የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es21 ገጽ 57-67
  • ሰኔ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰኔ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 1
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 2
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 3
  • ዓርብ፣ ሰኔ 4
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 5
  • እሁድ፣ ሰኔ 6
  • ሰኞ፣ ሰኔ 7
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 8
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 9
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 10
  • ዓርብ፣ ሰኔ 11
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 12
  • እሁድ፣ ሰኔ 13
  • ሰኞ፣ ሰኔ 14
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 15
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 16
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 17
  • ዓርብ፣ ሰኔ 18
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 19
  • እሁድ፣ ሰኔ 20
  • ሰኞ፣ ሰኔ 21
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 22
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 23
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 24
  • ዓርብ፣ ሰኔ 25
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 26
  • እሁድ፣ ሰኔ 27
  • ሰኞ፣ ሰኔ 28
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 29
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
es21 ገጽ 57-67

ሰኔ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 1

ጣውንቷ እሷን ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር።—1 ሳሙ. 1:6

የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመዋት ነበር። ለበርካታ ዓመታት መሃን ሆና ቆይታለች። (1 ሳሙ. 1:2) በእስራኤላውያን ባሕል ደግሞ መሃን የሆነች ሴት እንደተረገመች ተደርጋ ትቆጠር ነበር። ይህም ሐናን እንድትሸማቀቅ አድርጓት ነበር። (ዘፍ. 30:1, 2) በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሐና ባል፣ ፍናና የምትባል ሌላ ሚስት የነበረችው ሲሆን እሷም ልጆች ወልዳለት ነበር። ፍናና በሐና ላይ ትሳለቅባት ነበር። መጀመሪያ ላይ ሐና እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም ከብዷት ነበር። በጣም ከመረበሿ የተነሳ “እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት” ድረስ ታዝን ነበር። ሐና “በጣም ተማርራ ነበር።” (1 ሳሙ. 1:7, 10) ታዲያ ሐና መጽናኛ ያገኘችው እንዴት ነው? ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ በጸሎት ነገረችው። ከጸለየች በኋላም ስላለችበት ሁኔታ ለሊቀ ካህናቱ ለኤሊ አስረዳችው። ኤሊም “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ነገር ይስጥሽ” አላት። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሐና “ተነስታ ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።” (1 ሳሙ. 1:17, 18) ሐና መጸለይዋ ሰላሟ እንዲመለስላት ረድቷታል። w20.02 21 አን. 4-5

ረቡዕ፣ ሰኔ 2

ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።—ቆላ. 4:6

በቅርቡ ይሖዋ ይህን ሥርዓት ያጠፋዋል። ከጥፋቱ መትረፍ የሚችሉት “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ብቻ ናቸው። (ሥራ 13:48) ከዚህ አንጻር የቤተሰባችን አባላትም አብረውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ስንል ለእነሱ ለመመሥከር ጥረት ማድረጋችን የተገባ ነው። አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።” (2 ጴጥ. 3:9) የመዳንን መልእክት የምንናገርበት መንገድ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ለማናውቀው ሰው ስንመሠክር ዘዴኛ ለመሆን ጥረት እናደርጋለን፤ ለቤተሰባችን አባላት ስንመሠክር ግን ለስሜታቸው ያን ያህል አንጠነቀቅ ይሆናል። ብዙዎቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቤተሰባችን አባላት ለመመሥከር ያደረግነውን ጥረት ስናስታውስ ‘ምነው እንዲህ ባደረግሁ’ ብለን እንቆጭ ይሆናል። ለቤተሰባችን አባላት በምንመሠክርበት ወቅት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ማስታወሳችን በጣም ጠቃሚ ነው። ካልሆነ እነሱን ከማሳመን ይልቅ ከእውነት እንዲርቁ ልናደርጋቸው እንችላለን። w19.08 14-15 አን. 3-5

ሐሙስ፣ ሰኔ 3

ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ [ትቶላችኋል]።—1 ጴጥ. 2:21

ወልድን በተመለከተ የሚከተሉትን እውነቶች ስትማር ምን ተሰምቶህ ነበር? በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ሁለተኛውን ቦታ የያዘው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ቤዛችን ነው። በፈቃደኝነት ሕይወቱን ለእኛ ሲል አሳልፎ ሰጥቷል። በቤዛው ላይ እምነት እንዳለን በተግባር የምናሳይ ከሆነ የኃጢአት ይቅርታ፣ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት መብት እንዲሁም የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን ነው። ከቤዛው ጥቅም እንድናገኝና ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት ሊረዳን ይፈልጋል። (ዕብ. 4:15፤ 7:24, 25) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ስሙን የሚያስቀድሰው፣ ክፋትን የሚያጠፋው እንዲሁም ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ ዘላለማዊ በረከቶችን የሚያመጣው በእሱ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 6:9, 10፤ ራእይ 11:15) ኢየሱስ አርዓያችን ነው። በሕይወቱ ውስጥ የአምላክን ፈቃድ በማስቀደም ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐ. 4:34) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የሚያስተምረውን እውነት አምነህ ስትቀበል ለአምላክ ውድ ልጅ ፍቅር ይኖርሃል። ይህ ፍቅር የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ እንድታስቀድም ያነሳሳሃል። w20.03 10 አን. 12-13

ዓርብ፣ ሰኔ 4

ዘወትር ጸልዩ።—1 ተሰ. 5:17

ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ባጠናቀቀበት የመጨረሻ ቀን ላይ በተደጋጋሚ ጸልዮአል። የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ወቅት ለቂጣውና ለወይን ጠጁ ጸልዮአል። (1 ቆሮ. 11:23-25) የፋሲካን በዓል ካከበሩበት ቤት ከመውጣቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጸልዮአል። (ዮሐ. 17:1-26) ማታ ላይ እሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ከሄዱ በኋላ በተደጋጋሚ ጸልዮአል። (ማቴ. 26:36-39, 42, 44) ልክ ከመሞቱ በፊት የተናገረው ሐሳብ ራሱ ጸሎት ነበር። (ሉቃስ 23:46) ኢየሱስ በዚያን ዕለት ከተከናወነው ከእያንዳንዱ ወሳኝ ክንውን ጋር በተያያዘ ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ኢየሱስ የደረሰበትን ፈተና በጽናት መወጣት የቻለበት አንዱ ምክንያት በተደጋጋሚ ወደ አባቱ በመጸለይ የእሱን እርዳታ ይጠይቅ ስለነበር ነው። በሌላ በኩል ግን ሐዋርያቱ በዚያ ምሽት በጸሎት ሳይጸኑ ቀርተዋል። በመሆኑም የደረሰባቸውን ፈተና በድፍረት መወጣት አልቻሉም። (ማቴ. 26:40, 41, 43, 45, 56) እኛም ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ታማኝ ሆነን መቀጠል የምንችለው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ‘ሳናሰልስ ከጸለይን’ ብቻ ነው። w19.04 9 አን. 4-5

