የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 4/15 ገጽ 8-10
  • በግሪክ የተደረገ የተሳካ የምሥክርነት ዘመቻ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በግሪክ የተደረገ የተሳካ የምሥክርነት ዘመቻ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • የመንግሥት ባለሥልጣኖች የሰጡት ምላሽ
  • አቃቤ ሕጎች የሰጡት ምላሽ
  • የቤተ መጻሕፍት ኃላፊዎች የሰጡት ምላሽ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 4/15 ገጽ 8-10

በግሪክ የተደረገ የተሳካ የምሥክርነት ዘመቻ

በግሪክ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለረጅም ጊዜ ተቃውሞ ሲደርስባቸው ቆይቷል። አንዳንድ የፖሊስ፣ የፍርድ ቤትና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣኖች በግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት ገፋፊነት የይሖዋ ምሥክሮችን አሳደዋል። አንዳንድ ጊዜ ለስደቱ ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው ግሪክ ያወጣችው የሰውን ሃይማኖት ማስቀየር የሚከለክለው ሕግ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት መካፈልን ወይም ለሕክምና ደም መውሰድን በተመለከተ ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያለው እምነታቸው ነው።—ኢሳይያስ 2:2-5፤ ሥራ 15:28, 29

በግሪክ ያሉ ልበ ቅን ባለሥልጣኖች ሁኔታዎቹን በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ ለማድረግ የግሪክ መንግሥት ሃይማኖታዊ አገልጋዮች አድርጎ የተቀበላቸው 200 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮችና ጥቂት የሕግ ባለሙያ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ አገር አቀፍ ዘመቻ አድርገው ነበር። በዚህ ዘመቻ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች በግሪክ የተባለውን ልዩ ብሮሹርና የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለውን መጽሐፍ አበርክተዋል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰደዱት ያለ በቂ ሕጋዊ ምክንያት እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ ዶክሜንቶች አዘጋጅተው ነበር። ምሥክሮቹ የፖሊስ አዛዦችን፣ ከንቲባዎችን፣ አቃቤ ሕጎችንና ሌሎች ባለሥልጣናትን አነጋግረዋል።

ምን ምላሽ ተገኘ? በርካታ አስደሳች ተሞክሮዎች ተገኝተዋል። ጥቂቶቹን ተመልከት።

ምዕራብ መቄዶንያ የሚገኝ የአንድ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ወንድሞችን በደስታ ከተቀበለ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እኔ እናንተን የማውቃችሁ ዛሬ አይደለም። . . . ሥርዓታማነታችሁን አደንቃለሁ። . . . የሰውን ሃይማኖት ስለማስቀየር በሚናገረው ሕግ አልስማማም፤ ሥልጣኑ ቢኖረኝ ኖሮ ይህንን ሕግ እሰርዘው ነበር።”

በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያ አዛዦች እንደሚከተሉት ያሉ ሐሳቦች ሰጥተዋል፦ “እያከናወናችሁት ላለው ማኅበራዊ አገልግሎት አመሰግናችኋለሁ።” “የእናንተ ሰዎች ፈጽሞ ለፖሊሶች ተጨማሪ ሥራ አይፈጥሩም፤ ማኅበራዊ ሥራ እያከናወናችሁ ነው።” “በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት መጥፎ አመለካከት የለንም። እናከብራችኋለን እንዲሁም እናደንቃችኋለን።”

ፒሬስ በተባለች ከተማ ውስጥ አንድ የደህንነት ፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ይሖዋ የሚለውን ስም በመጠቀም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ይሖዋ እንደሚጸልይ ዓይኑ እንባ እያቀረረ ለወንድሞች ነገራቸው። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ከአርማጌዶን በፊት ስደት ይደርስብናል ብለው እንደሚጠብቁ ስለሚያውቅ ይህ ስደት በሚመጣበት ጊዜ ምሥክሮቹን ለመርዳት አምላክ ይጠቀምብኝ ይሆናል ብሎ እንደሚያስብ ሲነግራቸው በጣም ተገረሙ! ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ያቀረቡለትን ግብዣ ተቀብሏል።

