ከሰኔ 1-7, 2026
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
እየተጠሉም ደስተኛ መሆን ይቻላል?
‘ሰዎች በሚጠሏችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ።’—ሉቃስ 6:22
ዓላማ
ይሖዋን በማገልገላችን ምክንያት በምንጠላበት ጊዜ ደስተኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።
1. ኢየሱስ የትኛውን አስገራሚ ሐሳብ ተናግሯል?
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ‘ሰዎች በሚጠሏችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ’ ብሏል። (ሉቃስ 6:22) አድማጮቹ ይህን ሲሰሙ ተገርመው መሆን አለበት። ምክንያቱም መጠላት የሚፈልግ ማንም የለም። ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ መመርመራችን አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮች በብዙዎች ዘንድ የተጠሉ ናቸው። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሰዎች የሚጠሉን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ሌሎች ቢጠሉንም ደስተኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።
ሰዎች የሚጠሉን ለምንድን ነው?
2-3. እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚሰደዱበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? ይህን ማወቃችን ለሚቃወሙን ሰዎች ባለን አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? (ዮሐንስ 16:2, 3)
2 ሰዎች የሚጠሉን ይሖዋን ስለምናመልክ ነው። ኢየሱስ ሰዎች ተከታዮቹን የሚያሳድዱት አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹን የሚገድሉት ለምን እንደሆነ ሲናገር “እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 16:2, 3ን አንብብ።) በአምላክ ሕዝቦች ላይ ለሚደርሰው ስደት ዋነኛው ተጠያቂ ማን ነው? “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣን ነው። (2 ቆሮ. 4:3, 4) ሰይጣን ሰዎች ስለ ይሖዋ እውነቱን እንዳያውቁ ያሳውራቸዋል፤ እንዲሁም ይሖዋን የሚያውቁና የሚወዱ ሰዎችን እንዲቃወሙ ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። (ዮሐ. 8:42-44) ይህን ማወቃችን ለሚቃወሙን ሰዎች በሚኖረን አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? እነዚህ ሰዎች ስደት የሚያደርሱብን ተታለው እንደሆነ መገንዘባችን ለእነሱ ጥላቻ እንዳያድርብን ይረዳናል።
3 ሥራችን በታገደበት አገር ውስጥ የሚኖረውን የፓቬልንa ተሞክሮ እንመልከት። ፓቬል ይሖዋን በታማኝነት በማገልገሉ የተነሳ በቁጥጥር ሥር ውሎ ከባድ ድብደባ ደርሶበታል፤ እንዲሁም ለበርካታ ወራት ብቻውን እንዲታሰር ተደርጓል። ይህን ሁሉ ካሳለፈ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ስደት የሚደርስብን ሰይጣንና አጋንንቱ ንጹሕ አምልኮን ስለሚጠሉ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። እስር ቤት ውስጥ የሚሠሩት አብዛኞቹ ሰዎች ለእኛ ጥላቻ የላቸውም። እነዚያን ነገሮች የሚያደርጉት ሥራቸው ስለሚጠይቅባቸው ብቻ ነው።” በክሮኤሺያ የሚኖር አንድ ወንድም ደግሞ አማኝ ካልሆኑት ወላጆቹ ከባድ ስደት ደርሶበታል። እንዲህ ብሏል፦ “ጠላቴ ሰይጣን እንጂ ወላጆቼ እንዳልሆኑ ተገንዝቤያለሁ።”—ኤፌ. 6:12
4. ኢየሱስና እስጢፋኖስ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 እኛም የሚቃወሙንን ሰዎች አንጠላቸውም። እንዲያውም እንጸልይላቸዋለን። (ማቴ. 5:44) ኢየሱስና እስጢፋኖስ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተቸንክሮ ሳለ “አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው” በማለት ጸልዮአል። (ሉቃስ 23:34) ኢየሱስ ይህን ሲል እሱን እንዲገድሉ ትእዛዝ የተሰጣቸውን ወታደሮች ይሖዋ ይቅር እንዲላቸው መጠየቁ ነበር። በተጨማሪም ይህን ጸሎት ያቀረበው ጠላቶቹ ባደረሱባቸው ግፊት ተነሳስተው “ይሰቀል” እያሉ ይጮኹ የነበሩትን ሰዎች በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን እንደማያውቁ ተገንዝቦ ነበር። ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስም ሊገድሉት የተዘጋጁትን ሰዎች አምላክ ይቅር እንዲላቸው ጸልዮአል። (ሥራ 7:58-60) ታዲያ ኢየሱስና እስጢፋኖስ ያቀረቡትን ጸሎት ይሖዋ መልሶላቸዋል? አዎ። ኢየሱስ እንዲገደል ጥያቄ ያቀረቡ ብዙ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ንስሐ ገብተው፣ በኢየሱስ አምነው ተጠምቀዋል። (ሥራ 2:36-41) በሌላ በኩል ደግሞ፣ በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምተው ከነበሩት ሰዎች ቢያንስ አንዱ ማለትም የጠርሴሱ ሳኦል ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ሆኗል፤ ባለማወቅ ለፈጸማቸው በርካታ አስከፊ ነገሮችም ከልቡ ተጸጽቷል።—1 ጢሞ. 1:13
ኢየሱስና ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ላሳደዷቸው ሰዎች እንደጸለዩት ሁሉ እኛም ለሚያሳድዱን ሰዎች መጸለይ እንችላለን (አንቀጽ 4ን ተመልከት)
5. ከሴዛር ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
5 ይሖዋ በዛሬው ጊዜም የሚቃወሙንን ሰዎች አስመልክቶ የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል። በቬኔዙዌላ የሚኖረውን የሴዛርን ተሞክሮ እንመልከት። አባቱ እውነትን አጥብቆ ይቃወም ነበር። ሴዛር እንዲህ ብሏል፦ “እናቴ ጥሩ ሚስትና ጥሩ እናት ነበረች። የመንግሥቱን ጉዳዮች ሁልጊዜ የምታስቀድም ቢሆንም የሚስትነት ኃላፊነቷን ችላ ብላ አታውቅም። እኛንም አባታችንን እንድናከብረው አስተምራናለች። የአምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ እስካልጠየቀን ድረስ ልንታዘዘው እንደሚገባ ትነግረን ነበር።” ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የሴዛር አባት እየለሰለሰ መጣ። ሴዛር እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቀን ልባዊ ጸሎት ካቀረብኩ በኋላ አባቴን ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ጠየቅኩት። እሱም እሺ አለኝ። በዚህ ጊዜ የተሰማኝን ስሜት ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል።” በኋላ የሴዛር አባት ተጠመቀ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ለውጥ የሚያደርጉት ሁሉም ተቃዋሚዎች አይደሉም። ሆኖም አንዳንዶቹ አክብሮት የሚንጸባረቅበትን አነጋገራችንንና መልካም ምግባራችንን ሲያዩ አመለካከታቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ። እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ ደግሞ በጣም እንደሰታለን። “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነው መሐሪው አምላካችን ይሖዋ ወደፊትም እንዲህ ያሉ ሰዎችን ወደ ራሱ ሲስብ ለማየት እንጓጓለን።—ዘፍ. 18:25
6. በማርቆስ 13:13 መሠረት ሰዎች እኛን የሚጠሉበት ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?
6 ሰዎች የሚጠሉን ኢየሱስን እንደ ንጉሣችን አድርገን ስለምንቀበል ነው። ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች “[በስሙ] የተነሳ” በሰዎች ሁሉ ዘንድ እንደሚጠሉ ተናግሯል። (ማርቆስ 13:13ን አንብብ።) የኢየሱስ “ስም” ምን ያመለክታል? ማንነቱን እንዲሁም ሥልጣኑን ማለትም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል። ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን የጽንፈ ዓለሙ ገዢ አድርጎ የመረጠው ሲሆን ከ1914 አንስቶ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል። ሆኖም ብዙዎቹ ሰዎች የእሱን ሥልጣን ከመቀበል ይልቅ እምነታቸውን በሰብዓዊ መሪዎች ላይ ይጥላሉ። እኛ ግን የተለየ አቋም አለን፤ በዚህም የተነሳ ይጠሉናል። በቅርቡ ኢየሱስ የእሱን አገዛዝ የማይቀበሉትን መንግሥታት በሙሉ ያጠፋል።
7-8. አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ፌዝ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 15:18-20) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
