ታኅሣሥ
እሁድ፣ ታኅሣሥ 1
እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?—ሥራ 8:36
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለመጠመቅ በእርግጥ ዝግጁ ነበር? እስቲ ይህን ለማሰብ ሞክር፦ ኢትዮጵያዊው ሰው “ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር።” (ሥራ 8:27) ከዚህ እንደምንረዳው ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ ሰው መሆን አለበት። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ ስለ ይሖዋ እንደተማረ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ይበልጥ የማወቅ ጉጉት አድሮበታል። እንዲያውም ፊልጶስ መንገድ ላይ ሲያገኘው ይህ ሰው የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ የያዘ ጥቅልል እያነበበ ነበር። (ሥራ 8:28) ተጨማሪ እውቀት የማግኘት ፍላጎት ነበረው። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ ሲል ከኢትዮጵያ ተነስቶ ረጅም ጉዞ አድርጓል። ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የመሲሑን ማንነት ጨምሮ አንዳንድ አስፈላጊ እውነቶችን አስተምሮታል። (ሥራ 8:34, 35) ይህ ሰው ለይሖዋና ለልጁ ያለው ፍቅር ስለጨመረ ሕይወቱን የሚቀይር ውሳኔ ለማድረግ ተነሳሳ። ተጠምቆ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የመሆን ፍላጎት አደረበት። ፊልጶስም ሰውየው ዝግጁ እንደሆነ ሲያይ አጠመቀው። w23.03 8-9 አን. 3-6
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2
ንግግራችሁ ምንጊዜም . . . ለዛ ያለው ይሁን።—ቆላ. 4:6
እውነቱን የማንናገር ከሆነ ይሖዋን ማስደሰት አንችልም። (ምሳሌ 6:16, 17) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ውሸት ምንም ችግር እንደሌለው ቢሰማቸውም እኛ ስለ ጉዳዩ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን እንፈልጋለን። (መዝ. 15:1, 2) ዓይን ያወጣ ውሸት እንደማንናገር የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሌሎች የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ የሚያደርግ ነገርም ሆን ብለን አንናገርም። ሐሜት ከማሰራጨትም ልንቆጠብ ይገባል። (ምሳሌ 25:23፤ 2 ተሰ. 3:11) ከሌሎች ጋር ስታወራ ነገሩ ወደ ሐሜት እየተቀየረ እንደሆነ ካስተዋልክ ወሬው ወደ አዎንታዊ ነገር እንዲያመራ ለማድረግ ጥረት አድርግ። የምንኖረው መጥፎ ንግግር በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም ይሖዋን የሚያስደስት አነጋገር እንዲኖረን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። በአገልግሎትና በስብሰባዎች ላይ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ስናወራ ጥሩ አነጋገር እንዲኖረን የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ይባርካል። ፈሪሃ አምላክ የሌለው ይህ ሥርዓት በቅርቡ ሲጠፋ ይሖዋን በአንደበታችን ማክበር በጣም ቀላል ይሆንልናል።—ይሁዳ 15፤ w22.04 9 አን. 18-20
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 3
እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።—1 ዮሐ. 4:19
ይሖዋና ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚወዱን ስናስብ እኛም በምላሹ እነሱን ለመውደድ እንነሳሳለን። (1 ዮሐ. 4:10) ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን እንደሞተ መገንዘባችን ደግሞ ይበልጥ እንድንወዳቸው ያደርገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ እውነታ ያለውን አድናቆት ገልጿል፤ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘የአምላክ ልጅ ወዶኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ ብሏል። (ገላ. 2:20) ይሖዋ ቤዛውን መሠረት በማድረግ ወዳጁ እንድትሆን ወደ ራሱ ስቦሃል። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ አንድ መልካም ነገር እንዳየብህና ወዳጁ እንድትሆን ሲል ከሁሉ የላቀውን ዋጋ እንደከፈለ ስታስብ ልብህ በጥልቅ አይነካም? ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለህ ፍቅርስ አይጨምርም? እንግዲያው ‘ይህ ፍቅር ምን እንዳደርግ ግድ ይለኛል?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ለአምላክና ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ለሌሎች ፍቅር እንድናሳይ ያነሳሳናል።—2 ቆሮ. 5:14, 15፤ 6:1, 2፤ w23.01 28 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 4
ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።—ሶፎ. 3:9
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሕዝቦቹ “እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት” ያለውን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይሖዋ አብዛኞቹ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች እንዲጻፉ ያደረገው ትሑት የሆኑ አንባቢዎች ብቻ እንዲረዱት በሚያስችል መንገድ ነው። (ሉቃስ 10:21) በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያነብባሉ። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ በትክክል መረዳትና ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት ትሑት የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። (2 ቆሮ. 3:15, 16) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ጥበብ ይገልጣል። ይሖዋ ቅዱሳን መጻሕፍትን እኛን በቡድን ደረጃ ለመምራት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ ለማስተማርና ለማጽናናትም ይጠቀምባቸዋል። ሁላችንም የአምላክን ቃል ስናነብ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እንደሚያስብልን እንገነዘባለን። (ኢሳ. 30:21) ቅዱሳን መጻሕፍትን ስታነብቡ ልክ ለእናንተ የተጻፈ የሚመስል ጥቅስ ያገኛችሁበት ብዙ አጋጣሚ የለም? እንደዚያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ ይነካል። ታዲያ ለእያንዳንዳችን ሁኔታ የሚሠራ ወቅታዊ መረጃ ሊይዝ የቻለው እንዴት ነው? ይህ ሊሆን የቻለው መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው በጥበቡ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አካል ስለሆነ ብቻ ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ w23.02 4-5 አን. 8-10
