ታኅሣሥ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1
ሙታን [ይነሣሉ]።—ሉቃስ 20:37
ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ኃይሉ አለው? በሚገባ! እሱ “ሁሉን ቻይ” ነው። (ራእይ 1:8) በመሆኑም ሞትን ጨምሮ ማንኛውንም ጠላት ድል ለማድረግ ኃይሉ አለው። (1 ቆሮ. 15:26) ይሖዋ ሙታንን ማስነሳት እንደሚችል እርግጠኛ የምንሆንበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ገደብ የለሽ የማስታወስ ችሎታ ያለው መሆኑ ነው። እያንዳንዱን ኮከብ በስም ይጠራል። (ኢሳ. 40:26) የሞቱ ሰዎችንም ያስታውሳል። (ኢዮብ 14:13፤ ሉቃስ 20:38) ከሞት ከሚያስነሳቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እያንዳንዷን ዝርዝር ጉዳይ በቀላሉ ማስታወስ ይችላል፤ ይህም ጄነቲካዊ መረጃቸውን፣ የሕይወት ተሞክሯቸውንና ትዝታዎቻቸውን ይጨምራል። ይሖዋ የሞቱትን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው ስለምናውቅ የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን። አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት የምንጥልበት ሌላም ምክንያት አለ፦ ይሖዋ ከዚህ ቀደም የሞቱትን አስነስቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ኢየሱስን ጨምሮ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች ሙታንን እንዲያስነሱ ኃይል ሰጥቷቸዋል። w23.04 9-10 አን. 7-9
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2
ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።—ቆላ. 4:6
በዘዴና በገርነት የምንናገር ከሆነ ሰዎች እኛን ለማዳመጥና ውይይቱን ለመቀጠል ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ፍላጎቱ በክርክር ማሸነፍ ወይም በእምነታችን ላይ ማሾፍ ብቻ ከሆነ ለግለሰቡ ምላሽ የመስጠት ግዴታ የለብንም። (ምሳሌ 26:4) ይሁንና እንዲህ የሚያደርጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ምናልባትም ብዙዎች ለመስማት ፈቃደኛ መሆናቸው አይቀርም። በእርግጥም ገርነትን ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው። አከራካሪ ጥያቄ ሲቀርብልህ ወይም ተገቢ ያልሆነ ትችት ሲሰነዘርብህ ገር ለመሆን የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ገርነት ማሳየትህ የአመለካከት ልዩነቶች ወደ ጭቅጭቅ እንዳይሻገሩ ሊያደርግ እንደሚችል አስታውስ። በተጨማሪም ገርነትና አክብሮት የሚንጸባረቅበት ምላሽ መስጠትህ አንዳንድ ሰዎች ስለ እኛም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ስለ እምነትህ ‘መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁን፤ ይህን ስታደርግ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።’ (1 ጴጥ. 3:15) እንግዲያው፣ ገር በመሆን ጥንካሬህን አሳይ! w23.09 19 አን. 18-19
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3
ትዕግሥትን ልበሱ።—ቆላ. 3:12
ትዕግሥት ማሳየት የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት። አንደኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው ለቁጣ ይዘገያል። የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመው ወይም ውጥረት ውስጥ ሲሆን ለመረጋጋት ይሞክራል፤ እንዲሁም አጸፋ ከመመለስ ይቆጠባል። (ዘፀ. 34:6) ሁለተኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው ተረጋግቶ መጠበቅ ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው፣ አንድ ነገር ከጠበቀው በላይ ረጅም ጊዜ ቢወስድም እንኳ ላለመበሳጨት ጥረት ያደርጋል። (ማቴ. 18:26, 27) ሦስተኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው አይቸኩልም። አስፈላጊ ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት ሥራውን ተጣድፎ አይጀምርም፤ ወይም ሥራውን ለመጨረስ አይቸኩልም። ከዚህ ይልቅ ሥራውን በምን መንገድ እንደሚያከናውን ለማቀድ የተወሰነ ጊዜ ይመድባል። ከዚያም በቂ ጊዜ ሰጥቶ ሥራውን ያከናውናል። አራተኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው ሳያጉረመርም ፈተናዎችን ለመቋቋም ጥረት ያደርጋል። አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ለመጽናት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል። (ቆላ. 1:11) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሁሉንም የትዕግሥት ገጽታዎች ማንጸባረቅ ያስፈልገናል። w23.08 20-21 አን. 3-6
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4
ልብን የሚመረምር . . . ይሖዋ ነው።—ምሳሌ 17:3
ምሳሌያዊ ልባችንን ለመጠበቅ የሚያነሳሳን አንዱ ወሳኝ ምክንያት ይሖዋ ልባችንን የሚመረምር መሆኑ ነው። ይህም ሲባል ሰዎች ከሚያዩት ገጽታችን ባሻገር እውነተኛ ውስጣዊ ማንነታችንን ይመለከታል ማለት ነው። ሕይወት ሰጪ በሆነው ጥበቡ አእምሯችንን የምንሞላ ከሆነ ይወደናል። (ዮሐ. 4:14) እንዲህ ካደረግን ከሰይጣንና ከእሱ ዓለም የሚመጣውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መርዝ የምናስተናግድበት ቦታ አይኖረንም። (1 ዮሐ. 5:18, 19) ወደ ይሖዋ ይበልጥ በቀረብን መጠን ለእሱ ያለን ፍቅርና አክብሮት ይጨምራል። አባታችንን ማሳዘን ስለማንፈልግ ኃጢአት መፈጸምን ስናስበው እንኳ ይዘገንነናል። በክሮኤሺያ የምትኖር ማርታ የተባለች እህት የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም ተፈትና ነበር፤ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አጥርቼ ማሰብና ኃጢአት ከመፈጸም የሚገኘውን ቅጽበታዊ ደስታ ለማግኘት ያደረብኝን ፍላጎት መቋቋም ከብዶኝ ነበር። ሆኖም ለይሖዋ ያለኝ ፍርሃት ጥበቃ አድርጎልኛል።” ማርታ ለአምላክ ያላት ፍርሃት ጥበቃ ያደረገላት እንዴት ነው? መጥፎ ውሳኔ ብታደርግ የሚከተለውን መዘዝ ቆም ብላ ማሰቧ እንደረዳት ተናግራለች። እኛም እንደዚያው ማድረግ እንችላለን። w23.06 20-21 አን. 3-4
