የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ሚያዝያ ገጽ 8-13
  • “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን ይፈጽማል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን ይፈጽማል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የእውነት አምላክ በሆነው በይሖዋ የምንተማመነው ለምንድን ነው?
  • የእውነት አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል እስካሁን ምን አድርጓል?
  • የእውነት አምላክ እውነት ወዳዶችን እየሰበሰበ ነው
  • የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2025-2026 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ የሚገኝበት
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2025-2026 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚገኝበት
  • በሉዓላዊው አምላክ በይሖዋ ታመኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ሚያዝያ ገጽ 8-13

ከሰኔ 8-14, 2026

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው

“የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን ይፈጽማል

“የእውነት አምላክ የሆንከው ይሖዋ ሆይ፣ ዋጅተኸኛል።”—መዝ. 31:5

ዓላማ

ይሖዋ የገባውን ቃል ሁሉ እንደሚፈጽምና መንግሥቱ በቅርቡ የሰይጣንን ውሸቶች ሁሉ እንደሚያስወግድ ያለንን እምነት ማጠናከር።

1. በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው? (መዝሙር 31:2-5)

የምንኖረው በሰይጣን ዓለም ውስጥ ነው። ስለዚህ በዓለም ላይ ውሸት፣ ማታለያና ክህደት የተለመደ መሆኑ አያስገርምም። አንዳንድ ጊዜ ማንን ማመን እንዳለብን ግራ ሊገባን ይችላል። ነጋዴዎች አግባብ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ያጭበረብራሉ። ምርትና አገልግሎት የሚያስተዋውቁ ድርጅቶች ሸማቾችን የሚያሳስት መረጃ ይሰጣሉ። እንዲያውም አንዳንዶች የቅርብ ጓደኞቻቸውን እንኳ ማመን አቅቷቸዋል፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ ቃላቸውን ያጥፋሉ። የምንኖረው መተማመን በጠፋበት ዓለም ውስጥ ቢሆንም አንድ የሚያጽናናን ነገር አለ፤ ይሖዋን ምንጊዜም ልንተማመንበት እንችላለን። ምክንያቱም እሱ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:2-5ን አንብብ።) እውነት የማንነቱ ክፍልና መለያ ባሕርይው ነው። የተናገረውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 በዚህ ርዕስ ውስጥ በቅድሚያ፣ በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት መጣል የምንችልባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን። ከዚያም የእውነት አምላክ የሆነው ይሖዋ የሰይጣንን ዓለም የሚያጠፋው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ዓላማውን ለማሳካት በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ እንዳለ እንመረምራለን። እነዚህን ነገሮች መመርመራችን ስለ ይሖዋ በድፍረት ለመመሥከር ያነሳሳናል።

የእውነት አምላክ በሆነው በይሖዋ የምንተማመነው ለምንድን ነው?

3. በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችልበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

3 ይሖዋ ፈጣሪ ስለሆነ ልንተማመንበት እንችላለን። ሰማያትንም ሆነ ምድርን የሠራው እሱ ነው፤ የሕይወት ምንጭም እሱ ነው። (ዘፍ. 1:1፤ መዝ. 36:9፤ ራእይ 4:11) በተጨማሪም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ ፈጥሯል። አሁንም ሆነ ወደፊት በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከእሱ ቁጥጥር ውጭ የሆነ አንድም ነገር የለም። ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ ገደብ የለሽ የሆነ ጥበብና ኃይል አለው። ስለዚህ የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ሕይወታችንን በእሱ እጅ አደራ መስጠት እንችላለን።

4. ይሖዋ እንደሚወደን የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?