7 ሰዎች የሚጠሉን ከሰይጣን ዓለም የተለየን በመሆናችን ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል ባለመሆናቸው’ ዓለም እንደሚጠላቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:18-20ን አንብብ።) እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም በዓለም ላይ ተስፋፍቶ ከሚታየው መጥፎ አስተሳሰብ፣ አነጋገርና ምግባር እንርቃለን። በዚህም የተነሳ በርካታ ወንድሞችና እህቶች በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ይፌዝባቸዋል። (1 ጴጥ. 4:3, 4) ደስ የሚለው ግን፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ውሎ አድሮ አመለካከታቸውን በመቀየር አቋማችንን ማድነቅ ይጀምራሉ።
8 በማዕከላዊ አሜሪካ የሚኖረውን የኢግናሲዮን ተሞክሮ እንመልከት። ኢግናሲዮ የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ስለሚከተል አስተማሪው ለዓመታት ያሾፍበት ነበር። ሆኖም ኢግናሲዮ ትምህርቱን የሚጨርስበት ጊዜ ሲቃረብ አስተማሪው ይሄ ሁሉ ፌዝ እየደረሰበት የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ማክበሩን ሊቀጥል የቻለው እንዴት እንደሆነ ኢግናሲዮን ጠየቀው። እሱም ይህን ለማድረግ የረዳው የአምላክ ሕጎች ከመጥፎ ነገሮች እንደሚጠብቁት ማስታወሱ እንደሆነ ነገረው። ከዚያም በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ አስተማሪውን ጋበዘው። አስተማሪውም በስብሰባ ላይ ተገኘ። ኢግናሲዮም ይህን ሲያይ በጣም ተገረመ። አስተማሪው በጉባኤ ውስጥ ያየው ፍቅር ልቡን በጣም ስለነካው በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ቀጠለ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። የሚገርመው እሱም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቱ ምክንያት ተቃውሞ ይደርስበት ጀመር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ እድገት አድርጎ ተጠመቀ።
ወጣትም ሆንን አዋቂ ለእምነታችን በድፍረት ጥብቅና መቆም እንችላለን (አንቀጽ 8ን ተመልከት)b
9-10. (ሀ) ክርስቲያኖች ከሰይጣን ዓለም የሚለዩበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
9 ከሰይጣን ዓለም የተለየን እንድንሆን የሚያደርገን ሌላው ነገር የገለልተኝነት አቋማችን ነው። በፖለቲካዊ ጉዳዮችና በጦርነት አንካፈልም። (ዮሐ. 18:36) በሮም 13:1 ላይ በተመከርነው መሠረት ሕግ አክባሪ ዜጎች ለመሆን ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን በፖለቲካዊ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ አንገባም፤ ለፖለቲካዊ ምርጫ አንወዳደርም፤ ወይም ለተመራጮች ድምፅ አንሰጥም። ለምን? ምክንያቱም ለይሖዋና በክርስቶስ ለሚመራው መንግሥቱ ታማኞች መሆን እንዳለብን እናውቃለን። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ሆኖም እስር ቤት ውስጥ ሆነውም መስበካቸውን አላቆሙም። በዚህ መንገድ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ይከተላሉ። ጳውሎስ ለበርካታ ዓመታት በቁም እስርና በወህኒ ቤት ቆይቷል። (ሥራ 24:27፤ 28:16, 30) ሆኖም ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ምሥራቹን መስበኩን ቀጥሏል፤ ለምሳሌ ለእስር ቤት ጠባቂዎች፣ ለሕግ አካላት፣ ለአገረ ገዢዎች፣ ለነገሥታት፣ ምናልባትም ለንጉሠ ነገሥት ኔሮ ባለሟሎችም ጭምር ሰብኳል።—ሥራ 9:15
10 በተመሳሳይም በእስር ላይ ያሉ ወንድሞቻችን ዳኞችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና የእስር ቤት ጠባቂዎችን ጨምሮ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ሁሉ ምሥራቹን ይሰብካሉ። በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ከስድስት ዓመት በላይ የታሰረ አንድ ወንድም እስራቱን እንደ ቅጣት ሳይሆን ከይሖዋ እንደተቀበለው ምድብ አድርጎ እንደሚመለከተው ተናግሯል። ይሖዋ ወደዚያ የላከው በግ መሰል ሰዎችን እንዲፈልግ ብሎ እንደሆነ ተሰምቶታል። እኛም ይሖዋ እንዲህ ላሉት ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ ከተጠቀመብን በጣም ደስ ይለናል! (ቆላ. 4:3) ከዚህ በመቀጠል፣ ይሖዋን በማገልገላችን ምክንያት ብንጠላም ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉንን ተጨማሪ ምክንያቶች እንመለከታለን።