ቅዳሜ፣ ሰኔ 5

እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም።—ሚል. 3:6

ይሖዋ መናፍስታዊ ድርጊቶችን አጥብቆ ይጠላል! እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፣ ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።” (ዘዳ. 18:10-12) ክርስቲያኖች ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕጎች እንዲከተሉ አይጠበቅባቸውም። ያም ቢሆን ይሖዋ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ያለው አመለካከት እንዳልተቀየረ እናውቃለን። ይሖዋ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ ያስጠነቀቀን፣ ሰይጣን በዚህ ዘዴ አማካኝነት ሰዎችን ለመጉዳት እንደሚሞክር ስለሚያውቅ ነው። ሰይጣን በመናፍስታዊ ድርጊቶች ተጠቅሞ፣ ‘የሞቱ ሰዎች በሌላ ዓለም ይኖራሉ’ እንደሚሉት ያሉ ውሸቶችን ያስፋፋል። (መክ. 9:5) በተጨማሪም ሰዎች በፍርሃት እንዲዋጡና ከይሖዋ እንዲርቁ ለማድረግ ይሞክራል። ዓላማው በእነዚህ ድርጊቶች የሚካፈሉ ሰዎች ከይሖዋ ይልቅ በክፉ መናፍስት እንዲታመኑ ማድረግ ነው። w19.04 21 አን. 5-6

እሁድ፣ ሰኔ 6

ክፉ የምታደርግ ከሆነ . . . ልትፈራ ይገባሃል።—ሮም 13:4

ሕፃናትን ማስነወር ከባድ ኃጢአት ነው። በአንድ ልጅ ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽም ሰው ልጁን በብዙ መንገዶች ይጎዳዋል። በሚያምነው ሰው እንዲህ ያለ ድርጊት የተፈጸመበት ልጅ፣ ሰዎችን ለማመን ሊቸገርና ስጋት ሊያድርበት ይችላል። ልጆች እንዲህ ካለው የጭካኔ ድርጊት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤ እንዲህ ያለው ድርጊት ሰለባ የሆኑ ልጆች ደግሞ ማጽናኛና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) አንድ የጉባኤው አባል ሕፃናትን ቢያስነውር በጉባኤው ላይ ነቀፋ ያመጣል። (ማቴ. 5:16፤ 1 ጴጥ. 2:12) እንዲህ ያሉ አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽመው ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ የማይሆኑ እንዲሁም የጉባኤውን መልካም ስም የሚያጎድፉ ሰዎችን በጭራሽ አንታገሥም። የመንግሥትን ሕግ በመጣስ ወንጀል የሚሠራ፣ ለምሳሌ ሕፃናትን የሚያስነውር አንድ የጉባኤው አባል በሰብዓዊ ባለሥልጣናት ላይ ኃጢአት ይፈጽማል። (ከሐዋርያት ሥራ 25:8 ጋር አወዳድር።) ሽማግሌዎች የመንግሥትን ሕጎች የማስፈጸም ሥልጣን ባይኖራቸውም ሕፃናትን ያስነወረ ክርስቲያን ድርጊቱ ከሚያስከትልበት ሕጋዊ ቅጣት እንዲያመልጥ ከለላ አያደርጉም። w19.05 9 አን. 4-7

ሰኞ፣ ሰኔ 7

የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው።—1 ቆሮ. 3:19

ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ ስለሚመራን፣ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሁሉ መወጣት እንችላለን። (ኢሳ. 30:20, 21) ቃሉ ‘ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ የታጠቅን እንድንሆን’ እንዲሁም ‘ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆነን እንድንገኝ’ ይረዳናል። (2 ጢሞ. 3:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ሕይወታችንን የምንመራ ከሆነ ‘የዚህን ዓለም ጥበብ’ ከሚያራምዱ ሰዎች ይበልጥ ጥበበኛ እንሆናለን። (መዝ. 119:97-100) የሚያሳዝነው የዚህ ዓለም ጥበብ ሥጋዊ ፍላጎታችንን የሚማርክ ነው። በመሆኑም የዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎች አስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ እንዳይጋባብን መከላከል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” የሚል ምክር መስጠቱ ተገቢ ነው። (ቆላ. 2:8) መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች አስመልክቶ እንደተነበየው ብዙዎች “ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:4) እንደ ኤድስ ያሉ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች መስፋፋታቸው በዚህ ዓለም ጥበብ መመራት ሞኝነት እንደሆነ ከሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው።—2 ጴጥ. 2:19፤ w19.05 21 አን. 1-2፤ 22 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ሰኔ 8

የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች [ተቋቋሙ]።—ኤፌ. 6:11

ሰይጣን፣ እስራኤላውያን ጥሩ ምርት ለማግኘት በዙሪያቸው ያሉ አረማውያንን ልማዶች መከተል እንደሚኖርባቸው እንዲሰማቸው በማድረግ አታለላቸው። በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት፣ አማልክታቸው ዝናብ እንዲሰጧቸው አንዳንድ የአምልኮ ሥርዓቶችን መፈጸም እንዳለባቸው ያምኑ ነበር። በይሖዋ ላይ እምነት ያጡ አንዳንድ እስራኤላውያንም የድርቁ ወቅት እንዳይራዘም ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ይህ እንደሆነ ስለተሰማቸው የሐሰት አምላክ ለሆነው ለባአል በሚቀርቡ የአምልኮ ሥርዓቶች መካፈል ጀመሩ። ሰይጣን እስራኤላውያንን ለብልግና ምኞቶች እንዲሸነፉም አድርጓቸዋል። አረማዊ የሆኑት ብሔራት ለአማልክታቸው የሚያቀርቡት አምልኮ አስጸያፊ በሆኑ የብልግና ድርጊቶች መካፈልን የሚጨምር ነበር። አስነዋሪ በሆነው በዚህ የአምልኮ ሥርዓት ሴቶችና ወንዶች የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪዎች ይካፈሉ ነበር። ግብረ ሰዶማዊነትና ሌሎች የብልግና ድርጊቶች በሕዝቡ ዘንድ የማይወገዙ ከመሆንም አልፈው በስፋት ተቀባይነት አግኝተው ነበር! (ዘዳ. 23:17, 18፤ 1 ነገ. 14:24) አማልክቱ እንደዚህ ያሉ የአምልኮ ሥርዓቶች ሲቀርቡላቸው ምድሪቱን ምርታማ ለማድረግ እንደሚነሳሱ ሕዝቡ ያምን ነበር። በርካታ እስራኤላውያን፣ ብልግና የሚፈጸምባቸው የእነዚህ ብሔራት የአምልኮ ሥርዓቶች ስለማረኳቸው የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመሩ። w19.06 2 አን. 3፤ 4 አን. 7-8

ረቡዕ፣ ሰኔ 9

አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10

በሺዎች የሚቆጠሩ የቤቴል ቤተሰብ አባላትና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አዲስ የአገልግሎት ምድብ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች የሚወዱትን የአገልግሎት ምድብ መተው ከብዷቸው ሊሆን ይችላል። እናንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠማችሁ ከለውጡ ጋር ለመላመድ ምን ይረዳችኋል? ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ በማንበብ እንዲሁም በእነሱ ላይ በማሰላሰል ወደ ይሖዋ ይበልጥ ቅረቡ። በተጨማሪም በአዲሱ ጉባኤያችሁ ውስጥ በስብከቱ ሥራ የምትችሉትን ያህል መካፈላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ ቀደም ሲል ያደርጉ የነበረውን ያህል ባይሆንም እንኳ እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን የሚቀጥሉ ክርስቲያኖችን አይረሳም። አኗኗራችሁን ቀላል አድርጉት። የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረው ጭንቀት መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችሁን ‘እንዲያንቀው’ ወይም እንዲገድበው አትፍቀዱ። (ማቴ. 13:22) ይህ ዓለምም ሆነ አሳቢ የሆኑ ወዳጅ ዘመዶቻችሁ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ቁሳዊ ንብረት በማካበት ላይ እንድታተኩሩ ለሚያሳድሩት ተጽዕኖ እጅ አትስጡ። (1 ዮሐ. 2:15-17) በመንፈሳዊ፣ በስሜታዊና በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚያስፈልገንን ማንኛውንም እርዳታ “በሚያስፈልገን ጊዜ” ለማሟላት ቃል በገባው በይሖዋ ታመኑ።—ዕብ. 4:16፤ 13:5, 6፤ w19.08 20 አን. 4፤ 21 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ሰኔ 10

ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።—መዝ. 55:22

የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሟችኋል? ይሖዋ ጭንቀታችንን እንደሚረዳልን ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው። ይሖዋ አቅማችንን እንዲሁም ሐሳባችንንና ስሜታችንን ያውቃል። (መዝ. 103:14፤ 139:3, 4) በይሖዋ ከታመንን፣ እሱ ጭንቀት የሚፈጥሩብንን ችግሮች መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ አሉታዊ አመለካከት ያድርባችሁና ተስፋ ትቆርጡ ይሆናል። እንዲህ ከተሰማችሁ ይሖዋ ጭንቀታችሁን ለመቋቋም እንደሚረዳችሁ አስታውሱ። ይሖዋ የሚረዳችሁ እንዴት ነው? የሚያሳስባችሁን ነገር አውጥታችሁ እንድትነግሩት ጋብዟችኋል። እርዳታ ለማግኘት የምታቀርቡትን ልመና ይሰማል። (መዝ. 5:3፤ 1 ጴጥ. 5:7) ስለዚህ ያጋጠሟችሁን ችግሮች በተመለከተ አዘውትራችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። ይሖዋ በቀጥታ ባያነጋግራችሁም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስና በድርጅቱ በኩል መልስ ይሰጣችኋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምታነቧቸው ታሪኮች መጽናኛና ተስፋ ይሰጧችኋል። በተጨማሪም ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ያበረታቷችኋል።—ሮም 15:4፤ ዕብ. 10:24, 25፤ w19.06 16 አን. 7-8

ዓርብ፣ ሰኔ 11

በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።—ማቴ. 24:9

ስደት ሲደርስባችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ፤ ‘በእሱ ፊት ልባችሁን እንደ ውኃ አፍስሱ’፤ እንዲሁም ለአፍቃሪው አባታችሁ የሚያስፈራችሁንና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ ንገሩት። (ሰቆ. 2:19) በዚህ መንገድ መጸለይን ልማድ ካደረጋችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረባችሁ ትሄዳላችሁ። (ሮም 8:38, 39) የአምላክ መንግሥት እንደሚያመጣቸው ቃል የተገባልን በረከቶች እንደሚፈጸሙ ተማመኑ። (ዘኁ. 23:19) አምላክ በሰጣቸው በእነዚህ ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ከሌላችሁ ሰይጣንና ወኪሎቹ በቀላሉ ሊያሸብሯችሁ ይችላሉ። (ምሳሌ 24:10፤ ዕብ. 2:15) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚያመጣቸው ቃል ስለገባቸው ነገሮች እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ መተማመን የምትችሉት ለምን እንደሆነ ጊዜ ወስዳችሁ ምርምር አድርጉ። ይህን ማድረጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? በእምነቱ ምክንያት ለሰባት ዓመት ታስሮ የነበረውን ስታንሊ ጆንስን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ወንድም በታማኝነት እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አምላክ መንግሥት ያለኝ እውቀት እምነቴን ያጠናከረው ከመሆኑም ሌላ መንግሥቱ እውን መሆኑን እርግጠኛ መሆኔና ይህን ለቅጽበትም እንኳ አለመጠራጠሬ በአቋሜ እንድጸና ረድቶኛል።” እናንተም አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ካላችሁ በፍርሃት አትሸነፉም።—ምሳሌ 3:25, 26፤ w19.07 2 አን. 1፤ 3 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ሰኔ 12

በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ፤ እስክትወጡም ድረስ እዚያው ቆዩ።—ማቴ. 10:11

ደቀ መዛሙርት ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰዎች የአምላክ ወዳጆች መሆን የሚችሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ ብቻ ነው። በተጨማሪም የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት የሚመሩ ከመሆኑም ሌላ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። (ዮሐ. 14:6፤ 17:3) በእርግጥም ኢየሱስ በአደራ የሰጠን ኃላፊነት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ይህን ሥራ የምናከናውነው ብቻችንን አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱና አብረውት ስለሚያገለግሉ አንዳንድ ወዳጆቹ ሲናገር “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:9) ይሖዋና ክርስቶስ ፍጹም ላልሆኑ ሰዎች የሰጡት ይህ መብት ምንኛ ውድ ነው! በተጨማሪም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል። ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ልንወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ‘መፈለግ’ ነው። ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ የምንመሠክር ከሆነ እውነተኛ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን እናሳያለን። ክርስቶስ እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ የምናከብር ከሆነም እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን እናሳያለን። w19.07 15 አን. 3-5

እሁድ፣ ሰኔ 13

ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ ሁሉ ጥበብም ጥበቃ ታስገኛለችና፤ የእውቀት ብልጫ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ ማቆየት መቻሏ ነው።—መክ. 7:12

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙ ምክሮች የብዙዎችን ትኩረት ይስባሉ። ኒው ዮርክ ውስጥ ቻይንኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች የምትሰብክ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለሰዎቹ አሳቢነት ለማሳየትና የሚናገሩትን ለማዳመጥ ጥረት አደርጋለሁ። ወደዚህ አካባቢ የመጡት በቅርቡ እንደሆነ ካስተዋልኩ ‘እየለመዳችሁ ነው? ሥራ ማግኘት ቻላችሁ? ከአካባቢው ሰዎች ጋር እየተግባባችሁ ነው?’ ብዬ እጠይቃቸዋለሁ።” እንዲህ ማድረጓ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለእነሱ ለማካፈል አጋጣሚ የሚከፍትበት ጊዜ አለ። ይህች እህት አጋጣሚው ሲመቻች፣ የምታነጋግረውን ሰው እንዲህ ትለዋለች፦ “ከሰዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ቁልፉ ምን ይመስልሃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ምሳሌ ላሳይህ? ምሳሌው ‘ጠብ መጫር ግድብን ከመሸንቆር ተለይቶ አይታይም፤ ስለዚህ ጥል ከመነሳቱ በፊት ከአካባቢው ራቅ’ ይላል። ይህ ምክር ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር የሚረዳን ይመስልሃል?” (ምሳሌ 17:14) እንዲህ ያሉ ውይይቶች፣ ሌላ ጊዜ ተመልሰን እንድናነጋግራቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ለይተን እንድናውቅ ይረዱናል። w19.07 23 አን. 13

ሰኞ፣ ሰኔ 14

ደግፎ የሚያነሳው ሰው በሌለበት አንዱ ቢወድቅ እንዴት ይሆናል?—መክ. 4:10

በአዲስ ምድብ እንዲያገለግሉ የተመደቡ ክርስቲያኖች ከምንም በላይ የሚፈልጉት ያሉበትን ሁኔታ እንድትረዱላቸው ነው። እነሱ ራሳቸው ወይም የቤተሰባቸው አባል የጤና እክል አጋጥሟቸው ሊሆን ይችላል። የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው በሐዘን ተደቁሰው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ለሌሎች ባይናገሩትም እንኳ በቀድሞ የአገልግሎት ምድባቸው ያፈሯቸው ወዳጆቻቸው ናፍቆት ያስቸግራቸው ይሆናል። እንዲህ ያሉትን ግራ የሚያጋቡ ስሜቶች መቋቋም ጊዜ ሊወስድ ይችላል። እናንተ የምታደርጉላቸው ድጋፍና ጥሩ ምሳሌነታችሁ አዲሱን ምድባቸውን ለመልመድ ይረዳቸዋል። በሌላ አገር ለበርካታ ዓመታት ያገለገለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በቀድሞ የአገልግሎት ምድቤ ላይ በየቀኑ ብዙ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር። በአዲሱ ምድቤ ላይ ግን በአገልግሎት ላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብ ወይም ቪዲዮ ማሳየት እንኳ ብርቅ ነበር። በጉባኤዬ ያሉት አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቅ ወይም ጥናት ሲኖራቸው ይጋብዙኛል። ይህም አዎንታዊ አመለካከት እንዳዳብር ረድቶኛል። በአዲሱ ምድቤ በአገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር የሚቻልበትን መንገድ ተማርኩ። ይህ ሁሉ እንደገና ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።” w19.08 22 አን. 10፤ 23-24 አን. 13-14

ማክሰኞ፣ ሰኔ 15

በጌታ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ኤዎድያንን እመክራለሁ፤ ሲንጤኪንም እመክራለሁ።—ፊልጵ. 4:2

እንደ ኤዎድያን እና ሲንጤኪ ሁሉ እኛም ለሌሎች ፍቅር ማዳበር ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ዋነኛው ነገር በድክመታቸው ላይ ትኩረት ማድረጋችን ሊሆን ይችላል። ሁላችንም በየዕለቱ ስህተት እንሠራለን። በወንድሞቻችን ስህተት ላይ ካተኮርን ለእነሱ ያለን ፍቅር እየቀዘቀዘ ይሄዳል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም አብሮን የስብሰባ አዳራሹን ከማጽዳት ይልቅ ሌላ ነገር ሲሠራ ብናየው እንበሳጭ ይሆናል። ይህ ወንድም የሠራቸውን ሌሎች ስህተቶች መቁጠር ብንጀምር ይበልጥ እየተበሳጨን ስለምንሄድ ለእሱ ያለን ፍቅር ይቀንሳል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ የሚከተለውን እውነታ ማሰብህ ጠቃሚ ነው፦ ይሖዋ የእኛንም ሆነ የወንድማችንን ድክመት ያውቃል። ድክመታችንን እያወቀም እንኳ እኛንም ሆነ ወንድማችንን ይወደናል። ስለዚህ እኛም የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ፍቅር ማሳየትና ለወንድሞቻችን አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል። ወንድሞቻችንን ለመውደድ ልባዊ ጥረት ስናደርግ በመካከላችን ያለው አንድነት ይጠናከራል።—ፊልጵ. 2:1, 2፤ w19.08 9-10 አን. 7-8