4 ይሖዋ ስለሚወደን ልንተማመንበት እንችላለን። ለእኛ ያለውን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ገልጾልናል። የፈጠረን በሕይወት መኖር የሚያስገኘውን ደስታ ልክ እንደ እሱ እንድናጣጥም ስለፈለገ ነው። ደግሞም የሠራን ‘በራሱ መልክና አምሳል’ ነው። (ዘፍ. 1:26) የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። ውብ የሆነችውን ምድር የሠራት ለእኛ መኖሪያ እንድትሆን ነው። (መዝ. 115:16) በተጨማሪም ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምድርን ገነት የማድረግ አስደሳች ሥራ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍ. 1:28፤ 2:15) በምድር ላይ ያለውን የተትረፈረፈ ሀብት እንዲጠቀሙበትና እንዲደሰቱበት ፈቅዶላቸዋል። ይሖዋ ያደረጋቸው እነዚህ ነገሮች “ታማኝ [ፍቅሩ] ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚቀጥል ያሳያሉ።—መዝ. 103:17

5. (ሀ) ሰይጣን የይሖዋን ዓላማ ለማስተጓጎል ቢሞክርም ይሖዋ የተናገረውን እንደሚፈጽም ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የተናገራቸውና ፍጻሜያቸውን ያገኙ አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (“አምላክ ሁሌም እውነት እንደሚናገር የሚያሳዩ ማስረጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

5 ይሖዋ ሁሌም የተናገረውን ስለሚፈጽም ልንተማመንበት እንችላለን። ይሖዋ ምድርን የፈጠራት “መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ” አይደለም። (ኢሳ. 45:18, 19) ሆኖም አዳምና ሔዋን ሲያምፁ የሞት ፍርድ ተላለፈባቸው። ስለዚህ ሰይጣን የአምላክን ዓላማ ያስተጓጎለው ይመስል ነበር። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ የተናገረውን ነገር እንዳይፈጽም ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም። (ኢሳ. 46:10, 11) ምድር ጻድቅ በሆኑ የሰው ልጆች እንድትሞላ ያለው ዓላማ አልተቀየረም። አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ የፈቀደላቸው ለዚህ ነው። ዘሮቻቸውን ከኃጢአት ነፃ ለማውጣትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ ደግሞ አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጠ።—ዮሐ. 3:16

አምላክ ሁሌም እውነት እንደሚናገር የሚያሳዩ ማስረጃዎች

ይሖዋ የተናገረውን እንደሚፈጽም የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንመልከት፦

  • ይሖዋ እስራኤላውያን ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር እንዲወርሱ እንደሚያደርግ ለሙሴ ቃል ገብቶለት ነበር።—ዘፀ. 3:6-8፤ ዘዳ. 27:3

  • መሲሑ እንደሚመጣና የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት እርግማን ነፃ እንደሚያወጣቸው ቃል ገብቶ ነበር።—ኢሳ. 53:11, 12

  • ሰዎች እሱን የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ሲል መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ በመላው ዓለም እንዲከናወን እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር።—ማቴ. 24:14

ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ የሚያሳዩ ሌሎች ታሪኮችንስ መጥቀስ ትችላለህ?

የእውነት አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል እስካሁን ምን አድርጓል?

6. አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላ ይሖዋ ምን ትንቢት ተናገረ?

6 አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ያደረጋቸው “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራውa የጥንቱ እባብ” ነው። (ራእይ 12:9፤ ዘፍ. 3:4, 5፤ ዮሐ. 8:44) በዚህም የተነሳ ይሖዋ ወደፊት ሰይጣንን እንደሚያጠፋው ተነበየ። (ዘፍ. 3:15) ሆኖም ይህ ከመፈጸሙ በፊት ሰይጣንን የሚደግፉና የእሱን ምሳሌ የሚከተሉ ብዙዎች እንደሚኖሩ ትንቢቱ ይገልጻል። በሌላ በኩል ደግሞ በታማኝነት ከይሖዋ ጎን የሚቆሙ የተወሰኑ ሰዎች እንደሚኖሩ ይናገራል።

7. የዲያብሎስን ምሳሌ የሚከተሉት እነማን ናቸው? መጨረሻቸውስ ምን ይሆናል?