የመንግሥት ባለሥልጣኖች የሰጡት ምላሽ

በቴሳሊ የሚኖሩ አንድ ከንቲባ አዋጅ ነጋሪዎች የተባለው መጽሐፍ “በማዘጋጃ ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያ ቦታ ሊሰጠው ይገባል!” ብለዋል። ከዚያም መጽሐፉን በግልጽ ለማየት እንዲቻል ሌሎች መጽሐፎችን ከመደርደሪያው ላይ ካነሱ በኋላ አዋጅ ነጋሪዎች የተባለውን መጽሐፍ ብቻውን አስቀመጡት።

በሰሜናዊ ግሪክ አንድ ከንቲባ ወንድሞችን ሞቅ ባለ ሁኔታ ከተቀበሉ በኋላ “እኔ በማስተዳድረው ከተማ ውስጥ እንደ እናንተ ያሉ ሰዎች እንዲኖሩ እመኛለሁ” ብለዋል። ሰሜን ዩቢያ የሚገኙ አንድ ቅን ከንቲባ ወንድሞችን “የቀድሞ የሠራዊት አዛዥ ነኝ። በጣም ነው የማደንቃችሁ” ብለዋቸዋል። ወንድሞች ያቀረቡላቸውን ሐሳብ ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብለዋል። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ከታተሙት መጻሕፍት ውስጥ አንዳንዶቹን ሲያሳዩአቸው “ሁሉንም እንደማነባቸው ቃል ብገባ እነዚህን መጻሕፍት ትሰጡኛላችሁ?” አሉ። ወንድሞች “መጽሐፎቹ የእርስዎ ናቸው!” ብለው መለሱላቸው። በጣም የተደሰቱ ከመሆናቸውም በላይ ወንድሞች እንዲለዩአቸው አልፈለጉም ነበር።

ከአቲካ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ የሚኖሩ አንድ ከንቲባ ወንድሞች የሰጧቸውን ጽሑፎች በደስታ ከወሰዱ በኋላ ሳያቋርጡ የማኅበሩን ጽሑፎች ይዘውላቸው እንዲመጡ ወንድሞችን ጠየቋቸው። ወንድሞች ሊሄዱ ሲሉ እንዲህ አሏቸው፦ “ሰዉ በፖለቲካ ሰዎች በኩል ተስፋ ቆርጦ እውነትን ሌላ ቦታ እየፈለገ ነው። እናንተ እውነትን ስለያዛችሁ ከአሁን በኋላ ሥራ እንደሚበዛባችሁ እርግጠኛ ነኝ።”

አቃቤ ሕጎች የሰጡት ምላሽ

በሰሜናዊ ግሪክ የሚገኙትን ምክትል አቃቤ ሕግ ያነጋገሩ ወንድሞች ያጋጠማቸውን ነገር እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፦ “በጽሑፎቻችንና በአቀራረባቸው እንዲሁም ወንድሞቻችን ደም መውሰድን የመሳሰለ አሳሳቢ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው አውላላ ሜዳ ላይ እንዳይቀሩ በምናደርገው ጥረት ተገረሙ። በመጨረሻም መጥተን አንዳንድ ነገሮች ስላካፈልናቸው አመሰገኑን። ከአራት ዓመት በፊት ሁለት ወንድሞች በአገልግሎት ላይ ሳሉ ፖሊስ ጠርተው እንዲያዙ ያዘዙት እርሳቸው እንደነበሩ ከጊዜ በኋላ አወቅን።”

አቴንስ ውስጥ ወደሚገኘው የአቃቤ ሕግ ቢሮ የሄዱት የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት ጠበቆች ታዋቂ የሆኑትና ከፍተኛ አክብሮት ያተረፉትን በዕድሜ ጠና ያሉ አቃቤ ሕግ ቀርበው ሲያነጋግሯቸው ተደነቁ። ወንድሞችን ከሰው ገለል አደረጓቸውና የሰውን ሃይማኖት ማስቀየር የሚከለክለው ሕግ ምንም መሠረት እንደሌለውና ግሪክ ውስጥ ባለው ፍርድ አሰጣጥ ላይ ውዝግብ እንደፈጠረ ነገሯቸው። ወዳጃዊ በሆነ መንገድ በመጨበጥ ምስጋናቸውን ገልጸውላቸዋል።

