9 ሺፍራ፣ ፑሃ፣ አምራም፣ ዮካቤድ፣ ሚርያም
ሙሴን “የሸሸጉት በእምነት ነበር”
ዮሴፍ ከሞተ 60 ዓመታት አልፈዋል። ግብፃውያን በይሖዋ እርዳታ ሕዝባቸውን ከረሃብ የታደገላቸውን ታማኝ ሰው ውለታ ረስተዋል። እስራኤላውያንን የሚፈራና የሚጠላ አዲስ ፈርዖን ግብፅን ማስተዳደር ጀመረ። እስራኤላውያን ይሖዋ ስለባረካቸው በቁጥር እየበዙ ሄዱ። ይህ ያሰጋቸው ግብፃውያን ዕብራውያንን ባሪያ አድርገው መግዛትና ማንገላታት ጀመሩ። ይህ ግን እነዚህ ባሪያዎች እንዳይበዙ አላገዳቸውም።
ፈርዖን ይህን ሲያይ አንድ አሰቃቂ ስልት ቀየሰ። ሺፍራ እና ፑሃ የተባሉት ዕብራውያን አዋላጆች ፊቱ እንዲቀርቡ አዘዘ። ከዚያም የሚያዋልዷቸውን ወንዶች ልጆች ወዲያውኑ እንዲገድሏቸው ነገራቸው! ይህ ኃያል ገዢ እንዲህ ያለ መመሪያ ሲሰጣቸው ምን ተሰምቷቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? እነዚህ ሁለት ደፋር ሴቶች ግን “እውነተኛውን አምላክ [ፈሩ]።” ምንም ዓይነት ሥልጣን ቢኖረው አንድ ተራ ሰው የጽንፈ ዓለሙን ልዑል ትእዛዝ እንዲጥሱ የማድረግ መብት እንደሌለው ገብቷቸዋል። አምላክን ስለፈሩ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ወሰዱ። “የግብፅ ንጉሥ ያላቸውን አላደረጉም።” እንዲያውም የቻሉትን ያህል ጥረት በማድረግ ብዙ ሕፃናትን አተረፉ። ፈርዖን በዚህ በጣም ተቆጣ፤ አስጠርቶ ሲጠይቃቸው ግን ያደረጉትን ነገር በዘዴ መደበቅ ቻሉ። ይሖዋ እነዚህ ሴቶች የሚያደርጉትን ነገር ያይ ነበር። በምላሹም “ለአዋላጆቹ መልካም ነገር አደረገላቸው።” ከጊዜ በኋላ የራሳቸው ቤተሰብ ሰጣቸው።
አዋላጆቹ፣ ወላጆቹና እህቱ ድፍረት ባያሳዩ ኖሮ ሕፃኑ ሙሴ ምን ይሆን ነበር?
ፈርዖን ዕቅዱ እንዳልተሳካለት ሲያይ ሌላ የጭካኔ አዋጅ አወጣ። ወንዶቹ ሕፃናት አባይ ወንዝ ውስጥ እንዲጣሉ አዘዘ! በዚያ የጨለማ ጊዜ አምራም እና ዮካቤድ የተባሉ ዕብራውያን ባልና ሚስት ይኖሩ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ሚርያም እና አሮን የተባሉ ሁለት ልጆች ነበሯቸው። ዮካቤድ ሦስተኛ ልጇን ስትፀንስ ግን ከባድ ውሳኔ ተደቀነባቸው። ምክንያቱም ልጁ ወንድ ከሆነ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ያውቃሉ። ልጁ ከተወለደ በኋላ የቻሉትን ያህል ደብቀው ሊያቆዩት ሞከሩ። ሕፃን ደብቆ ማቆየት ግን ቀላል አይደለም። ልጁ ሦስት ወር ሲሆነው ዮካቤድ ቅጥራንና ዝፍት በተለቀለቀ ቅርጫት ውስጥ አድርጋ ወደ አባይ ወንዝ ይዛው ወረደች፤ ከዚያም ወንዙ ዳር ባለ ቄጠማ መሃል አስቀመጠችው። ሴት ልጇ ሚርያም ራቅ ብላ ቆማ ታናሽ ወንድሟን ትመለከተው ነበር።
ብዙም ሳይቆይ የፈርዖን ሴት ልጅ ልትታጠብ ወደ አባይ ወንዝ ወረደች። ቅርጫቱን ስታየው እንድታመጣው አገልጋይዋን ላከቻት። ቅርጫቱ ሲከፈት አንድ የሚያምር ሕፃን ልጅ እያለቀሰ ነበር፤ በጣም ስላዘነችለት ልታሳድገው ወሰነች። ሆኖም ልጁ፣ እያጠባች የምታሳድገው እናት እንደምታስፈልገው ገባት። ሚርያም ወዲያውኑ አንድ ሐሳብ መጣላት። በድፍረት ወደ ፈርዖን ሴት ልጅ ሮጥ ብላ በመሄድ ልጁን እያጠባች የምታሳድግላት ሞግዚት ትፈልግ እንደሆነ ጠየቀቻት። የፈርዖን ሴት ልጅም በሐሳቡ ተስማማች። ከዚያም ሚርያም ከእናቷ ጋር ተመልሳ መጣች። ዮካቤድ የተፈጠረውን ነገር ስታውቅ ምን ያህል እንደምትደሰት አስበው። የምትሳሳለትን ልጇን ሳትሳቀቅ ማሳደግ ትችላለች፤ ያውም እየተከፈላት! እሷና አምራም ትንሹን ልጃቸውን ስለ ይሖዋ ለማስተማር የሚችሉትን ሁሉ አድርገው መሆን አለበት። ውሎ አድሮ ግን ልጁን ለፈርዖን ሴት ልጅ የሚያስረክቡበት ቀን ደረሰ። እሷም ሙሴ ብላ ጠራችው።
