በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ማሠልጠን
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ፣ አእምሯቸውንና ልባቸውን በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት መሠረታዊ ትምህርቶች ያለፉ ነገሮችን መመገብ አለባቸው። (ዕብ. 5:12–6:1) ጥናት ደግሞ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። ይህም አዲስ ያገኘነውን እውቀት ከዚህ በፊት ከምናውቀው ጋር ማዛመድንና ይህ እውቀት የሚያስገኝልንን ጠቀሜታ ማስተዋልን ይጨምራል። (ምሳሌ 2:1-6) ጥናቶቻችን እንዴት ምርምር ማድረግ እንደሚችሉ መማራቸው፣ ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያስችላቸዋል። ጥናቶቻችን የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግ ከልብ ጥረት ማድረጋቸው፣ ክርስቲያን በመሆናቸው ምክንያት ወደፊት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲቋቋሙ ያስችላቸዋል።—ሉቃስ 6:47, 48
በዚህ ወር እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦
አንድን ንዑስ ርዕስ ወይም ምዕራፍ አጥንታችሁ ስትጨርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ የተማረውን ነገር በአጭሩ እንዲከልስልህ አድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሌለህ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ወይም የመጠበቂያ ግንብ አንቀጽ እንዴት በአጭሩ መከለስ እንደምትችል በመለማመድ፣ አንብቦ የመረዳት ችሎታህን ለማሳደግ ጥረት አድርግ።