የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ
እንደ በናያህ ደፋርና ታማኝ ሁን
በናያህ ንጉሥ ዳዊትንና ንጉሥ ሰለሞንን ያገለግል የነበረ ደፋር ተዋጊ ነው። በናያህ የካህን ልጅ ነበር። በአብዛኛው ካህናትና ሌዋውያን በጦርነት አይካፈሉም፤ የጦር መሣሪያም አይዙም። በናያህ ግን በይሖዋ ስም በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ ይካፈል ነበር። በናያህ አስደናቂ ድፍረት አሳይቷል። ለምሳሌ ወደ አንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ወርዶ አንበሳ ገድሏል፤ እንዲሁም መሣሪያ የታጠቀን አንድ ግዙፍ ወታደር አሸንፏል። ዳዊት በናያህን በጣም ያምነው ስለነበር የራሱ የክብር ዘብ አለቃ አድርጎ ሾሞታል።—2 ሳሙ. 23:20-23
አቢሴሎምና አዶንያስ ባመፁበት ወቅት በናያህ ለዳዊት ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። (2 ሳሙ. 8:18፤ 15:18፤ 1 ነገ. 1:8) ዳዊት ባረጀ ጊዜም በናያህ ሰለሞን እንዲነግሥ በማድረግ ለዳዊት ያለውን ታማኝነት አሳይቷል። (1 ነገ. 1:32-40) ሌሎች ታማኝ ሳይሆኑ በቀሩበት ጊዜም ጭምር በናያህ ለይሖዋና እሱ ለሾማቸው ሰዎች ታማኝ ሆኖ ኖሯል።
እኛም ኃያል ከሆነው ጠላታችን ከሰይጣንና ከግብረ አበሮቹ ጋር ለመዋጋት ድፍረት ያስፈልገናል። በተጨማሪም በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። (ኤፌ. 6:11፤ 1 ጴጥ. 5:8, 9) አንዳንዶች ይሖዋን ለመተው ቢወስኑም እንኳ እኛ ለእሱ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን እንኖራለን፤ እሱ ወሮታችንን እንደሚከፍለንም እንተማመናለን።—2 ሳሙ. 22:26