የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ጥር ገጽ 14-19
  • ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቤዛው ይቅርታ ያስገኛል
  • ቤዛው ፈውስ ያስገኛል
  • ቤዛው እርቅ ያስገኛል
  • ቤዛው የይሖዋን ምሕረት ያሳያል
  • ቤዛው ምን ያስተምረናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ለቤዛው ያለኝን አድናቆት ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • የይሖዋ ፍቅር የትኞቹን በረከቶች አስገኝቶልናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ለይሖዋ ይቅርታ አድናቆት ያለን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ጥር ገጽ 14-19

ከመጋቢት 16-22, 2026

መዝሙር 20 ውድ ልጅህን ሰጠኸን

ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

“እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?”—ሮም 7:24

ዓላማ

ቤዛው ይቅርታ፣ ፈውስና እርቅ የሚያስገኘው እንዴት ነው?

1-2. የሚታደገን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ሮም 7:22-24) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። አንድ ሕንፃ ተደርምሷል። በፍርስራሹ ውስጥ የተቀበረ ሰው አለ። ይህ ሰው በሕይወት ቢኖርም ከፍርስራሹ ራሱን ነፃ ማውጣት አይችልም። ማድረግ የሚችለው ነገር ቢኖር እርዳታ ለማግኘት መጮኽና የሚታደገው ሰው እንደሚመጣለት ተስፋ ማድረግ ብቻ ነው።

2 እያንዳንዳችን ያለንበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። እንዴት? አዳም በፈጣሪው ላይ ሲያምፅ ኃጢአተኛ ሆነ። ከዚያም ኃጢአቱን ለልጆቹ አወረሳቸው። በዚህም ምክንያት መላው የሰው ዘር በኃጢአት ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብሯል ሊባል ይችላል። ደግሞም ራሳችንን ከኃጢአት ነፃ ማውጣት የምንችልበት መንገድ የለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኃጢአት የሚያስከትለውን መዘዝ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። (ሮም 7:22-24ን አንብብ።) “እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?” ሲል ጠይቋል። ጳውሎስ፣ ኃጢአት እንደ ድንጋይ ክምር እንደተጫነው ተሰምቶታል፤ ይህ ኃጢአት ደግሞ ወደ ሞት ይመራል። (ሮም 6:23) እኛም ያለነው እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው። የሚታደገን ያስፈልገናል!

በሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበረ አንድ የቆሰለ ሰው እርዳታ ለማግኘት እጁን ዘርግቶ።

በሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበረ ሰው የሚታደገው ሰው እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም የወረስነው ኃጢአት እንደ ድንጋይ ክምር ተጭኖናል፤ በመሆኑም የሚታደገን ያስፈልገናል (አንቀጽ 1-2ን ተመልከት)


3. ቤዛው የሚታደገን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

3 ሆኖም ጳውሎስ ያለንበትን አሳዛኝ ሁኔታ በመግለጽ ብቻ አላበቃም። “እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ በልበ ሙሉነት “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” የሚል መልስ ሰጥቷል። (ሮም 7:25) ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው።a ቤዛው በሚከተሉት መንገዶች ይታደገናል፦ (1) ለኃጢአታችን ይቅርታ ያስገኝልናል፤ (2) ከወረስነው አለፍጽምና ይፈውሰናል፤ እንዲሁም (3) ከፈጣሪያችን ጋር ያስታርቀናል። እነዚህን ነጥቦች እየመረመርን ስንሄድ ‘ተስፋ ለሚሰጠው አምላካችን’ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ያድጋል። (ሮም 15:13) በተጨማሪም “ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ” ላደረገን ለኢየሱስ ያለን አድናቆት ይጨምራል።—ቆላ. 1:14

ቤዛው ይቅርታ ያስገኛል

4-5. ሁላችንም ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (መክብብ 7:20)

