ከመጋቢት 23-29, 2026
መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን
ለቤዛው ያለኝን አድናቆት ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?
“ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል።”—2 ቆሮ. 5:14
ዓላማ
ሁላችንም ለቤዛው ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
1-2. የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምን እንድናደርግ ግድ ሊለን ይገባል? ለምንስ? (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
ከተደረመሰ ሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ አንድ ሰው ቢያድንህ ያ ሰው ባለውለታህ እንደሆነ አይሰማህም? ሰውየው ያዳናቸው ሌሎች ሰዎች ቢኖሩም አንተ ግን በግለሰብ ደረጃ አመስጋኝነትህን መግለጽ እንደምትፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። ግለሰቡ የዋለልህን ውለታ አቅልለህ መመልከት አትፈልግም።
2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ የወረስነው ኃጢአት ከሚያስከትልብን መዘዝ ራሳችንን ማዳን አንችልም። ሆኖም የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በሚከተሉት መንገዶች ይታደገናል፦ (1) ለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ይቅርታ ያስገኝልናል፤ (2) ከአለፍጽምናችን ሙሉ በሙሉ ይፈውሰናል፤ እንዲሁም (3) ከአምላክ ጋር ያስታርቀናል። በዚህም ምክንያት በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን። በእርግጥም ቤዛው ኢየሱስ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ያሳያል፤ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ሰዎችን በጣም ይወድ ነበር። (ምሳሌ 8:30, 31) ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።) ይህም ሲባል የኢየሱስ ፍቅር ለቤዛው ያለንን አድናቆት በሆነ መንገድ እንድናሳይ ሊገፋፋን ይገባል ማለት ነው።
ከሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ ላዳነን ሰው አመስጋኝ እንደምንሆን ሁሉ ከወረስነው ኃጢአት ላዳነን አምላክ አመስጋኝ ልንሆን ይገባል (አንቀጽ 1-2ን ተመልከት)
3. እያንዳንዱ ሰው ለቤዛው ያለውን አድናቆት የሚያሳይበት መንገድ የተለያየ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ቤዛው አንተን ምን እንድታደርግ ግድ ይልሃል? ለዚህ ጥያቄ እያንዳንዳችን የምንሰጠው መልስ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ሦስት ሰዎች ወደ ተመሳሳይ ቦታ ለመሄድ እየተዘጋጁ ነው እንበል። ሆኖም ሦስቱም የሚነሱት ከተለያየ ከተማ ነው። በመሆኑም ለጉዞ የሚመርጡት መንገድ ይለያያል። አንተም በተመሳሳይ ለቤዛው ያለህን አድናቆት የምታሳይበትን መንገድ የሚወስነው አሁን ላይ ከይሖዋ ጋር ያለህ ዝምድና የቱ ጋ ነው የሚለው ነው። ከዚህ አንጻር ይህ ርዕስ በሦስት ቡድኖች ላይ ትኩረት ያደርጋል፦ (1) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፣ (2) የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንዲሁም (3) ከመንጋው የራቁ በጎች።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች
4. ይሖዋ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ምን ይሰማዋል?
4 መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ከሆነ ይህን አስታውስ፦ ለምሥራቹ የሰጠኸው ምላሽ ይሖዋ ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ከሳባቸው ሰዎች መካከል እንደሆንክ የሚጠቁም ነው። (ዮሐ. 6:44፤ ሥራ 13:48) ‘ይሖዋ ልብን የሚመረምር አምላክ ነው።’ በመሆኑም ይሖዋ ስለ እሱ ለመማር የምታደርገውን ጥረት ይመለከታል፤ እንዲሁም የእሱን መሥፈርቶች ለመከተል የምታደርጋቸውን ለውጦች ሲያይ ይደሰታል። (ምሳሌ 17:3፤ 27:11) ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ ያገኘኸው በቤዛው የተነሳ ነው። (ሮም 5:10, 11) ይህን ፈጽሞ አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በፊልጵስዩስ 3:16 ላይ የተገለጸውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሆንክ ለቤዛው አድናቆት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጣቸውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ነው፦ “ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።” (ፊልጵ. 3:16) ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረግ፣ በሕይወት መንገድ ላይ የምታደርገውን ጉዞ ምንም ነገር እንዲያደናቅፍብህ አትፍቀድ።—ማቴ. 7:14፤ ሉቃስ 9:62
6. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አንድን ትምህርት መቀበል ወይም ለውጥ ማድረግ ከከበዳቸው ምን ማድረግ ይችላሉ? (ዘዳግም 30:11-14) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 በቅርቡ የተማርከውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መቀበል ከባድ ቢሆንብህስ? በዚያ ትምህርት ላይ ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም ይሖዋ ትምህርቱን በደንብ ለመረዳት እንዲያግዝህ በጸሎት ጠይቀው። (መዝ. 86:11) እንዲህ አድርገህም ትምህርቱን መረዳት ከከበደህ ለጊዜው ተወት አድርገው፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን አታቋርጥ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘውን አንድ ልማድ መተው ከባድ ቢሆንብህስ? ይሖዋ ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች የሚጠብቀው ነገር ከአቅማቸው በላይ እንዳልሆነ አስታውስ። በእሱ መሥፈርቶች መመራት ትችላለህ። (ዘዳግም 30:11-14ን አንብብ።) ደግሞም ይሖዋ እንደሚረዳህ ቃል ገብቶልሃል። (ኢሳ. 41:10, 13፤ 1 ቆሮ. 10:13) እንግዲያው ተስፋ አትቁረጥ። እያጋጠመህ ባለው ተፈታታኝ ሁኔታ ላይ ከማተኮር ይልቅ የቤዛውን ዝግጅት ጨምሮ ይሖዋ ባደረገልህ መልካም ነገሮች ላይ ትኩረት አድርግ። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ሲያድግ ‘ትእዛዛቱ ከባድ እንዳልሆኑ’ እየተረዳህ ትሄዳለህ።—1 ዮሐ. 5:3a
ይሖዋ መቼም ቢሆን ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይረዳናል (አንቀጽ 6ን ተመልከት)
7. እውነት ቤት ውስጥ ያደጉ ልጆች ስለ ምን ማሰላሰል ይችላሉ?
7 እውነት ቤት ውስጥ ያደግክ ልጅ ከሆንክ አንተም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነህ። እንዲያውም ወላጆችህ ካሏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለአንተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕ. 4:8፤ 1 ዜና 28:9) አንተ ቅድሚያውን ወስደህ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት ስታደርግ እሱም በምላሹ ወደ አንተ ይቀርባል። ይሖዋ የሚያይህ በቤተሰብ ደረጃ ብቻ አይደለም። ይሖዋ ሰዎችን የሚስበው በግለሰብ ደረጃ ነው፤ ይህም በእውነት ቤት ያደጉ ልጆችን ይጨምራል። በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ የከፈተልህ ምንድን ነው? ቤዛው ነው። ይህን ፈጽሞ አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም። (ሮም 5:1, 2) እንግዲያው በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ ከመገኘትህ በፊት ‘የኢየሱስ ሞት ለእኔ ምን ትርጉም አለው?’ ብለህ ለምን አታሰላስልም? ከዚያም ‘ለቤዛው ያለኝን አድናቆት ለማሳየት የትኞቹን መንፈሳዊ ግቦች ላወጣ እችላለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።b
የተጠመቁ ክርስቲያኖች
8. የተጠመቁ ክርስቲያኖች በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
8 የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ በቤዛው ላይ ያለህን እምነት በብዙ መንገዶች አሳይተሃል። ለምሳሌ ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተህ ለመኖር እርምጃ ወስደሃል። እምነትህን ለሌሎች በማካፈል ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ትእዛዝ ፈጽመሃል። እንዲሁም ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ተጠምቀሃል። ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በመቆምህ ምክንያት ተቃውሞ አጋጥሞሃል? (2 ጢሞ. 3:12) በታማኝነት መጽናትህ ለይሖዋ ያለህን ፍቅርና ይሖዋ በልጁ በኩል ላዘጋጀው ቤዛ ያለህን አድናቆት ያሳያል።—ዕብ. 12:2, 3
9. የተጠመቁ ክርስቲያኖች የትኛው አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል?
