ዓርብ፣ ሚያዝያ 17
ማንም ሰው በምንም መንገድ አያሳስታችሁ።—2 ተሰ. 2:3
ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የማይስማማ ነገር ወይም አስደንጋጭ ወሬ ስንሰማ የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ይኖርብናል። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ ጠላቶቻችን ከዋናው መሥሪያ ቤት የተላከ የሚመስል ደብዳቤ አሰራጭተው ነበር። ደብዳቤው አንዳንድ ወንድሞች የራሳቸውን ድርጅት እንዲያቋቁሙ የሚያበረታታ ነበር። ደብዳቤው ሲታይ እውነተኛ ይመስላል። ታማኝ የሆኑ ወንድሞች ግን በዚህ አልተታለሉም። ደብዳቤው የያዘው መልእክት አስቀድመው ከተማሯቸው ነገሮች ጋር እንደማይስማማ አስተዋሉ። ዛሬም የእውነት ጠላቶች አንዳንድ ጊዜ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግራ እንድንጋባና በመካከላችን መከፋፈል እንዲፈጠር ለማድረግ ይጥራሉ። ‘የማመዛዘን ችሎታችን በቀላሉ እንዲናወጥ’ ከመፍቀድ ይልቅ የሰማነው ወይም ያነበብነው ነገር ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን በመመዘን ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።—2 ተሰ. 2:2፤ 1 ዮሐ. 4:1፤ w24.07 12 አን. 14-15
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 18
ማንም ኃጢአት ቢሠራ . . . ረዳት አለን።—1 ዮሐ. 2:1
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርገው ትልቁ ውሳኔ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ የይሖዋን አገልጋዮች ያቀፈውን ቤተሰብ መቀላቀል ነው። ይሖዋ ሁሉም ሰው ይህን ውሳኔ እንዲያደርግ ይፈልጋል። ለምን? የእሱ ወዳጆች እንዲሆኑና ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። (ዘዳ. 30:19, 20፤ ገላ. 6:7, 8) ያም ቢሆን ይሖዋ ማንንም ሰው እንዲያገለግለው አያስገድድም። እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ እንዲያደርግ ፈቅዷል። አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን የአምላክን ሕግ በመጣስ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ? ንስሐ ካልገባ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 5:13) ያም ሆኖ እንኳ ይሖዋ ጥፋተኛው ግለሰብ ወደ እሱ እንደሚመለስ ተስፋ ያደርጋል። እንዲያውም ቤዛውን ያዘጋጀበት አንዱ ወሳኝ ምክንያት ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ይቅርታ እንዲያገኙ ሲል ነው። አምላካችን ጥፋት የሠሩ ግለሰቦች ንስሐ እንዲገቡ ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦላቸዋል።—ዘካ. 1:3፤ ሮም 2:4፤ ያዕ. 4:8፤ w24.08 14 አን. 1-2
እሁድ፣ ሚያዝያ 19
ልብህ ጥበበኛ ቢሆን፣ የእኔ ልብ ሐሴት ያደርጋል።—ምሳሌ 23:15
ሐዋርያው ዮሐንስ ሦስተኛውን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስፋፉና ክፍፍል የሚፈጥሩ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ሌሎች ክርስቲያኖች ግን ‘በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን’ ቀጥለዋል። ይሖዋን ይታዘዙ እንዲሁም ‘በትእዛዛቱ መሠረት ይመላለሱ’ ነበር። (2 ዮሐ. 4, 6) እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ዮሐንስን ብቻ ሳይሆን ይሖዋንም አስደስተውታል። (ምሳሌ 27:11) ምን ትምህርት እናገኛለን? ታማኝነት ደስታ ያስገኛል። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋን እያስደሰትን እንዳለ ማወቃችን ያስደስተናል። ይሖዋ የዓለምን ፈተናዎች አሸንፈን ቃሉን ስንታዘዝ ይደሰታል። መላእክትም ይህን ሲያዩ ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:10) በተጨማሪም ሌሎች ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ ስንመለከት እኛም እንደሰታለን። (2 ተሰ. 1:4) ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ደግሞ፣ ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥም እንኳ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንዳስመሠከርን ማወቃችን ጥልቅ እርካታ ያስገኝልናል። w24.11 12 አን. 17-18