ትክክል ካልሆነ የደም አጠቃቀም ልጆቻችሁን መጠበቅ
1 “እነሆ፣ ልጆች የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ስጦታ ናቸው።” (መዝ. 127:3) እንዲህ ያለ ውድ ውርሻ ከይሖዋ ከተሰጣችሁ ልጆቻችሁን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማሰልጠን አስደሳች የሆነ ነገር ግን ከበድ ተደርጎ የሚታይ ኃላፊነት አላችሁ። ለምሳሌ ትንንሽ ልጆቻችሁ ደምን በደም ሥር ከመውሰድ የሚጠብቃቸውን ማንኛውንም እርምጃ ወስዳችኋልን? ልጆቻችሁ ደምን የመውሰድ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው እንዴት ያለ ምላሽ ይሰጣሉ? ደምን የመውሰድ አደገኛ ሁኔታ ቢያጋጥማችሁ ምን እንደምታደርጉ ውጤታማ በሆነ መንገድ በቤተሰብ ተወያይታችሁበት ታውቃላችሁን?
2 ቤተሰባችሁን እንደዚህ ላለው ሁኔታ ማዘጋጀት ከመጠን በላይ ጭንቀትን ወይም ስጋትን የሚፈጥር መሆን የለበትም። በሕይወት ላይ ለሚደርሱት ሁኔታዎች ሁሉ አስቀድማችሁ ማወቅና መዘጋጀት አትችሉም። ሆኖም ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ ደም እንዳይወስዱ አስቀድማችሁ ብዙ ነገሮችን ልታደርጉ ትችላላችሁ። እነዚህን ኃላፊነቶቻችሁን ችላ ማለታችሁ ልጃችሁ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት እያለ ደም ሊሰጠው ይችላል። ምን ማድረግ ይቻላል?
3 ስለ አቋማችሁ ጽኑ እምነት መያዝ አስፈላጊ ነው:- ደምን በሚመለከት አምላክ ያወጣውን ሕግ የቱን ያህል እንደምታምኑበት አጥብቃችሁ ልታስቡበት ይገባል። ስለ እውነተኝነት፣ ስለ ሥነ ምግባር፣ ስለ ገለልተኝነትና ስለ ሌሎች የሕይወት ጉዳዮች ልጆቻችሁን እንደምታስተምሯቸው ሁሉ ደምን በሚመለከት ይሖዋን እንዲታዘዙ ታስተምሯቸዋላችሁን? በዘዳግም 12:23 ላይ:- “ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ” ብሎ የአምላክ ቃል እንደሚያዘው በእርግጥ ይሰማቸዋልን? ቁጥር 25 በመጨመር:-“በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆላችሁ፣ አትብላው” ይላል። የታመመው ልጃችሁ ደም ቢወስድ ጥሩ እንደሚሆንለት ሐኪሙ ሊናገር ይችላል። ይሁን እንጂ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ደም መውሰድን መቃወም የሚያስፈልገው አደጋ ከመምጣቱ በፊት ከይሖዋ ጋር ያላችሁ ዝምድና የእርሱን መለኮታዊ ሕግ በመጣስ ከሚገኝ ማንኛውም የሕይወት ርዝማኔ ይልቅ የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን አስቀድማችሁ በቁርጠኝነት መወሰን ያስፈልጋችኋል። ነገሩ አሁን ከአምላክ ሞገስን ወደፊትም የዘላለም ሕይወት ማግኘትን ይመለከታል።
4 አዎ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወትን የሚወዱና የመኖር ዝንባሌ ያላቸው ናቸው፤ እንዲሞቱ አይፈልጉም። ይሖዋን ለማወደስና ፈቃዱን ለማድረግ እንዲችሉ በሕይወት ለመኖር ይፈልጉም። ራሳቸውም ሆነ ልጆቻቸው ህክምናን ለማግኘት እንዲችሉ ወደ ሆስፒታሎች የሚሄዱበት ምክንያት ይህ ነው። ሐኪሞች ህክምና እንዲያደርጉላቸውም ይጠይቃሉ። የሚደርግላቸው ህክምና ደም መውሰድን የሚጨምር ሲሆን ግን ደም አልባ አማራጭ ህክምና እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ። በደም ምትክ የሚሰጡ ብዙ የህክምና አማራጮች አሉ። ተሞክሮ ያላቸው ሐኪሞችም ይጠቀሙባቸዋል። እነዚህ አማራጮች የሐሰት ወይም የማስመሰያ መድኃኒቶች አይደሉም። እነዚህ የህክምና አማራጮች ጥሩና ትክክለኛ የሆኑ፣ በህክምና መጽሔቶች የተመዘገቡና የታወቁ የህክምና አሠራር ዘዴዎች ናቸው። ምንም እንኳ ምስክር የሆኑ ልጆችን ያለ ደም የሚያክሙ ሐኪሞችን ማግኘቱ ችግር ቢሆንም በዓለም ዙርያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሐኪሞች ያለ ደም ጥሩ የህክምና እንክብካቤ በማድረግ ይተባበሩናል።
5 ከአቋማችን ጋር የሚተባበር ሐኪም ፈልጎ ማግኘት:- ሐኪሞች በሽተኞችን ሲያክሙ ብዙ የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች አሉ። ልጆቻችሁን ያለ ደም እንዲያክሙላችሁ ስትጠይቋቸው ደግሞ ይህ የሥራቸውን ተፈታታኝነት ይጨምረዋል። አንዳንድ ሐኪሞች ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ ተቀባይነት ያለው ሰነድ ከተፈረመላቸው ለደም ያላቸውን አቋም አክብረው ትልልቅ ሰዎችን ያለ ደም ለማከም ይስማማሉ። በተመሳሳይም ፍርድ ቤቶች በአእምሮ የበሰሉ ልጆች የራሳቸውን ሕክምና የመምረጥ መብታቸውን እስካወቁላቸው ድረስ ትንንሽ ልጆችንም ያለ ደም ለማከም አንዳንድ ሐኪሞች ይስማማሉ። (የበሰለ ልጅ ምን ዓይነት እንደሆነ ለማወቅ መጠበቂያ ግንብ ሰኔ 15, 1991፣ ገጽ 16-17 ተመልከቱ) ይሁን እንጂ ሐኪሞች ትንንሽ ልጆችን በተለይም ህፃናትን ደም እንዲሰጡአቸው ካልተፈቀደላቸው በቀር ለማከም ፈቃደኛ አይሆኑ ይሆናል። እንዲያውም በማንኛውም ሁኔታ ሥር ልጆችን ሲደክሙ ደም እንደሚሰጡአቸው መቶ በመቶ ዋስትና የሚሰጡ ሐኪሞች ብዙ አይደሉም። አብዛኞቹ ሐኪሞች በሕክምናና ሕጋዊ በሆን ምክንያቶች እንዲህ ዓይነቱን ዋስትና ለመስጠት እንደሚችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል። የሆነው ሆኖ ለደም ያለንን አመለካከት በማክበር ለይሖዋ ምስክሮች ልጆች የሕክምና እርዳት ለመስጠት ፍላጎች ያላቸው ሐኪሞች ቁጥር ጨምሮአል።
6 ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ለልጆችሁ ተስማሚ ሐኪም ለማግኘት ስትጥሩ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመተባበር ጥሩ ስም ያለውን፤ ባለፉትም ጊዚያት ለሌሎች ምሥክሮች ደም አይሰጥም የሚል ዋስትና ለመስጠት ሕጉ እንደማይፈቅድለት ቢሰማው ምን ታደርጋላችሁ? ከዚህ የተሻለ አማራጭ አይኖርም ብላችሁ ትወስኑ ይሆናል። በእነዚህ ሁኔታዎች ሥር ሐኪሙ የሕክምና ሥራውን እንዲጀምር መፍቀድ እንደምትችሉ አድርጋችሁ ትደመድሙ ይሆናል። ሆኖም ልጃችሁ ሕክምና እንዲደረግለት መፍቀዳችሁ ደም እንዲሰጠው መፍቀዳችሁ እንዳልሆን ግልጽ አድርጉለት። ውሳኔአችሁ የአቋም መላላት ተደርጎ እንዳይታይ በመጠንቀቅ ይህ ዓይነት ውሳኔ በመወሰን በኩል ሙሉውን ኃላፊትን የምትሸከሙት እናንተው ናችሁ።
7 በእርግጥ ምክንያታዊ የሆነ ደም የመውሰድን ችግር ሊያስወግድ የሚችል አማራጭ የሕክምና መንገድ ካገኛችሁ አደጋው የሚቀንሰውን የሕክምና አሠራር ትመርጣላችሁ። ደምን ላለመስጠት የሚስማማ ሐኪም ወይም ሰርጀን ( የቀዶ ጥገና ሐኪም) ፈልጋችሁ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቅባችሁ ይሆናል። ከሁሉ የተሻለው መከላከያ ችግሮች እንደሚነሱ አስቀድሞ መጠበቅና መዘጋጀት ነው። የሚተባበራችሁ ሐኪም ለማግኘት አስቀድማችሁ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት አድርጉ። በተቻለ መጠን ተባባሪ ካልሆኑ ሐኪሞችና ሆስፒታሎች ለመራቅ ሞክሩ።
