የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ሚያዝያ ገጽ 2-7
  • ይሖዋ ከልጅነቴ ጀምሮ አሠልጥኖኛል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ከልጅነቴ ጀምሮ አሠልጥኖኛል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ እኔን ማሠልጠኑን ቀጠለ
  • በአቅኚነት ያገኘሁት ደስታ
  • የሴኔጋል ቆይታዬ
  • ኒው ብረንስዊክና ኩዊቤክ ውስጥ በአቅኚነት አገለገልን
  • በትጋት ያገለገሉ ወንድሞችና እህቶች
  • ከታማኝ ወንድሞች ያገኘኋቸው ትምህርቶች
  • ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄድን
  • ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች መማሬ ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • በግል ትኩረት መስጠት የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ሚያዝያ ገጽ 2-7
ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ቢሮው ውስጥ ሲሠራ።

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ከልጅነቴ ጀምሮ አሠልጥኖኛል

ዴቪድ ስፕሌን እንደተናገረው

አንድ ወንድም አንዲት ወረቀት ሰጠኝ። ወረቀቷን ሳያት “ዴቪድ ስፕሌን፣ ሚያዝያ 8, 1953፦ ‘የዓለምን መጨረሻ ማወጅ’” ትላለች። “ይሄ ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኩት። እሱም “በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንድታቀርብ የተሰጠህ ክፍል ነው” አለኝ።a እኔም “እኔ መች ክፍል ለማቅረብ ተመዘገብኩ!” አልኩት።

ታሪኬን ከመሃል ጀመርኩባችሁ አይደል? እስቲ ከመጀመሪያው አንስቶ ልንገራችሁ። የተወለድኩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ካልጋሪ፣ ካናዳ ውስጥ ነው። በ1940ዎቹ መገባደጃ ዶናልድ ፍሬዘር የተባለ አንድ ወጣት አቅኚ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል በራችንን አንኳኳ። እናቴም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። የተማረችውን እውነት በጣም ወደደችው። ሆኖም ከባድ የጤና እክል ስለነበረባት በጉባኤው እንቅስቃሴዎች አዘውትራ መካፈል አልቻለችም። እንደዚያም ሆኖ እድገት አድርጋ በ1950 ተጠመቀች። የሚያሳዝነው፣ ከተጠመቀች ሁለት ዓመት እንኳ ሳይሞላት አረፈች። አባቴ በወቅቱ አማኝ ባይሆንም እንኳ በይሖዋ ምሥክሮች ሥርዓት እንድትቀበር ፈቀደ።

እናቴ ከተቀበረች ከጥቂት ቀናት በኋላ አሊስ የተባለች በዕድሜ የገፋች አንዲት ቅቡዕ እህት በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘችኝ። እናቴ ጤንነቷ ሲፈቅድላት በእሁዱ ስብሰባ ላይ ይዛኝ ትሄድ ስለነበር እህት አሊስ ታውቀኝ ነበር። ስብሰባው ላይ መገኘት እችል እንደሆነ አባቴን ጠየቅኩት። እሱም ፈቀደልኝ፤ እንዲሁም የእናቴን የቀብር ንግግር የሰጠውን ወንድም ማመስገን ስለፈለገ “አንዴ ብቻ” አብሮኝ እንደሚሄድ ነገረኝ። የሄድነው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ በሚካሄድበት ምሽት ላይ ነው። አባቴ መጀመሪያ የተገኘው በእንዲህ ዓይነት ስብሰባ ላይ መሆኑ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በሕዝብ ፊት ንግግር ማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ሥልጠና ወስዶ ስለነበር በስብሰባው ላይ የሰማው ነገር በጣም ትኩረቱን ሳበው። ስለዚህ በየሳምንቱ በዚያ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰነ። ቀስ በቀስ ደግሞ በሌሎች ስብሰባዎች ላይም መገኘት ጀመረ።