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 5
እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።—1 ጢሞ. 4:15
እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን በጣም እንወደዋለን። ለእሱ በምናቀርበው አገልግሎት ምርጣችንን መስጠት እንፈልጋለን። ይሁንና ለይሖዋ ምርጣችንን ለመስጠት መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ያስፈልገናል። ከእነዚህም መካከል ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን መማር እንዲሁም ሌሎችን ማገልገል የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ይገኙበታል። መንፈሳዊ እድገት የማድረግ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው? በዋነኝነት፣ አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው። ይሖዋ ተሰጥኦዎቻችንን እና ክህሎቶቻችንን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመን እሱን ስናገለግለው ይደሰታል። በተጨማሪም መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይበልጥ ለመርዳት ያስችለናል። (1 ተሰ. 4:9, 10) እውነት ቤት ውስጥ የኖርነው ለምንም ያህል ጊዜ ቢሆን ሁላችንም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንችላለን። w22.04 22 አን. 1-2
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 6
ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።—ራእይ 17:16
በቅርቡ የዓለም መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ማለትም በዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ ይነሳሉ። ይህ ክንውን የታላቁ መከራ መጀመሪያ ነው። ታዲያ ሰዎች ይህን ሲያዩ ወደ ይሖዋ አምልኮ ይጎርፉ ይሆን? በፍጹም። ከዚህ በተቃራኒ ራእይ ምዕራፍ 6 እንደሚያሳየው ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ከለላ ለማግኘት ወደዚህ ዓለም የፖለቲካና የንግድ ሥርዓት ዞር ይላሉ፤ ራእዩ ላይ እነዚህ ነገሮች በተራሮች ተመስለዋል። እነዚህ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ስለማይደግፉ ይሖዋ እንደ ተቃዋሚዎቹ ይቆጥራቸዋል። (ሉቃስ 11:23፤ ራእይ 6:15-17) የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በዚያ የመከራ ወቅት ከሌሎች ተለይተው እንደሚወጡ የታወቀ ነው። በምድር ላይ ይሖዋን የሚያገለግለውና “ለአውሬው” ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆነው ብቸኛው ቡድን የይሖዋ ሕዝብ ይሆናል።—ራእይ 13:14-17፤ w22.05 16-17 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 7
በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ ነበር።—ራእይ 14:6
የአምላክ ሕዝቦች እንዲያውጁ የተነገራቸው መልእክት “የመንግሥቱ ምሥራች” ብቻ አይደለም። (ማቴ. 24:14) በራእይ ምዕራፍ 8 እስከ 10 ላይ መላእክት እንደሚያከናውኑት የተገለጸ ሥራ አለ፤ የአምላክ ሕዝቦች ይህን ሥራም መደገፍ አለባቸው። እነዚህ መላእክት የአምላክን መንግሥት በማይቀበሉት ሁሉ ላይ ተከታታይ ወዮታዎችን አስተላልፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም ‘በበረዶና በእሳት’ የተመሰለ የፍርድ መልእክት ሲያውጁ ቆይተዋል፤ ይህ መልእክት አምላክ ክፉ በሆነው የሰይጣን ዓለም የተለያዩ ክፍሎች ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ የሚገልጽ ነው። (ራእይ 8:7, 13) ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ አድርገው ከይሖዋ የቁጣ ቀን እንዲተርፉ መጨረሻው በጣም መቅረቡን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። (ሶፎ. 2:2, 3) ሆኖም ይህ መልእክት በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ አይደለም። መልእክቱን ማወጅ ድፍረት ይጠይቅብናል። በታላቁ መከራ ወቅት የምናውጀው የመጨረሻ የፍርድ መልእክት ደግሞ ይበልጥ የሚያም ይሆናል።—ራእይ 16:21፤ w22.05 7 አን. 18-19
እሁድ፣ ታኅሣሥ 8
አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።—ማቴ. 22:37
በቅርቡ ወላጅ ስለሚሆኑ ክርስቲያን ባልና ሚስት እናስብ። እነዚህ ባልና ሚስት ለዓመታት፣ ልጆች ስለማሳደግ ብዙ ንግግሮችን አዳምጠው ሊሆን ይችላል። አሁን ግን መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለእነሱ የተለየ ትርጉም ይኖራቸዋል። ምክንያቱም ወላጅነት አሁን የእነሱም የቤት ሥራ ነው። ይህ በእርግጥም ትልቅ ኃላፊነት ነው! በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሁኔታችን ሲቀየር አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ ትርጉም ይሰጡናል። የእስራኤል ነገሥታት እንደታዘዙት ሁሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ‘በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ’ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብና በዚያ ላይ ማሰላሰል ያለባቸው ለዚህ ነው። (ዘዳ. 17:19) ወላጆች ክርስቲያኖች ከሚያገኟቸው ታላላቅ መብቶች አንዱን አግኝታችኋል፤ ይህም ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ ማስተማር ነው። ሆኖም ስለ ይሖዋ አምላክ መረጃ ከማስተላለፍ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅባችኋል። ልጆቻችሁ ይሖዋን ከልብ እንዲወዱት መርዳት ያስፈልጋችኋል። w22.05 26 አን. 2-3
