መጋቢት
ቅዳሜ፣ መጋቢት 1
[ተስፋው] ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።—ሮም 5:5
አዲሱ ዓለም ገና አልመጣም። ሆኖም አሁን ያሉት ከዋክብት፣ ዛፎች፣ እንስሳት እንዲሁም ሰዎች ያልነበሩበት ጊዜ እንደነበር አስታውስ። እነዚህ ነገሮች ያልነበሩበት ጊዜ ቢኖርም ማንም ሰው እውን መሆናቸውን አይጠራጠርም። እነዚህ ነገሮች ሊኖሩ የቻሉት ይሖዋ ስለፈጠራቸው ብቻ ነው። (ዘፍ. 1:1, 26, 27) በተመሳሳይም አምላካችን አዲስ ዓለም የማምጣት ዓላማ አለው። ይህን ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰዎች ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ለዘላለም ይኖራሉ። ይሖዋ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ አዲሱ ዓለም ዛሬ ያለውን ጽንፈ ዓለም ያህል እውን ይሆናል። (ኢሳ. 65:17፤ ራእይ 21:3, 4) እስከዚያው ግን፣ የምታገኟቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅማችሁ እምነታችሁን አጠናክሩ። ለቤዛው አድናቆት አዳብሩ። በይሖዋ ኃይል ላይ አሰላስሉ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመዱ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ “አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት [ከሚወርሱት]” መካከል ትሆናላችሁ።—ዕብ. 6:11, 12፤ w23.04 31 አን. 18-19
እሁድ፣ መጋቢት 2
ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?—ዮሐ. 11:40
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመልክቶ በሕዝቡ ፊት ጸለየ። ቀጥሎ ለሚከናወነው ነገር ክብር ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ ለማሳየት ፈልጓል። ከዚያም ኢየሱስ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ተጣራ። (ዮሐ. 11:43) አልዓዛርም ከመቃብሩ ወጣ! ኢየሱስ አንዳንዶች ‘ሊሆን አይችልም’ ያሉትን ነገር አደረገ። ይህ ዘገባ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እንዴት? ኢየሱስ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት ቃል እንደገባላት አስታውስ። (ዮሐ. 11:23) እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ይህን ቃል ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ አለው። እንባውን ማፍሰሱ ሞትንና ተከትሎ የሚመጣውን ሐዘን ለማስወገድ ከልቡ እንደሚጓጓ ያሳያል። አልዓዛር ከመቃብሩ ሲወጣ ኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው ታይቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ለማርታ ምን እንዳላት ልብ በል። አምላክ የሰጠው የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸም እንድናምን የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ። w23.04 11-12 አን. 15-16
ሰኞ፣ መጋቢት 3
ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።—መዝ. 145:18
የይሖዋ ፈቃድ ይበልጥ ግልጽ ሲሆንልን በጸሎት የምንጠይቀውን ነገር መቀየር ሊያስፈልገን ይችላል። ይሖዋ ዓላማ እንዳለውና ዓላማውን የሚፈጽመው በወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይህ ዓላማው በዛሬው ጊዜ ብዙ መከራ እያስከተሉ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋትን ያካትታል፤ ከእነዚህ ችግሮች መካከል የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ሕመምና ሞት ይገኙበታል። ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ዓላማውን ይፈጽማል። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 21:3, 4) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ሰይጣን ዓለምን እንዲገዛ ፈቅዶለታል። (ዮሐ. 12:31፤ ራእይ 12:9) ይሖዋ የሰው ልጆች በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ቢፈታላቸው የሰይጣን አገዛዝ የተሳካለት ሊመስል ይችላል። ስለዚህ ይሖዋ የገባቸውን አንዳንድ ቃሎች እስኪፈጽም ድረስ መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህ ሲባል ግን ምንም ዓይነት እርዳታ አያደርግልንም ማለት አይደለም። ይሖዋ ይረዳናል። w23.05 8 አን. 4፤ 9-10 አን. 7-8
ማክሰኞ፣ መጋቢት 4
ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ [እወቁ]።—ቆላ. 4:6
ሌሎች ከመታሰቢያው በዓል እንዲጠቀሙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ልንጋብዛቸው ይገባል። በመደበኛው አገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ከመጋበዝ በተጨማሪ ልንጋብዛቸው የምንችላቸውን ሌሎች ሰዎች ዘርዝረን መጻፍ እንችላለን። ከእነዚህ መካከል ዘመዶቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን የሚማሩ ልጆች እንዲሁም ሌሎች ይገኙበታል። በወረቀት የታተመው መጋበዣ በበቂ መጠን ባይኖረንም እንኳ መጋበዣው የሚገኝበትን ሊንክ መላክ እንችላለን። ምን ያህል ሰዎች ግብዣችንን እንደሚቀበሉ ማን ያውቃል? (መክ. 11:6) የጋበዝናቸው ሰዎች፣ በተለይ በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው የማያውቁ ከሆነ ጥያቄ ሊኖራቸው እንደሚችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ምን ዓይነት ጥያቄ ሊያነሱ እንደሚችሉ ማሰብና መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርብናል። እንግዶቻችን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙ በኋላም ተጨማሪ ጥያቄዎች ሊኖሯቸው ይችላሉ። “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ከመታሰቢያው በዓል የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ከበዓሉ በፊት፣ በበዓሉ ወቅትም ሆነ ከበዓሉ በኋላ የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።—ሥራ 13:48፤ w24.01 11 አን. 13፤ 12 አን. 15፤ 13 አን. 16
ረቡዕ፣ መጋቢት 5
ለጥቂት ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ።—ያዕ. 4:14
መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የኖሩ ስምንት ሰዎችን ታሪክ ይዟል። እያንዳንዱን ታሪክ በጥልቀት ለማጥናት ለምን ጥረት አታደርግም? በምታጠናበት ጊዜ ከታሪኮቹ ምን ትምህርት እንደምታገኝ ቆም ብለህ አስብ። እያንዳንዱ ታሪክ አምላክ የሞቱትን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው የሚያረጋግጠው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ከሌሎቹ ትንሣኤዎች ሁሉ ይበልጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ አሰላስል። የኢየሱስ ትንሣኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዓይን ምሥክሮች እንዳሉትና ለእምነታችን አስተማማኝ መሠረት እንደሆነ አትዘንጋ። (1 ቆሮ. 15:3-6, 20-22) ይሖዋ የትንሣኤን ተስፋ ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ አለው። በዚህ ውድ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ፣ ለእያንዳንዳችን ‘ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ይነሳሉ!’ የሚል ቃል ወደገባልን አምላካችን ይበልጥ እንቀርባለን።—ዮሐ. 11:23፤ w23.04 8 አን. 2፤ 12 አን. 17፤ 13 አን. 20
ሐሙስ፣ መጋቢት 6
ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር [ሂድ]።—ሚክ. 6:8
ልክን ማወቅና ትሕትና ተቀራራቢ ባሕርያት ናቸው። ለራሳችንና ላለብን የአቅም ገደብ ተገቢውን አመለካከት በመያዝ ልካችንን እንደምናውቅ እናሳያለን። ራሳችንን ከሌሎች ዝቅ አድርገን በመመልከት ደግሞ ትሑት መሆናችንን እናሳያለን። (ፊልጵ. 2:3) በጥቅሉ ሲታይ፣ ልኩን የሚያውቅ ሰው ትሑት መሆኑ አይቀርም። ጌድዮን ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። የይሖዋ መልአክ፣ እስራኤላውያንን ኃያል ከሆኑት ምድያማውያን እንዲታደግ እንደተመረጠ ለጌድዮን ሲነግረው ይህ ትሑት ሰው እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቷል፦ “የእኔ ጎሳ እንደሆነ ከምናሴ ነገድ የመጨረሻው ነው፤ እኔም ብሆን በአባቴ ቤት ውስጥ እዚህ ግባ የምባል አይደለሁም።” (መሳ. 6:15) ጌድዮን ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንደሆነ አልተሰማውም፤ የይሖዋ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነበር። በይሖዋ እርዳታ ጌድዮን የተሰጠውን ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ መወጣት ችሏል። ሽማግሌዎች በሁሉም ነገር ትሕትናና ልክን ማወቅ ለማንጸባረቅ ጥረት ያደርጋሉ። (ሥራ 20:18, 19) ችሎታቸውንና ያገኙትን ስኬት በተመለከተ ጉራ አይነዙም፤ በአንጻሩ ደግሞ በድክመታቸው ወይም በስህተታቸው ምክንያት ተስፋ አይቆርጡም። w23.06 3 አን. 4-5
ዓርብ፣ መጋቢት 7
እሱ ራስህን ይጨፈልቃል።—ዘፍ. 3:15
የሰይጣን ራስ እስኪጨፈለቅ ድረስ ከ1,000 ዓመት በላይ ይቀራል። (ራእይ 20:7-10) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ከመሆኑ በፊት ስለሚከሰቱ ምድርን የሚያናውጡ ክንውኖች አስቀድሞ ተናግሯል። በመጀመሪያ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው ያውጃሉ። (1 ተሰ. 5:2, 3) ከዚያም ብሔራት በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ታላቁ መከራ “ድንገት” ይጀምራል። (ራእይ 17:16) ቀጥሎም ኢየሱስ በጎቹን ከፍየሎቹ በመለየት በሰው ልጆች መካከል ይፈርዳል። (ማቴ. 25:31-33, 46) ይሁንና ሰይጣን በዚህ ወቅት እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። ሰይጣን በጥላቻ ተነሳስቶ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ በማለት የሚጠራቸውን ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ያደርጋቸዋል። (ሕዝ. 38:2, 10, 11) በዚህ መሃል ቅቡዓን ቀሪዎች ከክርስቶስና ከሰማያዊ ሠራዊቱ ጋር ሆነው በአርማጌዶን ጦርነት ለመካፈል ወደ ሰማይ ይሄዳሉ፤ ይህ ጦርነት የታላቁ መከራ መደምደሚያ ይሆናል። (ማቴ. 24:31፤ ራእይ 16:14, 16) ከዚያም ክርስቶስ ለሺህ ዓመት ምድርን ይገዛል።—ራእይ 20:6፤ w23.10 20-21 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ መጋቢት 8
እኔ አገልጋይህ ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን ስፈራ ኖሬአለሁ።—1 ነገ. 18:12
በዛሬው ጊዜ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች አሉ። እነዚህ ውድ ወንድሞችና እህቶች ለመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገባቸውን ክብር ይሰጣሉ፤ ሆኖም እንደ አብድዩ ይሖዋን ማምለካቸውን ለማቆም ፈቃደኞች አይደሉም። (ማቴ. 22:21) ከሰው ይልቅ አምላክን በመታዘዝ ፈሪሃ አምላክ እንዳላቸው ያሳያሉ። (ሥራ 5:29) እንዲህ የሚያደርጉት ምሥራቹን ማወጃቸውን በመቀጠልና በዘዴ ስብሰባዎችን በማድረግ ነው። (ማቴ. 10:16, 28) ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ሥራችን ለተወሰነ ጊዜ ታግዶ በነበረበት አንድ የአፍሪካ አገር የሚኖረውን የሄንሪን ምሳሌ እንመልከት። በእገዳው ወቅት ሄንሪ ለእምነት ባልንጀሮቹ መንፈሳዊ ምግብ ለማከፋፈል ራሱን አቅርቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በተፈጥሮዬ ዓይናፋር ነኝ። . . . የሚያስፈልገኝን ድፍረት የሰጠኝ [ይሖዋ ነው]።” አንተስ እንደ ሄንሪ ደፋር መሆን የምትችል ይመስልሃል? ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ካዳበርክ እንዲህ ያለ ድፍረት ማሳየት ትችላለህ። w23.06 16 አን. 9, 11
