የናይጄሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሃይማኖት ነፃነት አስከበረ
መንደርተኞች የአንድን ገበሬ ምርት ዘረፉ። ሌሎች የአንድን ግንበኛ ቤት በመውረር መሣሪያዎቹን ያዙበት። ሌሎች ደግሞ አንዲትን ሴት መግዛትም ሆነ መሸጥ እንዳትችል ከለከሏት። እንዲህ ያለ ተገቢ ያልሆነ ነገር ለምን ተፈጸመ? ተጠቂዎቹ ሁሉ የይሖዋ ምስክሮች ስለሆኑ በዕድሜ እኩያሞች ማኅበር ውስጥ አንሳተፍም በማለታቸው ነበር። ‘በምን ውስጥ?’ በማለት ትገረም ይሆናል።
የዕድሜ እኩያሞች ማኅበር በአንድ ዓይነት ጊዜ በአንድ ዓይነት መንደር ውስጥ የተወለዱ ሰዎች ያሉበት ማኅበር ነው። አብዛኛውን ጊዜም ማኅበረተኞቹ ወንዶች ናቸው። የዕድሜ እኩያሞች ያሉባቸው ቡድኖች በምሥራቃዊ ናይጄሪያ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ለመንደሩ የሚጠቅም ፕሮጀክት ያካሂዱ ይሆናል። ነገር ግን የጣዖት አምልኮን ይፈጽማሉ፤ እንዲሁም አባላቱ ወደ ጉልምስና መድረሳቸውን ለማሳየት ሲሉ መናፍስታዊ በሆኑ ሥነ ሥርዓቶች ይካፈላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉት ድርጊቶች ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የማይገቡ እንደሆኑ በመግለጽ ስለሚያወግዛቸው የይሖዋ ምስክሮች በእንዲህ ዓይነቶቹ ቡድኖች ውስጥ ምንም ዓይነት ተካፋይነት የላቸውም።—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21፤ 1 ዮሐንስ 5:21
ሳሙኤል ኦኮግቡ በናይጄሪያ በምትገኝ አባ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖር ልብስ ሰፊ ነበር። በ1978 መጀመሪያ ላይ ኡሙንካሉ የተባለ የአላዪ ከተማ የዕድሜ እኩያሞች ማኅበር የጤና ጣቢያ ለማሠራት የሚረዳ “ግብር” እንዲከፍል ጠየቀው። እውነተኛ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን ሳሙኤል ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ይጥራል። ቢሆንም ለጥንቃቄ ሲል የዕድሜ እኩያሞቹ ቡድን ውስጥ አልገባም አለ። በዚያው ዓመት ሚያዝያ 22 ቀን የዚያ ቡድን ስድስት አባላት ሱቁን ሰብረው ገቡና የልብስ ስፌት መኪናውን ያዙበት። ገንዘቡን እስከሚከፍል ድረስ እንይዘዋለን በማለትም ተናገሩ። የማኅበራቸው አባል እስካልሆነ ድረስ ምንም ነገር እንዲከፍል እንደማይገደድ በመናገር ተከራከረ። ሳሙኤል የልብስ ስፌት መሣሪያውን ለማስመለስ ሳይችል በመቅረቱ ነገሩን ወደ ፍርድ ቤት አቀረበው።
ከፍርድ ቤት ወደ ፍርድ ቤት
በአውራጃው ፍርድ ቤት የዕድሜ እኩያሞቹ ቡድን ሳሙኤል በዕድሜ እኩያቸው እንደሆነና በዚህም ምክንያት በራሳቸው ተነሳስተው ለመክፈል የወሰኑትን ማንኛውንም ግብር የመክፈል ኃላፊነት አለበት ሲሉ ተከራከሩ። ከዚህም በተጨማሪ አንድ አባል ግብር ካልከፈለ ግብሩን እስኪከፍል ድረስ ንብረቱ እንደሚያዝ የሚያደርግ የአካባቢው ባሕል አለ የሚል ክርክር ቀረበ።
ችሎቱ በነገሩ ሳይስማማ ቀረ። ሳሙኤል የዕድሜ እኩያሞቹ ቡድን አባል እንዲሆን ሊገደድ አይችልም በማለት ፍርድ ቤቱ የካቲት 28, 1980 ላይ ወሰነ። የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ዳኛ እንዲህ አሉ፦ “አንድን ዜጋ ማኅበረተኛ የመሆን ነፃ ምርጫውን የሚከለክል ባሕል የናይጄሪያን ፌደራል ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 የሚጻረር ስለሆነ የሕግ ድጋፍ አያገኝም።”