ረቡዕ፣ ሰኔ 16

ይሖዋ . . . ትሑት የሆነውን ሰው ይመለከታል።—መዝ. 138:6

ይሖዋ ትሑት የሆኑ ሰዎችን ይወዳል። ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የሚችሉት እውነተኛ ትሕትና የሚያንጸባርቁ ሰዎች ብቻ ናቸው። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ‘ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ አይፈቅድም።’ ሁላችንም ይሖዋን ማስደሰትና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንፈልጋለን፤ በመሆኑም ትሕትናን እንድናዳብር የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለን። ትሕትና የሚለው ቃል ለራስ የተጋነነ አመለካከት አለመያዝን እንዲሁም ከኩራት ወይም ከእብሪት ነፃ መሆንን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው፣ ትሑት የሆነ ሰው ከይሖዋ አምላክና ከሌሎች ሰዎች አንጻር ስላለው ቦታ ትክክለኛ አመለካከት አለው። አንድ ሰው ትሑት ከሆነ፣ ሁሉም ሰው በሆነ መንገድ ከእሱ እንደሚበልጥ ይገነዘባል። (ፊልጵ. 2:3, 4) አንዳንዶች ከላይ ሲታዩ ትሑት ይመስሉ ይሆናል። ምናልባትም በባሕርያቸው ዓይናፋር ወይም ዝምተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። አሊያም ደግሞ በባሕላቸው ወይም በአስተዳደጋቸው ምክንያት ለሌሎች አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳዩ ነገሮችን ያደርጉ ይሆናል። በውስጣቸው ግን በጣም ኩሩዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይዋል ይደር እንጂ እውነተኛ ማንነታቸው መገለጡ አይቀርም።—ሉቃስ 6:45፤ w19.09 2 አን. 1, 3-4

ሐሙስ፣ ሰኔ 17

ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።—2 ተሰ. 1:8

“ስለ ጌታችን ኢየሱስ [የሚገልጸው] ምሥራች” ኢየሱስ ያስተማራቸውን እውነቶች በሙሉ ያጠቃልላል። ምሥራቹን ታዘናል የሚባለው በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ስናደርገው ነው። ይህም ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠትን፣ ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖርንና ስለ አምላክ መንግሥት ማወጅን ያካትታል። (ማቴ. 6:33፤ 24:14) እንዲሁም የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ሲወጡ ለእነሱ ድጋፍ መስጠትን ይጨምራል። (ማቴ. 25:31-40) በቅርቡ ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮች “ሌሎች በጎች” ያሳዩአቸውን ደግነት መልሰው የሚከፍሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ዮሐ. 10:16) እንዴት? የአርማጌዶን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት 144,000ዎቹ ቅቡዓን በሙሉ ወደ ሰማይ ሄደው የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ያገኛሉ። ከዚያም ጎግን የሚደመስሰውና ‘ለእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ማለትም በግ መሰል ለሆኑት የአምላክ አገልጋዮች ጥበቃ የሚያደርገው ሰማያዊ ሠራዊት ክፍል ይሆናሉ። (ራእይ 2:26, 27፤ 7:9, 10) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ ቅቡዓን የይሖዋ አገልጋዮች ገና ምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ እነሱን መደገፍ የሚችሉበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል! w19.09 12 አን. 16-18

ዓርብ፣ ሰኔ 18

እረፍት ታገኛላችሁ።—ማቴ. 11:29

ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ መሥራት እረፍት ያስገኝልናል የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከሁሉ የተሻሉ አሠሪዎች አሉን። ዋነኛው አሠሪያችን ይሖዋ ምስጋና ቢስ ወይም ጨካኝ አለቃ አይደለም። የምናከናውነውን ሥራ ያደንቃል። (ዕብ. 6:10) በተጨማሪም የኃላፊነት ሸክማችንን ለመሸከም የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ገላ. 6:5) ንጉሣችን ኢየሱስ ደግሞ የሚመራን እሱ ራሱ ምሳሌ በመሆን ነው። (ዮሐ. 13:15) እንዲንከባከቡን የተሾሙት ሽማግሌዎችም “ታላቅ የበጎች እረኛ” የሆነውን ኢየሱስን ለመምሰል ይጣጣራሉ። (ዕብ. 13:20፤ 1 ጴጥ. 5:2) መንጋውን የመመገብና የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ደግ፣ ደፋርና ሌሎችን የሚያበረታቱ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። በተጨማሪም ከሁሉ የተሻሉ የሥራ ባልደረቦች አሉን። በዓለም ላይ የእኛን ያህል ትልቅ ዓላማ ያለው ሥራ የሚያከናውንና በፍቅር የተሳሰረ ሕዝብ የለም። እስቲ አስቡት፦ ከሁሉ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ከሚከተሉ ሆኖም ራሳቸውን ከማያመጻድቁ ሰዎች ጋር አብረን የመሥራት መብት አግኝተናል። እነዚህ ሰዎች ሌሎች ከእነሱ የተሻሉ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እኛን የሚመለከቱን እንደ ሥራ ባልደረባቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ወዳጃቸው አድርገው ነው። ከእኛ ጋር ያላቸው ወዳጅነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ሕይወታቸውንም ጭምር ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው! w19.09 20 አን. 1፤ 23 አን. 12-14

ቅዳሜ፣ ሰኔ 19

በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ [እንደ] ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም።—1 ተሰ. 5:4

