ደግ በመሆን ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ለይሖዋ ምሥክሮች ጭፍን ጥላቻ የነበራት ሴት፣ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘችበትን ቀን እያስታወሰች “የተነጋገርነው ነገር ትዝ አይለኝም። የማስታውሰው ነገር ቢኖር ምን ያህል ደግ፣ ተግባቢና ትሑት እንደነበረች ነው። በደግነቷ በጣም ወደድኳት” ብላለች። ይህ አስተያየት ለምንሰብክላቸው ሰዎች ከልብ እንደምናስብላቸው ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጎላ ነው።—ፊልጵ. 2:4
2 ፍቅር ደግ ነው:- ቸር ወይም ደግ መሆን ለሰዎች ፍቅር እንዳለን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው። (1 ቆሮ. 13:4) ደግ ሰው የሌሎች ደኅንነት ከልብ ስለሚያሳስበው የሚጠቅማቸውን ነገር ለማድረግ ይጥራል። እርግጥ ነው፣ የስብከቱ ሥራ በራሱ የደግነት መግለጫ ነው። ይሁን እንጂ ለሰዎች ከልብ የመነጨ አሳቢነት እንዳለን የምናሳየው እንዲሁ በመስበክ ብቻ አይደለም። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የምናሳየው ምግባር ማለትም ወዳጃዊ አቀራረባችን፣ ትሕትናችን፣ የምናዳምጥበት መንገድ፣ የምንናገራቸው ነገሮችና የምንናገርበት መንገድ ሌላው ቀርቶ ፊታችን ላይ የሚነበበው ስሜት በእርግጥ እንደምናስብላቸው የሚያሳይ ነው።—ማቴ. 8:2, 3
3 ለሰዎች ያለን ፍቅራዊ አሳቢነት ተግባራዊ በሆኑ መንገዶች ጭምር እርዳታ እንድናደርግ ያነሳሳናል። አንድ አቅኚ ወንድም ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ያገኛቸው አንዲት አረጋዊት መበለት፣ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ሲያውቁ የመጥሪያ ደወላቸው የጮኸው የወጥ ቤታቸውን አምፑል ለመቀየር መሰላል ላይ እንዳሉ መሆኑን በመግለጽ መስማት እንደማይፈልጉ ነገሩት። ወንድምም “ለብቻዎ እንዲህ ማድረግዎ ጥሩ አይደለም” አላቸው። ከዚያም ወደ ውስጥ እንዲገባ ጋበዙት። አምፑሉን ከቀየረላቸው በኋላ ተሰናብቶ ሄደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሴትየዋ ወንድ ልጅ እርሳቸውን ለመጠየቅ ሲመጣ የተከሰተውን ነገር ነገሩት። ልጁ በሁኔታው በጣም ስለተገረመ አድናቆቱን ለመግለጽ ወንድምን ያፈላልግ ጀመር። ይህ ደግሞ ጥሩ ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ ከፈተላቸው፤ ከዚያም ልጁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነ።
4 ለሌሎች ደግ በመሆን ይሖዋ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ከማንጸባረቃችንም በላይ የመንግሥቱን መልእክት እናስውባለን። ስለዚህ ሁልጊዜ በደግነት ‘ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ለማቅረብ’ እንጣር።—2 ቆሮ. 6:4, 6