የዕድሜ እኩያሞቹ ቡድን ይህንን ውሳኔ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉና እነርሱን የሚደግፍ ውሳኔ ተወሰነ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ነገሩ ለተወለደበት መንደር ዕድገት የሚደረግ ቀላል መዋጮ እንደሆነ በመግለጽ ሳሙኤል ግብሩን እንዲከፍል አዘዙ።
ከዚያም ሳሙኤል ፍርዱ የተዛባ ነው በማለት ይግባኝ ጠየቀ። የይግባኝ ችሎት የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ፍርድ ሽሮ ለሳሙኤል ፈረደለት። ሽንፈትን ለመቀበል እምቢተኛ በመሆን የዕድሜ እኩያሞቹ ቡድን ጉዳዩን ወደ ናይጄሪያው ጠቅላይ ፍርድ ቤት አደረሰው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቡድኑ አባላት ሳሙኤል በሚኖርበት መንደር ውስጥ በምስክሮቹ ላይ ችግር ለመፍጠር ይጣደፉ ነበር። ምስክሮቹ የመንደሩን ፕሮጀክቶች ሁሉ የሚቃወሙ ናቸው በማለት የመንደሩ ሹም በአካባቢው ባለው የይሖዋ ምስክሮች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ እንዲያደርግ አሳመኑት። በመንደሩ ጥሩንባ እየነፋ በመዞር ማስታወቂያ የሚናገር ሰው ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም ሰው እንደሚቀጣ አስታወቀ። በአካባቢው ባሉ መንደሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች በነገሩ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ጉዳዩን ለመንደሩ ሽማግሌዎች ግልጽ አደረጉላቸው። የአምላክ ሕዝቦች በምንም መንገድ ማኅበረሰባዊ ዕድገቶችን እንደማይቃወሙ አብራሩላቸው። እንዲያውም ሳሙኤል በዕድሜ እኩያሞቹ ቡድን ላልተዘጋጁ የመንደሩ ፕሮጀክቶች መዋጮዎች የከፈለባቸውን ደረሰኞች ለፍርድ ቤቱ አሳየ። የመንደሩ ሽማግሌዎች ምስክሮቹን ለማግለል አድርገውት የነበረውን ውሳኔ ሻሩ።
የሃይማኖት ነፃነት አሸነፈ
ጥቅምት 21, 1991 የናይጄሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አምስት ዳኞች በሙሉ ድምፅ ለሳሙኤል ፈረዱለት። በዳኛ ፖል ንዎካዴ የተበየነውን ውሳኔ ዳኛ አቡበከር ዊሊ በዝርዝር ሲያብራሩ “ተከሳሹ [ሳሙኤል] የተቃወመው ግብር መክፈሉን ሳይሆን ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ከሃይማኖታዊ እምነቱ ጋር የሚቃረን የማንኛውም ማኅበር፣ ክበብ ወይም የዕድሜ እኩያሞች ቡድን አባል መሆንን ነው” ብለዋል።
ዳኛው ሐሳባቸውን በመቀጠል እንዲህ አሉ፦ “በ1963 የወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 24(1) ለሁሉም የናይጄሪያ ዜጎች የሕሊና፣ የአስተሳሰብና የሃይማኖት ነፃነት ዋስትና ይሰጣል። ተከሳሹ ከዕድሜ እኩያሞቹ ጋር እንዳይተባበር የሚከለክለውን የሃይማኖቱን ትምህርት፣ አስተሳሰብና ሕሊና የመያዝ መብት አለው። ከዚህ ውጭ የሆነ ማንኛውም ባሕል ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ስለሆነ ምንም ዓይነት ተፈጻሚነት አይኖረውም።”
ባጭሩ ፍርድ ቤቱ ምንም እንኳን በዕድሜ እኩያሞች ቡድን ውስጥ አባል መሆን ማኅበረሰባዊ ባሕል ቢሆንም ማንኛውም ሰው በዚያ ውስጥ እንዲገባ በሕግ አይገደድም በማለት ፈርዷል። እንዲሁም ማንኛውም ሰው መዋጮው ለማኅበረሰባዊ ዕድገት የሚረዳ ቢሆንም እንኳን የማኅበረተኝነት መዋጮ እንዲከፍል አባል ባልሆነበት ማኅበር አማካኝነት በሕግ እንደማይገደድ ደንግጓል። ስለዚህ በዚህ ቀላል በሚመስል አነስተኛ ነገር ለሁሉም ናይጄሪያውያን የሃይማኖት ነፃነት ተከበረላቸው።