የአላስካን የመጨረሻ ጠረፍ የሸፈነውን መጋረጃ መግለጥ
ሰው ሁሉ ሀብት ለማግኘት በሚሯሯጥባት በአላስካ ውስጥ በምትገኝ ኖም የምትባል ታዋቂ ከተማ ውስጥ አራታችንም በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ ተፋፍገን መኖር ከጀመርን ዛሬ ሁለተኛ ቀናችን ነው። በ1898 ከ40,000 የሚበልጡ ማዕድን ፈላጊዎች ከየቦታው ወደዚህ የጎረፉት አንድ ነገር ፍለጋ ነበር—ወርቅ! እኛ ግን ሌላ ውድ ሀብት ልንፈልግ ነበር የመጣነው።
ለጊዜው ያተኮርነው ከቤሪንግ የባሕር ወሽመጥ በስተምዕራብ በ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሴንት ላውሬንስ ደሴት ባሉት ጋምቤልና ሳቩንጋ በተባሉ መንደሮች ከሚኖሩ ነዋሪዎች ውስጥ ‘የተመረጠውን ነገር’ ለማግኘት ነው። (ሐጌ 2:7) በእነዚያ መንደሮች ውስጥ ኢንዩት የተባሉ ዘሮች ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ጥቂት ኪሎ ሜትር ብቻ ራቅ ብለው ከአርክቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ዓሣ ነባሪ እያጠመዱ በረዶውን ተቋቁመው ይኖራሉ። እኛን ግን በረዶውና አካባቢውን እንደ ብርድ ልብስ የሸፈነው ጥቅጥቅ ያለ ጉም አስሮ አስቀርቶናል። አውሮፕላናችን እንዳረፈች ናት።
የአየር ጠባዩ እስኪለወጥ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ሳለን ባለፉት ዓመታት ብዙም ሰው ባልሰፈረባቸው አካባቢዎች ምስክርነቱን ስንሰጥ ያጋጠሙንን ነገሮች እያሰላሰልኩ ይሖዋ አምላክን ስለሰጠን በረከት አመሰገንኩት። ከ1,600,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ምድረ በዳ በሆነው በአላስካ ውስጥ፣ ወይም አንዳንዶች እንደሚጠሩት በዓለም የመጨረሻው ጠረፍ ላይ፣ ከ150 በላይ በሚሆኑ አንዱን ከሌላው የሚያገናኝ ምንም ዓይነት መንገድ በሌለባቸው ተበታትነው በሚገኙ ሩቅ መንደሮች ውስጥ ከ60,000 የሚበልጡ የአገሪቱ ተወላጆች ይኖራሉ። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አውሮፕላኖች በመሆን ከእነዚህ ተበታትነው ከሚገኙት መንደሮች ከአንድ ሦስተኛ በላይ ለሚሆኑት የአምላክን መንግሥት ምሥራች አድርሰንላቸዋል።—ማቴዎስ 24:14
ወደነዚህ ሩቅ መንደሮች ለመድረስ ብዙውን ጊዜ አውሮፕላኑ አካባቢውን ለብዙ ቀናት ሸፍኖ በሚቆየው ደመናና ጭጋግ ውስጥ ለማረፍ ይገደዳል። ባረፍንበት ቦታ ደግሞ ሌላ ሊገለጥ የሚገባው ጭጋግ ያጋጥመናል። ይህ ጭጋግ የነዚያን ደግና ሰላማውያን ሰዎች አእምሮና ልብ ልክ እንደ መጋረጃ ጋርዶታል።—ከ2 ቆሮንቶስ 3:15, 16 ጋር አወዳድር።
አስቸጋሪ የሽግግር ወቅት
