እምነትን የሚፈታተን የሕክምና ሁኔታ ቢያጋጥምህ ለመቋቋም ዝግጁ ነህን?
ይህን ማብራሪያ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በፍጥነት ልታገኘው በምትችልበት ቦታ አስቀምጠው
1 ማንም ሰው ዛሬ ወይም ነገ ሆስፒታል ሊገባ እንደሚችል እምብዛም አያስብም። ይሁንና ‘ጊዜና አጋጣሚ የሚያመጣው አይታወቅም።” (መክ. 9:11) ለጤናህ እንክብካቤ ለማድረግ የመድሃኒት ሕክምናን የማትመርጥ ብትሆንም እንኳን አንድ ዓይነት አደጋ ደርሶብህ ራስህን ስተህ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድ ደም እንዳይሰጡህ ለመከላከል ምን ታደርጋለህ? አዎን፣ አደጋ ወይም ድንገተኛ የጤና መቃወስ ችግር እምነትህን ከሚፈታተን ሁኔታ ጋር በድንገት እንድትፋጠጥ ሊያደርግህ ይችላል።
2 በአንድ ምክንያት ሆስፒታል ለመግባት ብትገደድና በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው ደም ካልወሰድክ ትሞታለህ ቢልህ ንጹሕ አቋምህን ለመጠበቅ ምን ታደርጋለህ? በችኮላ ይህ አባባል የአንተን ሁኔታ በትክክል እንደሚገልጽ አድርገህ ትቀበለዋለህን? ደም መውሰድ እንደሌለብህ ሙሉ በሙሉ ታምንበታለህን? ይህንን የእምነት ፈተና ለመቋቋምና ‘ከደም ለመራቅ’ ዝግጁ ነህን?—ሥራ 15:28,29
3 የማይፈለገውን፣ በመንፈሳዊም የሚበክለውን በሕክምና ደም የመውሰድ እርምጃ ለመቋቋም የምትችለው በመጀመሪያ በነገሩ ጽኑ እምነት ካለህ ነው። እንደዚህ ያለው ጽኑ እምነት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገረውን በግልጽ በመረዳት ላይ መመሥረት ይኖርበታል። ያለበለዚያ ግን በጊዜያዊ ስሜት በቀላሉ ተደናግጠህ ከአንተ ይልቅ ስለ ሁኔታው የበለጠ አውቃለሁ የሚለው ሰው የነገረህን እሺ ልትል ትችላለህ። ምናልባት ዶክተሮች ስለ ደም ከአምላክ የበለጠ ሳያውቁ አይቀሩም ብለህ በማሰብ ትታለል ይሆን? በእርግጥም በእነዚህ ሁኔታዎች ሥር ማንኛውም ተራ ሰው ምንም ይበል ምን በይሖዋ ዓይን ‘ትክክል’ የሆነውን ለማድረግ ‘ቁርጥ ውሳኔ ያደረግህ’ መሆን ያስፈልግሃል። (ዘዳ. 12:23-25) ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ፈተና ብቻህን መቋቋም ይኖርብሃልን?—መክ. 4:9-12
የሆስፒታል የመረጃ አገልግሎቶችና የሆስፒታል ጉዳይ የሚከታተሉ ኮሚቴዎች
4 በሕክምና ደም የመውሰድ ፈተና በሚያጋጥማቸው ጊዜ እርዳታ የሚፈልጉትን ለመርዳት ማኅበሩ በብሩክሊን የሆስፒታል መረጃ አገልግሎቶችን እና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የሆስፒታል ጉዳይ የሚከታተሉ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። እነዚህ ኮሚቴዎች በተለይ ለዚህ ሥራ የሰለጠኑ ሽማግሌዎች አባል የሆኑባቸው ናቸው።
5 የሆስፒታል መረጃ አገልግሎቶች ያለ ደም የሚደረግ ብዙ ዓይነት ቀዶ ጥገናና ሕክምና ስለመኖሩና ስለ ውጤታማነቱ መረጃ ለማግኘት ከመላው ዓለም በተገኙ ከ3, 600 በሚበልጡ የሕክምና መጽሔቶች ላይ ምርምር ለማድረግ ይችላል። ከዚያም ለሆስፒታል ጉዳይ ኮሚቴዎች፣ ለጤና እንክብካቤ ጣቢያዎችና ለአንዳንድ ዶክተሮች ስለነዚህ የሕክምና ግኝቶች አንዳንድ መረጃዎችን ያቀርባል። (አንዳንድ ጊዜ የሆስፒታል መረጃ አገልግሎቶች ያለ ደም ምን ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳዩ የሕክምና መረጃዎች በመላክ በሆስፒታሉ የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ ተሳክቶለታል።) ዳኞች ጉዳያችንን በተጨማሪ ማስተዋል እንዲያዩት የሚያስችሉ ትክክለኛ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን የሚገልጹ ሰነዶችን በየጊዜው ለኮሚቴዎቹ ይልካል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር ሊተባበሩ ፈቃደኛ ስለሆኑ ሐኪሞች የሚገልጹ መዝገቦችን ይይዛል። ይህም የተደረገው ኮሚቴዎቹ ደም የመውሰድ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ ሊያገለግሉ የሚችሉ ወቅታዊ የሆኑ ፋይሎች እንዲኖራቸው ሲባል ነው።
6 የሆስፒታል መረጃ አገልግሎቶች በተጨማሪ የሆስፒታል ጉዳይ ኮሚቴዎችን ሥልጠናና ሥራ ይቆጣጠራል። የሆስፒታል ጉዳይ የሚከታተሉ ኮሚቴዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ከሆስፒታል ሠራተኞች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ዘወትር ቀርበው አንዳንድ ገለጻዎችን ያደርጉላቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ ኮሚቴዎች ያለ ደም ሊያክሙን የሚችሉ ተጨማሪ ዶክተሮችን እንዲፈልጉ ይረዱአቸዋል። እነዚህ ወንድሞች አንተን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱ ይህንን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያከናውኑት መሠረት ለመጣል አንተም በቅድሚያ የምትወስዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች አሉ።
በቅድሚያ የምትወስዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች አሉ—ታዲያ እነዚህን እርምጃዎች ወስደሃልን?
7 በመጀመሪያ በቤተሰብህ ውስጥ ያሉት በሙሉ በተሟላ ሁኔታ የተሞላ፣ ጊዜ ያላለፈበት፣ የተፈረመበትና የምሥክሮቹ ስምና ፊርማ ያለበት የግል የሕክምና መረጃ ሰነድ (ግለሰቡ ስለ ደም ያለውን አቋም የሚገልጽ ሰነድ ነው) ያላቸው መሆኑን አረጋግጥ። አንዳንድ ወንድሞች ቀኑ ያለፈበት ወይም የምሥክሮች ስምና ፊርማ የጐደለው ካርድ ይዘው ወደ ሆስፒታል በመሄዳቸው ሰነዱ ዋጋ የለውም የሚል ክርክር ተነስቷል። እንዲሁም ያልተጠመቁ ልጆቻችንን በሙሉ በደንብ የተሞላ ስለ ደም ያላቸውን አቋም የሚገልጽ መታወቂያ ካርድ አላቸውን? ይህ ካልሆነ በልጆቻችን ላይ አንድ ድንገተኛ አደጋ ቢደርስ ሆስፒታሉ ስለ ደም ያላችሁን አቋምና ማን መጠራት እንዳለበት እንዴት ለማወቅ ይችላል?
8 ከዚያም ሁሉም የቤተሰቡ አባሎች እነዚህ መታወቂያ ካርድ ይዘው እንደሚሄዱ አረጋግጡ። ልጆቻችሁ በየቀኑ ወደ ትምህርት ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ ለጨዋታ ወደ ሜዳ ወይም ወደ መዝናኛ ከመሄዳቸው በፊት መረጃዎቹን መያዛቸውን አረጋግጡ። ሁላችንም ወደ ሥራ ስንሄድ፣ እረፍት ወስደን ወደ አንድ ስፍራ ስንሄድ ወይም ክርስቲያናዊ በሆኑ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ እነዚህን ሰነዶች ስለመያዛችን እርግጠኞች እንሁን! በፍጹም አይለዩአችሁ!
