የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 11/1 ገጽ 23-27
  • ይሖዋ ያደረገልንን እዩ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ያደረገልንን እዩ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ የተገኘ ተጨማሪ ነፃነት
  • በደቡብ አፍሪካ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት
  • ወጣቶችም በምስክርነቱ ሥራ ይካፈላሉ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 11/1 ገጽ 23-27

ይሖዋ ያደረገልንን እዩ!

“እንዲህ የመሰለ አጋጣሚ እንድናገኝ እንጸልይ ነበር” በማለት አንድ ሰው ተናገረ። ሌላው ደግሞ ሁልጊዜ ከሌሊቱ በአሥር ሰዓት ለጸሎት ይነሳ ነበር። ስለ ምን ለመጸለይ? “አንድ ቀን ይሖዋን በግልጽ ለማምለክ እንድንችል ነፃነት እንዲሰጠን ለመጸለይ ነው” አለ። በጥር ወር 1992 በኢትዮጵያ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች “ነፃነት አፍቃሪዎች” የተባለውን የወረዳ ስብሰባቸውን ለማድረግ በአዲስ አበባ አንድ ላይ ሲገናኙ እነዚህ በትሕትና የቀረቡ ከልብ የመነጩ ጸሎቶች መልስ እንዳገኙ ግልጽ ነበር።

በኢትዮጵያ የተደረገው ይህ ትልቅ ስብሰባ በአፍሪካ ውስጥ ሁኔታዎች እንዴት እየተለወጡ እንዳሉ የሚያመለክት ነበር። በቅርብ ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች በፊት ታግደው ወይም ገደብ ተደርጐባቸው በነበሩባቸው 13 አገሮች ውስጥ ሕጋዊ ነፃነት በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። በኢትዮጵያ ኅዳር 11 ቀን 1991 የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች መንግሥታዊ እውቅና ሲሰጧቸውና ሲመዘግቧቸው የ34 ዓመታቱ መንግሥታዊ ዕገዳ አበቃለት። ምስክሮቹ ወዲያውኑ አገር አቀፍ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት አደረጉ። ሆኖም በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም ውስጥ 7,573 የሚሆን ሕዝብ ተሰብስቦ ማየት ማንም በጉጉት ከጠበቀውና ከገመተው በላይ ነበር። ይህም ለብዙዎቹ ተሰብሳቢዎች ሕልም እንደሚያዩ ያህል ሆኖባቸው ነበር። አሁንም አሁንም እርስ በርሳቸው “ወንድም፣ አምላካችን ይሖዋ ያደረገልንን እይ” ይባባሉ ነበር።—ከመዝሙር 66:1-5፤ 126:1 ጋር አወዳድር።

ለ34 ዓመታት በዕገዳ ሥር መቆየታቸው አንዳንድ ያልተጠበቁ ችግሮችን ፈጥሯል። ብዙዎቹ ውብ የሆኑትን የመንግሥቱ መዝሙሮች አያውቋቸውም ነበር። ከስብሰባው በፊት መዝሙሮቹን መዘመር እንዴት ይማሩ ይሆን? በስብሰባው ፕሮግራም ላይ የተጠቀሙባቸውን 17 መዝሙሮች ጨምሮ አርባ መዝሙሮች በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመው ተዘጋጁ። ከዚያም መዝሙሮቹን በካሴት ላይ ለመቅዳት ልዩ የመዝሙር ቡድን ተደራጀ። በዋና ከተማው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ጉባኤ የካሴቱን አንድ ቅጂ አገኘና ሙሉው ጉባኤ ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ 30 ደቂቃ በመውሰድ መዝሙሮቹን ተለማመዱ። ውጤቱስ? በስብሰባው ወቅት ስታዲየሙ ከልብ በመነጩ የደስታ መዝሙሮች ተሞላ።

በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በነበረው ረብሻ ምክንያት ከድሬዳዋና ከሐረር ወደ ዋና ከተማው የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ ነበር። ከዚያ ለመጓጓዝ የነበረው ብቸኛው መንገድ በአውሮፕላን ነበር። በሐረር የሚገኙ ስምንት ወንድሞች በስብሰባው ላይ ለመገኘት ቢቆርጡም የአየር ጉዞው ወጪ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው ወደ አንድ ወታደራዊ ሠፈር ሄዱና በወታደሮች አውሮፕላን እንዲሄዱ ጥያቄ አቀረቡ። በሚያስደንቅ ሁኔታ ጥያቄያቸው መልስ አገኘ። ወደ ስብሰባውም በነፃ እንዲጓዙ ተፈቀደላቸው!

ላለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት በችግርና በስደት ለጸኑት እንዲያውም አንዳንድ ጓደኞቻቸው በእምነታቸው ምክንያት በሞት ሲቀጡ ለተመለከቱ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን ወንድሞች የጸሎታቸውን መልስ ማግኘታቸው የደስታ እንባ አመጣባቸው። ለስብሰባው የመጣ አንድ ሰው እንዲህ አለ፦ “ስብሰባው ከተጀመረ ጀምሮ ሳለቅስ ነበር።” ሌላው ደግሞ “ልብን የማንበብ ችሎታ ቢኖራችሁ ኖሮ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ታዩ ነበር” አለ። አዎን፣ ይሖዋ ለእነዚህ ምስክሮች ያደረገላቸው እንዴት ያለ አስደናቂ ነገር ነበር!—መዝሙር 66:16, 19

በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ የተገኘ ተጨማሪ ነፃነት

የይሖዋ ሕዝቦች ሥራ በቅርቡ ሕጋዊ የሆነባት ሌላዋ አገር ቤኒን ናት። ምስክሮቹ ስለ ነፃነቱ የተሰማቸው እንዴት ነው? በአንድ የክርስቲያኖች ስብሰባ ላይ የነበረ አንድ ተናጋሪ፦ “በዚህ አገር የተገኘው የአምልኮ ነፃነት በእውነትም ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው” በማለት ተናገረ። አዎን፣ አሁን እዚያ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ብዙዎቻችን እንደ ተራ ነገሮች አድርገን የምንቆጥራቸውን ለአምልኮ አንድ ላይ የመሰብሰብና ስለ ይሖዋ መንግሥት ለጎረቤቶቻቸው የመናገር ያልተገደበ ነፃነት ስላገኙ በጥልቅ አመስጋኞች ናቸው።

ደስታቸውን እንዴት ያሳዩ ይሆን? ከላይ የተጠቀሰው ተናጋሪ ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉበትን አንዱን መንገድ እንዲህ በማለት አመልክቷል፦ “በስብከቱ ሥራ መካፈላችን በተለይም የምሥራቹን ይዘን ከቤት ወደ ቤት መሄዳችን ለዚህ ነፃነት ያለንን አድናቆት ያንጸባርቃል።” በቤኒን ውስጥ ይህ በእርግጥ ተደርጓል። እንደ ማስረጃ እንዲሆን የአቅኚዎችን ቁጥር ብቻ ተመልከቱ። በ1990 በዚያ አገር የ14 ዓመት ዕገዳቸው በተነሳበት በጥር ወር 77 አስፋፊዎች በዘወትር የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ነበሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ቁጥሩ ከሦስት እጥፍ በላይ ጨምሮ ወደ 244 ደርሷል!

ይህ ማለት ግን በቤኒን ያሉት ምስክሮች ዕገዳው ከመነሳቱ በፊት እንቅስቃሴ አያደርጉም ነበር ማለት አይደለም። በእርግጥም ጽናታቸው በሚያዙበት ጊዜ የሚታሰሩበትን ሠፈር እንዲያስጠብቅ በተመደበ በአንድ ወታደራዊ ባለ ሥልጣን ላይ ጥልቅ ውጤት አምጥቷል። ይሖዋን ለማገልገል ያላቸው ቁርጥ ውሳኔ ቶሎ ቶሎ መታሠርን ስላስከተለባቸው ሰውየው ከእነሱ ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ሊኖረው ቻለ። ይሁን እንጂ ይህ በፊት በሕጋዊ ነፃነታቸው ይደሰቱ በነበረበት ወቅት ከእነሱ ጋር ያደረጋቸውን አስደሳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይቶች እንዲያስታውስ አድርጎታል።

በመጨረሻም ጠንካራው እምነታቸው በውስጡ መንፈሳዊ ረሃብ እንዲቀሰቀስ አደረገ። የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖችንና የእምነት ቡድኖችን ዞሮ አየ። ግን ይህን ረሃቡን በፍጹም ሊያረካለት አልቻለም። በጥር 1990 ዕገዳው ከተነሳ በኋላ ብቻ ነበር ከምስክሮቹ ጋር ተገናኝቶ በነፃነት መጽሐፍ ቅዱስን ለመወያየትና ለሚያስፈልገው መንፈሳዊ ነገር መልስ ሊያገኝ የቻለው። አሁን እሱ ተጠምቆ በአቅኚነት እያገለገለ ነው። ይህ ሰው ያደረገው ለውጥ የቤኒን ወንድሞች “ያ ቀድሞ ያሳድደን የነበረው ሰው፣ ያን ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” የተባለለትን በጠርሴሱ ሳውል ላይ የደረሰውን ሁኔታ ያስታውሳቸዋል።—ገላትያ 1:23

