የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ጥር ገጽ 2-7
  • ‘መንፈሳዊ ጥማታችሁን’ ማርካታችሁን ቀጥሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘መንፈሳዊ ጥማታችሁን’ ማርካታችሁን ቀጥሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትሕትና፣ ጽናትና እምነት
  • እንደ ጴጥሮስ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችሁን ቀጥሉ
  • እንደ ጳውሎስ መንፈሳዊ ልብስ ልበሱ
  • እንደ ዳዊት በመንፈሳዊው መጠለያ ተጠለሉ
  • መንፈሳዊ ጥማታችሁን ማርካታችሁን ቀጥሉ
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የይሖዋንና የኢየሱስን አስተሳሰብ ኮርጁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2025-2026 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚገኝበት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ጥር ገጽ 2-7

ከመጋቢት 2-8, 2026

መዝሙር 97 የአምላክ ቃል ሕይወት ነው

‘መንፈሳዊ ጥማታችሁን’ ማርካታችሁን ቀጥሉ

የ2026 የዓመት ጥቅስ፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴ. 5:3

ዓላማ

ይሖዋ ከሚያዘጋጅልን መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

1. የሰው ልጆች የትኞቹ መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጓቸዋል? (ማቴዎስ 5:3)

ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠራቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲኖሯቸው አድርጎ ነው። ለምሳሌ በሕይወት ለመኖር ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያስፈልገናል። ለአጭር ጊዜ እንኳ ከእነዚህ ነገሮች አንዱን ብናጣ ሕይወት ከባድ ይሆንብናል። ይሁንና እነዚህ ቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችም ያስፈልጉናል፤ ይሖዋ የፈጠረን በዚህ መንገድ ነው። (ማቴዎስ 5:3ን አንብብ።) እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግን መንፈሳዊ ነገሮች እንደሚያስፈልጉን ማወቅና ይህን ጥማት ለማርካት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

2. ‘መንፈሳዊ ነገሮችን መጠማት’ ሲባል ምን ማለት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

2 ‘መንፈሳዊ ነገሮችን መጠማት’ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ አገላለጽ “መንፈስን ለማግኘት የሚለምኑ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እስቲ አንድን ለማኝ ለማሰብ ሞክር። የተቀዳደደ ልብስ ለብሶ መንገድ ዳር ኩርምት ብሎ ተቀምጧል። ረሃብ አጎሳቁሎታል፤ በገጽታው ምክንያት ሰዎች አግልለውታል፤ እንዲሁም የቀኑ ሐሩርና የሌሊቱ ቁር እየተፈራረቀበት ነው። ይህ ለማኝ በሕይወት ለመቀጠል የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልገው በሚገባ ያውቃል። በተመሳሳይም መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠማ ወይም መንፈስ ለማግኘት የሚለምን ሰው በሕይወቱ ውስጥ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያውቃል። በመሆኑም ይህ ሰው፣ ይሖዋ እሱን ለሚወዱ ሰዎች ካቀረበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ዝግጅት ለመጠቀም ይጓጓል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ መጀመሪያ፣ ኢየሱስን እንዲረዳት ከለመነችው ፊንቄያዊት ሴት የምናገኘውን ትምህርት እንመለከታለን። ይህ ዘገባ፣ መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ሰዎች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ ሦስት ባሕርያትን ጎላ አድርጎ ያሳያል። በተጨማሪም መንፈሳዊ ሰዎች የሆኑት ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ንጉሥ ዳዊት የተዉትን ምሳሌ እንመረምራለን።

ትሕትና፣ ጽናትና እምነት

4. አንዲት ፊንቄያዊት ሴት ኢየሱስ ምን እንዲያደርግላት ፈልጋ ነበር?

