ከግንቦት 25-31, 2026
መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’
ጥልቅ ማስተዋል ለስኬት ያበቃል
“አንድን ነገር ጠለቅ ብሎ የሚያስተውል ሰው ስኬታማ ይሆናል።”—ምሳሌ 16:20
ዓላማ
ጥልቅ ማስተዋል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተሳካ ሁኔታ ለማለፍ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. ጥልቅ ማስተዋል ምንድን ነው? የሚጠቅመንስ እንዴት ነው?
ሌሎች አክብሮት እንዳላሳዩህ ተሰምቶህ ያውቃል? አንድ ሰው በተሳሳተ መንገድ ተረድቶህ ወይም ቅር አሰኝቶህ ያውቃል? ወይም ደግሞ የሚያስፈራ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ከባድ ነው። ደስ የሚለው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህም ሆነ በሌሎች በርካታ ሁኔታዎች ውስጥ የሚጠቅመን አንድ ባሕርይ እንዳለ ይናገራል፤ ይህም ጥልቅ ማስተዋል ነው።
2 ጥልቅ ማስተዋል ፊት ለፊት ከሚታየው አልፎ የመመልከት ችሎታ ነው። ጥልቅ ማስተዋል ካለን አንድ ነገር የሆነበትን ወይም አንድ ሰው የሆነ ነገር ያደረገበትን ምክንያት ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን። ይህም ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ለመውሰድ ይረዳናል። ለምሳሌ ጥልቅ ማስተዋል ‘ከንፈራችንን እንድንገታ’ እንዲሁም መቼ ‘ጸጥ ማለት’ እንዳለብን እንድናውቅ ይረዳናል። (ምሳሌ 10:19፤ መዝ. 4:4) ቁጣችንን እንድንቆጣጠርና የሚደርስብንን በደል ችላ ብለን እንድናልፍም ይረዳናል። በተጨማሪም የሚሰጠንን እርማትና ምክር እንድንቀበል ይረዳናል። (ምሳሌ 19:20) ጥልቅ ማስተዋል በማዳበር ንግግራችንንና ድርጊታችንን የምንቆጣጠር ከሆነ ይሖዋን እናስደስታለን። ይህ ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም ሆነ በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች እንጠቅማለን። በተለይ በጣም የሚያበሳጭ ወይም ስሜታዊ የሚያደርግ ሁኔታ ሲያጋጥመን ጥልቅ ማስተዋል ይረዳናል። ጥልቅ ማስተዋል ትሑት እንድንሆን፣ እንድንረጋጋና በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እስቲ እንመልከት።
ኩሩ ከመሆን ይልቅ ትሑት ሁን
3. ንዕማን ማን ነበር?
3 ስኬታማ መሆን ከፈለግን ከኩራት መራቅ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 5:5) ጥልቅ ማስተዋል እንዲህ ለማድረግ ይረዳናል። እንዴት? የንዕማንን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የሠራዊት አለቃ የሆነው ንዕማን ከእስራኤል በስተ ሰሜን በምትገኘው በሶርያ የሚኖር የተከበረ ሰው ነበር። ሆኖም ይህ ሰው አስከፊ የቆዳ በሽታ ነበረበት።—2 ነገ. 5:1
4. ንዕማን አስተዋይ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
4 የንዕማን ሚስት አንዲት እስራኤላዊት አገልጋይ ነበረቻት። ይህች አገልጋይ በእስራኤል ያለው ነቢይ ባሏን ከሕመሙ ሊፈውሰው እንደሚችል ለእመቤቷ ነገረቻት። (2 ነገ. 5:2, 3) ንዕማን ይህን ሲሰማ ‘ከጠላት አገር የመጣች አንዲት አገልጋይ፣ ያውም ትንሽ ልጅ ምን ጠቃሚ ነገር ልትነግረኝ ትችላለች?’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። እሱ ግን እንዲህ አላደረገም። በኩራት ተነሳስቶ ሐሳቧን ከማጣጣል ይልቅ የተናገረችውን ሐሳብ በቁም ነገር ተመልክቶታል። ይህም ትሑትና አስተዋይ እንደሆነ ያሳያል። የሶርያን ንጉሥ ፈቃድ ጠይቆ ከበሽታው ለመፈወስ ወደ እስራኤል ሄደ።—2 ነገ. 5:4, 5
5. ንዕማን እስራኤል ከደረሰ በኋላ ምን አጋጠመው?
