የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 10/8 ገጽ 22-26
  • ‘ከሚልዮን ውስጥ አንድ’ አገኘሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ከሚልዮን ውስጥ አንድ’ አገኘሁ
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሙዚቀኛ መሆን
  • በሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነው ነገር
  • ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ
  • ሌሎችን መርዳት
  • አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ
  • ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም—ከናዚ የእስረኞች ካምፕ በሕይወት ተረፍኩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • የምትወደው ሰው ሲሞት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2019
  • ዳግም እንደማገኘው ተስፋ ተሰጥቷል
    ንቁ!—2005
  • ለሙዚቃ ያለኝ ፍቅር ገደቡን እንዳያልፍ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
ንቁ!—1993
g93 10/8 ገጽ 22-26

‘ከሚልዮን ውስጥ አንድ’ አገኘሁ

በ1969 በኒው ዮርክ ዉድስቶክ ተዘጋጅቶ የነበረው የሙዚቃ ፌስቲቫል በሙዚቃ ሙያዬ ከፍተኛውን ደስታ ያስገኘልኝ ወቅት ነበር። ዓይን ማየት እስከሚችለው ርቀት ድረስ ቢያማትር የሚያየው ሰዎችን ብቻ ነበር። እጅግ በጣም አስደናቂ ነበር!

በወቅቱ እጅግ ታዋቂ ከነበሩት የሙዚቃ ቡድኖች አንዱ በሆነው ስላይ ኤንድ ዘ ፋሚሊ ስቶን በተባለው ቡድን ውስጥ ቤዝ ጊታሪስትና ድምፃዊ ነበርኩ። ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ትርኢቱን እንድንደግምላቸው በመጠየቅ ከፍተኛ በሆነ የጩኸት ድምፅ አስተጋቡ።

በእርግጥ በጣም አስደሳች ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ይህ ሁኔታ በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከማስታውሳቸው ነገሮች አንዱ መሆኑ ቀርቷል። ‘ከሚልዮን ውስጥ አንድ’ እንደማግኘት የሚቆጠር እጅግ ከፍ አድርጌ የምመለከተው ውድ ሃብት አግኝቻለሁ። ነገሩ ምን እንደሆነ ከመግለጼ በፊት ሕይወቴን ስለቀረጹት ነገሮች ልንገራችሁ።

ሙዚቀኛ መሆን

በ1946 በቴክሳስ ክፍለ ሃገር በቢዩሞንት ከተማ ሙዚቀኛ ከሆነ ቤተሰብ ውስጥ ተወለድኩ። ለእናቴ ብቸኛ ወንድ ልጅዋ እኔ ነበርኩ። እናቴ የአንድ ቤተ ክርስቲያን የመዘምራን ቡድን ውስጥ ፒያኖ ትጫወት ነበር። አባቴ ደግሞ የጃዝ ጊታር ተጫዋች ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤተሰቦቼ ወደ ካሊፎርንያ ክፍለ ሃገር ወደ ኦክላንድ ከተማ ተዛወሩ። እዚያ በአምስት ዓመቴ ታፕ የተባለውን የዳንስ ዓይነት መደነስ ጀመርኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ በልጅነቴ ትንከባከበኝ የነበረችው አያቴ ፒያኖ መጫወት አስተማረችኝ።

የ11 ዓመት ልጅ ስሆን አባቴ የራሱን ጊታርና አምፕሊፋየር ሰጠኝ። እኔም በዚህ አዲስ መሣሪያ መጫወትን በጉጉት መማር ጀመርኩ። ትንሽ ቆይቼም ታንቡር መምታት፣ ክላሪኔትና ሳክስፎን መንፋት ተማርኩ። በ13 ዓመቴ ዘ ፋይቭ ራይፍስ የተባለ የራሴ የሮክ ‘ኤንድ’ ሮል ፕሮፌሽናል የሙዚቃ ባንድ ነበረኝ። በ15 ዓመቴ የደል ግራሃም ትርዮ ባንድ አባል በመሆን በዳንስ ቤቶች መጫወት ጀመርኩ። በባንዳችን ውስጥ ያለነው ተጫዋቾች እኔና እናቴ ነበርን። እናቴ ፒያኖ እኔ ደግሞ ሊድ ጊታር እጫወት እንዲሁም ታንቡር እመታ ነበር።