በሰሜን ግሪክ የሚገኙ አንድ የወዳጅነት መንፈስ የነበራቸው አቃቤ ሕግ ጽሑፎችን ወስደዋል። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ገለጥ ገለጥ እያደረጉ የተመለከቱት ሲሆን በርዕስ ማውጫው ላይ የተመለከቷቸው የተለያዩ ርዕሶች በጣም አስገርመዋቸዋል። “በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች በየትኛውም የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አልተመለከትኳቸውም” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

ቢኦሺ ተብላ በምትጠራ ክፍለ አገር ውስጥ የሚኖሩ አንድ አቃቤ ሕግ የይሖዋ ምሥክሮች ያለ ፈቃዳቸው ደም እንዲወስዱ ባለፉት ጊዜያት ትእዛዝ ይሰጡ እንደነበር አምነዋል። ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ ከወንድሞች ጋር ከተወያዩ በኋላ “ከእንግዲህ ይህን የመሰለ ትእዛዝ አልሰጥም!” ብለዋል። ያለ ደም የሚደረግ አማራጭ ሕክምና ፈልጎ ለማግኘት እንዲቻል በአካባቢው የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ማማከር ያስፈልጋል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የተባለውን መጽሐፍ በደስታ ወስደዋል።

የቤተ መጻሕፍት ኃላፊዎች የሰጡት ምላሽ

ጽሑፎቹ ብዛት ላላቸው የቤተ መጻሕፍት ኃላፊዎች ደርሰዋል። አቴንስ ውስጥ በሚገኝ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚሠራ አንድ ትሑት የቤተ መጻሕፍት ኃላፊ ጽሑፎቹን ከወሰደ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ቤተ መጻሕፍታችንን የሞሉት እናንተን የሚነቅፉ መጻሕፍት ስለሆኑ መጽሐፎቻችሁን ማምጣታችሁ በጣም ጥሩ ነው። . . . አንድ ቄስ መጽሐፎቻችሁን ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ስለተመለከቱ በጣም ተበሳጭተው ነበር። . . . ይህ የሚያበሳጭ አይደለም። ሁሉም ዓይነት አመለካከቶች ይፋ መውጣት አለባቸው።”

ክሪቲ በተባለች ከተማ በሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ያለው ቤተ መጻሕፍት ኃላፊ የይሖዋ ምሥክሮችን በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ያውቋቸው ነበር። ምሥክሮቹ በጦርነት አንካፈልም በማለት የወሰዱት አቋም ያስደንቃቸው እንደነበር ለወንድሞች ነግረዋቸዋል። ‘እነዚህ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ በማለት ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። ከወንድሞች ጽሑፍ ከወሰዱ በኋላ እያከናወኑት ስለነበረው ዘመቻ እንዲህ አሉ፦ “በጣም ጥሩ ሥራ ሠርታችኋል። እንዲያውም ቀደም ብላችሁ እንዲህ ማድረግ ነበረባችሁ። . . . ግሪክ ውስጥ ጭፍን ጥላቻ ተስፋፍቷል።” ብዙ ሳይቆዩ ተመልሰው እንዲያነጋግሯቸው ወንድሞችን ጠይቀዋቸዋል።

ወንድሞች በዚህ ልዩ ዘመቻ ወቅት ከ1,000 የሚበልጥ አዋጅ ነጋሪዎች የተባለውን መጽሐፍ፣ ከ1,600 በላይ በግሪክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር እንዲሁም በርካታ መጽሐፎችና መጽሔቶች አበርክተዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከብዙ የግሪክ ባለሥልጣኖች ጋር በአካል ተገናኝተው ለመነጋገር ችለዋል። አሁን በግሪክም ሆነ በዓለም ዙሪያ ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በግሪክ ያሉ ልበ ቅን ባለሥልጣኖች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን አመለካከት ይበልጥ ከአድሎ እንደሚያጸዱ ተስፋ ያደርጋሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