5 ንዕማን ከሕመሙ እንደሚፈወስ ተስፋ በማድረግ በመጀመሪያ የእስራኤል ንጉሥ ወደሆነው ወደ ኢዮራም ቤት ሄደ። ኢዮራም ግን የሶርያ ንጉሥ ንዕማንን ወደ እሱ የላከው ነገር ሊፈልገው አስቦ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ነቢዩ ኤልሳዕ ስለዚህ ጉዳይ ሲሰማ ንዕማንን ወደ እሱ እንዲልከው ለኢዮራም ነገረው። (2 ነገ. 5:6-9) ሆኖም ቀጥሎ የተፈጠረው ነገር ንዕማን ከጠበቀው የተለየ ነበር። ኤልሳዕ ከቤቱ ወጥቶ እንኳ አላነጋገረውም። ከዚህ ይልቅ ከሕመሙ ለመፈወስ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲነግረው መልእክተኛ ላከበት።—2 ነገ. 5:10
6. (ሀ) ንዕማን መልእክተኛው በሰጠው መመሪያ ያልተደሰተው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የንዕማን አገልጋዮች ጥልቅ ማስተዋል እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ? (2 ነገሥት 5:13, 14)
6 መጀመሪያ ላይ ንዕማን፣ ኤልሳዕ መልእክተኛ በመላኩም ሆነ መልእክተኛው በሰጠው መመሪያ አልተደሰተም። እንዲያውም “ተቆጥቶ ለመሄድ ተነሳ።” (2 ነገ. 5:11, 12) ለምን? ምናልባት ለአንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚገባው ዓይነት ክብር እንዳልተሰጠው ስለተሰማው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ንዕማን፣ ኤልሳዕ የሰጠው መመሪያ ለሶርያ አክብሮት እንደሌለው እንደሚያሳይ ተሰምቶት ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ንዕማን ከበሽታው የመፈወስ ሐሳቡን ትቶ ወደ ቤቱ ለመመለስ ወስኖ ነበር። ይሁንና ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው አገልጋዮቹ ውሳኔውን መለስ ብሎ እንዲያጤን ለመኑት። ንዕማንም ኩራቱን ዋጥ አድርጎ ኤልሳዕ ያለውን ነገር በትሕትና አደረገ። ይህን የጥበብ እርምጃ በመውሰዱ ከበሽታው ሊፈወስ ችሏል።—2 ነገሥት 5:13, 14ን አንብብ።
7. ከንዕማን ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ምሳሌ 22:4) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
7 ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም ፊት ለፊት ከሚታየው ነገር አልፈን በመመልከት ጥልቅ ማስተዋል እንዳለን ማሳየት እንችላለን፤ ይህም የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ ይጨምራል። ስሜታችን እንዲቆጣጠረን ባለመፍቀድም ጥልቅ ማስተዋል እንዳለን ማሳየት እንችላለን። በተጨማሪም ጥልቅ ማስተዋል ትሑት እንድንሆን ያነሳሳናል። ትሑት ከሆንን ሁሉንም ነገር እንደማናውቅና አንዳንድ ጊዜ የሌሎች እርዳታ ሊያስፈልገን እንደሚችል አምነን እንቀበላለን። በተለይ ደግሞ የይሖዋ እርዳታ በጣም እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለን። ንዕማን በወቅቱ የይሖዋ አገልጋይ ባይሆንም ሌሎችን በትሕትና በማዳመጥ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው አሳይቷል። የሚስቱ አገልጋይ የሆነችውን እስራኤላዊት ልጅ፣ የራሱን አገልጋዮች፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ወኪል የሆነውን ኤልሳዕን መስማቱ ጥበበኛ እንደሆነ ያሳያል። ንዕማን ክብሩ እንደተነካ ቢሰማውም በስተ መጨረሻ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ችሏል። ይህም ለስኬት አብቅቶታል። እኛም አንዳንድ ጊዜ የተሰጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ላይጥመን ወይም አንድ ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ላይዋጥልን ይችላል። በዚህ ጊዜ ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ‘ልናገር ወይም ላደርግ ያሰብኩት ነገር ትሑት እንደሆንኩ ያሳያል ወይስ ኩራተኛ እንደሆንኩ?’ የሚለውን ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።—ምሳሌ 22:4ን አንብብ።
ሌሎች ምክር ሲሰጡን፣ አንድን ችግር ሲጠቁሙን ወይም ከይሖዋ ድርጅት መመሪያ ሲደርሰን በትሕትና በማዳመጥ የንዕማንን ምሳሌ መከተል እንችላለን (አንቀጽ 7ን ተመልከት)
ተበሳጭተህ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ራስህን አረጋጋ
8. መረጋጋት የሚከብደን ምን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ሊሆን ይችላል?