9 የተጠመቁ ክርስቲያኖች አንድ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ለቤዛው ያለን አድናቆት ሊቀንስ ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የኤፌሶን ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ላሳዩት ጽናት አመስግኗቸዋል። ሆኖም እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል።” (ራእይ 2:3, 4) ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት እንደምንረዳው፣ አንድ ክርስቲያን የሚያቀርበው አምልኮ ቀስ በቀስ የዘልማድ እየሆነ ሊመጣ ይችላል። ግለሰቡ ሊጸልይ፣ ስብሰባ ሊሄድ ወይም በአገልግሎት ሊካፈል ይችላል። ሆኖም እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው እንዲሁ በዘልማድ ነው። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈል የሚያነሳሳው ፍቅር አይደለም። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር የቀድሞውን ያህል ጠንካራ እንዳልሆነ ከተሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
10. ስለ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህ ‘ማሰላሰልና ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ እንዲሆን’ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 4:13, 15)
10 ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ስለ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቹ ‘እንዲያሰላስልና ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ እንዲሆን’ ነግሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:13, 15ን አንብብ።) በዚህ ምክር መሠረት፣ አምልኮህ የበለጠ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክር፤ እንዲህ ካደረግክ ‘በመንፈስ የምትቃጠል መሆን’ ትችላለህ። (ሮም 12:11) ለምሳሌ ለጉባኤ ስብሰባዎች በደንብ መዘጋጀት ትችላለህ፤ ይህም በስብሰባው ላይ በትኩረት ለመከታተል ይረዳሃል። ወይም የግል ጥናትህን በምታደርግበት ወቅት ጸጥ ያለ አካባቢ መምረጥ ትችላለህ፤ ይህም በምታጠናው ነገር ላይ በማሰላሰል ከጥናትህ የተሟላ ጥቅም እንድታገኝ ይረዳሃል። እሳት መንደዱን እንዲቀጥል እንደምንቆሰቁሰው ሁሉ እነዚህን ነገሮች ማድረግህ ቤዛውን ጨምሮ ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች ያለህን አድናቆት እንድታቀጣጥል ይረዳሃል። በተጨማሪም ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ባገኘናቸው ለየት ያሉ በረከቶች ላይ ለምን አታሰላስልም? እንዲህ ማድረግህ፣ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ላስቻለህ ለቤዛው ያለህ አድናቆት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም።
11-12. ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቅንዓትህ ቢቀዘቅዝ የአምላክን መንፈስ አጥተሃል ማለት ነው? አብራራ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 አንዳንድ ጊዜ ለእውነተኛው አምልኮ ያለህ ቅንዓት እንደቀዘቀዘ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ፤ ወይም ‘የአምላክን መንፈስ አጥቻለሁ’ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ አገልግሎቱ ሲናገር “ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል” ብሏል። (1 ቆሮ. 9:17) ምን ማለቱ ነበር?
12 ጳውሎስ የመስበክ ፍላጎቱ የጠፋባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም እንዲህ በሚሰማው ጊዜም ጭምር በአገልግሎቱ ለመጽናት ቆርጦ ነበር። አንተም ተነሳሽነት በሚጎድልህ ጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ። እንግዲያው ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርብህና ኃይል እንድታገኝ’ ጸልይ። (ፊልጵ. 2:13) መንፈሳዊ ልማድህን ይዘህ ቀጥል። ይህን ስታደርግ ውሎ አድሮ ፍላጎትህ እንደሚጨምርና በልብህ ውስጥ ያለው ፍቅር መልሶ እንደሚቀጣጠል መተማመን ትችላለህ።
ተነሳሽነትህ በሚጠፋበት ጊዜም እንኳ መንፈሳዊ ልማድህን ይዘህ ለመቀጠል ጥረት አድርግ (አንቀጽ 11-12ን ተመልከት)
13. ‘በእምነት ውስጥ መሆናችንን ለማረጋገጥ’ ዘወትር ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?
13 በ2 ቆሮንቶስ 13:5 ላይ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት አልፎ አልፎ ራሳችንን መገምገማችን ተገቢ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ።” በየጊዜው ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠው ለመንግሥቱ ጉዳዮች ነው?’ (ማቴ. 6:33) ‘የመዝናኛ ምርጫዬ ክፉ የሆነውን ነገር እንደምጠላ ያሳያል?’ (መዝ. 97:10) ‘በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ጥረት አደርጋለሁ?’ (ኤፌ. 4:2, 3) የመታሰቢያው በዓል ስለ እነዚህ ነገሮች ለማሰብ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጉልን ነገር ስናስብ ‘የምኖረው ለክርስቶስ ነው ወይስ ለራሴ?’ የሚለውን ለመመርመር እንነሳሳለን።c
ከመንጋው የራቁ በጎች
14. አንዳንድ ክርስቲያኖች ከመንጋው እንዲርቁ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?
14 አንዳንድ ክርስቲያኖች ለተወሰኑ ወራት አልፎ ተርፎም ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ካገለገሉ በኋላ ከጉባኤው ርቀዋል። ለምን? አንዳንዶች “ስለ ኑሮ በመጨነቅ” ዝለዋል። (ሉቃስ 21:34) ሌሎች ደግሞ አንድ የእምነት አጋራቸው በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ተሰናክለዋል። (ያዕ. 3:2) ከባድ ኃጢአት ሠርተው እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ያሉም አሉ። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ከመንጋው ርቀህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? ለቤዛው ያለህ አድናቆት አንተን ምን እንድታደርግ ግድ ይልሃል?