ሌሎች ቢጠሉንም ደስተኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
11. የሚደርስብን ስደት እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
11 ዓለም የሚጠላን መሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ እናውቃለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው ትንቢት ሰይጣንና ተከታዮቹ ይሖዋን የሚወዱና የሚያገለግሉ ሰዎችን እንደሚጠሉ ይናገራል። (ዘፍ. 3:15) በአራቱም ወንጌሎች ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ኢየሱስም ይህን ሐሳብ በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ማቴ. 10:22፤ ማር. 13:9-12፤ ሉቃስ 6:22, 23፤ ዮሐ. 15:20) ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ቢሆኑ ይህንኑ ሐሳብ ተናግረዋል። (2 ጢሞ. 3:12፤ ያዕ. 1:2፤ 1 ጴጥ. 4:12-14፤ ይሁዳ 3, 17-19) ስለዚህ ስደት ሲደርስብን ከመደናገጥ ይልቅ እንደሰታለን። ምክንያቱም ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በእኛ ላይ እየተፈጸመ መሆኑ እውነተኛውን አምላክ እያገለገልን እንዳለ ያረጋግጥልናል። በሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉበት አገር ውስጥ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ራሴን ለይሖዋ በወሰንኩበት ወቅት፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በእኔም ላይ ስደት መድረሱ እንደማይቀር ገብቶኝ ነበር። ስለዚህ ያጋጠሙኝ ፈተናዎች በፍርሃት እንድዋጥም ሆነ እንድደናገጥ አላደረጉኝም።” እህታችንን ከተቃወሟት በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ባለቤቷ ነው። መጽሐፍ ቅዱሷንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቿን አቃጥሎባታል፤ እንዲሁም ሌሎች በደሎች አድርሶባታል። ሆኖም እህታችን በፍርሃት ከመሽመድመድ ይልቅ እምነቷ እየተጠናከረ ሄዷል። (ዕብ. 10:39) እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክ አገልጋዮች ስደት እንደሚደርስባቸው በትንቢት ተነግሯል፤ ስለዚህ ይህ ትንቢት መፈጸሙ የግድ እንደሆነ አውቅ ነበር። ይህ ስደት በእኔ ላይ መድረሱ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።”
12. አንድ ወንድም የደረሰበትን ስደት በጽናት እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው?
12 ስደት እንደሚደርስብን የምንጠብቅ ቢሆንም ስደቱ አፍጥጦ ሲመጣ ግን መቋቋም ሊከብደን ይችላል። አንድ ወንድም በእስር ያሳለፈውን ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በሐዘን ወይም በጭንቀት ተውጬ የማለቅስባቸው ጊዜያት ነበሩ።” ታዲያ ወንድማችን እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ሁልጊዜ እጸልይ ነበር። እያንዳንዱን ዕለት የምጀምረው በጸሎት ነው። ቀን ላይም አስቸጋሪ ሁኔታ ባጋጠመኝ ቁጥር እጸልያለሁ። የሚፈጸምብኝ ግፍ ሲያበሳጨኝ መጸዳጃ ቤት ውስጥ እገባና በሩን ቆልፌ እጸልያለሁ።” ወንድማችን በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን በኖሩ ታማኝ ሰዎች ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉም ጠቅሞታል። እንዲህ ማድረጉ የሚያጋጥመውን ስደት ለመቋቋምና ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንደሚሰጣቸው ቃል የገባውን ሰላም ለማግኘት ረድቶታል።—ዮሐ. 14:27፤ 16:33
13. ጥላቻን ለማሸነፍ የሚረዳን ምንድን ነው?
13 ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ከጥላቻ የበለጠ ኃይል አለው። ኢየሱስ የመጨረሻ እስትንፋሱን እስከተነፈሰበት ሰዓት ድረስ አባቱን በሙሉ ልቡ ይወደው ነበር። ኢየሱስ ለወዳጆቹም ፍቅር ነበረው። (ዮሐ. 13:1፤ 15:13) እኛም ለይሖዋ እንዲሁም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን እንዲህ ያለ ፍቅር ካዳበርን የሌሎችን ጥላቻ ማሸነፍ እንችላለን። እንዴት? እስቲ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት።
14. ጳውሎስ ሞትን በድፍረት እንዲጋፈጥ የረዳው ምንድን ነው?
