ቅንዓታችን እንዳይቀዘቅዝ ምን ማድረግ እንችላለን?
1 አጵሎስ አገልግሎቱን በጋለ ስሜት ያከናወነበት መንገድ በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን በተለይ ለስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት ያላቸውን ክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን ያስታውሰን ይሆናል። (ሥራ 18:24-28) ሁላችንም “በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ” ተብለን ተመክረናል። (ሮሜ 12:11) ለክርስቲያናዊው አገልግሎት ቅንዓት እንዲኖረንና ቅንዓታችን እንዳይቀዘቅዝ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 እውቀት ቅንዓት እንዲኖረን ይረዳናል:- ኢየሱስ ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ “በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን” ካስረዳቸው በኋላ ደቀ መዛሙርቱ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን . . . ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” በማለት ተናግረዋል። (ሉቃስ 24:27, 32) እኛስ ስለ አምላክ ቃል ያለን እውቀት ይበልጥ እየጨመረ ሲሄድ ልባችን በአድናቆት አይሞላም? አዎን፣ በእውቀት ስንሞላ እምነት ይኖረናል። ሮሜ 10:17 “እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው” ይላል። ይሖዋ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ሲዳብር የተማርናቸውን ነገሮች ከመናገር ዝም ማለት አንችልም!—መዝ. 145:7፤ ሥራ 4:20
3 ለአምላክ ያለን ፍቅር እንዲጠነክርና ለአገልግሎቱ ከፍተኛ ቅንዓት እንዲኖረን ከዚህ ቀደም ያካበትነው እውቀት ብቻ አይበቃንም። ስለ እውነት ያለንን ግንዛቤ ማስፋታችንን መቀጠልና ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ ይኖርብናል። አለዚያ ግን ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት ቀስ በቀስ በዘልማድ የሚከናወን እየሆነ ይሄዳል። (ራእይ 2:4) የአምላክ ቃል ‘እግዚአብሔርን በማወቅ እያደግን’ እንድንሄድ ይመክረናል።—ቈላ. 1:9, 10
4 የጥናት ልማዳችን:- እንግዲያው የጥናት ልማዳችንን መመርመራችን መልካም ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ ላይ መልሶቹን ማስመርና ትክክል የሆኑ ሐሳቦችን መስጠት እንችል ይሆናል። ሆኖም የተጠቀሱትን ጥቅሶች እናነባቸዋለን? በርዕሱ ሥር የቀረበውን ሐሳብ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ሥራ ላይ እንደምናውለው እናሰላስላለን? ሁኔታችን የሚፈቅድልን ከሆነ በሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ ተጨማሪ ምርምር እናደርጋለን? ባነበብነው ትምህርትስ ላይ እናሰላስላለን? (መዝ. 77:11, 12፤ ምሳሌ 2:1-5) በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችንና ትኩረት ማድረጋችን ምንኛ ጠቃሚ ነው! (1 ጢሞ. 4:15, 16) እንዲህ ዓይነቱ ትርጉም ያለው ጥናት በመንፈሳዊ ይገነባናል፤ እንዲሁም ‘መልካም የሆነውን ለማድረግ እንድንተጋ’ ኃይል ይሰጠናል።—ቲቶ 2:14