4 ከኃጢአታችን ይቅርታ ለማግኘት ቤዛው ያስፈልገናል። ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ በቃልም ይሁን በተግባር ኃጢአት ይሠራሉ። (መክብብ 7:20ን አንብብ።) አንዳንድ ኃጢአቶች ደግሞ ከባድ ናቸው። ለምሳሌ በሙሴ ሕግ ሥር ምንዝርና ነፍስ ማጥፋት በሞት የሚያስቀጡ ኃጢአቶች ነበሩ። (ዘሌ. 20:10፤ ዘኁ. 35:30, 31) እርግጥ ብዙዎቹ ኃጢአቶች በዚህ ልክ ከባድ አይደሉም፤ ግን ኃጢአት ናቸው። ለምሳሌ መዝሙራዊው ዳዊት “በምላሴ ኃጢአት እንዳልፈጽም አካሄዴን እጠብቃለሁ” ብሏል። (መዝ. 39:1) አዎ፣ አንዳንዴ በንግግራችንም ኃጢአት ልንሠራ እንችላለን።—ያዕ. 3:2

5 እስቲ ከዚህ በፊት የተናገርካቸውንና ያደረግካቸውን ነገሮች ለማሰብ ሞክር። አንድ ነገር ከተናገርክ በኋላ ‘ምነው አፌን በቆረጠው’ ብለህ ታውቃለህ? በኋላ ላይ የተጸጸትክባቸውን ነገሮች አድርገህ ታውቃለህ? ሁለቱንም ጥያቄዎች “አዎ” ብለህ እንደምትመልስ ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “‘ኃጢአት የለብንም’ ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ይላል።—1 ዮሐ. 1:8

6-7. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲል መሠረት የሚሆነው ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ቤዛው ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን የሚያስችል መሠረት ነው። (ኤፌ. 1:7) ሆኖም ይህ ሲባል፣ ይሖዋ ኃጢአት ብንሠራ ምንም አይመስለውም ወይም ኃጢአታችንን በቸልታ ያልፋል ማለት አይደለም። ይሖዋ ኃጢአትን ይጠላል። (ኢሳ. 59:2) ፍጹም የሆነ የፍትሕ መሥፈርት ስላለው ለይቅርታ መሠረት የሚሆን ነገር ይፈልጋል።

7 የሙሴ ሕግ፣ እስራኤላውያን ለኃጢአታቸው ስርየት ለማግኘት የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው ይናገራል። (ዘሌ. 4:27-31፤ 17:11) እነዚህ መሥዋዕቶች ኢየሱስ ለሚያቀርበው የላቀ መሥዋዕትና ይህ መሥዋዕት ለሚያስገኛቸው በረከቶች ጥላ ነበሩ። የኢየሱስ መሥዋዕት ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲል የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት ይሆናል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያሳየው የኢየሱስ መሥዋዕት ያለውን ዋጋ ተረድቶ ነበር። ቀደም ሲል የፈጸሟቸውን መጥፎ ተግባሮች ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችኋል።”—1 ቆሮ. 6:9-11

አንድ እስራኤላዊ ቤተሰብ ወደ ቤተ መቅደሱ በግ ወስዶ በደስታ ለካህኑ ሲሰጥ።

ኃጢአትን ለማስተሰረይ የሚቀርቡት የእንስሳት መሥዋዕቶች ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትና መሥዋዕቱ ለሚያስገኛቸው በረከቶች እንደ ጥላ ሆነው አገልግለዋል (አንቀጽ 6-7ን ተመልከት)


8. በዚህ ዓመት ለሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ስትዘጋጅ ስለ ምን ነገር ማሰብ ትችላለህ?

8 በዚህ ዓመት ለሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ስትዘጋጅ የይሖዋ ይቅርታ ለአንተ ምን ትርጉም እንዳለው ጊዜ ወስደህ ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ቤዛው ስላለ፣ ከዚህ በፊት ለሠራሃቸው ስህተቶች ንስሐ እስከገባህ ድረስ በእነዚህ ኃጢአቶች ምክንያት በበደለኝነት ስሜት መዋጥ አያስፈልግህም። ይሁንና ይህን ሐሳብ መቀበል ከባድ ቢሆንብህስ? ምናልባት እንዲህ እያልክ ታስብ ይሆናል፦ ‘ይሖዋ ይቅር ባይ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እኔ ግን ራሴን ይቅር ማለት አልችልም።’ እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይህን አስታውስ፦ ይቅር የማለት ሥልጣን ያለው ይሖዋ ነው፤ የመፍረዱን ሥልጣን ደግሞ ለልጁ ሰጥቶታል። ይሖዋ የእሱን ምሕረት ማን እንደሚያገኝ የመወሰን ሥልጣን ለአንተም ሆነ ለሌላ ለማንም ሰው አልሰጠም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ] በብርሃን እንዳለ ሁሉ እኛም በብርሃን የምንመላለስ ከሆነ . . . የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” (1 ዮሐ. 1:6, 7) በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ እምነት እንዳለን ሁሉ ይህንንም እውነት አምነን ልንቀበል ይገባል። ቤዛው ስለተከፈለ ይሖዋ እኛን ይቅር ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት አለው፤ ደግሞም ቃሉ ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነ ይናገራል።—መዝ. 86:5