በዚያ ዘመን የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች የዕለቱን ስብሰባ የሚጀምረው በትምህርት ቤቱ የተመዘገቡትን ወንድሞች ስም በመጥራት ነበር። እነሱም ስማቸው ሲጠራ “አለሁ” ብለው ይመልሳሉ። አንድ ምሽት፣ በቀጣዩ ስብሰባ ላይ የእኔም ስም እንዲጠራ እንደምፈልግ ለወንድም ነገርኩት። እሱም ስሜ ተጠራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ መሆኑን ሳያረጋግጥ አመስግኖኝ ብቻ ተለያየን።

ስሜ እንዲጠራ ስጠይቅ ‘በትምህርት ቤቱ ክፍል ማቅረብ እፈልጋለሁ’ እያልኩ እንደሆነ አልገባኝም ነበር። እኔ የፈለግኩት ስሜ እንዲጠራ ብቻ ነው! በቀጣዩ ሳምንት ስሜ ተጠራ። እኔም በልበ ሙሉነት “አለሁ” ብዬ መለስኩ። ስብሰባው ሲያልቅ ወንድሞችና እህቶች እየመጡ አድናቆታቸውን ገለጹልኝ። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ክፍል ተሰጠኝ።

በጣም ደነገጥኩ! በዚያ ዘመን የተማሪ ክፍሎች ከስድስት እስከ ስምንት ደቂቃ የሚወስዱ ንግግሮች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚነበብበት ክፍል አልነበረም። አባቴ ንግግሩን እንድዘጋጅ ረዳኝ፤ ከማቅረቤ በፊት 20 ጊዜ እንድለማመደው አድርጎኛል። ክፍሌን ካቀረብኩ በኋላ ደግሞ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ጠቃሚ ምክር ሰጠኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ አባቴን፣ መንፈሳዊ የሆኑ ወንድሞችና እህቶችን እንዲሁም ድርጅቱን ተጠቅሞ አሠልጥኖኛል።

ይሖዋ እኔን ማሠልጠኑን ቀጠለ

አገልግሎት ስጀምር ያሠለጠነችኝ ቅድም የጠቀስኳት እህት አሊስ ነች። በዚያ ዘመን፣ አገልግሎት ስንወጣ ለሰዎች ሦስት ጥቅስ እናነብና መጽሐፍ እናበረክት ነበር። የእኔ ተራ ሲሆን እህት አሊስ ውይይቱን ትጀምርልኛለች። ከዚያም የመጀመሪያውን ጥቅስ እንዳነብ ትጋብዘኛለች። ጥቅሱን ካነበብኩ በኋላ ውይይቱን አስቀጥላለሁ። ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ጥቅስ አነብና መጽሐፍ አበረክታለሁ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ ውይይቱን ማስጀመር የምችለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ። በ1954 መገባደጃ ላይ አባቴ ከተጠመቀ በኋላ እኔን በአገልግሎት የማሠልጠኑን ኃላፊነት ተረከበ። ነጠላ ወላጅ ቢሆንም ይሖዋን እንድወድ አድርጎ እኔን ለማሳደግ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ድርድር አያውቅም ነበር። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን፤ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ አገልግሎት እንወጣለን።

በጣም ጎበዝ የምባል ተማሪ ባልሆንም በትምህርት ቤት ባሳለፍኳቸው 12 ዓመታት ያገኘሁት ትምህርት በመላው ሕይወቴ ጠቅሞኛል። ለምሳሌ ጥሩ የሒሳብና የእንግሊዝኛ ሰዋስው እውቀት ቀስሜያለሁ። እዚያ ሳለሁ የወሰድኩት የሥነ ጽሑፍ ሥልጠናም በአሁኑ ጊዜ በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ለማከናውነው ሥራ ጠቅሞኛል።

ብዙ ጊዜ ሰዎች “ለሙዚቃ ፍቅር ያደረብህ እንዴት ነው?” ብለው ይጠይቁኛል። ሁለቱም ወላጆቼ ሙዚቃ ይወዱ ነበር። በሰባት ዓመቴ ፒያኖ መማር ጀመርኩ። ሆኖም አስተማሪዬ ጥሩ ችሎታ እንዳለኝ አልተሰማትም። ስለዚህ መማሬን ባቆም የተሻለ እንደሆነ ለአባቴ ነገረችው። እርግጥ እንዲህ ያደረገችበትን ምክንያት መረዳት አይከብደኝም፤ በወቅቱ ያን ያህል ሙዚቃ የመማር ፍላጎት አልነበረኝም።