በአላስካ ምድረ በዳ ኢንዩቶች፣ አሌውትያንና ህንዶች ይኖራሉ። ሁሉም የየራሳቸው ልማድና በውርስ ያገኙት የተለየ ባሕርይ አላቸው። የአርክቲክን የክረምት ወቅት በሕይወት ለማለፍ አደን በማደን፣ ዓሣ በማጥመድና ዓሣ ነባሪ በመያዝ በአገራቸው በሚያገኟቸው ነገሮች በቁጠባ ይጠቀማሉ።
የውጭ አገር ተጽዕኖ ወደ አገራቸው የመጣው በ17ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነበር። ጠጉራም የእንስሳት ቆዳ የሚነግዱ ሩስያውያን ወደዚያ አካባቢ ሲመጡ ጠጉራም ቆዳ የለበሱና የዓሣ ዘይት የዓሣ ዘይት የሚሸቱ ሰዎች አገኙ። ሰዎቹ የሚኖሩት ኢግሉ በሚባሉ ከበረዶ በተሠሩ ቤቶች ውስጥ ሳይሆን የሣር ክዳን ባላቸው እንደ ምድር ቤት ሆነው በተሠሩ ጎጆዎች ውስጥ ነው። የጎጆዎቹ በሮች እንደ ምድር ቤት በሮች ናቸው። ነጋዴዎቹ በነዚህ የለዘበ አነጋገር ባላቸው የዋህ ግን ጠንካሮች በሆኑ ሰዎች ላይ አዳዲስ ባሕሎችና የአንዳንዶቹን ነገዶች ቁጥር በግማሽ የጨረሱ አዳዲስ በሽታዎችን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ከባባድ ችግሮችን አምጥተውባቸዋል። ብዙም ሳይቆይ የአልኮል መጠጥ በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ ችግር ፈጠረ። አዲሱ ኢኮኖሚ ኅብረተሰቡ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮ ነግዶ ወደማትረፍ እንዲዞር አስገደደው። አንዳንዶች እስካሁን ድረስ ያ ጊዜ አስቸጋሪ የሽግግር ወቅት እንደነበረ ይሰማቸዋል።
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ሲመጡ የአላስካ ተወላጆች ሌላ ዓይነት ለውጥ ለማድረግ ተገደዱ። አንዳንዶች የነፋስን፣ የበረዶን፣ የድብን፣ የንስርንና የሌሎችን ነገሮች መናፍስት ማምለክን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን ሳይወዱ ተዉ። ሌሎቹ ደግሞ አመለካከቶቻቸውን አንድ አድርገው ሃይማኖቶችን ለማዋሐድ ሲሞክሩ የባሰ ግራ ተጋቡ። ይህ ሁሉ ብዙውን ጊዜ በእንግዶች ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸውና ሰው የማያምኑ እንዲሆኑ አደረጋቸው። አንዳንድ መንደሮች ብዙውን ጊዜ ለእንግዶች ጥሩ አቀባበል አያደርጉም።
ስለዚህ በዚህ ሰፊ ወሰን ላይ ተበታትነው የሚገኙትን ነዋሪዎች ሁሉ ልናነጋግራቸው የምንችለው እንዴት ይሆን? ጥርጣሬያቸው እንዲወገድ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? መጋረጃውን ለመግለጥ ምን ልናደርግ እንችል ይሆን? የሚሉት ፈታኝ ጥያቄዎች ከፊታችን ተጋረጡብን።
ምስክርነቱን ለመስጠት በመጀመሪያ ላይ የተደረገ ጥረት
