‘በበኩሌ ምን ማድረግ እችላለሁ? ’
1 ‘በበኩሌ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1870ዎቹ ባደራጀው አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አባላት አእምሮ ውስጥ ይህ ጥያቄ ይጉላላ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ቀደም ሲል የነበሩት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክን ፈቃድ ደረጃ በደረጃ እየተረዱ ሲመጡ ሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ ዓላማ እንዲማሩ ለመርዳት በበኩላቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ አስበው መሆን አለበት። እያገኙ የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በመላው ዓለም ማዳረስ በእርግጥ እጅግ ታላቅ ሥራ ነበር።
2 ደስ የሚለው ይህን ከባድ ሥራ በተሳካ ሁኔታ ተወጥተውታል። እንዴት? እያንዳንዱ ግለሰብ አነስተኛ መስሎ የሚታየውን የበኩሉን ድርሻ በማበርከቱ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ሊታወቁ በቅተዋል። ድርጅቱ በ234 አገሮችና ደሴቶች በሚገኙ 90, 000 በሚያክሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችን አቅፏል!—ኢሳ. 60:22
3 ሙሉ ድጋፍህን ስጥ:- እያንዳንዳችን ኢየሱስ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እንደሚከናወን አስቀድሞ በተናገረው ታላቅ ሥራ መካፈላችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ማር. 13:10) ይህ ሥራ የተወሰነ ቁጥር ላላቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች ብቻ የተተወ ወይም የስብከቱ እንቅስቃሴ በአቅኚዎች ጫንቃ ላይ ብቻ የተጣለ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ራሱን የወሰነ እያንዳንዱ ክርስቲያን ጠቃሚ ሚና ሊጫወት ይችላል። ሁላችንም በአንድ ዓይነት የስብከት እንቅስቃሴ መካፈል እንችላለን። (1 ጢሞ. 1:12) የምናከናውነው የሥራ መጠን ይነስም ይብዛ ለእኛም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ጥቅም እናስገኛለን።—1 ጢሞ. 4:16
4 በተጨማሪም እያንዳንዱ ክርስቲያን በሌሎች ጠቃሚ መንገዶች ለክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረታችን ሙሉ ድጋፍ ማበርከት ይችላል። አዘውትረን በመሰብሰብና በጋለ ስሜት በመሳተፍ ለጉባኤ ስብሰባዎች ድጋፍ መስጠት እንችላለን። (መዝ. 122:1, 8, 9) የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊ ንጽህና ለመጠበቅ የበኩላችንን ማድረግ እንችላለን። አቅማችን የሚፈቅድልንን ያህል ዓለም አቀፉን ሥራ በገንዘብ መደገፍ እንችላለን። የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳቱ ሥራ ተካፋይ ልንሆን እንችላለን። አዲሶችን፣ ወጣቶችንና በእድሜ የገፉትን በመርዳት እያንዳንዱ አስፋፊ በጉባኤ ውስጥ የፍቅርና የአንድነት መንፈስ እንዲሰፍን ማድረግ ይችላል።—ቆላ. 3:12, 14
5 ስለዚህ አንተም ‘በበኩሌ ምን ማድረግ እችላለሁ’ ብለህ ጠይቀህ ይሆናል? በግለሰብ ደረጃ የምታበረክተው አስተዋጽኦ እንዲያው እዚህ ግባ የማይባል መስሎ ቢታይህም የድርሻህን ከተወጣህ ጠንካራ፣ ንቁና ጤናማ ጉባኤ እንዲኖር ለማድረግ አስተዋጽዖ ማበርከት ትችላለህ። በመሆኑም ሁላችንም የይሖዋ ስም እንዲከበር በማድረግ ረገድ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት እንችላለን!