ከተወሰኑ ወራት በኋላ አባቴ ሌላ አስተማሪ ቀጠረልኝ። በዚህ ጊዜ ግን የሠለጠንኩት ፒያኖ ብቻ ሳይሆን ድምፃዊነትም ነው፤ በሁለቱም መስኮች ጥሩ ችሎታ አዳበርኩ። ደስ የሚል ድምፅ ስለነበረኝ አንዳንድ ውድድሮችን አሸንፌያለሁ። በሙዚቃ መስክ ዲግሪ ይዤ የሙዚቃ አስተማሪ የመሆን ግብ ነበረኝ፤ ይህም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስካፈል ራሴን ለማስተዳደር ይረዳኛል ብዬ አስቤ ነበር። ዲግሪውን ለማግኘት ግን ስለ ሙዚቃ ታሪክና ቅንብር ለረጅም ሰዓታት ማጥናት እንዲሁም ፈተናዎችን መውሰድ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ስለዚህ ይህን ግቤን ትቼ በ1963 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።

በአቅኚነት ያገኘሁት ደስታ

ለአንድ ዓመት ያህል በዘወትር አቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ በካፐስኬሲንግ፣ ኦንታሪዮ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። አብሮኝ እንዲያገለግል የተመደበው አቅኚ ዳንኤል ስኪነር ይባላል። ዕድሜው ከእኔ በእጥፍ ይበልጥ ነበር። ዳንኤል የጉባኤ ሥራዎች ስለሚከናወኑበት መንገድ ብዙ ነገር አስተምሮኛል። በጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ውስጥ እንዳገለግል የተሾምኩት ገና በ20 ዓመቴ ስለሆነ ብዙ የማላውቀው ነገር ነበር። በዛሬው ጊዜም ድርጅቱ አጽንኦት ሰጥቶ ወጣት ወንድሞችን እንድናሠለጥን የሚመክረን መሆኑ በጣም ያስደስተኛል። እነዚህ ወጣቶች በሚገባ ለመሠልጠን ፈቃደኞች ከሆኑ ይሖዋ ከልጅነታቸው አንስቶ በደንብ ሊጠቀምባቸው ይችላል።

በካፐስኬሲንግ መኖር ቀላል አልነበረም። በብርዱ ወቅት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 44 ዲግሪ ሴልሸስ ይደርሳል፤ “ሞቅ አለ” የሚባለው ደግሞ ከዜሮ በታች 33 ዲግሪ ሴልሸስ ሲደርስ ነው። በዚያ ላይ እኔና ዳንኤል የትም ቦታ የምንሄደው በእግራችን ነበር። ሆኖም ምድባችን ጥሩ ገጽታዎችም ነበሩት። ለምሳሌ ከእህት ሊንዳ ኮል ጋር የተገናኘሁት በዚያ ሳገለግል ነው። እሷም በኋላ ላይ ሚስቴ ሆናለች።

ሊንዳ አገልግሎት ትወድ ነበር፤ ብዙ ተመላልሶዎችም ነበሯት። ለጋስ፣ ደግና ተጫዋች ናት። እናቷ ጎልዲ የተባለች ታማኝ እህት ነበረች። አባቷ ደግሞ አለን ይባላል። ሊንዳ ጆንና ጎርደን የሚባሉ ወንድሞችም ነበሯት። አባቷ መጀመሪያ ላይ ተቃዋሚ ነበር። እንደዚያም ሆኖ እህት ጎልዲ ሊንዳንና ወንድሞቿን ስብሰባ ይዛቸው ትሄድ ነበር፤ በአገልግሎትም አሠልጥናቸዋለች። እህት ጎልዲ፣ ሊንዳ፣ ጆንና ጎርደን በተለያዩ ጊዜያት አቅኚ ሆነው አገልግለዋል። ከዓመታት በኋላ አባቷ አለንም ወደ እውነት መጥቶ ጎበዝ ወንድም ሆነ።