9 እስቲ ከባድ አደጋ ደርሶብህ ራስህን ስተህ ወይም መናገር አቅቶህ በአንድ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ መግባት ብትገደድ ሊደርስ የሚችለውን ሁኔታ አስበው። ስለ ደም ያለህን አቋም የሚገልጸውን ካርድ ይዘህ ካልሆነ ወይም ስለ አንተ ሆኖም የሚናገር ዘመድ ወይም ሽማግሌ በሆስፒታሉ ውስጥ ከሌለና ‘ደም ያስፈልገዋል’ ተብሎ ከተወሰነ ደም ሊሰጥህ ይችላል። ይህ ነገር የደረሰባቸው አሉ። ሆኖም መረጃውን ከያዝን ፈቃዳችን ምን መሆኑን በመግለጽ ስለ እኛ ሆኖ ይናገራል።
10 የሕክምና መረጃ ሰነድ በክንድ ወይም በአንገት ላይ ከሚታሠር ደም አልወስድም ከሚል ጽሕፈት የተሻለ የሆነው ለዚህ ነው። ይህ ጽሕፈት ስለያዝነው አቋም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክንያቶችን አይገልጽም፤ በዚያ ላይ የተጻፈውን የሚያረጋግጥ ፊርማም የለበትም። አንዲት እህት ይዛው ስለነበረው የሕክምና አቋም የሚገልጽ ሰነድ አንድ የካናዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲህ አለ፦ “[በሽተኛው] ለዶክተሮችና የጤና እንክብካቤ ለሚያደርጉ ለሌሎች ሰዎች ስለ አቋሟ ለማሳወቅ የሚያስችላትን ብቸኛ መንገድ መርጣለች፤ ራስዋን የሳተች ትሁንም አትሁን ደም ላለመውሰድ ያላትን ፍላጎት ልትቀይር አትችልም።” እንግዲያው ሰነዱን በፍጹም ትታችሁት አትሂዱ!
11 የእኛ የሕክምና ሰነድ ለድንገተኛ አደጋ ብቻ የተዘጋጀ ሲሆን ደኅና እያለህ በዕቅድ የቀዶ ጥገና ምርጫ ስታደርግ አንዳንድ ዝርዝሮችን ማለትም ምን ዓይነት የቀዶ ጥገና እንደሚደረግልህና ከተቻለም የዶክተሮቹንና የሆስፒታሉን ስም በመጥቀስ የግልህ የሆነ፣ ይበልጥ የተሟላ አስቀድሞ የተዘጋጀ መመሪያ (በሕክምና መረጃችን ላይ የተመሠረተ) ጽፈህ መስጠትህን አስተዋይነት ነው። በብዙ አገሮች ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ የመረጠው ዓይነት ሕክምና እንዲደረግለት ለማረጋገጥ እንደዚያ ብሎ ለመጻፍ መብት አለው። አንተም ሆንክ ዶክተሩ ከባድ ችግሮች ይደርሳሉ ብላችሁ አስቀድማችሁ ባታስቡም ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙ እነዚህን መመሪያዎች መከተል እንደሚያስፈልግ ግለጽለት።—ምሳሌ 22:3
12 የሚቀጥለው አስፈላጊ እርምጃ ደግሞ ደኅና እያለህ የመረጥከው ዓይነት ወይም ድንገተኛ ሕክምና በሚደረግበት ጊዜ ምን እንዲደረግልህ እንደምትፈልግ አንተን በማከሙ ተግባር ላይ የሚገቡትን የሕክምና ባለሙያዎች ማነጋገር ነው። በተለይ ማነጋገር ያለብህ የትኞቹን ሰዎች ነው?
