የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 የካቲት ገጽ 2-7
  • አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በርኅራኄ ተነሳስተህ እርዳቸው
  • ስሜትህን የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉ ሁኔታውን በጥሩ መንገድ ያዘው
  • ታጋሽና አዎንታዊ ሁን
  • እንደምትወዳቸው አሳያቸው
  • በቤተሰቦችህ ላይ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥባቸው
  • ሰላምን ሳይሆን ሰይፍን የሚያመጣው እውነት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2025-2026 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚገኝበት
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • ከመሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አሁንም መማር ትችላለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 የካቲት ገጽ 2-7

ከሚያዝያ 6-12, 2026

መዝሙር 82 “ብርሃናችሁ ይብራ”

አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

“ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”—ገላ. 6:9

ዓላማ

አማኝ ካልሆኑ ቤተሰቦቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት ይዘን መቀጠልና ከተቻለም እነሱን በመንፈሳዊ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

1-2. እውነትን ስንማር ከቤተሰቦቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ሊሻክር የሚችለው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ተከታዩ መሆን እንደሚፈልግ ለገለጸ አንድ ሰው እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ወደ ቤት ሄደህ ይሖዋ ያደረገልህን ነገር ሁሉ . . . ለዘመዶችህ ንገራቸው።” (ማር. 5:19) ኢየሱስ የተናገረው ነገር የሰው ልጆች ያላቸውን አንድ ተፈጥሯዊ ባሕርይ የሚያጎላ ነው፤ መልካም ነገር ሲያጋጥመን ለቤተሰቦቻችን ለመናገር እንጓጓለን።

2 ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን ስትማር ምን እንደተሰማህ ትዝ ይልሃል? የተማርከውን ነገር ለሌሎች ለመናገር በጣም እንደጓጓህ ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ቤተሰቦችህ በጎ ምላሽ አልሰጡህ ይሆናል። ወይም ደግሞ እውነትን ለእነሱ ለመናገር የሞከርክበት መንገድ በመካከላችሁ ግጭት እንዲፈጠር አድርጎ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ክርስቲያናዊ አቋምህን ሳታላላ ከቤተሰቦችህ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመለከታለን፦ (1) ርኅራኄ አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንa በጎ ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜም እንኳ ትኩረት ሰጥተን እንድንረዳቸው የሚያነሳሳን እንዴት ነው? (2) ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉ ሁኔታውን እንዴት መያዝ ይኖርብናል? (3) ትዕግሥተኛና አዎንታዊ መሆናችን ቤተሰቦቻችን እውነትን እንዲማሩ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? (4) እንደምንወዳቸው ልናሳያቸው የምንችለው እንዴት ነው?

በርኅራኄ ተነሳስተህ እርዳቸው

4. ኢየሱስ ለመልእክቱ ግድየለሽ የነበሩ ሰዎችን የያዛቸው በምን መንገድ ነው?

4 ኢየሱስ ለመልእክቱ ግድየለሽ የነበሩ ሰዎችን ቶሎ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። ፍሬ አላፈራ ያለች አንዲት የበለስ ዛፍ እንድታፈራ ለማድረግ ሲል ከፍተኛ ጥረት ካደረገ የወይን አትክልት ሠራተኛ ጋር ራሱን አመሳስሏል። (ሉቃስ 13:6-9) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ በተናገረበት ወቅት አይሁዳውያን ወገኖቹ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ከሦስት ዓመት በላይ በትጋት ሲሠራ ቆይቶ ነበር። እነሱን ለመርዳት መሞከሩን የቀጠለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ለሰዎች ርኅራኄ ነበረው። ይህም እነሱን በትዕግሥት እንዲይዛቸው አነሳስቶታል።

5. ኢየሱስ ለአይሁዳውያን ወገኖቹ ርኅራኄ እንዲያሳይ ያነሳሳው ምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ለአይሁዳውያን ወገኖቹ የራራላቸው የሃይማኖት መሪዎቻቸው በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት እንዲያዳብሩ እንዳልረዷቸው ስላስተዋለ ነው። ኢየሱስ ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” መሆናቸውን ተመልክቷል። (ማር. 6:34) እንዲያውም ኢየሱስ አብዛኞቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እምነት የለሽ በመሆናቸው ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ስላወቀ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለኢየሩሳሌም ከተማ አልቅሶላታል። (ሉቃስ 19:41-44) እኛም ለቤተሰቦቻችን እንዲህ ያለ ርኅራኄ ካዳበርን እነሱን ለመርዳት እንነሳሳለን።

6. አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን በትዕግሥት ልንይዛቸው የሚገባው ለምንድን ነው? (ገላትያ 6:9)

6 ገላትያ 6:9ን አንብብ። ቤተሰቦቻችን ስለ እምነታችን ለማወቅ እስካሁን ፍላጎት ባይኖራቸውም ትዕግሥት ልናሳያቸው እንዲሁም ‘ተስፋ ሳንቆርጥ መልካም ሥራ መሥራታችንን’ ልንቀጥል ይገባል። ሥር የሰደደ ጥላቻን ማስወገድና እምነት ማዳበር ጊዜ እንደሚወስድ እናውቃለን። አንተስ በአንድ ወቅት “በዓለም ውስጥ ያለተስፋና ያለአምላክ” ትኖር ነበር? (ኤፌ. 2:12) ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ስለ ይሖዋ ልትማር የቻልከው አንድ ሰው ስለረዳህ ነው። ታዲያ የሚቻል እስከሆነ ድረስ አንተም ቤተሰቦችህን በዚህ መልኩ ልትረዳቸው አትፈልግም?

ስሜትህን የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉ ሁኔታውን በጥሩ መንገድ ያዘው

7. የኢየሱስ ወንድሞች እንዳያምኑበት እንቅፋት የሆነባቸው ምን ሊሆን ይችላል?

7 የኢየሱስ ወንድሞች ኢየሱስ በገሊላ ስለፈጸማቸው ተአምራት ሰምተው መሆን አለበት። (ሉቃስ 4:14, 22-24) ነገር ግን መጀመሪያ ላይ አላመኑበትም ነበር። (ዮሐ. 7:5) ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን አይነግረንም። ሆኖም አንዳንድ አይሁዳውያን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዳይሆኑ እንቅፋት የሆኑባቸውን ቢያንስ ሁለት ነገሮች ይገልጽልናል። አንዳንዶቹ በማኅበረሰቡ እንዳይገለሉ ይፈሩ ነበር። (ዮሐ. 9:18-22) ሌሎች ደግሞ ኢየሱስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለሚያውቁት የአምላክ ወኪል ነው ብለው ማሰብ ከብዷቸው ነበር። (ማር. 6:1-4) የኢየሱስ ወንድሞችንም ተጽዕኖ ያሳደረባቸው እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል። የእኛ ቤተሰቦችስ እውነትን እንዳይቀበሉ እንቅፋት የሆኑባቸው እንዲህ ያሉት ምክንያቶች ይሆኑ?

8. አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችን ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር እንዲናገሩ ወይም እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ምን ሊሆን ይችላል?

8 ከንግግራቸውና ከድርጊታቸው በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት ከግምት አስገባ። ኢየሱስ “አእምሮውን ስቷል” ብለው ከተናገሩት ዘመዶቹ መካከል ወንድሞቹም ይገኙበት ይሆናል። (ማር. 3:21) እንዲህ ብለው ያሰቡት ለምን ሊሆን ይችላል? ከአውዱ እንደምንረዳው ኢየሱስ ሕዝቡን በማስተማርና የታመሙትን በመፈወስ ከመጠመዱ የተነሳ ምግብ ለመብላት እንኳ ጊዜ አልነበረውም። (ማር. 3:20) ታዲያ ዘመዶቹ ይህን ሲያዩ ጽንፈኛ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆን? ሊሆን ይችላል። የእኛ ቤተሰቦችም በጣም አክራሪ እንደሆንን ይሰማቸው ይሆናል። እንዲህ የሚሰማቸው ከሆነ፣ ሚዛናዊ ሰዎች እንደሆንን በተግባራችን ልናሳያቸው እንችላለን።