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ አላስካውያን የሆኑ ብዙ ጠንካራ ምስክሮች ኃይለኛውን ነፋስና ቅዝቃዜ እንዲሁም በረዶውን ተቋቁመው ባለ አንድ ሞተር በሆኑ የግል አውሮፕላኖቻቸው በመሆን በሰሜን በኩል ተበታትነው በሚገኙ መንደሮች ለመስበክ ሄደው ነበር። መለስ ብለን ስናስበው እነዚያ ደፋር ወንድሞች ያን ሁሉ ያደረጉት በሕይወታቸው ቆርጠው ነበር። የአውሮፕላኑ ሞተር ቢበላሽ ትልቅ አደጋ ሊደርስባቸው ይችል ነበር። በደህና ቢያርፉ እንኳን እርዳታ ሊያገኙ ከሚችሉበት አካባቢ በጣም ርቀው ሊያርፉ ስለሚችሉ ከዜሮ በታች በሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ ምንም የመጓጓዣ መንገድ ሳያገኙ ይቀሩ ነበር። በሕይወት የመትረፋቸው ጉዳይ ምግብና መጠለያ በማግኘታቸው ላይ የተመካ ይሆናል። ይህን ደግሞ ላያገኙ ይችላሉ። እስካሁን ያን ያህል ከባድ አደጋ ባለመድረሱ በጣም አመስጋኞች ነን፤ ሆኖም እንዲህ ዓይነት አደጋ ሊያጋጥም ይችል የነበረ መሆኑ አይካድም። ስለዚህ በአላስካ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ዓይነቱን የምስክርነት መስጫ መንገድ አይደግፈውም።
በፌርባንክስ እና በኖርዝ ፖል ጉባኤዎች የሚገኙ ታማኝ ወንድሞች እንደ ኖም፣ ባሮ እና ኮትሴቢዩ ባሉ የንግድ አየር መንገዶች በሚገኙባቸው ትልልቅ መንደሮች ላይ በማተኮር ሥራውን ቀጠሉ። በሰሜንና በምዕራብ በኩል 720 ኪሎ ሜትር ርቀት ወዳላቸው ወደነዚህ አካባቢዎች የሚጓዙት በራሳቸው ወጪ ነበር። አንዳንዶቹ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ሲሉ ለብዙ ወራት በኖም ይቆዩ ነበር። ከዜሮ በታች 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከሚደርሰው ቅዝቃዜ ለመዳን በባሮ አንድ አንድ አፓርታማ ተከራየን። ባለፉት ረጅም ዓመታት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ስበኩ የሚለውን የኢየሱስን ትዕዛዝ ከልብ የተቀበሉ ወንድሞች ይህን ለመፈጸም ከ15,000 የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ወጪ አውጥተዋል።—ማርቆስ 13:10
ያልተጠበቀ እርዳታ ተገኘ
በጣም ርቀው በሚገኙ ሰፈሮች ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለማነጋገር የሚቻልበትን መንገድ ለመቀየስ የሚደረገው ጥረት ቀጠለ። ይሖዋም መንገዱን ከፈተልን። ወጣ ገባ የሆነውን የአላስካን የተራራ ሰንሰለት በደህና ለማለፍ የሚያስፈልገንን ባለ ሁለት ሞተር አውሮፕላን ማግኘት ቻልን። አላስካ ውስጥ ከ4,200 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው በጣም ብዙ ተራሮች አሉ። ረጅሙ ተራራ ታዋቂው የማክኪንሌይ (የዴናሊ) ተራራ ሲሆን ከፍታውም ከባሕር ወለል በላይ 6,193 ሜትር ነው።