ሐኪሞችን ማነጋገር
13 የሕክምናው ቡድን። ሰውን መፍራት መታየት የማይገባው በዚህን ጊዜ ነው። (ምሳሌ 29:25) በአቋምህ እርግጠኛ መስለህ ካልታየህ ከልብህ እንደማታምንበት አድርገው ሊወስኑ ይችላሉ። በግል ምርጫም ይህን በድንገተኛ ጊዜ ቀዶ ጥገና እንዲደረግልህ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አንተ ወይም ቅርብ የቤተሰብ አባል ለቀዶ ጥገናው ቡድን መሪ ቁርጥ ሐሳብ ያለህ መሆኑን የሚያሳዩ ወሳኝ ጥያቄዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል። አንዱ አስፈላጊ ጥያቄ የሕክምና ቡድኑ በሁሉም ሁኔታዎች የበሽተኛውን ፍላጎቶች አክብሮ ያለ ደም ሕክምና ይሰጣል ወይ? የሚል ነው። ይህ ማረጋገጫ ካልተገኘ ከማይፈለግ ሕክምና እንደምትጠበቅ ልትተማመን አትችልም።
14 ፍላጎትህ ምን እንደሆነ በግልጽና አክብሮት ባለው የእርግጠኝነት መንፈስ አስረዳ። ያለ ደም ሌላ አማራጭ ሕክምና ቢደረግልህ እንደምትፈልግ ግልጽ አድርግ። ምን ዓይነት ሕክምና እንደምትፈልግ ስላጻፍከው መግለጫና ሆስፒታሉን ከተጠያቂነት ነፃ ስለሚያደርገው ቅጽ ረጋ ብለህ በቁርጠኝነት አወያያቸው። ሆስፒታሉ የዚህ ዓይነት ቅጽ ከሌለው የይሖዋ ምሥክሮችና የደም ጥያቄ (Jehovah’s Witnesses and the question of Blood) በተሰኘው ንዑስ መጽሐፍ ገጽ 29 አንቀጽ 2 ላይ የሚገኘውን ቅጽ እንደ መመሪያ አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ። የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ፍላጎትህን ለማሟላት ፈቃደኛ ካልሆነ ሌላ ዶክተር እንዲያገኙልህ የሆስፒታሉን አስተዳዳሪ (በተለይም የግል ሐኪም ቤት አስተዳዳሪ ከሆኑ) ጠይቅ። በብዙ አካባቢዎች አንዱ የሥልጠናው ክፍል ይህ ነው።
15 የአኔስተዥያ ሐኪም። ልታነጋግራቸው ከሚያስፈልጉህ ከሁሉም የሕክምና ቡድኖች መካከል ከዚህ ዶክተር ጋር ሳትነጋገር መቅረት የለብህም። ቀዶ ጥገናው በሚከናወንበት ጊዜ አንተን ህያው አድርጎ የማቆየት ኃላፊነት የተጣለበት ይህ ሐኪም አኔስተዝዮሎጂስቱ በደም መጠቀምና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ውሳኔ የሚያደርገው እርሱ ነው። ስለዚህ ከቀዶ ጥገና ሐኪሙ ጋር በመነጋገር ብቻ ከአደጋ ሙሉ በሙሉ ልትጠበቅ አትችልም። እንግዲያው አቋምህን የአነስተዝያውን ሐኪም ማነጋገርና ማሳመን ይኖርብሃል። ከዚያም አቋምህ ይከበርልህ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ አለብህ።—ከሉቃስ 18:3-5 ጋር አወዳድር።
16 በልምድ እንደታየው ከሆነ አኔስተዝዮሎጂስቱ በደም ላይ ያለህን አቋም የሚቃወም ከሆነ እንደ ነገ ቀዶ ጥገና ሊደረግልህ እንደ ዛሬ ማታ መጥቶ ላጭር ጊዜ አነጋግሮህ ይሄዳል። በምርጫህ ስለምታደርገው የቀዶ ጥገና ሕክምና በደንብ ልታነጋግረው የምትችል ተባባሪ አኔስተዝዮሎጂስት እንዲመርጥልህ የግል ዶክተርህን አስቀድመህ አጠንክረህ ጠይቀው። እንደዚያ ካደረግህ የመጀመሪያው ሐኪም ፈቃድህን ለማሟላት ባይስማማም እንኳ ሌላ ሰው ለመፈለግ ጊዜ ይኖርሃል። በተለይ በግል ሐኪም ቤቶች ውስጥ ለሚደረግልህ የቀዶ ጥገና ሕክምና ከአኔስተዝዮሎጂስቱ አርኪ ውጤት ለማግኘት መብት አለህ።