እሁድ፣ መጋቢት 9
በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ።—ሮም 5:12
አዳምና ሔዋን ሲያምፁ አምላክ፣ ምድር ፍጹምና ታዛዥ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ያወጣውን ዓላማ ሰይጣን ያከሸፈው ሊመስል ይችላል። ሰይጣን፣ ይሖዋ ከዚያ በኋላ ብዙ አማራጭ እንደሌለው አስቦ ሊሆን ይችላል። አንደኛው አማራጭ አዳምንና ሔዋንን ማጥፋትና ለሰዎች ያለውን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ሌሎች ፍጹም ባልና ሚስት መፍጠር ነበር። ሆኖም አምላክ ይህን ቢያደርግ ኖሮ ዲያብሎስ እሱን “ውሸታም ነው” ብሎ ይከሰው ነበር። ለምን? ምክንያቱም በዘፍጥረት 1:28 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን፣ ምድር በእነሱ ዘሮች እንደምትሞላ ነግሯቸዋል። ወይም ደግሞ ሰይጣን አዳምና ሔዋን መቼም ቢሆን ፍጽምና ደረጃ ላይ መድረስ የማይችሉ ልጆችን እንዲወልዱ ይሖዋ ይፈቅድላቸዋል ብሎ አስቦ ይሆናል። (መክ. 7:20፤ ሮም 3:23) ይህ ቢሆን ኖሮ ዲያብሎስ፣ ይሖዋ ዓላማውን መፈጸም እንደማይችል በመግለጽ ይከሰው እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም። ለምን? ምክንያቱም ይህ አማራጭ፣ አምላክ ገነት የሆነችው ምድር ፍጹምና ታዛዥ በሆኑ የሰው ልጆች እንድትሞላ ያወጣውን ዓላማ ሊያሳካ አይችልም። w23.11 6 አን. 15-16
ሰኞ፣ መጋቢት 10
ከተጻፈው አትለፍ።—1 ቆሮ. 4:6
ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ግልጽ የሆነ መመሪያ ይሰጠናል። ታዲያ እሱ በሰጠን መመሪያ ላይ የራሳችንን የምናክልበት ምን ምክንያት አለ? (ምሳሌ 3:5-7) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው አልፈን መሄድ ወይም ለምርጫ ከተተዉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ የራሳችንን ደንቦች ማውጣት አንፈልግም። ሰይጣን “ከንቱ ማታለያ” እንዲሁም ‘የዓለምን መሠረታዊ ነገሮች’ በመጠቀም ሰዎችን ለማሳሳትና ለመከፋፈል ይሞክራል። (ቆላ. 2:8) ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሰብዓዊ አመለካከት ላይ የተመሠረቱ ፍልስፍናዎችን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ የአይሁድ ትምህርቶችን እንዲሁም ‘ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ ሊያከብሩ ይገባል’ የሚለውን ትምህርት ተጠቅሟል። እነዚህ ትምህርቶች ማታለያ ነበሩ፤ ምክንያቱም የሰዎችን ትኩረት በመስረቅ የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ዘወር እንዳይሉ አድርገዋል። በዛሬው ጊዜም ሰይጣን የመገናኛ ብዙኃንንና የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይጠቀማል፤ እነዚህ ሚዲያዎች የሴራ ትንታኔዎችንና ፖለቲከኞች የሚነዟቸውን የሐሰት ዘገባዎች ያሰራጫሉ። w23.07 16 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ መጋቢት 11
ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ታላቅ ነው! ሐሳብህም እንዴት ጥልቅ ነው!—መዝ. 92:5
ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን ቢያምፁም ይሖዋ ለሁኔታው መፍትሔ የሰጠበት መንገድ ሰይጣንን በጣም አስደንግጦት መሆን አለበት። ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ በመፍቀድ ውሸታም አለመሆኑን አሳይቷል። በተጨማሪም ይሖዋ ምንም ነገር ዓላማውን ከመፈጸም ሊያግደው እንደማይችል አሳይቷል። ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮችን የሚያድን “ዘር” እንዲገኝ በማድረግ ዓላማውን ለማስፈጸም እርምጃ ወስዷል። (ዘፍ. 3:15፤ 22:18) ሰይጣን፣ ይሖዋ ያደረገውን የቤዛውን ዝግጅት ሲመለከት በጣም ደንግጦ መሆን አለበት! ለምን? ምክንያቱም ቤዛው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ዝግጅት ነው። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16) ራስ ወዳድ የሆነው ሰይጣን ደግሞ እንዲህ ያለው ባሕርይ የለውም። ታዲያ የቤዛው ዝግጅት ምን ውጤት ያስገኛል? በሺህ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ፍጹምና ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ገነት የሆነችውን ምድር ይወርሳሉ፤ በዚህ መንገድ የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ይፈጸማል። w23.11 6 አን. 17
ረቡዕ፣ መጋቢት 12
አምላክ [ይፈርዳል]።—ዕብ. 13:4
ይሖዋ ስለ ሕይወትና ስለ ደም ቅድስና የሰጠውን ሕግ እናከብራለን። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ እንደተናገረው ደም ከእሱ ያገኘነውን ውድ ስጦታ ይኸውም ሕይወትን ይወክላል። (ዘሌ. 17:14) ይሖዋ፣ ሰዎች እንስሳትን እንዲበሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈቅድ ደሙን እንዳይበሉ አዟቸዋል። (ዘፍ. 9:4) የሙሴን ሕግ ለእስራኤላውያን በሰጠበት ወቅትም ይህን ትእዛዝ ደግሞታል። (ዘሌ. 17:10) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደግሞ በበላይ አካሉ አማካኝነት ለሁሉም ክርስቲያኖች ባስተላለፈው ውሳኔ ‘ከደም እንዲርቁ’ መመሪያ ሰጥቷል። (ሥራ 15:28, 29) የሕክምና ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ በዚህ ትእዛዝ ላይ አንደራደርም። በተጨማሪም የይሖዋን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ እንከተላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ የአካል ክፍሎቻችሁን “ግደሉ” በማለት ምስል ከሳች የሆነ አገላለጽ ተጠቅሟል፤ ይህ አገላለጽ መጥፎ የሥጋ ምኞቶችን ለማስወገድ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ያስታውሰናል። ወደ ፆታ ብልግና የሚመራ ማንኛውንም ነገር ከማየትም ሆነ ከማድረግ እንቆጠባለን።—ቆላ. 3:5፤ ኢዮብ 31:1፤ w23.07 15 አን. 5-6
ሐሙስ፣ መጋቢት 13
በመጨረሻም የልቡን ሁሉ አውጥቶ . . . ነገራት።—መሳ. 16:17
ሳምሶን ለደሊላ ባለው ፍቅር ከመታወሩ የተነሳ ምን ለማድረግ እንዳሰበች ማስተዋል ተስኖት ይሆን? ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ደሊላ ከፍተኛ ጥንካሬ የሰጠው ምን እንደሆነ እንዲነግራት ሳምሶንን ወተወተችው። እሱም በስተ መጨረሻ ሚስጥሩን ነገራት። የሚያሳዝነው፣ ሳምሶን የሠራው ስህተት ጥንካሬውንና በይሖዋ ፊት ያለውን ሞገስ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያጣ አደረገው። (መሳ. 16:16-20) ሳምሶን ከይሖዋ ይልቅ ደሊላን ማመኑ አስከፊ መዘዝ አስከትሎበታል። ፍልስጤማውያን ሳምሶንን ይዘው ዓይኑን አሳወሩት። ሳምሶን በጋዛ ታሰረ፤ እዚያም እህል ፈጪ ሆነ። ከዚያም ፍልስጤማውያን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡበት ጊዜ አዋረዱት። ሳምሶንን በእጃቸው እንደሰጣቸው በመግለጽ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት አቀረቡ። ከዚያም ሳምሶን “እንዲያዝናናቸው” ከእስር ቤት አውጥተው ሊቀልዱበት ወደ ግብዣው አመጡት።—መሳ. 16:21-25፤ w23.09 5-6 አን. 13-14
ዓርብ፣ መጋቢት 14
በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት አድርጉ።—ሮም 12:17
ለምሳሌ አንድ የሥራ ባልደረባችን ወይም አብሮን የሚማር ልጅ ከምንከተላቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር በተያያዘ ጥያቄ አነሳ እንበል። የግለሰቡን አመለካከት እንደምናከብር በሚያሳይ መንገድ ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። (1 ጴጥ. 3:15) ጥያቄውን እንደ ትችት ከመቁጠር ይልቅ የግለሰቡን አመለካከት ለማወቅ እንደሚረዳን መንገድ አድርገን መመልከታችን ብዙውን ጊዜ ሊጠቅመን ይችላል። ግለሰቡ ጥያቄውን ያነሳበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን በገርነትና በደግነት ምላሽ መስጠታችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለ ምላሽ መስጠታችን አመለካከቱን መለስ ብሎ እንዲያጤን ሊያነሳሳው ይችላል። ለምሳሌ የሥራ ባልደረባችን ልደት የማናከብረው ለምን እንደሆነ ቢጠይቀን ከጥያቄው በስተ ጀርባ ያለው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? መዝናናት እንደማይፈቀድልን አስቦ ይሆን? በመጀመሪያ ግለሰቡ ለሥራ ባልደረቦቹ አሳቢነት በማሳየቱ ልናመሰግነው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን አእምሮውን ክፍት አድርጎ እንዲያዳምጠንና መጽሐፍ ቅዱስ ከልደት ጋር በተያያዘ ምን እንደሚል ጥሩ ውይይት እንድናደርግ መንገድ ሊከፍት ይችላል። w23.09 16-17 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ መጋቢት 15
ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ጽኑ አቋማችሁ እንዳይናጋ ተጠንቀቁ።—2 ጴጥ. 3:17
የቀረውን ጊዜ ተጠቅመን ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች ምሥክርነት መስጠት መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን ‘በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ አበረታቶናል። (2 ጴጥ. 3:11, 12) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአዲሱ ዓለም ውስጥ በምናገኛቸው በረከቶች ላይ ከተቻለ በየቀኑ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። ንጹሕ አየር ስትተነፍሱ፣ ጤናማ ምግብ ስትመገቡ፣ ከሞት የተነሱ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ስትቀበሉ እንዲሁም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ለኖሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ ስታስተምሩ ይታያችሁ። በዚህ መልኩ ማሰላሰላችሁ የይሖዋን ቀን በጉጉት እንድትጠባበቁ እንዲሁም መጨረሻው መቅረቡን እንዳትዘነጉ ይረዳችኋል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ‘አስቀድመን ስላወቅን’ በሐሰተኛ አስተማሪዎች ‘ተታልለን አንወሰድም።’ w23.09 27 አን. 5-6
እሁድ፣ መጋቢት 16
ከጌታ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ የጽድቅ ተግባር ነውና።—ኤፌ. 6:1
ወጣት ክርስቲያኖች፣ አብዛኞቹ እኩዮቻቸው “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ይሁንና ብዙዎቹ ወጣቶች ታዛዥ ያልሆኑት ለምንድን ነው? አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን የሚያዙትን ነገር እነሱ ራሳቸው አያደርጉትም። በመሆኑም ልጆቻቸው እነሱን መታዘዝ ይከብዳቸዋል። ሌሎች ደግሞ የወላጆቻቸው ምክር ጊዜ ያለፈበት፣ ምክንያታዊነት የጎደለው ወይም ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ወጣቶች፣ እናንተስ እንደዚህ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ብዙዎች በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ ከባድ ይሆንባቸዋል። ታዲያ ይህን ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል? ኢየሱስ በታዛዥነት ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ ነው፤ አንተም ከእሱ መማር ትችላለህ። (1 ጴጥ. 2:21-24) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር፤ ወላጆቹ ግን ፍጹማን አልነበሩም። የኢየሱስ ወላጆች ስህተት ቢሠሩም፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ቢረዱትም ኢየሱስ እነሱን ማክበሩን ቀጥሏል።—ዘፀ. 20:12፤ w23.10 7 አን. 4-5
