ከመጋቢት 9-15, 2026
መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር
አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ ትችላለህ
“እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!”—ሮም 7:24
ዓላማ
አፍራሽ አስተሳሰቦችንና ስሜቶችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
1-2. ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ ምን ይሰማው ነበር? የእኛ ሁኔታስ ከእሱ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ሮም 7:21-24)
ሐዋርያው ጳውሎስን ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ደፋር ሚስዮናዊና ጎበዝ አስተማሪ እንደነበር እንዲሁም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን እንደጻፈ ታስታውስ ይሆናል። ደግሞም እውነት ነው። ሆኖም ጳውሎስ እንደ ብዙዎቻችን ከአፍራሽ ስሜቶች ጋር ይታገል ነበር።
2 ሮም 7:21-24ን አንብብ። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተሰማውን ስሜት ገልጿል። ብዙዎቻችን እነዚህን ስሜቶች አስተናግደን እናውቃለን። ጳውሎስ ታማኝ ክርስቲያን ቢሆንም በውስጡ ትግል ነበር። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት ቢኖረውም ከመጥፎ ምኞቶቹ ጋር መታገል ነበረበት። ከዚህም በተጨማሪ፣ ጳውሎስ በቀድሞ ሕይወቱ በፈጸመው ነገርና አሁን እያጋጠመው ባለው ችግር የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ከአፍራሽ ስሜቶች ጋር ይታገል ነበር።
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውንም ተመልከት።)
3 ጳውሎስ በውስጡ ትግል ቢኖርበትም አፍራሽ ስሜቶችa አስተሳሰቡን እንዲቆጣጠሩት አልፈቀደም። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ጳውሎስ “ጎስቋላ” እንደሆነ እንዲሰማው ያደረገው ምንድን ነው? አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? እኛስ አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
ጳውሎስ አፍራሽ ስሜቶች ያደሩበት ለምንድን ነው?
4. ጳውሎስ አፍራሽ ስሜቶች እንዲያድሩበት ያደረገው ምንድን ነው?
4 በቀድሞ ሕይወቱ ያደረጋቸው ነገሮች። ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በርካታ መጥፎ ነገሮችን ፈጽሟል። ለምሳሌ ታማኙ እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወገር በውሳኔው ተስማምቶ ቆሞ ተመልክቷል። (ሥራ 7:58፤ 8:1) በተጨማሪም ጳውሎስ ግንባር ቀደም ሆኖ ክርስቲያኖችን ክፉኛ አሳዷል።—ሥራ 8:3፤ 26:9-11
5. ጳውሎስ በቀድሞ ሕይወቱ የፈጸመው ነገር ምን እንዲሰማው አድርጎታል?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ፣ በቀድሞ ሕይወቱ የፈጸማቸው ነገሮች አልፎ አልፎ ይረብሹት ነበር። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ጳውሎስ በቀድሞ ሕይወቱ የሠራው ስህተት ይበልጥ እየጸጸተው ሳይሄድ አልቀረም። ለምሳሌ በ55 ዓ.ም. ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የመጀመሪያ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር . . . ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ።” (1 ቆሮ. 15:9) ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ራሱን ‘ከቅዱሳን ሁሉ የማንስ’ ሲል ጠርቷል። (ኤፌ. 3:8) ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ደግሞ “ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ [ነበርኩ]” ብሏል። (1 ጢሞ. 1:13) ጳውሎስ ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ወቅት ቀደም ሲል ያሳደዳቸውን ክርስቲያኖች ወይም ቤተሰቦቻቸውን ሲያገኝ ምን ሊሰማው እንደሚችል መገመት ትችላለህ?