7 የሰይጣንን መጥፎ ምሳሌ እየተከተሉ ያሉት በይሖዋ ላይ ያመፁት መላእክትና ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህ አጋንንትና ዓመፀኛ ሰዎች የይሖዋን ዓላማ ስለሚቃወሙ ራሳቸውን የሰይጣን ዘር አድርገዋል። ሆኖም አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ሰይጣንና ተከታዮቹ ድምጥማጣቸው ይጠፋል።—ዳን. 2:44፤ ሮም 16:20

8. ኢየሱስ በ1914 ምን እርምጃ ወስዷል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

8 ይሖዋ ሰይጣንንና ተከታዮቹን ለማጥፋት ያለውን ዓላማ እንደሚፈጽም በምን እርግጠኞች መሆን እንችላለን? በ1914 ኢየሱስ ከሰይጣን ዲያብሎስና ከአጋንንቱ ጋር ተዋግቶ ወደ ምድር ወርውሯቸዋል። (ራእይ 12:7-9) ውጊያው የተካሄደው በሰማይ ቢሆንም በምድር ላይ ያሉ ሰዎችም የጦርነቱን ውጤት ቀምሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” (ራእይ 12:12) ከ1914 አንስቶ ሰይጣን ሙሉ ትኩረቱን በምድር ላይ አሳርፏል። በዚህም የተነሳ የዓለም ሁኔታ እየተባባሰ ሄዷል። በእርግጥም ምድር ‘ወዮልሽ’ መባሏ ተገቢ ነው። በቅርቡ ግን ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ያስራቸዋል፤ ዓመፀኛ ሰዎችንም ያጠፋል። በዚህ መንገድ ‘ድሉን ያጠናቅቃል።’ (ራእይ 6:2) ኢየሱስ፣ ሰይጣን ስለ ይሖዋ ያስፋፋቸውን ውሸቶች በማጋለጥ የይሖዋን ስም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከነቀፋ ነፃ ያደርጋል። (መዝ. 45:4-6) ያኔ ይሖዋ የእውነት አምላክ እንደሆነ ሁሉም ሰው ያውቃል!—ሕዝ. 38:23

ሥዕሎች፦ ከ1914 ወዲህ በምድር ላይ እየተከናወኑ ያሉ ነገሮች። 1. ሰባት ራስ ባለው ዘንዶ የተመሰለው ሰይጣን ወደ ምድር ሲጣል። 2. የታጠቁ ወታደሮች በጦርነት መሃል ምሽግ ውስጥ አድፍጠው ሲጠብቁ። 3. የቦምብ ፍንዳታ ጭስ ከደመና በላይ ወጥቶ። 4. መኖሪያ ቤት የሌላት አንዲት ሴት፣ እያለቀሰ ያለ ልጇን አቅፋ መንገድ ዳር ቁጭ ብላ። 5. አንድ ወታደር ጠመንጃውን ሊተኩስ ተዘጋጅቶ። 6. አንድ ሰው በጦርነት በወደመ ከተማ መሃል ሲሄድ። 7. ከአንድ ፋብሪካ አየሩን የሚበክል ጭስ ሲወጣ። 8. ከተማ ውስጥ ማስክ አድርገው የሚሄዱ ሰዎች። 9. ተቃዋሚዎች ከፖሊሶች ጋር ሲጋጩ።

World War I: U.S. National Archives photo; bomb: USAF photo; pandemic: blvdone/stock.adobe.com; riot: inhauscreative/E+ via Getty Images

ከ1914 ወዲህ የዓለም ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል (አንቀጽ 8ን ተመልከት)


የእውነት አምላክ እውነት ወዳዶችን እየሰበሰበ ነው

9. በአሁኑ ወቅት ይሖዋ እነማንን እየሰበሰበ ነው?