ሰኞ፣ መጋቢት 17
የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና ፍሬ ቢስ በመሆኑ ተሽሯል።—ዕብ. 7:18
ሐዋርያው ጳውሎስ በሕጉ መሠረት የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደማይችሉ አብራርቶላቸዋል። በዚህም የተነሳ ሕጉ “ተሽሯል።” በመሆኑም ጳውሎስ ጥልቀት ያላቸውን አንዳንድ እውነቶች አስተማራቸው። የእምነት አጋሮቹ ‘ወደ አምላክ እንዲቀርቡ’ ሊረዳቸው የሚችል በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ “የተሻለ ተስፋ” እንዳላቸው አስታውሷቸዋል። (ዕብ. 7:19) ጳውሎስ የክርስቲያኖች የአምልኮ ሥርዓት ቀደም ሲል በሕጉ ሥር ያቀርቡ ከነበረው አምልኮ በእጅጉ የላቀ እንደሆነ ለዕብራውያን ወንድሞቹ አብራርቶላቸዋል። በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩት የአምልኮ ዝግጅቶች “ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው፤ እውነተኛው ነገር ግን የክርስቶስ ነው።” (ቆላ. 2:17) የአንድ ነገር ጥላ የሚያሳየው የእውነተኛውን ነገር መሠረታዊ ቅርጽ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥንት የነበረው የአይሁዳውያን የአምልኮ ሥርዓት ወደፊት ለሚመጣው የተሻለ ነገር ጥላ ብቻ ነበር። ይሖዋ ለኃጢአታችን ይቅርታ አግኝተን ለእሱ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ማቅረብ እንድንችል ስላደረገልን ዝግጅት በሚገባ መረዳት ይኖርብናል። w23.10 25 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ መጋቢት 18
በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ ጋር ይጋፋል፤ የሰሜኑም ንጉሥ . . . እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣበታል።—ዳን. 11:40
ዳንኤል ምዕራፍ 11 ዓለምን ለመቆጣጠር ስለሚታገሉ ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት ወይም የፖለቲካ ኃይሎች ይናገራል። ይህን ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር በማወዳደር ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ሩሲያንና አጋሮቿን፣ “የደቡቡ ንጉሥ” ደግሞ የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ያመለክታል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን። ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ንጉሥ ስደት እየደረሰባቸው ነው። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ተደብድበዋል እንዲሁም ወህኒ ወርደዋል። ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ የሚያደርገው ነገር ወንድሞቻችንን ከማሸበር ይልቅ እምነታቸውን ያሳድግላቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ወንድሞቻችን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው ስደት ዳንኤል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ዳን. 11:41) እኛም ይህን ማወቃችን ብሩህ ተስፋ እንዲኖረንና ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። w23.08 11 አን. 15-16
ረቡዕ፣ መጋቢት 19
እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል።—ዘካ. 2:8
ይሖዋ ስለሚወደን ስሜታችንን ይረዳልናል፤ እንዲሁም ጥበቃ ሊያደርግልን ይጓጓል። ስንጎዳ ያዝናል። በመሆኑም “እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቀኝ” ብለን በልበ ሙሉነት መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 17:8) ዓይናችን የምንሳሳለትና ውድ የሆነ የአካላችን ክፍል ነው። ስለዚህ ይሖዋ ከዓይኑ ብሌን ጋር ሲያመሳስለን ‘እናንተን የነካ ውድ ንብረቴን እንደነካ ይቆጠራል’ ያለን ያህል ነው። ይሖዋ እያንዳንዳችንን እንደሚወደን እንድንተማመን ይፈልጋል። ሆኖም ቀደም ሲል ባጋጠሙን ነገሮች የተነሳ እሱ እንደማይወደን ሊሰማን እንደሚችል ያውቃል። ወይም ደግሞ አሁን እያጋጠሙን ባሉት ሁኔታዎች የተነሳ ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ልንጠራጠር እንችላለን። ታዲያ ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለኢየሱስ፣ ለቅቡዓኑና ለሁላችንም ያለውን ፍቅር ያሳየባቸውን መንገዶች መመርመራችን ይጠቅመናል። w24.01 27 አን. 6-7
ሐሙስ፣ መጋቢት 20
የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበር፤ እሱም በመንገድ ላይ ከጠላት እጅና ከሽምቅ ጥቃት ታደገን።—ዕዝራ 8:31
ዕዝራ በፈተና ወቅት ይሖዋ ሕዝቦቹን የደገፋቸው እንዴት እንደሆነ አይቷል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በ484 ዓ.ዓ. ንጉሥ አሐሽዌሮስ በፋርስ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ እንዲጠፉ አዋጅ ባወጣበት ወቅት ዕዝራ ይኖር የነበረው በባቢሎን ሳይሆን አይቀርም። (አስ. 3:7, 13-15) የዕዝራ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር! ይህ አደጋ ሲደቀንባቸው ‘በሁሉም አውራጃዎች’ ያሉት አይሁዳውያን በመጾምና በማልቀስ ይሖዋ እንዲረዳቸው ለመኑ። (አስ. 4:3) አይሁዳውያንን ለማጥፋት ያሴሩት ሰዎች ተንኮላቸው በራሳቸው ላይ ሲመለስባቸው ዕዝራና ሌሎቹ አይሁዳውያን ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! (አስ. 9:1, 2) ዕዝራ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ያየው ነገር ወደፊት ለሚያጋጥሙት ፈተናዎች አዘጋጅቶት ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቦቹን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ይበልጥ እንዲተማመን አድርጎት መሆን አለበት። w23.11 17 አን. 12-13