17 በዚህ ሁሉ ላይ ግን ደም አልወስድም የሚለው ለድርድር የማይቀርበውን አቋምህን ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል። ለአንተ የሚስማማ ያለ ደም የሚደረግ ሕክምና እንዲደረግልህ ጠይቅ። ለአንተ ሁኔታ የሚሆን በደም ፋንታ ሊደረግ የሚችል የምታውቀውን አማራጭ ሕክምና ሁሉ ጥቀስ። የሕክምና ቡድኑ እነዚህ ዘዴዎች ለአንተ ሁኔታ አይጠቅሙም ቢሉህ በሕክምና ጽሑፎች ውስጥ ሌሎች መንገዶች ካሉ ምርምር እንዲያደርጉ ጠይቃቸው። ምናልባትም የሚፈልጉ ከሆነ በጉባኤህ ሽማግሌዎችህ እርዳታ አንድ ዓይነት መረጃ ልታገኝላቸው ትችል ይሆናል። የሚቻል ከሆነ አንተ ወይም ሽማግሌዎቹ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው በማንኛውም ጊዜ ጽፋችሁ ሐሳብ ማግኘት ትችላላችሁ።
በመብቶችህ ተጠቀም
18 ለቀዶ ጥገና ሕክምና በምትገባበት ጊዜ ሆስፒታሉ እንድትፈርምበት የሚያቀርብልህን የውዴታና የግዴታ ቅጽ በጥንቃቄ መርምረው። አንዳንድ ጊዜ ፍላጎትህን እንደሚያከብሩ የሚገልጽ ሐተታ ከተጻፈ በኋላ በሚቀጥለው አንቀጽ ላይ ችግሮች ቢያጋጥሙ ሆስፒታሉ “ሕይወት አድን” ሕክምና ሊሰጥ እንደሚችል ፈራሚው የተስማማ መሆኑን የሚገልጽ ሐሳብ ይታከልበት ይሆናል። ይህ አባባል ደምን ሊጨምር ይችላል። እንደነዚህ ያሉት ዓረፍተ ነገሮች ደምን እንዳይጨምሩ አድርገህ ለመለወጥ ወይም ሁሉንም ለመሰረዝ መብት አለህ። ነርሶቹ ይህንን ማድረግ አትችልም ብለው ሊነግሩህ ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ትችላለህ። ማንም ሰው ከፈቃድህ ውጭ እንድትፈርም ሊያስገድድህ ቢሞክር አስተዳዳሪውን ወይም በዚያ የጤና ጥበቃ ጣቢያ ውስጥ የሕመምተኞች ተወካይ ካለ እርሱን ለማነጋገር እንደምትፈልግ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። እንደዚያ ለማድረግ ትችላለህን? አዎን፣ እንደ አንድ በሽተኛ መጠን የተወሰኑ መብቶች ስላሉህ ይህን ማድረግ ትችላለህ።
19 ከእነዚህ መብቶች አንዱ በዕውቀት የተደረገ ስምምነት መብት የሚባለው ነው። ይህም ሲባል ያለ አንተ ፈቃድ ምንም ዓይነት ሕክምና ሊሰጥ አይችልም ማለት ነው። ካልፈለግህ ሁሉንም ዓይነት ሕክምና አሻፈረኝ ለማለት ትችላለህ። ሕክምና እንዲደረግልህ አብዛኛውን ጊዜ የምትስማማው የሕክምና ቡድኑ ምን ለማድረግ ዕቅድ እንዳለው፣ ሊደርሱ ስለሚችሉ አደጋዎችም ጭምር ግልጽ ማብራሪያ ካገኘህ በኋላ መሆን አለበት። ቀጥሎ ስላሉት አማራጮች ሁሉ ሊነግሩህ ይገባል። ይህን ሁሉ እንድታውቅ ከተደረገ በኋላ የትኛውን ሕክምና እንደምትፈልግ ትመርጣለህ።
20 ስምምነት ስለምታደርግበት ነገር እርግጠኛ ለመሆን ስላልገቡህ አንዳንድ ነገሮች በተለይም ሐኪሙ ረዘም ያሉ ቃላትን ሲናገር ወይም በሕክምና ቃላት ሲጠቀም መጠየቅ አለብህ። ለምሳሌ ዶክተሩ “ፕላዝማ” እጠቀማለሁ ቢል “ፕላዝማ በደም ሥር ውስጥ የሚተላለፈው ፈሳሽ እንዳያንስ የሚጨመር ፈሳሽ” ማለቱ ነው ብለህ በቅንነት ትደመድም ይሆናል፤ ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም። በነገሩ ከመስማማትህ በፊት “ፈሳሹ የደም ክፍል የነበረ ነውን?” ብለህ ጠይቅ። በአንድ ዓይነት መሣሪያ እንደሚጠቀም ከገለጸም፦ “በዚህ ዓይነቱ መሣሪያ ስትጠቀም ደሜ ተቀድቶ በሆነ ዕቃ ላይ ይቀመጣልን?” ብለህ ጠይቅ።
