የይሖዋ ምሥክሮች እቤታችሁ ሲመጡ
የካቶሊክ እምነት ተከታዮች አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታቸው በሚሄድበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? የኢጣሊያ ጳጳሳት ብሔራዊ ኮንፈረንስ የካቴኪስቲክ ቢሮ ያዘጋጀው በቅርቡ የወጣ አንድ ጽሑፍ “በደግነት ሆኖም ፈርጠም ባለ አነጋገር ውይይት አለመፈለግን መግለጽ ከክፋት ሊቆጠር አይችልም” በማለት ተናግሯል።
በኢጣሊያ፣ ፎጊያ የሚኖር አንድ ሰው በየዕለቱ ለሚወጣው ጋዜታ ዴል ሜዞጂዮርኖ ለተባለ አንድ ጋዜጣ የላከው ደብዳቤ ሁሉም የካቶሊክ አማኞች በዚህ እንደማይስማሙ ያሳያል።
“እኔ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም። እኔ ካቶሊክ ነኝ። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባላት በበራቸው የይሖዋ ምሥክሮችን እንደማይፈልጉ የሚገልጽ ትንሽ ማስታወሻ እንዲለጥፉ አንዳንድ ደንቦችን ማውጣቷ በጣም አስገርሞኛል። ደግሞም እነዚህ ሰዎች የአምላክን ቃል የሚሰብኩና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ እውቀት እንዲኖራቸው ሌሎች ሰዎችን የሚረዱ ናቸው። ይህ መመሪያ ኢጣሊያ በኮሌራ ወረርሽኝ የተጠቃችበትን ጊዜና በሽታው እንዳይዘን እንዴት መከላከል እንደምንችል የተሰጠንን ምክር ያስታውሰኛል።
“በእኔ አመለካከት የተላለፈው ውሳኔ ቤተ ክርስቲያኒቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባላትን ፍላጎት ግምት ውስጥ ሳታስገባ የራሷን ደንቦች በግድ እንደምታወጣ ያሳያል። ይሁን እንጂ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ካቶሊኮች የይሖዋ ምሥክሮችን ቤት እንኳ ሳይቀር እየጎበኙ ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ አይቻለሁ። የይሖዋ ምሥክሮችም ማንንም ሰው ሳያባርሩ ወደ ቤታቸው አስገብተው ከእነርሱ ጋር ይወያያሉ።”
የይሖዋ ምሥክሮች መልእክታቸውን እንዲቀበሏቸው ሰዎችን አያስገድዱም። ከዚያ ይልቅ በዚህ ችግር በተሞላ ጊዜ ውስጥ አጽናኝ ሆኖ ያገኙትን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ ለሌሎች ለማካፈል ይጥራሉ። ከቤት ወደ ቤት በመሄድም ሆነ በመንገድ ላይ ለሚያገኟቸው ሰዎች በመናገር የይሖዋ ምሥክሮች ሊያዳምጧቸው ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ያካፍላሉ።— ማቴዎስ 24:14፤ ሥራ 5:42፤ 17:17