ቆይተን እኔና እናቴ ባንድ ላይ ሆነን መዝፈን ጀመርን። ታንቡር መቺ ስላልነበረን የሙዚቃው ድምፅ ልክ እንዲመጣልን የቤስ ጊታሬን ክሮች እመታ ነበር። በዚህ መንገድ የራሴ የሆነ ልዩ የቤዝ ጊታር አጨዋወት ስልት ፈጠርኩ። አዘውትራ በገንዘብ ትረዳኝ የነበረች አንዲት ሴት በዚህ አጨዋወት ስልቴ በጣም ከመገረሟ የተነሣ የስላይ ስቶን የሙዚቃ ባንድ ኦፕሬተር ለሆነው ሰው ስልክ ደውላ ዘፈኔን እንዲያዳምጥ ነገረችው። ከዚያም በኋላ በ1966 ሰባት አባላት የነበሩት ስላይ ኤንድ ዘ ፋሚሊ ስቶን በመባል ይታወቅ የነበረው ቡድን በቤዝ ጊታር ተጨዋችነት ተቀበለኝ።

“ዳንስ ቱ ዘ ሚዩዚክ” የሚለው የሸክላ ክራችን ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን አተረፈ። እኛም የዘመኑ እጅግ ታዋቂ የጥቁሮች ቡድን ሆንን። “ሆት ፈን ኢን ዘ ሰመር ታይም”፣ “ኤቪሪዴይ ፒፕል” እና “ታንክ ዩ ፎር ሌቲንግ ሚ ቢ ማይሰልፍ አጌን” የሚሉትን ጨምሮ ሌሎች ተወዳጅ ሙዚቃዎች ወዲያው አከታትለን አወጣን። ከዚያም ዓለም አቀፍ እውቅና ካገኙ ሌሎች ሙዚቀኞች ጋር አንድ ላይ በመሆን በዉድስቶክ ፌስቲቫል አዘጋጀን። ከዚያ በኋላም ዌይት በምትባል የብሪታኒያ ደሴት ስንጫወት 300,000 ሰዎች እንዲሁም በምዕራብ ጀርመን ተዘጋጅቶ በነበረው የሙዚቃ ትርኢት ላይ 350,000 የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተው ተመልክተውናል።

በ1971 ለሕይወቴ የሚያሰጋ ነገር አጋጠመኝ። በሎስ አንጀለስ ስታዲየም በምናቀርበው የሙዚቃ ትርኢት ላይ የሙዚቃው ድምፅና የሕዝቡ ጩኸት ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ እንደሚተኮስብኝ ተነገረኝ። በጣም ፈራሁ። ይሁን እንጂ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቹ በመበላሸታቸው የትርኢቱ አዘጋጅ ወደ መድረኩ ወጥቶ ፕሮግራሙ መሰረዙን ተናገረ። አምላክ በሆነ መንገድ ሕይወቴን ለማዳን ጣልቃ እንደገባ ሆኖ ተሰማኝ። በፍርሃት ተውጬ ከስታዲየሙ ወደ አረፍኩበት ሆቴል እየሮጥኩ ሄጄ በፍጥነት ዕቃዎቼን ጠቀለልኩና ከተማውን ለቅቄ ወጣሁ።

ይህ አስፈሪ ገጠመኝ ግራሃም ሴንትራል ስቴሽን የሚባል የግሌን የሙዚቃ ባንድ ካቋቋምኩ በኋላም ቢሆን በጣም ያሳስበኝ ነበር። ከዚህ ቡድን ጋር ያስቀረፅኩት ሁለተኛ ክር ሽፋኑ ላይ “በአምላክ የተዘጋጀ” (ፕሮዲውስድ ባይ ጎድ) የሚሉ ቃላት ተጽፈውበት ነበር። እንዲህ ያልኩት የአምላክን ስም በከንቱ ለማንሳት ፈልጌ ሳይሆን አምላክ ባደረገልኝ ጥበቃ ከመሞት የዳንኩበትን ሁኔታ ለመግለጽ በማሰብ ነበር።

በሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነው ነገር

በ1973 በዓለም አቀፍ አየር መንገድ ውስጥ የአውሮፕላን አስተናጋጅ ከሆነችው ከቲና ጋር ተገናኘሁ። የሙዚቃ ትርኢቶችን ለማሳየት ዝግጅት በማደርግበት ጊዜ ፀጉሬን ስትጎነጉንልኝ በአምላክ ላይ ስላለኝ እምነት ብዙ ጊዜ እነግራት ነበር። በዚያው ወቅት የቲና እናት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው ነበር።