በመጨረሻ አውሮፕላኑ መጣ። ግን አውሮፕላኑ ሲያርፍ አሮጌ፣ የተላላጠና የተጠጋገነ መሆኑን ስናይ ምን ያህል እንዳዘንን ገምቱት። አውሮፕላኑ አየር ላይ ሊበር ይችል ይሆን? በወንድሞቻችን ሕይወት ቆርጠን እንዲሳፈሩበት ማድረግ አለብን? በዚህም ጊዜ ቢሆን የይሖዋ እጅ አጭር እንዳልሆነ ታይቷል። 200 የሚሆኑ ፈቃደኛ ወንድሞች ፈቃድ ባላቸው መካኒኮች በመመራት በሺህ የሚቆጠር ሰዓት በማጥፋት አውሮፕላኑን ሙሉ በሙሉ አደሱት።
በጅራቷ ላይ 710 ደብልዩ ቲ ተብሎ የተጻፈባት የምታበራና አዲስ የምትመስል አውሮፕላን ወደ አላስካ ሰማይ ሽቅብ ስትወጣ ማየት እንዴት ደስ ይል ነበር! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰባትና አሥር ሙሉነትን የሚያመለክቱ በመሆናቸው 710 የሰዎቹን ልብ የሸፈነውን የጭለማ መጋረጃ ለመግፈፍ የይሖዋ ድርጅት የምትሰጠውን ድጋፍ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ያገለግላል።
ወደ አሌውትያን የደሴቶች ሰንሰለት መሄድ
አውሮፕላኑ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ 80,000 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው በበረዶ የተሸፈነ ምድረ በዳ ከ54 በላይ በሚሆኑ መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አድርሰናል። ይህም የዩናይትድ ስቴትስን የቆዳ ስፋት 19 ጊዜ ተመላልሶ እንደማቋረጥ ያክል ነው።
ሰላማዊ ውቅያኖስን ከቤሪንግ ባሕር በሚከፍሉት 1,600 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላቸው የአሌውትያን ደሴቶች ሦስት ጊዜ ተመላልሰናል። እንደ ሰንሰለት የተቀጣጠሉት ምንም ዛፍ የሌለባቸው ከ200 በላይ የሚሆኑት ደሴቶች የአሌውት ተወላጆች ብቻ ሳይሆን በሺህ የሚቆጠሩ የባሕር አእዋፍ፣ ቦልድ ኢግል የሚባል የንስር ዝርያ፣ በጣም ነጭ የሆነ ራስና ጥቁርና ነጭ መስመር ያለበት ላባ ያላቸው ኢምፐረር ጊዝ የሚባሉ ዝዮች መኖሪያ ናቸው።
አካባቢው ማራኪ ውበት ቢኖረውም አደገኛ ነው። ከባሕሩ በላይ ስንበር ከ3–5 ሜትር ከፍታ ያለው ማዕበል ወዲህና ወዲያ ሲል ይታየናል። ውኃው በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ በበጋ እንኳን አንድ ሰው ውስጡ መቆየት የሚችለው ለአሥር ወይም ለአሥራ አምስት ደቂቃ ብቻ ነው። ለማረፍ ከተገደድን የአውሮፕላኑ አብራሪ የሚኖረው ዕድል ወጣ ገባና ድንጋያማ በሆነ ደሴት ላይ አለዚያ በጣም ቀዝቃዛ በሆነው ውኃ ላይ መከስከስ ነው። የአውሮፕላኑን ሙሉ ጤንነት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የሆኑትን የአውሮፕላንና የሞተር (ኤርክራፍት ኤንድ ኤንጅንስ) መካኒክነት ማዕረግ ያላቸውን በጣም ጎበዝ ወንድሞቻችንን እናመሰግናቸዋለን!