9. ቤተሰቦቻችን ለእኛ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 ጥሩ ምግባር ማሳየትህን ቀጥል። በንግግርም ሆነ በተግባር ደግነት ማሳየታችን ቤተሰቦቻችን ለእኛ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2ን አንብብ።) አማኝ ያልሆነ ባል፣ ሚስቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝ ወይም አገልግሎት ስትወጣ ችላ እንደተባለ ሊሰማውና ሊበሳጭ ይችላል። ሚስቱ እንዲህ ያለ ስሜት እንዳያድርበት ለማድረግ ስትል በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምትካፈልበትን ፕሮግራም አስተካክላ ከእሱ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ልትሞክር ትችላለች። ለምሳሌ ባሏ ሥራ ላይ በሚሆንበት ወይም ቤት በማይኖርበት ጊዜ አገልግሎት ለመውጣት ልትወስን ትችላለች። አንዲት ክርስቲያን ሚስት ምክንያታዊና እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆን ባለቤቷ ለይሖዋ ምሥክሮች ያለውን አመለካከት እንዲቀይር ልትረዳው ትችል ይሆናል።

ሥዕሎች፦ 1. አንዲት እህት የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባሏ ወደ ሥራ ከመሄዱ በፊት ይዞት የሚሄደው ምሳና ቡና ስታዘጋጅለት። 2. በኋላ ላይ ከሌላ እህት ጋር አብራ ታገለግላለች፤ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ላገኘቻት ሴት ከስልኳ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ እያሳየቻት ነው።

በንግግራችንና በተግባራችን ደግነት የምናሳይ ከሆነ አማኝ ያልሆነ የትዳር አጋራችን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያለውን አመለካከት እንዲቀይር ልንረዳው እንችላለን (አንቀጽ 9ን ተመልከት)g


10. ሌሎች ትችት ሲሰነዝሩብን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

10 ለሚሰነዘርብህ ትችት ሁሉ ምላሽ መስጠት እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ኢየሱስ ከልክ በላይ እንደሚበላና እንደሚጠጣ የሚገልጽ የሐሰት ክስ በተሰነዘረበት ወቅት ክሱ ስህተት መሆኑን ለማሳየት አልታገለም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች እውነታውን በራሳቸው እንዲመለከቱ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 11:19) በተጨማሪም ሚዛናዊ ሕይወት እንደሚመራ በተግባር አሳይቷል። (ከዮሐንስ 2:2, 6-10 ጋር አወዳድር።) አንተም ለሚሰነዘርብህ ትችት ሁሉ ምላሽ መስጠት እንዳለብህ አይሰማህ። ከዚህ ይልቅ ሚዛናዊና ደስተኛ እንደሆንክ ለቤተሰቦችህ በአኗኗርህ አሳያቸው፤ ከዚያም የራሳቸው መደምደሚያ ላይ መድረስ ይችላሉ። ስለ እኛ የሰሙት ነገር የተሳሳተ እንደሆነ ይገነዘቡ ይሆናል።

ታጋሽና አዎንታዊ ሁን

11. ኢየሱስ አማኝ ያልሆኑ ወንድሞቹን የያዛቸው በምን መንገድ ነው?

11 የወንጌል ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ኢየሱስ ወንድሞቹን እስከ መጨረሻው በትዕግሥት ይዟቸዋል። ለምሳሌ በቃና የመጀመሪያ ተአምሩን በፈጸመበት ወቅት እነሱም በዚያ እንደነበሩ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ዮሐ. 2:11, 12) ሆኖም ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የኢየሱስ ወንድሞች አላመኑበትም። ያም ቢሆን ኢየሱስ ከእነሱ ጋር አልተቆራረጠም። በቃና የመጀመሪያ ተአምሩን ከፈጸመ ከሦስት ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ወንድሞቹን በደግነት እንዳነጋገራቸው የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እናገኛለን።—ዮሐ. 7:5-8

12. ከቤተሰቦቻችን መካከል አንዳንዶቹ አንድ ቀን እውነትን ይቀበላሉ የሚል አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ምን ሊረዳን ይችላል?