9 በአሁኑ ወቅት ይሖዋ “ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ” እየሰበሰበ ነው። (ኤፌ. 1:10) “በሰማያት የሚሆኑ ነገሮች” የተባሉት ይሖዋ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ የመረጣቸው ቅቡዓን ናቸው። “በምድር የሚሆኑ ነገሮች” የተባሉት ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ሁሉም የሰይጣንን ውሸቶች ለማጋለጥና ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ለመርዳት ተግተው እየሠሩ ነው።

10. ይሖዋ ሰዎችን ከሐሰት ሃይማኖት ውሸቶች ነፃ እያወጣ ያለው እንዴት ነው? (ራእይ 14:6, 7)

10 ይሖዋ እውነት ወዳዶችን እየሰበሰበ ያለው በስብከቱ ሥራ አማካኝነት ነው። ይህ የስብከት ሥራ እስከ ዛሬ ታይቶ በማይታወቅ መጠን በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። (ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።) ይሖዋ ምሥራቹን እያስነገረ ያለው በሰዎች አማካኝነት ቢሆንም መላእክትም ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ በመሰብሰቡ ሥራ ድርሻ አላቸው። ዲያብሎስ ስለ ይሖዋ ውሸቶችን ለማስፋፋት ለብዙ ዘመናት በታላቂቱ ባቢሎን ማለትም በሐሰት ሃይማኖቶች ሲጠቀም ቆይቷል። የስብከቱ ሥራ ታላቂቱ ባቢሎን የምታስተምረው ነገር ውሸት መሆኑን ያጋልጣል። (ራእይ 18:2, 4) በቅርቡ ሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳሉ። ያኔ የእውነት አምላክ የሆነው ይሖዋ የሚገባውን ክብር ይቀበላል።—ራእይ 17:16

11. እውነተኛዎቹን የይሖዋ አገልጋዮች ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

11 እውነት ወዳዶች ከመላው ዓለም የተውጣጡ ናቸው፤ ባሕላቸውና የኑሮ ደረጃቸውም የተለያየ ነው። (ራእይ 7:9, 10) እነዚህ ሰዎች ልክ ‘ምሥራቹን’ እንደሰሙ የሰሙት ነገር እውነት መሆኑን ተገንዝበው ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ተቀላቅለዋል። (ማር. 13:10) ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ በሚያመልኩና በማያመልኩ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ነቢዩ ሚልክያስ ይህን ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።” (ሚል. 3:18) የይሖዋ አገልጋዮች ጥሩ ምግባር ማሳየታቸውና ምሥራቹን መስበካቸው የእውነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን እንደሚያመልኩ በግልጽ ያሳያል።

12. የስብከቱ ሥራ የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?

12 ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ስንሰብክ ኢየሱስን እየታዘዝን ነው፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:18-20) የስብከቱ ሥራ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑና የእውነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለዘላለም የማምለክ አጋጣሚ እንዲያገኙ ያስችላል። ስለዚህ በስብከቱ ሥራ ስንካፈል የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ማለት ነው። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን

13. ዋነኛ የሰይጣን ጥቃት ዒላማ የሆኑት እነማን ናቸው? ለምንስ?

13 ሰይጣን ዲያብሎስ እሱ የሚቆጣጠረው ሥርዓት ሊጠፋ “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው” ስላወቀ እጅግ ተቆጥቷል። (ራእይ 12:12, 13) በዋነኝነት የጥቃቱ ዒላማ ያደረገው “የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁትንና ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ የተሰጣቸውን” ቅቡዓኑን ነው። (ራእይ 12:17፤ 14:12) በተጨማሪም ሰይጣን እነሱንም ሆነ የሚያከናውኑትን ሥራ በሚደግፍ በማንኛውም ሰው ላይ ስደት ያደርሳል።