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 9
አዲሱን ስብዕና ልበሱ።—ቆላ. 3:10
በፈጸምነው ኃጢአት ወይም በተከተልነው የተሳሳተ አካሄድ መጸጸታችን ብቻውን በቂ አይደለም። እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆንም ይኖርብናል። ይሖዋ ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት ሲወስን ግምት ውስጥ የሚያስገባው ወሳኝ ነገር መለወጣችን ነው። መለወጥ ማለት “መመለስ” ማለት ነው። በሌላ አባባል ግለሰቡ መጥፎ አካሄዱን መተውና የይሖዋን መንገድ መከተል ይኖርበታል። (ኢሳ. 55:7) እንዲሁም አእምሮውን ለውጦ በይሖዋ አስተሳሰብ መመራት ይኖርበታል። (ሮም 12:2፤ ኤፌ. 4:23) መጥፎ አስተሳሰቡንና ድርጊቱን ወደ ኋላ ለመተው ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለበት። (ቆላ. 3:7-9) እርግጥ ይሖዋ ይቅር እንዲለንና ከኃጢአታችን እንዲያነጻን መሠረት የሚሆነው ዋነኛው ነገር በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ ያለን እምነት ነው። ይሖዋ መጥፎ ምግባራችንን ለማስተካከል ልባዊ ጥረት እያደረግን እንዳለን ሲያይ የልጁን መሥዋዕት መሠረት አድርጎ ይቅር ይለናል።—1 ዮሐ. 1:7፤ w22.06 6 አን. 16-17
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 10
ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ።—ራእይ 2:10
ሰዎች ለበርካታ ዘመናት እርስ በርስ ሲጎዳዱ ኖረዋል። (መክ. 8:9) ለምሳሌ ባለሥልጣኖች ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ይጠቀማሉ፤ ወንጀለኞች አሰቃቂ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፤ ጉልበተኛ ተማሪዎች አብረዋቸው የሚማሩ ልጆችን ይሳደባሉ እንዲሁም ያስፈራራሉ፤ ይባስ ብሎም በቤተሰባቸው አባላት ላይ የጭካኔ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች አሉ። በእርግጥም ሰዎች ሌሎች ሰዎችን የሚፈሩ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም! ሰይጣን እኛን ለማጥቃት የሰው ፍርሃትን የሚጠቀመው እንዴት ነው? ሰይጣን የሰው ፍርሃትን ተጠቅሞ አቋማችንን እንድናላላ እና መስበካችንን እንድናቆም ሊያስገድደን ይሞክራል። አንዳንድ መንግሥታት በሰይጣን ግፊት ሥራችን ላይ እገዳ ይጥላሉ እንዲሁም ስደት ያደርሱብናል። (ሉቃስ 21:12) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተዛባ መረጃ ወይም ዓይን ያወጣ ውሸት ይናገራሉ። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ውሸቶች በማመን ሊያሾፉብን አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት ሊያደርሱብን ይችላሉ። (ማቴ. 10:36) ሰይጣን እነዚህን ዘዴዎች መጠቀሙ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም! ምክንያቱም እነዚህን ዘዴዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ተጠቅሞባቸዋል።—ሥራ 5:27, 28, 40፤ w22.06 16-17 አን. 10-11
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 11
የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን [የሚረዱ] ለዘላለም እንደ ከዋክብት ያበራሉ።—ዳን. 12:3
የጽድቅን ጎዳና ከሚከተሉት “ብዙ ሰዎች” መካከል እነማን ይገኙበታል? ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች፣ አርማጌዶንን የሚያልፉት ሰዎች እንዲሁም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚወለዱት ልጆች ይገኙበታል። በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በሙሉ ፍጹማን ይሆናሉ። አንድ ሰው ፍጹም ስለሆነ ብቻ የዘላለም ሕይወት ያገኛል ማለት እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ለምሳሌ አዳምና ሔዋን ፍጹማን ቢሆኑም እንኳ የዘላለም ሕይወት ከማግኘታቸው በፊት ለይሖዋ አምላክ ያላቸውን ታዛዥነት ማስመሥከር እንደነበረባቸው አስታውሱ። የሚያሳዝነው ደግሞ ይሖዋን ሳይታዘዙ ቀርተዋል። (ሮም 5:12) በ1,000 ዓመቱ መጨረሻ ላይ ሁሉም ፍጽምና ደረጃ ላይ ስለሚደርሱ እነዚህ ፍጹማን ሰዎች ለዘላለም የይሖዋን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ? ወይስ እንደ አዳምና እንደ ሔዋን ፍጹማን ቢሆኑም እንኳ ታማኝነታቸውን ያጓድላሉ? እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል። w22.09 22-23 አን. 12-14
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 12
የዓለም መንግሥት የጌታችንና የእሱ መሲሕ መንግሥት ሆነ።—ራእይ 11:15
የዓለምን ሁኔታ ስትመለከቱ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከባድ ይሆንባችኋል? ቤተሰቦች እየፈራረሱ ነው። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሰዎች ዓመፀኛ፣ ራስ ወዳድና ቁጡ ሆነዋል። ብዙዎች በባለሥልጣናት ላይ ያላቸውን እምነት አጥተዋል። ሆኖም እነዚህ ነገሮች በዓለም ላይ መታየታቸው እምነታችንን ያጠናክርልናል። ለምን? ምክንያቱም የሰዎቹ ምግባር ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” የሚናገረው አስደናቂ ትንቢት ፍጻሜ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) የትኛውም ሐቀኛ ሰው ይህ ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ሊክድ አይችልም። ይህ ትንቢት መፈጸሙ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረ ያረጋግጣል። ሆኖም ይህ ትንቢት ስለ መንግሥቱ ከሚናገሩት በርካታ ትንቢቶች አንዱ ብቻ ነው። እነዚህ ትንቢቶች እንደ ተገጣጣሚ ሥዕል ናቸው፤ አንድ ላይ ሆነው ሲታዩ በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ የት ቦታ ላይ እንደምንገኝ ግልጽ ምስል ይሰጡናል። w22.07 2 አን. 1-2