ቤዛው ፈውስ ያስገኛል

9. ኃጢአት ማለት መጥፎ ነገር መፈጸም ማለት ብቻ ነው? አብራራ። (መዝሙር 51:5 እና የግርጌ ማስታወሻ)

9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአት” የሚለው ቃል የምንፈጽመውን ስህተት ብቻ ሳይሆን ስንፀነስ ጀምሮ የወረስነውን አለፍጽምናም ያመለክታል። (መዝሙር 51:5ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) አለፍጽምናችን መጥፎ ነገር እንድንሠራ ከመገፋፋት ባለፈ ሰውነታችን ይሖዋ ባሰበው መንገድ እንዳይሠራ አድርጎታል፤ በዚህም ምክንያት እንታመማለን፣ እናረጃለን እንዲሁም እንሞታለን። ምንም ዓይነት የኃጢአት ድርጊት ያልፈጸሙ ጨቅላ ሕፃናት የሚታመሙት ብሎም የሚሞቱት ለዚህ ነው። መጥፎ ሰዎችም ሆኑ ጥሩ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸውና የሚሞቱትም ለዚህ ነው። በአዳም ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም አለፍጽምናን ወርሰናል።

10. አለፍጽምና አዳምና ሔዋን ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

10 አለፍጽምና የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት እንዴት እንደጎዳቸው ለማሰብ ሞክር። ስሜታቸው እንዲረበሽ አድርጓል። አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ካመፁ በኋላ የአምላክን ሕግ መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ ወዲያውኑ ቀምሰዋል፤ “በልባቸው እንደተጻፈ” ሕግ የሆነው ሕሊናቸው ወቀሳቸው። (ሮም 2:15) ከዚያ በፊት የማያውቁት መጥፎ ስሜት ተሰማቸው። ሰውነታቸውን ለመሸፈንና ልክ እንደ ወንጀለኛ ከፈጣሪያቸው ለመደበቅ ተነሳሱ። (ዘፍ. 3:7, 8) አዳምና ሔዋን በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ጥፋተኝነት ስሜት፣ ጭንቀት፣ ስጋት፣ ሥቃይና ኀፍረት ያሉ ስሜቶችን ማስተናገድ ጀመሩ። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እነዚህ ስሜቶች እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አብረዋቸው ቀጥለዋል።—ዘፍ. 3:16-19

11. አለፍጽምና ምን ጉዳት አድርሶብናል?

11 አለፍጽምና ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ሁሉ በእኛም ላይ ጉዳት አድርሷል። ለአካላዊና ለስሜታዊ ሥቃይ የምንዳረገው ኃጢአተኞች ስለሆንን ነው። ሁኔታችንን ለማሻሻል ምንም ያህል ብንፍጨረጨር ማድረግ የምንችለው ነገር በጣም ውስን ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘ለከንቱነት ተገዝተናል።’ (ሮም 8:20) ይህ ሐሳብ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቡድን ደረጃ መላውን የሰው ዘር ይመለከታል። ለምሳሌ የሰው ልጆች ሥርዓተ ምህዳሩን ለመንከባከብ፣ ወንጀልን ለመቆጣጠር፣ ድህነትን ለማጥፋት እንዲሁም በብሔራት መካከል ሰላም ለማስፈን ጥረት ያደርጋሉ። ይሁንና በአንዳንድ አቅጣጫዎች መጠነኛ መሻሻል ቢታይም በጥቅሉ ሲታይ የሚያደርጉት ጥረት ከንቱ ነው። ታዲያ ቤዛው ከአለፍጽምናችን የሚታደገን እንዴት ነው?

12. ቤዛው ስለተከፈለ ምን ተስፋ አግኝተናል?