12 ስለ ይሖዋ ምሕረት ያገኘነው ግንዛቤ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። የሐሰት ሃይማኖት ሲጠፋ ቤተሰቦቻችን ስለዚህ ክንውን ነግረናቸው እንደነበር ያስታውሱ ይሆናል።b (ራእይ 17:16) እንዲያውም ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ አብረውን በንጹሕ አምልኮ መካፈል ሊጀምሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ቤተሰቦቻችን በአሁኑ ወቅት ችግር ሲያጋጥማቸው እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። ከልባችን እንደምንወዳቸውና እንደምናስብላቸው ሲያስተውሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

እንደምትወዳቸው አሳያቸው

13. በይሖዋ አገልግሎት ሰፊ ጊዜ ብናሳልፍም ስለ ምን ነገር ልንጠነቀቅ ይገባል?

13 በይሖዋ አገልግሎት ሰፊ ጊዜ ብናሳልፍም ቤተሰቦቻችን ለእነሱ ጊዜ እንደሌለን ወይም ለእነሱ ያለን ፍቅር እንደቀነሰ እንዲሰማቸው አንፈልግም። (ማቴ. 7:12) ታዲያ እንደምናስብላቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ መንገዶችን እስቲ እንመልከት።

14-15. አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

14 አዘውትረህ አነጋግራቸው፤ እንዲሁም ፍቅርህን ግለጽላቸው። ቤተሰቦቻችን በየጊዜው ስላለንበት ሁኔታ እንዲያውቁ በማድረግ እንደምንወዳቸው እናሳያለን። ለምሳሌ የጽሑፍ መልእክትና አንዳንድ ፎቶግራፎችን ልንልክላቸው እንችል ይሆናል፤ ምናልባት ሽርሽር ሄደን ወይም ከጓደኞቻችን ጋር ሰብሰብ ብለን ስንጫወት የተነሳናቸውን ፎቶግራፎች ልንልክላቸው እንችላለን። ትንሽ ስጦታ መስጠታችን ወይም ደግነት የሚንጸባረቅበት ደብዳቤ መላካችን ብቻ እንኳ ግንኙነታችን እንዲሻሻል ሊያደርግ ይችላል። ቅድሚያውን ወስደን እንዲህ ያሉ ነገሮችን ስናደርግ እንደምንወዳቸው ማየት ይችላሉ።

15 በአርሜኒያ የምትኖረውን የአናን ምሳሌ እንመልከት። ቤተሰቦቿ በተለይ በልደትና በበዓላት ወቅት አብረው ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። አና እውነትን ስትቀበል ቤተሰቦቿ አዲሱ ሃይማኖቷ ከእነሱ እንደሚያርቃት በማሰብ ሰግተው ነበር። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር መሆኗ ሕይወቷን ከባድ እንደሚያደርግባት ተሰምቷቸው ነበር። ታዲያ አና የረዳቻቸው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ስሄድ ስለ ሕይወቴ እንዲሁም ስላከናወንኳቸው ነገሮች እነግራቸዋለሁ። በተጨማሪም ቤቴ ጋብዤ ከጓደኞቼ ጋር አስተዋውቃቸዋለሁ። በዚህም የተነሳ ከቤተሰቦቼ መካከል አብዛኞቹ ጓደኞቼን ያውቋቸዋል እንዲሁም ይግባቧቸዋል። ብዙዎቹ የቤተሰቤ አባላት ደስተኛ መሆኔን እንዳስተዋሉ ነግረውኛል፤ በመሆኑም ስለ እኔ መጨነቃቸውን አቁመዋል።”

16. ኢየሱስ ለወንድሙ ለያዕቆብ ትኩረት የሰጠው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

16 ትኩረት ስጣቸው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወንድሙን ያዕቆብን በግል ሄዶ በማነጋገር ትኩረት ሰጥቶታል። (1 ቆሮ. 15:7) ያዕቆብ፣ ኢየሱስ ተስፋ እንዳልቆረጠበት ሲገነዘብ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? ያዕቆብ፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያመነው በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ከዚያ በኋላ ያዕቆብ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላትም የኢየሱስን ማንነት እንዲገነዘቡ ረድቷቸው ሊሆን ይችላል።c—ሥራ 1:14