8 በአንዳንድ አገሮች ደምን የመውሰድና ያለመውሰድ ጉዳይ ሆስፒታሉ ለሚያደርገው እንክብካቤ በሚከፈለው ገንዘብ ላይ ይመካል። ወላጆች ወደመረጡት ሐኪም ለመሄድ የሚያስችል የጤና ኢንሹራንስ ወይም የደኅንነት ዋስትና ካላቸው ልጆቹ ተባባሪ ካልሆኑ ሐኪሞች ወይም የሆስፒታል ሠራተኞች በቀላሉ ሊያመልጡ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ በቂ የሆነ የገንዘብ ዋስትና ከሐኪሞችና ከሆስፒታሎች የምታገኙትን ትብብርና አገልግሎት ይወስናል። በተጨማሪም አንድ ሆስፒታል ወይም ሐኪም ልጁን ተቀብሎ ለሚደርገው እንክብካቤ በሚከፍሉት ገንዘብ ላይ የተመካ ነው። እንዲሁም ወላድ እናቶች በእርግዝና ወቅት ጤንነታችሁን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው! ይህን ማድረጋችሁ አለጊዜው ከሚመጣ ወሊድና ይህ ከሚስከትላቸው ውስብስብ ችግሮች ትድናላችሁ። ምክንያቱም አለቀናቸው የሚወለዱ ሕፃናትን ለመንከባከብ የሚደረገው ሕክምና በዙውን ጊዜ ደም መስጠትን ይጨምራል።
9 የይሖዋ ምስክሮች እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ለደም ያላቸውን ተቃውሞ አያስረዱም በማለት አንዳንድ ጊዜ ሐኪሞች ቅሬታ ያሰማሉ። ይህ በፍጹም መሆን የሌለበት ጉዳይ ነው። ምስክር የሆኑ ወላጆች ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ወይም የአንድን ሐኪም አገልግሎት ለማግኘት ሲወስኑ መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው ነገር ለደም ያላቸውን አቋም ማስረዳት ነው። የቀዶ ሕክምና የሚጨምር ከሆነ ማደንዘዣውን ከሚሰጠው ሐኪም ጋር አስቀድማችሁ ለመገናኘት እንድትችሉ ጥያቄ አቅርቡ። በዚህም የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ሊረዳችሁ ይችላል። ሆስፒታል ስትገቡ የማስተኛ ቅጾች በትክክል መሞላታቸውን ማረጋገጥ አለባችሁ። የማትስማሙበትን ማንኛውንም ነገር የመሰረዝ መብት አላችሁ። ማንኛውምንም ጥርጥር ለማስወገድ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ቢሆን በሃይማኖታዊና በጤንነት ምክንያት ደም ለመውሰድ የማትፈልጉና የማትፈቅዱ መሆናችሁን በሆስፒታሉ የማስተኛ ቅጽ ላይ በግልጽ ጻፉ።
10 ከይሖዋ ድርጅት የሚገኝ እርዳታ:- የይሖዋ ድርጅት ልጆቻችሁን ከደም ለመጠበቅ የሚረዳ ምን ያደረገው ዝግጅት አለ? ማኅበሩ ስለ ደምና ደም አልባ ስለሆኑ የሕክምና አማራጮች እኛን ለማስተማር ብዙ ጽሑሮችን አትሞአል። ደም ሕይወታችሁን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የተባለውን ብሮሹርና በዚህ ርዕስ ላይ የወጡ ሌሎች ጽሑሮችን አጥንታችኋል። እንዲሁም በጉባኤችሁ ብዙ እርዳታና ድጋፍ ሊሰጡአችሁ የሚችሉ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ አሉ። አስጊ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ሽማግሌዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ ማድረጉ የተሻለ ነው ብለው ሊወስኑ ይችላሉ። ምናልባት ከበሽተኛው ወላጅ ወይም ቅርብ የቤተሰብ አባል ጋር አንድ ሽማግሌ እንዲቆይ ሊመድቡ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ለበሽተኞች ደም የሚሰጠው ሁሉም ዘመዶችና ጓደኞች ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በማታ ነው።