14 ጳውሎስ ከመገደሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ለውድ ወዳጁ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “አምላክ [የኃይልና የፍቅር] መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም።” (2 ጢሞ. 1:7) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን ለይሖዋ ጠንካራ ፍቅር ካለው ከባድ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ እንደሚሆን መናገሩ ነው። (2 ጢሞ. 1:8) ጳውሎስም እውነተኛውን አምልኮ ሳይተው ሞትን በድፍረት እንዲጋፈጥ የረዳው ለይሖዋ ያለው ፍቅር ነው።—ሥራ 20:22-24
15. በዘመናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለወንድሞቻቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 ስደት ቢያጋጥማቸውም በታማኝነት የጸኑ የእምነት አጋሮቻችንን በጣም እንወዳቸዋለን። አቂላና ጵርስቅላ ጳውሎስን ለመርዳት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው እንደነበር ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ራሳቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ። (ሮም 16:3, 4) ለምሳሌ ሩሲያ ውስጥ ወንድሞቻችን ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት በርካታ የእምነት አጋሮቻቸው እነሱን ለማበረታታት ይመጣሉ። አንዲት እህትም ታስራ ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ብዙ ወንድሞችና እህቶች እሷን ለማበረታታት ሄደው ነበር። ይህን ስታይ ልቧ ከመነካቱ የተነሳ መናገር እንኳ አቃታት። የእምነት አጋሮቿ ያሳዩአት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማበረታቻ በጣም ባስፈለጋት ጊዜ እንድትበረታታ ረድቷታል። በእርግጥም ከጥላቻ የበለጠ ኃይል ያለው ፍቅር በመካከላችን በመኖሩ በጣም ደስተኞች ነን!
በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ በተጣለባቸው አገሮችም ጭምር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለእምነት አጋሮቻቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያሉ (አንቀጽ 15ን ተመልከት)c
16. ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክን በማገልገላቸው ምክንያት ስደት የሚደርስባቸው ሰዎች ደስተኞች እንደሆኑ የተናገረው ለምንድን ነው? (1 ጴጥሮስ 4:14)
16 ጥላቻን በጽናት መቋቋማችን የአምላክን ሞገስ እንደሚያስገኝልን እናውቃለን። (1 ጴጥሮስ 4:14ን አንብብ።) ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክን በማገልገላቸው ምክንያት ስደት የሚደርስባቸው ሰዎች ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። ለምን? ምክንያቱም ስደት የሚደርስብን መሆኑ ‘የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ እንዳረፈ’ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ጴጥሮስ የአምላክን ሞገስ እንዳገኘ ማወቁ ስደትን ለመቋቋም ረድቶታል። በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት እየሰበኩ ሳሉ የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው። ሆኖም ጴጥሮስ በድፍረት ለእምነቱ ጥብቅና ቆሟል። (ሥራ 5:24-29) እሱና ሌሎቹ ሐዋርያት ከተገረፉ በኋላም እንኳ መስበካቸውን አላቆሙም። ከዚህ ይልቅ “ስለ [ኢየሱስ ስም] ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ደስ ብሏቸዋል። እኛም ፈተናን በጽናት ስንቋቋም ደስተኞች መሆን እንችላለን።—ሥራ 5:40-42
17. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ደቀ መዛሙርቱን ምን ብሏቸዋል?
17 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔን የሚወደኝን ሁሉ . . . አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ።” (ዮሐ. 14:21) በቅርቡ ደግሞ፣ ይሖዋን በማገልገላችን ምክንያት የሚወደን እንጂ የሚጠላን አንድም ሰው አይኖርም። ያን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (2 ተሰ. 1:6-8) እስከዚያው ድረስ ግን ሌሎች ቢጠሉንም እንኳ ደስተኛ ለመሆን የሚያበቁ ብዙ ምክንያቶች አሉን። በእነዚህ ምክንያቶች ላይ ማሰላሰላችን ማጽናኛና ብርታት ለማግኘት ይረዳናል።
መዝሙር 149 የድል መዝሙር
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢግናሲዮ ለአስተማሪው ሲመሠክርለት የሚያሳይ ትወና።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ በእምነቷ ምክንያት ወደ እስር ቤት እየተወሰደች ያለችን እህት ለማበረታታት የመጡ ወንድሞችና እህቶችን የሚያሳይ ትወና።