ዓለምን ስንመለከታት
የሰውነት እንቅስቃሴና ጤና
ሳይንቲስቶች መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ጥቅሞች እንዳሉት የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አሁንም እያገኙ ናቸው። አሜሪካን ሄልዝ የተባለው መጽሔት በ17,000 ወንዶች ላይ ለ30 ዓመት የተካሄደ አንድ ጥናት በቅርቡ አውጥቷል። አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በሳምንት ከ1,000 በላይ ካሎሪዎችን የሚያቃጥሉ ሰዎች በትልቁ አንጀት ካንሰር የመያዛቸው አጋጣሚ የአካል እንቅስቃሴ ከማይሠሩት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ የሚቀንስ ይመስላል። ከአንድ ሚልዮን በላይ በሆኑ ስዊድናውያን ወንዶች ላይ ለ19 ዓመታት የተደረገ አንድ ጥናት ከሥራ ሰዓታቸው ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ጊዜ ተቀምጠው የሚሠሩ ሰዎች ከሥራ ሰዓታቸው ውስጥ 20 በመቶ ለማይሞላ ጊዜ ከሚቀመጡ ሰዎች በትልቁ አንጀት ካንሰር የመያዛቸው አጋጣሚ 30 በመቶ የላቀ መሆኑን ደርሶበታል። በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በ5,400 ሴቶች ላይ በተካሄደ አንድ ጥናት በኮሌጅ በነበሩበት ጊዜ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ያደረጉት ሴቶች እጅግም የሰውነት እንቅስቃሴ ካላደረጉትና በዚህም ምክንያት 2.5 ጊዜ እጥፍ ለማሕፀን ካንሰር ከተጋለጡት የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር ሲወዳደር በጡት ካንሰር የተያዙት ቁጥር በግማሽ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል። መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ለሰውነታችን በሽታን የመከላከል ኃይል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና በፍጥነት ቫይረሶችን ከሰውነት ለማስወገድ የሚረዳ መሆኑን የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎችም አሉ። እንደ ማራቶን ያሉ ከባድ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ውጤት ያስከትላሉ። አንዳንድ ጊዜም የሰውነትን በሽታን የመቋቋም ኃይል ያዳክማሉ።
በወላጆች ላይ የሚፈጸም ድብደባ
በወላጆች ላይ የሚደርሰው “ድብቁና አሰቃቂው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ቁጣ” እየተባለ ይነገር የነበረው ድርጊት በአውስትራሊያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ፖሊስና የደህንነት ቡድኖች ወላጆቻቸውን የሚደበድቡ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ቁጥር በዚህች አገር ውስጥ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል። ምንም እንኳን ብዙውን ጊዜ የድርጊቱ ሰለባ የሚሆኑት እናቶች ቢሆኑም አባቶችና አያቶችም ጭካኔ ከተሞላበት ጥቃት አላመለጡም። ሲድኒ ውስጥ እየታተመ የሚወጣው ሰንደይ ቴሌግራፍ የተባለው ጋዜጣ የአንድ የደህንነት ድርጅትን ዲሬክተር ጠቅሶ ሲናገር “የ10 ዓመትን ያህል አነስተኛ ዕድሜ ያላቸው ልጆች እናቶቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በማስፈራራት በአካል ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚችሉ መሆናቸውን ሰዎች ሲሰሙ ይደነቃሉ” ብሏል። የአንድ ማኅበረሰብ የደህንነት አገልግሎት ድብደባ የደረሰባቸው ወላጆች በሚያደርጉት የስልክ ጥሪ ብዛት የተነሳ ለድርጊቱ ሰለባዎችና ለጥፋተኞቹ ብቻ የሚሆን ልዩ ፕሮግራም ለማውጣት አቅዷል።