11 በይናትድ ስቴትስ በትልልቆቹ ከተሞች የሚገኙ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች አሉ። ሁሉም ጉባኤዎች እርዳት ሊሰጡ እንዲችሉ የሰለጠኑ ወንድሞችን ወደያዘ አንድ ኮሚቴ ተመድበዋል። በሚያስፈልግበት ጊዜ በሽማግሌዎቻችሁ አማካኝነት እርዳታ እንዲሰጧቸው ልትጠይቁ ትችላላችሁ። በጥቃቅን ጉዳዩች ሁሉ መጠየቅ የለባቸውም። ይሁን እንጂ ከባድ ችግር እስኪነሳ ድረስ ለረጅም ጊዜ መዘግየት የለባችሁም። እነዚህ ወንድሞች ብዙውን ጊዜ የሚተባበሩአችሁን ሐኪሞች ስምና አማራጭ የሕክምና መንገዶችን ሁሉ ሊጠቁሟችሁ ይችላሉ። አስፈላጊና የሚቻል ሲሆንም እነዚህ ወንድሞች በቦታው ለመገኘትን ችግሩን ለማስተካከል ዝግጅት ያደርጋሉ።
12 የፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነትን መጠበቅና እንደ አመጣጡ መያዝ:- አንድ ሐኪም ወይም ሆስፒታል ለልጃችሁ ደም እንዲሰጠው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማምጣት ቢያስብስ? ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል በማሰብ ዝም የምንልበት ወቅት ነውን? በፍጹም አይደለም! አሁንም ቢሆን ደምን ከመውሰድ አደጋ መዳን የሚቻልበት አጋጣሚ አለ። ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አስቀድሞ መዘጋጀት ይገባል። ምን ሊደረግ ይቻላል?
13 በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሆስፒታሎችና ዳኞች የሚመሩባቸውን አንዳንድ መሠረታዊ የሕግ ደንቦችን ማወቅ መከላከያ ለመስጠት የሚያስችላቸሁ ትልቅ እርዳታ ታገኛላችሁ። ከእነዚህ መሠረታዊ ደንቦች አንዱና አስፈላጊ የሆነ ነገር ሕጉ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጠውን ሕክምና ለመቀበልም ሆነ እንቢ ለማለት ገደብ የለሽ ሥልጣን የማይስጣቸው መሆኑን ነው። ትልልቅ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል አጠቃላይ የሆነ መብት ቢኖራቸውም ወላጆች ለልጆቻቸው ደኅነነት አስፈላጊ ነው ተብሎ የታሰበን የህክምና ዓይነት በሃይማኖታዊ እምነቶች የተመሠረተም እንኳ ቢሆን ለመቃወም ነፃ አይደሉም።
14 ይህ መሠረታዊ ሕግ የታየው በ1944 የዩ.ኤስ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት:- “ወላጆች ራሳቸው ሰማዕት ለመሆን ከፈለጉ ነፃ ናቸው። ነገር ግን ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ልጆቻቸው ለራሳቸው ራሳቸው የመምረጥና የመለየት ሙሉ ሕጋዊ ዕድሜ ላይ ሳይደርሱ ልጆቻቸውን ሰማእት ለማድረግ ነፃ አይደሉም” በማለት በደነገገበት ጊዜ ተንጸባርቋል። የልጆችን ደኅንነት የሚያስጠብቁ የዛሬዎቹ ሕጎች የልጁን አካላዊ ጤንነትና ደኅንነት የሚያጠቃልል መሠረታዊ ዓላማ ይዘዋል። እነዚህ ሕጎች ሕፃናት ልጆችን ከማጎሳቆልና የሕክምና እርዳት በማግኘት ረገድ ችላ ከመባል ይጠብቃቸዋል።