21 ይሁን እንጂ ከላይ ያሉትን ሁሉ ካደረግህ በኋላ ምንም ትብብር ብታጣ ወይም ስለያዝከው አቋም ተቃውሞ ቢያጋጥምህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እርዳታ ለማግኘት ለመጠየቅ አታመንታ። አንዳንዶች እርዳታ ለመጠየቅ ረጅም ጊዜ በመቆየታቸው ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል።
በአስፈላጊ ጊዜ ላይ የሚገኝ ጠቃሚ እርዳታ
22 ተፈላጊውን እርዳታ ለማግኘት የሚከተለውን መንገድ ልብ በል፦ (1) አንተ ወይም ከቤተሰብህ አንዱ በምርጫ ወይም በድንገተኛ አደጋ ምክንያት የቀዶ ጥገና ሕክምና ቢያስፈልጋችሁና ሆስፒታሉ በደም ለመጠቀም በመፈለጉ ምክንያት ክርክር ቢነሳ፤ ወይም (2) የአንተ ወይም የቤተሰብህ አባል የሆነ ሰው ጤንነት እየተባባሰ ቢሄድ፤ ወይም (3) በአንድ ልጅ (በአንድ ትልቅ ሰው) ሁኔታ ላይ ዶክተሩ፣ አንዷ ነርስ፣ ወይም አስተዳዳሪው ደም ሊሰጡ እንደሆነ ቢናገሩ፦
23 እስከዚያን ጊዜ ድረስ አድርገኸው ካልሆነ ከጉባኤህ ሽማግሌዎች ጋር ተገናኝተህ ሁኔታውን አስረዳ። (በእርግጥም ስለ ደም ባለን አቋም ምክንያት ወደ ጤና ተቋሞች በምንሄድበት በማናቸውም ጊዜ ለሽማግሌዎች ማሳወቁ የጥበብ መንገድ ነው።) ሽማግሌዎቹ ልትወስደው ያለውን ቀጣይ እርምጃ ለመወሰን ሊረዱህ ይችላሉ።—ኢሳ. 32:1, 2
24 ሽማግሌዎች በአካባቢህ ካሉት አንተን ለመርዳት ፈቃደኛ ከሆኑ ተባባሪ ዶክተሮች ጋር እንድትገናኝ ሊረዱህ ይችሉ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት ዶክተሮች በአካባቢህ ሊገኙ ካልቻሉም ሽማግሌዎቹ በቅርብ ባሉ ቦታዎች ሊሞክሩ ይችሉ ይሆናል። ይህ ካልተሳካም የሚቻል ከሆነ ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ግንኙነት ሊያደርጉ ይችላሉ።
25 ሽማግሌዎች ከዶክተሩ ወይም ከአስተዳዳሪው ጋር በመነጋገር አንተን ወይም ዘመድህን ሊረዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ያንን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብሃል። እነዚህ ወንድሞች ለአንተ ውሳኔ ሊያደርጉልህ አይችሉም። ሆኖም ስለ ጉዳዩ ማኅበር ያላትን አመለካከት እንድትመረምር ሊረዱህ ይችላሉ። እንዲሁም በሕክምናውና በሕጉ አንጻር ላሉት አማራጮች ያዘጋጁሃል።
26 የሕክምናው ቡድን አሁንም ለመተባበር ፈቃደኛ ካልሆነ የሆስፒታሉን አስተዳዳሪ አነጋግረህ እዚያ ካሉት ዶክተሮች ውስጥ ፍላጎትህን የሚያከብር ዶክተር ይኖር እንደሆነ ጠይቅ። ይህ የማይቻል ከሆነ ሕክምና ለማግኘት ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ሊያስፈልግህ ይችላል። ሁኔታህ እየተባባሰ ሄዶ አደገኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አስፈላጊውን የሕክምና እርዳታ የማግኘቱን አስፈላጊነት አስታውስ። አስፈላጊውን ነገር ለማድረግ አትዘግይ!