15. ይሖዋ ከመንጋው ለባዘኑ በጎች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሕዝቅኤል 34:11, 12, 16)
15 ይሖዋ ከመንጋው ስለራቁ በጎች ምን እንደሚሰማው ለማሰብ ሞክር። ይሖዋ አይረሳቸውም። እንዲያውም የጠፉ በጎቹን ይፈልጋቸዋል፤ ይመግባቸዋል፤ እንዲሁም ወደ እሱ እንዲመለሱ ይረዳቸዋል። (ሕዝቅኤል 34:11, 12, 16ን አንብብ።) ይሖዋ ለአንተስ እንዲህ እያደረገልህ ይሆን? እንዴታ! ይህን ርዕስ እያነበብክ መሆኑ በራሱ ልብህ ወደ ጽድቅ ያዘነበለ እንደሆነ ይጠቁማል። ይሖዋ የልብህን ዝንባሌ አይቶ ወደ እውነት እንድትመጣ እንደሳበህ ሁሉ አሁን ደግሞ ወደ ቤቱ እንድትመለስ እየሳበህ ይሆን?
16. ከመንጋው የራቁ በጎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 ወደ ይሖዋ ተመለስ የሚለው ብሮሹር የሚከተለውን አበረታች ሐሳብ ይዟል፦ “ወደ ይሖዋ ለመመለስ ስታስብ እሱ እጁን ዘርግቶ እንደሚጠብቅህ እርግጠኛ ሁን። ይሖዋ ጭንቀትን እንድትቋቋም፣ ስሜትህ ተጎድቶ ከነበረ ጠባሳው እንዲሽር እንዲሁም ከንጹሕ ሕሊና የሚገኘው የአእምሮና የልብ ሰላም እንዲኖርህ ይረዳሃል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ሆነህ እንደገና ይሖዋን ለማገልገል ሊያነሳሳህ ይችላል።” ሽማግሌዎች አንተን ለመርዳት እንደሚጓጉም አስታውስ። “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” ሊሆኑልህ ይችላሉ። (ኢሳ. 32:2) ለቤዛው ባለህ አድናቆት ተነሳስተህ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በእኔና በይሖዋ መካከል “የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት” የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እችላለሁ?’ (ኢሳ. 1:18፤ 1 ጴጥ. 2:25) ለምሳሌ በጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘት ትችል ይሆን? ወደ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ቀርበህ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት መጠየቅ ትችል ይሆን? እሱም ለተወሰነ ጊዜ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራልህ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። ይሖዋ ለቤዛው ያለህን አድናቆት ለማሳየት የምታደርገውን ጥረት እንደሚባርከው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በእኔና በይሖዋ መካከል “የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት” የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እችላለሁ?’ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)
ምን ታደርግ ይሆን?
17-18. ከመታሰቢያው በዓል በፊት ያሉትን ቀናት እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
17 ኢየሱስ፣ ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው “በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል” እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 3:16) ቤዛው ይሖዋ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለመታደግ ሲል ያደረገው ዝግጅት ነው። በመሆኑም ማናችንም አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። (ሮም 3:23, 24፤ 2 ቆሮ. 6:1) ከመታሰቢያው በዓል በፊት ያሉት ቀናት ይሖዋና ኢየሱስ ስላሳዩን ፍቅር ለማሰላሰል የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጡናል፤ ይህ ፍቅር ደግሞ አድናቆታችንን እንድናሳይ ግድ ሊለን ይገባል።
18 ታዲያ ቤዛው አንተን ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ከሌላ ሰው የተለየ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ በሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩት የእምነት አጋሮችህ ‘ለራስህ ከመኖር ይልቅ ለአንተ ለሞተው ለመኖር’ ጥረት ስታደርግ ይባርክሃል።—2 ቆሮ. 5:15
መዝሙር 14 አዲሱን የምድር ንጉሥ አወድሱ
a በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ እድገት እንድታደርግ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ላይ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን “ግብ” የሚለውን ሣጥን ተጠቀም።
b መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ለማየት በታኅሣሥ 2017 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወጣቶች—‘የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c አድናቆትህን ይዘህ መቀጠል የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አምላክን እንድታገለግሉ የሚገፋፋችሁ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።