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5
“ዓይኖቻቸው እያዩ በመካከላችሁ በምቀደስበት ጊዜ” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ “ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”—ሕዝ. 36:23
ኢየሱስ፣ የይሖዋ ዓላማ ስሙን መቀደስ ማለትም ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ ያውቃል። ጌታችን፣ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ማቴ. 6:9) ኢየሱስ ሁሉንም ፍጥረታት የሚመለከተው ወሳኝ ጉዳይ ይህ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ካሉ ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት መካከል የኢየሱስን ያህል የይሖዋን ስም ለማስቀደስ ጥረት ያደረገ ማንም የለም። ሆኖም ኢየሱስ በታሰረ ጊዜ ጠላቶቹ የከሰሱት ምን ብለው ነው? አምላክን ተሳድቧል ብለው ነው! ኢየሱስ የአባቱን ቅዱስ ስም መሳደብ ከኃጢአቶች ሁሉ የከፋው እንደሆነ እንደሚሰማው ምንም ጥያቄ የለውም። በዚህ ኃጢአት መከሰሱ በጣም ረብሾት ነበር። ኢየሱስ ከመያዙ በፊት በነበሩት ሰዓታት “በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ” የነበረው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።—ሉቃስ 22:41-44፤ w24.02 11 አን. 11
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 6
ቤት በጥበብ ይገነባል።—ምሳሌ 24:3
በሕይወት ሩጫ ስንካፈል ከቤተሰቦቻችን ይልቅ ይሖዋንና ኢየሱስን መውደድ እንዳለብን ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴ. 10:37) ይህ ሲባል ግን የቤተሰብ ኃላፊነታችንን ችላ እንላለን ማለት አይደለም። እንዲያውም በአምላክና በክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን የቤተሰብ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 5:4, 8) እንዲህ ስናደርግ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ደግሞም ይሖዋ ባልና ሚስት እርስ በርስ ሲዋደዱና ሲከባበሩ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲወዱና ሲያሠለጥኑ እንዲሁም ልጆች ወላጆቻቸውን ሲታዘዙ ቤተሰቦች ደስተኛ እንደሚሆኑ ያውቃል። (ኤፌ. 5:33፤ 6:1, 4) በቤተሰብ ውስጥ ያለህ ሚና ምንም ይሁን ምን በስሜት፣ በባሕል ወይም ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር ከመመራት ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ተከተል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። ጽሑፎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ጠቃሚ ምክር ይዘዋል። w23.08 28 አን. 6-7
እሁድ፣ ታኅሣሥ 7
በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው፤ እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።—ኢያሱ 1:8
ክርስቲያን ሴቶች ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። አንዲት ሴት በልጅነቷ የምትማራቸው አንዳንድ ክህሎቶች በመላ ሕይወቷ ሊጠቅሟት ይችላሉ። ለምሳሌ ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ማዳበር። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ማንበብና መጻፍ ለሴቶች አስፈላጊ እንደሆኑ ክህሎቶች ተደርገው አይታዩም። ይሁንና ሁሉም ክርስቲያኖች እነዚህን ክህሎቶች ማዳበር ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞ. 4:13) ስለዚህ ማንኛውም እንቅፋት ጥሩ አድርጋችሁ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ከማዳበር እንዲያግዳችሁ አትፍቀዱ። እንዲህ ማድረጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? እነዚህ ክህሎቶች ሥራ ለማግኘትና ራሳችሁን ለማስተዳደር ሊረዷችሁ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ የአምላክን ቃል በመማርና በማስተማር ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ትሆናላችሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የአምላክን ቃል ማንበባችሁና ማሰላሰላችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርቡ ይረዳችኋል።—1 ጢሞ. 4:15፤ w23.12 20 አን. 10-11
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8
ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን . . . ያውቃል።—2 ጴጥ. 2:9