በታኅሣስ ወር 1991 ላይ የይሖዋ ምስክሮች በሌላው የምዕራብ አፍሪካ አገር በኒጀር እንደ ሕጋዊ ማኅበር ተደርገው ተመዘገቡና በሥራቸው ላይ የነበረው ዕገዳ አበቃ። እዚህም ቢሆን የተገኘው ነፃነት ደስታ አምጥቷል። የኒጀርን ሥራ ይከታተል የነበረው የናይጄሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የነበረውን አዎንታዊ ምላሽ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል፦ “ዐርብ ዕለት በመርዲ ከተማ የስብሰባውን መሠረታዊ ዓላማ የሚገልጽ ንግግር ከተደረገ በኋላ አሁን በኒጀር ውስጥ ሕጋዊ እውቅና እንዳለን ለወንድሞች ማስታወቂያ ተነገራቸው። በጣም ተደስተው ለበርካታ ደቂቃዎች አጨበጨቡ። በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ ወንድሞች እርስ በእርስ በመተቃቀፍ ይህን በመሰለው የምሥራች እንደተደሰቱ ገለጹ።” ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን በመመልከት እኛም ከእነሱ ጋር ለመደሰት እንችላለን።

እዚያ ያሉ ወንድሞች አዲስ ያገኙትን ነፃነታቸውን እንዴት ይጠቀሙበት ይሆን? በኒጀር ያለች አንዲት አቅኚ እህት የጥያቄው መልስ ምን መሆን እንዳለበት ጥርጣሬ የላትም። እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “እውነታዎቹ እንደሚያሳዩት በኒጀር የአገልግሎት ክልላችን ውስጥ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ከታላቂቱ ባቢሎን የሚወጡ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። በየወሩ ከ80 እስከ 85 ተመላልሶ መጠየቅ ሪፖርት ማድረጌና ብዙዎቹን ተመላልሶዎች ለሌሎች አስፋፊዎች አስረክቤም እንኳን ከ13 እስከ 14 የሚደርሱ ጥናቶችን ለመምራት መቻሌ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆናል።” ይህች ታማኝ እህት ጨምራም፦ “በጤንነት ችግር ምክንያት በመስክ አገልግሎቱ እንደምፈልገው ያህል ለመሥራት አልቻልኩም። ግን እያንዳንዱ ሰው የሚሠራው የሚችለውን ያህል ነው” አለች።

በመካከለኛው አፍሪካ በሩዋንዳ ውስጥ የይሖዋ ምስክሮች ያሉበት ሁኔታ በአስደናቂ ሁኔታ ተቀይሯል። በመጨረሻ በሚያዝያ 1992 በመጨረሻ ላይ ሕጋዊ እውቅና ያለው ድርጅት መሆናቸውን የሚገልጽ ሰነድ ተሰጣቸው። ሰነዱ የተሰጣቸው የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሳምንት ስለነበር 1,526 የሚሆኑት በሩዋንዳ ያሉ አስፋፊዎች 6,228 ሰዎች በዚያ ወቅት ተገኝተው በማየታቸው በጣም ተደንቀው ነበር። እነዚህ ውድ ወንድሞች ደስታቸውንና አድናቆታቸውን ከበፊቱ በበለጠ የምሥራቹን በማወጅ ያሳዩ ይሆን? በግልጽ አሳይተዋል! በዚያው በሚያዝያ ወር የጉባኤ አስፋፊዎች 27.7 የሆነ አማካይ ሰዓት በመመስከሩ ሥራ ሲያውሉ 17 ተመላልሶ መጠየቆች በማድረግ በአማካይ 2.4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርተዋል። እንዲሁም ከእነሱ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት

ወደ ደቡባዊ አፍሪካ ወረድ ስንል ትኩስ የነፃነት አየር በሁለት ውብ አገሮች ማለትም በሞዛምቢክና በአንጐላ ላይ እየነፈሰ እንዳለ እንገነዘባለን። በየካቲት ወር 1991 ላይ በሞዛምቢክ ሕጋዊ እውቅና ተሰጠ። በዚያ የነበረው ሁኔታ ሲረጋጋ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በእርስ በርስ ጦርነት በሚያሳዝን ሁኔታ ወደፈራረሰችው አገር ሚስዮናውያንን ላከ። ሚስዮናውያኑ ለም አፈር አገኙ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በተለይም የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለው መጽሐፍ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው። አንዲት ሚስዮናዊ ከሁለት ሰዓት ተኩል ባነሰ ጊዜ ውስጥ 50 መጻሕፍት እንዳበረከተች ሪፖርት አድርጋለች።

ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በፍጥነት ምላሽ ሰጡ። ለማኅበር ተሰጥቶ በነበረው አንድ አድራሻ መሠረት አንድ ሚስዮናዊ ጉብኝት ሲያደርግ ሰውየው በውትድርና ውስጥ የሚያገለግል ሰው ሆኖ ተገኘ። ከሰውየውና ከሁለት ዘመዶቹ ጋር ጥሩ ውይይት ተደረገ። በተመላልሶ መጠየቁም ጊዜ ከሰውየውና ከሌሎች አምስት ሰዎች ጋር ሌላ ፍሬያማ ውይይት ተካሄደ። ከዚያም በሕዝብ ንግግርና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ እንዲገኙ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ። ይህ ሁሉ የሆነው በአራት ቀናት ውስጥ ነው።