በ1965 በካናዳ ቤቴል በሚደረገው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ፤ ትምህርት ቤቱ አንድ ወር ይፈጃል። በትምህርት ቤቱ ሳለሁ በጊልያድ ለመማር ማመልከቻ እንድሞላ ተጠየቅኩ። እርግጥ ሚስዮናዊ ስለመሆን አስቤ አላውቅም፤ ብቁ እንደሆንኩም አይሰማኝም ነበር። ያም ቢሆን ማመልከቻውን ሞላሁ። ከዚያም በ42ኛው ክፍል ላይ እንድማር ተጋበዝኩ። ጊልያድ ሳለን አስተማሪዎቻችን በየጊዜው እንቅስቃሴያችንን እየገመገሙ ሪፖርት ካርድ ይሰጡን ነበር። በመጀመሪያው ሪፖርት ካርዴ ላይ፣ በትምህርት ቤቱ ያለኝን ቆይታ ስለ ድርጅቱ የቻልኩትን ያህል ለማወቅ እንድጠቀምበት ማበረታቻ ተሰጠኝ። በወቅቱ ገና 21 ዓመቴ ስለነበር ይህ ምክር በጣም ያስፈልገኝ ነበር።

በጊልያድ ካገኘኋቸው ሥልጠናዎች አንዱ ከሕዝብ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ከሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ከቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ከጋዜጣ አዘጋጆች ጋር መሥራትን ይጠይቃል። ሥልጠናውን በጣም ወደድኩት። ግን ወደፊት ምን ያህል እንደሚጠቅመኝ አልተገነዘብኩም ነበር። ይህን ጉዳይ በኋላ እንመለስበታለን።

የሴኔጋል ቆይታዬ

ከጊልያድ ከተመረቅን ከጥቂት ቀናት በኋላ እኔና በሚስዮናዊነት አብሮኝ እንዲያገለግል የተመደበው ማይክል ሆለ ወደ ምድባችን አቀናን። የተመደብነው በአፍሪካ በምትገኘው በሴኔጋል ነበር። በወቅቱ በመላው አገሪቱ የነበሩት አስፋፊዎች ቁጥር ከመቶ አይበልጥም።

ለተወሰኑ ወራት ካገለገልኩ በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በሳምንት አንድ ቀን እንዳገለግል ተጠየቅኩ። ቅርንጫፍ ቢሮ ስላችሁ ትልቅ ሕንፃ እንዳይመስላችሁ፤ በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ያለች አንዲት ክፍል ነች። ሆኖም የቅርንጫፍ ቢሮው አገልጋይ የነበረው ወንድም ኢማኑዌል ፓተራኪስ ሥራው የሚከናወነው በአንዲት ክፍል ውስጥ ቢሆንም ይህ ቅርንጫፍ ቢሮ በዚያች አገር ውስጥ የይሖዋን ድርጅት እንደሚወክል እንዳልረሳ ሁልጊዜ ይነግረኝ ነበር። በአንድ ወቅት ወንድም ኢማኑዌል በአገሪቱ ላሉት ሚስዮናውያን የሚያበረታታ ደብዳቤ እንድንጽፍ ሐሳብ አቀረበ። በዚያ ዘመን ብዙ ወጪ ሳናወጣ በቀላሉ ደብዳቤዎችን ማባዛት የምንችልበት መንገድ አልነበረም። ስለዚህ ያንኑ ደብዳቤ በተደጋጋሚ በታይፕራይተር መጻፍ ይጠበቅብናል ማለት ነው። በታይፕራይተር ስንጽፍ ደግሞ አንዲትም ፊደል ላለመሳሳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብን። ስለዚህ ሥራው ከባድ ነበር።

እስከ ምሽት ድረስ ስሠራ ቆይቼ ወደ ቤቴ ልመለስ ስል ወንድም ኢማኑዌል አንድ ፖስታ ሰጠኝ። ከዚያም “ዴቪድ፣ ከማኅበሩ ደብዳቤ ተልኮልሃል” አለኝ። በኋላ ላይ ፖስታውን ስከፍተው ለካ እኔው ራሴ የጻፍኩት ደብዳቤ ነው! ይህ ገጠመኝ፣ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን የድርጅቱ ክፍል ስለሆነ ፈጽሞ አቅልዬ ልመለከተው እንደማይገባ አስተምሮኛል።