አንድ ቀን ቲና እናቷ ሲያለቅሱ አገኘቻቸው። የሚያለቅሱበት ምክንያትም በኦክላንድ ስታዲየም በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ እሳቸው ሲጠመቁ ከልጆቻቸው አንዳቸውም በስብሰባው ላይ የማይገኙ በመሆናቸው ነበር። ቲና የቤተሰቡ መገኘት ይህን ያህል የሚያሳስባቸው ከሆነ ዓርብ በጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደምትገኝ ቃል ገባችላቸው።

ቲና በ1974 በዚያ ሐምሌ ወር በተደረገው ስብሰባ ላይ ባየችውና በሰማችው ነገር በጣም በመነካቷ ከስብሰባው ስትመለስ ስልክ ደወለችልኝና ቅዳሜ ዕለት በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድገኝ ለማግባባት ሞከረች። ሆኖም ዓርብ ማታ ዘፈን ስንቀርጽ ስላመሸን በጣም ደክሞኝ ነበር። እሁድ ዕለት ቲና እንደገና ደውላ በስብሰባው እንድገኝ አጥብቃ አሳሰበችኝ። ቲናን እንዲህ በጣም የነካት ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ጉጉት አደረብኝና ሄድኩ።

አንድ ፖሊስ የተሰብሳቢዎች የመኪና ማቆሚያ ትኬት ስላልያዝኩ መኪናዬን በመኪና ማቆሚያ ቦታ ማቆም እንደማልችል ነገረኝ። ቀጥሎም “ያም ሆነ ይህ አንተ ይህን ትምህርት ማዳመጥ አትፈልግም!” አለ። እኔም ትንሽ ቆም አልኩና መኪናዬን አስነስቼ ሄድኩ። ቆይቼ ግን እንደገና አሰብኩበትና መኪናዬን አጠምዝዤ ወደዚያው አመራሁ። ስታዲየሙ ውስጥ የገባሁበት የመጨረሻው ንግግር ሊያልቅ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ነበር።

አብዛኛውን ሕይወቴን ዘፋኝ ሆኜ ስላሳለፍኩት ሰዎች ተሰብስበው ማየት ለእኔ አዲስ አልነበረም። በተለያዩ ምክንያቶች ኦክላንድ ስታዲየም ገብቼ አውቃለሁ። ይህ ግን ካየሁት ሁሉ የተለየ ነበር። የተለያየ ዘር፣ አስተዳደግና የትምህርት ደረጃ ያላቸው 60,000 የሚሆኑ ሰዎች በሙሉ አንድ ላይ በሰላም ተቀላቅለዋል። በተሰበሰቡት ሰዎች ላይ የሚታየው “ስሜት” ብቻውን ይህ በጣም ትልቅ ጉዳይ መሆኑን አሳመነኝ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ‘ከሚልዮን ውስጥ አንድ’ ቢገኝ ነው!

ከስታዲየሙ ስወጣ ምሥክር አለመሆኔን ከሁኔታዬ የተረዳች በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ አንዲት ልጅ መጣችና ሕይወት ይህ ብቻ ነውን? የሚለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ አንድ ቅጂ ሰጠችኝ። የሚያስፈልገኝ ይህ ነበር! ወደ መኪናዬ እየሄድኩ ገጽ 24⁠ን ስገልጥ የዳክዬ፣ የዔሊ፣ የዛፍና የሰዎች ሥዕል ተመለከትኩ። ዳክዬ ለ80 ዓመት፣ ኤሊ ለ150 ዓመት፣ ዛፍ ደግሞ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት መኖር መቻላቸውን ስንመለከት “የሰው ልጅ ዕድሜ አጭር መሆኑ ትርጉም ይሰጣልን?” በማለት መጽሐፉ ጥያቄ ያቀርባል። የዚህ ሥዕላዊ መግለጫ መልእክት ያኔውኑ ልዩ ስሜት አሳደረብኝ።

ከዚያ በኋላ ቲናን ብዙ ጥያቄዎች ጠየቅኳት። ሆኖም ቲና ከእኔ የተሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አልነበራትም። ስለዚህ የቲናን እናት የምታስጠናቸውን ሴት ለመጠየቅ ወሰንን። የሴትየዋን ቤት ለቅቀን እንደወጣን ቲናን “ይህቺ ሴት አስመሳይ ናት! ማንም ሰው እንዲህ ጥሩ ሊሆን አይችልም! ታያለሽ በሚቀጥለው ሳምንት ትለወጣለች!” አልኳት። ይሁን እንጂ ሳምንት አልፎ ሳምንት ቢተካም ሁሉንም ጥያቄዎቻችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣች ስትመልስልን ምንም ለውጥ አላየንባትም።