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13
ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል።—ማቴ. 11:19
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የጉባኤ ስብሰባዎች ማድረግና በስብከቱ ሥራ መካፈል ስለምንችልበት መንገድ ግልጽ መመሪያ አግኝተናል። ወዲያውኑ የጉባኤ፣ የወረዳና የክልል ስብሰባዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ማድረግ ጀመርን። በተጨማሪም አገልግሎታችንን በዋነኝነት በደብዳቤና በስልክ አማካኝነት ማከናወን ጀመርን። ይሖዋም ጥረታችንን ባርኮልናል። በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የአስፋፊዎች ቁጥር በእጅጉ እንደጨመረ ሪፖርት አድርገዋል። እንዲያውም ብዙ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ወቅት አበረታች ተሞክሮዎችን አግኝተዋል። አንዳንዶች ድርጅቱ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም የተሰጠን መመሪያ ጥበብ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። ኢየሱስ ሕዝቡን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እየመራ ያለው እንዴት እንደሆነ ስናሰላስል፣ ነገ ምንም ነገር ቢመጣ ይሖዋና የሚወደው ልጁ አብረውን እንደሚሆኑ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ዕብ. 13:5, 6፤ w22.07 13 አን. 15-16
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 14
ዘወትር ጸልዩ። ለሁሉም ነገር አመስግኑ። አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ያለው ፈቃድ ይህ ነው።—1 ተሰ. 5:17, 18
በምንጸልይበት ወቅት ይሖዋን ከማወደስ በተጨማሪ ለሰጠን ግሩም ነገሮች እሱን ለማመስገንም እንነሳሳለን። ለምሳሌ በቀለማት ላሸበረቁት አበቦች፣ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ጣፋጭ ምግቦች እንዲሁም ከጓደኞቻችን ጋር ጊዜ በማሳለፍ ለምናገኘው ደስታ ልናመሰግነው እንችላለን። የሚወደን አባታችን እነዚህንና ሌሎችም ነገሮችን የሰጠን ደስተኛ እንድንሆን ስለሚፈልግ ነው። (መዝ. 104:12-15, 24) ከዚህ ይበልጥ ደግሞ ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ስለሚያቀርብልን እንዲሁም ለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባል። ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ቢያደርግልንም እሱን ማመስገን ልንረሳ እንችላለን። ታዲያ ለማስታወስ ምን ሊረዳን ይችላል? በጸሎት የጠየቅናቸውን የተለያዩ ነገሮች ዘርዝረን ከጻፍን በኋላ ይሖዋ እንዴት እንደመለሰልን ለማየት አልፎ አልፎ ዝርዝሩን መመልከት እንችላለን። ከዚያም ላደረገልን ነገር ይሖዋን በጸሎት እናመስግነው።—ቆላ. 3:15፤ w22.07 22 አን. 8-9
እሁድ፣ ታኅሣሥ 15
በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል።—መዝ. 1:2
እርግጥ ነው፣ እውነትን ማጥናታችን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ እናውቃለን። የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በእውነት ውስጥ መመላለስ፣ ማለትም የተማርነውን ነገር በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልገናል። እውነት እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (ያዕ. 1:25) በእውነት ውስጥ እየተመላለስን መሆኑን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ወንድም፣ ራሳችንን በሐቀኝነት በመመርመር በየትኞቹ አቅጣጫዎች ጥሩ እየሠራን እንደሆነ፣ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ደግሞ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን መገምገም እንደምንችል ሐሳብ ሰጥቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።” (ፊልጵ. 3:16) ‘በእውነት ውስጥ ለመመላለስ’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እስቲ ለማሰብ ሞክር! ሕይወታችን ይሻሻላል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን የደስታ ምንጭ እንሆናለን። (ምሳሌ 27:11፤ 3 ዮሐ. 4) እውነትን ለመውደድና በእውነት ውስጥ ለመመላለስ የሚያነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? w22.08 18-19 አን. 16-18
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 16
የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ።—1 ጴጥ. 5:2
ሽማግሌዎች ይሖዋንና ኢየሱስን እንደሚወዱ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ ወሳኝ መንገድ የኢየሱስን በጎች መንከባከብ ነው። (1 ጴጥ. 5:1, 2) ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን በግልጽ ነግሮታል። ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ከካደው በኋላ ለጌታው ፍቅር እንዳለው ማሳየት የሚችልበት አጋጣሚ ለማግኘት ጓጉቶ መሆን አለበት። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ጴጥሮስን “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ትወደኛለህ?” ብሎ ጠየቀው። በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ለጌታው ያለውን ፍቅር ለማሳየት ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስም ጴጥሮስን “ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው። (ዮሐ. 21:15-17) ደግሞም ጴጥሮስ በቀሪ ሕይወቱ ሁሉ የጌታውን በጎች በመንከባከብ ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። እናንት ሽማግሌዎች፣ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ለተናገረው ሐሳብ ትኩረት እንደምትሰጡ ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? በእረኝነቱ ሥራ አዘውትራችሁ በመካፈልና የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት ልዩ ጥረት በማድረግ ይሖዋንና ኢየሱስን ምን ያህል እንደምትወዷቸው ማሳየት ትችላላችሁ።—ሕዝ. 34:11, 12፤ w23.01 29 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 17
አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም።—1 ቆሮ. 10:13
‘እያጋጠመኝ ያለውን ፈተና ማንም ሰው ሊረዳው አይችልም’ ብለህ ከማሰብ ተቆጠብ። እንደዚህ ብለህ ማሰብህ ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ እንዲሁም መጥፎ ምኞቶችህን ማሸነፍ እንደማትችል እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ ይዟል። እንዲህ ይላል፦ “ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ ያደረብን መጥፎ ምኞት በቀላሉ የማይጠፋ ቢሆንም እንኳ በጽናት ልንቋቋመው እንችላለን። በይሖዋ እርዳታ፣ ይህን ምኞት ከመፈጸም መታቀብ እንችላለን። ምንጊዜም ይህን አስታውስ፦ ፍጹማን ስላልሆንን መጥፎ ምኞቶች ጨርሶ እንዳይፈጠሩብን ማድረግ አንችል ይሆናል። ሆኖም ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት በፍጥነት እንደሸሸ ሁሉ እኛም መጥፎ ምኞቶች ሲፈጠሩብን እነሱን ለማስወገድ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንችላለን። (ዘፍ. 39:12) መጥፎ ምኞቶች ቢፈጠሩብንም ምኞቶቹን ላለመፈጸም መምረጥ እንችላለን! w23.01 12-13 አን. 16-17
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18
በአምላክ ዘንድ አድልዎ የለም።—ሮም 2:11
ፍትሕ አንዱ የይሖዋ ባሕርይ ነው። (ዘዳ. 32:4) ፍትሕ ከአድልዎ ነፃ ከመሆን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፤ ይሖዋ ደግሞ ከአድልዎ ነፃ ነው። (ሥራ 10:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች ይሖዋ የማያዳላ መሆኑን ያሳያሉ። ይሖዋ በፍጻሜው ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ‘እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ ቃል ገብቷል። ብዙዎች ይህን እውነት ይረዱታል። (ዳን. 12:4) የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲበዛ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ነገር መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በስፋት መተርጎማቸው፣ መዘጋጀታቸውና መሰራጨታቸው ነው። የይሖዋ ሕዝቦች እስካሁን ድረስ የአምላክን ቃል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከ240 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተርጉመዋል፤ ማንም ሰው እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሶች በነፃ ማግኘት ይችላል። ይህም በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ የሚሰሙበት አጋጣሚ ፈጥሯል። (ማቴ. 24:14) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ቃሉን በማንበብ እሱን የሚያውቁበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ምክንያቱም ሁላችንንም በጣም ይወደናል። w23.02 5 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19
ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ . . . አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2
ጽድቅን ትወዳለህ? እንደምትወድ ጥያቄ የለውም። ሆኖም ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም። በመሆኑም ካልተጠነቀቅን ዓለም ለጽድቅ ያለው አመለካከት በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። (ኢሳ. 5:20) ብዙዎች ‘ጻድቅ ሰው’ ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ኩሩ፣ ተቺና ተመጻዳቂ ሰው ነው። ሆኖም አምላክ እነዚህን ባሕርያት ፈጽሞ አይወዳቸውም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የራሳቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች በማውጣታቸው አጥብቆ አውግዟቸዋል። (መክ. 7:16፤ ሉቃስ 16:15) እውነተኛ ጽድቅ ራስን ከማመጻደቅ ፈጽሞ የተለየ ነው። ጽድቅ ማራኪ ባሕርይ ነው። በአጭር አነጋገር ጽድቅ ማለት በይሖዋ አምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽድቅ” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት ከሁሉ በላቁት የይሖዋ መሥፈርቶች መመራትን ያመለክታሉ። w22.08 27 አን. 3-5
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 20
ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።—ዮሐ. 15:15
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስህተት ቢሠሩም እንኳ ይተማመንባቸው ነበር። (ዮሐ. 15:16) ያዕቆብና ዮሐንስ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ልዩ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን በጠየቁበት ወቅት ኢየሱስ ይሖዋን የሚያገለግሉበትን ዓላማ አልተጠራጠረም፤ ወይም ከሐዋርያነት አልሻራቸውም። (ማር. 10:35-40) በኋላም ኢየሱስ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ምሽት ላይ ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ጥለውት ሸሽተዋል። (ማቴ. 26:56) ያም ቢሆን ኢየሱስ በእነሱ ላይ ያለውን እምነት አላጣም። ድክመቶቻቸውን በደንብ ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ‘እስከ መጨረሻው ወዷቸዋል።’ (ዮሐ. 13:1) እንዲያውም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የመምራትና ውድ በጎቹን የመንከባከብ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ዮሐ. 21:15-17) ኢየሱስ በእነዚህ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች መተማመኑ ተገቢ መሆኑ ታይቷል። ሁሉም እስከ ሕይወታቸው ማብቂያ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። በእርግጥም ኢየሱስ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በማመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። w22.09 6 አን. 12