ወንድም ስፕሌን ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር የተነሳው ፎቶ።

ሴኔጋል ውስጥ ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር፣ 1967

በጉባኤው ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር በጣም ተቀራረብን። በአብዛኛው ቅዳሜ ምሽትን የማሳልፈው በጉባኤው ውስጥ ካሉ ቤተሰቦች ጋር ነበር። በዚያ ስላሳለፍኩት ጊዜ ጥሩ ትዝታዎች አሉኝ። ከእነዚህ ወንድሞች ጋር አሁንም ድረስ እንደዋወላለን። በተጨማሪም በዚያ ሳለሁ ፈረንሳይኛ እናገር ነበር፤ ይህ ደግሞ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስጎበኝ ጠቅሞኛል።

በ1968 እኔና ሊንዳ ተጫጨን። እዚያው ሴኔጋል በአቅኚነት ለማገልገል ስላሰብን ሙሉ ጊዜዬን የማይዝ ሥራ መፈለግ ጀመርኩ። ሆኖም በሴኔጋል ያሉ ድርጅቶች የውጭ አገር ዜጋ መቅጠር ስለማይፈቀድላቸው ለተወሰኑ ወራት ሥራ ብፈልግም ማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ ወደ ካናዳ ተመለስኩና እዚያው ተጋባን። ከዚያም ኒው ብረንስዊክ ግዛት ውስጥ በምትገኘው በኤድመንድስተን ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ተመደብን። ይህች ትንሽ ከተማ የምትገኘው ከኩዊቤክ ግዛት አጠገብ ነው።

ዴቪድ እና ሊንዳ በአበቦች ተከበው ፈገግ ብለው ቆመዋል።

በሠርጋችን ዕለት፣ 1969

ኒው ብረንስዊክና ኩዊቤክ ውስጥ በአቅኚነት አገለገልን

በወቅቱ በኤድመንድስተን የአካባቢው ተወላጅ የሆነ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም፤ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ቢሆኑ በጣም ትንሽ ናቸው። የሰዎቹን ሕይወት የምትቆጣጠረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ነች ማለት ይቻላል። አብዛኞቹ ቤቶች በር ላይ “የይሖዋ ምሥክሮችን አንፈልግም” የሚል ምልክት ተለጥፏል። እርግጥ በዚያ ዘመን እንዲህ ያሉ ምልክቶችን የማክበሩ ጉዳይ ያን ያህል አያሳስበንም ነበር። ስለዚህ ምልክት ኖረም አልኖረ እያንዳንዱን ቤት እናንኳኳለን። ቤተ ክርስቲያኗ “የይሖዋ ምሥክሮችን አድነን እንያዛቸው” የሚል ማስታወቂያ በየሳምንቱ ጋዜጣ ላይ ታወጣ ነበር። በከተማዋ ውስጥ ያለነው አራት የይሖዋ ምሥክሮች ማለትም ቪክቶርና ቬልዳ ኖርበርግ እንዲሁም እኔና ሊንዳ ብቻ ነበርን፤ ስለዚህ እኛን ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው!

የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኘን የሰጠንን ምክር ፈጽሞ አልረሳውም። አንድ ሳምንት አብሮን ካሳለፈ በኋላ እንዲህ አለን፦ “እዚህ ባላችሁ ቆይታ ሰዎቹ ለይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ጥላቻ እንዲቀንስ ማድረግ ከቻላችሁ ትልቅ ስኬት ነው።” ስለዚህ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ግባችን ይህ ሆነ። ደግሞም ተሳክቶልናል! ቀስ በቀስ ሰዎቹ ትሑት በሆኑት የይሖዋ ምሥክሮችና ኩሩ በሆኑት የካቶሊክ ቀሳውስት መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል ጀመሩ። አሁን በዚያች ከተማ አንድ ትንሽ ጉባኤ አለ።