እኔና ቲና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት በሚለው መጽሐፍ አማካኝነት ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን። ሆኖም ከትንሽ ጊዜ በኋላ ከባንዱ ጋር ሆኜ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ዝግጅት የምናሳይበት ጊዜ ደረሰ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በምንሄድባቸው ከተሞች ሁሉ በአካባቢው ወደሚገኙት ጉባኤዎች እየደወልኩ የእውነትን መጽሐፍ ካቆምኩበት ምዕራፍ ጀምሮ የሚያስጠናኝ ሰው እንድጠይቅ ተነግሮኝ ነበር።

ከምሥራቃዊ ጫፍ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ማዕከላዊ ምዕራብ፣ ከዚያም እስከ ደቡባዊ ክፍለ አገሮች ድረስ ስለተዘዋወርኩ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ጉባኤዎችን ጎብኝቻለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑኝ የነበሩት ሰዎች ከተለያየ ዘርና የኑሮ ደረጃ የመጡ ናቸው። ነገር ግን በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የሚያስተምሩት መልእክት አንድ ዓይነት ነበር። ድርጅቱ እኛ በምንኖርበት ኦክላንድ ባይ በተባለው ከተማ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን አገር አቀፍ የሆነ መንፈሳዊ ስምምነት ያለው ድርጅት መሆኑ በጣም ነካኝ።

ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

በዩናይትድ ስቴትስ ያደረግነውን ጉብኝት ጨርሰን ወደ አውሮፓ ስንሄድም እዚያ ከሚገኙ ምሥክሮች ጋር ማጥናቴን ቀጠልኩ። ፓሪስ ስንደርስ ለቲና ስልክ ደወልኩና እንድንጋባ ሐሳብ አቀረብኩላት። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በየካቲት ወር 1975 በኔቫዳ ከተማ የጋብቻችንን ሥነ ሥርዓት ፈጸምን። ባገባሁ ገና በአምስት ቀኔ ከክለቡ ጋር በዩናይትድ ስቴትስ ሌላ ጉብኝት ማድረግ ጀመርን። በዚህ ጊዜ ግን ቲና አብራኝ ነበረች።

በብሩክሊን ኒው ዮርክ የይሖዋ ምሥክሮችን ዋና መሥሪያ ቤት ጎበኘን። አለባበሳችን በጣም የተለየ ነበር። በሱሪያችን እግርና በኮታችን ጀርባ ላይ ደማቅ ቀይና ብርማ ቀለም ያለው ዘንዶ የተሳለበት ሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሰን ነበር። አለባበሳችንን ስናስብ እስካሁን ያሳፍረናል። ያም ሆኖ በደግነት አስተናገዱን። ልብሳችንን አስመልክቶ የተናገረን አልነበረም።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ወረዳ ስብሰባ በሄድንበት በዚያው ቦታ ልክ አንድ ዓመት ቆይቶ በሐምሌ 1975 በኦክላንድ በተደረገ የወረዳ ስብሰባ ላይ እኔና ቲና ተጠመቅን። በጣም የሚያስደስተው ደግሞ እኔና ቲና ማጥናት እንደጀመርን ወዲያው ደኒዝና ሺላ የተባሉት የቲና ሁለት እህቶች እንዲሁም እናቴ ማጥናት ጀምረው ስለነበር ሁላችንም ባንድ ላይ መጠመቃችን ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ አያቴም በ82 ዓመቷ ተጠመቀች።

የኔ ባንድ ካስቀረጸው የሙዚቃ ሸክላ ላይ ስለ ተማርኳቸው ነገሮች በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። ሚረር በሚል ርዕስ በ1976 የተቀረጸው የሙዚቃ ክር በሽፋኑ ላይ የእኔንና የባንዱን ሌሎች አባሎች ፎቶ ግራፍ አውጥቶ ነበር። በሸክላው ላይ በአንዱ በኩል ፀጉራችን አስረዝመን፣ ጥቁር መነጽር አድርገንና ቀለሙ የለቀቀ ልብስ ለብሰን በሌላው የመስታወቱ ነጸብራቅ ላይ ደግሞ ንጹሕ ሆነን፣ ፀጉራችን አሳጥረንና ልከኛ ልብስ ለብሰን የተነሳነው ፎቶ ይታይ ነበር።