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 21
ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም።—መዝ. 118:6
ይሖዋ እንደሚወደንና ከጎናችን እንደሆነ ከተማመንን ሰይጣን ሊያስፈራን አይችልም። ለምሳሌ የመዝሙር 118 ጸሐፊ በጣም የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ብዙ ጠላቶች ነበሩት፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው (ቁጥር 9, 10)። ከባድ ጫና የደረሰበት ጊዜም ነበር (ቁጥር 13)። በተጨማሪም ይሖዋ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጥቶታል (ቁጥር 18)። ያም ቢሆን መዝሙራዊው “አልፈራም” ብሎ ለመዘመር ተነሳስቷል። ይሖዋ ተግሣጽ ቢሰጠውም እንደሚወደው ያውቅ ነበር። መዝሙራዊው ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመው አፍቃሪ የሆነው አምላኩ እሱን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። (መዝ. 118:29) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደን ልንተማመን ይገባል። ይህን ማመናችን ሦስት የተለመዱ የፍርሃት ዓይነቶችን እንድናሸንፍ ይረዳናል፦ (1) ‘ቤተሰቤን ማስተዳደር ቢያቅተኝስ’ የሚል ፍርሃት፣ (2) ሰውን መፍራት እንዲሁም (3) ሞትን መፍራት። w22.06 15 አን. 3-4
እሁድ፣ ታኅሣሥ 22
ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ . . . የሕይወት አክሊል ይቀበላል።—ያዕ. 1:12
በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን አምልኮ ልናስቀድም ይገባል። ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን አምልኳችን ይገባዋል። (ራእይ 4:11፤ 14:6, 7) በመሆኑም እሱ በሚፈልገው መንገድ ማለትም “በመንፈስና በእውነት” እሱን ለማምለክ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል። (ዮሐ. 4:23, 24) በቃሉ ውስጥ ከሚገኙት እውነቶች ጋር በሚስማማ መንገድ አምልኮ ማቅረብ እንድንችል በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመራት ይኖርብናል። የምንኖረው በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ በተጣለበት አገር ውስጥ ቢሆንም እንኳ ለአምልኳችን ቅድሚያ መስጠት አለብን። በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ምክንያት ብቻ የታሰሩ ከ100 በላይ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ያም ቢሆን ለመጸለይ፣ ለማጥናት እንዲሁም ስለ አምላካችንና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች ለመናገር አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በደስታ ያደርጋሉ። ነቀፋ ወይም ስደት ሲደርስብን ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነና ወሮታ እንደሚከፍለን ማወቃችን ያስደስተናል።—1 ጴጥ. 4:14፤ w22.10 9 አን. 13
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 23
ጥበብ . . . ጥበቃ ታስገኛለች።—መክ. 7:12
ይሖዋ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ጊዜ የማይሽራቸውን ምክሮች ሰጥቶናል፤ እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ካዋልን ሕይወታችን ይሻሻላል። እንዲህ ካሉት ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ምክሮች መካከል ሁለቱን ብቻ ተመልከት። የመጀመሪያው ባለን ነገር ረክተን ስለመኖር ነው። ምሳሌ 23:4, 5 እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል፦ “ሀብት ለማግኘት አትልፋ። . . . የንስር ዓይነት ክንፎች አውጥቶ ወደ ሰማይ ይበርራልና።” ያም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች፣ ሀብት የማካበት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ይህም መልካም ስማቸውን፣ ከሌሎች ጋር ያላቸውን ዝምድና አልፎ ተርፎም ጤንነታቸውን የሚጎዳ ነገር እንዲያደርጉ ምክንያት ይሆናል። (ምሳሌ 28:20፤ 1 ጢሞ. 6:9, 10) ሁለተኛው ከመናገራችን በፊት ስለማሰብ ነው። ካልተጠነቀቅን በንግግራችን ከፍተኛ ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። ምሳሌ 12:18 “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው” ይላል። ሌሎች ስላለባቸው ድክመት ሐሜት ከማውራት የምንቆጠብ ከሆነ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።—ምሳሌ 20:19፤ w22.10 21 አን. 14፤ 22 አን. 16-17
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 24
ይህን ጥቅልል ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር።—ሕዝ. 3:1
ሕዝቅኤል የሚያውጀው መልእክት ሙሉ በሙሉ ሊዋሃደው ይገባል። ለመስበክ እንዲነሳሳ በመልእክቱ ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረው ይገባ ነበር። ከዚያም አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጠረ። ሕዝቅኤል ጥቅልሉ ‘እንደ ማር ጣፈጠው።’ (ሕዝ. 3:3) ለምን? ለሕዝቅኤል ይሖዋን የመወከል መብት ጣፋጭ ወይም አስደሳች ነገር ነበር። (መዝ. 19:8-11) ይሖዋ ነቢይ አድርጎ ስለሾመው አመስጋኝ ነበር። በኋላ ላይ ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የምነግርህን ቃል ሁሉ በልብህ ያዝ፤ ደግሞም አዳምጥ” አለው። (ሕዝ. 3:10) ይሖዋ ይህን መመሪያ የሰጠው ሕዝቅኤል በጥቅልሉ ውስጥ የተጻፈውን ሐሳብ እንዲያስታውስና እንዲያሰላስልበት ነው። ሕዝቅኤል እንዲህ ማድረጉ እንደ ምግብ ብርታት ሰጥቶታል። በተጨማሪም ለሕዝቡ የሚያውጀው ወሳኝ መልእክት በጥቅልሉ ውስጥ አግኝቷል። (ሕዝ. 3:11) የአምላክ መልእክት በልቡና በአንደበቱ ላይ ስለነበር ሕዝቅኤል የተሰጠውን ተልእኮ ለመጀመርና ለመፈጸም ዝግጁ ሆነ። w22.11 6 አን. 12-14
