ሥራውን ለመፈጸም የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልጋል
1 እያንዳንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለመደገፍና በሥራው ለመሳተፍ የሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው መገንዘብ ይኖርበታል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የሚያፈሩት የመንግሥቱ ፍሬ በመጠኑ የተለያየ እንደሚሆን ተገንዝቦ ነበር። (ማቴ. 13:23) በስብከቱ ሥራ ሰፊ ድርሻ የሚያበረክቱ ብዙ ትጉ አቅኚዎች ቢኖሩም አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል ፍሬ በማፍራት አምላክን ማክበራቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።—ዮሐ. 15:8
2 በጋራ የተደረገ ጥረት ብዙ ፍሬ ያስገኛል፦ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በጋራ በሚያደርጉት ጥረት እሱ ካከናወነው የበለጠ ነገር እንደሚሠሩ አስቀድሞ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:12) በግል ሁኔታችን ምክንያት በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የምናደርገው ተሳትፎ የተገደበ ሆነም አልሆነ ወይም በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ረጅም ሥራ ማሳለፍ ቻልንም አልቻልን ለሥራው የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልጋል። ጉዳዩ ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል እንደገለጸው ነው:- “አካልም በሙሉ የተያያዘው በመገጣጠሚያዎቹ ነው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተመደበለትን ተግባር ሲያከናውን አካል በሙሉ ያድጋል።”—ኤፌ. 4:16 የ1980 ትርጉም
3 አንዳንዶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ያን ያህል ጉልህ እንዳልሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም በይሖዋ ዓይን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር አገልግሎታችን በሙሉ ነፍስ የቀረበ መሆኑ ነው። ለእርሱ ስንል የምናደርገው ማንኛውም ነገር ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።—ከሉቃስ 21:1-4 ጋር አወዳድር።
4 ሥራውን መደገፋችሁን ቀጥሉ፦ ሁላችንም ዓለም አቀፉን ሥራ በቁሳዊ ረገድ የመደገፍ መብት አግኝተናል። አንዳንዶች ደግሞ ለመንግሥቱ ሥራ የጉልበት ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ። እያንዳንዳችን በስብሰባዎች ላይ ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው ሐሳቦች ለመስጠትና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመሳተፍ ልንጥር እንችላለን። ሌሎችን ለማበረታታት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መጠቀማችን ለጉባኤው መንፈሳዊነት ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ከመሆኑም ሌላ ጉባኤው በአደራ የተሰጠውን ሥራ ለመፈጸም የተሻለ ብቃት እንዲኖረው ያግዛል።
5 በእርግጥም ለሥራው የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልጋል። ማናችንም ብንሆን ለዚህ ሥራ የምናበረክተው ድርሻ እንደሌለ ሊሰማን አይገባም። በዛም አነሰ ይሖዋን ለማገልገል የምናደርገው የጋራ ጥረት እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን ያሳያል። (ሚል. 3:18) እያንዳንዳችን ይሖዋን በማክበርና ሌሎች እሱን እንዲያውቁና እንዲያገለግሉት በመርዳት ረገድ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ልናደርግ እንችላለን።