ጳውሎስ በማሳሰቢያው ላይ ስለ “ይሖዋ ቀን” ተናግሯል። (1 ተሰ. 5:1-6) “የይሖዋ ቀን” የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው፣ ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ (በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ታመለክታለች) ላይ በሚሰነዘረው ጥቃት ጀምሮ በአርማጌዶን የሚደመደመውን ጊዜ ነው። (ራእይ 16:14, 16፤ 17:5) በተጨማሪም የጳውሎስ ማሳሰቢያ ‘ለይሖዋ ቀን’ ዝግጁ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለብን ይጠቁመናል። ‘እንደ ሌሎቹ ማንቀላፋት’ የለብንም። እንዲያውም ‘ነቅተን መኖር’ እና በዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ በመግባት የገለልተኝነት አቋማችንን እንዳናላላ ንቁ መሆን ይኖርብናል። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የምንሳተፍ ከሆነ “የዓለም ክፍል” እንሆናለን። (ዮሐ. 15:19) በዓለም ላይ ሰላም ሊያሰፍን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። በተጨማሪም ሌሎች እንዲነቁና መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ እንደሚፈጸሙ ስለተናገራቸው ክንውኖች እንዲያውቁ መርዳትም እንፈልጋለን። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ፣ ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ የተከፈተላቸው አጋጣሚ ይዘጋል። የስብከቱ ሥራችን በጣም አጣዳፊ የሆነው ለዚህ ነው! w19.10 8 አን. 3፤ 9 አን. 5-6

እሁድ፣ ሰኔ 20

አንድ ጥቅልል ውሰድና [በእስራኤልና በይሁዳ] ላይ አመጣዋለሁ ብዬ የነገርኩህን ቃል በሙሉ ጻፍበት።—ኤር. 36:2

የማስጠንቀቂያው መልእክት በጥቅልሉ ላይ ከተጻፈ በኋላ ኤርምያስ፣ መልእክቱን እንደሚያደርስ በመተማመን ባሮክን ላከው። (ኤር. 36:5, 6) ባሮክም ይህን አደገኛ ተልእኮ በድፍረት ተወጣ። ኤርምያስ፣ ባሮክ ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ ሄዶ የታዘዘውን ነገር እንዳደረገ ሲያውቅ በእሱ ምን ያህል እንደኮራ አስበው። (ኤር. 36:8-10) የይሁዳ መኳንንት ባሮክ ያደረገውን ሲሰሙ፣ ጥቅልሉን ለእነሱም ጮክ ብሎ እንዲያነብላቸው አዘዙት። (ኤር. 36:14, 15) መኳንንቱ የኤርምያስን መልእክት ለንጉሥ ኢዮዓቄም ለመናገር ወሰኑ። ንጉሥ ኢዮዓቄም፣ ኤርምያስ የጻፈውን መልእክት ሲሰማ በጣም ከመናደዱ የተነሳ ጥቅልሉን አቃጠለው፤ ከዚያም ኤርምያስና ባሮክ እንዲታሰሩ ትእዛዝ አስተላለፈ። ኤርምያስ ግን ሌላ ጥቅልል ወስዶ ለባሮክ ሰጠው፤ ከዚያም ባሮክ፣ ኤርምያስ በቃል እያስጻፈው የይሖዋን መልእክት ይኸውም “የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓቄም በእሳት ባቃጠለው ጥቅልል ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ” በጥቅልሉ ላይ አሰፈረ።—ኤር. 36:26-28, 32፤ w19.11 3 አን. 4-6

ሰኞ፣ ሰኔ 21

እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13

ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል። ለምሳሌ ይሖዋ አስተማሪ፣ አጽናኝ እና ወንጌላዊ ሆኗል፤ እነዚህ ይሖዋ ከሆናቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። (ኢሳ. 48:17፤ 2 ቆሮ. 7:6፤ ገላ. 3:8) በሌላ በኩል ደግሞ ዓላማውን ለመፈጸም ብዙ ጊዜ ሰዎችን ይጠቀማል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20፤ 2 ቆሮ. 1:3, 4) ይሖዋ፣ ለማንኛችንም ቢሆን ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስፈልገንን መሆን እንድንችል ጥበብና ኃይል ሊሰጠን ይችላል። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የይሖዋ ስም ትርጉም፣ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያጠቃልላል። ሁላችንም ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ቢጠቀምብን ደስ ይለናል፤ ሆኖም አንዳንዶች ይሖዋ እየተጠቀመባቸው መሆኑን ይጠራጠራሉ። ለምን? ዕድሜያቸውና ያሉበት ሁኔታ፣ ማከናወን የሚችሉትን ነገር እንደሚገድቡባቸው አሊያም ችሎታ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ነው። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶች፣ እያደረጉ ያሉት ነገር በቂ እንደሆነና ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደማያስፈልጋቸው ያስባሉ። w19.10 20 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ ሰኔ 22

የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው።—1 ጢሞ. 6:10

ፍቅረ ንዋይ ትኩረታችን እንዲከፋፈልና የእምነት ጋሻችንን ችላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ አያጠላልፍም።” (2 ጢሞ. 2:4) እንዲያውም የሮም ወታደሮች በሌላ በማንኛውም ሥራ እንዲካፈሉ አይፈቀድላቸውም ነበር። ዝግጁ እንደሆኑት ወታደሮች ሁሉ እኛም ዋነኛው ግባችን አዛዦቻችንን ይኸውም ይሖዋንና ክርስቶስን ማስደሰት ነው፤ ትኩረታችን ተከፋፍሎ ይህን ከማድረግ ወደኋላ ማለት አንፈልግም። ይሖዋንና ኢየሱስን ማስደሰት፣ የሰይጣን ዓለም ከሚያቀርብልን ከማንኛውም ነገር እንደሚበልጥ ይሰማናል። በመሆኑም ይሖዋን ለማገልገል እንዲሁም የእምነት ጋሻችንንና ሌሎች መንፈሳዊ የጦር ትጥቆቻችንን ለማጠናከር የሚሆን ጊዜና ጉልበት ላለማጣት ጥረት እናደርጋለን። ምንጊዜም ቢሆን መዘናጋት የለብንም! ለምን? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ . . . ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል” በማለት አሳስቧል።—1 ጢሞ. 6:9, 10፤ w19.11 17 አን. 12, 14-15

