የወደፊቱ ጊዜ ለወጣቶቻችን ምን ይዞላቸዋል?
በሽብር ፈጣሪዎችም ይሁን በኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ድንገት በሚፈጠሩ አደጋዎች ሳቢያ የኑክሌር ቦንብ ሊፈነዳ ይችላል የሚለው ስጋት በሁሉም ላይ ያንዣብባል። በተለይ ደግሞ ስለ ልጆችዎ ወይም ስለ ልጅ ልጆችዎ ይጨነቁ ይሆናል። በማንኛውም ልጅ ጤንነትና የወደፊት ሕይወት ላይ የኑክሌር አደጋ እንዳጠላበት ማወቁ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው።
ቢሆንም ተስፋ አይቁረጡ። ወጣቶች ከፊት ለፊታቸው ጥሩ ጊዜ እንደሚጠብቃቸው ሙሉ በሙሉ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለ። ይህ ተስፋ የተመሠረተው ልጆቻችንን ከአደጋ ለመጠበቅ ሰዎች በሚያደርጉት ጥረት ላይ ሳይሆን ፈጣሪያችን በገባው ቃል ላይ ነው።
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ በመካከለኛው ምሥራቅ ያስተምር በነበረበት ጊዜ ለሕፃናት የሚያስብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። (ማርቆስ 9:36, 37, 42፤ 10:13–16) በመጨረሻ አምላክ በላያችን የሚያንዣብበውን የኑክሌር ስጋት ገፎ መላዋን ምድር ገነት በሚያደርግበት ጊዜም ለሕፃናት እንደዚያው እንደሚያስብላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ወጣቶቻችንም ሆኑ እርስዎ በዚሁ ገነት ውስጥ ገብታችሁ ልትደሰቱ ትችላላችሁ።
በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለምም እንኳ ስለ አምላክ፣ ስለ መንግሥቱና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው አስደናቂ ዓላማ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘት ደስተኛ መሆን ይችላሉ። ተጨማሪ መረጃ ብንሰጥዎ ደስ የሚልዎት ከሆነ ወይም አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርዎትና መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስተምርዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ.ሣ.ቁ 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 2 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።