27 እኛ ማንም ሰው የጤና ኢንሹራንስ ሊኖረው ያስፈልጋል ወይም በግል ዶክተሮችና የሕክምና ተቋሞች መጠቀም ያስፈልገዋል ብለን ለመናገር ባንችልም ብዙውን ጊዜ የግል ጤና ጥበቃ ሠራተኞችና ድርጅቶች ለድርድር የማይቀርበውን አቋማችንን ማክበርን በተመለከተ የበለጠ ተባባሪዎች ሆነው መገኘታቸውን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።
ጥንቃቄ ልናደርግባቸው የሚገቡ ብዛት ያላቸው ጥያቄዎች
28 ዶክተሮችና ሌሎች የሚያነሷቸው ብዙውን ጊዜ በጥሩ ዓላማ የማይጠየቁ ጥያቄዎች መኖራቸውንም ማወቅ ይኖርብሃል። በተደጋጋሚ በዶክተሮችና (በሌሎች) ከሚጠየቁት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ፦
•‘ሕይወት አድን የሆነውን ደም የመውሰድ ሕክምና’ ከመቀበል ይልቅ ለመሞት (ወይም ልጅህ እንዲሞት) ትመርጣለህን?’ የሚል ነው።
30 አዎን ብለህ ከመለስክ በሃይማኖታዊ መንገድ ሲታይ መልሱ ትክክል ነው። ይሁን እንጂ ይህን መልስ ብዙውን ጊዜ በትክክል አይረዱትም፤ አንዳንድ ጊዜም መጥፎ ውሳኔዎችን አስከትሏል። በዚህን ጊዜ በመስክ አገልግሎት ላይ እንዳይደለህ ማስታወስ ይኖርብሃል። ከዚህ ይልቅ የምትነጋገረው አስፈላጊ የሆነ ሕክምና ስለማግኘት ነው። እንግዲያው በዚያ ወቅት ላሉት አዳማጮችህ (ሐኪሞች ወይም ዳኞች) የሚስማማ መልስ ስጥ።—መዝ. 39:1፤ ቆላ. 4:5, 6
31 ለአንድ ዶክተር፣ ለአንድ ዳኛ፣ ወይም ለሆስፒታል አስተዳዳሪ “አዎን” ብሎ መመለስ ሰማዕት መሆን ትፈልጋለህ ወይም በእምነትህ ምክንያት ልጅህን መስዋዕት ለማድረግ ትፈልጋለህ ማለት ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለህ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ስላለህ ጠንካራ እምነት መናገሩ ብዙውን ጊዜ አይጠቅምም። ሕይወት በአደጋ ላይ በወደቀበት ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማድረግ የማትፈልግ ጭፍን ሃይማኖተኛ እንደሆንህ አድርገው ሊያዩህ ይችላሉ። ነገሩ ልጅህን የሚመለከት ከሆነ “ሕይወት አድን” ብለው የሚጠሩትን ሕክምና ዘዴ እንደማይቀበል ኃላፊነቱን የዘነጋ ወላጅ አድርገው ያዩሃል።
32 ሆኖም አንተ ሕክምናውን አልተቃወምክም። ከዶክተሩ ጋር የተለያየኸው ምን ዓይነት ሕክምና ይሰጥ በሚለው ላይ ነው። ይህ አቋም እንዳለህ መታወቁ ብዙውን ጊዜ ለአንተና ለእነርሱ አጠቃላዩን መልክ ይለውጣል። ከዚህም በተጨማሪ ደሙ ለአደጋ እንደማያጋልጥና እርሱ ብቻ “ሕይወት አድን” ሕክምና እንደሆነ አስመስሎ ማቅረቡ አሳሳች አነጋገር ነው። ስለዚህ ይህንን ነጥብ በጣም ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል። ይህንን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ ብለህ ልትመልስ ትችላለህ፦
•“እኔ (ወይም ልጄ) መሞት አንፈልግም። እኔ (ወይም ልጄ) እንድንሞት ብፈልግ ኖሮ እዚህ የመጣሁት ለመኖር ስለምፈልግ (ወይም ልጄ እንዲኖር) ስለምፈልግ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ነው። አሁን ለእኔ (ወይም ለልጄ) የምፈልገው አማራጭ የሆነ ያለ ደም የሚደርግ ሕክምና ነው። አማራጭ ዘዴዎች አሉ።”
33 ብዙውን ጊዜ በዶክተሮች ወይም በዳኞች የሚጠየቁት ሌሎች ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፦
•“በግድ ደም ቢሰጥህ ምን ትሆናለህ? በኃላፊነት ትጠየቃለህን?”