ፈተናን ለማሸነፍ እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቅ። ፍጹማን ስላልሆንን መጥፎ ነገር ላለማድረግ ሁልጊዜ መታገል ያስፈልገናል። ሰይጣን ደግሞ ይህን ትግል ይበልጥ ለማክበድ ይጥራል። አስተሳሰባችንን ለመመረዝ የሚሞክርበት አንዱ መንገድ ወራዳ መዝናኛ በመጠቀም ነው። እንዲህ ያለው መዝናኛ አእምሯችን በርኩስ ሐሳቦች እንዲሞላ ያደርጋል፤ እነዚህ ሐሳቦች ደግሞ ውስጣዊ ማንነታችንን ሊያበላሹትና ወደ ከባድ ኃጢአት ሊመሩን ይችላሉ። (ማር. 7:21-23፤ ያዕ. 1:14, 15) መጥፎ ነገር እንድናደርግ የሚደርስብንን ፈተና ለመወጣት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ውስጥ “ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” የሚለውን ልመና አካቷል። (ማቴ. 6:13) ይሖዋ ሊረዳን ይፈልጋል፤ ሆኖም እርዳታውን ልንጠይቅ ይገባል። ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃም መውሰድ አለብን። w23.05 6-7 አን. 15-17
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9
በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም።—መክ. 4:12
አንድ ባልና ሚስት ከሰማዩ አባታቸው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ከሆነ ምክሮቹን ወዲያውኑ በሥራ ላይ ያውላሉ። ይህ ደግሞ በመካከላቸው ያለው ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ሊያደርጉ የሚችሉ ችግሮችን ለማስወገድ ወይም ለማሸነፍ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች እንደ ደግነት፣ ትዕግሥትና ይቅር ባይነት ያሉትን ባሕርያት በማዳበር ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 4:32–5:1) ባለትዳሮች እነዚህን ባሕርያት የሚያሳዩ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ፍቅር ማደጉ አይቀርም። በትዳር ዓለም ከ25 ዓመት በላይ ያሳለፈች ሌና የተባለች እህት “መንፈሳዊ የሆነን ሰው መውደድና ማክበር ቀላል ነው” በማለት ተናግራለች። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ለመሲሑ ወላጆች ሲመርጥ በወቅቱ ከነበሩት በርካታ የዳዊት ዘሮች መካከል ዮሴፍንና ማርያምን መርጧል። ለምን? ሁለቱም በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ነበራቸው። ይሖዋም በትዳራቸው ውስጥ እሱን እንደሚያስቀድሙ እርግጠኛ ነበር። w23.05 21 አን. 3-4
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10
በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ።—ዕብ. 13:17
መሪያችን ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም ምድር ላይ አመራር እንዲሰጡን የሚጠቀምባቸው ወንድሞች ፍጹማን አይደሉም። በተለይ ማድረግ የማንፈልገውን ነገር እንድናደርግ በሚጠይቁን ጊዜ እነሱን መታዘዝ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ለመታዘዝ አመንትቶ ነበር። አንድ መልአክ በሙሴ ሕግ መሠረት ርኩስ የሆኑ እንስሳትን እንዲበላ ባዘዘው ጊዜ ጴጥሮስ ከአንዴም ሦስት ጊዜ አልበላም ብሏል። (ሥራ 10:9-16) ለምን? አዲሱ መመሪያ ምክንያታዊ እንደሆነ አልተሰማውም። በሌላ በኩል ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ሕጉን እንደሚከተል ለማሳየት አራት ሰዎችን ይዞ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄድና የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጽም ሲያዙት በፈቃደኝነት ታዟል። ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር እንዳልሆኑ ያውቃል። እንዲሁም ምንም ያጠፋው ጥፋት የለም። ያም ቢሆን “በማግስቱ ሰዎቹን ይዞ በመሄድ አብሯቸው የመንጻት ሥርዓቱን ፈጸመ።” (ሥራ 21:23, 24, 26) የጳውሎስ ታዛዥነት አንድነት እንዲሰፍን አድርጓል።—ሮም 14:19, 21፤ w23.10 10 አን. 15-16
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 11
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እሱን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው።—መዝ. 25:14
ፍርሃት ለጥሩ ጓደኝነት አስፈላጊ ባሕርይ ነው ብለህ ላታስብ ትችላለህ። ያም ቢሆን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ‘እሱን ሊፈሩት’ ይገባል። ይሖዋን ስናገለግል የቆየነው ለምንም ያህል ጊዜ ቢሆን ሁላችንም ለእሱ ምንጊዜም ጤናማ ፍርሃት ሊኖረን ይገባል። ሆኖም አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? ለአምላክ ተገቢ ፍርሃት ያለው ሰው እሱን ይወደዋል፤ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና የሚያበላሽ ምንም ነገር ማድረግ አይፈልግም። ኢየሱስ እንዲህ ያለ “አምላካዊ ፍርሃት” ነበረው። (ዕብ. 5:7) ይህ ሲባል በፍርሃት ይንቀጠቀጣል ማለት አይደለም። (ኢሳ. 11:2, 3) ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር የነበረው ከመሆኑም ሌላ እሱን መታዘዝ ይፈልግ ነበር። (ዮሐ. 14:21, 31) ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮትና አድናቆት አለን፤ ምክንያቱም እሱ አፍቃሪ፣ ጥበበኛ፣ ፍትሐዊና ኃያል ነው። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚወደንና ለመመሪያዎቹ የምንሰጠው ምላሽ በእሱ ስሜት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ እናውቃለን። ይሖዋ ካልታዘዝነው እጅግ ያዝናል፤ ስንታዘዘው ደግሞ ልቡ ይደሰታል።—መዝ. 78:41፤ ምሳሌ 27:11፤ w23.06 14 አን. 1-2፤ 15 አን. 5
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 12
በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ . . . በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።—2 ዜና 26:16