8 የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥመን ጥልቅ ማስተዋል በቁጣ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እንድንረጋጋ ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ሌሎች ደግነት በጎደለው መንገድ ሲያነጋግሩን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብን መበሳጨታችን የሚጠበቅ ነገር ነው። (ምሳሌ 22:4) ዳዊትና አቢጋኤል አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ባጋጠማቸው ወቅት ጥልቅ ማስተዋል እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
9. ናባል በዳዊት ላይ ምን በደል አደረሰበት?
9 እስቲ ታሪኩን በምናብህ ለመሣል ሞክር፦ ዳዊትና ሰዎቹ ስደተኛ ሆነው በፋራን ምድረ በዳ እየኖሩ ነው። (1 ሳሙ. 25:1) በዚያ አካባቢ የሚኖር ናባል የተባለ አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር። ዳዊትና ሰዎቹ በምድረ በዳ ሳሉ በደግነት ተነሳስተው የናባልን መንጎችና እረኞች ከጉዳት ይጠብቋቸው ነበር። (1 ሳሙ. 25:15, 16) በጎች የሚሸለቱበት ጊዜ ሲደርስ ዳዊት ለናባል መልእክተኞችን ልኮ የከበረ ሰላምታ አቀረበለት። ከዚያም የቻለውን ያህል ምግብ እንዲልክለት በትሕትና ጠየቀው። (1 ሳሙ. 25:6-8) ናባል ግን ዳዊትና ሰዎቹ ያደረጉለትን ነገር ሁሉ ከቁብ አልቆጠረውም። ጥያቄያቸውን አለማስተናገዱ ሳያንስ ሙልጭ አድርጎ ሰደባቸው።—1 ሳሙ. 25:10, 11
10. ዳዊትና አቢጋኤል ጥልቅ ማስተዋል እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? (1 ሳሙኤል 25:32, 33) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 አንተ በዳዊት ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? ዳዊት በጣም የተበሳጨበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም። እንዲያውም እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ ናባልን ለመግደል ቆርጦ ተነሳ! (1 ሳሙ. 25:13, 21, 22) መንገድ ላይ ሳለ ብልህ የሆነችው የናባል ሚስት አቢጋኤል ልታገኘው መጣች። አቢጋኤል ጥልቅ ማስተዋል እንዳላት ያሳየችው እንዴት ነው? ዳዊት የሰጠው ምላሽ የተጋነነ ቢሆንም ጥሩ ሰው እንደሆነ አስተውላ ነበር። በመሆኑም ቁጣውን እንዲቆጣጠር ልትረዳው ሞክራለች። ብዙ ስጦታ አመጣችለት፤ እንዲሁም በአክብሮት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጠችው። (1 ሳሙ. 25:18, 23-31) ዳዊትም አቢጋኤል የተናገረችውን ነገር በጥሞና በማዳመጥ ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው አሳይቷል። የተናገረችው ሐሳብ የይሖዋን አመለካከት የሚያንጸባርቅ እንደሆነ አስተውሎ ነበር። በዚህም የተነሳ ዳዊት ሊረጋጋና ከባድ ስህተት ከመፈጸም ሊተርፍ ችሏል።—1 ሳሙኤል 25:32, 33ን አንብብ።
ዳዊትና አቢጋኤል ጥልቅ ማስተዋል እንዳላቸው በማሳየታቸው የብዙ ሰው ሕይወት ሊተርፍ ችሏል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)
11. የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመን ጥልቅ ማስተዋል የሚረዳን እንዴት ነው? (ምሳሌ 19:11)