4 በአንድ ወቅት አንዲት ፊንቄያዊት ሴት ወደ ኢየሱስ መጣች። ልጇ “ጋኔን ስለያዛት ክፉኛ እየተሠቃየች” ነበር። (ማቴ. 15:21-28) ሴትየዋ ተንበርክካ ኢየሱስን እንዲረዳት ለመነችው። ይህች ፊንቄያዊት ሴት ወደ ኢየሱስ በሄደችበት ወቅት ግሩም ባሕርያትን አሳይታለች። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

5. ፊንቄያዊቷ ሴት የትኞቹን ባሕርያት አሳይታለች? ኢየሱስስ ምን አደረገላት? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ፊንቄያዊቷ ሴት እውነተኛ ትሕትና አሳይታለች። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ከቡችላ ጋር ባመሳሰላት ወቅት በተናገረው ነገር ቅር አልተሰኘችም፤ በወቅቱ አሕዛብ ቡችሎችን በቤታቸው ማሳደጋቸው የተለመደ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ አንተን እንዲህ ቢልህ ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ‘ተሰደብኩ’ ብለህ የእሱን እርዳታ ለማግኘት መሞከርህን ታቆማለህ? ፊንቄያዊቷ ሴት ግን እንዲህ አላደረገችም። ትሕትና ብቻ ሳይሆን ጽናትም አሳይታለች። ኢየሱስ እንዲረዳት በድጋሚ መለመኗ ይህን ያሳያል። እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳት ምንድን ነው? በኢየሱስ ላይ ያላት እምነት ነው። እንዲያውም ኢየሱስ በሴትየዋ እምነት በጣም ስለተገረመ አንድ አስደናቂ ነገር ለማድረግ ተነሳስቷል። “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች [ነው]” ብሏት የነበረ ቢሆንም ከአሕዛብ ወገን ከሆነችው ከዚህች ሴትዮ ልጅ ላይ ርኩሱን መንፈስ አስወጣላት።

አንዲት ፊንቄያዊት ሴት ተንበርክካ ኢየሱስን እንዲረዳት ስትለምነው። ኢየሱስና ሦስት ደቀ መዛሙርቱ በመመገቢያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ያዳምጧታል።

ፊንቄያዊቷ ሴት የምትፈልገውን እርዳታ ለማግኘት ትሕትና፣ ጽናትና እምነት አስፈልጓታል (አንቀጽ 5ን ተመልከት)


6. ስለ ፊንቄያዊቷ ሴት ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 እኛም መንፈሳዊ ጥማታችንን ለማርካት እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብናል። ትሕትና፣ ጽናትና ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። አምላክ እንዲረዳቸው በጽናት የሚለምኑት ትሑት የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። በተጨማሪም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ጠንካራ እምነት ሊኖረን እንዲሁም እሱ ደቀ መዛሙርቱን ለመምራት በሾማቸው ሰዎች ልንተማመን ይገባል። (ማቴ. 24:45-47) ይሖዋና ልጁ እንዲህ ያለ ባሕርይ በሚያሳዩ ሰዎች ይደሰታሉ፤ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውንም ያሟሉላቸዋል። (ከያዕቆብ 1:5-7 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ቀጥሎ ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ የሚሰጠን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ንጉሥ ዳዊት የተዉትን ምሳሌ በማየት እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን እንመረምራለን።

እንደ ጴጥሮስ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችሁን ቀጥሉ

7. ጴጥሮስ ምን ትእዛዝ ተሰጥቶታል? እሱ ራሱስ ምን ማድረግ ነበረበት? አብራራ። (ዕብራውያን 5:14–6:1)