ዓርብ፣ መጋቢት 21
አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ [ይቆጥራል]።—ሮም 4:6
ሐዋርያው ጳውሎስ በዋነኝነት ያተኮረው ‘በሕግ ሥራ’ ማለትም በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ ላይ ነበር። (ሮም 3:21, 28) በጳውሎስ ዘመን አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሙሴ ሕግ እንደተሻረ እንዲሁም ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው መቀበል ከብዷቸው የነበረ ይመስላል። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ የአብርሃምን ምሳሌ በመጥቀስ፣ በአምላክ ዘንድ ጻድቅ ሆኖ መቆጠር የሚቻለው “የሕግን ሥራ በመፈጸም” እንዳልሆነ ገለጸ። ከዚህ ይልቅ በእምነት ነው። ይህን ማወቃችን በጣም ያበረታታናል፤ ምክንያቱም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻል ነገር እንደሆነ ያረጋግጥልናል። ስለዚህ በአምላክና በክርስቶስ ላይ እምነት ማዳበርና በውጤቱም የይሖዋን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በያዕቆብ ምዕራፍ 2 ላይ የተጠቀሰው “ሥራ” ጳውሎስ ከጠቀሰው ‘የሕግ ሥራ’ የተለየ ነው። ያዕቆብ እየተናገረ የነበረው ክርስቲያኖች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ስለሚያከናውኑት ሥራ ነው። (ያዕ. 2:24) እንዲህ ያለው ሥራ፣ አንድ ክርስቲያን በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት ያለው መሆን አለመሆኑን ያሳያል። w23.12 3 አን. 8፤ 4-5 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ መጋቢት 22
ባልም የሚስቱ ራስ ነው።—ኤፌ. 5:23
ለማግባት የሚያስቡ እህቶች የትዳር አጋራቸውን በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርባቸዋል። ለምታገቡት ሰው የራስነት ሥልጣን መገዛት እንደሚኖርባችሁ አስታውሱ። (ሮም 7:2፤ ኤፌ. 5:33) ስለዚህ እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘የጎለመሰ ክርስቲያን ነው? በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ያስቀድማል? ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ያደርጋል? ስህተቱን አምኖ ይቀበላል? ለሴቶች አክብሮት አለው? እኔን በመንፈሳዊ፣ በቁሳዊና በስሜታዊ ለመንከባከብ የሚያስፈልጉት ክህሎቶች አሉት?’ እርግጥ ነው፣ ጥሩ ባል ማግኘት ከፈለጋችሁ ከጥሩ ሚስት የሚጠበቁትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርባችኋል። አንዲት ጥሩ ሚስት ለባሏ “ረዳት” እና “ማሟያ” ናት። (ዘፍ. 2:18) ይሖዋን ስለምትወደው ባለቤቷ በሌሎች ዘንድ አክብሮት እንዲያተርፍ ለመርዳት ጥረት ታደርጋለች። (ምሳሌ 31:11, 12፤ 1 ጢሞ. 3:11) ለዚህ ኃላፊነት መዘጋጀት የምትችሉት ለይሖዋ ያላችሁን ፍቅር በማጠናከር እንዲሁም በቤታችሁም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት በማድረግ ነው። w23.12 22-23 አን. 18-19
እሁድ፣ መጋቢት 23
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን።—ያዕ. 1:5
ይሖዋ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ጥበብ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። በተለይ ቀሪውን ሕይወታችንን የሚነኩ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ አምላካዊ ጥበብ ያስፈልገናል። ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። ይሖዋ ለሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገለት ሁሉ እኛም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም እንድንችል ኃይል ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:13) ይሖዋ እኛን ለመርዳት መንፈሳዊ ቤተሰባችንን ይጠቀማል። ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ አጥብቆ ጸልዮ ነበር። አምላክን እንደተሳደበ ተደርጎ መቆጠሩ ከሚያስከትልበት ነቀፋ እንዲታደገው ይሖዋን ለመነው። ይሖዋ፣ ኢየሱስ የጠየቀውን ነገር ከማድረግ ይልቅ አንድ መልአክ በመላክ አበረታታው። (ሉቃስ 22:42, 43) ይሖዋ እኛንም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት እንዲደውሉልን ወይም እንዲጠይቁን በማነሳሳት ሊረዳን ይችላል። ሁላችንም ለእምነት ባልንጀሮቻችን “መልካም ቃል” ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፈለግ እንችላለን።—ምሳሌ 12:25፤ w23.05 10-11 አን. 9-11
ሰኞ፣ መጋቢት 24
እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።—1 ተሰ. 5:11
በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ጥሩ አቀባበል እንደማይደረግላቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የሚያሸማቅቁ ጥያቄዎች በመጠየቅ ወይም ስሜት የሚጎዳ ነገር በመናገር አታስጨንቋቸው። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የእምነት አጋሮቻችን ናቸው። አብረውን በድጋሚ ይሖዋን እንዲያገለግሉ እንመኛለን። (መዝ. 119:176፤ ሥራ 20:35) ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በየዓመቱ እንድናከብር ማዘዙ ምን ያስገርማል? በዓሉን ስናከብር ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን በተለያዩ መንገዶች እንጠቅማለን። (ኢሳ. 48:17, 18) ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለን ፍቅር ያድጋል። ላደረጉልን ነገር ያለንን አድናቆት እናሳያለን። ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን አንድነት እናጠናክራለን። እንዲሁም ሌሎችም ቤዛው የሚያስገኛቸውን በረከቶች ማጣጣም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲማሩ መርዳት እንችል ይሆናል። እንግዲያው በዚህ ዓመት ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ቀን፣ ይኸውም ለመታሰቢያው በዓል ዝግጁ ለመሆን የቻልነውን ሁሉ እናድርግ! w24.01 14 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ መጋቢት 25