ረቡዕ፣ ሰኔ 23

ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።—1 ተሰ. 5:3

“የይሖዋ ቀን” ከመምጣቱ በፊት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ ይታወጃል። (1 ተሰ. 5:1-6) በ1 ተሰሎንቄ 5:2 ላይ የተጠቀሰው “የይሖዋ ቀን” የሚያመለክተው “ታላቁን መከራ” ነው። (ራእይ 7:14) ይህ መከራ ሊጀምር መሆኑ የሚታወቀው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ለየት ያለ አዋጅ እንደሚታወጅ ይነግረናል። ይህ አዋጅ ታላቁ መከራ ሊጀምር መሆኑን የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ያገለግላል። አዋጁ፣ በትንቢት የተነገረው “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ ነው። የሃይማኖት መሪዎች ይህን አዋጅ በማወጅ ይተባበሩ ይሆን? ይተባበሩ ይሆናል። የሆነው ሆኖ ግን ይህ አዋጅ አጋንንት ከሚያናፍሷቸው በርካታ ውሸቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም ይህ ውሸት ከሌሎቹ ውሸቶች ሁሉ የከፋ ነው፤ ምክንያቱም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ መከራ ሊጀምር በተቃረበበት ጊዜ ላይ ሰዎች የተሳሳተ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ከዚያም “ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።” ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችስ? የይሖዋ ቀን ድንገት መጀመሩ ሊያስገርማቸው ቢችልም ዝግጁ ሆነው ስለሚጠብቁ አይደናገጡም። w19.09 9 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ሰኔ 24

ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው።—መክ. 3:1, 6

ውሳኔ ስታደርግ በግልጽ የተቀመጠ ግብ ይኑርህ። ግልጽ የሆነ ግብ ካወጣህ የጀመርከውን ዳር ማድረስ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ለማንበብ ወስነህ ይሆናል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ካላወጣህ ግን ዓላማህን ዳር ማድረስ ላይሳካልህ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የአንድ ጉባኤ ሽማግሌዎች ለመንጋው ይበልጥ እረኝነት ለማድረግ ወስነው ይሆናል፤ ይሁንና የተወሰነ ጊዜ ቢያልፍም ውሳኔያቸውን ተግባራዊ አላደረጉም። ያሰቡት እንዲሳካላቸው በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰባቸው ጠቃሚ ነው፦ “እረኝነት ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች እነማን እንደሆኑ ተወያይተናል? እነዚህን ወንድሞች የምንጎበኝበትን ጊዜ መድበናል?” በተጨማሪም ምክንያታዊ ሁን። ማናችንም ብንሆን ያሰብነውን ሁሉ ለማሳካት የሚያስችል ጊዜ፣ ንብረት ወይም ጉልበት የለንም። ስለዚህ እውነታውን ከግምት ለማስገባት እንዲሁም ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት አድርግ። ያደረግከውን ውሳኔ ዳር ማድረስ ከአቅምህ በላይ ከሆነብህ በውሳኔህ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። w19.11 29 አን. 11-12

ዓርብ፣ ሰኔ 25

እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።—ራእይ 7:14

በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው በኢሳይያስ 65:21-23 ላይ የሚገኘው ትንቢት ይገልጻል። ያ ዘመን ምንም ነገር ሳንሠራ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ጊዜ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ጠቃሚና አርኪ የሆነ ሥራ እናከናውናለን። ይህ ጊዜ ሲያበቃ “ፍጥረት ራሱ . . . ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሮም 8:21) ይሖዋ ለጥንት እስራኤላውያን እንዳደረገው ሁሉ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅትም ሕዝቦቹ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲሠሩና እንዲያርፉ ዝግጅት ያደርጋል። ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚመደብ ጊዜ እንደሚኖር ጥርጥር የለውም። አምላክን ማምለክ ለደስታችን የግድ አስፈላጊ ነው፤ በአዲሱ ዓለምም ቢሆን ይህ እውነታ አይቀየርም። በእርግጥም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በምናከናውናቸው መልካም ሥራዎችና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንደምንደሰት አንጠራጠርም። w19.12 12 አን. 15፤ 13 አን. 17-18

ቅዳሜ፣ ሰኔ 26

እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ፤ በልጆችህም ውስጥ ቅረጻቸው።—ዘዳ. 6:6, 7

‘መቅረጽ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ደግሞ ደጋግሞ በመናገር ማስተማርና ማስገንዘብ” የሚል መልእክት አለው። ይህን ለማድረግ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው ጊዜ ማሳለፍ አለባቸው። መመሪያዎችን ለልጆች ደጋግሞ መናገር አንዳንድ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወላጆች፣ ልጆቻቸው የአምላክን ቃል እንዲያስተውሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት የሚችሉት በዚህ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ስለዚህ አስተዋይ ሁኑ። መዝሙር 127 ልጆችን ከፍላጻዎች ጋር ያመሳስላቸዋል። (መዝ. 127:4) ፍላጻዎች የሚሠሩበት ነገርም ሆነ መጠናቸው እንደሚለያይ ሁሉ ሁለት ልጆችም ፍጹም አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚያስፈልገው መለየት አለባቸው። የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ ሁለት ልጆች ያሏቸው በእስራኤል የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ነገር ሲናገሩ “እያንዳንዱን ልጅ በተናጠል መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ በዚህ መንገድ ልጆችን ማስጠናት አስፈላጊና የሚቻል ነገር መሆን አለመሆኑን መወሰን የእያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ ኃላፊነት ነው። w19.12 26-27 አን. 18-20

