በጭካኔ የተገደሉ ንጹሐን ያላቸው ተስፋ
ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ሲባል ሕፃናትን መሠዋት የሰው ልጆች ከፈጸሟቸው እጅግ አሠቃቂ ወንጀሎች መካከል አንዱ ነው። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያለው ዘግናኝ ድርጊት ተፈጽሟል ብለው ማመን ያዳግታቸዋል። ይሁን እንጂ የፊንቃውያን አምልኮ ተለይቶ የሚታወቅበት ይህ ድርጊት በተለያዩ የአርኪዮሎጂ ተመራማሪዎች ተረጋግጧል።
የነገሥታት ቤተሰብ ልጆች ታኒት እና በኣል–ሃሞን ለተባሉ አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ቀርበዋል። በካርቴጅ ትንንሽ ልጆች ክሮንስ ለተባለ ከነሐስ ለተሠራ ሐውልት መሥዋዕት ሆነው በእሳት ይቃጠሉ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ዲያዶረስ ስኪለስ ሲናገር የሕፃኑ ዘመዶች እንዲያለቅሱ አይፈቀድላቸውም ነበር ብሏል። ይህም የሆነበት ምክንያት የሐዘን ለቅሶ ማሰማት የመሥዋዕቱን ዋጋማነት ይቀንሰዋል ተብሎ ስለሚታመን ሊሆን ይችላል።
ለተወሰነ ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ አምልኮታዊ ሥነ ሥርዓት በኢየሩሳሌም ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው በጥንቷ ቶፌት ይፈጸም ነበር። በሞሎክ ሆድ ላይ በተሠራው ምድጃ ውስጥ ሕፃናት በሚወረወሩበት ጊዜ የሚያሰሙትን ጩኸት እንዳይሰማ ለማድረግ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አምልኮ ፈጻሚዎች እየጨፈሩ ከበሮ ይደልቁ ነበር።—ኤርምያስ 7:31
የሌሎችን ሥቃይ ላለመስማት ጆሯቸውን በሚደፍኑ ሰዎች ላይ ይሖዋ ታላቅ ቁጣውን ያወርድባቸዋል። (ከምሳሌ 21:13 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ለሕፃናት ከአንጀቱ የሚራራ አምላክ ስለሆነ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን” በሚነሱበት ጊዜ በጭካኔ የተገደሉ ንጹሐንንም ጨምሮ እንደሚያስነሳ የተረጋገጠ ነው።—ሥራ 24:15፤ ዘጸአት 22:22–24