የመሬት የሙቀት መጠን እየጨመረ ነው
የ1980ዎቹ ዓመታት ከምን ጊዜውም የበለጠ ሞቃታማ ነበሩ። በዓለም አቀፉ የአካባቢና የልማት ኢንስቲትዩት የሚታተመው ፐርስፔክቲቭስ የተባለው መጽሔት “በ140 ዓመት ጊዜ ከተከሰቱት ሰባት እጅግ ሞቃታማ ዓመታት ውስጥ ስድስቱ የተመዘገቡት ከ1980 ወዲህ ነው” ሲል ሪፖርት አድርጓል። የብሪታንያ የሜትሮሎጂ ቢሮ ባወጣው ስታትስቲካዊ መረጃ መሠረት 1990 እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛው የሙቀት መጠን የተመዘገበበት ዓመት ነው። ይህ መረጃ ይላል ፐርስፔክቲቭስ “የምድር አማካይ የአየር ሙቀት መጠን እያደገ መምጣቱን የሚያረጋግጥና መሬት አጠቃላይ በሆነ ሞቃታማ ሁኔታ የተዋጠች መሆኗን የሚያሳይ አዲስ ማስረጃ ነው።”
በአሜሪካ ውስጥ በግድ የተነወሩ ሴቶች ቁጥር
በቅርብ ጊዜ የወጣው ብሔራዊ የሴቶች ጥናት በ1990 በዩናትድ ስቴትስ ውስጥ 683,000 ሴቶች ተገደው የተነወሩ መሆናቸውን ደርሶበታል። ለ4,000 ሴቶች በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ የተመረኮዘው ይህ ግምት በዚያው ዓመት ብሔራዊ የወንጀል ጥናት 130,000 አስገድዶ የማስነወር ሙከራዎች ተደርገዋል ወይም ተፈጽመዋል ሲል ከሰጠው ቁጥር አምስት ጊዜ እጥፍ ይበልጣል። በተጨማሪም ተገደው ከተነወሩት መካከል የተፈጸመባቸውን ወንጀል ለፖሊስ ያሳወቁት 16 በመቶ ብቻ መሆናቸው ታውቋል፤ ይህም በመሆኑ በ1990 የቀረቡት ተገዶ የመነወር ሪፖርቶች 102,560 ብቻ እንደነበሩ ያሳያል። አብዛኛዎቹ አስገድዶ የማስነወር ድርጊቶች የተፈጸሙት የድርጊቱ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች በሚያውቋቸው በዘመዶቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸውና በጓደኞቻቸው ነው። በተጨማሪም ይህ የተደረገው ጥናት 12.1 የሚሆኑ አሜሪካውያን ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ ቢያንስ አንዴ ተገዶ የመነወር ድርጊት ሰለባ እንደሚሆኑ ደርሶበታል። ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ፣ ማለትም 62 በመቶ የሚሆኑት ድርጊቱ የሚፈጸምባቸው ገና ለአቅመ ሔዋን ከመድረሳቸው በፊት መሆኑን ተናግረዋል፤ ከእነርሱም መካከል 29 በመቶዎቹ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ዕድሜያቸው ከ11 ዓመት በታች በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዕድሜና መርሳት