አንድ ቀን ወደ ደች ወደብና በአንአላስካ ከተማ ወደምትገኝ አንዲት የዓሣ ማጥመጃ መንደር ተጓዝን። አካባቢው በሰዓት ከ130 እስከ 190 ኪሎ ሜትር በሚጓዘው ነፋስ የታወቀ ነው። ምንም እንኳን አውሮፕላኑን ትንሽ ትንሽ ያናውጠው ስለነበረ ብዙ ጊዜ ቢያጥወለውለንም የዚያን ቀን ብዙም ነፋስ ስላልነበረ ደስ አለን። የአውሮፕላን ማረፊያውን ስናየው በጣም ደነገጥን። ድንጋያማ በሆነ ተራራ ላይ ያለ ጠፍጣፋ ቦታ ነበር! ባንድ በኩል ከፍተኛ ጥልቀት ያለው ገደል በሌላው ወገን ደግሞ በረዶ የሆነ የቤሪንግ ባሕር አለ! ያረፍነው በዝናብ በረሰረሰ ቦታ ላይ ነበር። በዚህ አካባቢ በዓመት ከ200 ለሚበልጡ ቀናት ይዘንባል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ስለ አምላክ ቃልና ስለ ዓላማው መወያየት እንዴት ደስ ይላል! ብዙ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ጦርነት የሌለበት ዓለም ይመጣል ለሚለው ተስፋ ያላቸውን አድናቆት ይገልጻሉ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የደች ወደብ በጃፓኖች በቦምብ ስትደበደብ የነበረውን ሁኔታ እስካሁን በደንብ ያስታውሱታል። ምስክርነቱን ለመስጠት ባደረግናቸው በእንዲህ ዓይነቶቹ ጉዞዎች ወቅት ያሳለፍነው ትዝታም የዚያኑ ያህል የማይረሳ ነው።
ቀስ በቀስ ሞቅ ያለ ስሜት አሳዩ
የአየር ጠባዩን ሙቀት መለኪያ ስንመለከት ሙቀቱ ትንሽ እንደጨመረ ተገነዘብን። ይህም ባልተነካው ክልል ውስጥ ስለላለን ሥራ እንዳስብ አደረገኝ። ቀስ እያለ ነው እንጂ የሕዝቡ ልብ ያለማቋረጥ ሞቅ ያለ ስሜት እያሳየ ሲሄድ ተመልክተናል።
ሕዝቡን የሸፈነውን የውጭ ሰዎችን የመጠርጠርና ያለማመን ግርዶሽ ለመግፈፍ ረጅም ጊዜ ወስዶብናል። ወደዚያ አካባቢ ሄደን ባደረግነው የመጀመሪያ ሙከራ ወቅት ቄሶች ወደ አውሮፕላናችን መጥተው የመጣንበትን ዓላማ ከጠየቁን በኋላ ቶሎ መንደራቸውን ለቅቀን እንድንሄድላቸው በቁጣ መጠየቃቸው የተለመደ ነበር። በርግጥ እንዲህ ዓይነት አቀባበል ተስፋ ያስቆርጥ ነበር። ሆኖም በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በማቴዎስ 10:16 ላይ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” ሲል የሰጠንን ምክር አስታወስን። ስለዚህ በአውሮፕላናችን ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ ካንታሎውፕ እና ሌሎችም በአካባቢው በቀላሉ የማይገኙ ነገሮች ይዘን ተመልሰን መጣን። በፊት ጠልተውን የነበሩት ነዋሪዎች አሁን ዕቃ የጫነው አውሮፕላናችን በመምጣቱ ደስ አላቸው።
አንድ ወንድም “መደብሩ” ውስጥ ቀርቶ ለዕቃዎቹ ዋጋ በፈቃዳቸው የሚያመጡትን ነገር ሲቀበል ሌሎች ብዙ ወንድሞች ደግሞ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ አውሮፕላናችን ትኩስ ነገሮችን ይዞ መምጣቱን ይነግራሉ። ይህን ከነገሯቸው በኋላ ግን የቤቱን ባለቤት “በነገርዎ ላይ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያነባሉ እንዴ? የሚያነቡ ከሆኑ ይህን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳና አምላክ ገነትን ሊያመጣልን ቃል እንደገባ የሚገልጽ መጽሐፍ ቢያገኙ ደስ እንደሚልዎት አምናለሁ” ብለው ይጠይቃሉ። እንዲህ ዓይነቱን የሚያጓጓ ግብዣ አልቀበልም የሚል ማን አለ? ሁሉም ያመጣንላቸውን ለሰውነት የሚረዳ ምግብም ሆነ መንፈሳዊ ምግብ በአድናቆት ተቀበሉት። ጥሩ አቀባበል አደረጉልን፤ ብዙ ጽሑፎችም ተበረከቱ። እንዲሁም የጥቂት ሰዎች ልብ ሞቅ ያለ ስሜት አሳየ።
ወደ ጠረፉ መሻገር
በዩኮን ክልል የሚገኘው የዋይትሆርስ ጉባኤ ወደ ካናዳ ‘ተሻግረን’ በሰሜናዊ ምዕራብ ርቀው ከሚገኙ የገጠር አካባቢዎች አንዳንዶቹን እንድንሸፍን የ“መቄዶንያ” ጥሪ አቀረበልን። (ሥራ 16:9) ስለዚህ አምስት ሆንንና በመርከብ ተሳፍረን ከአርክቲክ መስመር በስተሰሜን በቢዩፎርት ባሕር በሚገኘው በማኬንዜይ ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ ወዳለ ቱክቶያክቱክ የሚባል መንደር አቀናን።
እዚያ እንደደረስን ‘ይህን አስቸጋሪ ስም እንዴት አድርጋችሁ ትጠሩታላችሁ?’ ብለን በመገረም ጠየቅናቸው።
አንድ ወጣት ፈገግ ብሎ “ቱክ” ሲል መለሰልን።
“እንዲህ ብሎ መጥራት እንደሚቻል እንዴት አላሰብነውም?” ተባባልን።
የቱክቶያክቱክ ሕዝብ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚገባ የሚያውቅ ሆኖ በማግኘታችን ተገረምን። በዚህም ምክንያት ከብዙ ሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ማድረግ ቻልን፤ ብዙ ጽሑፎችም አበረከትን። ከወጣት አቅኚዎቻችን መካከል አንዱ ከአንድ ሰው ጋር ትምህርት አዘል ውይይት አድርጎ ነበር።
ሰውየው “እኔ’ኮ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን አባል ነኝ!” አለው።
አቅኚውም “ግን የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰዶምን እንደፈቀደ አውቀዋል?” ብሎ ጠየቀው።
“ፈቀደ እንዴ?” አለ ሰውየው በመጠራጠር። ከዚያም “እንግዲያው ከዛሬ ጀምሮ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን አባል አይደለሁም” አለ። በዚህ መንገድ አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ምሥራች ለመቀበል ልቡን ከፈተ።—ኤፌሶን 1:18
አንድ ሽማግሌ በአካባቢው ወዳሉ ቤቶች ሁሉ ሄደን ለመስበክ በምናደርገው ጥረት በጣም ተነኩ። ባብዛኛው የምናገለግለው በእግራችን እየተጓዝን ነበር። ብዙውን ጊዜ አውሮፕላናችን ካረፈበት ቦታ እስከ መንደሩ ድረስ አንድ ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያም በላይ መጓዝ ይኖርብናል። ወደ እያንዳንዱ ቤት ለመሄድ ደግሞ ኮረኮንች በሆነ ወይም በጨቀየ መንገድ ላይ ብዙ መጓዝ ነበረብን። ከዚያም ሰውየው ከኋላዋ ክፍት የሆነች [ፒክ አፕ] መኪናቸውን አዋሱን። እንዴት ጥሩ ነገር ነበር! ወሰኑን ተሻግረን በካናዳ ግዛት ውስጥ ለማገልገል የሚያስችል ትልቅ መብት አገኘን።
ይህ ሁሉ ጥረት ዋጋ አስገኝቷልን?
