየቀጣህ እንደሆነ ወይም ጸሎትህን መስማት እንዳቆመ ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ትክክለኛውን እይታ ለመያዝ ምን ማድረግ ትችላለህ?
14. በመከራ ውስጥ ስትሆን ምን ዓይነት ጸሎት ማቅረብ ትችላለህ? (ፊልጵስዩስ 4:13)
14 ይሖዋ እንዲረዳህ ጠይቀው። ስለደረሰብህ መከራ እንዲሁም መከራው ስላሳደረብህ ስሜት ንገረው። በጸሎትህ ላይ፣ ይሖዋ ምን ዓይነት እርዳታ እንዲሰጥህ እንደምትፈልግ ለይተህ መጥቀስ ትችላለህ። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ ጠይቀው። መንፈሱን ካገኘህ ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬና ጥበብ ይኖርሃል። ሆኖም ይሖዋ ለጸሎትህ የሚሰጠው መልስ ከጠበቅከው የተለየ ሊሆን እንደሚችል አትርሳ። (ኤፌ. 3:20) ለምሳሌ መላእክቱን ወይም ወንድሞችህንና እህቶችህን ተጠቅሞ ሊረዳህ ይችላል። (መዝ. 34:7) እንግዲያው ይሖዋ ጸሎትህን የሚመልስበት መንገድ ምንም ሆነ ምን እርዳታውን አመስግነህ ተቀበል። ያጋጠመህን የትኛውንም ሁኔታ ለመቋቋም በሚያስችል መጠን መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።
15. መከራን በጽናት ለመቋቋም ምን ይረዳሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 መንፈሳዊ ልማድህን አታቋርጥ። የበፊቱን ያህል ማድረግ ባትችል እንኳ አቅምህ የፈቀደውን ያህል በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተካፈል። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ይበልጥ የሚያስፈልገን “ጭንቀትና ችግር” በሚያጋጥመን ወቅት ነው። (መዝ. 119:143) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህንና ማጥናትህን እንዲሁም በዚያ ላይ ማሰላሰልህን ቀጥል። አቅምህ በፈቀደው መጠን በአገልግሎት ለመካፈል ጥረት አድርግ። በስብሰባዎች ላይ ተገኝ፤ እንዲሁም ተሳትፎ አድርግ። ብቻህን መሆን ቢያሰኝህም እንኳ ከወንድሞችህና ከእህቶችህ አትራቅ።—ምሳሌ 18:1
አቅምህ የፈቀደልህን ያህል በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትረህ ተካፈል (አንቀጽ 15ን ተመልከት)
16. መከራ ሲደርስብህ ምን ዓይነት ጥርጣሬ ሊያድርብህ ይችላል? እነዚህን ጥርጣሬዎች ማሸነፍ የምትችለውስ እንዴት ነው? (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5)
16 ጥርጣሬህን አሸንፍ። መከራ በሚደርስብህ ጊዜ ራስህን ወይም ይሖዋን በተመለከተ ጥርጣሬ ሊያድርብህ ይችላል። እነዚህ ጥርጣሬዎች እንደ “ምሽግ” ጠንካራ ሊሆኑ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5ን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስና ድርጅቱ ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው ‘ስለ አምላክ የሚገልጸው እውቀት’ እነዚህን ጥርጣሬዎች ለማሸነፍ ይረዳሃል። ለምሳሌ ‘የይሖዋን ሞገስ አጥቼ ይሆን?’ የሚል ጥርጣሬ ካደረብህ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ አጥና። ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ብዙ መከራ ደርሶበታል፤ ሆኖም እነዚህ መከራዎች የደረሱበት መሆኑ በራሱ የይሖዋንና የኢየሱስን ሞገስ እንዳገኘ ይበልጥ እንዲተማመን አድርጎታል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ‘ከዚህ ቀደም ለሠራኋቸው ኃጢአቶች እውነት ይሖዋ ይቅር ብሎኛል?’ ብለህ ከተጠራጠርክ ደግሞ ይሖዋ በእርግጥ ይቅር ባይ መሆኑን የሚያሳዩ ጥቅሶችን ዘርዝረህ ጻፍ። (ኢሳ. 43:25) ከዚያም እነዚህን ጥቅሶች እያነበብክ አሰላስልባቸው። (መዝ. 119:97) በሌላ በኩል ደግሞ፣ ያጋጠመህ ከባድ መከራ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚጠብቅ የገባውን ቃል እንድትጠራጠር አድርጎህ ሊሆን ይችላል። ከሆነ፣ ‘አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ እንዲሁም ‘ምንም ዓይነት መከራ ቢያጋጥመን ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?’ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ምርምር አድርግ። (መዝ. 91:9-12) በተጨማሪም ከባድ መከራዎችን በጽናት የተቋቋሙ ወንድሞችንና እህቶችን ተሞክሮ አንብብ።a
17. መከራ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 አሁን የምትገኘው ይህ ነው የሚባል ከባድ ችግር የሌለበት ጥሩ ቀን ላይ ነው? እንደዚያ ከሆነ፣ ላሉህ መልካም ነገሮች ይሖዋን አመስግነው። (መክ. 7:14) መከራ ሲያጋጥምህ ደግሞ ትክክለኛውን እይታ ለመያዝና በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት ለማጠናከር ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ መከራውን ‘በጽናት መቋቋም እንድትችል መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልሃል።’ (1 ቆሮ. 10:13) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መከራ ሲያጋጥማቸው እነሱን መርዳት የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህን ጉዳይ በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ
a ለምሳሌ jw.org ላይ “ከባድ ውጣ ውረዶችን ያለፈ ደስተኛ ቤተሰብ” የሚለውን የሕይወት ታሪክ ልታነብ ትችላለህ። የሕይወት ታሪኩ ወንድም ዴቪድ ሜዛ ልጁን በሞት ባጣበት ወቅት እሱና ቤተሰቡ ይህን መከራ የተቋቋሙት እንዴት እንደሆነ ይተርካል።