አምራም፣ ዮካቤድና ሚርያም ላሳዩት እምነትና ድፍረት ይሖዋ ባርኳቸዋል? በሚገባ! አምራምና ዮካቤድ፣ ሚርያምንና አሮንን ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች አድርገው በማሳደግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። እንዲሁም ይሖዋ ለሙሴ ጥበቃ ሲያደርግለት ማየት ችለዋል። ዕድሜ አግኝተው ሙሴ ምን ዓይነት ሰው እንደወጣው ማየትስ ችለው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። (ዘፀ. 6:20) ሚርያም ግን ይህን ለማየት በቅታለች፤ አሮንም እንደዛው። ሁለቱም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች አይተዋል። እንዲሁም ሦስቱም አስደናቂ እምነትና ድፍረት አሳይተዋል። በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ስለ ሙሴ አስተዳደግና ይሖዋን ለማገልገል ስላደረገው ውሳኔ እንመለከታለን።
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
አዋላጆቹና የሙሴ ቤተሰብ ድፍረት ያሳዩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
1. አርኪኦሎጂ የዚህን ታሪክ ትክክለኛነት የሚደግፈው እንዴት ነው? (g04 4/8 4 አን. 4 እስከ 5 አን. 1-wcgr)
2. ስለ ደንገል ቅርጫትና ፈርዖን ዕብራውያን ሕፃናትን ለመፍጀት ስላወጣው አዋጅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ የሚደግፍ ምን ማስረጃ አለ? (g04 4/8 6 አን. 1-2-wcgr) ሀ
Christine Osborne Pictures/Alamy Stock Photo
ሥዕል ሀ፦ በዛሬው ጊዜም እንኳ በደንገል ጀልባ ይሠራል
3. ስለ ዕብራውያኑ አዋላጆች ምን የምናውቀው ነገር አለ? ምን በረከትስ አግኝተዋል? (w03 11/1 8 አን. 3-4፤ it “አዋላጅ”-wcgr) ለ
ሥዕል ለ
4. ሚርያም እስከ እርጅናዋ ድረስ አስደናቂ እምነት ያሳየችው እንዴት ነው? (ijwia ርዕስ 7 አን. 14-18)
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
ወላጆች ከአምራምና ከዮካቤድ ምን መማር ይችላሉ?
ወንድም ወይም እህት ያላቸው ልጆች ከትንሿ ሚርያም ምን መማር ይችላሉ? ሐ
ሥዕል ሐ
የሺፍራን እና የፑሃን የድፍረት ምሳሌ በሕይወትህ ውስጥ በየትኞቹ መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ከሞት ሲነሱ ምን ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
የፈርዖንን ትእዛዝ በድፍረት ከጣሱት ሴቶች ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ተመልከት።
ይሖዋ ከሰው ይልቅ እሱን በመታዘዝ ድፍረት የሚያሳዩ አገልጋዮቹን ሁልጊዜም ይንከባከባል?