ንጉሥ ዖዝያ በበረታ ጊዜ የብልጽግናውና የብርታቱ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ዘነጋ። እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ያሉን በረከቶችና መብቶች ከይሖዋ የተገኙ መሆናቸውን ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። ባገኘናቸው ስኬቶች የተነሳ ጉራ ከመንዛት ይልቅ ላከናወንነው ነገር ይሖዋን ልናመሰግን ይገባል። (1 ቆሮ. 4:7) ፍጹማን እንዳልሆንንና ተግሣጽ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን መቀበል ይኖርብናል። በ60ዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለራሴ ከፍ ያለ አመለካከት ሊኖረኝ እንደማይገባ ተምሬያለሁ። አንዳንድ ጊዜ በሠራኋቸው የሞኝነት ስህተቶች የተነሳ ተግሣጽ ሲሰጠኝ ማሻሻያ ለማድረግና ወደፊት መግፋቴን ለመቀጠል ጥረት አደርጋለሁ።” እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይሖዋን የምንፈራና ለራሳችን ትሕትና የሚንጸባረቅበት አመለካከት የምናዳብር ከሆነ ሕይወታችን የተሻለ ይሆናል።—ምሳሌ 22:4፤ w23.09 10 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 13
የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋል።—ዕብ. 10:36
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መጽናት ያስፈልጋቸው ነበር። በሁሉም ሰው ላይ ከሚደርሰው ችግር በተጨማሪ ሌላም ፈተና ነበረባቸው። ብዙዎቹ ስደት ደርሶባቸዋል፤ ከአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችና ከሮም ባለሥልጣናት በተጨማሪ የገዛ ቤተሰቦቻቸው ይቃወሟቸው ነበር። (ማቴ. 10:21) በጉባኤው ውስጥ ደግሞ ከሃዲዎችንና የእነሱ ከፋፋይ ትምህርት የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መፋለም ነበረባቸው። (ሥራ 20:29, 30) ያም ቢሆን እነዚያ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ በጽናት ተቋቁመዋል። (ራእይ 2:3) ለመጽናት የረዳቸው ምንድን ነው? እንደ ኢዮብ ባሉ የጽናት ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላቸው ጠቅሟቸዋል። (ያዕ. 5:10, 11) ኃይል ለማግኘት ጸልየዋል። (ሥራ 4:29-31) ጽናታቸው ያስገኘው ግሩም ውጤት ላይ ማተኮራቸውም ረድቷቸዋል። (ሥራ 5:41) እኛም በአምላክ ቃልና በጽሑፎቻችን ላይ ስለተጠቀሱ የጽናት ምሳሌዎች አዘውትረን የምናጠናና የምናሰላስል ከሆነ መጽናት እንችላለን። w23.07 3 አን. 5-6
እሁድ፣ ታኅሣሥ 14
እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።—ማቴ. 6:33
ይሖዋና ኢየሱስ ተስፋ አይቆርጡብንም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቶስን ከካደው በኋላ ትልቅ ውሳኔ ከፊቱ ተደቅኖ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆኖ ይጸናል? ወይስ እሱን መከተሉን ያቆማል? ኢየሱስ የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ወደ ይሖዋ ምልጃ አቅርቦ ነበር። ኢየሱስ ለጴጥሮስ ስለዚህ ጸሎት የነገረው ከመሆኑም ሌላ ጴጥሮስ በኋላ ላይ ወንድሞቹን እንደሚያበረታ እምነት እንዳለው ገለጸለት። (ሉቃስ 22:31, 32) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር መለስ ብሎ ሲያስብ ምንኛ ተጽናንቶ ይሆን! በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ውሳኔ ሲደቀንብን ይሖዋ አፍቃሪ የሆኑ እረኞችን በመጠቀም ታማኝ ሆነን እንድንጸና ብርታት ሊሰጠን ይችላል። (ኤፌ. 4:8, 11) ይሖዋ ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት በቁሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዳሟላላቸው ሁሉ እኛም የይሖዋን አገልግሎት በሕይወታችን ካስቀደምን የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ያሟላልናል። w23.09 24-25 አን. 14-15
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15
ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል።—ምሳሌ 19:17
ይሖዋ ለሌሎች የምናሳየውን ትንሿን ደግነት እንኳ ያስተውላል። ውድ ዋጋ እንዳለው መሥዋዕት አድርጎ ይመለከተዋል፤ ለእሱ እንዳበደርነው አድርጎም ይቆጥረዋል። የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነህ የማገልገል መብትህን አጥተህ ከሆነ ይሖዋ ያከናወንከውን ሥራና ይህን ለማድረግ ያነሳሳህን ፍቅር እንደማይረሳ አስታውስ። (1 ቆሮ. 15:58) አሁን እያሳየህ ያለኸውንም ፍቅር ያስተውላል። ይሖዋ ሁላችንም ለእሱም ሆነ ለሌሎች ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ይፈልጋል። ቃሉን በማንበብና በማሰላሰል እንዲሁም አዘውትረን ወደ እሱ በመጸለይ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። አጋጣሚዎች ፈልገን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በማገዝ ለእነሱ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። ፍቅራችን እያደገ ሲሄድ ወደ ይሖዋም ሆነ ወደ መንፈሳዊ ቤተሰባችን ይበልጥ እንቀርባለን። ይህ ወዳጅነት ደግሞ ለዘላለም ይዘልቃል! w23.07 10 አን. 11፤ 11 አን. 13፤ 13 አን. 18
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