ማርጀትና መርሳት ጎን ለጎን የሚሄዱ ነገሮች ናቸውን? ብዙ ሰዎች እንደዚህ ብለው ያስባሉ። ይህ ሐሳብ በኢጣሊያ ውስጥ በተካሄደውና በኮሪየር ሳሉቴ ላይ በተጠቃለለው አንድ ምርምር አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል። ምርመራው ከ20 እስከ 70 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ያካተተ ነበር። የተገኙት ውጤቶች በግልጽ ለሚታየው የመርሳት ሁኔታ መንስኤው በዕድሜ የገፉት ሰዎች በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣታቸው ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል። ለምሳሌ አንድ ወጣት ቢረሳ ለዕድሜው ምንም ትኩረት አይሰጠውም። አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው ቢረሳ ግን ዕድሜ ምክንያት ሆኖ ይቀርባል። በዚህ መንገድ መርሳት አለቦታው ከዕድሜ ጋር ሊያያዝ ይችላል። በሌላ አነጋገር ብዙውን ጊዜ “የማስታወስ ችሎታችንን በተመለከተ የምንሰጠው ግምት ካሉብን ጭንቀቶች ጋር በጣም የተያያዘ ነው፤ ስለዚህ በአጠቃላይ አንድ የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር በራስ መተማመን ነው።” በተጨማሪም ይህ የተደረገው ጥናት ምንም እንኳን አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው የአንድን ወጣት ያህል ፈጣን የመማር ችሎታ ባይኖረውም ቀደም ሲል ያወቃቸውን ነገሮች በማስታወስ ረገድ ዕድሜ እንቅፋት ሊሆን አይችልም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።
አሳዛኙ የደም ልግስና
በፈረንሳይ ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደም በመውሰዳቸው ኤድስ ያዛቸው። ፈረንሳይ ከሌሎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከአምስት እስከ አሥር ጊዜ እጥፍ የላቀ የኤድስ በሽተኞች ቁጥር ሊኖራት የቻለው ለምንድን ነው? የጎረቤት አገሮች ከእስረኞች የደም ልግስና መቀበል ካቆሙ ከሦስት ዓመት በኋላም እስከ 1985 ድረስ በፈረንሳይ የሚገኙት የእስር ቤት ባለ ሥልጣኖች ከእስረኞች የደም ልግስና መቀበላቸውን ቀጥለዋል ሲል ላ ሞንድ ይገልጻል። በመቀጠልም ሪፖርቱ የደም ልግስና “እስረኞች በቀላሉ ወደ ቀድሞው ኑሮአቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችል ተግባር ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ በዚህም መንገድም ለረጅም ጊዜ በስፋት ሲሠራበት ቆይቷል። ደም መስጠት ከቅጣቶች ነጻ ያደርጋል፤ በተጨማሪም እስረኞቹ ደም ከሰጡ . . . አንድ ብርጭቆ ወይን እንዲጠጡ ይፈቀድላቸዋል፤ የዕፅ ሱሰኛ የሆኑት ደግሞ ዕፅ በመውሰዳቸው የሚደርስባቸው ቅጣት ይነሳላቸዋል” በማለት ገልጿል። እስረኞች ደም መስጠታቸው የተፈረደባቸውን የእስር ጊዜም ለመቀነስ ሊረዳቸው ይችላል።
አእምሮን የሚያስት ማግኔት
ጥንታዊቷ ከተማ ኢየሩሳሌም በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባህርያት አድርገው የሚቆጥሩትን ወይም ለዓለም ሰላም ቁልፉ እነርሱ ብቻ እንደሆኑና ይህንንም በኢየሩሳሌም ግንቦች ውስጥ ማሳወቅ እንደሚገባ የሚያምኑ አእምሮአቸውን የሳቱ ሰዎችንም ትማርካለች። “ክርስቲያኖች እኔ ኢየሱስ ነኝ ወይም ድንግል ማርያም ነኝ ወይም በአብዛኛው መጥምቁ ዮሐንስ ነኝ ብለው ይመጣሉ። ብዙውን ጊዜ እንደ ቪያ ዶሎሮሳና በአትክልቱ ሥፍራ እንዳለው መቃብር ባሉ ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ባላቸው ቦታዎች ላይ ሲደርሱ አእምሯቸውን ይስታሉ” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ይናገራል። “አይሁዶች ደግሞ እኔ ሙሴ ነኝ፣ እኔ ንጉሥ ዳዊት ነኝ እያሉ ይናገራሉ። በብሉይ ኪዳን ላይ ያሉትን ሌሎች ገጸ ባሕርያት በመጥቀስ እኔ እከሌ ነኝ በማለት ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች በደብረ ዘይት ተራራ ወይም በምዕራብ በኩል ወዳለው ግንብ ሲሄዱ አእምሯቸውን ይስታሉ።” በቅርብ ጊዜ አንድ ቱሪስት አእምሮውን ስቶ ወደ ሆሊ ሴፑልቸር ቤተ ክርስቲያን እየሮጠ በመሄድ መስቀሉን አንስቶ ከሰከሰው፣ መብራቶቹን ሰባበራቸው፣ ጣዖታትን ማምለክ አይገባም ብሎ እየጮኸ አንድ ሐውልትም ለማፍረስ ሞክሮ ነበር። በየዓመቱ ከ50 እስከ 200 የሚሆኑ ግለሰቦች የአእምሮ ሕክምና ጠበብት ጀሩሳሌም ሲንድሮም ብለው በሚጠሩት በሽታ በመለከፍ የአእምሮ ሕክምና ወደ ሚሰጥበት ካፋር ሻኡል ሆስፒታል ይወሰዳሉ። ከዚህ ቀደም የአእምሮ ህመም የነበረባቸው ሰዎች የአእምሮ ህመም ያልነበረባቸውን ሰዎች በ4 እጥፍ ይበልጣሉ፤ ይህ ህመም የገጠማቸው ወንዶች ከሴቶቹ 2 እጥፍ ይበልጣሉ።
የወባን ትንኝ መከላከል
የወባ በሽታን ለመከላከል የሚወሰድ አንድ እርምጃ በወባ በሽታ የሚከሰተውን ሞት በከፍተኛ መጠን ሊቀንሰው ይችላል። በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በጋምቢያ በ73 መንደሮች በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት አልጋዎችን የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት በተደረገባቸው መረቦች በመሸፈን እነዚህ መረቦች ባልተደረጉባቸው ቦታዎች በወባ በሽታ ከሚያልቁት ልጆች ጋር ሲወዳደር የሞቱን ቁጥር 70 በመቶ መቀነስ የሚቻል መሆኑን አመልክቷል። በሽታውን የምታስተላልፈው የወባ ትንኝ በይበልጥ የምትናከሰው ሌሊት ስለሆነ ሰዎች ይበልጥ ሊጠቁ በሚችሉበት በመኝታ ጊዜያቸው መረቦቹ ጥሩ መከላከያ ሆነዋቸዋል። ምንም እንኳን መረቦቹ ትንንሽ ቀዳዳዎች ያሏቸው ቢሆንም ፐርሜትሪን የተባለውን የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት በመረቦቹ ላይ ማድረጉ የበለጠ ውጤት ይኖረዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ከሆነ የወባ በሽታ በየዓመቱ እስከ ሁለት ሚልዮን የሚደርሱ ብዛት ያላቸው ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል። ከበሽታው ሰለባዎች መካከል 25 በመቶ የሚያክሉት ልጆች ናቸው።
የሳንባ ነቀርሳ አገረሸ
የዓለም የጤና ድርጅት የቀድሞው መቅሠፍት የሳንባ ነቀርሳ በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ የሦስት ሚልዮን ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው በማለት ሪፖርት አድርጓል። በቶሮንቶ ካናዳ ውስጥ የሚታተመው ዘ ግሎፕ ኤንድ ሜል በየዓመቱ ለበሽታው ከሚጋለጡት ስምንት ሚልዮን ሰዎች መካከል 96 በመቶው የሚከሰተው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ነው፤ ይህም የሚሆነው በጤና እንክብካቤ ጉድለትና በሕክምና እቃዎች እጥረት የተነሳ ነው በማለት ጨምሮ ገልጿል። “የሳንባ ነቀርሳ በይበልጥ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች የሚያጠቃ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ በሽታ እየሆነ መጥቷል” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ሂሮሺ ናካጂማ ገልጸዋል። በጣም በበለጸጉት አገሮች በሽታው በተለይ የሚያጠቃው በዕድሜ የገፉ ሰዎችን፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ጎሳዎችና ለተሻለ ኑሮ ወደ ሌላ አገር የሄዱ ሰዎችን ነው። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የዓለም የጤና ድርጅት የሕክምና ባለ ሥልጣን ብዙ ሕሙማን ለበሽታው የተጋለጡበት ምክንያት የሰውነታቸው በሽታን የመከላከል ኃይል በአደንዛዥ ዕፅና በኤድስ በመዳከሙ የተነሳ ነው።
“አያቶችን መጣል”
የሆስፒታል ሠራተኞች ድርጊቱን አያቶችን መጣል በማለት ይጠሩታል። የቤተሰብ አባሎች በዕድሜ የገፋ ዘመዳቸውን ወደ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ይዘው ይመጣሉ፤ ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትሉ ምርመራዎችን ሊጠይቁ የሚችሉ አንዳንድ አካላዊ ህመሞችን በመጥቀስ ለአንድ ወይም ከዚያ ለበለጡ ሌሊቶች በዚያው ክፍል እንዲቆዩ ያደርጋሉ። ምርመራዎቹ ከተካሄዱ በኋላ ሆስፒታሉ በዕድሜ የገፋውን ሰው ቤተሰብ ለማግኘት ይሞክራል። ይሁን እንጂ የተሰጠው አድራሻና ስልክ የተጭበረበረ መሆኑን ከማወቅ በቀር የሚገኝ ነገር የለም። በአንዳንድ የነርሶች እርዳታ በሚሰጥባቸው ማዕከሎችም እንዲህ ዓይነት ሥራ ይሠራል። በሆስፒታል ውስጥ የተኛ በዕድሜ የገፋ ሰው እያለ ብዙውን ጊዜ እርሱን አልጋ ነጥቀው ገንዘብ እንደሚከፍል ይበልጥ ለሚታመንበት ታካሚ ይሰጡታል። ከዚያም ሆስፒታሉ ህመምተኛውን ለመመለስ ሲሞክር እሺ ብለው አይቀበሉም። ኒውስዊክ የተባለው መጽሔት እንዳለው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እየጨመረ መጥቷል። በአንድ መደበኛ ባልሆነ ጥናት “አንዳንድ ዶክተሮች በድንገተኛ ክፍል ውስጥ በየሳምንቱ ቁጥራቸው እስከ ስምንት የሚደርስ በዕድሜ የገፉ ህመምተኞች ተጥለው እንደሚያገኙ ሪፖርት አድርገዋል” ሲል መጽሔቱ ገልጿል።
ኤድስና ጡት ማጥባት
ኤድስ ያለባቸው እናቶች ጡት በማጥባት በሽታውን ለህጻናቶቻቸው ማስተላለፍ የሚችሉበት አጋጣሚ በፊት ከተሰጠው ግምት ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ ነው በማለት ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣው ሪፖርት በማእከላዊ አፍሪካ በምትገኘው በሩዋንዳ ዋና ከተማ በኪጋሊ ውስጥ በሚኖሩት እናቶች ላይ በተደረገ ጥናት የተመረኮዘ ነው። ምንም እንኳን ሕጻናቱ በበሽታው የመያዛቸው አጋጣሚ 50 በመቶ ያህል ሊሆን ቢችልም በተበከለ ውኃ ተጠቅሞ ለሕጻናቱ የዱቄት ወተት ማዘጋጀት ከሚያስከትለው የህጻናት ሞት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። ስለዚህ አሁንም ቢሆን በእነዚህ አካባቢዎች ጡት ማጥባት የሚመረጥ ነገር ነው። ሁሉም ኤድስ የያዛቸው ሴቶች ቫይረሱን በጡት ወተት ያስተላልፋሉ ማለት አይደለም። በዚህ መንገድ በሽታው በከፍተኛ ቁጥር እንደሚዛመት የተገለጸውም ጥናቱ ልጅ ከወለዱ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ወራት ካለፉ በኋላ ኤድስ በያዛቸው ሴቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው በበሽታው እንደተያዘ በሰውነቱ ውስጥ የሚኖሩት ቫይረሶች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው።