መጽሐፍ ቅዱስን በመማራቸው ሕይወታቸው ተለውጧል
ይህ ርዕስ የቬትናም ተወላጅ የሆኑ ሁለት ሰዎችን ታሪክ ይዟል። እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ አስደናቂ ለውጥ አድርገዋል። አብዛኛውን የሕይወታቸውን ክፍል፣ አስደሳችና አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት ቁልፉ ሀብታም መሆን እንደሆነ ያምኑ ነበር። እንዲያውም ሀብት ለማግኘት ሲሉ በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም ነበር። በኋላ ላይ ግን እውነተኛ ሰላምና እርካታ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስን በመማር ብቻ እንደሆነ ተገነዘቡ። የእነሱ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ኃላፊነት የሚሰማን፣ ሕግ አክባሪና በሥነ ምግባር የታነጽን ዜጎች ለመሆን የሚረዱን እንዴት እንደሆነ ያሳያል።
ገንዘብ ማሳደዱን ትቶ እውነተኛ ደስታ አገኘ
ላን ቫን ንጉየን ያደገው በጦርነት፣ በብጥብጥና በድህነት በተሞላ አካባቢ ነው። በጊዜ ሂደት፣ አንድ ሰው ደስተኛ ሊሆን የሚለው ሀብታም ከሆነ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ጀመረ። በ1988 ሥራ ፍለጋ ወደ ጀርመን ሄደ። በዚያም ገንዘብ ለማግኘት ሲል ሌት ተቀን ይሠራ ጀመር።
ከአሥር ዓመት በኋላ ላን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። እነሱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለሆነው ስለ ምሳሌ መጽሐፍ ነገሩት። ላን ምሳሌያዊ አነጋገሮችንና አባባሎችን መሰብሰብ ያስደስተው ስለነበር ምሳሌ መጽሐፍን ወደደው። መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር እንደያዘ ሲያውቅ ይበልጥ ለመማር ተነሳሳ። በመሆኑም ያነጋገረችውን የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስ እንድትገዛለት ጠየቃት። እሷም ከእሷና ከባለቤቷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለመወያየት ፈቃደኛ ከሆነ በነፃ እንደሚሰጡት ነገረችው። በቀጣዩ ጊዜ ስትሄድ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር የሚረዳ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ መጽሐፍ ይዛለት ሄደች።
ላን የተሰማራበት ንግድ መሣሪያዎችን መግዛትና መሸጥ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲማር ‘ይህ ንግድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ያስኬዳል?’ ብሎ ማሰብ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ንግዱን ማቆም እንዳለበት ተገነዘበ። ካቆመ በኋላ ግን ገቢው 80 በመቶ ቀነሰ። ስለዚህ ስለ ጉዳዩ ጸለየ። ከዚያም ሌሎች ነገሮችን መሸጥ ጀመረ። ቀስ በቀስ ገቢው እየጨመረ መጣ።
ላን ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥቶ ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ፈለገ። ግን ጀርመንኛ በደንብ አለመቻሉ የተማረውን ነገር እንደ ልቡ ለሌሎች እንዳያካፍል እንቅፋት ሆነበት። ስለዚህ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ሲል ወደ ትውልድ አገሩ ቬትናም ተመለሰ።
ላን መጽሐፍ ቅዱስን ከተማረ በኋላ አስተሳሰቡም ሆነ አኗኗሩ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። አሁን እሱ፣ ሚስቱና ልጆቹ በደስታ እየኖሩ ነው።
ላን እና ባለቤቱ
ወንጀለኛነቱን ትቶ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ጀመረ
ታንግ ቪየት ፉንግ የተወለደው በ1976 በኔ አን፣ ቬትናም ነው። በ19 ዓመቱ ሀብት ለማሳደድ ሲል ከቤት ወጣ። ከዚያም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ጀርመን ገባ። በዚያ ሳለ በወንጀል እንቅስቃሴው የሚታወቅን አንድ የወሮበሎች ቡድን ተቀላቀለ። ታንግ ሽጉጥ አይለየውም ነበር፤ ሲተኛም እንኳ ትራሱ ሥር አድርጎት ነበር የሚተኛው። ከጊዜ በኋላ የእገታ ወንጀል በመፈጸሙ ተይዞ የስድስት ዓመት እስራት ተፈረደበት። ሆኖም ሁለት ዓመት ብቻ ታስሮ ነፃ ተለቀቀ።
በኋላም ታንግ አዲስ የወሮበሎች ቡድን ተቀላቅሎ በወንጀሉ ገፋበት። በዚህም የተነሳ ድጋሚ ታሰረ። ሆኖም ፍርድ ቤት አልቀረበም። ምክንያቱም ወንጀሉን ሲፈጽም ያዩት ሰዎች በእሱ ላይ ለመመሥከር አልደፈሩም። ታንግ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ የወጣለት ወንጀለኛ ሆነ። በመጨረሻም ድጋሚ ተይዞ የአሥር ዓመት እስራት ተፈረደበት። አብረውት የታሰሩት ሰዎችም ሆኑ የእስር ቤት ጠባቂዎቹ የሚያውቁት ቁጡና ተደባዳቢ በመሆኑ ነበር።
በእስር ቤቱ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ይደረግ ነበር። አንድ ቀን አንድ እስረኛ ታንግን እዚህ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋበዘው። መጀመሪያ ላይ ታንግ ስብሰባው ላይ ለመገኘት አመንትቶ ነበር። ስብሰባው ላይ ሲገኝ ግን ከዚያ በፊት ተሰምቶት የማያውቀው ዓይነት ውስጣዊ ሰላም ተሰማው። በተጨማሪም በዚያ ስብሰባ ላይ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለ መጽሐፍ ተሰጠው። ታንግ ያን መጽሐፍ በአንድ ምሽት አንብቦ ጨረሰው። እዚያ መጽሐፍ ላይ ካሉት ምዕራፎች አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ የሚያስተምረውን ትምህርት ያብራራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ልክ እንደተኛ ሰው ምንም እንደማያውቁ ያስተምራል። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11-14) ከዚያ በፊት ታንግ የሞቱ ዘመዶቹ እንደሚያዩትና ጥበቃ እንደሚያደርጉለት ስለሚያምን ‘ታዲያ መጥፎ ነገር ሳደርግ ያልከለከሉኝ ለምንድን ነው?’ እያለ ያስብ ነበር።
ታንግ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘቱን ቀጠለ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በቋሚነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣል። ታንግ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በመገኘቱ አምላክ እሱን ጨምሮ ሁሉንም የሰው ልጆች እንደሚወድ ተማረ። ማድረግ ስላለበትና ስለሌለበትም ነገር በደንብ ማወቅ ቻለ። በተጨማሪም ለገንዘብ ያለውን የተጋነነ አመለካከት ለማስተካከልና ባሕርይውን ለማሻሻል ጠንክሮ መሥራት ጀመረ። ከሁሉ የከበደው ቁጣውን መቆጣጠር ነበር። ግን በጸሎትና በብዙ ጥረት መጨረሻ ላይ ተሳካለት። በ2009 እዚያው እስር ቤት እያለ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በኋላም ታንግ ወደ ቬትናም ተመለሰ። እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት አለኝ። እኔና ቤተሰቤ ይሖዋ አምላክን በአንድነት እናገለግላለን። ይሖዋ ሕይወቴን አትርፎልኛል። አትረፍርፎ ባርኮኛል። ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ ‘ይሖዋን ባላውቅ ኖሮ መጨረሻዬ ምን ይሆን ነበር?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ።”
ታንግ እና ቤተሰቡ
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጥሩ ዜጎችን ለማፍራት ያስችላል
ላን እና ታንግ በሕይወታቸው ላይ ያደረጉት ለውጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው። ሁለቱም ገንዘብ ማሳደዳቸውን ትተዋል። በአንድ ወቅት፣ ደስታ የሚያስገኘው ሀብታም መሆን ብቻ ነው ብሎ ያምን የነበረው ላን አሁን ከእምነቱና ከቤተሰብ ሕይወቱ እውነተኛ ደስታ ማግኘት ችሏል። ሀብታም ለመሆን ሲል ምንም ዓይነት ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ የማይለው ታንግ ደግሞ አሁን ሰዎች ሐቀኛና ሕግ አክባሪ እንዲሆኑ እያስተማረ ይገኛል። ሁለቱም ለማኅበረሰባቸው ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሰዎች ሆነዋል። ትኩረታቸው ያረፈው ሀብት በማካበት ላይ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ላይ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሰዎች ትርጉም ያለውና አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ እንዲሁም ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ ይረዳሉ።