‘ጤናዬን እንዴት ልንከባከብ?’ የሚለው ጉዳይ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የተተወ ውሳኔ ነው። የአንድን ክርስቲያን የሕክምና ምርጫ የሚነኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቀጥተኛ ሕጎች ጥቂት ናቸው፤ እነሱም ከደምና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ የተሰጡት ሕጎች ናቸው። (ሥራ 15:20፤ ገላ. 5:19, 20) ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ ለግለሰቡ ምርጫ የተተወ ነው። ለእኛ ይበጀናል ብለን የመረጥነው የሕክምና ዓይነት ምንም ይሁን ምን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የራሳቸውን የሕክምና ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸው ልንገነዘብ ይገባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነጥቦች ማስታወስ ይኖርብናል፦ (1) የተሟላና ዘላቂ ፈውስ የሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። (ኢሳ. 33:24) (2) እያንዳንዱ ክርስቲያን ይበጀኛል ብሎ የመረጠው ሕክምና “ሙሉ በሙሉ ያመነበት” ሊሆን ይገባል። (ሮም 14:5) (3) በሌሎች ላይ መፍረድ ወይም የሚያሰናክል ነገር ማስቀመጥ አይኖርብንም። (ሮም 14:13) (4) ክርስቲያኖች ለሌሎች ፍቅር ያሳያሉ፤ የግል ምርጫ ከማድረግ መብታቸው የሚበልጥባቸው የጉባኤው አንድነት ነው።—ሮም 14:15, 19, 20፤ w23.07 24 አን. 15
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 17
ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ ቅዱስ ይሆናል።—ዘኁ. 6:8
ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? እንደምትመለከተው ጥያቄ የለውም! ከጥንት ዘመን አንስቶ እንዲህ የተሰማቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች አሉ። (መዝ. 104:33, 34) ብዙዎች ይሖዋን ለማምለክ መሥዋዕት ከፍለዋል። በጥንቷ እስራኤል የኖሩት ናዝራውያን (ለአንድ ዓላማ የተወሰኑ ሰዎች) ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። “ናዝራውያን” የሚለው ቃል፣ ይሖዋን ልዩ በሆነ መንገድ ለማገልገል ሲሉ አንዳንድ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኛ የነበሩትን ቀናተኛ እስራኤላውያን ጥሩ አድርጎ ይገልጻቸዋል። የሙሴ ሕግ፣ አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለይሖዋ ልዩ ስእለት በመሳል ለተወሰነ ጊዜ ያህል ናዝራዊ ሆነው ለመኖር መምረጥ እንደሚችሉ ይናገራል። (ዘኁ. 6:1, 2) አንድ ሰው እንዲህ ያለውን ስእለት ከተሳለ፣ ሌሎች እስራኤላውያን እንዲታዘዙ የማይጠበቅባቸውን አንዳንድ መመሪያዎች መታዘዝ ይጠበቅበታል። ታዲያ አንድ እስራኤላዊ የናዝራዊነት ስእለት ለመሳል የሚመርጠው ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ስእለት ለመሳል የሚያነሳሳው ለይሖዋ ያለው ጥልቅ ፍቅርና ከእሱ ላገኛቸው በረከቶች ያለው ልባዊ አድናቆት እንደሆነ ግልጽ ነው።—ዘዳ. 6:5፤ 16:17፤ w24.02 14 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 18
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ . . . ታማኝ ፍቅር [ታሳያለህ]።—ዳን. 9:4
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ታማኝነት” ወይም “ታማኝ ፍቅር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት አምላክ ከአገልጋዮቹ ጋር ያለውን ፍቅራዊ ቁርኝት ለማመልከት ነው። ይኸው ቃል በአምላክ አገልጋዮች መካከል ያለውን ፍቅር ለማመልከትም ተሠርቶበታል። (2 ሳሙ. 9:6, 7) ታማኝነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሊሄድ ይችላል። የዳንኤል ታማኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሄደው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ዳንኤል በመላ ሕይወቱ ለይሖዋ ያለው ታማኝነት ተፈትኗል። ሆኖም ከደረሱበት ትላልቅ ፈተናዎች አንዱ ያጋጠመው በ90ዎቹ ዕድሜ ሳለ ነው። የቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት ዳንኤልን ይጠሉት ነበር፤ ለሚያመልከው አምላክም አክብሮት አልነበራቸውም። በመሆኑም ዳንኤልን ለማስገደል ሴራ ጠነሰሱ። ‘ዳንኤል ታማኝ የሚሆነው ለአምላኩ ነው ወይስ ለንጉሡ’ የሚለውን ለመፈተን አንድ አዋጅ እንዲታወጅ አደረጉ። ዳንኤል ለንጉሡ ያለውን ታማኝነት ለማረጋገጥ ማድረግ የሚጠበቅበት ለ30 ቀናት ያህል ወደ ይሖዋ መጸለዩን ማቆም ብቻ ነበር። ዳንኤል አቋሙን ለማላላት ፈቃደኛ አልሆነም።—ዳን. 6:12-15, 20-22፤ w23.08 5 አን. 10-12
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 19
እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል።—1 ዮሐ. 4:7
ይሖዋ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር በማሳየት እንድንጸና ይፈልጋል። አንድ ወንድማችን አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሳያሳይ ከቀረ፣ ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ቢፈልግም እንኳ ሳያስበው ስሜታችንን እንደጎዳው ልናስብ እንችላለን። (ምሳሌ 12:18) አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ ድክመት ቢኖርባቸውም እንኳ ይወዳቸዋል። ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ተስፋ አይቆርጥብንም፤ ወይም ቂም አይዝብንም። (መዝ. 103:9) ይቅር ባይ የሆነውን አባታችንን መምሰላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ኤፌ. 4:32–5:1) ከዚህም ሌላ፣ ወደ መጨረሻው እየተቃረብን ስንሄድ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተቀራርበን መኖር እንደሚያስፈልገን ማስታወስ ይኖርብናል። የሚደርስብን ስደት እየጨመረ እንደሚመጣ መጠበቅ እንችላለን። ምናልባትም በእምነታችን ምክንያት እንታሰር ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ያስፈልጉናል።—ምሳሌ 17:17፤ w24.03 15-16 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 20