ምንም ጉባኤ በሌለበት በዚያ ቦታ ለአንድ ዓመት ገደማ ካገለገልን በኋላ በኩዊቤክ ሲቲ በሚገኝ አንድ ትልቅ ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ ካሉት እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር ስድስት አስደሳች ወራት አሳለፍን። ከዚያም በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን።

ለቀጣዮቹ 14 ዓመታት በኩዊቤክ ግዛት ያሉ ወረዳዎችን በመጎብኘት አስደሳች ጊዜ አሳለፍን። ኩዊቤክ ውስጥ የመንግሥቱ ሥራ እየተጧጧፈ ነበር! በየጉባኤው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠኑና እድገት የሚያደርጉ ብዙ ቤተሰቦች ነበሩ።

በትጋት ያገለገሉ ወንድሞችና እህቶች

በኩዊቤክ የሚኖሩ ሰዎች ቋንቋቸው ፈረንሳይኛ ሲሆን ባሕላቸውም ለፈረንሳይ ባሕል የቀረበ ነው። በዚያ ያሉት ወንድሞችና እህቶች በጣም የሚወደዱ ናቸው። የሚሰማቸውን ፊት ለፊት የሚናገሩ፣ ደስተኛና ሞቅ ያሉ ሰዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ወደ እውነት የመጡት ብዙ ፈተና አልፈው ነው። ከባድ የቤተሰብ ተቃውሞም አጋጥሟቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ወላጆቻቸው “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናትህን ካላቆምክ ከቤት እናባርርሃለን!” ብለው አስፈራርተዋቸዋል። ደስ የሚለው ግን፣ በዚህ ዛቻ አልተሸነፉም። መቼም ይሖዋ በጣም እንደሚደሰትባቸው ምንም ጥያቄ የለውም!

በእነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት በኩዊቤክ ያገለገሉትን ታታሪ የዘወትር አቅኚዎችና ልዩ አቅኚዎች በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ። አብዛኞቹ፣ ከሌሎች የካናዳ ክፍሎች የመጡ ናቸው። ፈረንሳይኛ ቋንቋን ብቻ ሳይሆን የሰዎቹን ባሕልና አስተሳሰብም ጭምር መማር አስፈልጓቸዋል። የሰዎቹ አስተሳሰብ ደግሞ በዋነኝነት የተቀረጸው በካቶሊክ እምነት ነው።

ልዩ አቅኚዎቹ ብዙ ጊዜ የሚመደቡት ምንም አስፋፊ በሌለባቸው አካባቢዎች ነበር። ሰዎቹ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥላቻ ስላላቸው አቅኚዎቹ ቤት ለማግኘት በጣም ይቸገራሉ። ኑሯቸውን ለመደጎም የሚያስችል ሥራ ማግኘት ደግሞ ከዚያም ይበልጥ ከባድ ነው። አዲስ ተጋቢዎች እንኳ ወጪ ለመቆጠብ ሲሉ ከሌሎች ጋር ተዳብለው ይኖሩ ነበር። ብዙውን ጊዜ የሚኖሩት አራት፣ ስድስት ወይም ስምንት ሆነው ነው። አለዚያ ወጪውን አይችሉትም። እነዚያ አቅኚዎች ትጉ ነበሩ። ጥናት ሲያገኙ ጥናቱ እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። አሁን ግን ኩዊቤክ ውስጥ ብዙ አስፋፊዎች ስላሉ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ አቅኚዎች አያስፈልጉም። ስለዚህ ከእነዚያ አቅኚዎች መካከል አብዛኞቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ሌሎች ቦታዎች ሄደዋል።

ጉባኤዎችን ስንጎበኝ በአብዛኛው ቅዳሜ ጠዋት የምናገለግለው በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ነበር። ይህም እያጋጠሟቸው ስላሉት ፈተናዎች በቅርበት ለማወቅ ረድቶናል። ከእነዚያ ወጣቶች መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ በሌሎች ቦታዎች በሚስዮናዊነት ወይም በሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እያገለገሉ ነው።