6. ጳውሎስን ያስጨነቀው ሌላው ነገር ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
6 ሥጋውን የሚወጋ እሾህ። ጳውሎስ ከባድ ጭንቀት ያስከተለበትን አንድ ችግር “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮ. 12:7) ጳውሎስ ይህ ችግር ምን እንደሆነ አልገለጸም፤ ሆኖም የተጠቀመበት ዘይቤያዊ አገላለጽ ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ሌላ ዓይነት ችግር እንደሆነ ይጠቁማል።b
7. ጳውሎስ አለፍጽምናው ተጽዕኖ ያሳደረበት እንዴት ነው? (ሮም 7:18, 19)
7 አለፍጽምናው። ጳውሎስ ከአለፍጽምናው ጋር መታገል አስፈልጎታል። (ሮም 7:18, 19ን አንብብ።) ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቢፈልግም ፍጹም ያልሆነው ሥጋው እንዲህ እንዳያደርግ እንቅፋት ሆኖበታል። በሥጋዊ ዝንባሌውና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ባለው ፍላጎት መካከል ሁልጊዜ ትግል እንዳለ ሳይሸሽግ ተናግሯል። ሆኖም ጳውሎስ ራሱን ለማሻሻል ብርቱ ጥረት አድርጓል። (1 ቆሮ. 9:27) ያም ቢሆን ጳውሎስ ድክመቶቹ ያገረሹበት ጊዜ መኖሩ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ምንኛ አዝኖ ይሆን!
ጳውሎስ አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?
8. ጳውሎስ ድክመቶቹን ማሸነፍ ስለቻለበት መንገድ ከደብዳቤዎቹ ምን እንማራለን?
8 ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች የኃጢአት ዝንባሌዎችን በአምላክ መንፈስ እርዳታ ማሸነፍ ስለሚችሉበት መንገድ ያሰላስል ነበር። የጻፋቸው ደብዳቤዎች ይህን ይጠቁማሉ። (ሮም 8:13፤ ገላ. 5:16, 17) ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሊዋጓቸው ስለሚገቡ መጥፎ ባሕርያትና ምኞቶች በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ገላ. 5:19-21, 26) ጳውሎስ በድክመቶቹ ላይ ጊዜ ወስዶ እንዳሰላሰለ፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት ምክር ለማግኘት እንደሞከረ እንዲሁም ድክመቶቹን ለማሸነፍ የሚረዱትን የተለያዩ እርምጃዎች እንደወሰደ ጥርጥር የለውም። ለሌሎች የሰጠውን ምክር እሱም በሥራ ላይ እንዳዋለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
9-10. ጳውሎስ አፍራሽ ስሜቶችን እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው? (ኤፌሶን 1:7) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
9 ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ በሐዘን ቢዋጥም አዎንታዊ አመለካከት ይዞ መቀጠል ችሏል። ለምሳሌ ከጉዞ አጋሮቹ የሚሰማው መልካም ዜና ያስደስተው ነበር። (2 ቆሮ. 7:6, 7) ከእምነት አጋሮቹ ጋር ያለው ወዳጅነትም ደስታ አስገኝቶለታል። (2 ጢሞ. 1:4) እንዲሁም የይሖዋ ሞገስ እንዳልተለየው ያውቃል። በእርግጥም ጳውሎስ አምላክን “በንጹሕ ሕሊና” በማገልገሉ ደስተኛ መሆን ችሏል። (2 ጢሞ. 1:3) ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ጊዜም እንኳ የእምነት አጋሮቹን “በጌታ ደስ ይበላችሁ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ፊልጵ. 4:4) ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት በአፍራሽ አስተሳሰብ እንዳልተሸነፈ ያሳያሉ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ አፍራሽ አስተሳሰብ ወደ አእምሮው ሲመጣ ይህን ስሜት አሸንፎ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ችሏል።
10 ጳውሎስ አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ የረዳው ሌላው ነገር ቤዛው በግለሰብ ደረጃ ለእሱ የተሰጠው ስጦታ እንደሆነ ማመኑ ነው። (ገላ. 2:20፤ ኤፌሶን 1:7ን አንብብ።) በመሆኑም ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይቅር እንዳለው ሙሉ በሙሉ መተማመን ችሏል። (ሮም 7:24, 25) ጳውሎስ ቀደም ሲል የሠራቸው ስህተቶችና አሁን የሚያታግሉት ድክመቶች ቢኖሩም ደስተኛ ሆኖ ለአምላክ ‘ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ’ ችሏል።—ዕብ. 9:12-14
ጳውሎስ በቀድሞ ሕይወቱ የፈጸማቸው ስህተቶች አልፎ አልፎ ቢረብሹትም በቤዛው ላይ በማሰላሰል አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ ችሏል (አንቀጽ 9-10ን ተመልከት)
11. የጳውሎስ ምሳሌ የሚያበረታታን እንዴት ነው?