15 ልጆች በወላጆቻቸው ከመጎሳቆልና ቸላ ከመባል የሚጠብቀውን ሕግ ክርስቲያን ወላጆች የሚቃወሙት አይደለም። ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጎችና ሕፃናት ችላ እንዳይባሉ የወጡት ሕጎች የይሖዋ ምሥክሮችን ልጆች በተመለከተ የሚጠቀሱት አግባብ በሌለው መንገድ ነው። ለምን? ምክንያቱም መጀመሪያ ነገር ምስክር ወላጆች ልጆቻቸውን ሰማእት የማድርግ ሐሳብ የላቸውም። እንዲህ ዓይነቱ አሳብ ቢኖራቸው ኖሮ መጀመሪያውኑ ወደ ሆስፒታል ይወስዱአቸው ነበርን? ከዚህ በተቃራኒ ምስክር ወላጆች ልጆቻቸው እርዳታ እንዲያገኙላቸው በፈቃደኝነት ወደ ሆስፒታል ይወስዱአቸዋል። ልጆቻቸውን ይወዳሉ፣ ጥሩ ጤንነት እንዲኖራቸውም ይፈልጋሉ። ሆኖም ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን የሕክምና ዓይነት ለመምረጥ ከአምላክ የተሰጠ ኃላፊነት እንዳላቸው ያምናሉ። የልጆቻቸው የጤና ችግሮች ያለ ደም መፍትሄ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ደም አልባ የሆነ አማራጭ የሕክምና ዝግጅቶች የተሻሉና የሚያስከትሉት አደጋ አነስተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ልጆቻቸው በሕይወት ሰጭው በይሖዋ አምላክ ፊት ሞገስ እንዲያገኙ ስለሚያደርጉ ነው።
16 ምንም እንኳ ደም አልባ የሆነ ሕክምና ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የተረጋገጠ ቢሆንም ብዙ ሐኪሞችና የሕፃናት ደኅንነት ተቋሞች ባል ሥልጣኖች ደምን በመስጠት ማከም በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር አስፈላጊ ወይም መሠረታዊ ሕይወት አድን እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ። ስለሆነም ምስክር ወላጆች ለልጆቻቸው ደም እንዲሰጣቸው የሚያደርገውን ትዕዛዝ አንቀበልም ሲሉ ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ። በአጠቃይ አነጋገር ሐኪሞች ያለ ወላጆች ፈቃድ ልጆችን ማከማቸው ሕጋዊ ሊሆን አይችልም። በአንዳንድ አገሮች ሐኪሞች ወይም የሆስፒታል ሠራተኞች በደም ለማከም የወላጆችን ድጋፍ ሲያጡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መልክ ፈቃድ ለማግኘት ይፈልጉ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ልጁን ከማሳከም ቸል ከማለት ለመጠበቅ በተወከሉ በህፃናት ደኅንነት ባለ ሥልጣኖች ወይም ሐኪሞች ወይም የሆስፒታል ሠራተኞች አማካኝነት ሊገኝ ይችላል።a
17 ደም እንዲሰጥ የሚፈቅዱ የፍርድ ቤት ትዕዛዞች የሚሰጡት ብዙውን ጊዜ ወላጆች በጥቂቱ ተገልጾላቸው ወይም ምንም ሳያውቁት በፍጥነት ነው። ሐኪሞች፣ የሆስፒታል አስተዳዳሪዎችና የህፃናት ደህንነት ባለ ሥልጣኖች እንዲህ ዓይነቱ አፋጣኝ ትዕዛዝ ያስፈለገበት ምክንያት ልጁ ያጋጠመው ድንገተኛ ሆኔታ ምን እየተደረገለት እንዳለ በሚገባ ለወላጆቹ ለማስታወቅ ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ነው ብለው ለማስረዳት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በወቅቱ ድንገተኛ ሁኔታ በእርግጥ ስለመኖሩ ሲጠየቁ ብዙ ሐኪሞች እውነተኛ ድንገተኛ የሆነ ነገር ያልነበረ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፈለጉት በራሳቸው አመለካከት ደም መስጠት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ቢመጣ ፈቃዱን ይዞ መቆየት ይበጃል በማለት ነው። በተፈጥሮ የልጆቻችሁ ጠባቂ እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁን በተመለከተ ሐኪሞች፣ የሆስፒታል አስተዳዳሪዎች ወይም የህፃናት ደህንነት ባለ ሥልጣኖች በማንኛውም ጊዜ ስለሚያደርጉት ነገር ሁሉ የማወቅ መሠረታዊ የሆነ መብት አላችሁ። በአንዳንድ አገሮች ያለው ሕግ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማስታወቅ የሚችል ከሆነ በእናንተ በኩል የምታቀርቡት የመከራከሪያ ነጥብ ካለ ከቀጠሮ በፊት ማቅረብ ያለባችሁ መሆኑን እንድታውቁ ይፈቅዳል።
18 እነዚህ ሕጋዊ እውነታዎች ተባባሪ ሐኪም የመፈለግን ዋጋማነት ያጎላሉ። ከሚተባበራችሁ ሐኪም ጋር አብራችሁ ሥሩ። እንዲሁም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባሎች ወይም የጉባየአችሁ ሽማግሌዎች በሚሰጡአችሁ እርዳት ሐኪሙ የልጃችሁን የጤና ችግር በደም አልባ ዝግጅቶች በማከም ማቃለሉን እንዲቀጥል እርዱት። ወይም ልጃችሁ እንዲህ ዓይነቱን ህክምና ወደሚሰጥ ሐኪም ወይም ሆስፒታል እንዲዘዋወር አድርጉ። ነገር ግን ሐኪሙ፣ የሆስፒታል አስተዳዳሪ ወይም የህፃናት ደኅንነት ሠራተኞች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማግኘት ያሰቡ መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክት ካያችሁ ለማድረግ ያቀዱት ነገር ይህ መሆኑን ለመጠየቅ ንቁ መሆን አለባችሁ። አንዳንድ ጊዜ ይህ የሚደረገው በሚስጢር በስልክ ነው። ወደ ፍርድ ቤት የመሄድ እቅድ ካለ እንናተም በበኩላችሁ ለዳኛው ምክንያታችሁን ለማቅረብ እንድትችሉ ስለጉዳዩ ለማወቅ የምትፈልጉ መሆናችሁን በጥብቅ አሳስቡ። (ምሳሌ 18:17) ጊዜ ካለ የጠበቃ እርዳታ መፈለግ ብዙውን ጊዜ የተሻለ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጠበቆች በፍርድ ቤቱ የተመረጡ ናቸው። የራሳችሁም ይሁን ፍርድ ቤቱ የመረጠው ጠበቃ በእነዚህ ሁኔታዎች በሚቻለው ሁሉ ከሁሉ የተሻለ መከላከያ ማቅረብ እንዲችል የማኅበሩ የሕግ ክፍል መረጃዎችን ሊያፍለው ይችላል።
19 ደምን የአለመፈለጋችሁ ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ከቀረበ ደም የልጃችሁን ሕይወት ጠብቆ ለማቆየት ወይም ለጤንነቱ አስፈላጊ ነው የሚለው የሐኪሙ ሐሳብ ይበልጥ አሳማኝ ሊመስል ይችላል። ዳኛው ስለ ህክምና የማያውቅ ተራ ሰው እንደመሆኑ መጠን ብዙውን ጊዜ በሐኪሙ የህክምና እውቀት ይመራል። በተለይ ወላጆች በእነርሱ በኩል ያለውን ምክንያት ለማቅረብ ጥቂት ወይም ምንም አጋጣሚ ብቻ ሲኖራቸውና ሐኪሙ ያለ ተቀናቃኝ ደም “በአስቸኳይ” ስለማስፈለጉ የራሱን የመከራከሪያ ነጥብ ሲያቀርብ ይህ መሆኑ እውነት ነው። ፍርድ ቤት የአንዱን ወገን ብቻ በመስማት ፍርድ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች እውነቱን ለመወሰን አይረዱም። እንደውነቱ ከሆነ ሐኪሞች መቼና ለምን ደም እንደሚያስፈልግ የሚያድርባቸው እምነት በጣም አከራካሪና አጠራጣሪ መሆኑ ነው። ብዙውን ጊዜ አንድ ሐኪም ደም የልጁን ሕይወት ለማዳን የግድ ያስፈልጋል ሲል ሌላው ሐኪም ያንኑ የጤንነት ችግር ያለ ደም የማከም ልምድ ስላገኘ በሽተኛውን ለማከም የግድ ደም አስፈላጊ አይደለም ብሎ ይናገራል።