11 ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ጥልቅ ማስተዋል ለመቆጣት የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት በሚኖረን ጊዜም እንኳ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንድንሰጥ ይረዳናል። በተጨማሪም ንግግራችንና ድርጊታችን የሚያስከትለውን መዘዝ ቆም ብለን እንድናስብ ያነሳሳናል። (ምሳሌ 19:11ን አንብብ።) ዳዊት በአቢጋኤል እርዳታ፣ ይሖዋ ምን እንደሚሰማው ቆም ብሎ በማሰቡ ቁጣውን ሊቆጣጠር ችሏል። አንተም የሚያስቆጣ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥምህ ስሜታዊ ሆነህ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ቆም ብለህ አስብ። (ያዕ. 1:19) ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም ጊዜ ወስደህ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት አድርግ። ይህም እንድትረጋጋ ይረዳሃል።
12. ሌሎች ጥልቅ ማስተዋል እንድናሳይና እንድንረጋጋ ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
12 ይሖዋ፣ ዳዊት ሁኔታውን ጠለቅ ብሎ እንዲያስተውል ለመርዳት በአቢጋኤል እንደተጠቀመ ሁሉ እኛንም ሌሎችን ተጠቅሞ ሊረዳን ይችላል። እንግዲያው የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ስሜታዊ ሆነህ እርምጃ ከመውሰድህ በፊት አንድን የጎለመሰ ክርስቲያን ማማከርህ ጥሩ ሊሆን ይችላል፤ እሱም ጉዳዩን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድታየው ሊረዳህ ይችላል። (ምሳሌ 12:15፤ 20:18) በሌላ በኩል ደግሞ፣ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመውን ሰው የመርዳት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። ከሆነ፣ እንደ አቢጋኤል የይሖዋን አመለካከት እንዲገነዘብ ልትረዳው ትችላለህ። ሌሎች ቆም ብለው እንዲያስቡና እንዲረጋጉ ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክልህ አትጠራጠር።
በፍርሃት ከመዋጥ ይልቅ በይሖዋ ታመን
13. ጥልቅ ማስተዋል ፍርሃታችንን ለማሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
13 በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ፍርሃት ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ጥልቅ ማስተዋል ካለን፣ በዓለም ላይ ሊከሰት የሚችለው የትኛውም አስፈሪ ነገር ከይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይል ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ እናስታውሳለን፤ ይህም ፍርሃታችንን ለማሸነፍ ይረዳናል። (መዝ. 27:1) ይሖዋ ምንም መፍትሔ የሌላቸው የሚመስሉ ሁኔታዎችንም ጭምር እንድናልፍ ሊረዳን ይችላል። የነቢዩ ዮናስ ታሪክ ይህን ያስተምረናል። ዮናስ መንፈሳዊ ሰው ቢሆንም የተሰጠውን ከባድ ተልእኮ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ጥልቅ ማስተዋል ማዳበር አስፈልጎታል።
14. ዮናስ ይሖዋ የሰጠውን ተልእኮ መቀበል የከበደው ለምን ሊሆን ይችላል?