የምመራህ እኔ ይሖዋ . . . ነኝ።—ኢሳ. 48:17
ይሖዋ የሚመራን እንዴት ነው? በዋነኝነት የሚመራን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ሆኖም ይሖዋ ሰብዓዊ ወኪሎቹንም ይጠቀማል። ለምሳሌ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ተጠቅሞ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳንን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ እኛን ለመምራት፣ ብቃት ያላቸውን ሌሎች ወንዶችም ይጠቀማል። ለምሳሌ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዳ ማበረታቻና መመሪያ ይሰጡናል። በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህ መመሪያ የይሖዋ ወዳጆች ሆነን እንድንቀጥል እንዲሁም ከሕይወት መንገድ እንዳንወጣ ይረዳናል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን አመራር መከተል ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል፤ በተለይ መመሪያው የመጣው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች አማካኝነት ከሆነ ታዛዥ መሆን ይበልጥ ሊከብደን ይችላል። በተለይ እንዲህ ባሉት ጊዜያት፣ ሕዝቦቹን እየመራ ያለው ይሖዋ እንደሆነ እንዲሁም የእሱን አመራር መከተል በረከት እንደሚያስገኝ መተማመን ይኖርብናል። w24.02 20 አን. 2-3
ረቡዕ፣ መጋቢት 26
በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።—1 ዮሐ. 3:18
ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ የሚረዳን አንዱ ነገር ቃሉን በትጋት ማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ እያንዳንዱ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምርህ ለማስተዋል ሞክር። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ዘገባ ይሖዋ እንደሚወደኝ የሚጠቁመው እንዴት ነው? ይሖዋን እንድወደው የሚያነሳሳ ምን ምክንያትስ ይዟል?’ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ አዘውትረን መጸለይና ልባችንን በፊቱ ማፍሰስ ነው። (መዝ. 25:4, 5) ይህንን ስናደርግ ይሖዋም ጸሎታችንን ይመልስልናል። (1 ዮሐ. 3:21, 22) ለሌሎች ያለንም ፍቅር እያደገ መሄድ አለበት። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ክርስትናን ከተቀበለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ጢሞቴዎስ ከተባለ ግሩም ወጣት ጋር ተገናኘ። ጢሞቴዎስ ይሖዋንም ሰዎችንም ይወድ ነበር። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ [ጢሞቴዎስ] ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” ሲል ጽፏል። (ፊልጵ. 2:20) ጳውሎስን ያስደነቀው ጢሞቴዎስ ለወንድሞችና ለእህቶች ያለው ፍቅር እንደሆነ ግልጽ ነው። ጢሞቴዎስ የጎበኛቸው ጉባኤዎችም የእሱን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 4:17፤ w23.07 9 አን. 7-10
ሐሙስ፣ መጋቢት 27
በምንም ዓይነት አልጥልህም።—ዕብ. 13:5
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ ሞተ። ታዲያ ይህ ታማኝ ሰው ስለሌለ ይሖዋ ሕዝቡን መንከባከቡን አቁሟል? በፍጹም! ታማኝነታቸውን እስከጠበቁ ድረስ ይሖዋ ይንከባከባቸው ነበር። ሙሴ ከመሞቱ በፊት፣ ይሖዋ ኢያሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ እንዲሾመው አዞታል። ሙሴ ኢያሱን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት አሠልጥኖታል። (ዘፀ. 33:11፤ ዘዳ. 34:9) በተጨማሪም አመራር የሚሰጡ ብቃት ያላቸው የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች ነበሩ። (ዘዳ. 1:15) የአምላክ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ አግኝተዋል። በኤልያስ ዘመንም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞ ነበር። ኤልያስ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ግንባር ቀደም ሆኖ እስራኤላውያን በንጹሕ አምልኮ እንዲካፈሉ ይረዳቸው ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ይሖዋ በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ሌላ የአገልግሎት ምድብ ሰጠው። (2 ነገ. 2:1፤ 2 ዜና 21:12) ታዲያ አሥሩን ነገድ ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ተጥለዋል? በፍጹም! ኤልያስ ለተወሰኑ ዓመታት ኤልሳዕን ሲያሠለጥነው ቆይቷል። ይሖዋ ዓላማውን ማስፈጸሙን እንዲሁም ታማኝ አገልጋዮቹን መንከባከቡን ቀጥሏል። w24.02 5 አን. 12
ዓርብ፣ መጋቢት 28
የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:8