11 ልክ እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ሁልጊዜ በውስጣችን ትግል እንዳለ ይሰማን ይሆናል። በምናስበው፣ በምናደርገው ወይም በምንናገረው ነገር ይሖዋን ላለማሳዘን መታገል ሊያስፈልገን ይችላል። እኛም “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!” እንል ይሆናል። በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ኤሊዛc የተባለች እህት ስለሚሰማት ስሜት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የጳውሎስን ሁኔታ ሳስብ እበረታታለሁ። እንዲህ ዓይነት ትግል ያለብኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ ማወቄ ያጽናናኛል። ይህ፣ ይሖዋ ሕዝቦቹ ያለባቸውን ችግር እንደሚረዳ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።” ልክ እንደ ጳውሎስ እኛም ንጹሕ ሕሊና ለመያዝና አፍራሽ ስሜቶችን አሸንፈን ደስተኛ ለመሆን ምን ይረዳናል?
አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
12. ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበራችን አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
12 ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ አዳብር። ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ካዳበርን አዎንታዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ቀላል ይሆንልናል። እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ልማድ አካላዊ ጤንነታችንን ለመጠበቅ ከሚረዱን ልማዶች ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። ጤናማ ምግብ ከተመገብን፣ አዘውትረን እንቅስቃሴ ካደረግንና በቂ እንቅልፍ ካገኘን ጥሩ ስሜት ይሰማናል። በተመሳሳይም የአምላክን ቃል አዘውትረን ስናነብ፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች ስንዘጋጅና በስብሰባ ላይ ተገኝተን ሐሳብ ስንሰጥ እንዲሁም በአገልግሎት ስንካፈል ኃይላችን ይታደሳል። እንዲህ ባሉ አበረታች እንቅስቃሴዎች መካፈላችን አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ ይረዳናል።—ሮም 12:11, 12
13-14. አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበራቸው የረዳቸው እንዴት ነው?
13 እስቲ የጆንን ምሳሌ እንመልከት። ጆን ገና በ39 ዓመቱ ካንሰር እንዳለበት ታወቀ። መጀመሪያ አካባቢ በአፍራሽ ስሜቶች ተውጦ ነበር። ‘ገና በዚህ ዕድሜዬ እንዴት ካንሰር ይይዘኛል?’ ብሎ ያስብ ነበር። በዚያ ወቅት የጆን ልጅ ገና ሦስት ዓመቱ ነበር። ጆን አፍራሽ ስሜቶቹን እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ሰውነቴ ቢዝልም ቤተሰባችን ቋሚ መንፈሳዊ ልማድ ይዞ እንዲቀጥል ጥረት አደርግ ነበር። በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን፤ በየሳምንቱ በአገልግሎት እንካፈላለን፤ እንዲሁም አመቺ በማይሆንበት ጊዜም ጭምር በቋሚነት የቤተሰብ አምልኮ እናደርጋለን።” ጆን ያንን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥመን መጀመሪያ ላይ ልንደነግጥ እንችላለን። ብዙም ሳይቆይ ግን የይሖዋን ፍቅርና እርዳታ እናስተውላለን፤ በዚህ ጊዜ የሚሰማን አፍራሽ ስሜት እየደበዘዘ ይሄዳል። ይሖዋ እኔን ጠንካራ እንዳደረገኝ እናንተንም ያጠነክራችኋል።”
14 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሊዛ እንዲህ ብላለች፦ “በስብሰባዎች ላይ በተገኘሁና የግል ጥናት ባደረግኩ ቁጥር ይሖዋ እንደሚሰማኝና በጣም እንደሚወደኝ አስታውሳለሁ። ይህ ደግሞ ያስደስተኛል።” በአፍሪካ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ኖላን እሱና ባለቤቱ ዳያን ስለሚሰማቸው ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚሰማን ጊዜም ጭምር መንፈሳዊ ልማዳችንን አናቋርጥም። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ ሁልጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ይረዳናል። ይሖዋ እንደሚረዳንና እንደሚባርከን ለማስታወስ እንሞክራለን። ይህን የሚያደርግልን እንዴት እንደሆነ አናውቅም፤ ግን እንደሚረዳን እርግጠኞች ነን።”
15. አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ ምን ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።
15 አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ ሌላም ነገር ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ የወገብ ሕመም አጋጠመህ እንበል። በየቀኑ የተወሰነ መንገድ በእግር መሄድ ሊረዳህ ይችላል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ብቻውን በቂ አይደለም። የሕመምህን መንስኤ ለማወቅ ምርምር ማድረግ አልፎ ተርፎም ሐኪም ማማከር ሊያስፈልግህ ይችላል። በተመሳሳይም አፍራሽ ስሜቶች በተደጋጋሚ የሚመላለሱብን ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን ተጠቅመን ምርምር ማድረግ እንዲሁም የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማማከር ሊኖርብን ይችላል። ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ምክሮችን እስቲ እንመልከት።
16. አፍራሽ ስሜት የሚፈጥርብህ ምን እንደሆነ ለማወቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? (መዝሙር 139:1-4, 23, 24)
16 ምን እንደሚያስፈልግህ ለማወቅ እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው። ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ በደንብ እንደሚያውቀው እርግጠኛ ነበር። በመሆኑም ዳዊት ‘የሚያስጨንቁት ሐሳቦች’ ከምን የመነጩ እንደሆኑ ለማወቅ እንዲረዳው ይሖዋን ጠይቋል። (መዝሙር 139:1-4, 23, 24ን አንብብ።) አንተም አፍራሽ ስሜት የሚፈጥርብህ ምን እንደሆነ ለማወቅና ይህን ስሜት ማሸነፍ የምትችልበትን መንገድ ለመረዳት እንዲያግዝህ ይሖዋን መጠየቅ ትችላለህ። በተጨማሪም እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራስህን መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘የሚያስጨንቁኝ ሐሳቦች መንስኤ ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ አፍራሽ ስሜት የሚያድርብኝ ምን ሲያጋጥመኝ ነው? አፍራሽ ሐሳብ ሲመጣብኝ ሐሳቡን ከአእምሮዬ ከማውጣት ይልቅ አውጠነጥንበታለሁ?’
17. አእምሮህ በሚያንጹ ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩር ስለ የትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ማጥናት ትችላለህ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 የግል ጥናትህ ካለህበት ሁኔታ ጋር የሚስማማ እንዲሆን አድርግ። አልፎ አልፎ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ማጥናትህ ይጠቅምህ ይሆናል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በቤዛውና በይሖዋ ይቅር ባይነት ላይ ማሰላሰሉ በእጅጉ ጠቅሞታል። አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን መጽሐፍ ወይም ሌሎች የምርምር መሣሪያዎችን ተጠቅመህ ስለ ይሖዋ ምሕረት፣ ስለ ይቅር ባይነቱ፣ ስለ ታማኝ ፍቅሩ እንዲሁም ስለ ሌሎች ባሕርያቱ ማጥናት ትችላለህ። ሊጠቅሙህ የሚችሉ ርዕሶችን ካገኘህ ዘርዝረህ ጻፋቸው። ዝርዝሩን ልታየው በምትችለው ቦታ ላይ ለጥፈው፤ ከዚያም ስሜትህ ሲደቆስ በዝርዝሩ ውስጥ ካሉት ርዕሶች መካከል አንዳንዶቹን አንብብ። በተጨማሪም ያነበብከው ሐሳብ ለአንተ ሁኔታ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ አስብ።—ፊልጵ. 4:8
አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ የሚረዱህን ርዕሶች መርጠህ አጥና (አንቀጽ 17ን ተመልከት)
18. አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን አጥንተዋል?