መጥፎ የአየር ሁኔታ ኖሮ መነቃነቅ ሲያቅተን፣ ወይም ልንሄድ ካሰብንበት ቦታ ሲያዘገየን፣ ወይም ቀኑን ሙሉ ስንመሰክር ውለን አንድም ፍላጎት ያለው ሰው ሳናገኝ ስንቀር፣ አንዳንድ ጊዜም ጥላቻ ሲገጥመን ይህን ሁሉ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ አውጥተን እዚህ ድረስ መምጣታችን ምን ዋጋ አለው? ብለን እናስባለን። ፍላጎት ያላቸው የሚመስሉ እንዲሁም ደብዳቤ በመጻጻፍ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች አግኝተን ግን ደብዳቤ እንዳልጻፉልን ስናስብ የዚህ አገር ሰዎች ደብዳቤ የመጻፍ ልማድ እንደሌላቸው ትዝ ይለናል። የሰዎቹ ተጫዋችነት ስናይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት ያላቸው ይመስለንና እንሳሳት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሥራችን ምን ያህል ተሳክቶልናል የሚለውን ለመገመት ያስቸግራል።
ሌሎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያገኟቸውን ተሞክሮዎች ስናስብ ግን እነዚህ አፍራሽ ሐሳቦች ሁሉ በቶሎ ጠፉልን። ለምሳሌ ከፌርባንክስ የመጣች አንዲት ምስክር በሰሜን በኩል ራቅ ብሎ በሚገኘው ባሮ የተባለ መንደር ውስጥ ስትሰብክ ከምትማርበት ከካሊፎርኒያ ኮሌጅ ለእረፍት ወደ ቤቷ የመጣች አንዲት ወጣት አገኘች። እህት ልጅቷ ወደ ኮሌጅ ከተመለሰችም በኋላ ደብዳቤ በመጻፍ የነበራትን ፍላጎት መገንባትና ማበረታታት ቀጠለች። ዛሬ ወጣቷ ደስተኛና የተጠመቀች የይሖዋ አገልጋይ ነች።
በር ሲንኳኳ ከሐሳቤ ብንን አልኩ፤ በሩን ያንኳኳው ሰው ራሱ በርግጥም ሥራው ጥረት ቢደረግለትም የማይቆጭ መሆኑን የሚያሳይ ሌላ ማረጋገጫ ነበር። ኤልመር የተባለ በኖም ከተማ የሚኖር ብቸኛው የተጠመቀ የኢንዩት ተወላጅ የሆነ ምስክር በሩ ላይ ቆሞ ነበር።
“ወደ አገልግሎት የምትሄዱ ከሆነ እኔም አብሬአችሁ ልሂድ?” ሲል ጠየቀን። ወደሚኖርበት አካባቢ ቀረብ ከሚለው ጉባኤ በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖረው ይህ ሰው አጋጣሚውን ሲያገኝ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በአገልግሎቱ ለመካፈል ፈለገ።
አሁን የፀሐዩ ጨረር ደመናውን ሰንጥቆ ማብራት ጀምሯል፤ ስለዚህ ብዙም ሳንቆይ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ እንችላለን። ኤልመር ወደ አውሮፕላኑ ሲገባ ብሩህ ፊቱ ላይ ይታይ በነበረው ደስታ ተጽናናን። ይህ ቀን ለኤልመር ልዩ ቀን ነው። ሕዝቦቹ ለሆኑት ለኢንዩት ሰዎች ለመስበክ ወደምንሄድበት መንደር አብሮን ሄዶ በዓለም ጠረፍ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ልብ የሸፈነውን መጋረጃ ለመግለጥ በምናደርገው ሙከራ ሊተባበረን ነው።—በአንድ ወንድም የተነገረ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
1. ጋምቤል
2. ሳቩንጋ
3. ኖም
4. ካትሴቢዩ
5. ባሮ
6. ቱክቶያክቱክ
7. ፌርባንክስ
8. አንከሬጅ
9. አናላስካ
10. የደች ወደብ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ለመሄድ ብዙውን ጊዜ በአላስካ ውስጥ ከሚገኙት በርካታ የተራራ ሠንሰለቶች አንዱን ማቋረጥ ያስፈልጋል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤቲ ሃውስ፣ ሶፊ ሜዛክ እና ኬሪ ቲፕልስ ሦስቱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በድምሩ ከ30 ዓመታት በላይ ቆይተዋል