Thai Liang Lim/E+ via Getty Images
ነቅታችሁ ጠብቁ!
ማኅበራዊ ሚዲያ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኗል
በ2025 በዓለም ዙሪያ የተለያዩ አገራት ማኅበራዊ ሚዲያ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ስጋት እንደሆነባቸው እየገለጹ ነው። ለአብነት ያህል፣ አንድ አገር ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አግዷል፤ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እያሰቡ ነው።
የሚገርመው ደግሞ ይኸው ስጋት ከራሳቸው ከልጆቹ መስተጋባቱ ነው። አሜሪካ ውስጥ አንድ ድርጅት ስለዚህ ጉዳይ ጥናት አካሂዶ ነበር፤ የጥናቱን ውጤት ሚያዝያ 2025 ላይ ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዲህ የሚል መረጃ አስነብቧል፦ “ከታዳጊዎች መካከል ግማሽ ገደማ (48 በመቶ) የሚሆኑት፣ [የማኅበራዊ ሚዲያ] ድረ ገጾች በእኩዮቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ይናገራሉ።
የጤና ባለሙያዎች፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በልጆች አእምሮ ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት የአሜሪካ የማኅበረሰብ ጤና ባለሥልጣን የነበሩት ዶክተር ቪቬክ ሙርቲ እንዲህ ብለዋል፦ “በወጣቶች ላይ እየታየ ያለው የአእምሮ ጤና ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ለዚህ ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ እንደሆነ ተስተውሏል።”
ወላጆች፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ከሚያስከትለው አደጋ ልጆቻቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ምክሮች ይዟል።
ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?
እስቲ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተመልከት።
“ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15
ማኅበራዊ ሚዲያ ካሉት አደጋዎች አንጻር ልጃችሁን እንዳይጠቀም ብትከለክሉት ስህተት እንደሆነ አይሰማችሁ። ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ከመፍቀዳችሁ በፊት የፈቀዳችሁለትን የጊዜ ገደብ ማክበር፣ ጤናማ ወዳጅነት መመሥረትና ተገቢ ካልሆነ ነገር መራቅ የሚችልበት የብስለት ደረጃ ላይ መድረሱን አረጋግጡ።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ልጄ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ልፍቀድለት?” እና “በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያን በማይጎዳ መንገድ እንዲጠቀም ማሠልጠን” የሚሉትን ርዕሶች አንብቡ።
“ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:16
ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ከፈቀዳችሁ ስለ አጠቃቀሙ ደንቦች አውጡ፤ እንዲሁም እነዚህ ደንቦች ለደህንነቱ እንደሚጠቅሙት አስረዱት። በልጃችሁ ጠባይ ላይ ለውጥ ካለ በንቃት ተከታተሉ፤ ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ ላይ ተጨማሪ ገደብ መጣል እንዳለባችሁ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።
ገደቦች አስፈላጊ የሆኑት ለምን እንደሆነ ለልጃችሁ ለማስረዳት ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ስትጠቀም አስተዋይ ሁን የሚለውን የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን ቪዲዮ መጠቀም ትችላላችሁ።
ለወላጆች የሚጠቅሙ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮችን ማግኘት ከፈለግህ “አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በወጣቶች ላይ ስለደቀነው ስጋት አስጠነቀቁ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ግንዛቤያችሁን አስፉ
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) መጽሐፍ ቅዱስ የዘመኑን አስከፊነት ከመናገር ባለፈ ሁኔታውን ለመቋቋም የሚረዱ ዘመን የማይሽራቸው ምክሮች ይዞልናል። “የወጣቶች የአእምሮ ጤንነት ማሽቆልቆል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” የሚለው ርዕስ ለወላጆችና ለልጆች ታስበው የተዘጋጁ ከ20 በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን ይዘረዝራል።