የኤፌሶን ክርስቲያኖች ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት የሚፈነጥቀውን ብርሃን ተቀብለዋል። (መዝ. 119:105) እነዚህ የኤፌሶን ሰዎች የሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶችንና የሥነ ምግባር ብልግናን ትተዋል። ‘አምላክን መምሰል’ ጀምረዋል፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማምለክና እሱን ለማስደሰት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነበር። (ኤፌ. 5:1) እኛም እውነትን ከመማራችን በፊት በሃይማኖታዊና በሥነ ምግባራዊ ጨለማ ውስጥ ነበርን። አንዳንዶቻችን የሐሰት ሃይማኖታዊ በዓላትን እናከብር ነበር፤ ሌሎቻችን ደግሞ ሥነ ምግባር የጎደለው የአኗኗር ዘይቤ ነበረን። ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑት ነገሮች የይሖዋን መሥፈርቶች ከተማርን በኋላ ግን ለውጥ አደረግን። በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታችንን መምራት ጀመርን። ይህም ብዙ ጥቅሞች አስገኝቶልናል። (ኢሳ. 48:17) ያም ቢሆን አሁንም ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጣችን አይቀርም። ትተነው ከመጣነው ጨለማ ለመራቅና ‘የብርሃን ልጆች ሆነን ለመመላለስ’ ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። w24.03 21 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ መጋቢት 29
ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።—ፊልጵ. 3:16
ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ እንዳልሆንክ ይሰማህ ይሆናል። ምናልባትም በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራት በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ እምነትህን ለማጠናከር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልግህ ይሆናል። (ቆላ. 2:6, 7) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት ይለያያል፤ በተጨማሪም ሁሉም ልጆች ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ የሚሆኑበት ዕድሜ አንድ ዓይነት አይደለም። ራስህን ከሌላ ሰው ጋር ሳታወዳድር መንፈሳዊ እድገትህን ከራስህ ሁኔታ አንጻር ገምግም። (ገላ. 6:4, 5) ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጁ እንዳልሆንክ ብትገነዘብም እንኳ ይህን ግብ ምንጊዜም በአእምሮህ ያዝ። አስፈላጊዎቹን ለውጦች ሁሉ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክልህ ጸልይ። (ፊልጵ. 2:13) ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማና ምላሽ እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—1 ዮሐ. 5:14፤ w24.03 5 አን. 9-10
እሁድ፣ መጋቢት 30
እናንተ ባሎች [ከሚስቶቻችሁ] ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ።—1 ጴጥ. 3:7
በአንድ ወቅት ሣራ በጭንቀት በመዋጧ ስሜቷን አውጥታ ለአብርሃም ነግራው ነበር፤ እንዲያውም ለደረሰባት ነገር እሱን ወቅሳዋለች። አብርሃም፣ ሣራ እንደምትገዛለትና እንደምትደግፈው ያውቅ ነበር። በጥሞና ያዳመጣት ከመሆኑም ሌላ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት አደረገ። (ዘፍ. 16:5, 6) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ባሎች፣ ለቤተሰባችሁ ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን እንዳላችሁ የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 11:3) ያም ቢሆን፣ ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት የትዳር ጓደኛችሁን በጥሞና ብታዳምጡና አመለካከቷን ግምት ውስጥ ብታስገቡ ፍቅር ይሆናል፤ በተለይ ውሳኔው እሷንም የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ እንዲህ ማድረጋችሁ ተገቢ ነው። (1 ቆሮ. 13:4, 5) በሌላ ወቅት ደግሞ አብርሃም ያልተጠበቁ እንግዶች ሲመጡበት እነሱን ለማስተናገድ አሰበ። በመሆኑም ሣራ የምትሠራውን ነገር ትታ በርከት ያለ ቂጣ እንድትጋግር ጠየቃት። (ዘፍ. 18:6) ሣራም አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ የአብርሃምን ውሳኔ እንደምትደግፍ አሳይታለች። ሚስቶች፣ የባሎቻችሁን ውሳኔ በመደገፍ የሣራን ምሳሌ መከተል ትችላላችሁ። እንዲህ ስታደርጉ ትዳራችሁ ይጠናከራል።—1 ጴጥ. 3:5, 6፤ w23.05 24-25 አን. 16-17
ሰኞ፣ መጋቢት 31
ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ለመታዘዝ ዝግጁ [ነው]።—ያዕ. 3:17
ጌድዮን መስፍን ሆኖ ከተሾመ በኋላ ታዛዥነቱና ድፍረቱ ተፈትኖ ነበር። የአባቱን የባአል መሠዊያ የማፈራረስ አደገኛ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። (መሳ. 6:25, 26) ሠራዊቱን ካሰባሰበ በኋላም የሠራዊቱን ቁጥር እንዲቀንስ ሁለት ጊዜ ታዟል። (መሳ. 7:2-7) በመጨረሻም፣ በውድቅት ሌሊት በጠላት ሰፈር ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ተነግሮታል። (መሳ. 7:9-11) ሽማግሌዎች “ለመታዘዝ ዝግጁ” መሆን አለባቸው። ታዛዥ የሆነ ሽማግሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትንና ከይሖዋ ድርጅት የሚሰጡትን መመሪያዎች ቶሎ ብሎ በሥራ ላይ ያውላል። በዚህ መንገድ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ያም ቢሆን ታዛዥነቱ ሊፈተን ይችላል። ለምሳሌ የሚሰጡትን መመሪያዎች ተከታትሎ ተግባራዊ ማድረግ ሊከብደው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የተሰጠው መመሪያ ምክንያታዊ ወይም የሚያስኬድ መሆኑን ሊጠራጠር ይችላል። ወይም ነፃነቱን አደጋ ላይ የሚጥል ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል። ታዲያ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የጌድዮንን ታዛዥነት መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚሰጣችሁን መመሪያ በጥሞና አዳምጡ፤ እንዲሁም በሥራ ላይ አውሉ። w23.06 4-5 አን. 9-11