በዚያ ዘመን አንዳንዶቹ ጉባኤዎች የጉዞ ወጪያችንን ለመሸፈን አቅም አልነበራቸውም። በመሆኑም በወሩ መጨረሻ አካባቢ እጃችን ላይ ምንም ገንዘብ የማይኖርበት ጊዜ ነበር። እንዲህ ባሉት ጊዜያት፣ ያለንበትን ሁኔታ የሚያውቀው ይሖዋ ብቻ ስለሆነ ያለን አማራጭ በእሱ መታመን ብቻ ነው። እሱም አሳፍሮን አያውቅም። ሁሌም ወደ ቀጣዩ ጉባኤ የምንጓዝበት መንገድ አናጣም።

ከታማኝ ወንድሞች ያገኘኋቸው ትምህርቶች

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት፣ ጊልያድ ሳለሁ የወሰድኩት ከሕዝብ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሥልጠና በጣም ጠቅሞኛል። ኩዊቤክ ውስጥ ስናገለግል በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በጋዜጦች አማካኝነት ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች አግኝተናል። ብዙውን ጊዜ፣ ሊዮንስ ክሪፖ ከተባለ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጋር አብሬ እንድሠራ እመደብ ነበር። እሱም የሚዲያ ሰዎችን እንዴት ማነጋገር እንዳለበት በደንብ ያውቃል። በዚህ ሙያ የተሰማሩ ሰዎችን ሲያነጋግር እንደ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆኖ ለመቅረብ አይሞክርም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላቸዋል፦ “እኔና ጓደኛዬ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ነን። በሚዲያ መግለጫ ስለመስጠት ያለን እውቀት በጣም ውስን ነው። የመጣነው የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያካሂዱት ትልቅ ስብሰባ ማብራሪያ እንድንሰጥ ስለተመደብን ነው። በምትችሉት መንገድ ብትረዱን ደስ ይለናል።” እንዲህ ያለው ትሕትና የተሞላበት አቀራረብ ሰዎቹ የሚችሉትን ያህል ትብብር እንዲያደርጉልን ያነሳሳቸዋል።

ከጊዜ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው የድርጅቱ ጠበቃ ከሆነው ከወንድም ግሌን ሃው ጋር እንድሠራ መደበኝ። ወንድም ግሌን የሚዲያውን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ውስብስብ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ይሠራ ነበር። በጊልያድ ያገኘሁት ሥልጠናና ከወንድም ሊዮንስ ጋር ስሠራ ያገኘሁት ተሞክሮ በዚህ ወቅት ጠቅሞኛል። ከወንድም ግሌን ጋር መሥራት ትልቅ በረከት ነው። ፍርድ ቤት ቀርቦ ለድርጅቱ ጥብቅና ሲቆም የሚያሳየው ድፍረት በጣም ያስደንቀኛል። በዋነኝነት የሚታወቀው ግን ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ያለው መንፈሳዊ ሰው በመሆኑ ነው።

በ1985 በምዕራባዊ ካናዳ በሚገኝ ወረዳ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። ይህም በዚያ አካባቢ የሚኖረውን አባቴን ለመንከባከብ አስቻለን። ሆኖም ከሦስት ወር በኋላ አባቴ አረፈ። እስከ 1989 ድረስ በምዕራባዊ ካናዳ የሚገኙ ወረዳዎችን መጎብኘታችንን ቀጠልን። ከዚያም በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። ይህ ያልጠበቅነው ነገር ነበር! ምክንያቱም ለ19 ዓመታት ያህል በወረዳ ሥራ ተካፍለናል። በእነዚያ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ውስጥ አርፈናል፤ በሺዎች ከሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ደግሞ አብረን ተመግበናል። በዚህ መልኩ እንግዳ ተቀባይነት ያሳዩንን ሁሉ በጣም ማመስገን እንፈልጋለን!