ከዘፈኖቹ አንዱ “ፎርኤቨር” (ዘላለም) የሚል ርዕስ ነበረው። ዘፈኑ ከፊት ለፊታችን ተደቅኖ ባለው የዘላለም ሕይወት አባቴን ከሞት ተነሥቶ ለማየት ባለኝ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነበር። ከዘፈኖቹ በአንዱ ላይ የነበሩት ግጥሞች አዲስ የተጠመቅኩ ምሥክር መሆኔን የሚያሳዩ ነበሩ።

ሌሎችን መርዳት

እምነታችንን ለሌሎች ለማካፈል የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩን። ኦርጋኒስቱና ታምቡር መቺው ላደረግነው ምሥክርነት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ራሳቸውን ለይሖዋ ወሰኑ። ይህ ታምቡር መቺ አሁን በዌስት ሆሊውድ ጉባኤ ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ ነው።

በ1975 ባደረግነው ጉብኝት ላይ ኦርጋኒስቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በምሥክርነቱ ሥራ ሲካፈል በአትላንታ ጆርጂያ ነጮች ብቻ ወደሚኖሩበት የሃብታሞች ሰፈር ወሰድኩት። ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ሳለ የፖሊስ መኪኖች አጠገባችን ሲጥጥ ብለው ቆሙ። ፖሊሶች ከመኪኖቹ እየዘለሉ ወርደው ምን እያደረጋችሁ ነው? ብለው ጠየቁን። በዚያው ሰዓት የፖሊስ ሄሊኮፕተር ከእኛ በጥቂት የጫማ ርቀት ላይ ታንዣብብ ነበር። በአካባቢው ከሚኖሩት መካከል አንዱ “ጥርጣሬ የሚያሳድር” ነገር መኖሩን ለፖሊሶች ሪፖርት ሳያደርግ አልቀረም። ነገር ግን እዚያ የተገኘነው የይሖዋ ምሥክርነት ተልዕኮአችንን ለመፈጸም እንደሆነ ለፖሊሶቹ ስንነግራቸው ትተውን ሄዱ። ኦርጋኒስቱ የምሥክርነቱን ሥራ በመጀመረበት ዕለት እንዲህ ያለ ነገር አጋጠመው!

ከተጠመቅን በኋላ ባደረግነው ጉብኝት ላይ 4 ሜትር ተኩል ርዝመት ባለው ስክሪን ላይ የሚታይ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ባለድምፅ የፊልም ትርኢት አዘጋጀን። ፊልሙን ለማሳየት ሁለት ባለ ተሳቢ የጭነት መኪኖችንና ሁለት አውቶቡሶችን መጠቀም ያስፈልግ ነበር። ፊልሙ አሰቃቂ ስለሆኑት የዓለም ሁኔታዎች ያሳይና ከዚያም ቀጠል አድርጎ በአምላክ መንግሥት በኩል የሚመጣውን መፍትሔ ይጠቁማል። የፊልሙ ስላይዶች በኦክላንድ ስታዲየም የተደረገውን የወረዳ ስብሰባና የእኛን ጥምቀት የሚያሳዩ ፎቶዎች ጭምር የያዙ ነበሩ። ፊልሙ በሙዚቃ የተቀነባበረ ነበር። በየዘፈኖቹ መካከል ማብራሪያ እሰጥ ነበር።

በአንድ የጉብኝት ወቅት በፍሎሪዳ በሆሊውድ ከተማ ለመስክ አገልግሎት ወጣሁ። ቡድኑን የሚመራው ወንድም ከቤት ወደ ቤት እንድናገለግል መድቦን ነበር። ድንገት በአካባቢው ባለ አንድ ቤት ውስጥ የእኔን ዘፈን ሰማሁት። በሩን አንኳኳሁ። በአደንዛዥ ዕጽ የሰከሩ ሦስት ወጣት ወንዶች የሚያዳምጡትን ሙዚቃ ዘፋኝ በራቸው ላይ ቆሞ በማየታቸው አፋቸውን ይዘው ቀሩ! ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ከጊዜ በኋላ አጥንተው ምሥክሮች እንደሆኑ ሰምቻለሁ።