17. በሮም 12:15 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 ሮም 12:15ን አንብብ። ቤተሰቦቻችን ይበልጥ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ማለትም በደስታና በሐዘን ወቅት ከጎናቸው ከሆንን ለእኛ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ ልንረዳቸው እንችል ይሆናል።d ለምሳሌ ልጅ ከወለዱ ደስታችንን በመግለጽ እንዲሁም ስጦታ በመስጠት የደስታቸው ተካፋይ እንደሆንን ማሳየት እንችላለን። ቤተሰቦቻችን ሐዘን ካጋጠማቸው በሚያጽናና መንገድ ልናነጋግራቸው፣ ተግባራዊ እርዳታ ልንሰጣቸው ወይም የሚያጽናና መልእክት ልንልክላቸው እንችላለን። በተጨማሪም በተለይ ችግር ውስጥ ሲሆኑ አዘውትረን ልንደውልላቸው እንዲሁም ሄደን ልንጠይቃቸው እንችላለን።

ቀደም ባሉት ሥዕሎች ላይ የነበረችው እህት የይሖዋ ምሥክር ካልሆነው ባሏና ከአማቷ ጋር ሰልፊ እየተነሳች ነው፤ አማቷ ዊልቼር ላይ ተቀምጣለች።

ቤተሰቦቻችን እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ትኩረት ከሰጠናቸው ለእኛና ለእምነታችን ያላቸውን አመለካከት ሊቀይሩ ይችላሉ (አንቀጽ 17ን ተመልከት)h


በሠርግ ወይም በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ይኖርብሃል?

ቤተሰቦች በሠርግና በለቅሶ ላይ መሰብሰባቸው የተለመደ ነገር ነው። ከዚህ ጋር በተያያዙ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመገኘት ከመወሰንህ በፊት የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግምት ማስገባት ትችላለህ።

  • ፕሮግራሙ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓትን ያካተተ ነው? (2 ቆሮ. 6:14, 15)

  • በፕሮግራሙ ላይ ብትገኝ ሃይማኖታዊ በሆኑ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ልማዶች እንድትካፈል የሚደረግብህን ጫና መቋቋም ትችላለህ? (ምሳሌ 22:3)

  • አማኝ ያልሆኑ ዘመዶችህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ልማዶች እንደማትካፈል ያውቃሉ?

  • በአምልኮ ቦታ ውስጥ በሚካሄድ ፕሮግራም ላይ ብትገኝ የእምነት አጋሮችህ ውሳኔህን በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? (ፊልጵ. 1:10)

ውሳኔህ ምንም ይሁን ምን አቋምህን ለቤተሰቦችህ በግልጽና በዘዴ አስረዳቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ውሳኔህ በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና ለመያዝ የሚያስችልህ እንዲሆን ጥረት አድርግ።f

18. ደቀ መዝሙሩ እንድርያስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

18 ከእምነት አጋሮችህ ጋር አስተዋውቃቸው። ደቀ መዝሙሩ እንድርያስ፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ሲገነዘብ ወዲያውኑ ወንድሙን ጴጥሮስን ከኢየሱስ ጋር አስተዋውቆታል። (ዮሐ. 1:40-42) እኛስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችል ይሆን? ለምሳሌ ቤተሰቦቻችንን አልፎ አልፎ ስብሰባ ልንጋብዛቸው እንችላለን፤ ወይም ደግሞ ጓደኞቻችንን ቤታችን ስንጋብዝ እነሱንም አብረን ልንጋብዛቸው እንችል ይሆናል። ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ስናስተዋውቃቸው የይሖዋ ምሥክሮች ልክ እንደ ማንኛውም ሰው እንደሆኑና ጥሩ ሰዎች እንደሆኑ ማስተዋል ይችላሉ።

19. ቤተሰቦቻችን አንዳንድ ነገሮችን የማናደርግበት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባይገባቸውም በምን መንገድ ልንይዛቸው ይገባል? (1 ጴጥሮስ 3:15)