እሁድ፣ ሰኔ 27

ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።—ማቴ. 7:12

አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ፣ ወዳጆቻችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች በማከናወን ሲያግዙን በጣም እንደሰታለን! አሳዛኝ በሆነ አደጋ አባቱን ድንገት ያጣው ራያን እንዲህ ብሏል፦ “ሐዘን ውስጥ በምትሆኑበት ወቅት ብዙዎቹን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ማከናወን ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ይሰማችኋል። በመሆኑም ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮችም እንኳ ሌሎች የሚያደርጉላችሁ እርዳታ በእጅጉ ያጽናናል።” ቀላል የሚመስሉ ጠቃሚ ነገሮችን ማድረጋችሁ ሌሎችን በእጅጉ ሊያጽናና እንደሚችል አትዘንጉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ በሥራ የተጠመደ ክርስቲያን ነበር። ያም ቢሆን ማርቆስ ሐዋርያው ጳውሎስን ለማጽናናት የሚሆን ጊዜ አላጣም፤ ጳውሎስም ቢሆን የእሱን እርዳታ ለመጠየቅ አልተሳቀቀም። ከቤተሰቧ አባላት አንዱ የተገደለባት አንጀላ በሐዘኗ ያጽናኗት ወዳጆቿ የፈቃደኝነት መንፈስ ስለነበራቸው አመስጋኝ ናት። እንዲህ ብላለች፦ “ወዳጆችህ ከልባቸው ሊረዱህ እንደፈለጉ ካስተዋልክ የእነሱን እርዳታ መጠየቅ አይከብድህም። እንዲህ ያሉ ወዳጆች፣ አንተን መርዳት እንደከበዳቸው እንዲሰማህ አያደርጉም።” እንግዲያው ‘የእምነት ባልንጀሮቼ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ፈቃደኛ በመሆኔ እታወቃለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው። w20.01 11-12 አን. 14-16

ሰኞ፣ ሰኔ 28

የማይገባው ሆኖ ሳለ ከቂጣው የሚበላ ወይም ከጌታ ጽዋ የሚጠጣ . . . ተጠያቂ ይሆናል።—1 ቆሮ. 11:27

አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን “የማይገባው ሆኖ ሳለ” በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚኖረው ቂጣና የወይን ጠጅ ሊወስድ የሚችለው እንዴት ነው? አኗኗሩ ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የማይስማማ ሆኖ ሳለ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ከወሰደ ነው። (ዕብ. 6:4-6፤ 10:26-29) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” ማግኘት ከፈለጉ በታማኝነት መጽናት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። (ፊልጵ. 3:13-16) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ፣ ትዕቢተኛ ከመሆን ይልቅ ትሑታን እንዲሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን ይረዳቸዋል። (ኤፌ. 4:1-3፤ ቆላ. 3:10, 12) በመሆኑም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ አይሰማቸውም። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ በመንፈስ ስለተቀቡ ብቻ ይሖዋ ለሌሎች አገልጋዮቹ ከሚሰጠው የበለጠ መንፈስ ቅዱስ እንደሰጣቸው አድርገው አያስቡም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከሌሎች የበለጠ ጥልቅ እውቀት እንዳላቸውም አይሰማቸውም። በተጨማሪም ለማንም ሰው፣ በመንፈስ እንደተቀባና በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መውሰድ እንደሚገባው የሚገልጽ ሐሳብ ፈጽሞ አይሰነዝሩም። ከዚህ ይልቅ ወደ ሰማይ የሚሄዱትን የሚጋብዘው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ። w20.01 27-28 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ሰኔ 29

ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8

ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብና እንድናነጋግረው ይፈልጋል። “ሳትታክቱ ጸልዩ” በማለት ያበረታታን ከመሆኑም ሌላ በማንኛውም ጊዜ እኛን ለመስማት ፈቃደኛ ነው። (ሮም 12:12) እኛን ለመስማት የሚሆን ጊዜ አያጣም፤ እንዲሁም ጸሎታችንን ለመስማት አይታክትም። እኛ ደግሞ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም ቃሉን ለመረዳት የሚያስችሉንን ጽሑፎች በማንበብ ይሖዋን ማዳመጥ እንችላለን። በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ በትኩረት በመከታተል እሱን ማዳመጥ እንችላለን። ከይሖዋ ጋር አዘውትረን መነጋገራችን ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል። ይሖዋ ወደ እሱ ስንጸልይ ልባችንን እንድናፈስስ ይፈልጋል። (መዝ. 62:8) እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ጸሎት ሳቀርብ የሌላ ሰውን ሐሳብ የምደግም እመስላለሁ? ወይስ ጸሎቴ በእጄ እንደጻፍኩት ደብዳቤ ከልብ የመነጨ ነው?’ ይሖዋን በጣም እንደምትወደውና ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ይህ እንዲሆን ግን አዘውትረህ ልታነጋግረው ይገባል። ይሖዋን ሚስጥረኛህ አድርገው። የሚያስደስትህንና የሚያሳዝንህን ነገር ንገረው። እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ ምንም ሳትሳቀቅ ለምነው። w20.02 9 አን. 4-5

ረቡዕ፣ ሰኔ 30

የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ጠብቁ።—1 ጴጥ. 5:2

ይሖዋ ለሽማግሌዎች ሕዝቡን እንደ እረኛ የመጠበቅ ከባድ ኃላፊነት በአደራ ሰጥቷቸዋል። ሽማግሌዎች ነህምያ የይሖዋን ሕዝቦች የያዘበትን መንገድ በመመርመር ትልቅ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ነህምያ የይሁዳ አገረ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። (ነህ. 1:11፤ 2:7, 8፤ 5:14) እስቲ ያጋጠሙትን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማሰብ ሞክሩ። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን እንዳረከሱና ሌዋውያኑን በገንዘብ እንዲደግፉ የተሰጣቸውን ሕግ እንደጣሱ ተገንዝቦ ነበር። አይሁዳውያኑ የሰንበትን ሕግ የማያከብሩ ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶቹ ወንዶች የባዕድ አገር ሴቶችን አግብተው ነበር። አገረ ገዢው ነህምያ ለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍትሔ መስጠት ነበረበት። (ነህ. 13:4-30) ነህምያ የራሱን ሕጎች በአምላክ ሕዝቦች ላይ በመጫን ሥልጣኑን አላግባብ አልተጠቀመም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን አመራር ለማግኘት ልባዊ ጸሎት አቅርቧል፤ እንዲሁም የይሖዋን ሕግ ለሕዝቡ አስተምሯል። (ነህ. 1:4-10፤ 13:1-3) ከዚህም በተጨማሪ ነህምያ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከወንድሞቹ ጋር ሠርቷል፤ ሌላው ቀርቶ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አብሯቸው ገንብቷል።—ነህ. 4:15፤ w19.09 15-16 አን. 9-10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