Troy Harrison/Moment via Getty Images
ንድፍ አውጪ አለው?
የቢቨሮች የግንባታ ጥበብ
እስከ 850 ሜትር የሚደርስ ርዝመትና እስከ 5.3 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያላቸው የቢቨር ግድቦች ተገኝተዋል። ለመሆኑ ቢቨሮች እንዲህ ያሉ ትላልቅ ግድቦችን የሚሠሩት እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ቢቨሮች ከ30 ሴንቲ ሜትር የማይበልጥ ስፋት ያላቸውን ዛፎች ከቆረጡ በኋላ ግንዱን በሚፈልጉት ቁመት ይቆራርጡታል። ከዚያም የቆራረጧቸውን ክብደት ያላቸው እንጨቶች ወደ ወንዙ በመውሰድ እንደ ምሰሶ ያቆሟቸዋል። ቀጥሎም ቀጫጭን ቅርንጫፎችንና ቀንበጦችን በምሰሶዎቹ ላይ ይጠላልፋሉ። የሠሩትን ግድብ ውኃ እንዳይወስደው በትላልቅ ድንጋዮች ይደግፉታል፤ እንዲሁም የግድቡን ጫፍና ጫፍ ከዛፍ ወይም ከዓለት ጋር ያያይዙታል። በተጨማሪም ግድቡ የሚመጣውን ውኃ ግፊት መቋቋም እንዲችል በተቃራኒው አቅጣጫ በእንጨት ያስደግፉታል። ውኃ በሚመጣበት አቅጣጫ ደግሞ ግድቡን በጭራሮና በትናንሽ ተክሎች ሞልተው በጭቃ ይለስኑታል። ከዚህም ሌላ ግድቡ ከልክ በላይ ውኃ እንዳይዝ ጫፍና ጫፉ ላይ ውኃ የሚያሳልፍ ክፍተት ይተዋሉ፤ ኃይለኛ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት ደግሞ ክፍተቱን ያተልቁታል።
የቢቨሮች ግድብ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ፦ (1) ምሰሶዎች፣ (2) የተጠላለፉ ቀጫጭን ቅርንጫፎች፣ (3) መደገፊያ እንጨቶች፣ (4) ውኃ እንዳይወስደው የሚከላከሉ ድንጋዮች እንዲሁም (5) ጭቃ የተለሰነባቸው ጭራሮዎችና ትናንሽ ተክሎች
ተመራማሪዎች ቢቨሮች የሚሠሩት ግድብ ለአካባቢው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ደርሰውበታል። ለምሳሌ የቢቨር ግድቦች የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳሉ፤ የውኃ ጥራትን ያሻሽላሉ፤ እንዲሁም የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጨምር ያደርጋሉ። በተጨማሪም ቀደም ሲል በጋ ላይ ይደርቁ የነበሩ ወንዞች ቢቨሮች በአካባቢው ግድብ ከሠሩ በኋላ ዓመቱን ሙሉ መፍሰስ እንደጀመሩ ተስተውሏል። ግድቦቹ ከባድ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት ውኃ መጠው የሚይዙ ረግረጋማ ቦታዎች እንዲፈጠሩ ስለሚያደርጉ የጎርፍ መጥለቅለቅን ይቀንሳሉ። እነዚህ ረግረጋማ ቦታዎች እሳት እንዳይዛመት ሊከላከሉም ይችላሉ፤ በዙሪያቸው ሰደድ እሳት ቢኖርም በእነዚህ ቦታዎች ያሉት ተክሎች አይጎዱም። ከዚህም ሌላ፣ በግድቦቹ የተነሳ የሚፈጠሩት ረግረጋማ ቦታዎች በርካታ የዱር እንስሳት እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ።
በአንድ ጥናት ላይ ተመራማሪዎች “የቢቨር ግድቦች በመሐንዲስ የተሠሩ እንደሚመስሉ” ገልጸዋል። እንዲያውም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎች የቢቨሮችን የግድብ አሠራር በመኮረጅ በርካታ ግድቦችን ሠርተዋል። በእርግጥም ቢቨሮች የሥርዓተ ምህዳር መሐንዲሶች ተብለው መጠራታቸው የተገባ ነው።
አንድ ቢቨር ግድብ ሲሠራ ተመልከት
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የቢቨሮች የግንባታ ጥበብ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?