20 አንድ ጠበቃ ወይም ዳኛ “ሕይወት አድን” የሆነው ደም ለልጃችሁ እንዲሰጥ ለምን ፈቀደኛ እንዳልሆናችሁ ሲጠይቃችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ምንም እንኳ የመጀመሪያው ዝንባሌያችሁ በትንሳኤና ልጃችሁ ቢሞት አምላክ መልሶ ወደ ሕይወት እንደሚያጣው ያላችሁን ጠንካራ እምነት ማስረዳት ቢሆንም እንዲህ ያለው መልስ ዋናው የሚያሳስበው የልጁ አካላዊ ደኅንነት ለሆነው ዳኛ ሃይማኖተኛ ግትሮች መሆናችሁንና ልጃችሁን ለማዳን እርምጃ መውሰድ ያለበት እርሱ መሆኑን ከማሳመን በስተቀር ሌላ ሊያደርገው የሚችል ነገር አይኖርም።
21 ምንም እንኳ በጥልቅ በተመሠረተ ሃይማኖታዊ ምክንያት ደምን ለመውሰድ ፈቃደኞች ባትሆኑም የሕክምና እርዳት አንቀበልም ያለማለታችሁን ፍርድ ቤቱ ማወቅ ያስፈልገዋል። ልጃችሁን ችላ የምትሉ በአግባቡ የማትይዙ ወላጆች አለመሆናችሁንና ከዚህ ይልቅ ልጃችሁ እንዲታከም የምትፈልጉ አፍቃሪ ወላጆች መሆናችሁ ዳኛው ማወቅ ያስፈልገዋል። የደም ጥቅም ቆይቶ ከሚያመጣቸው አደጋዎችና የጤንነት ቀውሶች ይበልጥ ዋጋ አለው ስለተባለ በቀላሉ አትስማሙ። በተለይ ይህን አደጋ የማያስከትሉ አማራጭ ሕክምናዎች ሲኖሩ።
22 ደም አስፈላጊ ነው የሚለው የአንድ ሐኪም አስተያየት እንደ ሆነ ዳኛው እንዲያውቅ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ሐኪሞች በአስተሳሰባቸው የሚለዩ መሆናቸውና ለልጃሁ ያለ ደም በስፋት የሚደረጉ ህክምናዎችን ለመስጠት የሚችል ሐኪም ለመፈለግ አጋጣሚ እንዲሰጣቸው መፈለጋችሁን ግለጹ። የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ወይም የጉባኤ ሽማግሌዎች በሚሰጡት እርዳት ልጃችሁን ያለ ደም የሚያክምና ለፍርድ ቤት ጠቃሚ ምሥክርነት በስልክ ሊሰጥ የሚችል ሐኪም ታገኙ ይሆናል። ሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ የልጃችሁ የጤና ችግር ያለ ደም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ሊወገድ እንደሚችል የፍርድ ቤት ማዘዣ ለማግኘት እየጣረ ላለው ሐኪም ወይም ለዳኛው የሕክምና ጽሑፍ ሊያሳየው ይችላል።
23 ዳኞች በግፊት አስቸኳይ የሆነ የፍርድ ትዕዛዝ እንዲሰጡ በሚደርግበት ጊዜ በደም የሚመጡ ኤድስን ጨምሮ ሔፓታይትስና ሌሎች ብዙ አደጋዎችን ግምት ውስጥ አያስገቡም። እነዚህን ነገሮች ለዳኛው ልትጠቅሱለት ትችላላችሁ፤ እንዲሁም ክርስቲያን ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ሕይወትን ለማቆየት ተብሎ የሌላውን ሰው ደም የመውሰድ ሙከራ ማድረግ የአምላክን ሕግ የሚሽር ከባድ ስህተት እንደሆነ አድርጋችሁ እንደምትመለከቱትና ለልጃችሁ አስገድዶ ደምን እንዲወስድ ማድረግ ልክ አስገድዶ በፆታ እንደማስነወር አደርጋችሁ እንደምትቆጥሩት ንገሩት። እናንተና ልጃችሁ (የራሱን ፅኑ አቋም መያዝ በሚችልበት ዕድሜ ላይ ደርሶ ከሆነ) እንዲህ ላለው በሰውነታችሁ ላይ የሚደረግ ወረራ ያላችሁን ጥላቻ ልታስረዱ ትቻላላችሁ። ዳኛው ለልጃችሁ አማራጭ ሕክምና መፈለጋችሁ እንድትቀጥሉ እንዲፈቅድላችሁ ለዳኛው አቤቱታ ልታቀርቡ ትችላላችሁ።
24 ተገቢ መከላከያ ከቀረበ ዳኞች ሌላውን ጐን ይኸውም የእናንተን የወላጆች ጎን የበለጠ በግልጽ ለማየት ይችላሉ። ደም እንዲሰጥ ትእዛዝ ለማስተላለፍ በጣም ፈጣኖች አይሆኑም። አንዳንድ ጊዜ ዳኞች ሐኪሞች በደም እንደልብ እንዳይጠቀሙ አግደዋቸዋል፤ እንዲያውም መጀመሪያ በሌሎች አማራጮቹ እንዲጠቀሙ አዘዋቸዋል፤ ወይም ወላጆች ያለ ደም የሚያክምላቸውን ሐኪም እንዲፈልጉ ፈቅደውላቸዋል።