19 አንደኛ ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ። የቤተሰባችን አባላት አንዳንድ ነገሮችን የማናደርግበት ምክንያት ሙሉ በሙሉ አይገባቸው ይሆናል፤ ሆኖም የምናሳያቸውን ደግነትና አክብሮት ምንጊዜም ያስታውሱታል። በተጨማሪም በአንዳንድ ወቅቶች አብረናቸው ጊዜ ማሳለፍ ባንችልም ይህን ለማካካስ የምናደርገውን ጥረት ሊያደንቁ ይችላሉ። ለምሳሌ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ በዓላትና ልማዶች መካፈል ባንችልም በሌሎች ጊዜያት ሄደን ልንጠይቃቸው፣ አብረናቸው ምግብ ልንበላ እንዲሁም ስጦታ ልንሰጣቸው እንችላለን።

በቤተሰቦችህ ላይ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥባቸው

20. የያዕቆብ ታሪክ የሚያበረታታን ለምንድን ነው?

20 ያዕቆብ፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት እሱን የመከተል አጋጣሚ አምልጦታል፤ ሆኖም ውሎ አድሮ የእሱ ደቀ መዝሙር ሆኗል። (ገላ. 1:18, 19፤ 2:9) ያዕቆብ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ባይሆንም ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ያስተማራቸውን ትምህርቶች እንደተማረ ምንም ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ በመንፈስ ተመርቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከተራራው ስብከት ጋር የሚመሳሰሉ አንዳንድ ሐሳቦችን ጠቅሷል።e

21. አማኝ ባልሆኑ ቤተሰቦቻችን ላይ ተስፋ ልንቆርጥባቸው የማይገባው ለምንድን ነው?

21 ለቤተሰቦቻችን ትኩረት ለመስጠትና እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ብናደርግም እውነትን የመቀበል ፍላጎት ላይኖራቸው ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ ሊይዙን ይችላሉ። ታዲያ ተስፋ ልንቆርጥባቸው የማይገባው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለእነሱ ደግነት ባሳየን ቁጥር መሐሪ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስን እየመሰልን ነው። (ሉቃስ 6:33, 36) የምናሳያቸው ፍቅር፣ ውሎ አድሮ ለእኛ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። በተጨማሪም ስለ እምነታችን የነገርናቸውን ነገር ያስታውሱት ይሆናል። ተስፋ ካልቆረጥንባቸው፣ ከምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን አንዳንዶቹ እውነተኛውን አምልኮ ሲቀበሉ የማየት መብት እናገኝ ይሆናል!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ርኅራኄ አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

  • አማኝ ካልሆኑ ቤተሰቦቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ታጋሽና አዎንታዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

  • አማኝ ያልሆኑ ቤተሰቦቻችንን እንደምንወዳቸው ልናሳያቸው የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 60 ስብከታችን ሰው ያድናል

a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አማኝ ያልሆነ” ወይም “የማያምን” የሚሉት አገላለጾች የሚያመለክቱት ሃይማኖት የሌለውን ወይም በአምላክ የማያምንን ሰው ብቻ አይደለም። (1 ቆሮ. 7:12) በዚህ ርዕስ ውስጥ እነዚህ አገላለጾች የሚያመለክቱት የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ነው።

b በግንቦት 2024 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ይሖዋ ወደፊት ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ምን እናውቃለን?” የሚለውን ርዕስ ገጽ 11 ከአን. 11-13ን ተመልከት።

c ከኢየሱስ ወንድሞች መካከል ቢያንስ ሁለቱ ማለትም ያዕቆብና ይሁዳ፣ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ እውነትን ተቀብለዋል።

d “በሠርግ ወይም በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ይኖርብሃል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

e ያዕቆብ 1:2ን ከማቴዎስ 5:11, 12፣ ያዕቆብ 1:19ን ከማቴዎስ 5:22፣ ያዕቆብ 1:22ንና 2:24ን ከማቴዎስ 7:21 እንዲሁም ያዕቆብ 2:13ን ከማቴዎስ 5:7 እና 6:14, 15 ጋር አወዳድር።

f ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በግንቦት 15, 2002 እና በኅዳር 15, 2007 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡትን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

g የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት አገልግሎት ከመውጣቷ በፊት ለባለቤቷ ምግብ በማዘጋጀት ደግነት ታሳየዋለች።

h የሥዕሉ መግለጫ፦ ያችው እህት ጊዜ መድባ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነችውን አማቷን ትጠይቃለች።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