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄድን

ብሩክሊን ቤቴል ስንደርስ በአገልግሎት ዘርፍ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚያ ሳገለግል ላገኘሁት ሥልጠና በጣም አመስጋኝ ነኝ። ካገኘኋቸው ትምህርቶች አንዱ፣ ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ መረጃ ሳይኖረኝ ምንም ዓይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ እንደሌለብኝ ነው። በ1998 ደግሞ በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ። አሁንም በዚህ ክፍል ውስጥ እያገለገልኩ ሲሆን ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ ገና መማር ያለብኝ ብዙ ነገር አለ። በወቅቱ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ አስተባባሪ የነበረው ወንድም ጆን ባር ነው። ለተወሰኑ ዓመታት ከእሱ ጋር የመሥራት ልዩ መብት አግኝቻለሁ። ወንድም ጆን ባር ግሩም ክርስቲያናዊ ማንነት ነበረው። ከእሱ ያገኘሁትን ሥልጠናና አብሬው ያሳለፍኩትን ጊዜ አሁንም ድረስ እንደ ትልቅ ነገር እቆጥረዋለሁ።

ዴቪድ እና ሊንዳ ከጆን ባር እና ከሚልድሬድ ጋር ፎቶግራፍ ሲነሱ።

ከጆን ባር እና ከባለቤቱ ከሚልድሬድ ጋር

በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ከሚያገለግሉት ትሑት ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መሥራት በጣም ያስደስተኛል። ሥራቸውን ሲያከናውኑ ሁልጊዜ የይሖዋን እርዳታ በጸሎት ይጠይቃሉ። የትኛውም ሥራ የሚሳካላቸው በእነሱ ችሎታ ሳይሆን በይሖዋ መንፈስ እንደሆነ ይገነዘባሉ።

ወንድም ስፕሌን 20 ወንድሞችና እህቶች ያሉትን የመጠበቂያ ግንብ የመዘምራን ቡድን ሲያዘምር፤ አንዲት እህት ፒያኖ እየተጫወተች ነው።

በ2009 ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የመጠበቂያ ግንብ የመዘምራን ቡድንን ሳዘምር

ወንድም ስፕሌን ፈገግ ብሎ ለአንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስ ሲሰጣት።

በ2014 በሶል፣ ኮሪያ በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሳድል

እኔና ሊንዳ በ110 አገሮች የሚኖሩ ታማኝ የእምነት አጋሮቻችንን የመጎብኘት ውድ መብትም አግኝተናል። ይህም ሚስዮናውያን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር በዓይናችን የመመልከት አጋጣሚ ሰጥቶናል። በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ አስፋፊዎች ያላቸውን ቅንዓትና ጽናት ማየታችንም አስደስቶናል። ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ችግር እንዲሁም ስደት ሳይበግራቸው መንግሥቱን ያስቀድማሉ። ይሖዋ በጣም እንደሚወዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም!

ባለፉት አሥርተ ዓመታት በተለያዩ ምድቦች ሳገለግል ባለቤቴ ሊንዳ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋልኛለች። ሰው ወዳድ ናት፤ ሁሌም ሌሎችን መርዳት የምትችልባቸውን መንገዶች ትፈልጋለች። ከሰዎች ጋር ጭውውት መጀመር ትችልበታለች። ብዙ ሰዎች ወደ እውነት እንዲመጡና አንዳንድ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ወደ እውነት እንዲመለሱ መርዳትም ችላለች። በእርግጥም ከይሖዋ ያገኘኋት ውድ ስጦታ ናት! አሁን ደግሞ እኔና ሊንዳ ዕድሜያችን እየገፋ ስለሆነ ወጣት ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ መንገዶች ያግዙናል። እነሱ ለሚያደርጉልን እርዳታ በጣም አመስጋኞች ነን።—ማር. 10:29, 30

ያለፉትን 80 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ በአመስጋኝነት ስሜት እሞላለሁ። የሚከተለውን ሐሳብ ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር እስማማለሁ፦ “አምላክ ሆይ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ አስተምረኸኛል፤ እኔም እስካሁን ድረስ ድንቅ ሥራዎችህን አስታውቃለሁ።” (መዝ. 71:17) የእኔም ምኞት በሕይወት እስካለሁ ድረስ ይህን ማድረግ ነው።

a በአሁኑ ጊዜ ይህ ሥልጠና የሚሰጠው በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