25 አስገድደው ደም እንድትወስዱ የሚፈልጉ ደኞችን በምትቋቋሙበት ጊዜ በምንም ዓይነት በእምነታቸሁ የመወላወል ፍንጭ አላማሳየት አስፈላጊ ነው። ዳኞችና ሐኪሞች የወላጆችን ህሊና ለማሳረፍ ቀላል ነው ብለው በማሰብ ወላጆች ውሳኔ የማድረጉን ኃላፊነት ለእነርሱ እንዲተዉላቸው ይጠይቃሉ። ይሁን እንጂ ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ደም እንዳይሰጠው የምትችሉትን ሁሉ የማድረግ ግዴታ እንዲሰማችሁ ለሚመለከታቸው ሁሉ ግለጽ ማድረግ ይሆርባችኋል። ይህ ከአምላክ የተሰጣችሁ ኃላፊነት ነው። ኃላፊቱ ለሌላ የሚተላለፍ አይደለም።
26 ስለዚህ ከሐኪሞችና ከዳኞች ጋር ስትነጋገሩ አቋማችሁን ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማስረዳት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋችኋል። ምንም እንኳ የምትችሉትን ሁሉ ጥረት አድርጋችሁ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢተላለፍ ሐኪሙ ለልጃችሁ ደም እንዳይሰጥ መለመናችሁን ቀጥሉ፤ አማራጭ ሕክምና እንዲፈልግ ገፋፉት። ያለ ደም የጤና ችግሮችን ለማስወገድ የወጡ የሕክምና ጽሑፎችንና የአንዳንድ ፈቃደኛ ሐኪሞችን ምክሮች ለመመልከት ፈቃደኛ እንዲሆን ማሳሳባችሁን ቀጥሉ። በአቋሙ ጽኑ የነበረ ሐኪም በደም እንዳልተጠቀመ በትምክህት እያስታወቀ ከኦፕሬሽን ክፍል የወጣባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ከሰጠ በኋላም ቢሆን እንኳን በፍጹም ተስፋ አትቁረጡ!—ሰኔ 15, 1991 የመጠበቂያ ግንብ እትም “የአንባብያን ጥያቄ” የሚለውን ተመልከቱ።
27 ኢየሱስ:- “ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰደላችሁ” ያለውን አስታውሱ። በእነዚህ ሁኔታዎች ጊዜ እኛን ለማጽናናት መንፈስ ቅዱስ በዚያ ወቅት ንግግራችን ተገቢና ጠቃሚ እንዲሆን እንደሚረዳን ኢየሱስ ጨምሮ ተናግሮአል—ማቴዎስ 10:16-20
28 “ቃልን የሚያዳምጥ [የሚያስተውል አዓት] መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] የታመነ ምሥጉን [ደስተኛ አዓት] ነው። (ምሳሌ 16:20) ወላጆች፣ ደም በመውሰድ ልጆቻችሁን ከመንፈሳዊ ብክለት ለመጠበቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 22:3) ልጆች፣ ወላጆቻችሁ እነዚህን ዝግጅቶች ሲያደርጉ ጥሩ ምላሽ በመስጠት ማሰልጠኛዎቹን ከልባችሁ በሥራ ላይ አውሉ። ቤተሰቡ በሙሉ መልካም እንዲሆንላችሁ ደምን ላለመብላት ጥብቅ ሁኑ። ምክንያቱም የይሖዋን በረከትና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን ታገኛላችሁ።—ዘዳ 12:23-25
[Footnotes]
a በሐኪሙ አስተያየት ድንገተኛ የሆነ ነገር ከተፈጠረ ብቻ ለልጁ ሕይወት ወይም ጤንነት አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን (ደም መስጠት ጭምር) አስቸኳይ ሕክምና ያለ ፍርድ ቤትም ሆነ ያለ ወላጆች ፈቃድ ቢሰጥ ሕጋዊ ይሆናል። በእርግጥ፣ ሐኪሙ በዚህ የድንገተኛ ሕግ ተማምኖ ሲጠቀም ለተደረገው ነገር መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆን አለበት።