በ1979 ሎስ አንጀለስ መጥተን መኖር ጀመርን። እዚያም መዋኛ ያለውና ከተማዋን ለማየት በሚያስቸል ቦታ ላይ የተሠራ መናፈሻ ያለው ሰፊ ቤት ነበረን። ከቤቱ አጠገብ 24 የመቅጂያ መሣሪያዎችን የያዘ የሙዚቃ መቅረጫ ስቱዲዮ አቋቋምኩ። እዚያ በመጀመሪያ ያስቀረጽኩት ዘፈን ከአንድ ሚልዮን ቅጂዎች በላይ የተሸጠና “ዋን ኢን ኤ ሚሊየን ዩ” የሚል ርዕስ የነበረውን ክር ነበር። ከዚያ ጊዜ ትንሽ ቆይቶ ዲያቆን ሆኜ የማገልገል መብት አገኘሁ። በ1982 ልጃችን ላቲያ ከመወለዷ አንድ ሳምንት አስቀድሞ ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ።

አንድ እሁድ ዕለት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እየመራሁ ሳለ የሃዋይ ተወላጅ የሆነ አንድ ወጣት ሰው ወደ መንግሥት አዳራሹ ገባ። ሰውዬው በመገረም አፍጥጦ ያየኝ ጀመር። ሰውዬው በ1975 በሃዋይ ፀጉሬን አስረዝሜ ፖፕ ሙዚቃ ስጫወት አይቶኝ ነበር። ስለዚህ አሁን ሥርዓታማ ልብስ ለብሼና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስመራ በማየቱ ደነገጠ። ወደ ሎስ አንጀለስ የመጣው ታዋቂ ሙዚቀኛ ለመሆን ፈልጎ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ከእኔ ጋር ለማጥናት ተስማማ። አሁን በጉባኤያችን የዘወትር አቅኚ ሆኖ ያገለግላል።

አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ

በእውነቱ፣ እኔ እና ቲና በ1982 አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ደስተኞች ሆነናል ለማለት እችላለሁ። በመንፈሳዊ እድገታችን ተጨማሪ መሻሻል ያሳየንበት ሌላው መስክ አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ ነው። ቤታችን በጣም ትልቅ በመሆኑ በደንብ እንዲያዝ ስንል ብዙ አትክልተኞችና ሠራተኞች የቀጠርን ቢሆንም 90 በመቶ የሚሆነውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው በሁለት ክፍሎች ውስጥ ብቻ ነበር። በከተማ ውስጥ የምንነዳት ሊንኮሊን የተባለች መኪና፣ የ1955 ሞዴል የሆነች ተንደርበርድ፣ ኮርድ፣ ማርቸዲስ ቤንዝ፣ 25 ጫማ ያለው ባለ ሞተር ተጎታች ቤት፣ የጭነት መኪና እና ብዙ ሞተር ብስክሌቶች የነበሩን ቢሆንም ሙሉ በሙሉ አንጠቀምባቸውም ነበር። ስለዚህ በ1985 ከተደረገው የወረዳ ስብሰባ በኋላ ቤታችንና አብዛኞቹን መኪኖቻችንን ሸጥን።

አሁን መጠነኛ በሆነ የከተማ ቤት ውስጥ እንኖራለን። ቲናም አቅኚ ሆና እያገለገለች በቀላሉ ልትይዘው ትችላለች። አሁንም በተወሰነ ደረጃ በሙዚቀኛነት ብሠራም እውነተኛ ደስታ የማገኘው ግን አቅኚ ሆኜ በማገልገሌና ትንሿ ልጃችን በመንፈሳዊ እድገት ስታደርግ በማየቴ ነው። ልጃችን ገና ትንሽ ብትሆንም የማያወላውል መንፈሳዊ ግብ አላት። ራሷን ለይሖዋ መወሰኗን በጥምቀት ማሳየት የምትችልበትን ጊዜ እንደምትናፍቅ አዘውትራ ትናገራለች።

ሌላው በናፍቆት የምጠብቀው በረከት እናቴ ከሞት ተነሥታ እንደገና ማየትና የዘወትር አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ እያለች በታማኝነት ከሞተችበት ከ1987 በኋላ ስለተከናወኑት ነገሮች ለእርሷ መተረክ ነው። አዎን፣ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሙዚቃዎችን በመጫወት ከማገኘው ደስታ ይልቅ አሁን መዝሙራዊው “ሃሌ ሉያ። ለእግዚአብሔር አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው” ብሎ የተናገራቸውን ቃላት ለመታዘዝ የተቻለኝን ሁሉ በማድረጌ እውነተኛ እርካታ አግኝቻለሁ። (መዝሙር 149:1) — ላሪ ግራሃም እንደተናገረው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚህ የዉድስቶክ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ግማሽ ሚልዮን በሚሆን ሕዝብ ፊት ተጫውቻለሁ

[ምንጭ]

John Dominis, LIFE MAGAZINE © Time Inc.

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ እና ከልጄ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