ይሖዋ የሰውን አካሄድ ይመራል።—ምሳሌ 20:24
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ይሖዋ የቀረቡ፣ የእሱን ሞገስ ያገኙና አስደሳች ሕይወት መምራት የቻሉ ወጣቶችን ታሪክ ይዟል። ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ዳዊት ነው። ዳዊት በወጣትነቱ ከይሖዋ ጎን ለመቆም መርጧል፤ በኋላም ታማኝ ንጉሥ ሆኗል። (1 ነገ. 3:6፤ 9:4, 5፤ 14:8) ስለ ዳዊት ሕይወት እንዲሁም በታማኝነት ስላቀረበው አገልግሎት ማጥናትህ ሊያበረታታህና ለሥራ ሊያነሳሳህ ይችላል። አሊያም ደግሞ ስለ ማርቆስ ወይም ስለ ጢሞቴዎስ ሕይወት ማጥናት ትችላለህ። እነዚህ ሰዎች ከልጅነታቸው አንስቶ ሕይወታቸውን በሙሉ ይሖዋን በማገልገላቸው የእሱን ሞገስ ማግኘት እንደቻሉ ትገነዘባለህ። የወደፊት ሕይወትህ የተመካው በአሁኑ ጊዜ ሕይወትህን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ ነው። በይሖዋ ከታመንክና በገዛ ራስህ ማስተዋል ካልተመካህ እሱ አካሄድህን ይመራልሃል። ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ትችላለህ። ይሖዋ ለእሱ ስትል የምታደርገውን ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አትዘንጋ። አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ከማገልገል ሌላ ሕይወትህን ልትጠቀም የምትችልበት ምን የተሻለ መንገድ አለ? w23.09 13 አን. 18-19
እሁድ፣ ታኅሣሥ 21
እርስ በርስ . . . በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 3:13
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ፍጹማን እንዳልሆኑ ያውቅ ነበር። ለምሳሌ ከጉባኤው ጋር ለመቀላቀል ጥረት ማድረግ በጀመረበት ወቅት ወንድሞች አላመኑትም ነበር። (ሥራ 9:26) ከጊዜ በኋላም አንዳንዶች ስለ እሱ መጥፎ ነገር በመናገር ስሙን አጥፍተዋል። (2 ቆሮ. 10:10) ጳውሎስ፣ ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም ሌሎችን ሊያሰናክል የሚችል መጥፎ ውሳኔ ሲያደርግ ተመልክቷል። (ገላ. 2:11, 12) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ከቅርብ ጓደኞቹ አንዱ የሆነው ማርቆስ እንደጠበቀው ሆኖ ሳይገኝ በመቅረቱ በጣም አዝኗል። (ሥራ 15:37, 38) ጳውሎስ በእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳ፣ ቅር ካሰኙት ወንድሞች ለመራቅ ሊወስን ይችል ነበር። ያም ቢሆን ለወንድሞቹና ለእህቶቹ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ጸንቷል። ታዲያ ጳውሎስን እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? ጳውሎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን ይወዳቸው ነበር። ጳውሎስ ለሌሎች ያለው ፍቅር በድክመቶቻቸው ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። በተጨማሪም ጳውሎስ ፍቅር ያለው መሆኑ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ሥራ ላይ እንዲያውል ረድቶታል። w24.03 15 አን. 4-5
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22
የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር [ሊሆን ይገባዋል]።—2 ጢሞ. 2:24
መጽሐፍ ቅዱስ የገርነትን ጥቅም የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። የይስሐቅን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይስሐቅ የፍልስጤማውያን ክልል በሆነው በጌራራ መኖር በጀመረበት ወቅት ጎረቤቶቹ ስለቀኑበት የአባቱ አገልጋዮች የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች ደፈኑ። ይስሐቅ መብቱን ለማስከበር ከመታገል ይልቅ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ሌሎች የውኃ ጉድጓዶችን ቆፈረ። (ዘፍ. 26:12-18) ይሁንና ፍልስጤማውያን ይሄኛውም ውኃ የእነሱ እንደሆነ ተናገሩ። ያም ቢሆን ይስሐቅ ሰላማዊ መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍ. 26:19-25) ይስሐቅ ሌሎች ሆን ብለው የሚያበሳጭ ነገር ቢያደርጉበትም ገርነት እንዲያሳይ የረዳው ምንድን ነው? ወላጆቹ ከተዉት ምሳሌ እንደተማረ ምንም ጥያቄ የለውም። አብርሃም ያሳየውን ሰላማዊነትና ሣራ ያሳየችውን “የሰከነና ገር መንፈስ” ኮርጇል።—1 ጴጥ. 3:4-6፤ ዘፍ. 21:22-34፤ w23.09 15 አን. 4
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23
ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም።—ኢሳ. 46:11
የሚወደን አባታችን ይሖዋ፣ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ሰዎችን ስለ መንግሥቱ እንዲያስተምርና ቤዛውን በመክፈል ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንዲያወጣን አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከው። ከዚያም ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ በመሄድ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ፣ ይሖዋ በክርስቶስ በሚመራው መንግሥቱ አማካኝነት ለምድር ያለውን ዓላማ በመፈጸም ስሙን ከነቀፋ ነፃ እንደሚያደርገው የሚገልጽ ነው። የይሖዋ ዓላማ አይቀየርም። ዓላማውን እንደሚያሳካ ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳ. 46:10፤ ዕብ. 6:17, 18) ከጊዜ በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች፤ በዚያም ፍጹምና ጻድቅ የሆኑ የአዳምና ሔዋን ዘሮች ‘ለዘላለም ተደስተው ይኖራሉ።’ (መዝ. 22:26) ይሁንና የይሖዋ ዓላማ ይህ ብቻ አይደለም። ዋነኛ ዓላማው፣ በሰማይና በምድር ያሉ ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታቱን በሙሉ አንድ ማድረግ ነው። ከዚያም ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ለእሱ ሉዓላዊነት በታማኝነት ይገዛሉ። (ኤፌ. 1:8-11) ይሖዋ ዓላማውን የሚፈጽምበት ግሩም መንገድ አያስደንቅህም? w23.10 20 አን. 7-8
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24
“በርቱ . . . እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።—ሐጌ 2:4
ከባቢሎን ነፃ የወጡት አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም ከደረሱ ብዙም ሳይቆይ የኢኮኖሚ ችግር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም ተቃውሞ አጋጠማቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ በመገንባቱ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ ከብዷቸው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የሕዝቡን ቅንዓት መልሶ ለማቀጣጠል ሁለት ነቢያትን ማለትም ሐጌንና ዘካርያስን ላከላቸው። እነዚህ ነቢያት የሰጧቸው ማበረታቻ ግሩም ውጤት አስገኝቷል። (ሐጌ 1:1፤ ዘካ. 1:1) ይሁንና አይሁዳውያኑ ከ50 ዓመት ገደማ በኋላ በድጋሚ ማበረታቻ አስፈልጓቸው ነበር። የተካነ የሕጉ ገልባጭ የሆነው ዕዝራ በዚያ ወቅት ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ የአምላክ ሕዝቦች ለእውነተኛው አምልኮ ቅድሚያ እንዲሰጡ አበረታታቸው። (ዕዝራ 7:1, 6) የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው በይሖዋ መታመናቸውን እንዲቀጥሉ እንደረዷቸው ሁሉ እኛም ተነዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ስንኖር ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን ይረዱናል።—ምሳሌ 22:19፤ w23.11 14 አን. 2-3
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25
ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።—ቆላ. 3:14
ለእምነት አጋሮቻችን ያለንን ፍቅር የምናሳየው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እነሱን ማጽናናት ነው። ርኅራኄ ካለን ‘ሁልጊዜ እርስ በርሳችን ለመጽናናት’ እንነሳሳለን። (1 ተሰ. 4:18) አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሌሎችን ስህተት ይቅር ለማለት የቻልነውን ሁሉ በማድረግ ነው። በተለይ በአሁኑ ጊዜ አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንዳለን ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ ምክንያቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ . . . አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ።” (1 ጴጥ. 4:7, 8) የዚህ ክፉ ዓለም መጨረሻ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሲቃረብ ምን እንደሚሆን እንጠብቃለን? ኢየሱስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏል። (ማቴ. 24:9) እንዲህ ያለውን ጥላቻ ለመቋቋም አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ፍቅር ስለሚያስተሳስረን ሰይጣን እኛን ለመከፋፈል የሚያደርገው ጥረት ይከሽፋል።—ፊልጵ. 2:1, 2፤ w23.11 13 አን. 18-19
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 26
እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።—1 ቆሮ. 3:9
በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውነት ትልቅ ኃይል አለው። ሰዎችን ስለ ይሖዋና ስለ ባሕርያቱ ስናስተምራቸው አስደናቂ ውጤት እናያለን። በሰይጣናዊ ውሸት የታወረው ዓይናቸው ቀስ በቀስ ይበራል፤ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ውድ የሆነውን አባታችንን እኛ በምናየው መንገድ ማየት ይጀምራሉ። ገደብ የለሽ ኃይሉ ያስደምማቸዋል። (ኢሳ. 40:26) ፍጹም የሆነው ፍትሑ እንዲተማመኑበት ያደርጋቸዋል። (ዘዳ. 32:4) ጥልቅ ከሆነው ጥበቡ ብዙ ትምህርት ያገኛሉ። (ኢሳ. 55:9፤ ሮም 11:33) እንዲሁም እሱ ፍቅር መሆኑን ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። (1 ዮሐ. 4:8) ወደ ይሖዋ ሲቀርቡ ልጆቹ ሆነው ለዘላለም የመኖር ተስፋቸው የተረጋገጠ ይሆናል። ሰዎች ወደ አባታቸው እንዲቀርቡ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሥራ ባልደረቦቹ አድርጎ ይመለከተናል።—1 ቆሮ. 3:5፤ w24.02 12 አን. 15
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27
ስእለት ተስለህ ሳትፈጽም ከምትቀር ባትሳል ይሻላል።—መክ. 5:5
መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ከሆነ ወይም ወላጆችህ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ለመጠመቅ እያሰብክ ነው? ይህ በጣም ጥሩ ግብ ነው! ይሁንና ከመጠመቅህ በፊት ራስህን ለይሖዋ መወሰን ይኖርብሃል። ራስህን ለይሖዋ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ በመጸለይ፣ እሱን ብቻ እንደምታመልክ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ የእሱን ፈቃድ እንደምታስቀድም ቃል ትገባለህ። እንዲህ ስታደርግ እሱን ምንጊዜም “በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ” እንደምትወድ ለይሖዋ ቃል መግባትህ ነው። (ማር. 12:30) ራስህን የምትወስነው በግልህ ነው፤ ይህ በአንተና በይሖዋ መካከል ያለ ጉዳይ ነው። የምትጠመቀው ግን በሕዝብ ፊት ነው። ጥምቀት፣ ራስህን መወሰንህን ለሌሎች ለማሳየት ያስችላል። ራስን መወሰን ቅዱስ ስእለት ነው፤ ይሖዋም ይህን ስእለት እንድትፈጽም ይጠብቅብሃል፤ አንተም ይህን ስእለት ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።—መክ. 5:4፤ w24.03 2 አን. 2፤ 4 አን. 5
እሁድ፣ ታኅሣሥ 28
ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።—ኤፌ. 5:33
በሁሉም ትዳሮች ውስጥ ችግር መፈጠሩ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮ. 7:28) ለምን? ምክንያቱም በትዳር የሚጣመሩት ፍጽምና የጎደላቸው ሁለት ሰዎች ናቸው፤ ሁለቱም ባሕርያቸው እንዲሁም የሚወዱትና የሚጠሉት ነገር የተለያየ ነው። ባልና ሚስቱ የተለያየ ባሕል ወይም አስተዳደግ ይኖራቸው ይሆናል። ከመጋባታቸው በፊት ተደብቀው የነበሩ አንዳንድ ባሕርያት ውሎ አድሮ ብቅ ማለት ሊጀምሩ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች በባለትዳሮቹ መካከል ግጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ባለትዳሮቹ በችግሩ ውስጥ የሁለቱም እጅ እንዳለበት አምነው ከመቀበልና ችግሩን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የትዳር አጋራቸውን ተጠያቂ ማድረግ ይጀምሩ ይሆናል። ይባስ ብሎም ብቸኛው መፍትሔ መለያየት ወይም መፋታት እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁንና መፍትሔው ትዳሩን ማፍረስ ነው? አይደለም። ይሖዋ፣ ባለትዳሮች የትዳር አጋራቸው አብሮ ለመኖር አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ የጋብቻን ዝግጅት አክብረው እንዲኖሩ ይፈልጋል። w24.03 16 አን. 8፤ 17 አን. 11
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29
ተስፋውም ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።—ሮም 5:5
ራስህን ወስነህ ከተጠመቅክ በኋላ ይበልጥ እየተማርክና በመንፈሳዊ እየጎለመስክ ስትሄድ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋህ ማደጉን ቀጥሏል። (ዕብ. 5:13–6:1) በሮም 5:2-4 ላይ ያለውን ሐሳብ እውነተኝነት በገዛ ሕይወትህ ተመልክተህ መሆን አለበት። የተለያዩ መከራዎች ቢያጋጥሙህም እነሱን በጽናት በመቋቋምህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተሃል። አምላክ ሞገሱን እንዳሳየህ ስለምታውቅ እሱ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደምታገኝ ከበፊቱ ይበልጥ እርግጠኛ ነህ። ተስፋህ ከመጀመሪያው ይበልጥ ተጠናክሯል። ይበልጥ እውን ሆኖልሃል። በግለሰብ ደረጃ ይነካሃል። በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ማለትም ቤተሰብህን በምትይዝበት መንገድ፣ ውሳኔ በምታደርግበት መንገድ አልፎ ተርፎም ጊዜህን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘን በኋላ ስለምንጎናጸፈው ተስፋ ሌላ ወሳኝ ሐሳብ ተናግሯል። ተስፋችን እንደሚፈጸም ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ሮም 15:13፤ w23.12 12-13 አን. 16-19
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30
[ይሖዋ] አጽንቶ . . . ያቆማችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ስሜታችን፣ አስተሳሰባችን እንዲሁም ለተለያዩ ነገሮች የምንሰጠው ምላሽ እንደ ቀድሞው ሚዛኑን የጠበቀ ላይሆን ይችላል። በስሜት ማዕበል እንደምንናወጥ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ያሉ ስሜቶች ሲያናውጡን ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? ይሖዋ አጽንቶ እንደሚያቆመን ቃል ገብቶልናል። አንድ መርከብ ማዕበል ሲያጋጥመው በኃይል ሊወዛወዝ ይችላል። ብዙ መርከቦች እንዲህ ያለውን ነውጥ ለመቀነስ የሚያስችል በሁለቱም ወገን ወደ ውኃው ውስጥ የሚገባ ክንፍ አላቸው። ይህ የመርከቡ ክፍል መርከቡ በኃይል እንዳይናወጥ ያደርገዋል፤ ይህም ተሳፋሪዎቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ተመችቷቸው እንዲጓዙ ያስችላል። ይሁንና እነዚህ ክንፎች ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት መርከቡ ወደፊት እየተጓዘ ከሆነ ነው። በተመሳሳይም በመከራ ወቅት በታማኝነት ወደፊት መጓዛችንን ስንቀጥል ይሖዋ አጽንቶ ያቆመናል። w24.01 22 አን. 7-8
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 31
በአምላክ እታመናለሁ፤ አልፈራም።—መዝ. 56:4
ፍርሃት ሲሰማህ ‘ይሖዋ ከዚህ በፊት ምን አድርጓል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እሱ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ አሰላስል። ለምሳሌ ይሖዋ በእሱ መልክ ያልተፈጠሩትንና እሱን የማምለክ ችሎታ የሌላቸውን ወፎችና አበቦች የሚንከባከብበትን መንገድ ‘ልብ ብለን ስንመለከት’ እኛንም እንደሚንከባከበን ያለን እምነት ይጠናከራል። (ማቴ. 6:25-32) ይሖዋ ከዚህ በፊት ለአገልጋዮቹ ያደረገላቸውን ነገርም አስብ። አስደናቂ እምነት ስላሳየ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ልታጠና ወይም በዘመናችን የኖረን አንድ የይሖዋ አገልጋይ ተሞክሮ ልታነብ ትችላለህ። ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ እስካሁን ባደረገልህ እንክብካቤ ላይ አሰላስል። ወደ እውነት የሳበህ እንዴት ነው? (ዮሐ. 6:44) ጸሎትህን የመለሰልህ እንዴት ነው? (1 ዮሐ. 5:14) የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት በማድረጉ በየዕለቱ እየተጠቀምክ ያለኸው እንዴት ነው?—ኤፌ. 1:7፤ ዕብ. 4:14-16፤ w24.01 4 አን. 6፤ 7 አን. 17