12 ቤዛው ስለተከፈለ “ፍጥረት ራሱ . . . ከመበስበስ ባርነት ነፃ [እንደሚወጣ]” ተስፋ አለን። (ሮም 8:21) በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ቤዛው ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ሲውል አካላዊ፣ አእምሯዊም ሆነ ስሜታዊ ሕመም አያጋጥመንም፤ እንዲሁም በጥፋተኝነት፣ በጭንቀት፣ በስጋት፣ በሥቃይ ወይም በኀፍረት ስሜት አንሽመደመድም። በተጨማሪም ምድርን ለመንከባከብና በሰላም ለመኖር የምናደርገው ጥረት ከንቱ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ቤዛችን በሆነው ‘በሰላሙ መስፍን’ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር ይሳካል።—ኢሳ. 9:6, 7

13. ለዘንድሮው የመታሰቢያው በዓል ስትዘጋጅ ሌላስ ስለ ምን ማሰብ ትችላለህ?

13 ከአለፍጽምና ነፃ ስትወጣ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖርህ ለማሰብ ሞክር። ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ ፍጹም ጤንነት ይሰማሃል፤ ስለ ራስህም ሆነ ስለምትወዳቸው ሰዎች ስታስብ እንራባለን፣ እንታመማለን ወይም እንሞታለን ብለህ አትሰጋም። ‘ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነውን ይህን ተስፋ አጥብቀን መያዛችን’ ዛሬም እንኳ አንጻራዊ ሰላም ያስገኝልናል። (ዕብ. 6:18, 19) መልሕቅ አንድን ጀልባ አጽንቶ እንደሚያቆመው ሁሉ ክርስቲያናዊ ተስፋህም እምነትህን ሊያጠናክርልህና የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል። በእርግጥም ይሖዋ ‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታቸውን እንደሚከፍል’ መተማመን ትችላለህ። (ዕብ. 11:6) ለአሁኑ ጊዜ መጽናኛ፣ ለወደፊቱ ጊዜ ደግሞ ተስፋ ሊኖርህ የቻለው በቤዛው አማካኝነት ብቻ ነው።

ቤዛው እርቅ ያስገኛል

14. ኃጢአት ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ያበላሸው እንዴት ነው? ለምንስ?

14 አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች ከአምላክ ጋር ተራርቀዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር በአጠቃላይ ከፈጣሪው ጋር እንደተጣላ ይናገራል። (ሮም 8:7, 8፤ ቆላ. 1:21) ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ፍጹም መሥፈርት ስላለው ኃጢአትን በቸልታ ሊያልፍ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ዓይኖችህ ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፤ ክፋትንም ዝም ብለህ ማየት አትችልም።” (ዕን. 1:13) በዚህ መንገድ ኃጢአት በአምላክና በሰዎች መካከል ክፍተት ፈጥሯል። ይህ ክፍተት እስካልተደፈነና ከይሖዋ ጋር እርቅ እስካልፈጠርን ድረስ ማናችንም ብንሆን ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት አንችልም። ከይሖዋ ጋር እርቅ ለመፍጠር ያስቻለን ቤዛው ነው።

15. የኢየሱስ ሞት ሰዎችን ከይሖዋ ጋር ያስታረቀው እንዴት ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ “ለእኛ ኃጢአት የቀረበ የማስተሰረያ መሥዋዕት” እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐ. 2:2) የኢየሱስ መሥዋዕት ከይሖዋ ጋር እንድንታረቅ ያስቻለን እንዴት ነው? የኢየሱስ ሞት የይሖዋ የፍትሕ መሥፈርት እንዲሟላ አስችሏል። ይህም በሰዎችና በይሖዋ መካከል ያለውን ዝምድና ለማደስ የሚያስችል መሠረት ሆኗል። (ሮም 3:23-26) ይሖዋ፣ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት የኖሩ ታማኝ አገልጋዮቹንም ጭምር ጻድቅ አድርጎ መቁጠር ችሏል። (ዘፍ. 15:1, 6) እንዴት? ወደፊት የሚከፈለውን ቤዛ መሠረት አድርጎ ነው። ይሖዋ፣ ልጁ ኢየሱስ ቤዛውን እንደሚከፍል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። (ኢሳ. 46:10) ቤዛው ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ መንገድ ከፍቷል።