የአንጐላ ምስክሮች በሚያዝያ 1992 ለሥራቸው ሕጋዊ እውቅና እስካገኙበት ጊዜ ድረስ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ነፃነት አግኝተው ነበር። ይህንን ተጨማሪ ነፃነታቸውን እንዴት እየተጠቀሙበት ይሆን? በመስክ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው! በአንጎላ ወደ 17,000 የሚሆኑ አስፋፊዎች ይገኛሉ። እነዚህ አስፋፊዎች ወደ 60,000 የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ። ወደፊት ሊገኝ የሚችለው ጭማሪ ምንኛ ብዙ ነው!

ወጣቶችም በምስክርነቱ ሥራ ይካፈላሉ

የስብከቱ ሥራ በቅርቡ ሕጋዊ በተደረገባቸው በእነዚህ አገሮች ወጣቶችና ገና ያልተጠመቁት እንኳን በአገልግሎቱ በመሳተፍ አድናቆታቸውን እያሳዩ ናቸው። በኅዳር ወር 1990 ላይ የይሖዋ ምስክሮች በሕግ በታወቁበት በኬፕ ቨርዴ ሪፑብሊክ ውስጥ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንዲት የ17 ዓመት ልጃገረድ እምነቷን በሕዝብ ፊት ለማሳየት ቆመች። ከጥምቀቱ በኋላም አንድ ጎብኚ ዙሪያዋን የከበባትን ሕዝብ ተመለከተ። እንኳን ደስ ያለሽ ሊላት ሄደና ሰዎቹ እነማን እንደነበሩ ጠየቃት። “እነዚህማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ናቸው” በማለት መለሰችለት። ሰባት ጥናቶችን ትመራ ነበር። እነሱም በጥምቀቷ ጊዜ እንኳን ደስ ያለሽ ሊሏት እዚያ ተገኝተው ነበር። ረዳት አቅኚ ሆና ለማገልገል ማመልከቻ አስገብታለች፤ እንዲሁም ወደፊት የዘወትር አቅኚ እንደምትሆን ተስፋ ታደርጋለች።

በአንጎላ አንዲት የአሥር ዓመት ልጅ አስፋፊ ነሽ ወይ ተብላ ተጠየቀች። “አዎን” ስትል መለሰች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ትመራ ይሆን? “አዎን እመራለሁ” አለች። ምን ያህል ናቸው? ይህች የአሥር ዓመት ልጅ “ሰባት” ስትል መለሰች።

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአንድ ወቅት ላይ ስለሆነው ሁኔታ እንዲህ እናነባለን፦ “በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም [በይሖዋም አዓት] ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።” (ሥራ 9:31) እኛም በአፍሪካ ላሉ ወንድሞቻችን ይህ ጊዜ የሰላም ጊዜ እንዲሆንላቸው እንጸልያለን። እየታነጹ ሲሄዱ እኛም ከእነርሱ ጋር እንደሰታለን። እንዲሁም ነፃነታቸውን የምሥራቹን ለማሠራጨት ሲጠቀሙበትና እየበዙ ሲሄዱ የይሖዋ መንፈስ በእነሱ ላይ እንዲሆን እንጸልያለን።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የይሖዋ ምስክሮች ሕጋዊ እውቅና የተሰጠባቸው ወይም እገዳው የተነሳላቸው አገሮች

 1. ጋምቢያ፣ ታኅሣሥ 1989

 2. ቤኒን፣ ጥር 1990

 3. የኬፕ ቨርዴ ሪፑብሊክ፣ ኅዳር 1990

 4. ሞዛምቢክ፣ የካቲት 1991

 5. ጋና፣ ኅዳር 1991

 6. ኢትዮጵያ፣ ኅዳር 1991

 7. ኮንጎ፣ ኅዳር 1991

 8. ኒጀር፣ ታኅሣሥ 1991

 9. ቶጐ፣ ታኅሣሥ 1991

10. ቻድ፣ ታኅሣሥ 1992

11. ኬንያ፣ መጋቢት 1992

12. አንጎላ፣ ሚያዝያ 1992

13. ሩዋንዳ፣ ሚያዝያ 1992

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤኒን አንድ የመንግሥት አስፋፊ የማቴዎስ 24:14⁠ን ቃላት ሰው በሚረዳው መንገድ በከበሮ እየመታ ለሌሎች ያሰማል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብዙ የአፍሪካ አገሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች አዲስ ያገኙትን ነፃነታቸውን በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀሙበት ነው

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳዲስ ምስክሮች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ያሳያሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