18 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሊዛ በግል ጥናቷ ላይ ኢዮብን በተመለከተ ምርምር አድርጋ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የኢዮብ ታሪክ በጣም ይነካኛል። መከራዎች ተደራርበውበት ነበር። ኢዮብ የመከራው መንስኤ ማን እንደሆነ ባያውቅም እንኳ በከፋ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ጊዜም ወደ ይሖዋ ዘወር ማለቱን አላቆመም።” (ኢዮብ 42:1-6) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዳያን ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ እያጠናን ነው። ይሖዋ ልክ እንደ ሸክላ ሠሪ እየቀረጸን መሆኑ ያስደስተናል። በራሳችን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይሖዋ የተሻልን ሰዎች እንድንሆን እየቀረጸን እንዳለ ለማሰብ እንሞክራለን። ይህም ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ አድርጎናል።”—ኢሳ. 64:8
የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ተጠባበቅ
19. አልፎ አልፎ አፍራሽ ስሜቶች ቢያድሩብንም ምን መጠበቅ እንችላለን?
19 ጥሩ መንፈሳዊ ልማድና ሁኔታችንን ያማከለ ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም ቢኖረንም አፍራሽ አስተሳሰቦችና ስሜቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚጠፉልን አንጠብቅም። ይህን አድርገንም በተስፋ መቁረጥ ስሜት የምንዋጥባቸው ቀናት ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ፣ የሚመጡብንን አፍራሽ ስሜቶች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን። በአብዛኞቹ ቀናት ደግሞ ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል፤ በሕይወታችን እርካታ እናገኛለን፤ እንዲሁም ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ደስተኛ እንሆናለን።
20. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
20 ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች፣ አሁን በሚያጋጥሙን መከራዎች ወይም በአለፍጽምናችን የተነሳ የሚያድሩብን አፍራሽ ስሜቶች እንዲቆጣጠሩን ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በይሖዋ እርዳታ አፍራሽ ስሜቶችን ማሸነፍ እንችላለን። (መዝ. 143:10) በቅርቡ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ መታገል የማያስፈልገን ጊዜ ይመጣል። በዚያ ወቅት፣ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ በአእምሯችን ውስጥ ምንም ዓይነት አፍራሽ ሐሳብ አይኖርም። አፍቃሪውን አምላካችንን ይሖዋን ያለምንም ጭንቀት በደስታ ማገልገል እንችላለን።
መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህ ርዕስ ውስጥ “አፍራሽ ስሜቶች” የሚለው አገላለጽ አልፎ አልፎ የሚሰማንን ሐዘንና የሚያጋጥመንን የስሜት መለዋወጥ የሚያመለክት ነው። የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገውን ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ድባቴ አያመለክትም።
b ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች የማየት ችግር እንደነበረበት ይጠቁማሉ፤ ይህም ደብዳቤዎችን መጻፍና አገልግሎቱን ማከናወን ከባድ እንዲሆንበት አድርጎ ሊሆን ይችላል። (ገላ. 4:15፤ 6:11) ወይም ደግሞ አንዳንድ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የተናገሩት ነገር በጭንቀት እንዲዋጥ አድርጎት ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 10:10፤ 11:5, 13) ሁኔታው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ባናውቅም በጳውሎስ ላይ ከባድ ጭንቀት እንደፈጠረበት እናውቃለን።
c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።