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25
መታዘዝ ከመሥዋዕት . . . ይበልጣል።—1 ሳሙ. 15:22
ድርጅታዊ ማስተካከያዎች ታማኝነትህን ከፈተኑት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ድርጅታዊ ማስተካከያዎችን ሙሉ በሙሉ ደግፍ። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በሚጓዙበት ወቅት ቀአታውያን በሕዝቡ ሁሉ ፊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ነበር። (ዘኁ. 3:29, 31፤ 10:33፤ ኢያሱ 3:2-4) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ሆኖም እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ሁኔታው ተቀየረ። አሁን ታቦቱ ከቦታ ቦታ መጓጓዝ አያስፈልገውም። በመሆኑም ቀአታውያን ሌሎች ሥራዎች ተሰጧቸው። (1 ዜና 6:31-33፤ 26:1, 24) ቀአታውያን ቅሬታ እንዳሰሙ ወይም ደግሞ ቀደም ሲል ከነበራቸው ልዩ መብት አንጻር ትልቅ ቦታ ያለው ሥራ እንዲሰጣቸው እንደጠየቁ የሚገልጽ አንድም ዘገባ አናገኝም። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የአንተን የአገልግሎት ምድብ በቀጥታ የሚነካ ቢሆንም እንኳ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚደረጉትን ማስተካከያዎች በሙሉ በታማኝነት ደግፍ። ከሚሰጥህ ከየትኛውም የአገልግሎት ምድብ ደስታ ለማግኘት ሞክር። ዋጋማነትህ የሚለካው በአገልግሎት ምድብህ እንዳልሆነ አትዘንጋ። ይሖዋ ከየትኛውም የአገልግሎት ምድብ በላይ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ታዛዥነትህን ነው። w22.11 23 አን. 10-11
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 26
በታሰርኩበት ሰንሰለትም አላፈረም።—2 ጢሞ. 1:16
ኦኔሲፎሮስ ሐዋርያው ጳውሎስን አፈላልጎ አገኘው፤ ከዚያም ተግባራዊ እርዳታ ሰጠው። ኦኔሲፎሮስ ይህን ያደረገው የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ ነው። እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የሰው ፍርሃት እንዲያሽመደምደን ወይም ስደት የሚደርስባቸውን ወንድሞች ከመደገፍ ወደኋላ እንድንል እንዲያደርገን መፍቀድ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ለእነሱ ጥብቅና ልንቆምና ልንረዳቸው ይገባል። (ምሳሌ 17:17) እነዚህ ወንድሞች ፍቅራችንና እርዳታችን ያስፈልጋቸዋል። በሩሲያ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚታሰሩበት ጊዜ እንዴት እንደረዷቸው ለማሰብ ሞክሩ። አንዳንዶች ችሎት ፊት ሲቀርቡ ብዙ ወንድሞችና እህቶች እነሱን ለመደገፍ ወደ ፍርድ ቤት ይመጣሉ። ከእነሱ ምሳሌ ምን እንማራለን? ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ስማቸው ሲጠፋ፣ ሲታሰሩ ወይም ስደት ሲደርስባቸው አትሸበሩ። ጸልዩላቸው፤ ቤተሰቦቻቸውን ተንከባከቡላቸው፤ እንዲሁም በሌሎች ተግባራዊ መንገዶች እነሱን ለመርዳት ሞክሩ።—ሥራ 12:5፤ 2 ቆሮ. 1:10, 11፤ w22.11 17 አን. 11-12
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 27
የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።—ቆላ. 4:11
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከሚያከናውኑት ሥራ መካከል መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ መስጠት ይገኝበታል። (1 ጴጥ. 5:2) አደጋ በሚከሰትበት ወቅት፣ ሽማግሌዎች በመጀመሪያ እያንዳንዱ አስፋፊ ደህና መሆኑን እንዲሁም ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማግኘቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሆኖም አደጋው የደረሰባቸው ክርስቲያኖች፣ አደጋው ከተከሰተ በኋላ ባሉት በርካታ ወራት ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (ዮሐ. 21:15) በቅርንጫፍ ኮሚቴ አባልነት የሚያገለግለውና በአደጋ ከተጎዱ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር የተገናኘው ሃሮልድ እንዲህ ብሏል፦ “ከአደጋው ለማገገም ጊዜ ይወስዳል። ሕይወታቸው ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው እየተመለሰ ቢመጣም እንኳ በሞት ያጡትን ወዳጅ ዘመዳቸውን፣ በጣም የሚወዱትን ዕቃ ወይም ከአደጋው ለጥቂት ያመለጡበትን ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሊያስታውሱ ይችላሉ። እነዚህ ትዝታዎች ደግሞ እንደ አዲስ ሐዘናቸውን ሊቀሰቅሱባቸው ይችላሉ። እንዲህ ያለው ስሜት እምነት እንደጎደላቸው የሚያሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ማንኛውም ሰው ሊሰማው የሚችለው ተፈጥሯዊ ስሜት ነው።” ሽማግሌዎች “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ።—ሮም 12:15፤ w22.12 22 አን. 1፤ 24-25 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 28
በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ . . . እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።—ገላ. 5:16
ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ስንታገል እኛን ለመርዳት ቅዱስ መንፈሱን አትረፍርፎ ይሰጠናል። የአምላክን ቃል ስናጠና መንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ እንዲያደርግብን እንፈቅዳለን። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝም መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን። በእነዚህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደ እኛው ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከሚጥሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ያበረታታናል። (ዕብ. 10:24, 25፤ 13:7) በተጨማሪም ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ አንድን ድክመት ለማሸነፍ እንዲረዳን ስንጠይቀው ከዚያ ድክመት ጋር መታገላችንን ለመቀጠል የሚያስችለንን ኃይል በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይሰጠናል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካፈላችን መጥፎ ምኞቶቻችን እንዲወገዱ ላያደርግ ቢችልም እንኳ እነዚህን ምኞቶች እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ስሜት ለመቋቋም ይረዳናል። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የመካፈል ጥሩ ልማድ ካዳበርን በኋላ ይህን ልማድ ይዘን መቀጠላችን እንዲሁም ጥሩ ምኞቶችን ለማዳበር ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። w23.01 11 አን. 13-14
እሁድ፣ ታኅሣሥ 29
ለምንም ነገር ተገዢ መሆን አልሻም።—1 ቆሮ. 6:12
ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ጤንነትን ለመንከባከብ ወይም የአመጋገብ መመሪያ ለመስጠት የተጻፈ መጽሐፍ ባይሆንም ይሖዋ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ይሖዋ ‘ጎጂ ነገሮችን ከሰውነታችን እንድናርቅ’ አሳስቦናል። (መክ. 11:10) መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ እንደ መብላትና እንደ መጠጣት ያሉ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ልማዶችን ያወግዛል። (ምሳሌ 23:20) ይሖዋ የምንበላውንና የምንጠጣውን ነገር መጠን ስንወስን ራሳችንን እንድንገዛ ይጠብቅብናል። (1 ቆሮ. 9:25) አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት እንዳለን የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የማመዛዘን ችሎታችንን ልንጠቀም ይገባል። (መዝ. 119:99, 100፤ ምሳሌ 2:11) ለምሳሌ የምንበላቸውን ምግቦች ስንመርጥ የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። አንድ የምንወደው ምግብ እንደሚያሳምመን የምናውቅ ከሆነ ያን ምግብ ከመብላት እንቆጠባለን። በቂ እንቅልፍ ማግኘታችን፣ አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋችን፣ የግል ንጽሕናችንን መጠበቃችንና ቤታችንን ማጽዳታችንም ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለን ያሳያል። w23.02 21 አን. 6-7
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30
ምን ትረዳለህ?—ሉቃስ 10:26
መጽሐፍ ቅዱስን በምታነቡበት ጊዜ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:16, 17 ምን እንደሚል ልብ በሉ። ጥቅሱ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ” ለሚከተሉት ነገሮች ‘እንደሚጠቅሙ’ ይናገራል፦ (1) ለማስተማር፣ (2) ለመውቀስ፣ (3) ነገሮችን ለማቅናትና (4) ለመገሠጽ። ብዙ ጊዜ ከማትጠቀሙባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትም እንኳ እነዚህን አራት ጥቅሞች ማግኘት ትችላላችሁ። ዘገባው ስለ ይሖዋ፣ ስለ ዓላማዎቹ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን እንደሚያስተምራችሁ ለማጤን ሞክሩ። ለመውቀስ የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ አስቡ። ይህን ማድረግ የምትችሉት ጥቅሶቹ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን ወይም አመለካከቶችን ለመለየትና ለማስወገድ እንዲሁም በታማኝነት ለመጽናት የሚረዷችሁ እንዴት እንደሆነ በማስተዋል ነው። ዘገባውን ነገሮችን ለማቅናት ወይም የተሳሳተ አመለካከትን ለማስተካከል እንዴት ልትጠቀሙበት እንደምትችሉ አስቡ፤ ምናልባትም አገልግሎት ላይ የምታገኟቸው ሰዎች ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ልታስቡ ትችላላችሁ። በተጨማሪም በጥቅሶቹ ውስጥ ራሳችሁን ለመገሠጽና የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለማንጸባረቅ የሚረዳችሁ ነጥብ እንዳለ ለማስተዋል ሞክሩ። እነዚህን አራት ጥቅሞች በአእምሯችሁ ከያዛችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ታገኛላችሁ። w23.02 11 አን. 11
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 31
መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።—ዳን. 7:14
በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ትንቢት ኢየሱስ መንግሥቱን የሚቀበለው “ሰባት ዘመናት” ተብሎ በተጠራው ጊዜ ማብቂያ ላይ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ አስደሳች ክንውን መቼ እንደተከሰተ ማወቅ ይቻላል? (ዳን. 4:10-17) ‘ሰባቱ ዘመናት’ 2,520 ዓመታትን ያመለክታሉ። ይህ ጊዜ የጀመረው በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የይሖዋ ዙፋን ላይ የመጨረሻውን ንጉሥ ባስወገዱበት ወቅት ነው። ያበቃው ደግሞ በ1914 ዓ.ም. ይሖዋ “ሕጋዊ መብት” ያለውን ኢየሱስን የአምላክ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ዙፋን ላይ ባስቀመጠበት ወቅት ነው። (ሕዝ. 21:25-27) ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት ነው? ስለ ‘ሰባቱ ዘመናት’ የሚገልጸውን ትንቢት መረዳታችን ይሖዋ የገባውን ቃል ልክ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚፈጽም ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ይሖዋ መንግሥቱ የሚቋቋምበትን ቀን እንደቆረጠ ሁሉ ሌሎቹ ትንቢቶች በሙሉ በእሱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲፈጸሙ ያደርጋል። አዎ፣ የይሖዋ ቀን “አይዘገይም!”—ዕን. 2:3፤ w22.07 2-3 አን. 3-5