7 እስቲ የሐዋርያው ጴጥሮስን ምሳሌ እንመልከት። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ከተገነዘቡት የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን መካከል አንዱ ነው፤ ይሖዋ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ለማስተማርና ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለመመገብ በኢየሱስ እየተጠቀመ እንዳለ አስተውሏል። (ዮሐ. 6:66-68) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ጴጥሮስን “ግልገሎቼን መግብ” በማለት አዞታል። (ዮሐ. 21:17) ጴጥሮስ ይህን ትእዛዝ በታማኝነት ፈጽሟል። እንዲያውም ይሖዋ ሁለት ደብዳቤዎችን እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል፤ እነዚህ ደብዳቤዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነዋል። ሆኖም ጴጥሮስ ራሱንም በመንፈሳዊ መመገብ ነበረበት። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ የጻፋቸውን ደብዳቤዎች አጥንቶ ነበር። ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ የጻፋቸው አንዳንዶቹ ነገሮች “ለመረዳት የሚከብዱ” እንደሆኑ ተናግሯል። (2 ጴጥ. 3:15, 16) ሆኖም ጴጥሮስ ተስፋ አልቆረጠም፤ ይሖዋ ይህን “ጠንካራ ምግብ” ለማብላላት ማለትም ለመረዳትና በሥራ ላይ ለማዋል እንደሚረዳው ተማምኖ ነበር።—ዕብራውያን 5:14–6:1ን አንብብ።

8. ጴጥሮስ የአምላክ ወኪል ለገለጠለት አዲስ ብርሃን ምን ምላሽ ሰጥቷል?

8 ጴጥሮስ የተሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለው አሳይቷል። ለምሳሌ በኢዮጴ ከተማ ሳለ አንድ ራእይ ተመለከተ። በራእዩ ላይ አንድ የአምላክ ወኪል በሙሴ ሕግ መሠረት ርኩስ የሆኑ እንስሳትን አርዶ እንዲበላ ነገረው። ለአይሁዳውያን እንዲህ ያለው መመሪያ አስደንጋጭ ነው። መጀመሪያ ላይ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ፣ በጭራሽ፤ ምክንያቱም እኔ ንጹሕ ያልሆነና የረከሰ ነገር በልቼ አላውቅም።” ከዚያም “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” የሚል መልስ ተሰጠው። (ሥራ 10:9-15) በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ አስተሳሰቡን አስተካከለ። ይህን እንዴት እናውቃለን? ራእዩን ካየ ብዙም ሳይቆይ፣ ከአሕዛብ ወገን የሆነው ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሦስት ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጥተው ጌታቸውን ሄዶ እንዲያነጋግረው ጠየቁት። በፊት ቢሆን ኖሮ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ወደሆነ ሰው ቤት ለመግባት ፈጽሞ አይስማማም ነበር። ምክንያቱም አይሁዳውያን አሕዛብን እንደ ርኩስ ይመለከቷቸው ነበር። (ሥራ 10:28, 29) ሆኖም ጴጥሮስ ይሖዋ የገለጠለትን አዲስ ብርሃን ወዲያውኑ ተቀብሏል። (ምሳሌ 4:18) ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ የሰበከላቸው ሲሆን እውነትን ሲቀበሉ፣ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድባቸውና ሲጠመቁ የማየት መብት አግኝቷል።—ሥራ 10:44-48

9. አዘውትረን ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን የትኞቹን ሁለት ጥቅሞች ያስገኝልናል?

9 እንደ ጴጥሮስ ሁሉ እኛም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ወተት አዘውትረን መጠጣት ማለትም መሠረታዊ እውነቶችን ማጥናት ይኖርብናል። በተጨማሪም ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ማለትም ለመረዳት ከባድ የሆኑ እውነቶችን የማጥናት ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። የአምላክን ቃል በጥልቀት ለመረዳት ጊዜ መመደብና ጥረት ማድረግ ይጠይቃል፤ ሆኖም ጥረቱ የሚያስቆጭ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ቢያንስ በሁለት መንገዶች ጥቅም ስለምናገኝ ነው። አንደኛ፣ ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አድናቆት የሚያሳድጉ ነገሮችን እንማራለን። ሁለተኛ፣ ስለ አስደናቂው የሰማዩ አባታችን ለሌሎች ለመናገር ይበልጥ እንነሳሳለን። (ሮም 11:33፤ ራእይ 4:11) ከጴጥሮስ ምሳሌ የምናገኘው ሌላም ትምህርት አለ፦ ስለ አምላክ ቃል ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ሲደረግ አስተሳሰባችንንና ምግባራችንን ለማስተካከል ፈጣኖች መሆን ይኖርብናል። በመንፈሳዊ ራሳችንን መገንባትና ይሖዋ የሚጠቀምብን ሰዎች መሆን የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።