16. ለዘንድሮው የመታሰቢያ በዓል ስትዘጋጅ ሌላስ ስለ ምን ማሰብ ትችላለህ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 ከአምላክ ጋር መታረቅህ ምን እንዳስገኘልህ ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ኢየሱስ እንዳስተማረው ይሖዋን ‘አባቴ’ ብለህ ትጠራው ይሆናል። (ማቴ. 6:9) እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ‘ወዳጄ’ ብለህ ትጠራው ይሆናል። ይሖዋን ‘አባቴ’ ወይም ‘ወዳጄ’ ብለን ስንጠራው ይህን የምናደርገው በጥልቅ አክብሮትና በትሕትና ሊሆን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ኃጢአተኞች ስለሆንን በራሳችን ጥረት ወደ ይሖዋ መቅረብ አንችልም። ከይሖዋ ጋር ዝምድና መመሥረት የቻልነው ራሱ፣ ቤዛው ስለተከፈለልን ብቻ ነው። ይሖዋ፣ ኢየሱስ “በመከራው እንጨት ላይ ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ . . . ከራሱ ጋር ለማስታረቅ” እርምጃ ወስዷል። (ቆላ. 1:19, 20) ፍጹማን ባንሆንም እንኳ በአሁኑ ጊዜም ጭምር ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የቻልነው በዚህ ምክንያት ነው።

ሮማውያን ወታደሮች ኢየሱስን በመከራ እንጨቱ ላይ በሚስማር ለመቸንከር ሲዘጋጁ። ሁለት ሮማውያን ወታደሮች ኢየሱስን ወደ እንጨቱ ሲያመጡት ሌላ ሮማዊ ወታደር ደግሞ መዶሻና ሚስማር ይዟል።

በይሖዋና በሰው ልጆች መካከል ያለው ዝምድና እንዲታደስ የሚያስችለው ሕጋዊ መሠረት የኢየሱስ ሞት ብቻ ነው (አንቀጽ 16ን ተመልከት)


ቤዛው የይሖዋን ምሕረት ያሳያል

17. ቤዛው የይሖዋን ምሕረት የሚያሳየው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 2:4, 5)

17 ቤዛው ይሖዋ “ምሕረቱ ብዙ” እንደሆነ ያረጋግጣል። እሱ ‘በበደላችን ሙታን በነበርንበት ጊዜ ሕያዋን አድርጎናል።’ (ኤፌሶን 2:4, 5ን አንብብ።) “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች በኃጢአት ፍርስራሽ ውስጥ እንደተቀበሩና የሚታደጋቸው እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበው እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ። (ሥራ 13:48) ይሖዋ የመንግሥቱ መልእክት እንዲደርሳቸው እንዲሁም ስለ እሱና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ እንዲያውቁ በማድረግ ለሚያሰሙት የእርዳታ ጩኸት ምላሽ ይሰጣል። (ዮሐ. 17:3) ሰይጣን የአዳምና የሔዋን ውድቀት የይሖዋን ዓላማ እንደሚያሰናክለው አስቦ ከነበረ ምንኛ ተሳስቷል!

18. በቤዛው ላይ ስናሰላስል የትኛውን ነገር መዘንጋት አይኖርብንም?

18 ቤዛው ስላስገኘልን ጥቅሞች ስናሰላስል ቤዛው የተከፈለበትን ዋነኛ ዓላማ መዘንጋት አይኖርብንም። ቤዛው ለእኛ ጥቅም ሲባል ብቻ የተደረገ ዝግጅት እንደሆነ ከማሰብ ይልቅ ይሖዋ ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ላነሳው ግድድር መልስ ለመስጠት እንደተጠቀመበት ማስታወስ ይኖርብናል። (ዘፍ. 3:1-5, 15) ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ስሙን ያስቀድሳል፤ እንዲሁም ከነቀፋ ነፃ ያደርገዋል። በተጨማሪም እኛን ከኃጢአትና ከሞት በማዳን የፍቅር አምላክ መሆኑን አሳይቷል። ይሖዋ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ለሰይጣን ግድድር መልስ በመስጠት ረገድ የበኩላችንን ድርሻ እንድናበረክት በመፍቀድ ጸጋውን አሳይቶናል። (ምሳሌ 27:11) ታዲያ ለቤዛው ያለህን አድናቆት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

ቤዛው የሚከተሉትን ነገሮች የሚያስገኘው እንዴት ነው?

  • ይቅርታ

  • ፈውስ

  • እርቅ

መዝሙር 19 የጌታ ራት

a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ቤዛ አንድን አካል ነፃ ለማውጣት ሲባል የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት፣ ቤዛ የተባለው ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ስለሚያወጣ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