14 ይሖዋ ለዮናስ ከባድ ተልእኮ ሰጥቶት ነበር፤ ወደ ነነዌ ሄዶ ለነዋሪዎቿ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ነገረው። (ዮናስ 1:1, 2) አንተ ይህ ተልእኮ ቢሰጥህ ምን ይሰማህ ነበር? የአሦር ከተማ ወደሆነችው ወደ ነነዌ ለመድረስ ለአንድ ወር ያህል በእግር መጓዝ ይጠይቃል። በዚያ ላይ ደግሞ አሦራውያን ጨካኝና ዓመፀኛ በመሆናቸው የታወቁ ነበሩ። እንዲያውም ነነዌ “ደም አፍሳሿ ከተማ” ተብላ ተጠርታለች። (ናሆም 3:1, 7) በመሆኑም ዮናስ ተልእኮውን ከመቀበል ይልቅ ለመሸሽ ወሰነ።—ዮናስ 1:3
15. ዮናስ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጠናክር የረዳው ምንድን ነው? (ዮናስ 2:6-9)
15 ዮናስ በመሸሽ ላይ ሳለ ይሖዋ አስደናቂ በሆነ መንገድ ሕይወቱን በማዳን ኃይሉን አሳየው። (ዮናስ 1:15, 17) በዚህ ጊዜ ዮናስ አንድ ትልቅ ትምህርት አገኘ። ይሖዋ ከየትኛውም አደገኛ ሁኔታ ሊጠብቀው ስለሚችል ተልእኮውን መወጣት ሊያስፈራው እንደማይገባ ተገነዘበ። (ዮናስ 2:6-9ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን ተልእኮ መቀበል የሚችልበት ሁለተኛ አጋጣሚ ሲሰጠው ዮናስ ያለምንም ማቅማማት ወደ ነነዌ ሄደ፤ በአገልግሎቱም ትልቅ ስኬት አገኘ።—ዮናስ 3:5
16. የሚያስፈራ ሁኔታ ሲያጋጥመን ጥልቅ ማስተዋል የሚረዳን እንዴት ነው? (ምሳሌ 29:25) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
16 ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሰውን መፍራት ለይሖዋ አምልኮ ከማቅረብ እንዲያግደን ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም። (ምሳሌ 29:25ን አንብብ።) ዮናስ ጥልቅ ማስተዋል በማዳበሩ የአገልግሎት ምድቡ ባሉት አስቸጋሪ ገጽታዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ በይሖዋ ድጋፍ ላይ ማተኮር ችሏል። እኛም ይሖዋ ቀደም ሲል ባደረገልን እርዳታና ጥበቃ ላይ ካሰላሰልን የሚሰማንን ፍርሃት ማሸነፍ እንችላለን። በይሖዋ ታምነው አስፈሪ ሁኔታዎችንና ከባድ ኃላፊነቶችን በተሳካ ሁኔታ በተወጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተሞክሮ ላይ ማሰላሰላችንም ይጠቅመናል።a (ዕብ. 13:6) እንግዲያው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመታመን እንዲሁም ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ በመርዳት ጥልቅ ማስተዋል እንዳለን እናሳይ።
ከዮናስ ታሪክ እንደምንማረው ጥልቅ ማስተዋል የይሖዋን ትእዛዝ ለመፈጸምና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመወጣት ይረዳናል (አንቀጽ 16ን ተመልከት)
ጥልቅ ማስተዋልን ማግኘትና ጠብቆ ማቆየት
17. ጥልቅ ማስተዋልን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
17 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ጥልቅ ማስተዋል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተሳካ መንገድ ለመወጣት ይረዳናል። ይሁንና ጥልቅ ማስተዋልን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ከሁሉ የላቀው የጥልቅ ማስተዋል ምንጭ ይሖዋ ነው። እሱ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለአገልጋዮቹ ጥልቅ ማስተዋል ይሰጣቸዋል። (ነህ. 9:20፤ መዝ. 32:8) ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግና ስሜታችንን ለመቆጣጠር የሚረዳ ምክር ይሰጠናል። (መዝ. 119:97-101) መጽሐፍ ቅዱስን በትኩረት ካጠናን እንዲሁም ይሖዋ ኃያል የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ከጸለይን ጥልቅ ማስተዋል ማግኘት እንችላለን። ይህም ስላጋጠመን ጉዳይ የተሟላ ግንዛቤ ለማግኘት እንዲሁም በዚያ ሁኔታ ውስጥ ይሖዋን የሚያስደስተው እርምጃ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል።—ምሳሌ 21:11 ግርጌ
18. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
18 ከይሖዋ የሚገኘውን ጥልቅ ማስተዋል መፈለጋችንንና ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንቀጥል። (መዝ. 14:2) እንዲህ ካደረግን፣ መቼም ቢሆን “ከማስተዋል መንገድ” አንወጣም። (ምሳሌ 21:16) ይልቁንም በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ጥልቅ ማስተዋል እንዳለን ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን። ይህም ስኬታማ ያደርገናል።
መዝሙር 42 የአምላክ አገልጋይ ጸሎት
a ለምሳሌ ያህል “የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች” በሚለው ተከታታይ ርዕስ ሥር የወጣውን የጆርጂ ፖርኩልያንን ተሞክሮ JW ላይብረሪ ወይም jw.org ላይ አንብብ።