እንደ ጳውሎስ መንፈሳዊ ልብስ ልበሱ

10. መንፈሳዊ ልብስ መልበስ ምን ያካትታል? (ቆላስይስ 3:8-10)

10 ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን እሱ ካደረገው ሌላም ዝግጅት መጠቀም ይኖርብናል፤ ይህም መንፈሳዊ ልብስ ነው። “መንፈሳዊ ልብስ” ስንል ምን ማለታችን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘አሮጌውን ስብዕና ገፈን መጣልና አዲሱን ስብዕና መልበስ’ እንዳለብን ጽፏል። (ቆላስይስ 3:8-10ን አንብብ።) አዲሱን ስብዕና መልበስ በቀጣይነት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የራሱን የጳውሎስን ሁኔታ እንመልከት። ከወጣትነቱ ጀምሮ አምላክን ለማስደሰት ይጥር ነበር። (ገላ. 1:14፤ ፊልጵ. 3:4, 5) ሆኖም ስለ አምላክ ዓላማ ትክክለኛ እውቀት ስላልነበረው በመንፈሳዊ ተጎድቶ ነበር። የክርስቶስን ትምህርት አለማወቁ ኩራተኛ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ መጥፎ ባሕርያትን የለበሰ “እብሪተኛ” ሰው አድርጎት ነበር።—1 ጢሞ. 1:13

11. ጳውሎስ ከየትኛው ድክመቱ ጋር መታገል አስፈልጎታል? አብራራ።

11 ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ቁጡ ሰው ነበር። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ጳውሎስ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በጣም ከመናደዱ የተነሳ ‘እንደዛተባቸውና እነሱን ለመግደል ቆርጦ እንደተነሳ’ ይናገራል። (ሥራ 9:1) ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የአሮጌው ስብዕና ክፍል የሆነውን ይህን ባሕሪውን ለማስወገድ ጥረት አድርጎ መሆን አለበት። (ኤፌ. 4:22, 31) ያም ቢሆን በጳውሎስና በበርናባስ መካከል አለመግባባት በተፈጠረበት ወቅት በመካከላቸው “ኃይለኛ ጭቅጭቅ” ተነስቶ ነበር። (ሥራ 15:37-39) በዚህ ወቅት ጳውሎስ በድክመቱ ቢሸነፍም ተስፋ አልቆረጠም። የይሖዋን ሞገስ ላለማጣት ሲል ‘ሰውነቱን መጎሰሙን’ ማለትም ከአለፍጽምናው ጋር መታገሉን ቀጥሏል።—1 ቆሮ. 9:27

12. ጳውሎስ መጥፎ ባሕርያቱን ገፎ ለመጣል የረዳው ምንድን ነው?

12 ጳውሎስ መጥፎ ባሕርያቱን ገፎ በመጣልና አዲሱን ስብዕና በመልበስ ረገድ ሊሳካለት የቻለው በራሱ ኃይል ስላልታመነ ነው። (ፊልጵ. 4:13) ልክ እንደ ጴጥሮስ ሁሉ ጳውሎስም “አምላክ በሚሰጠው ኃይል” ታምኗል። (1 ጴጥ. 4:11) እርግጥ ጳውሎስ የከንቱነት ስሜት የተሰማው ጊዜ ነበር። ሆኖም እንዲህ ሲሰማው የሰማዩ አባቱ ያደረገለትን ጥሩ ነገሮች ያስብ ነበር። ይህም ከድክመቶቹ ጋር መታገሉን ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል።—ሮም 7:21-25

13. ጳውሎስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

13 እኛም ጳውሎስን መምሰል እንችላለን። ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገልን ቢሆንም አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣልና አምላክ ያዘጋጀልንን መንፈሳዊ ልብስ ማለትም አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። በድክመታችን ብንሸነፍ፣ ለምሳሌ ቁጣችንን መቆጣጠር ቢያቅተን ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ አንድን ሰው ብናነጋግር የከንቱነት ስሜት ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን ለመለወጥ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። (ሮም 12:1, 2፤ ኤፌ. 4:24) እንዲህ ስናደርግ ግን አንድ እውነታ ማስታወስ አለብን፦ አንድ ልብስ ልካችን ካልሆነ መስተካከል ይችላል፤ ይሖዋ ከሚሰጠን መንፈሳዊ ልብስ ጋር በተያያዘ ግን መስተካከል ያለብን እኛ ነን። ደግሞም የአምላክን መሥፈርቶች ለማሟላት መስተካከል ያለብን እኛ ነን ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።

እንደ ዳዊት በመንፈሳዊው መጠለያ ተጠለሉ

14-15. ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንፈሳዊ መጠለያ ያዘጋጃል ሲባል ምን ማለት ነው? (መዝሙር 27:5) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከመንፈሳዊ ምግብና ከመንፈሳዊ ልብስ በተጨማሪ መንፈሳዊ መጠለያም ያስፈልገናል። መንፈሳዊ መጠለያ ምንድን ነው? በዚህ መጠለያ ሥር ጥበቃ ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው?

15 ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ ስላዘጋጀው መንፈሳዊ መጠለያ ተናግሯል። (መዝሙር 27:5ን አንብብ።) ይሖዋ ሕዝቦቹን ዘላቂ መንፈሳዊ ጉዳት ከሚያደርስ ከማንኛውም ጉዳት ይጠብቃቸዋል። ይሖዋ አገልጋዮቹን ከውጫዊ አደጋ የሚጠብቃቸው እንዴት ነው? እነሱን ለማጥቃት የሚሠራ ማንኛውም መሣሪያ እንደሚከሽፍ ቃል ገብቷል። (መዝ. 34:7፤ ኢሳ. 54:17) ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ ኃያል ቢሆኑም ምንም ዓይነት ዘላቂ ጉዳት ሊያደርሱብን አይችሉም። ሕይወታችንን እንድናጣ ቢያደርጉን እንኳ ይሖዋ በትንሣኤ ከሞት ያስነሳናል። (1 ቆሮ. 15:55-57፤ ራእይ 21:3, 4) በተጨማሪም ይሖዋ ውስጣዊ ፈተናዎችን ማለትም ዘላቂ ጉዳት ሊያደርሱብን የሚችሉ አስጨናቂ ሁኔታዎችን እንድንቋቋም ይረዳናል። (ምሳሌ 12:25፤ ማቴ. 6:27-29) ከዚህም ሌላ አፍቃሪው አባታችን የሚደግፉን መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶችን እንዲሁም እረኛ የሆኑ ሽማግሌዎችን ሰጥቶናል። (ኢሳ. 32:1, 2) በስብሰባ ላይ ስንገኝ የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች እንማራለን።—ዕብ. 10:24, 25

አንዲት እህት “በመጠበቂያ ግንብ” ጥናት ላይ ሐሳብ ለመስጠት እጇን ስታወጣ። ሌሎች ወንድሞችና እህቶችም እጃቸውን አውጥተዋል።

አንዲት እህት ከወንድሞቿና ከእህቶቿ ጋር በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝታ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ (አንቀጽ 14-15ን ተመልከት)