14. ሰይጣን በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ምን ይከሰታል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ የሰይጣን ወኪሎች በይሖዋ ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ይህ ጥቃት ወደ አርማጌዶን ጦርነት ይመራል። (ራእይ 16:13, 14, 16) በዚህ ወቅት ኢየሱስና በሰማይ ያለው ሠራዊቱ የይሖዋን ሕዝቦች ይታደጋሉ፤ እንዲሁም የቀሩትን የሰይጣን ዓለም ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ይደመስሳሉ። (ራእይ 19:19-21) ክፉዎች፣ አታላዮች፣ ውሸታሞችና አጭበርባሪዎች ሁሉ ከምድር ገጽ ይወገዳሉ። (ራእይ 21:8) ይሖዋ የእውነትና የጽድቅ አምላክ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል።

ኢየሱስና ሰማያዊ ሠራዊቱ በነጭ ፈረሶች ላይ በመጋለብ ምድር ላይ ያሉ ወታደሮችን ሲወጉ። ኢየሱስ ቀስቱን ደግኗል፤ ሌሎቹ መላእክት ደግሞ ሰይፋቸውን መዘዋል።

ኢየሱስና በሰማይ ያለው ሠራዊቱ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት የአምላክን ጠላቶች ለማጥፋት ሲገሰግሱ (አንቀጽ 14ን ተመልከት)


15. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 65:16, 17) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 ዓለም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተከፋፍሏል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን በእሱ እርዳታ አንድነታቸውን ጠብቀው እየኖሩ ነው። ይሖዋ አሁንም እውነት ወዳዶችን ወደ ቤተሰቡ እየሰበሰበ ነው። ሕዝቦቹንም ሆነ የሚያከናውኑትን ሥራ እንዳይባርክ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም። (ኢሳይያስ 65:16, 17ን አንብብ።) በሮም 8:38, 39 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን [አይችልም]።” ስለዚህ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን።

ወንድ ልጅና ሴት ልጅ ያላቸው ወላጆች ደጃፋቸው ላይ ቁጭ ብለው፤ ማዶ ላይ ለምለም አካባቢ ይታያል። በአቅራቢያቸው አውራሪሶች ሣር እየጋጡ ነው።

በዛሬው ጊዜ ያሉት ችግሮች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ጨርሶ አይታወሱም (አንቀጽ 15ን ተመልከት)


16. በሙሉ ልብህ በይሖዋ የምትተማመነው ለምንድን ነው?

16 በእርግጥም የእውነት አምላክ በሆነው በይሖዋ ለመተማመን የሚያበቁ ብዙ ምክንያቶች አሉ። እሱ ፈጣሪያችን ነው። እንዲሁም በጥልቅ ይወደናል። በተጨማሪም አሁንም ቢሆን ዓላማውን ለመፈጸም እየሠራ እንዳለ ማየት እንችላለን። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ እየመጡ ስለሆነ የእጅግ ብዙ ሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው። (ኢሳ. 60:22፤ ዘካ. 8:23) ይሖዋ ምንጊዜም የተናገረውን እንደሚፈጽም እናውቃለን። በቅርቡም የሰውን ዘር ከሰይጣን ውሸቶችና ማታለያዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ያወጣል። ዳዊት ያቀረበው ጸሎት የእኛንም ስሜት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል፦ “እሱ ብቻ አስደናቂ ነገሮችን የሚያደርገው . . . ይሖዋ ይወደስ። ክብራማ ስሙ ለዘላለም ይወደስ፤ ምድርም ሁሉ በክብሩ ትሞላ።”—መዝ. 72:18, 19

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • “የእውነት አምላክ” በሆነው በይሖዋ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ የሰይጣንን ዓለም የሚያጠፋው እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜስ ዓላማውን ለመፈጸም ምን እያደረገ ነው?

  • የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

a መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ላይ ያመፀው ይህ መልአክ ስሙ ማን እንደሆነ አይነግረንም። “ዲያብሎስ” [ስም አጥፊ] እና “ሰይጣን” [ተቃዋሚ] የሚሉት መጠሪያዎች ተግባሩን የሚገልጹ ስያሜዎች ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