•ደም በግድ መሰጠቱን ብትቀበል ወይም እንዲሁ አስገድደን ብንሰጥህ ከሃይማኖቱ መባረርን ወይም የዘላለም ሕይወት ማጣትን ያስከትልብሃልን? ጉባኤህ እንዴት አድርጎ ይመለከትሃል?”
34 አንዲት እህት ለአንድ ዳኛ ስለ ጉዳዩ እርሱ ለወሰነው ነገር ኃላፊ እንደማትሆን መልስ ሰጠች። በአንድ በኩል ሲታይ አነጋገሯ ትክክል ቢሆንም ዳኛው እርስዋ ኃላፊነቱን ካልወሰደች እርሱ የእርስዋን ኃላፊነት እንዲወስድላት መናገርዋ እንደሆነ አድርጎ ተመለከተው። ስለዚህ ደም እንዲሰጣት አዘዘ።
35 አንዳንዶች እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች የሚጠይቁት ብዙውን ጊዜ ደም ላለመውሰድ ባደረግኸው ውሳኔ ዙሪያ ደም ለመውሰድ የሚያስችል መንገድ ለማግኘት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብሃል። ዝም ብለህ ያለ ማስተዋል አትመልስላቸው። ታዲያ እንደዚህ ካለው አለመግባባት ለመራቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንዲት እህት እንዲህ ብላ ልትመልስ ትችላለች፦
•“ደም በግድ ቢሰጠኝ ይህ ለእኔ በግድ በጾታ እንደመነወር ያህል ነው። በቀረው የሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይህ የማይፈለግ ጥቃት በእኔ ላይ ባስከተላቸው መጥፎ የስሜትና መንፈሳዊ ውጤቶች ምክንያት እሰቃያለሁ። ያለ ፈቃዴ በገዛ አካሌ ላይ ይህን የመሰለ አመጽ መፈጸሙን ለመከላከል ባለኝ ሁሉ እታገላለሁ።”
36 በግድ ደም ቢሰጠን በሰውነታችን ላይ የተደረገ አሰቃቂ ድፍረት እንደሆነ አድርገህ ጠንከር አድርገህ ግለጽ። በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ከአቋምህ ፍንክች አትበል። ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን እንደምትፈልግ ግልጽ አድርግ።
ዝግጁ ለመሆን ምን ታደርጋለህ?
37 ከማይፈለግ ደም የመውሰድ ሕክምና ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን ለመጠበቅ ማድረግ ያሉብህን አንዳንድ ነገሮች ተወያይተንባቸዋል። (ወደፊትም ሕፃናት ወይም ልጆች በግድ ደም ይሰጣቸዋል የሚሉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙ ችግሮቹን እንዴት ለመፍታት እንደሚችል የሚገልጽ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ለማቅረብ ተስፋ እናደርጋለን።) በተጨማሪም ማኅበር በፍቅር በመነሣሣት አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ እርዳታ ለማቅረብ ያዘጋጀችውን ተመልክተናል። እምነትን ለሚፈታተን የሕክምና ሁኔታ ዝግጁ መሆንህን ለማረጋገጥ ይህን ማብራሪያ ምን ልታደርገው ይገባሃል?
በመጀመሪያ፦ ስለእነዚህ ነገሮች የቤተሰብ ውይይት አድርጋችሁ በተለይ ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥም ምን እንደምትሉ ወይም እንደምታደርጉ በትዕይንት ተለማመዱ።
ቀጥሎም፦ የሚያስፈልጉት ሰነዶች ሁሉ ያሏችሁ መሆኑን አረጋግጡ።
ከዚያም፦ ይሖዋ ‘ከደም ለመራቅ’ ባደረጋችሁት ቁርጥ ውሳኔ እንዲደግፋችሁ አጥብቃችሁ የምትፀልዩበት ጉዳይ አድርጉት። ይሖዋ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ ማክበሩ የእርሱን ሞገስና የማያልቀውን ሕይወት ለማግኘታችን ማረጋገጫ ነው።—ሥራ 15፡29፤ ምሳሌ 27:11,12