16. ይሖዋ ለዳዊት ጥበቃ ያደረገለት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

16 ዳዊት ይሖዋን በታዘዘበት ወቅት ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ከሚደርስባቸው ጉዳት ጥበቃ አግኝቷል። (ከምሳሌ 5:1, 2 ጋር አወዳድር።) በአንጻሩ ግን ዳዊት የአምላክን መሥፈርቶች በጣሰ ጊዜ የሠራው ስህተት ካስከተለበት መዘዝ ይሖዋ አልጠበቀውም። (2 ሳሙ. 12:9, 10) እርግጥ ዳዊት ያለጥፋቱ መከራ የደረሰበት ጊዜም አለ። ስለ እነዚህ ጊዜያትስ ምን ማለት ይቻላል? ዳዊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመው በይሖዋ ፊት ልቡን ያፈስ ነበር፤ ይሖዋም ዳዊትን እንደሚወደውና እንደሚንከባከበው አስታውሶታል፤ በዚህ መንገድ ከልክ በላይ እንዳይጨነቅ ረድቶታል።—መዝ. 23:1-6

17. የዳዊትን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

17 ውሳኔዎችን ስናደርግ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠን በመጠየቅ ዳዊትን መምሰል እንችላለን። በተጨማሪም መጥፎ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ወቅት ይሖዋ ውሳኔዎቻችን ከሚያስከትሉት መዘዝ እንደማይከልለን ማስታወስ ይኖርብናል። (ገላ. 6:7, 8) ያለጥፋታችን መከራ በሚደርስብን ጊዜ ደግሞ ይሖዋ ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅልን በመተማመን ወደ እሱ በጸሎት እንቀርባለን።—ፊልጵ. 4:6, 7

መንፈሳዊ ጥማታችሁን ማርካታችሁን ቀጥሉ

18. ምን ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመናል? መንፈሳዊ ጥማታችንን ማርካታችንን መቀጠል የምንችለውስ እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

18 የ2026 የዓመት ጥቅስ እንዲህ ይላል፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።” ይህን ማድረጋችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም በዙሪያችን የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች መንፈሳዊ ጥማት የላቸውም፤ ወይም ይህን ጥማታቸውን ለማርካት የሚሞክሩት በሐሰት ሃይማኖት ወይም በሰብዓዊ ፍልስፍና አማካኝነት ነው። በዚህም ምክንያት ደስታ ርቋቸዋል። የእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ያዘጋጀልንን መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ፣ አዲሱን ስብዕና በመልበስ እንዲሁም በይሖዋ ጥበቃ ሥር በመጠለል ነው።

ሥዕሎች፦ ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የነበረችው እህት መንፈሳዊ ጥማቷን ስታረካ። 1. “መጠበቂያ ግንብ” ስትዘጋጅ። 2. ወደ አንድ ባልና ሚስት ቤት ሄዳ ምግብ ስታደርስላቸው። ባልየው ጭንቅላቱ በፋሻ ተጠቅልሎ ሶፋ ላይ ተቀምጧል፤ እጁ ላይ የግሉኮስ መስጫ ተሰክቷል። 3. ሁለት ወንድሞች እረኝነት ሲያደርጉላት።

ይሖዋ ካዘጋጀልን መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ በመጠቀም መንፈሳዊ ጥማታችንን ማርካት ይኖርብናል (አንቀጽ 18ን ተመልከት)a

ይሖዋ ካደረገልን ከሚከተሉት ዝግጅቶች መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

  • መንፈሳዊ ምግብ

  • መንፈሳዊ ልብስ

  • መንፈሳዊ መጠለያ

መዝሙር 162 ልቤ ቃሉን ይጠማል

a የሥዕሉ መግለጫ፦ ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የነበረችው እህት መጠበቂያ ግንብ በመዘጋጀት መንፈሳዊ ምግብ ስትመገብ፣ ለሌሎች ደግነት በማሳየት አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት ስታደርግ እንዲሁም የሽማግሌዎችን ፍቅራዊ እርዳታ ስትቀበል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